ከቁርጠኛ ጀግኖች አንዷ ልዕልት ከበደች
ሥዩም መንገሻ
“በሳል፣ በጉንፋን የምትሞተውን ሞት ከሩቅ አገር እኛን ለማጥቃት ለመጣው ጠላታችን ባገርህና በርስትህ በቤትህ
ላይ ሁነህ መመከት አቅቶህ ላገርህ ኢትዮጵያ ሞት ብትነፍጋት፣ ደምህንም ሳታፈስ ብትቀር በፈጣሪህ የምትወቀስበት
በዘርህ የምትረገምበት ነውና የተለመደ የጀግንነት ልብህን ሳታበርድ፣ ወደፊት የሚቆይህን ታሪክህን እያሰብህ ጠንክረህ
ለመዋጋት ቆርጠህ ተነሣ”
ይህ ከላይ የሰፈረው ኃይለ ቃል፣ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከሰማንያ አራት
ዓመታት በፊት ፋሺስት ጣሊያን በሰሜን በኩል መረብን ተሻግሮ ኢትዮጵያን በወረረበት ጊዜ፣ ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት
ብለው ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዓርብ መስከረም 23 ቀን 1928 ዓ.ም. ባስታወቁበት ወቅት ያስተላለፉት አዋጅ ነበር፡፡
ይህቺ
ታሪካዊት ቀን ለአፍሪካውያን እንደ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት ይቆጥሯታል፡፡ የታሪክ ምሁራኑ ፍሬድሪክ ኩፐር ሆነ
ጥላሁን ጣሰው አገላለጽ፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጀመረው ጣሊያን ኢትዮጵያን በ1928 ዓ.ም. በወረረችበት ጊዜ
ሲሆን አጠቃላይ ጦርነቱ ያበቃው በ1937 ዓ.ም. ነበር፡፡
የፋሺስት ጣሊያን ጦር ወረራውን ረቡዕ መስከረም 21 ቀን መፈጸሙን ተከትሎ ሕዝበ ኢትዮጵያ ለቀረበለት የክተት ጥሪ ሳያወላውል ምላሽ ሰጥቷል፡፡
በዳግማዊ
ምኒልክ ዘመን (1888 ዓ.ም.) ዓድዋ ላይ ድል የተመታው የጣሊያን ወራሪ ሠራዊት ከ40 ዓመታት ቆይታ በኋላ
በፋሺስቱ ቤኔቶ ሙሶሎኒ አማካይነት ኢትዮጵያን መውረሩና በተለይ በዓለም የተከለከለው የመርዝ ጋዝ በመጠቀም በ1928
ዓ.ም. ጥፋትና ዕልቂት በተምቤን፣ በሐሸንጌ፣ በዑጋዴን፣ ወዘተ አድርሷል፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያን
ነፃነትና ክብርን የሚሹ የጀግንነት መንፈስን የሰነቁ እርመኛ አርበኞችና ሕዝቡ በስምንቱ ማዕዝናት ተነስተው
የአባቶችና የእናቶችንም የጀግንነት ጋሻ በማንገብ ከአምስት ዓመታት ተጋድሏቸው በኋላ ሚያዝያ 27 ቀን 1933
ዓ.ም. ድላቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በእርመኛ አርበኝነታቸው የድሉን ሰንደቅ ከፍ ካደረጉት መካከልም ሴት አርበኞች
ይገኙበታል፡፡
ሴቶችና ተጋድሏቸው
‹‹ሰንበሌጥ
[ለቤት ክዳን የሚሆን ሳር] ውስጥ ሆኖ ሲተኩስ አየው ነበር፡፡ ድንገት ፊቱን ወደኔ መለስ አደረገ፣ ወደቀም፡፡
እኔም የያዝኩትን ቦታ ለቅቄ ወደ እሱ ሄድኩኝ፤ ሞቶ ነበር፡፡ በወንዙ ሌላኛው አቅጣጫ በጎን በኩል የጠላት ወታደሮች
ተጠግተው ነበር፡፡ ከነበርኩበት ቦታ ከማፈግፈጌ በፊት ወደ ወንዙ አቅጣጫ ተኩስ ከፈትኩ፣ ሦስት ሰዎችንም
ገደልኩ፡፡ ከዚያም የባሌን አስከሬኑንና መሣሪያውን እየተጎተትኩ ወደ ኋላ አፈገፈኩ፤ የተቀሩትና ከኔ ጎን ተሠልፈው
የነበሩት ሁሉ ግን ደህና ነበሩ፡፡ ወደ ጦር ሠፈሩ ተመለስኩ፡፡ በማግሥቱም አስከሬኑን በዲርማ ገብርኤል ቤተ
ክርስቲያን አስቀበርኩ፡፡››
ከባላቸውና ከልጃቸው ጋር የዘመቱት አርበኛዋ ወ/ሮ ልኬለሽ በያን በፋሺስት
ጣሊያን ወረራ ጊዜ ባለቤታቸው ሰማዕትነትን ሲቀበሉ ያዩትንና እሳቸው የፈጸሙትን ጀብዱ ማመልከታቸውን ፀሐይ ብርሃነ
ሥላሴ፣ ኖርዝኢስት አፍሪካን ስተዲስ ባሳተመው መድበል ውስጥ “Women guerrilla fighters” በሚለው
መጣጥፋቸው ገልጸውታል፡፡
ከቆፍጣና ጀግኖች አንዷ ወ/ሮ ልኬለሽ
በያን (ከመሀል)
በሰሜን የማይጨው ግንባር ከዘመቱት ሴቶች መካከል ከአርሶ አደር ቤተሰብ እስከ ልዕልታቱ ይገኙባቸዋል፡፡
“Africa and World War II” በሚል ርዕስ በአሜሪካ ካምብሪጅ ፕሬስ በታተመውና በሁለተኛው የዓለም
ጦርነት ስለነበረው አፍሪካዊ ገጽታ በሚተነትነው የጥናት መድበል ውስጥ ዶ/ር ኃይሉ ሀብቱ፣ “Fighting
Fascism Ethiopian Women Patriots 1935 – 1941” በሚለው ጥናታቸው እንደጠቀሱት፣ ወ/ሮ
ዘነበች ወልደየስ ባለቤታቸውን ተከትለው የዘመቱት አርበኛ ከአርሶ አደር ቤተሰብ የተገኙ ሲሆኑ፣ ሌላዋ ዘማች ልዕልት
ሮማነ ወርቅ ኃይለ ሥላሴ ከባለቤታቸው ከባሌው ገዢ ጋር አብረው ከትተዋል፡፡ በተመሳሳይም የሸዋው ንጉሥ ሳህለ
ሥላሴ የልጅ ልጅ ልጅ ወ/ሮ ላቀች ደምሰው ከባለቤታቸው ደጃዝማች መንገሻ አቦዬ ጋር የወንድ ልብስ ለብሰው
ሽጉጣቸውን ታጥቀው ዘምተዋል፡፡ ወ/ሮ ዘነበች ወልደየስ ከባለቤታቸው ከራስ አበበ አረጋይ፣ ወ/ሮ ሸዋነሽ አብርሃ
አርአያ ከባለቤታቸው ከደጃዝማች ኃይሉ ከበደ (ሌተና ጄኔራል) ጋር እንዲሁ ከትተዋል፡፡
ወ/ሮ ሸዋነሽ
አባታቸው ደጃዝማች አብርሃ አርአያ የአፄ ዮሐንስ አጎት የራስ አርአያ ድምፁ ልጅ ናቸው፡፡ ባለቤታቸው ደጃዝማች/ዋግ
ሹም ኃይሉ ከበደ እንደ አፄ ዮሐንስ አንገታቸውን በኢትዮጵያ ጠላቶች የተሰየፉ ናቸው፡፡ ፋሺስቶች ከሰየፏቸው በኋላ
ጭንቅላታቸውን ወደ ሮም መስደዳቸው ይወሳል፡፡
አንዳንድ ሴቶች አባቶቻቸውንና ወንድሞቻቸውንም
ተከትለዋል፡፡ ሴቶች ከባለቤታቸው ጋር ቢዘምቱም የግድ በነሱ እዝ ውስጥ መዋሉን አይመርጡም ነበር፡፡ አንዱ ማሳያ
የደጃዝማች ሀብተ ሚካኤል ባለቤት የወሰዱት ቆራጥ ዕርምጃ ነው፡፡ ሰው ተጎድቶባቸው ነበርና በዶሎ ግንባር የመጣውን
የጣሊያን ጦር ለመግጠም ያመነቱትን ባለቤታቸው ደጃዝማች ሀብተ ሚካኤል አቋም ባለመቀበል 150 ወታደሮች ይዘው ክተት
ያሉት በቅሎ ላይ ፊጥ ብለው ነበር፡፡ የጣሊያንን ሠራዊት ገጥመው ሠራዊታቸው በርካታ የፋሺስት ወታደሮችን
ገድሏል፡፡ የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች ማርኳል፡፡ ስማቸው በውል ባለመገለጹ አንዳንድ ጸሐፍት ‹‹ስሟ ያልታወቀው››
እያሉ ይጠቅሷታል፡፡
ሌላዋ አርበኛ ወ/ሮ ቀለመወርቅ ጥሩነህ ተመሳሳይ ርምጃ ወስደዋል፡፡ ባላቸው በ1929 ዓ.ም. ወደ ጣሊያኖች ቢገቡም በርሳቸው ሥር የነበሩትን አርበኞች ይዘው ወደ ኬንያ ማፈግፈጋቸው ተጽፏል፡፡
የአፄ
ዮሐንስ የልጅ ልጅ ልጅ፣ የልዕልት ከበደች ሥዩም መንገሻ ባለቤት ደጃዝማች አበራ ካሳ፣ ለፋሺስቶች እጅ መስጠትና
መገደል፣ ልዕልት ከበደችን ከተዋጊነት አልመለሳቸውም፡፡ አርባ ወታደሮችን ይዘው ከሌሎች ሽምቅ ተዋጊዎች ጋር
ፍልሚያውን ተቀላቅለውታል፡፡
ስመ ጥር አርበኛውና ታሪክ ጸሐፊው አቶ ተስፋሚካኤል ትኩእ፣ በ1948 ዓ.ም.
በጻፉት “ሀገሬ የሕይወቴ ጥሪ” መጽሐፋቸው የአርበኛዋን ልዕልት ከበደች ሥዩምን ገድል ከዘረዘሩ በኋላ ከእቴጌ
ጣይቱ ብጡል ጋር ያስተሳስራቸዋል፡፡ “የሸዋን ቤተ መንግሥት መሥርተው ያቋቋሙ፣ በዓድዋም የኢትዮጵያና የጣሊያን
ጦርነት እንዲነሣ ያደረጉና ድልም የመቱን እኒያ ደፋር በኃይለኝነታቸው የሚያንቀጠቅጡት ሴት እቴጌ ጣይቱ ናቸው” ብሎ
ኮንተ አንቶነሊ ራሱ ጠላታቸው መሰከረላቸው፡፡ እንደዚሁ የእቴጌ ጣይቱ ብጡልን ጀግንነት የወረሱ ደፋር የሴት
አርበኛ ወይዘሮ ከበደች ሥዩም መንገሻ ናቸው፡፡”
የሕክምና/ነርስነት አገልግሎት ከሰጡ
አርበኞች አንዷ ወ/ሮ ስንዱ ገብሩ
በኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፣ ከአምስት አሠርታት በፊት በተጻፈው የአርበኞች ተጋድሎ ታሪክ ውስጥ፣ ስማቸው ጎልቶ
የተጠቀሰው ሴት አርበኛ ወ/ሮ አበባ በላቸው ናቸው፡፡ ወ/ሮ አበባ ከባለቤታቸው ከሜታ ሮቢ ባላባት ልጅ ስመ ጥሩው
አርበኛ ከልጅ ገርቢ ቡልቶ ጋር አራት ዓመት ከነራስ አበበ፣ ከነልጅ ኃይለ ማርያም ማሞ ጋር እስከ 5,000
በተቆጠሩ ወታደሮች ጋር ሆነው በመዘዋወር ጀብዱ የሠሩ ናቸው፡፡ የጀግንነት ቦታቸውም በሜታ ሮቢ፣ በዱላ ቆርቻ፣
በሰላሌ፣ በወሊሶና ዓባይ ዳር ነው፡፡ በአንድ ቀን 16 ጣሊያን ከባለቤታቸው ጋር አብረው ማርከው አስረክበዋል ይላል
የኢትዮጵያ ድምፅ ጋዜጣ፡፡
የጠላትን ሁኔታ ለመሰለል፣ ምስጢራዊ መልዕክቶችን ለማስተላለፍ፤ ሴቶች
ከወንዶች የተሻለ ችሎታ ለማሳየታቸው አንዷ ተጠቃሽ የውስጥ አርበኛዋ ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ተድላ
ዘገየ እንደጻፉት፣ አርበኞች የአዲስ ዓለምን ምሽግ ደጋግመው ለማጥቃትና ለመጨረሻም ለማስለቀቅ የቻሉት በቆፍጣናዪቷ
ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ ድጋፍ ጭምር ነው፡፡
በሕክምና ሥራም የረዱ ብዙ ናቸው፡፡ ሰው በቆሰለ ጊዜ ደሙን
አጥበው፣ መግሉን አጥበው፣ የተገኘውን የአገር ባህል መድኃኒት አድርገው፣ መግበውና ውኃ አጠጥተው ያድናሉ፡፡
የሞተባቸውም እንደሆነ ለማያውቁት ሰው ጭምር እርር ብለው አልቅሰው ቀባሪ ለምነው ያስቀብራሉ፡፡
ሕክምናን
በተመለከተ ወ/ሮ ስንዱ ገብሩና ወ/ሮ ጽጌ መንገሻ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ‹‹ኢጣልያ በኢትዮጵያ – ከወልወል እስከ
ጎንደር›› በተሰኘው የአቶ ተድላ ዘገየ መጽሐፍ እንደሚያብራራው፣ ወይዘሪት ስንዱ በአዲስ አበባ ከአባታቸው ከከንቲባ
ገብሩ ጋራ ጎሬ ከተማ ገቡ፡፡ ወይዘሪት ጽጌ መንገሻ ደግሞ ከወንድማቸው ከአቶ ይልማ መንገሻ ጋር አምቦ ከተማ፣
ከጥቁር አንበሳ ጦር ጋር ተቀላቀሉ፡፡ እነዚህ ሁለት ወጣቶች ጎሬ ካለው ሐኪም ቤት ያገኙትን ያህል መድኃኒት ወስደው
ጦሩ በየሄደበት ቦታ ሁሉ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት እስከ መጨረሻው አገልግለዋል፡፡ ደንበኛውን የቀይ መስቀል
መለዮ አድርገው፣ እንደ ወንድ ኮትና ሱሪ ለብሰው፣ ቡሽ ባርኔጣ አድርገው በጦርነት ጊዜ የቆሰለውንና የታመመውን
በማከም ታላቅ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡
ወ/ሮ ስንዱ ባርበኝነት ጉዟቸው ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋራ በጣሊኖች
እጅ ከወደቁ በኋላ ለሁለት ዓመት ተኩል በጣሊያን ተግዘው ቆይተዋል፡፡ ከድል በኋላ በኢትዮጵያ ፓርላማ ለሕግ መምርያ
ምክር ቤት ለሕዝብ እንደራሴነት በአዲስ አበባ ለጉለሌ አካባቢ ተወዳድረው በማሸነፍ ያገለገሉ ሲሆን እስከምክትል
ፕሬዚዳንትነትም ደርሰዋል፡፡
በአምስቱ ዘመን በተለያዩ ግንባሮች በውጊያው አውድማ ውስጥ ከዘመቱት በሺዎች
ከሚቆጠሩት ሴቶች መካከል ፊታውራሪ በላይነሽ ገብረ አምላክ አንዷ ናቸው፡፡ ከ14 ዓመት በፊት የ90 ዓመት አረጋዊት
ሳሉ ያነጋገራቸው ሺበሺ ለማ እንደጻፈው፣ በ1928 ዓ.ም. ፋሺስት ጣሊያን ኢትዮጵያን ሲወር ባለቤታቸው በጅጅጋ
በኩል ወደ ጅቡቲ ለስድስት እንዲሄዱ ቢገፋፏቸው አገራቸውን ትተው እንደማይሄዱ ተጋድሏቸውን እንደሚቀጥሉ ነግረዋቸው
ተለያይተዋል፡፡ በምሥራቅ ግንባር ሰርጎ የገባው የፋሺስት ወራሪን ሱሪ ታጥቀው፣ ዝናር ታጥቀው ብረት አንግተው
ተፋልመዋል፡፡ ከወረራው 10 ዓመት በፊት ያረፉትን የአባታቸውን ፊታውራሪ ገብረአምላክ ውብነህ ማዕረግን የያዙት
ፊታውራሪ በላይነሽ፡፡
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ለኢትዮጵያ ድል 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ መታሰቢያ ያሳተመው ‹‹እኔ ለአገሬ›› መጽሔት የፊታውራሪ በላይነሽን ገድል ዘርዝሮታል፡፡
‹‹ጣሊያን
አሁንም ዋጩ በሚባል አገር ለአሰሳ መጣ፡፡ ኃይለ ማርያም መብረቁ ለሚባሉ አርበኛ ወረቀት ጻፍኩና፣ ‹‹ኑ
ዕርዱኝ›› አልኩ፡፡ እኔን ለመርዳት ብዙዎች ብረት ይዘው መጡልኝ፡፡ ለጋራሙለታው ሰው ለፊታውራሪ ሺመልስ ሀብቴም
ወረቀት ጽፌ መሣሪያ ይርዱኝ ብዬ ላኩባቸው፡፡ እሳቸውም አንድ መትረየስና 15 ጠመንጃ ላኩልኝ፡፡ ከዚህ በኋላ
አርበረከቴ የነበረውን ጣሊያንን እንዲህ እያልን እያቅራራን እንወጋው ጀመር፡፡
‹‹ጣሊያን መልሶ ማጥቃት ሲያረግብን ቦረዳ የሚባል አካባቢ ሄደን ተዋጋን፡፡ ከዚያም ከሺመልስ ሀብቴ ጋር ሆነን
ወደ ሸዋ አቅጣጫ ውጊያ ጀመርን፡፡ እስከ አርባጉጉ ድረስ እየተዋጋን ቀጠልን፡፡ ነገር ግን በዚያ መቆየት
ስላልቻልን ወደ ባሌ ተጓዝን፡፡ ጣሊያንም እዚያ ድረስ ተከታትሎን መጣ፡፡ እኛም መልሰን ወጋነው፤ ፊታውራሪ ሺመልስ
ሲዋጉ፣ ሲዋጉ ቆይተው ሲዳሞና ባሌ ጠረፍ ላይ ሞቱ፡፡ የጣሊያን ኃይል እያየለ በመምጣቱና በሌሎቹም ችግሮች ምክንያት
አቅማችን ስለተዳከመ መበታተን የግድ ሆነብን፡፡ እኔም ወደ ሸዋ መጣሁ፡፡
‹‹ሸንኮራ፣ ደጃዝማች
ፍቅረማርያም የሞቱበት አገር እንዳለሁ፣ አሁንም ጣሊያን ተከትሎኝ መጣ፡፡ እጄን ሳልሰጥ ስዋጋ ቆይቼ ወደ አድአ
አፈገፈግሁ፡፡ ጣሊያንም እንደገና ዱካዬን አፈንፍኖ መጣ፣ ቢሾፍቱ ቡርቃ የሚባል፣ ምንጃር ቡልጋ የሚገኝበት ቦታ
ጦርነት ገጠምነው፡፡
‹‹እዚያ በጥይት ተመትቼ ቆሰልኩ፡፡ ከዚያም ብረቴን ቀብሬ ቁጭ አልኩ፡፡ እዚያ
እየበላሁ፣ እየጠጣሁ፣ ባንዳው እንዳያሳብቅብኝ፣ ጣሊያንም እንዳያገኘኝ ጎፈሬዬንም ተቆርጬ እያለሁ የጃንሆይን ወደ
አገር መግባት ሰማሁ፡፡ የእሳቸውን መምጣት ስንሰማ አዲስ አበባ ለመቀበል መጣን፡፡ ግን አልመጡም አሉን፡፡ ገሚሱ
እሳቸውን ለመቀበል ጎጃም ሄደ፣ እኔ ተመለስኩ፡፡
‹‹ጃንሆይ ከገቡ በኋላ እንደገና መጣሁና እየፎከርን
ገብተን ጃንሆይን አገኘናቸው፡፡ እኔ ቀሚስ ለብሼ ከአርበኞቹ ተለይቼ ጃንሆይን እጅ ነሳሁ፡፡ የእኔ ዝና ቀድሞውንም
ተሰምቶ ነበርና፣ ደጃዝማች ይገዙ ሀብቴ እጄን ይዘው ለጃንሆይ ፣ ‹ጉድ ላሳይዎት› ብለው አቀረቡኝ፡፡ እኔም ቆንጆ
ሆኜ የከተማ ሰው መስዬ ነበር የቀረብኩት፡፡
‹‹ጄኔቭ በነበርንበት ጊዜ፣ በላይነሽ የምትባለው ሴት
ትዋጋለች እየተባለ የምንሰማው እሷን ነው?› ብለው ጠየቁ፡፡ ደጃዝማች ይገዙም ‹አዎ› ብለው አቀረቡኝ፡፡ ጃንሆይም
በፈገግታ ተቀበሉኝ፡፡ ‹አለሽ እንዴ! ማን ትባያለሽ?› አሉኝ፡፡ እኔም፣ ‹ፊታውራሪ በላይነሽ ነኝ› አልኳቸው፡፡
‹በስምሽ ተጠሪበት› ብለው ሹመቱን አፀደቁልኝ፡፡››
የውስጥ አርበኛዋ ወ/ሮ ሸዋረገድ
ገድሌ
‹‹እስከዳር››
በስም
ከሚታወቁት ውጪ ሱሪ ታጥቀው ጠመንጃ አንግተው ፍልሚያውን የተቀላቀሉ በርካታ ሴቶች ነበሩበት፡፡ ከነዚህ በስም
ከማይታወቁት ሴቶች መካከል ስለ አንዷ እንስት ታዋቂው ደራሲና አርበኛ፣ ሚኒስትርና ዲፕሎማት አቶ ሐዲስ ዓለማየሁ
‹‹ትዝታ›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ከገጽ 84 እስከ 86 ሐተታ ታሪክ ጽፈውላት ነበር፡፡ ይህን ታሪክ ያነበቡት ባሕር
ማዶ የሚገኙት ሻለቃ ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ ስሟ ላልተጠቀሰው አርበኛ ‹‹እስከዳር›› የሚል መጠርያ በመሰጠት
ታሪካዊ ልብ ወለድ ጽፈው በ2002 ዓ.ም. አሳትመውላታል፡፡ ደራሲው ዳዊት በመግቢያቸው ላይ እንዲህ ከትበውላታል፡፡
‹‹[አቶ
ሐዲስ ዓለማየሁ] ከገጽ 84 እስከ 86 ስለአንዲት ሴት የጻፉት ለብዙ ጊዜ በሐሳቤ ውስጥ ሲንገዋለል ቆይቷል፡፡
በሐሳቤ ‹ይህች ሴት ማን ትሆን? ከየት ነው የመጣችው? ትውልዷ ምንድነው? እንዴት እዚህ እሳት ውስጥ ገባች?›
እያልኩ ራሴን ስጠይቅ ቆይቼ ዛሬ እነዚህን ጥያቄዎች ለመመለስ ሞከርኩኝ፡፡ ይህችን ስም ያልነበራትን ሴት ስም
ሰጠኋት፡፡ እስከዳር አልኳት፡፡ ታሪክ አበጀሁላት፡፡ በኢትዮጵያ የሴት አርበኞች ያሸበረቀ ታሪክ ውስጥ
አስቀመጥኳት፡፡ ይኸ መጽሐፍ የወይዘሪት እስከዳር ልብ ወለድ ታሪክ ነው፡፡››
እዚች መጣጥፍ ላይ ልብወለዱን ሳይሆን የምናነሣው አቶ ሐዲስ ስለእርመኛዋ አርበኛ በደራሲ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ ስያሜ ‹‹እስከዳር›› ያወጉትን ነው፡፡
‹‹ያንለትና
ከዚያ በፊት በነበረው ሌሊት ከዚህ በላይ ባጭሩ እንደ ተረክሁት፣ መንገድ ለመንድ ይታይ የነበረውን የመከራና
የስቃይ ትርዒት ሳስታውስ ከሁሉም ጎልቶ ባይነ ህሊናዬ ፊት የሚታየኝ ባንድ ሴት ላይ ሲደርስ ያየሁት ነው፡፡ አንድ
ያይሮፕላን ቡድን ደብድቦን ካለፈ በኋላ ዛፍና ቁዋጥኝ ወይም ሌላ ተገን ወዳለበት መሸሹን ያልረሳን ሰዎች
ከየተሸሸግንበት ወጥተን ስንሄድ እንደቆየን አይሮፕላኖች ከኋላችን እንደገና ቦምብ እየጣሉ ሲመጡ ሰማን፡፡ ያን ጊዜ
የደረስንበት ቦታ የዘንባባ ዛፎችና ሌሎች ዛፎች አለፍ አልፍ ብለው የበቀሉበት ስለነበረ መንገዱን ይዞ ከሚጉዋዘው
ሠራዊት መካከል ጥቂታችን ዛፎች ወዳሉበት እየሸሸን ተጠጋን፡፡ በበቅሎ ተቀምጣ ከሠራዊቱ ጋር የምትሄድ አንድ ሴት
ነበረች፡፡
ይች ሴት ባለማኅደር ዳዊት ባንገቷ አግብታ ካንድ ብብትዋ ሥር አንጠልጥላ አንድ አጭር ዲሞትፈር
ጠመንጃ እንዲሁ ባንገቷ አግብታ በጀርባዋ አዝላ ባንድ እጇ የተቀመጠችበትን በቅሎ ዛብ በሌላ እጇ የተጫነች አጋሰስ
በረዥም ላኰ ይዛ ከኋላዋ እየሳበች ትሄድ ነበር፡፡ በክፉ አጋጣሚ አይሮፕላኖች እዚያ ቦታ ሊደርሱ ሲቃረቡ አጋሰስዋ
ገረገረችባት (ቆማ ወደ ኋላ ሳበቻት)፡፡ ዘወር ብትል ያጋሰስዋ ጭነት ባንድ ወገን አጋድሎ ከጀርባዋ ወደ ሆዷ
ወርዷል፡፡ ከዚያ ሴትዮዋ ከበቅሎ ወርዳ ያጋደለውን ጭነት ወዳጋሰሷ ጀርባ መልሳ ለመጫን ትታገል ጀመር፡፡ ያን ጊዜ
ሁላችንም ያይሮፕላኖችን መድረስ አይተን ‹ሴትዮ አይሮፕላኖች መጡብሽ በቅሎዎችን ተይና ነይ! እባክሽ ተያቸውና ወዲህ
ነይ!› እያልን ከያለንበት ጮህን፡፡ እሷ የእኛን ጩኸትም ሆነ በምብ እየጣሉ የመጡትን አይሮፕላኖች አታይም
አትሰማም ነበር፡፡ ዓይኗንም፣ ጆሮዋንም፣ አሳቧንም ሁሉ ተሰብስቦ ያተኮረው ያን ያጋደለ ጭነት መልሳ ለመጫን
በጀመረችው ትግል ላይ ብቻ ነበር፡፡ ከየዛፉና ከየቁዋጥኙ ሥር ስንጮህ ከነበርነው መካከል አንድ ሰው ሴትዮዋን
ለማዳን ወደሷ ሮጦ ነበር፡፡ ነገር ግን አይሮፕላኖች ስለቀደሙት ከመሀል መንገድ ወደ መሸሸጊያው ተመለሰ፡፡ ያች ሴት
እንዲያ ካጋሰስዋ ጭነት ጋር በመታገል ላይ እንዳለች አይሮፕላኖች ከጣሉዋቸው ቦምቦች አንዱ እስዋና በቅሎዎችዋ
በቆሙበት መሀል ወደቀ፡፡ ወዲያው ያ የቆሙበትና በዙሪያው የነበረው መሬት ሁሉ ተጎርዶ ብዙ ሜትር ወደ ሰማይ ሲነሳ
የስዋና የበቅሎዎችዋ፣ የመሬቱ፣ የድንጋዩ፣ የሳሩና የቁጥቁዋጦው ብጥስጣሽ ባንድነት ተደባልቆ ባየር ውስጥ ከጓነ
በኋላ ተመልሶ ቦምቡ መሬቱን ጎርዶ ሲያስነሳው እስር ተቆፍሮ በቀረው ሰፊ ጉድጉዋድ ዙሪያ ተበተነ፡፡ ታዲያ
የሚያስገርመው አይሮፕላኖች እዚያ ባጠገባችን በጣሉት ብዙ ቦምብ ከዚያች ሴትና ከበቅሎዎቹ በቀር ከዚያ ሁሉ ሠራዊት
ሞቶ ወይም ቆስሎ ሲወድቅ ያየነው አልነበረም፡፡
በሚያዝያ 27 አደባባይ ከቆመው የድል
ሐውልት አካል ውስጥ ከተቀረፁ ኪነ ቅርፅ አንዱ የሴት አርበኞችን የሚወክል ነው
‹‹አይሮፕላኖች ከሄዱልን በኋላ ከየዛፉ ስር ወጥተን መንገዳችንን ስንቀጠል ሴትዮዋን ለማዳን ሩጫ ጀምሮ
የነበረው ሰው እንደነገረን ያቺ ሴት ያንድ መኰንን በጣም የሚዋደዱት የጭን ገረድ ኖራለች፡፡ ከሁለት ቀን በፊት
የመኰንኑ አሽከሮች እጦርነቱ ውስጥ አልቀው እሳቸውም ክፉኛ ሲቆስሉ ከሞትም ከመቁሰልም የዳኑ እስዋና አንድ ወንድ
አሽከራቸው ብቻ ኖረዋል፡፡ ጌትየው በጽኑ ቆስለው በጣእር ውስጥ እንዳሉ እስዋ ባጠገባቸው ሆና ስታስታምማቸው
እንደማይተርፉ ተረድተውት ኖሮ ‹አንቺና ተስፋ (ወንዱ አሽከራቸው) ከሞት ተርፋችሁ አገራችሁ ለመግባት የበቃችሁ
እንደሆነ፤ መሣሪያየንና አባቴ ሲሞቱ ለመታሰቢያቸው የሰጡኝን ዳዊቴን ለልጄ ለንጋቱ እንድታደርሱልኝ አደራ፡፡ እሱ
እስኪያድግ የናቱ ወንድም ብላታ በየነ ባላደራ ሆነው ይጠብቁለት፤› ብለው ተናዘው ሞተዋል፡፡ እንግዲህ ይቺ፣ ሰው
ሁሉ ነፍስዋን እንድታድን ያን ያክል ሲማፀናት ዓይኗን እያየ በቦምብ ተቃጥላ የሞተች የወዳጇን ያደራ ኑዛዜ ለመፈጸም
ኖሮዋል! ምን ዓይነት እስከ ሞት የሚያደርስ ታማኝነት፣ ምን ዓይነት ኃያል ፍቅር ቢሆን ነው? ‹‹ለሃይማኖትዋ ብላ
ለማተብዋ ብላ እንዲያ ተቃጥላ ሞተች!›› አለ ሰውየው የሴትየዋን ታሪክ ከተረከልን በኋላ እየተከዘ፡፡
‹‹እንዴት
ለሃይማኖትዋ ብላ? ያይሮፕላን ቦምብ ስንቱን አቃጥሎ ሲጨርስ እያየች ካጋሰስ ጭነት ጋር ስትታገል መሞትዋ
‹ሃይማኖተኛ› የሚያሰኛት መስሎዋት ነው? እንዲህ ያለው ሞኝነት ወይም እብደት ነው እንጂ ሃይማኖተኛነት
አይደለም!›› አለ ጤናው ከማዘኑ የተነሳ ቆጣ ብሎ ግን ኃያል ፍቅር ሞኝም፣ እብድም፣ ሃይማኖተኛም ሁሉንም
ያደርጋልኮ!››
https://ethioreportermagazines.com/1828
|
Great post and success for you...
ReplyDeleteKontraktor Interior
Kontraktor Booth Pameran
Jasa Pembuatan Booth
Kontraktor Pameran
Jasa Pembuatan Booth Pameran
Jasa Pembersihan Kaca Gedung