Wednesday, December 26, 2018

የአገር አውራ ስንብት


‹‹ሥርዓቶች ቢለዋወጡ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሥልጣን ላይ ቢቀያየሩ መሪ ቢመጣ ቢሄድ ይህ ሁሉ ኃላፊ እንደሆነ ሥርዓትና አገር የተለያዩ እንደሆኑ መተኪያ የሌላት አገር ግን ትናንትና ዛሬ ነገ እንደምትኖር ቀጣይነት እንዳላት በዚህ ላይ መቀለድ እንደማይቻል ይህንንም ርዕሰ ብሔር ሆነው ለ12 ዓመታት ባገለገሉበት ወቅት በንግግራቸው፣ በሁኔታቸው በአስተሳሰባቸው አሳይተዋል፡፡››
ስለቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በሥርዓተ ቀብራቸው ላይ ይህንን ዓቢይ ምስክርነት የሰጡት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ናቸው፡፡
94ኛ ዓመታቸውን ለማክበር የሁለት ሳምንታት ጊዜ ሲቀራቸው ያረፉት አቶ ግርማ ሥርዓተ ቀብራቸው ለርዕሰ ብሔር በሚመጥን አገራዊ ክብር ታኅሣሥ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ተፈጽሟል፡፡ ከፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ጋር ርዕሰ መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰአረ መኰንን ተገኝተዋል፡፡
ሺሕ ሰማንያ አካባቢ ከሚገኘው ስፍራ ለክብራቸው 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል፡፡ ረፋዱ ላይ በሚሌኒየም አዳራሽ በተከናወነው የሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ዲስኩር ያሰሙት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ፣ ‹‹ክቡር ፕሬዚዳንት ረጅሙን ጉዞ ጨርሰዋል፤ የእርስዎ ከዚህ ዓለም መለየት የቤተ መጻሕፍት መዘጋት ነው፤›› ብለዋል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አብዛኛውን የዕድሜያቸውን ጊዜ ኢትዮጵያን በተለያየ የሥልጣንን እርከን ከወታደርነት እስከ ርዕሰ ብሔርነት በቅንነት ማገልገላቸውን ጠቅሰው፣ በኅልፈታቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል።
በሚሌኒየም አዳራሽ የነበረው ፕሮግራም ከተጠናቀቀ በኋላ በክብር ሰረገላና በፈረሰኞች እንዲሁም በወታደራዊ ማርሽ ባንድ ታጅቦ በአፍሪካ ጎዳና እና በዳግማዊ ምኒልክ ጎዳና በመጓዝ አስክሬናቸው ካረፈበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በማምራት ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአንድ ቀን ብሔራዊ የሐዘን ቀን እና ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ያወጀላቸው የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ሥርዓተ ቀብር የተፈጸመው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ መሪነት ጸሎተ ፍትሐት ከተደረገ በኋላ ነው፡፡
የቀብር ሥነ ሥርዓት አስተባባሪ ብሔራዊ ኮሚቴ ባወጣው መርሐ ግብር መሠረት፣ ማክሰኞ ታኅሣሥ 9 ቀን በመኖሪያ ቤታቸው ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ሹማምንትና የውጭ አገሮች ዲፕሎማቶች በተዘጋጀው መዝገብ ላይ የሐዘን መልዕክቶቻቸውን ማስፈራቸው ታውቋል። ብሔራዊ የሐዘን ቀን መታወጁን ተከትሎ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች፣ እንዲሁም በውጭ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ለአንድ ቀን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብምደርጓል።
በሦስት መንግሥታት ከፓርላማ ፕሬዚዳንትነት እስከ ርዕሰ ብሔርነት ኢትዮጵያን የመሩት፡፡ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በሰባት አሠርታት የሥራ ጉዟቸው፣ በዕውቀታቸውና በሙያቸው በተሰማሩባቸው የተለያዩ መስኮች ጉልህ ሚና እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል፡፡ ከበጎ ፈቃድና በጎ አድራጎት አገልግሎት ጋር ስማቸው ይያያዛል፡፡ ከመንግሥታዊ ተግባራቸው ጡረታም ቢወጡ፣ በተፈጥሮ ጥበቃና አካባቢ ክብካቤ ዙሪያ በለም ኢትዮጵያ ያደረጉት ልጨኛ ተግባር ይጠቀሳል፡፡
ለሁለት ተከፍለው የቆዩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሶችን ወደ አንድነት ለማምጣት፣ በኢትዮ ኤርትራ መካከል ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ ለማድረግ ጥረት ካደረጉ ታዋቂዎች መካከልም ይገኙበታል፡፡
የስድስት ቋንቋዎች ኦሮሚኛ፣ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ጣሊያንኛ፣ እንግሊዝኛና ፈረንሣይኛ ተናጋሪ የነበሩት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ቀደም ባሉት ስድስት አሠርታት ውስጥም በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና በኅብረተሰብዓዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በተለያዩ ኃላፊነት ቦታ ላይ አገልግለዋል፡፡
በዘውዳዊው ሥርዓት በአዲስ አበባ ከተማ የልደታ ወረዳ እንደራሴ በመሆን በ1954 ዓ.ም. ለፓርላማ በመመረጥ የሕግ መምርያ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትም ነበሩ፡፡ በ52ኛው የዓለም ፓርላማዎች ኅብረት ጉባዔ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሠርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ዘመን በ1992 ዓ.ም. በተደረገው አገራዊ ምርጫ በምዕራብ ሸዋ ዞን በቾ ወረዳ በግል ተወዳድረው በማሸነፍ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ፕሬዚዳንት እስከሆኑበት 1994 ዓ.ም. ድረስ አገልግለዋል፡፡
ከአባታቸው ከግራዝማች ወልደ ጊዮርጊስ ሉጫና ከእናታቸው ከወ/ሮ ወሰንየለሽ መኩሪያ ቅዳሜ ታኅሣሥ 19 ቀን 1917 ዓ.ም የተወለዱት መቶ አለቃ ግርማ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ካረፉት ባለቤታቸው ወ/ሮ ሳሌም ጳውሎስ መንአመኖ አምስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፣ የልጅ ልጆችም አይተዋል፡፡
94 ዓመታቸው ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን ያረፉት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያን ከ1994 እስከ 2006 ዓ.ም. መምራታቸው ይታወቃል፡፡

No comments:

Post a Comment