Monday, July 23, 2018

የሥነ ልሳንና የትምህርት ባለሙያው ዶ/ር ብቅአለ ሥዩም (1943-2010)


በሔኖክ ያሬድ
ከአራት አሠርታት ለበለጠ ዘመን በመምህርነትና በሥነ ልሳን ባለሙያነት እንዲሁም በትምህርት ቢሮ ኃላፊነት በኢትዮጵያ ትምህርት ሕዋ ውስጥ ብቅ ያሉት ዶ/ር ብቅአለ ሥዩም ባበረከቱት አስተዋጽኦ ይጠቀሳሉ፡፡
ዶ/ር ብቅአለ ከልጅነታቸው ጀምሮ ቀልባቸውን የሰረቀውን ያስተማሪነት ሙያ እጅግ ከመውደዳቸው የተነሳ ለ30 ዓመታት በአንደኛ ደረጃና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ (የአሁኑ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ) እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አገልግለዋል፡፡ በተለይ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ከማስተማሩ ባሻገር ኮሌጁን በዲንነት መርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ልሳን የትምህርት ክፍል በረዳት ፕሮፌሰርነት በመምህርነትና በተመራማሪነት አገልግለዋል፡፡
ዶ/ር ብቅአለ ከማስተማሩ ወደ አስተዳደር በገቡበት ከ1985 እስከ 1993 ዓ.ም. ባለው ጊዜ የአማራ ብሔራዊ ክልል የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡
በተለይ በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ሕፃናትና ወጣቶች በሥነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ዓይነተኛ መሣሪያ እንደሆነ የታመነበት ‹‹የኢትዮጵያ ተረቶች ፕሮጀክት›› በአማራ ክልል እውን እንዲሆን ካደረጉት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ በቀላል እንግሊዝኛ መጻሕፍትን በማዘጋጀት በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ተማሪዎች እንግሊዝኛን ማንበብ እንዲለማመዱና እግረ መንገዳቸውንም ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያንፀባርቁትን ተረቶች እንዲያውቁ ማድረግ ነው፡፡
 በአማርኛ የተሰበሰቡትና በጽሑፍና በድምፅ ከተሰነዱት ተረቶች መካከል የተወሰኑት ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉመው እንዲታተሙ ያስተባበሩት ዶ/ር ብቅአለ ሥዩም ናቸው፡፡ የተረቶቹ መጻሕፍት ለእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማሪያነት ከመዋላቸው በላይ ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከተሰበሰቡ ተረቶች ጋር በአንድነት በድረ ገጽ ውስጥ ለአገልግሎት ውለዋል፡፡
ከእናታቸው ከወ/ሮ አበበች በንቲና ከአባታቸው ከአቶ ሥዩም ተፈሪ በቀድሞው ጋሞጎፋ ጠቅላይ ግዛት፣ ጋርዱላ አውራጃ ጊዶሌ ከተማ ታኅሣሥ 3 ቀን 1943 ዓ.ም. የተወለዱት ዶ/ር ብቅአለ ሥዩም፣  የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን  በጊዶሌ ከተማ በሚገኘው ፈታውራሪ ገበየሁ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጨንቻ ከተማ ደጃዝማች ወልደማርያም፣ በአርባ ምንጭ ከተማ፣ በአምቦ ማዕረገ ሕይወት ዘቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በወቅቱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሥር በሚገኘው ልዑል በዕደ ማርያም ትምህርት ቤት አጠናቀዋል፡፡ ለሦስት ዓመታት በመምህርነት ተቀጥረው ካስተማሩ በኋላ፣ በአዲስ አበባ መምህራን ኮሌጅ ገብተው በሁለተኛ ደረጃ መምህርነት በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡
በተለያዩ ዓመታትም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያና የሁለተኛ፣ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት ዶ/ር ብቅአለ በተጨማሪም እንግሊዝ  ከሚገኘው ኦፕን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አስተዳደር ተመርቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ሥነ ልሳንን በተመለከቱ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር ብቅአለ ሥዩም ከረዥም ዘመን አገልግሎት በኋላ በ2005 ዓ.ም. በጡረታ ቢሰናበቱም ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በአሜሪካ በተለያዩ ሆስፒታሎችና በአገር ውስጥ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሐምሌ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በተወለዱ 67 ዓመታቸው አርፈው በማግስቱ በጴጥሮስ ወጳውሎስ ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡
የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ታላቅ እህት የወ/ሮ ቦካ ዲነግዴ የልጅ ልጅ የሆኑት ዶ/ር ብቅአለ  ከወ/ሮ ዕፀ ገነት ጽጌ ጋር ትዳር መሥርተው ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆች አፍርተዋል፡፡ 
                            (ሪፖተር፣ እሑድ ሐምሌ 15 ቀን 2010 ዓ.ም.)

No comments:

Post a Comment