![]() |
ነፍስ ኄር አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ
|
በሔኖክ ያሬድ
ከኅብረተሰብአዊት
ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ እስከ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) በነበሩት አሥራ ሰባት ዓመታት
(1967-1983) የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር የነበረውና ብዙኃኑ የዘመረውን፣ ከአብዮት አደባባዮች እስከ ትምህርት ቤቶች፣ ከስፖርት
ስታዲየሞች እስከ ኦሊምፒክ አደባባይ (የሞስኮ ኦሊምፒክ የምሩፅ ይፍጠር ወርቃማ ድሎች) የተዜመውን ‹‹ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቅደሚ
በኅብረሰባዊነት አብቢ ለምልሚ…›› ብሔራዊ መዝሙር ደራሲነታቸው ይታወቃሉ፡፡ አቶ አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ፡፡
እንደ
ዘውዳዊው ሥርዓት ሰንደቅ ዓላማ ሲወጣና ሲወርድ ሲዜም እንደነበረው ‹‹ተጣማጅ አርበኛ ባገር መውደድ ቀንበር…›› እና ‹‹ደሙን
ያፈሰሰ ልቡ የነደደ…›› ዓይነትም፣ በዘመነ ደርግ እንዲዜም ከዘመኑ ርዕዮት ጋር የተዛመደ ሰንደቅ ዓላማ ሲወጣና ሲወርድ የሚዜመውን
ግጥም ገጣሚው አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ ደርሰው ነበር፡፡ የሰንደቅ ዓላማ መዝሙሮች አያስፈልጉም ተብሎ በመተዉ ለአደባባይ ባይበቁም
በመድበል ከመታተም ግን አልታቀቡም፡፡ ሁለቱ የታተሙ የግጥም መድበሎቻቸው ‹‹የመስከረም ጮራ›› እና “The Voice” ናቸው፡፡
‹‹ተቀፀል ባንዲራ›› - አሰፋ
ገጣሚው
አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ ለፍቅረ ባንዲራ እጅ ሰጥተዋል፡፡ ‹‹ተቀፀል ጽጌ›› አበባን ተቀዳጅ እየተባለ፣ የአበባ ወቅት (ዘመነ
መፀው) በሆነው መስከረም ጥቅምት፣ ኅዳርና ታኅሣሥ እንደሚባለው፣ ለአገር ክብር ልዕልናም ሀገራዊውን ሰንደቅ ዓላማ - ባንዲራን
ተቀዳጅ የሚል ዜማ ያለው ግጥም ከገጣሚው ጎታ ይገኛል፡፡ በ1967 ዓ.ም. ለባንዲራዋ እንዲህ ስንኝ አሠፈሩላት፡፡
‹‹ያገራችን
ውበት የወንዝ የተራራ
የተስፋችን
ብርሃን የማለዳ ጮራ
የታሪክ
ቅርሳችን የደም ያንጥታችን
ትውለብለብ
ዘላለም ሰንደቅ ዓላማችን!
ለፍትሕ
ለእኩልነት ለሰብአዊ መብት
ለሰላም
ለፍቅር ለሀገር ዕድገት
ለኢትዮጵያ
ነፃነት ለልጆቿ ክብር
ሰንደቅ
ዓላማችን ዘላለም ትኑር!››
ከግጥሙ
አንጓም አንድም እንዲህ እያሉ ተረጐሙ፡፡
‹‹ያገራችን
ውበት የወንዝ የተራራ… አረንጓዴ
የተስፋችን
ብርሃን የማለዳ ጮራ… ቢጫ
የታሪክ
ቅርሳችን የደም ያጥንታችን…ቀይ››፡፡
አቶ
አሰፋ፣ በየድርሰቶቻቸውም ሆነ በየጦማሮቻቸው ሙሉ ስማቸውን ብቻ ሳይሆን አያታቸውንም ጨምረው ይከትባሉ፡፡ ይህም የሆነው ከሌላኛው
ታዋቂ ደራሲና ዲፕሎማት አሰፋ ገብረማርያም ለመለየት ነው፡፡ ደራሲው አሰፋ ገብረማርያም በ‹‹እንደወጣች ቀረች›› ልቦለዳቸው ይታወቃሉና፡፡
የአሰፋ ገብረማርያም ሌላው ገጽታ
የአንድ
ኅብረተሰብ ሥነ ቃል የዚያ ኅብረተሰብ አጠቃላይ የቁስ አካላዊና የህሊናዊ፣ መንፈሳዊ ባህል አካል እንደመሆኑ፣ ስለ ሥነ ቃል ምዝገባና
ጥናት አስፈላጊነት በ1970ዎቹ መጀመርያ ላይ ሲያቀነቅኑ ከነበሩ ምሁራን አንዱ አቶ አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ ነበሩ፡፡
ከ35
ዓመታት በፊት ‹‹የሥነ ቃል ንድፈ ሐሳብ ግንዛቤና የአጠናን ዘዴ›› በሚለው ጥናታቸው፣ ከዚህ በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ
ቋንቋዎች ሥነ ጽሑፍ ክፍል በ1970 እና በ1973 በተደረጉት ሴሚናሮች ላይ ከቀረቡት ጥቂት የሥነ ቃል ወረቀቶች በቀር፣ የኢትዮጵያን
ተጨባጭ ሁኔታ አስመልክቶ ስለሥነ ቃል የተደረገ ሰፊ ጥናትና ምርምር እስከዛሬ ድረስ ባለመኖሩ፣ ወደፊት ለብዙ ዘመናት ከትውልድ
ወደ ትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ሥነ ቃል በሚገባ ተሰብስቦ፣ በኢትዮጵያውያን ምሁራን ሳይንሳዊ ጥናትና
ምርምር ተደርጎበት፣ ከባህላዊ ቅርስ መዘክርነቱ ባሻገር ምርቱ ከግርዱ ተለይቶ ለአዲሱ ሶሻሊስታዊ የባህል ግንባታ እንደሚውል ሙሉ
እምነት እንደነበራቸው ገልጸው ነበር፡፡
በመላው
ኢትዮጵያ በ1971 ዓ.ም. ታውጆና ተተግብሮ የነበረው ብሔራዊ የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ከስኬት እንዲደርስ ሥነ ቃል ዓይነተኛ መሣሪያ
ሊሆን እንደሚችል እንዲህ አሳስበውም ነበር፡፡ ‹‹የመሠረተ ትምህርት ዘመቻ ሰፊውን ሕዝብ ከማይምነት ለማሳቀቅ በሚደረገው ጥረት
ሥነ ቃል አገልግሎት ላይ የማይውልበት ምክንያት የለም፡፡ የማስተማሪያ መጻሕፍት ምርቱን ከግርዱ፣ ጠቃሚውን ባህል ከጎጂው በመለየት
በአካባቢው የሚነገሩትን እንቆቅልሾች፣ አፈ ታሪኮች፣ ምሳሌያዊ ንግግሮችን መሠረት በማድረግ በየብሔረሰቡ ቋንቋ ቢዘጋጅ ሕዝቡ ባህሉን
እንዲያውቅ ከመርዳቱም በላይ ለማስተማር በጣም ይቀላል፡፡ ከዚህም በቀር ሕዝቡም ሥነ ቃል ባህላዊ ቅርሱ መሆኑን ተረድቶ ምርቱን
ከግርዱ በመለየትና እንክብካቤ በመያዝ ተራማጅና ዴሞክራሲያዊ የሆነ አዲስ ባህል ለመገንባት ያስችለዋል፡፡››
ለድራማና
ለሙዚቃም ሊቃውንት ሥነ ቃል ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ባህላዊ ዘፈኖችንና ዜማዎችን በማጥናትና እነሱን መሠረት በማድረግ አዳዲስ
ዘፈኖችንና ዜማዎችን፣ ሙዚቃዎችንና ኦፔራዎችን ለማውጣት እንደሚቻል ያሳሰቡ የነበሩት አቶ አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ፣ የሠርግና የለቅሶ፣
የአረሆ እና የቃልቻ፣ የዝየራም ወዘተ… ሥነ ቃሎች ለሙዚቃ፣ ለድራማና በአጠቃላይም ለሥነ ጥበባት መዳበር ሊያደርጉ የሚችሉት አስተዋጽኦ
በቀላል የሚገመት እንዳይደለ ሳያመሰጥሩ አላለፉም፡፡ እነሱንም መሠረት በማድረግ አጫጭርና ረዣዥም ልብ ወለድና የቴአትር ድርሰቶችን፣
ሙዚቃዊ ድራማዎችን ወዘተ… መድረስ እንደሚቻል አያሌ አፈ ታሪኮች ልማዳዊ እምነቶችና ባህላዊ ዘፈኖችም ጠቀሜታቸውን ለዘመኑ ኅብረተሰብ
ከባልደረቦቻቸው ጋር ሲያስተጋቡ ነበር፡፡ ‹‹ለወደፊት የኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የሥነ ቃል ቅርስ በሥርዓት ሲሰበሰብና ሲጠና ኪነታዊ
የሥነ ጽሑፍ፣ የሙዚቃ፣ የሥዕል… ወዘተ የፈጠራ ሥራዎች መውጣታቸው እንደማይቀርም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡
ይህም
ሆኖ የኢትዮጵያ ብሐረሰቦች ሥነ ቃል ማለት ግጥሙ፣ ዘፈኑ፣ ተረቱ፣ እንቆቅልሹ፣ አፈ ታሪኩ፣ ምሳሌያዊ ንግግሩ፣ ባህላዊ ወጉ… ወዘተ
በአስቸኳይ ካልተሰበሰበና ካልተመዘገበ የአብዮቱ ሒደት ያስከተለው ባህላዊ ለውጥና የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሥርጭት እጅግ ፈጣን በመሆኑ
ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው የየብሔረሰቡ ሥነ ቃል ቅርፅ እንዳይደመሰስና ታሪካዊ ዋጋው ባህላዊ ቅርስነቱ እንዳይጠፋ በወቅቱ በሥነ ቃል
ሴሚናር ላይ ያስተጋቡት ደወል፣ ለኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ ስንቅ ሆኖ በተከታታይ ዓመታት የበርካታ ብሔረሰቦች ሥነ ቃሎች ተሰብስበው
ተሰንደዋል፣ ለኅትመትም በቅተዋል፡፡
ለማኅበራዊ
ሚዲያና ለጋዜጠኞች ቅርብ የነበሩት አቶ አሰፋ፣ በስደት አገራቸው በሀገረ አሜሪካ ለኢትዮጵያውያን ማኅበረሰብ በየማኅበራዊና ስፖርታዊ
ድግሱ የግጥም ትሩፋት ብቻ ሳይሆን፣ ‹‹ነውን ለማወቅ ነበርን ጠይቅ›› ነውና አገራዊ ባለውለታዎችን ከጥንት እስከዛሬ በምስል እያስደገፉ
ዜና ሕይወታቸውን ባጭሩ ከማቅረብ ችላም አላሉ፡፡
በአሜሪካ
በሚዘጋጀው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ሻምፒዮና አጋጣሚ ነባሮቹን የእግር ኳስ ባለውለታዎች ለአፍሪካና ለዓለም የበቁትንም ጭምር በማስታወስ
ለአደባባይ አብቅተዋል፡፡ ‹‹ዘመናዊ መወድስ ዘ’ግር ኳስ›› በሚል ርዕስ በሦስቱ ቀለማተ ኢትዮጵያ (አረንጓዴ ቢጫና ቀይ) የተቀለመ
ግጥም እንዲህ ቀርቧል፡፡
‹‹አለ
በያገሩ ብዙ ዓይነት ጨዋታ
ዋና፣
የቅርጫት ኳስ፣ ዝላይና ሩጫ!
ግን
ማን እንደ’ግር ኳስ ተወዳጅ ጨዋታ
ስሜት
የሚማርክ የሚሰጥ እርካታ?! ብሎ ግጥሙ ይንደረደርና፤
‹‹የ’ነ
ይድነቃቸው ቀለም የ’ነ መንግሥቱ ፊርማ
የ’ነ
‘ለውጤ’ ጥበብ የ’ነ ነፀረ አርማ
የ’ነ
አየለ ጅቦ የ’ነ ፀጋዬ አብዶ አሻራ
የ’ነ
ድሬ ቴርሲኖ የ’ነ አመለወርቅ ቴስታ
የታተመብሽቱ
ውዲቷ የ’ግር ኳስ ጨዋታ
ውብ
ድንቅ ነሽ’ኮ ለአካል ለመንፈስ ግንባታ!››
መካተቻ
ከአባታቸው
ከአቶ ገብረማርያም ተሰማና ከእናታቸው ከወ/ሮ ተዋበች መስከረም 16 ቀን 1928 ዓ.ም. የተወለዱት አቶ አሰፋ፣ ባሕር ማዶ ድረስ
በዘለቀው ከፍተኛ ትምህርታቸው እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ደርሰዋል፡፡ ከመምህርነታቸው ባሻገር በባህል ሚኒስቴር ሥር በሚገኘው የኢትዮጵያ
ቋንቋዎች አካዴሚ ዋና ጸሐፊም ነበሩ፡፡
ስድሳኛ
ዓመታቸውን በአዲስ አበባ መስከረም 16 ቀን 1988 ዓ.ም. በልዩ መሰናዶ ባከበሩበት ጊዜ የራሳቸውን የጥበብና ባህል ግንባታ ማዕከል
ለማቆም ፕሮጀክት ነድፈው ነበር፡፡
ኑሯቸውን
በአሜሪካ በተለይ በላስቬጋስ ከተማ በማድረግ እስከ ኅልፈታቸው ድረስ ኖረውበታል፡፡ በጦማሮቻቸው (ደብዳቤዎቻቸው) ግርጌ ‹‹አሰፋ
ገብረማርያም ተሰማ - ከእሳቱ ከተማ ወቁማሩ አውድማ›› በማለትም የመኖርያ ከተማቸው ገጽታ ሠርክ ሳይገልጹ አያልፉም ነበር፡፡
በላስቬጋስ
ከተማ በመኖርያ ቤታቸው እሑድ ሚያዝያ 28 ቀን 2010 ዓ.ም. ያረፉት አቶ አሰፋ፣ ባለትዳርና የአራት ልጆች አባት ነበሩ፡፡ የስድስት
ልጆች አያትና የአንድ ልጅ ቅም አያት እንደነበሩም ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ ሥርዓተ ቀብራቸው ግንቦት 4 ቀን እሑድ በኖሩበት
ላስቬጋስ ከተማ እንደሚፈጸም ታውቋል፡፡
በቀደመው
ትውልድ በሕዝብ መዝሙር ደራሲነታቸውና በባህል ጥናት ይታወቁ የነበሩት አሰፋ ገብረማርያም ተሰማ ትናንት ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን በአፀደ
ሥጋ የሉም፡፡ በመዝመራቸውም ተሸኑ፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ቅደሚ
በኅብረሰባዊነት አብቢ ለምልሚ!
ቃል ኪዳን ገብተዋል ጀግኖች ልጆችሽ
ወንዞች ተራሮችሽ ድንግል መሬትሽ
ለኢትዮጵያ አንድነት ለነፃነትሽ
መስዋዕት ሲሆኑ ለክብር ለዝናሽ!
ተራመጅ ወደፊት በጥበብ ጎዳና
ታጠቂ ለሥራ ላገር ብልጽግና!
የጀግኖች እናት ነሽ በልጆችሽ ኩሪ
ጠላቶችሽ ይጥፉ ለዘላለም ኑሪ!››
በኅብረሰባዊነት አብቢ ለምልሚ!
ቃል ኪዳን ገብተዋል ጀግኖች ልጆችሽ
ወንዞች ተራሮችሽ ድንግል መሬትሽ
ለኢትዮጵያ አንድነት ለነፃነትሽ
መስዋዕት ሲሆኑ ለክብር ለዝናሽ!
ተራመጅ ወደፊት በጥበብ ጎዳና
ታጠቂ ለሥራ ላገር ብልጽግና!
የጀግኖች እናት ነሽ በልጆችሽ ኩሪ
ጠላቶችሽ ይጥፉ ለዘላለም ኑሪ!››
(ግጥም: አሰፋ ገብረማርያም፤ ዜማ:
ዳንኤል ዮሐንስ)
No comments:
Post a Comment