Thursday, April 5, 2018

የትንሣኤው ብርሃን

የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የትንሣኤው ምስል በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ውስጥ የሚገኝ


በሔኖክ ያሬድ
‹‹ሽው ሽው ላሌ
እሰይ ለዓመት በዓሌ
ታተይ ከቋቱ ላይ ያለው እንቁላል ድመት በላው
አንቺ የት ሄደሽ? እኔማ ለገብርዬ ያን እሰጥ ብዬ
አግባኝ ሳልለው አግብቶኝ ነጋዴ
ሲያበላኝ ከረመ ነጭ ጤፍ ከስንዴ›› እያሉ ሹላሌ የተሰኘ ጨዋታን እየተመላለሱ የሚጫወቱት የላሊበላ ልጃገረዶች ናቸው፡፡
በላሊበላ ከተማም የፋሲካ በዓል ሲከበር ከሚከናወኑት ድርጊቶች አንዱ የሆነው ሹላሌ፣ በባህል ባለሙያው አቶ ዓለሙ ኃይሌ አገላለጽ፣ ከትልቅ ዛፍ ላይ ጠፍር ታስሮ ልጃገረዷ በጠፍሩ ላይ ተቀምጣ የምትጫወተው ነው፡፡ ሌሎች እየገፏት እየዘፈኑ ዥዋዥዌውን ይጫወታሉ፡፡

በሰሜን ኢትዮጵያ ተዘውታሪው ሽው ሽው ላሌ (ሽውየ ሽውላሎ) ጨዋታ




ሹላሌ የተሰኘው ጨዋታ ከፋሲካ (ትንሣኤ) እስከ ዳግማይ ትንሣኤ ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ ልጃገረዶቹ በጠፍር ላይ ሆነው መወዛወዛቸው ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁዶች የክስ አደባባይ ከሔሮድስ ወደ ጲላጦስ፣ ከጲላጦስ እንደገና ወደ ሔሮድስ መመለሳቸውን ምሳሌ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
ሸካ ዞን የሚገኙት ሸከቾዎችም ፋሲካን በራሳቸው ባህላዊ መለያ ያከብሩታል፡፡ በዓሉ ሐሙስ የሚጀምር  ሲሆን ዕለቱ ‹‹ዳጲ ማዮ ማዮ›› ይባላል፡፡ ይህም የንፍሮ ቀን ማለት ሲሆን፣ ቀኑን በጾም በማሳለፍ ወደማታ የሚበላው ምግብ ንፍሮ ብቻ ነው፡፡ በሌሎች ቦታዎችም በጸሎተ ሐሙስም ጸዋሚዎቹ ጉልባንና ንፍሮ ቀምሰው እስከ ትንሣኤ ሌሊት ሳይመገቡ ያከፍላሉ፡፡ ባቄላ፣ ስንዴና ጥራጥሬ ተቀላቅሎበት የሚዘጋጅ የምግብ ዓይነት ጉልባን  ነው፡፡ ዓርብ ስቅለት ከስግደት መልስም ጉልባን ይበላል፡፡ የሐዘን መግለጫ ሆኖ የተወከለ ነውና፡፡
በሸከቾዎች ዓርብ ስቅለት ‹‹አኪላቶስ›› ሲባል በዚህ ቀን በተለይ እናቶች ቀኑን በልዩ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡ እናቶች ጠንካራ የፈትል ገመድ አዘጋጅተው የሁለቱን እጃቸውን ክንድ ባንድ ላይ የኋሊት በማሰር ይውላሉ፡፡ ወደማታ ሲሆን እጃቸውን ከፈቱ በኋላ በሠፈሩ ያሉ ሴቶች በኅብረት ‹‹ዮዲ›› በሚባል በደንና በዕፅዋት በተከበበና በተከበረ ቦታ በመሰባሰብ ቅጠል አንጥፈው ድምፃቸውን ከፍ  አድርገው ዘለግ ባለ ድምፀትና ተመስጦ ‹‹እቶማራማራ እቶስ›› ‹‹ዮሻ ዮሻ ኢቶስ›› እያሉ ለረዥም ሰዓታት ይሰግዳሉ፡፡ ‹‹መሐሪ የሆነው ክርስቶስ ተይዞ ለሞት ተሰጠ›› የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፣ በየሁሉም ሠፈር የሚከናወነው ስግደት ከሠፈር ሠፈር የሚሰማ ነው፡፡
 ስለሸካቾ ብሔረሰብ የሚያወሳ አንድ ድርሳን እንደሚያመለክተው፣ ‹‹በስቅለት ዕለት (ዓርብ) ምዕመናኑ ሙሉ ቀን ጹመውየሺ-ቅቶሶች ይለምናሉ፡፡የሺ-ቅቶሶችማለት ከሥረ መሠረቱ ከእኛ ጋር ያለን ጌታ፤ ተይዞ ለእኛ የተሰቀለው፤ ለእኛ ብሎ የሞተ፤…›› የሚለውን ቃል ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም የጸሎት አዝማቹ ‹‹እቶ ማራማራ እቶስ!›› የሚለውም የክርስቶስ ተከታዮችን ያመለክታል፡፡  
‹‹ፋሲካ መጣ ገበታው ቀና አለ!›› የሚሉት ሸካዎች ናቸው፡፡ በቋንቋቸው ‹‹ማዲካም›› ይሉታል፡፡ በቀጥተኛ ትርጉሙ ቀና ያለ ገበቴ ማለት ነው፡፡ እሑድ ፋሲካ ወይም የዋናው ማዲካም ዕለት በመሆኑ ከብት ይታረዳል፤ እናቶች ገሪግዮ በሚባል ጎምዛዛ ቅጠል አፋቸውን አራት ጊዜ ‹‹ጮሚበቾ›› በማለት ካበሱ በኋላ መመገብ ይጀምራሉ፡፡ በጾሙ ወቅት ተከድነውና ተሰቅለው የቆዩ የምግብ ዕቃዎች ታጥበውና ፀድተው ለምግብ የሚዘጋጁበት፣ ፋሲካ መጣ ገበታው ቀና አለ ማለት እንደሆነ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡
ምንጃሮችም በዕለተ በዓሉ እሑድ ዕለት ጠዋት ሁሉም የቤተሰብ አባላት ይሰበሰቡና ቡና ተፈልቶ ዳቦ ይቆረሳል፡፡ በግም ሆነ ፍየል የተዘጋጀው ይታረዳል፡፡ ከዚህ ባለፈ እንደቤተሰቡ የአቅም ሁኔታ የከብት ቅርጫ ሥጋ ተካፍሎ ለቤተሰቡ በማስገባት በዓሉ ይከበራል፡፡ ‹‹እንኳን ጾሙን ልጓሙን ፈታላችሁ›› የበዓሉ የመልካም ምኞት መግለጫ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ሥርዓት መሠረት፣ በእሑድ ፋሲካ ዋዜማ ቀዳም ሥዑር (ቅዳሜ ሹር) ማለዳ ቄጠማ እየታደለገብረ ሰላመ በመስቀሉ ወአግሀደ ትንሣኤሁ” (በመስቀሉ ሰላምን አደረገ፤ ትንሣኤውም ግልጽ ሆነ) ተብሎ ይከበራል፡፡

   ኢየሩሳሌም በሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳማት ያለው የትንሣኤ በዓል አከባበር

ምሽት ላይ ምእመናን ወደየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው ጧፍና ሻማ በመያዝ በምሥራቹና በሥርዓተ ቅዳሴው ለመካፈል የሚጓዙበት ነው፡፡ እስከ መንፈቀ ሌሊት ይቆያሉ፤ በፋሲካ ሌሊት የምሥራቹን ጧፍና ሻማ በመለኮስ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የሚደረገው ዑደትትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ” (ትንሣኤህን ላመንን ለእኛ ብርሃንህን ላክልን) በሚለው ዝማሬ የታጀበ ነው፡፡ ዶሮ ሲጮህ ይፈስካሉ፤ ለምእመናኑ በመንፈሳዊ እርሻ የተመሰለው ሁዳዴው ሲጀመር
ጀግናው ዐቢይ ጾም ቢታይ ብቅ ብሎ፣
ቅቤ ፈረጠጠ አገር ርስቱን ጥሎ
ተብሎ በቃል ግጥም የታጀበው ጾም ሲፈታ፣ በተለይ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ከቅባት የተለየው አካል እንዳይጎዳ ልዩ ምግብ ይዘጋጅለታል፡፡ ማለስለሻ እንዲሆን ተልባ ይቀርባል፡፡
እንደየኅብረተሰቡ ባህል የፋሲካ ድፎ ዳቦ፣ ዶሮ ዳቦ፣ ኅብስት፣ የዶሮ ወጥ እንቁላል፣ የዕርድ ከብቶችን ማዘጋጀት ጠጅና ጠላ መጠጥ ማዘጋጀት የክብረ በዓሉ አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ከመልካም ምኞቱ እንኳን አደረሳችሁ፣ ጾመ ልጓሙን እንኳን ፈታልዎ በአነጋገር ደረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከርቀትም ሆነ ከቅርበት ያሉ ቤተሰቦች የሚሰባሰቡበት ስጦታ ሙክት፣ ድፎ ዳቦና መጠጦች የሚለዋወጡበትም ነው፡፡ 
ሸከቾች ከዐቢይ ጾምና ከፋሲካ ጋር በተያያዘ ለየት ያለ የወራት አሰያየም አላቸው፡፡   የካቲት፡- ‹‹መዴጉፓ›› የሁዳዴ ጾም በየካቲት ወር ስለሚጀምር፣ እስካሁን በቅበላ ቆይተሃልና ገበታህን አጥበህ ድፋው ወይም ጾም ጀምር የሚል አንድምታ ያለው ነው፡፡ መጋቢት፡- ‹‹ገኤውቆ›› የጾም እኩሌታ የሚደርስበት ወር በመሆኑ በርታ እንደማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የደብረዘይት በዓል የሚከበርበት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ሚያዝያ፡- ‹‹መካሞ›› ጾም ልትፈታ ነው፡፡ ስለዚህ ተደፍቶ (ተቀምጦ) የከረመውን ገጽታህን ቀና አድርገህ ጾምህን ፍታ፣ የፋሲካ በዓልን አክብር ማለት ነው፡፡ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም አከባበሩ ጉልህ ይሆናል፡፡
የወጣቶች ጨዋታ
የላሊበላ ወንዶች የሚጫወቱት ጨዋታ ደግሞ የጊጤ ጨዋታ ይሰኛል፡፡ ስለዚህ ጨዋታ አቶ ዓለሙ ኃይሌ እንዲህ ይላሉ፡፡
ወንዶች ቁልቋል የሚባል ተክል ቆርጠው ግንዱን መሬት ቆፍረው ይተክሉታል፡፡ ከዚያ የሾላ አንካሴ ይዘው እሱን እየወረወሩ ይወጋሉ፡፡ ውድድር አለው በተራ በተራ ያሸነፈ ይጨበጨብለታል፡፡ ረቺው በተረቺው ላይ ተፈናጦ ይሄዳል፡፡ ይጋልባል፡፡ በአንካሴ ቁልቋሉን ይወጋል፡፡ ይኸው ጨዋታ ኢየሱስ በጦር የመወጋቱ ምሳሌ መሆኑ ይነገራል፡፡ በትውፊት እንደሚነገረው ጨዋታውን የኢየሱስን መቃብር ሲጠብቁ የነበሩት ወታደሮች ይጫወቱት የነበረው ጨዋታ ጋርም ያይዙታል፡፡
አቶ ዓለሙ ከምዕመናኑ ሌላ አገልጋዮችም የራሳቸው ጨዋታ እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ ነጫጭ ልብስ ለብሰው፣ ጥምጥማቸውን አሳምረው ‹‹ተስዒነነ ዘወንጌል ቃለ››- የወንጌል ቃልን ተጫምተን መስቀልን ተመርኩዘን- እያሉ በየቤቱ በዓሉን የሚመለከት ወረብ እንደሚወርቡ ያስታውሳሉ፡፡
‹‹አማን በአማን ተንሥአ እሙታን›› - እውነት በእውነት ከሙታን ተለይቶ ተነሣ- በማለት ትንሣኤውን ያበስራሉ፡፡ ከፋሲካ በዓል ጋር ተያይዞ በሚኖረው ጨዋታ ማንጎራጎሩም ያለ ነው፡፡
‹‹አብ እየበደለኝ እያዘነ ሆዴ
ለወልድ እነግራለሁ ለሥጋ ዘመዴ
አብን ተዉትና ንገሩት ለወልድ
ተሰቅሏል ተገርፏል እርሱ ያውቃል ፍርድ፡፡››
   የእሽኬ ጨዋታ
የፋሲካ በዓል በተለይ ለወጣት ልጃገረዶችና ወጣት ወንዶች የተለየ ጊዜ በመሆኑ በምንጃሮች አጠራር ‹‹ሸንጎ›› ላይ በመውጣትና በመጫወት የሚተጫጩበት፣ ወጣት ወንዶችም የትግል ጨዋታ የሚጫወቱበትና አሸናፊና ተሸናፊ የሚባባሉበት፣ ‹‹እሽኬ›› የተባለውን ጨዋታ ይጫወቱበታል፡፡
በዓሉ የምቾት፣ የድሎትና የደስታ ጊዜ መሆኑን ለማመልከት ልጃገረዶች እንዲህ እያሉ ያዜማሉ ይላል፤ በሰሜን ሸዋ ላይ የተሠራው የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ኢንቬንቶሪ ሰነድ፡፡
 ‹‹አወይ ፋሲካ ኮበለለ
         የሽሮ ቅሉን እያንከባለለ
አወይ ፋሲካ ጀግናው
        ሥጋ እንደጎመን የሚበላው
አወይ ፋሲካ የተውሶ
         ይሄዳል ተመልሶ
የፋሲካ ዕለት እነማዬ ቤት እነአባዬ ቤት
          ያለ ደስታ ያለ ድሎት
የስንዴ ቆሎ በገበታ
         አወይ ፋሲካ የኛ ጌታ››
እያሉ በዘፈኖቻው ይገልጻሉ፡፡
በወጣቶች በኩል በተለይ በዕለተ በዓሉ በቡድን የሚከወን የሩጫ ውድድር በአሸናፊና ተሸናፊ ቡድኖች መካከል በዜማ መወራረፍ አለ፡፡
‹‹አምና የፋሲካ ዕለት ሱሪዬን ባውሰው
         እጓሮ ዞረና ቆሻሻ ለወሰው
አስረጂ2- ይኼን ግርንቡዱን ከወገቡ ጎርዶ
         አንዱን ለሙቀጫ አንዱን ለማገዶ
አምና ይኼን ጊዜ ሽልጦ
         አላስሮጥም አለው ጎኑ ተሸጦ››
እየተባለ ተሸናፊ ቡድን አለመቻሉን በውረፋ መልክ እየገለጹ ይገጥማሉ፡፡
·                     የፋሲካ ቀመር
የፋሲካ (ትንሣኤ) በዓል አከባበር በአቆጣጠር ልዩነት የተነሣ 16ኛው ምእት በኋላ ምሥራቆችና ምዕራቦች ከመለያየታቸው በፊት 326 እስከ 1582 ድረስ 325 በተካሄደው ኒቅያ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ክብረ በዓሉ በተመሳሳይ ቀን ይውል ነበር፡፡ 

ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12 12 ሰዓት የሆነበትመጋቢት 25 (በጁሊያን ማርች 21 ቀን) በሲሲሊያ ጣሊያን

በዓሉ ምንግዜም ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12 12 ሰዓት ከሚሆንበት መጋቢት 25 (በጁሊያን ማርች 21) በኋላ፣ ከአይሁድ ፍሥሕ (ፋሲካ) በኋላ፣ ባለው እሑድ ሁልጊዜ እንዲውል ይደነግጋል፡፡ ከጥቅምት 1575 .. (1582) በኋላ የጁሊያን አቆጣጠርን ያሻሻለው የጎርጎርዮስ ቀመር በአብዛኛው የአውሮፓ ካቶሊኮች ተቀባይነት በማግኘቱና በተፈጠረው የቀናት መሳሳብ ሌላ የትንሣኤ በዓል ሊፈጠር ችሏል፡፡ 
የኦርቶዶክስ ፋሲካ የጁሊያንን ቀመር፣ ኢትዮጵያና ኮፕት ደግሞ በራሳቸው ቀመር የኒቅያውን ድንጋጌ ይዘው በመዝለቃቸው ክብረ በዓሉን በአንድ ቀን ያከብራሉ፡፡ በኢትዮጵያና በኮፕት ባሕረ ሐሳብ መሠረት የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ዓርብ መጋቢት 27 ቀን 34 .. ትንሣኤው እሑድ መጋቢት 29 ቀን የዋለ ሲሆን፣ በየዓመቱ እነዚህ ዕለታት  የስቅለት መነሻና የትንሣኤ መነሻ ተብለው ይታሰባሉ፡፡
ትንሣኤን ተከትለው ቀናቸው በየዓመቱ የሚዘዋወሩት ጾሞችና በዓሎች የአወጣጥ ሥርዓት መደበኛውን ፀሐያዊ አቆጣጠር ሳይሆን የፀሐይና ጨረቃን ጥምር አቆጣጠር (ሉኒ-ሶላር) ይከተላል፡፡ ይህም በመሆኑ ትንሣኤ በመጋቢት 26 እና በሚያዝያ 30 መካከል ባሉት 35 ቀናት ውስጥ ይመላለሳል፡፡ 
ጥንታዊ መጽሐፍ ፍትሐ ነገሥት በፍትሕ መንፈሳዊ ክፍሉ ስለ ትንሣኤ በዓል አከባበር እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹… የትንሣኤውን በዓል በዕለተ እሑድ እንጂ በሌላ ቀን አታድርጉ፤ በመንፈቀ ሌሊት ብሉ፤ ያም ባይሆን በነግህ ብሉ. . . ከዚህም በኋላ ፈጽሞ ደስ እያላቸሁ ጾማችሁን በመብል በመጠጥ አሰናብቱ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና፡፡››
·                     የፋሲካ ቀን ቋሚ ለማድረግ ?
በባሕር ማዶ 1920ዎቹ ጀምሮ በየዐረፍተ ዘመኑ የፋሲካ በዓል ቋሚ ቀን ተቆርጦለት እንዲከበር ሐሳብ እየቀረበ ነው፡፡ የሩቁን ትተን 2006 .. ወዲህ በአማራጭነት የቀረበውና በካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ ጁስቲን ወልቢ እንደተስተጋባው፣ ‹‹የኤፕሪል ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ እሑድ›› ላይ እንዲውል ነው፡፡
እንዲህ ይባል እንጂ የቀረበው ሐሳብ በሌሎች ወገኖች ተቀባይነት እያገኘ አይደለም፡፡ 325 .. ኒቅያ ጉባኤ ድንጋጌ፣ ምሳሌው በጨረቃ የሚወጣው የአይሁድ ፋሲካ (ፍሥሕ) የሆነለት የክርስቶስ ፋሲካ ስሌቱ በጨረቃ ጭምር የሚገኝ መሆኑ በደነገገበት፣  ተዘዋዋሪነቱን ትቶ እንዴት ቋሚ ይሆናል ብለው ይጠይቃሉ፡፡
የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፋሲካን የምታከብረው በኒቅያ ድንጋጌ መሠረት በመሆኑ በዓሉ ቋሚ ፈጽሞ አይሆንም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ይልቅስ ምዕራቦች 16ኛው ምዕት ዓመት በፊት ከምሥራቆች ጋር በአንድነት ያከብሩት እንደነበረው ወደዚያው እንዲመለሱ ይመክራሉ፡፡

የሁለት ፋሲካዎች ወግ

ከሃምሳ አምስት ቀናት ዓቢይ ጾም በኋላ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችና በዓለም ዙርያ ያሉ የኦርቶዶክስ ክርስትና እምነት ተከታዮችም የራሳቸውን የጾም ትውፊት አልፈው ዛሬ መጋቢት 30 ቀን 2010 .. ፋሲካን (ትንሣኤ) እያከበሩ ነው፡፡ ምዕራባውያኑና ተከታዮቻቸው ደግሞ ከሳምንት በፊት አክብረዋል፡፡ ፋሲካ በተመሳሳይ ምክንያት የሚዘከር በዓል ሆኖ ሳለ በተለያየ ቀን መከበሩ የብዙዎች ጥያቄ ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተለይቶ የተነሣበት ቀን በካቶሊክ ሃይማኖት ምዕራባውያኑ) ከኦርቶዶክሳውያኑ (ምሥራቃውያኑ) ቀናት ቀድሞ ይከበራል፡፡ ሊቃውንት እንደሚያስረዱት፣ በሁለቱ ሃይማኖቶች መካከል ክብረ በዓሉ የሚውልበት ቀን ልዩነት የመጣው አንድም በሚከተሉት የቀን መቁጠሪያ ነው፡፡
በኦርቶዶክስ ክርስትና ሃይማኖት ፋሲካ የሚውልበት ቀን የሚሰላው በጁልያን ቀን መቁጠሪያ ሲሆን (ኢትዮጵያና ኮፕት በራሳቸው መንገድ ያሰላሉ) የተቀሩት የክርስትና ሃይማኖቶች ጎርጎርዮሳዊውን ቀመር ይከተላሉ፡፡ በሁለቱ አቆጣጠሮች መካከል በዚህኛው ምዕት ዓመት 13 ቀናት ልዩነት ያለ ሲሆን፣ ግሪጐሪያኑ ከጁልያን ቀድሞ ይመጣል፡፡
ሌላው ምክንያት ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን 325 .. በኒቂያ የተካሔደው የመጀመሪያው ኢኩሜኒካል ጉባኤ ያወጣውን መርህ መከተሏ ነው፡፡ መርሁ ፋሲካ ከአይሁዳውያን ፍሥሕ (ፓስኦቨር) በኋላ አንዲከበር ይደነግጋል፡፡ ይህም ኦሪቱ የሚያትተውን ታሪካዊ አካሔድ በመከተል ነው፡፡ ከኦርቶዶክስ ውጪ ያሉ የክርስትና እምነቶች በዚህ መርህ ስለማይተዳደሩ የክርስቶስ ፋሲካ ከአይሁዳውያኑ ፍሥሕ ቀድሞ ወይም አብሮ ይከበራል፡፡
በተጠቀሱት ምክንያቶች መሠረት የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ከተቀሩት በተለየ ፋሲካን ከሦስት እስከ አምስት በሚደርሱ ሳምንታት ልዩነት ብታከብርም፣ አንዳንዴ በተመሳሳይ ቀን ይውላል፡፡ ከዚህ ቀደም ፋሲካ ተመሳሳይ ቀን የዋለው 2002 2003፣ 2006 ዓምና 2009 .. ነበር፡፡ በቀጣይ ፋሲካ በአንድ ቀን የሚከበረው ከ12 ዓመት በኋላ በ2022 .. ይሆናል፡፡
ፋሲካ በተመሳሳይ ቀን የሚውለው በዩልዮስም ሆነ በጎርጎርዮስ ቀመር መሠረትጨረቃ ሚያዝያ 14 ቀን ባንድነት ከገጠሙ ነው፡፡ ይህ በተደጋጋሚ አይከሰትም፡፡ ክርስቲያኖች  ሆነው ኦርቶዶክስ በሆኑና ባልሆኑ መካከል ፋሲካ የሚከበርበት ቀን መለያየቱ ብዙዎችን ግራ የሚያጋባ ቢሆንም፣ በሁለቱም የፋሲካ ቀን የሚታወቅበት የተለያየ ቀመር አላቸው፡፡
አባ ጆን ማጉሊያስ ‹‹Why Orthodox Christian Easter is Later than the Catholic One›› በሚል ርእስ እንደጻፉት፣ የክርስትና እምነት በመጀመርያዎቹ ሦስት አሠርታት ላይ ፋሲካ የሚከበርበት ወጥ ቀን አልነበረውም፡፡ አንዳንድ የእምነቱ ተከታዮች የአይሁዳውያን ፍሥሕ አልፎ በሚመጣው የመጀመርያው እሑድ ያከብሩ ነበር፡፡ ሌሎች ደግሞ ከፍሥሕ ጋር በተመሳሳይ ወቅት ያከብራሉ፡፡ ወጥ ቀን ለበዓሉ ለመስጠት ያሰቡ ቅዱሳን አባቶች 325 .. የመጀመርያውን ኢኩሜኒካል ጉባኤ አካሔዱ፡፡ በቀደምት ክርስቲያኖች አካሔድና በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮት መሠረት ወጥ የሆነ ቀን ለማግኘት ተማከሩ፡፡
የደረሱበት ቀመር ፋሲካ ጨረቃ ሙሉ በሆነችበት የመጀመርያው እሑድ ማለትም ከአይሁድ ፍሥሕ በኋላ እንዲከበር ነው፡፡ ይህም ከፀደይ እኩሌ ‹‹ቨርናል ኢኩኖክስ›› (ቀንና ሌሊት እኩል እኩል 12 ሰዓት ከሚሆኑበት ቀን) በኋላ ነው፡፡ ይህ ቀን ግራ መጋባት እንዳይፈጥር ቀኑ በዩልዮስ ቀን መቁጠሪያ ‹‹ማርች 21›› በኢትዮጵያ መጋቢት 25 ቀን እንዲሆን ተወሰነ፡፡ በዓለም ላይ ፋሲካ የሚከበርበት ቀንም አንድ ሆነ፡፡ ይህን መርህ የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ተከትላው ብትዘልቅም፣ የምዕራብ ቤተ ክርስቲያን ፖፕ ጎርጎርዮስ በ16ኛው ምዕት ዓመት የዩልዮስን ቀመር በመከለሳቸው ከጊዜ በኋላ አልተከተሉትም፡፡
የምዕራብ ነገረ መለኮት ምሁራን (ጥቂት ኦርቶዶክሶችን ጨምሮ) የጉባኤው ዓላማ ፋሲካ ምንጊዜም የአይሁዳውያንን ፍሥሕ ተከትሎ እንዲከበር ለማድረግ አይደለም በሚል ይቃወሙታል፡፡
የጉባኤውን ውሳኔ አለመቀበል ግን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሞት የተነሣበት ቀን ማለትም 325- 1582 .. የተከበረበትን ደንብ መጻረር ይሆናል የሚሉ አሉ፡፡ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ተመራማሪዎችና ሊቃውንት እንደሚገልጹት፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ‹‹ማንኛውም ጳጳስ ወይም ዲያቆን ቀንና ሌሊት እኩል 12 ሰዓት ከሚሆኑበት ቀን ቀድሞ ፋሲካን ከአይሁዳውያኑ ጋር ቢያከብር ይጋለጥ፤›› ይላል፡፡
የጎርጎርዮሳዊው ቀመር በአብዛኛው የዓለም ክፍል ግልጋሎት ላይ የሚውልም ነው፡፡ ከምዕራባውያን ቤተ ክርስቲያኖች አብዛኞቹ ይህን ቀን መቁጠሪያ መጠቀም ሲጀምሩ፣ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ግን ቀመሩን  በጥብቅ ተቃውማለች፡፡
... 1920 የኦርቶዶክስ ተከታዮች አጠቃላይ ጉባኤ በቁስጥንጥንያ (ኮንስታንቲኖፕል) ተካሒዶ ነበር፡፡ ጉባኤውን መላው የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያኖች ባይካፈሉም ብዙዎች ተገኝተው ነበር፡፡ ጉባኤው በአወዛጋቢ ሁኔታ ከጎርጎርዮሳዊ ቀመር ጋር ተቀራራቢ የሆነና የተከለሰ ቀን መቁጠሪያ በሥራ ላይ ለማዋል ተስማምቷል፡፡ ይህ በተግባር የሚውለው ከፋሲካ ክብረ በዓል ዕለት ውጪ ላሉት ሲሆን፣ ፋሲካ ግን ዛሬም በኦርጅናሉ የዩልዮስ ቀመር  ቀጥሏል፡፡ የቀመሩ መሻሻል የሚታየው ልደትና ጥምቀትን የመሰሉ በዓላትን ከምዕራባውያን ቤተ ክርስቲያኖች ጋር በተመሳሳይ ቀን በመከበሩ ነው፡፡ ከፋሲካ ጋር ጴንጤቆስጤና ዕርገት በዩልዮስ ቀመር መሠረት በተለየ ቀን ሲከበሩ፣ ለኦርቶዶክሳውያን በዚህ መልክ የቀደመውን ሥርዓት መከተል ከፍተኛ ቦታ የሚሰጠው ነው፡፡    
   ኢየሩሳሌም በሚገኙ የኢትዮጵያ ገዳማት ያለው የትንሣኤ በዓል አከባበር

No comments:

Post a Comment