በመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት (1923 - 1967) ከነበሩት መሳፍንት ብቸኛው
በሕይወት ያሉ ራስ ናቸው፡፡ ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ዮሐንስ፣ የአፄ ዮሐንስ 4ኛ የልጅ ልጅ ልጅ፡፡ በሃያኛው መቶ ክፍለ ዘመን
የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በሚኒስትርነት፣ በአውራጃና ጠቅላይ ግዛት አገረ ገዥነት የረዥም ዘመን አገልግሎት ሰጥተዋል፡፡ የሥራና መገናኛ
ሚኒስትር (1950 - 1953 ዓ.ም.) በነበሩበት ወቅት በቦርድ ሊቀመንበርነታቸው የኢትዮጵያ አየር መንገድን ወደ ጄት ዘመን ያሸጋገሩ፣
በተመሳሳይ ኃላፊነት በአውራ ጎዳና ባለሥልጣን ዓብይ ድርሻ የነበራቸው ናቸው፡፡ ከአፍሪካ አዳራሽ እስከ ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ
ግንባታ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ የትግራይ ገዥ ከመሆናቸው በፊት ሦስት ግዛቶችን የጅባትና ሜጫ አውራጃ፣ የአርሲና የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛቶችን
አስተዳድረዋል፡፡ የመጀመርያው ዘመናዊ የአመራር ትውልድ አባል ሆነው መገኘታቸው የሚወሳላቸው ልዑል ራስ መንገሻ በ1966 ዓ.ም.
አብዮት ምክንያት ዘውዳዊ ሥርዓቱ ሲያበቃ፣ መንበረ መንግሥቱን የያዘውን ደርግ ለመታገል የተቋቋመው የኢትዮጵያ
ዴሞክራቲክ ኅብረት (ኢዲኅ) ግንባር ቀደም መሥራችና መሪ ከነበሩት ሰዎች አንዱ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ቀበና ሠፈር ኅዳር
29 ቀን 1919 ዓ.ም. የተወለዱት ልዑል ራስ በቅርቡ ‹‹የትውልድ አደራ›› የተሰኘ ግለ ታሪካቸውን አዘጋጅተው የኢትዮጵያ አካዴሚ
ፕሬስ አሳትሞላቸዋል፡፡ ዘጠና አንደኛ ዓመታቸው ላይ የሚገኙት ልዑል ራስ በድርሳናቸው ውስጥ ‹ለተግባረ ነፍስ ለተግባረ ሥጋ ለመብቃት፣
ወርቅ በእሳት እንደሚነጥር ሁሉ የሰውም ልጅ እንደ እሳት በሚያቃጥል የሕይወት ፈተና ውስጥ ማለፍ ይኖርበታል፡፡ ይህን መሬት ጠብ
የማይል ሀቅ፣ ከእኔ ግለ ሕይወት አንፃር ሳገናዝበው ረዥም ዕድሜና ጤና ከማታ እንጀራ ጋር መታደሌ፣ እንደ እሳት በሚነድ ሥቃይና
መከራ ተፈትኜ ማለፌን ያስታውሰኛል› ያሉት አጋጣሚዎቹን በመጥቀስ ነው፡፡ ‹‹በ13 ዓመት ዕድሜዬ በንጉሠ ነገሥቱ ዙፋን ችሎት ተከስሼ
በሞት እንድቀጣ ተደግሶልኝ የነበረው ፍርድ፣ እንደዚሁም የደርግን የመፈንቅለ መንግሥት አመፅ በትጥቅ ትግል ለመደምሰስ በበረሃና
አገር ላገር በመንከራተት ያሳለፍኩት 17 ዓመት ከባድ የፈተና ዘመኖቼ ነበሩ፤›› ይላሉ፡፡ በትውልድ አደራ ድርሳናቸውና በወቅታዊ
ጉዳይ ላይ ከልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም ጋር ሔኖክ ያሬድ ያደረገው
ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡
ሪፖርተር፡-
‹‹የትውልድ አደራ››ን ለመጻፍ ምን አነሳሳዎት?
ልዑል ራስ መንገሻ፡- በአገራችን
ታሪክን የመጻፍ አስፈላጊነትና ጠቃሚነት እየጎላ መምጣቱ ነው የሕይወት ታሪኬን እንድጽፍ ያነሳሳኝ፡፡ በቅርብም በሩቅም ያሉ ዘመድ
ወዳጆቼ ታሪኬን እንድጽፍ ጎትጉተውኛል፡፡ ብዙ ሠርተሃል፣ ለአገር ሊጠቅም ይችላልና የምታስታውሰውን ነገር ብትገልጸልን ባሉት መሠረት
መጽሐፉን ጽፌያለሁ፡፡ ፕሮፌሰሮችም በበኩላቸው ጥሩ አድርገው የተቻላቸውን ያህል አከናውነውልኛል፡፡ በአንዳንድ ጉዳይ የዘነጋሁት
ቢኖርም እያስታወሱኝ ለመጻፍና ለመዘከር ተሞክሯል፡፡
እንዴት ተሠራ? በዚያ ዘመንህ ምን አደረክ?
ሲባል ሰው የሠራው ነገር ካለ ያንን የሠራውን ሁሉ መንገር ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ስለዚህ የተቻለኝን ያህል ጽፌያለሁ፡፡ ለማስተላለፍ
የፈለግሁትም ትውልዱ እንዲማርበት እንጂ እንዲሁ ነበር ለማለት አይደለም፡፡ ታሪክ ሲባል ደግሞ የሆነውን እንጂ ሊሆን ነበር ማለት
የለበትም፡፡ ስለዚህ የተቻለኝን ያህል ለማስረዳት የሞከርኩት በዚህ ሰው ምን ሊያደርግ ይችላል? ምንድነው ኢትዮጵያዊነት? ከምን
ወደ ምን ይሄዳል? እያመዛዘኑ እንዲሠሩ ለማድረግ ነው የመጻፉ ቁም ነገር፡፡
ሪፖርተር፡- በዘመናዊ የኢትዮጵያ ታሪክ በልማት ተግባር ውስጥ፣ በሥራና መገናኛ ሚኒስቴርም ሆነ በትግራይ
ጠቅላይ ገዥነትዎ ጊዜ ከፍተኛ ሚና እንደተጫወቱ በምሁራን ይገለጻል፡፡ ውጣ ውረድም አጋጥሞዎታል፡፡ እንዴት ይገልጹታል?
ልዑል ራስ መንገሻ፡-
ሥራ በሚሠራበት ጊዜ ችግር መኖሩ አይቀርም፡፡ ችግር በመጣ ጊዜ ደግሞ ችግሩን ተጋጥሞ መጨረሻ ላይ ድል ለማድረግ መሞከር ነው እንጂ
ማፈግፈግ አያስፈልግም፡፡ ወደኋላ መሄድ አይገባም፡፡ ካልተሠራና ችግር ካልገጠመ ደግሞ አይፈታም፡፡ በእኔ በኩል በእያንዳንዱ ተፈትኜ
ነው ያለፍኩት፡፡ አንዱ ነገር የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢ ሳለሁ በጄት አውሮፕላን ግዥ ያጋጠመኝ ነበር፡፡ በዘመኑ
በአገልግሎት ላይ የነበሩትና ዲሲ6ቢ (DC6B) አውሮፕላኖች ናቸው፡፡ ለሁለት ጄት አውሮፕላኖች ግዥ 45 ሚሊዮን ዶላር እንዲፈቀድልን
ለሚኒስትሮች ምክር ቤት አቀርብኩ፡፡ ሚኒስትሮች ምክር ቤት ይዤ ከመቅረቤ በፊት ግን በቦርዳችን ውስጥ የነበሩ የገንዘብ ሚኒስቴር
አባላት ይመስሉኛል ቀድመው የተናገሩት ‹አዳዲስ ጄቶች እንድንገዛ አሁን የመጣው ሚኒስትር ሐሳብ እያቀረበ ነው፡፡ እኛንም በቦርዱ
በግድ እንድንስማማ አድርጎናል› የሚል ነበርና ሚኒስትሩ ክቡር አቶ ይልማም [ዴሬሳ] ይህንኑ ተቀብለው በበኩላቸው ምኞት ነው በማለት፣
በዚያ መንገድ ፍላጎታችንን ለማፅደቅ እንደሚሞከር አድርገው ነበር የወሰዱት፡፡ እኔ ቴክኖሎጂ ያመጣው ነው እንጂ በራሴ በምኞት እንደዚህ
በሆነልኝ ብዬ እነሱ በሚሉት አይደለም ያደረግሁት፡፡ ፈረስና አህያ አብረው አይሄዱም፣ ፈረሱ ጄቱ ነው፣ አህያው ፕሮፔለር ነው አልኩ፡፡
ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ያቀረብኩትን ሐሳብ ገንዘብ
ሚኒስትሩ ‹‹በቅርቡ 28 ሚሊዮን ዶላር ያወጡ ሦስት ዲሲ6ቢ አውሮፕላኖች ገዝተን አስረክበናል፡፡ እነዚህን አዲስ የተገዙ አውሮፕላኖች
ሳይጠቀሙባቸው እንደገና ደግሞ አዲስ ባዩት ጄት አውሮፕላን እበራለሁ በሚል ጉጉት ይሆናል ይህንን ጥያቄ ያቀረቡት፤›› በማለት ይመልሳሉ፡፡
‹‹እንግዲህ የእናንተ ውሳኔ ይኼ ነው?›› ብዬ ስላቸው፣ ‹‹አዎ! አቅማችን ሲችል ነው እንጂ ከአቅማችን በላይማ ምን ማድረግ እንችላለን?
ሊሆን አይችልም፡፡ ተጠንቶ ወደፊት ይደረጋል፤›› የሚል ውሳኔ ሰጡ፡፡ እኔ በልምዴ መሠረት እንግዲህ ለበላይ ላሰማ በሚል ‹‹ይግባኝ››
አልኳቸው ጠቅላይ ሚኒስትሩን፡፡ ‹‹ይግባኝ ማለት ምን ማለት ነው?›› አሉ፡፡ ሚኒስትሩ ክቡር አቶ አበበ ረታ ምላሽ ሰጡ፡፡
‹‹እኛ ከትምህርት እንደመጣን ሥራ እንመደባለን፡፡
ዲሬክተር፣ ከዚያ ምክትል ሚኒስትር፣ ከዚያ በኋላ ሚኒስትር እንሆናለን፡፡ እሳቸው ግን ወረዳ ገዥ፣ አውራጃ ገዥ፣ ጠቅላይ ገዥ እያሉ
ከሥር ጀምረው ያጠኑና ያደጉ በመሆናቸው፣ ከዚያም ፍርድ ሚኒስቴርን ወክለው ዳኛ ሆነው አሟልተዋል ማለት ነው፡፡ እኛ ይኼንን ሥራ
አልሠራንም፡፡ እኛና እሳቸው ግራ ቀኝ ባለንበት ቦታ ላይ ይግባኝ የሚለው ሰው ያው የተረታው ሰው ነው፣ የለም ለእኔ የሰጣችሁት
ፍርድ ልክ አይደለምና ለበላይ አሰማለሁ ማለት ነው፡፡›› ጸሐፌ ትዕዛዝም አጋጣሚው ሆኖላቸው ‹ለማን ልበል› ብለው ቁጭ አሉ፡፡
‹እንዴ ምን ዓይነት ጥያቄ መጣ? እማውቀው ጃንሆይን ነው፡፡ ግርማዊ ጃንሆይን፤› አልኳቸው፡፡ ‹‹እኛ እኮ ነን የእሳቸው አማካሪዎች
ይኼንን አጥንተን ሊሆን ይችላል፣ አይችልም ብለን የምንሠራው፤›› አሉኝ፡፡ ይኼንን ጉዳይ እሳቸው ሄደው ለግርማዊ ጃንሆይ አስረድተዋል፡፡
እኔ ዓቃቤ ሰዓት ስላለኝ በዚያ ሥራዬ ብዬ ወደ ጃንሆይ እገባለሁ፡፡ ጃንሆይ ገና ሲያዩኝ ‹‹ዛሬስ ምን አመጣህ?›› ነው ያሉኝ፡፡
ገና ከአፌ ሳልጨርስ፣ ‹‹እውነታቸውን ነው እኮ፣ እነሱ ናቸው የእኛ አማካሪዎች፣›› አሉና እንደገና ራሳቸው፣ ‹‹አሁን እነሱ አቅራቢ
ቢሆኑ አንተ ምን ይሁን ትላለህ?›› በማለት ራሳቸው በሩን ከፈቱ፣ ‹‹እስቲ ያንተን ሐሳብ ንገረኝ›› ሲሉኝ እነሱ አይቻልም ብለዋል በማለት ከገንዘብ ሚኒስቴር ጀምሮ የተጻፈውን
አቶ ይልማ ባቀረቡት ሐሳብ ሁሉም ተስማምተዋል፡፡ ለዚህ ጉዳይ ግን፣ እኔ በበኩሌ ኢትዮጵያ ለ45 ሚሊዮን ዶላር ብድር አትበቃም
የሚል እምነት ስለሌለኝ ልሞክርና ካልተሳካ ይቀራል አልኩ፡፡
ያኔ በቃ ጃንሆይ ምንም አላሉ፡፡ እቺን ብቻ
ስላልኳቸው ስልኩን አነሱና ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጠሩ፡፡ ጸሐፌ ትዕዛዝ ሲገቡ እኔን እዚያ ቆሜ ጃንሆይ ደግሞ ቁጭ ብለው ሲያዩ ያስጠራኝ
ለአንድ ነገር ነው ብለው ሳቁ፡፡ ‹‹ጃንሆይም ምንድነው እምትለው?›› አሏቸው፡፡ ‹‹ጃንሆይ እንደዚህ ያለ ተሟጋች እኮ አይተንም
አናውቅም›› አሉ፡፡ ጸሐፌ ትዕዛዝም ‹‹ጽፌ አቀርባለሁ፡፡ ግርማዊነትዎ ይፈርሙለትና መንግሥትን ወክሎ ይሂድ፤ የማያምን ሰው እውነትም
መሥራት አይችልም›› ብለው መሰከሩልኝና ተወክዬ ሄድኩኝ፡፡ ሁሉም ነገር ተከናወነ፡፡
ሪፖርተር፡-
በዘመናችን ለኃይል ምንጭነት ታዳሽ ኃይል (ጂኦተርማል) በተግባር
ላይ እየዋለ ነው፡፡ በእርስዎ ዘመን ጥናቱ መጀመሩ መጽሐፍዎ ያሳያል፡፡
ልዑል ራስ መንገሻ፡-
ጂኦተርማል በእውነቱ እንደዚህ በአጋጣሚ የመጣ ነው፡፡ ጂኦተርማል አለ ብዬ ለመጠየቅ ወይም ለማስጠናት የሞከርኩት ነገር የለም፡፡
በሒደት የመጣ ውጤት ነው፡፡ እኔ ትግራይ ከሄድኩም በኋላ ቢሆን በሌሎችም አካባቢዎች በሄድኩበት ቦታ ሁሉ የራሴ አስተሳሰብ ሁልጊዜም
መገናኛ የሚለው ነገር ላይ ነው፡፡ መንገድ የደም ሥር ነው፡፡ ትምህርት ይሁን፣ ጤና ይሁን፣ አስተዳደር ይሁን፣ ዕድገት ይሁን ሁሉም
ሊታይ የሚችለው መንገድ ሲኖር ነው፡፡ በምድረ ገጹ፣ ዛፍ ምናምን ነገር ውኃ ከታች አለው፡፡፡ በምን ይተዳደራል የሚለውን ሁሉ ለማጥናት
ወይም ሕይወት በሙሉ የሚሄደው በዚህ የደም ሥር በሆነው መንገድ ነው፡፡ ስለዚህ የመንገድ ሥራ የመጀመርያ ሥራዬ ብዬ የጀመርኩት
በዚሁ ምክንያት ነው፡፡ ስለዚህ ያ መንገድ ምን አመጣ? ምን አፈራ ነው? እንዳልኩት ልማት ለማምጣት አስቻለ፡፡ አንዱ በአፋር ጂኦተርማል
መኖሩ መታወቁ ነው፡፡
ጂኦሎጂስቶቹ እንደገለጹልን ጂኦተርማል የሚባለው
የእንፋሎት ኃይል የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት የሚቻልበት፣ ነዋሪ የሆነ ኃይል፣ ይኼ ደግሞ ታዳሽ ነው፡፡ ታዳሽ ኃይሉ መገኘቱ ደስ
የሚያሰኝ ቢሆንም ለተጨማሪ ጥናት አራት ሚሊዮን ዶላር ወጪ መጠየቁ እንኳን በጠቅላይ ግዛት ደረጃ በአገር ግዛት ሚኒስቴርም ሊሠራ
የማይችል በመሆኑ እንደተለመደው ለግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ጉዳዩን አቀረብኩ፡፡ እሳቸውም በዚሁ በጥናቱ ላይ መጀመርያው የነበሩበት
ስለሆነ ‹‹በጣም ጥሬ ነዋ፣ አቅርባቸውና እናነጋግራቸዋለን›› አሉ፡፡ ጂኦሎጂስቶቹም ዘርዝረው አስረዷቸው፡፡
ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም
በፈቀደው ድጋፍ በኢንፍራሬድ (በታህተ ቀይ ጨረር) የሚነሳው ካርታም ተነሳ፡፡ ጥናታቸውን በሙሉ በሁለተኛው ዓመት ላይ ያጠናቀቁትን
የጥናት ሰነድ ለማዕድን ሚኒስቴር ተሰጥቶ በዚያው ተቀመጠ፡፡
ሪፖርተር፡-
የጂኦተርማል ጥናቱ ከምን ደረሰ? በዚህ ዘመን ስለዚህ ማዕድን እንሰማለን፡፡
ከዚያኛው ጋር የሚያያዝ ነገር አለው?
ልዑል ራስ መንገሻ፡- የጥናቱ ሰነድ ማዕድን ሚኒስቴር ተቀምጦ እያለ የግርማዊ ጃንሆይ ዘመነ መንግሥት
አልቆ፣ መፈንቅለ መንግሥት ተደርሶ ነገሩ ቆመ፡፡ ከትግራይ በለቀቅሁ በ35ኛው ዓመት ላይ በጊዜው የትግራይ ፕሬዚዳንት ከነበሩት
አለቃ ፀጋዬ በርሄ ጋር ስለ ልማት ጉዳይ ለመጫወት ችለን ነበር፡፡ እሳቸውም ‹‹ስለ ልማት ሥራ ብዙ ደክመው ነበር፡፡ እዚህ በነበሩበት
ጊዜ ሁሉ በአቅምም የሠሩት ብዙ ነገር አለ፡፡ በሐሳብዎ በዕቅዶ የነበረ ወይም ጀምረውት ተቋርጦ የቀረ ሥራ ይኖራል ወይ?›› ብለው
ይጠይቁኛል፡፡ እኔም ‹‹የነበረውን እያዳበራችሁ፣ እያሳደጋችሁ መሄዳችሁን አይቻለሁኝ፡፡ አንድ ቅር ያለኝ ነገር ካለ ግን፣ ደክሜበት
የሥራ ክፍሉ ዋጋ አልሰጠውም ብዬ ያልኩት በማዕድን ሚኒስቴር ውስጥ የተቀመጠ የጂኦተርማል ጥናት አለ፡፡ ይኼ ጥናት ለምን ሥራ ላይ
አልዋለም? ምንድነው የሚጠብቁት እያልኩ ነበር ሳሰላስል የቆየሁት አልኩ፡፡ ከዚያ ውይይት በኋላ የትኛው ነገር ተቀሰቀሰ፡፡ የጥናቱ
መሪዎች የነበሩ ጆኦሎጂስቶች በዕድሜ ቢያልፉም የእነሱ ምክትሎች አብረውን ሲሠሩ የነበሩት በመኖራቸው ጣሊያን አገር ሄደን አገኘኛቸው፡፡
የመንግሥት እንግዳ ሆነው አዲስ አበባ መጥተው ሥራው እንደገና መጀመር እንዳለብን ተስማማን፣ ሥራውም ተጀመረ፡፡ አሁን ይህን የእኛን
ጥናት ምን እናድርገው ለሚለው ጥያቄ ኢትዮጵያዊ የሆነ፣ ድርጅት መቋቋም እንዳለበትና ይህንኑ ቦታ አጥንተን ያገኘነውን ሥራ ላይ
ለማዋል ተነሳን፡፡
የአፋር ክልል አንተነህ ይኼን ያሠራኸውና አሁንም
እንዲቀጥል ቢደረግልን ብለው እንዳማክራቸው ጠየቁኝ፡፡ ድሮ ሸኸት የምንለው አሁን አብኣላ በሚባለው ከመቐለ 60 ኪሎ ሜትር ከሚገኘው
ከተማ ስብሰባ ተደርጎ የጂኦተርማል ጥናት አድርገዋል፡፡ አባላቸውንም መርጠዋል፡፡ ያንን በክልል ደረጃ አዘጋጅተው ጥናቱ ሁሉ ቀርቦ
ነበር፡፡ አሁን በቅርቡ እንደተናገሩት ከሆነ ውጤቱ ለማዕድን ሚኒስቴር ከሄደ በኋላ ፈቃድ ሳይሰጠው እስካሁን ድረስ ሁለት ዓመት
ሆኗቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡-
በትግራይ ውስጥ ጋዜጣ አቋቋመው ነበር?
ልዑል ራስ መንገሻ፡-
ፍላጎት ነው የፈጠረው፣ ምክንያቱም ትግራይ እንደሄድን በሙሉ የታጠበ ተራራ ነው ያጋጠመኝ፡፡ አፈራችንን በሙሉ ለሱዳንና ለግብፅ
ገብረናል፡፡ አሁን ደግሞ ይኼ ሁኔታ እንዴት ይቀጥላል ለራሳችን መሥራት ይገባናል በሚል ተግባራችን የነበረው ዕርከን የሚባለውን
በትዕዛዝ ብቻ ነበር የምናሠራው፡፡ አሁንም እግዚአብሔር ሲረዳ ‹‹ምግብ ለሥራ›› የሚል ፕሮግራም እናስፈቅድ በሚል ለክቡር አቶ
አበበ ረታ የእርሻ ሚኒስትር ነበሩ፤ አቅርበን አስፈቅደን ሥራውም ተጀመረ፡፡ ሕዝቡን ለማንቃትና ይሄንን አድርጉ ለማለት ደግሞ ስብስባ
እንጠራለን፡፡ በጭቃ ሹም ጀምሮ በትግራይ ወደ 1350 ጭቃ ሹሞች ነበሩ፡፡ 130 የሚሆን ደግሞ ምክትል ወረዳ፣ 56 ወረዳ፣ ስምንት
አውራጃ ጠቅላላ ስብሰባ እናደርግና ስለ ልማት ጉዳይ እናወራለን፡፡ ምን ይሻላል? ምን እናድርግ? ራሳችሁን ጠቅማችሁ አገራችሁን
ትረዳላችሁ በሚል ዓይነት እንወያያለን፡፡ ሁሉም ተሰማምተው እንወስናለን፡፡ ይህንን ወደ ሕዝባችን እንዲደርስና ንቃትም ለመስጠት
መሣሪያ ያስፈልጋል፡፡ እዚህ [አዲስ አበባ] ካሉት ጋዜጠኞች ስለ እኛ ጉዳይ አንድ አሳምነው ገብረወልድ የሚባል እየመጣ ነበር የሚያይልን፡፡
እሱም አልተመሰገነም፡፡ ‹‹ደጃዝማች መንገሻ ሥዩም ምን ያህል ደመወዝ ቆርጦልህ ነው አንተ ስለ ትግራይ እየመጣህ እንዲህ ተደርጓል
እያልክ እምታወራው?›› አሉት፡፡ ‹‹እኔ አገሬ ነው ስለ አገሬ ደግሞ ሄጄ ማጥናት ተገቢ ነው፡፡ ምንም ሳይኖራቸው እነሱ እንደዚህ
ዓይነት መሬት እያለ ያ በእውነቱ ለብዙ ዘመን ያገለገለ ለአገር ለነፃነት ጋሻ ሆኖ ያገለገለ አገር ዋጋው ሊመለስለት ይገባል ብዬ
መናገሬ በእኔስ በኢትዮጵያዊነቴ ነው እንጂ እኔን የምልበት የለም፡፡ ከመመስገን ፈንታ ደግሞ መቀሌ ከሳችሁኝ የፈለጋችሁትን ልታደርጉ
ትችላላችሁ›› ብሎ አለ፡፡ በዚህም የተነሳ እኛ የራሳችንን ማድረግ አንችልም ወይ አልንና ሰሜናዊ ኮከብ ጋዜጣን አቋቋምን፡፡ ከዚያ
በኋላ ታዕድል/ታይድል (የትግራይ የእርሻና የኢንዱስትሪ ልማት እንቅስቃሴ ማስታወቂያና መግለጫ ማስተማሪያና ማነቃቂያ ሆነ፡፡
ሪፖርተር፡-
የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኅብረት (ኢድኅ) መሥራችና መሪ ነበሩ፡፡
የጫካውን ትግልና ሰላማዊ ትግሉን እንዴት ይገልጹታል?
ልዑል ራስ መንገሻ፡-
ትግል እኮ ስሙ ነው እንጂ ተመጣጣኝ ነው፡፡ ምንም ኃይለኛ ነገር የለበትም፡፡ ሰላማዊ ትግሉም ማስረዳት መግባባትና መረዳት ነው፡፡
ለእሱም መሣሪያ ሆኖ የተሰጠን ዴሞክራሲያዊ የሚለው ኃይል ቃል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት የነበረው አስተሳሰብ ሙሉውን
ኢትዮጵያን የያዘ ነው፡፡ ይህን ለማግኘት ዕድል ማግኘታችንም አንድ ነገር ነው፡፡ ለሕዝቡ ይጠቅማል በሚለው ነገር ሰላማዊ የሆነ
የፖለቲካ ትግሉም ለአገር ይጠቅማል ብለው እስከተነሱ ድረስ ጥቅም እንጂ ጉዳት አያስከትልም፡፡ ጎደለ የሚባለው ነገር እንደ ልብ
መናገርና ማስረዳት ከተቻለ ሰሚ ጆሮ ደግሞ ካገኘ፣ ያ ሥራ ላይ ከዋለ ያው አስተካክልን ማለት ነው፡፡ ‹‹ከበሮ በሰው እጅ ያምራል
በእጅ ሲይዙት . . .›› እንደሚባለው የሥልጣን ነገር ሁሉም ሥልጣን ይመኛል፡፡ ከያዙት በኋላ ነው ጣጣ የሚመጣው፡፡ በደርግ ጊዜ
17 ዓመት ቀላል ነገር አልነበረም፡፡ ይህን ያህል ዓመት ቁጭ ያሉት ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም›› በሚለው ዓላማ ነው፡፡ እኔም አገር
ለቅቄ እንድሄድ ያበቃኝ አንደኛው እሱ ነው፡፡ የመንግሥት ግልበጣ በሚካሄድበት ጊዜ እስከ መጨረሻው ድረስ ትግራይ ነበርኩ፡፡ ጃንሆይ
በሚወርዱበት ጊዜ ትግራይ ነበርኩ፡፡ ንዑስ ደርግ የሚል ደግሞ በየጠቅላይ ግዛቱ ተቋቁሟል፡፡ እኔም ጋ ተቋቁማል፡፡ መድፈኛ ክፍል
አዲግራት ነበር፡፡ በእኔ አስተዳደርና አሠራር መልክ ለ14 ዓመት ያህል የቆየሁበት ቦታ ስለሆነ ሁሉም ያውቃል፡፡ በሚደርሳቸውም
ሪፖርት ማመዛዘን ችለዋል፡፡ እስከ ጳጉሜ ድረስ እዚያው ነበርኩ፡፡ ጥሪ ሲደርሰኝ እኔ መጀመርያ ነገር መልስ የሰጠኋቸው እኔ የትግራይ
ሕዝብ ስለ ኢትዮጵያ ትቅደም ከእሱ እማር እንደሆን እንጂ እነ ላስረዳውና ላስቀምጠው የምችለው ነገር የለም፡፡ ሕይወቱን እየሰዋ
ነው እስካሁን ኢትዮጵያን ያቆያት፤ በጂኦግራፊ አቀማመጡ ምክንያት ነው ጋሻ የሆነው፡፡ እንደሌላው መሀል አገር ቢሆን ኖሮ ይህን
ያህል ትግል አይደርስበትም ነበር፡፡ ማንኛውም ጦርነት ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄደው በመጀመርያው እስከ መጨረሻው ትግራይና ኤርትራ
ገፈት ቀማሾች ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡-
በኢትየጵያ ታሪክ ላይ ከቅርብ ዘመን ወዲህ አወዛጋቢ ነገር እየታየ
ነው፡፡ ታሪካችንን መጻፍም ማንበብም አልቻልንም፡፡ ምን አጋጠመን?
ልዑል ራስ መንገሻ፡-
የኢትዮጵያን ጥንታዊ ታሪክ ለትውልድ ማስተላለፍ አልተቻለም፡፡ በዛሬው የአገራችን አስተሳሰብ ደግሞ በጣም የሚያሳዝነው ነገር ካለ
ታሪክ ሲጠቀስ ከአፄ ቴዎድሮስ ጀምሮ ያለችው ኢትዮጵያ ናት የምትገለጸው፡፡ ከዚያ በፊት ያለው የኢትዮጵያ ታሪክ ግን ‹‹ከኖኅ እስከ
ኢሕአዴግ አምስት ሺሕ ዓመት›› ከሚል መጽሐፍ በስተቀር ሌላ የለም፡፡ ዛሬ ተበጣጥሶ ዓድዋ ብቻ ሆና ቀረች፡፡ ድሉም የተገኘው ዓድዋ
ነው፤ የተሠራውም ዓድዋ ነው፡፡ ከዚያ በፊትስ የስድስት ሺሕ ዓመት ታሪክ አለ፡፡ ኢትዮጵያ ስትባል ማን ነች? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል፡፡
አካል እየተቆራረጠ የሄደበት ዘመን ሁሉ መጥቀስ ይገባል፡፡ ለትውልድ ማስተላለፍ እኮ አልተቻለም፡፡ ዛሬ ያለው ተማሪ ቢጠየቅ የሚመልሰው
ስለአፄ ቴዎድሮስ ሰምቶ ይሆናል፡፡ ከዚያም ስለ ዓድዋ ጦርነት ነው የሚያውቀው፡፡ ከዚያ በፊትስ ነፃነታቸውን ጠብቀው የኖሩ አባቶቻችን
ተረሱ ማለት ነው? ዋጋቸው ሁሉ በዘመን ብዛት ተረሳ ማለት ነው? ታሪክ የተጻፈ ይወሳል፣ የተነገረ ይረሳል ይባላል፡፡ ታሪኮቹ ለምን
ይጠፋሉ? አሁን እኔ ለራሴ እኔ ከኖኅ እስከ ኢሕአዴግ የሚለውን መጽሐፍ ካገኘሁ በኋላ የአገሬን ማንነቷን ለማወቅ የበለጠ ረዳኝ፡፡
ያኔ ሱዳን ኢትዮጵያ ነች፡፡ ሶማሊያ ኢትዮጵያ ነች፡፡ በየጊዜው ተለይተውናል፡፡ ዛሬ ተሸማቀን የደረስንበት ቦታ ላይ ነን፡፡ እቺም
በዛች ተብላ እየተቆረጠች የምትሄድ አገር ሆናለች፡፡
ሪፖርተር፡
በኢትዮጵያ በተለይ ከስድስት አሠርታት ወዲህ በየዐረፍተ ዘመኑ ግርግርና
አብዮት ታይቷል፡፡ ለውጥ በመጣ ቁጥር በነበረው ከመቀጠል ሀ . . ብሎ የመጀመር ነገር ይታያል፡፡ በዚህ ረገድ እርስዎ ምን ይላሉ፡፡
የኢትዮጵያ ተስፋዋ እስከ ምንድረስ ነው?
ልዑል ራስ መንገሻ፡-
አገራችን ካለጥርጥር
በዘመናት ብዛት ያሉት ችግሮች በየመልካቸው ሊቀርቡ ይችላሉ፡፡ የዴሞክራሲ ንቅናቄዎችና ሁኔታዎች ሁሉ በየበኩላቸው የሚመጡ ነገሮች
አሏቸው፡፡ እና አሁን ከተያዘው እኔም ራሴ በኢትዮጵያዊነቴ የሚሰማኝ ነገር አለ፡፡ የአሁኑ ሕገ መንግሥት እንደ ሁናቴውና እንደ
ጊዜው የመጣ ነገር ነው፡፡ በራሴ አንቀጽ 39 ‹‹እስከ መገንጠል›› የሚለው ሰው አንድ እንሁን እንጠናከር ይላል እንጂ እንበተን
የሚለው ነገር ከየት የመጣ ነው? ጀርመኖች በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ላይ ምሥራቅና ምዕራብ ተብለው ለሁለት ከፍለዋቸው ነበር፡፡ ዕድል ሲያጋጥማቸው ግን ጀርመን ጀርመን ነው፣
ኢስት ዌስት የሚባል ነገር አናውቅም፤ አንድ ጀርመንን ነው የምናውቀው አሉ፡፡ በዚህም አንድነት ኃይል መሆኑን አሳዩ፡፡ በአገራችን
ግን መንምነን መንምነን አሁንም ቢሆን ይህ መንፈስ የሚራባበት ሆኗል፡፡ በዘመናችን ዛሬ እንኳን በሕይወት ያለ፣ መቃብር ውስጥ ያለው
ተነስቶ በረዳ በሚባልበት ጊዜ፣ ብዙ በስደት ዓለም ላይ መኖሩ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው፡፡ በመንግሥት ደረጃ ዳያስፖራ ተባሉ
የተጀመረ አንድ ነገር አለ፡፡ በዚህ መልክ ቢሆንም በውጭ ያለው እንዲገባ ወደ አገሩ ተመልሶ እንዲኖር መምከር ይገባል፡፡ ስለ ኤርትራ
ወገኖቻችንም ማሰብ አለብን፡፡ እንደነ ዘርዓይ ድረስ ያሉት ጀግኖች የሚሆኑት ከኤርትራ የተገኙ እንጂ ከትግራይ ከአማራ ወይም ከሌላ
ቦታ አይደለም፡፡ ስለዚህ ከእነዚህ ወንድሞቻችን ጋር አብረን የጋራ ኃይላችን የምናጠናክርበትን ማድረግ ይገባናል፡፡ ሌሎቹ የኢትዮጵያን
መመንመን የሚፈልጉ ኤርትራን ለብቻ አገር አድርገው አሁን እንደሆነላቸው ማለት ነው፡፡ በዚያ ‹‹አሁን እኛ እንረዳችኋለን፤ አስቸጋሪ
ምንም ነገር የለም›› በሚል ከፋፍለህ ግዛ በሚለው መልክ እየተጫወቱብን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ኢሕአዴግ ዴሞክራሲያዊነት
እየቀጠለ እንዲሄድ ጥሩ ዕርምጃ እየወሰደ ነው፡፡ አሁን በቅርቡ የተሰጠው ውሳኔ በራሴ በኩል ጥሩ ዕርምጃ ነው የምለው፡፡ እንደዚህ
ዓይነት አስተሳሰብ ደግሞ አንድ አካል መሆናችንን ነው የሚያሳየው በጥሩ መንገድ ላይ እየሄድን መሆናችንን ያሳያል፡፡ እንዳየሁት
ሕዝቡ በሰላም እየኖረ መተዳደር የሚፈልግ ነው እንጂ ሌላ ምኞት ያለው አይመስለኝም፡፡ እኔ ያልሠራሁበት ቦታ የለም፡፡ ጅባትና ሜጫ
አውራጃ፣ አርሲ፣ ሐዋሳ፣ በሌሎችም ሠርቻለሁ፡፡ እግዚአብሔር ምሕረቱን አውርዶ ወደ ሰላም የሚመራበትን መንገድ በእውነቱ እንዳሁኑ
ዓይነት ውጤት ቢገኝ በጣም ጥሩ ይሆናል፡፡ አዲሱ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በቅርቡ ይሆናሉ፡፡ አቶ ኃይለ
ማርያም ደሳለኝም የተቻላቸውን ያህል ሞክረዋል፡፡ ያጋጠመውንም ችግር እንደዚሁ ለሕዝብ እውነቱን ተናግሮ መልቀቅን የመሰለ ትልቅ
ነገር የለም፡፡ ችግሮች አሉ፣ ችግሮችን ለመፍታት በሰላም መመልከትና አብሮ መሥራት አብሮ መተማመን ያስፈልጋል፡፡
አገርን ከማጥ ውስጥ ለማውጣት መሞከር ተገቢ
ነው፡፡ ዴሞክራሲያዊ መብት ወይም ዴሞክራሲ በቃል ሳይሆን በሥራ በተግባር መሆን አለበት፡፡ አሁን ለምሳሌ የጀርመን ቻንስለር አንጌላ
መርኬል እዚህ መጥተው ፓርላማውን ለመጎብኘት ፕሮግራም ተይዞላቸው ነበር፡፡ እሳቸው ግን አይ ያለው የአንድ ፓርቲ ሲስተም ነው፤
ጠቅላይ ሚኒስትሩንና ፕሬዚዳንቱንም አይቼያለሁ፤ ፓርላማው ውስጥ ያለው የአንድ ፓርቲ መንግሥት ነውና ምኑ ነው የሚጎበኘው አሉ ይባላል፡፡
ወደፊት በከባድ መሥራትና የመተባበር ጊዜ እንደሚሆን ተስፋ አለኝ፡፡ በፖለቲካ ታስረው የነበሩት መፈታት የማሰሪያ
ማዕከሉ እንዲዘጋ መደረጉ ጥሩ ነው፡፡ በልማት በኩል እንደዚህ የታደሰ መንግሥት የለም፡፡ መሬትም ራሷ እየመሰከረች ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በእናንተ ዘመን ለካቢኔ አባልነት የሚታጩት እንዴት ነው? መስፈሪያው
ምንድነው?
ልዑል ራስ መንገሻ፡-
ጃንሆይ ይመርጣሉ፡፡ የፈለጉትን እዚያ ቦታ እዚህ ቦታ ያደርጋሉ፡፡ እገሌ ይሁን ማለት ብቻ አይደለም፤ ስትሾመው ግን የሚያስፈልገው
መሣሪያ መስጠት አለብህ፡፡ ምናልባት መሪ ሆኖ የኃላፊነት የመሪ ቁልፍ ሌላ ቦታ ከሆነ እሱ ተመሪ እንጂ መሪ አይደለም፡፡ እዚህ ላይ ተጣምሮ በመሪነት ያን ቦታ ኃላፊነትን
ወስዶ እንዲሠራ ሲደረግ ግን ምን ይሉኛል? የሚለው ነገር መኖር የለበትም፡፡ ስለዚህ የሚያሠራው ካለ፣ ቁልፍ ምናልባት ሌላ ዘንድ
ሆኖ እኔ ይኼንን አድርግ ይኼንን አታድርግ የሚለው ካለ ያ ያልታየ ኃይል የሚሠራው ማለት ነው፡፡ እሱ በስም ነው ተናገር የተባለውን
ይናገራል፣ ሥራ የተባለውን ይሠራል፡፡
ሪፖርተር፡-
ልዑልነትዎ በጠቅላይ ገዥነትና በሚኒስትር ቦታ ሁሉ ሠርቷል፡፡ ትልቅ
ስኬት ያሳዩበት ሥራ ሙሉ ድጋፍ ቢያገኝም የት በደረሱ ነበር ብለው ያሉ ሰዎች አሉ?
ልዑል ራስ መንገሻ፡-
የትም የሚያደርስ እግዚአብሔር ነው፡፡ ዋናው ዕድሉ ነው፡፡ ያቺ ዕድል ግን የተወሰነች ነች፡፡
No comments:
Post a Comment