Friday, February 2, 2018

ሐምሌና ጥቅምት ጥርና ኅዳር የሕገ መንግሥት ወራት

 የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት (ኢንነ) መንግሥት ዓርማ (1923-1967)

የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) መንግሥት ዓርማ (1980-1983)

    የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) መንግሥት ዓርማ (1988-)
ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967)
ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም (1980-1983)
አቶ መለስ ዜናዊ (1988-2004)


የኢትዮጵያ ዘውዳዊ መንግሥት የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት (1923-1967) ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ የመጀመርያውን ዘመናዊ ሕገ መንግሥት ሐሙስ ሐምሌ 16 ቀን 1923 ዓ.ም. ሲያወጡ፣ ከሩብ ምዕት ዓመት በኋላ ሐሙስ ጥቅምት 1948 ዓ.ም. እንዲከለስ አድርገዋል፡፡ የ1966 ዓ.ም. አብዮት ሲፈነዳ ያልተተገበረና በረቂቅነት የቀረ ‹‹የብሔረ ኢትዮጵያ›› ሕገ መንግሥትም ለውይይት ቀርቦ ነበር፡፡
ደርግ (የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት) መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. መንበረ መንግሥቱን ከተቆናጠጠ በኋላ ለ13 ዓመታት ያለ ሕገ መንግሥት በአዋጆች ብቻ አገርን ሲያስተዳድር ኖሯል፡፡ በመሪ ፓርቲው ኢሠፓ አማካይነትና በኢትዮጵያ ብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት አጋፋሪነት የተረቀቀው የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢሕዲሪ) ሕገ መንግሥት፣ በተለያዩ መድረኮች በአገር ውስጥና በባሕር ማዶ ውይይቶች ከተደረጉበት በኋላ በውሳኔ ሕዝብ (ሪፈረንደም) የጸደቀው፣ ከ31 ዓመት በፊት እሑድ ጥር 24 ቀን 1979 ዓ.ም. ነበር፡፡ በዐሥራ ሰባት ምዕራፎችና በ119 አንቀጾች የተደራጀው የሕገ መንግሥቱ ሰነድ በሥራ ላይ መዋል የጀመረው የካቲት 15 ቀን 1979 ዓ.ም. ሲሆን ኢሕዲሪም እውን የሆነው መስከረም 1 ቀን 1980 ዓ.ም. ነበር፡፡
ለአገሪቱ ሦስተኛ የሆነው የኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት ከአራት ዓመት በላይ ማለፍ አልቻለም፡፡ ኢሠፓ/ኢሕዲሪን ግንቦት 20 ቀን 1983 ዓ.ም. የፈነቀለው ኢሕአዴግ (የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር)፣ ባቋቋመው ጊዜያዊ መንግሥት በይቀጥላልም የሽግግር መንግሥት በነደፈው ቻርተር መሠረት፣ ለአራት ዓመት ካስተዳደረ በኋላ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ (ኢፌዴሪ) እውን የሆነበት ሕገ መንግሥት ሐሙስ ኅዳር 29 ቀን 1987 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች አማካይነት የፀደቀበት ነበር፡፡
ዘመናዊት ኢትዮጵያ ያሳለፈቻቸው አራቱ ሕግጋተ መንግሥት የሐምሌና ጥቅምት፤ የጥርና የኅዳር ትሩፋቶች ሲሆኑ፣ የኢሕዲሪ ሕገ መንግሥት በውሳኔ ሕዝብ [ሕዝበ ውሳኔ አይደለም] በእሑድ ዕለት ከመፅደቁ ውጪ፣ ሦስቱ ማለትም የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለቱና የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የፀደቁት በተመሳሳይ ዕለት ሐሙስ ነበር፡፡
-    ሔኖክ መደብር

No comments:

Post a Comment