ከአርባ ሦስት ዓመት በፊት ያረፉት የኢትዮጵያ
ዘውዳዊ ሥርዓት የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት (1923-1967) የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ስለነበሩ፣ ሉልና
ዘውድንም የጨበጡት በቤተ ክርስቲያን ሥርዓትም ስለነበረ ከቤተ ክርስቲያን በዓላት አልተለዩም፡፡ ይህም አልጋወራሽ ልሁል ራስ ተፈሪ
መኰንን ከሚባሉበት ዘመን አንሥቶ መሆኑ ነው፡፡
አልጋወራሹ ከነገሡም በኋላ እስከ ወረዱበት ድረስ
ከቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ በዓላት ሌሊትም ሆነ ቀን ተለይተው አያውቁም፡፡ ከነዚህም አንዱ በጥምቀት በዓል ከከተራው እስከ ቃና
ዘገሊላ በሦስቱ ቀናት ከቤተ ክርስቲያን እስከ ጃንሜዳ ታቦታቱን ከማጀብ አልተለዩም፡፡ አንዱ ማሳያ ይኼ ፎቶ ነው፡፡ ጥር 11 ቀን
1939 ዓ.ም. ጃንሜዳ ከመሳፍንቱ መኳንንቱ ጋር ሆነው በዓለ ጥምቀቱን ሲያከብሩ፣ እንዲሁም ከከብር ዘበኛ ሠራዊታቸው ጋር ሆነውም
ታቦታቱን ሲያጅቡ ይታያሉ፡፡
ይኼ ታሪክ ከተመዘገበ ከሰባት አሠርታት በኋላ
የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመን የሆኑት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እንደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁሉ ከቤተ ክርስቲያናቸው
በዓላት ልደት ሆነ ፋሲካ በሌሊቱ፣ ጥምቀትን በቀትሩ እየተገኙ ከማክበር ቸል ያሉበት ጊዜ የለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በሞስኮም
በዓለ ጥምቀቱ ጥር 11 ቀን ሲከበር በሩሲያ ኦርቶዶክስ ትውፊት መሠረት ከዜሮ በታች 6 ዲግሪ ሴንቲግሪድ በሆነ በረዷማ ቅዝቃዜ
ውስጥ እየጠለቁ ሲጠመቁ ታይተዋል፡፡
ሔኖክ መደብር
No comments:
Post a Comment