Tuesday, January 9, 2018

ካፒቴን ዓለማየሁ አበበ የመጀመርያው አፍሪካዊ ጄት አብራሪ (1916-2010)

በሔኖክ ያሬድ
በሃያኛው ክፍለ ዘመን የመጀመርያው ሩብ ኢትዮጵያ ከውጭው ዓለም ጋር በአየር ትራንስፖርት ለመገናኛት በር ከፋች አጋጣሚ የተፈጠረበት ነበር፡፡ በንግሥተ ነገሥት ዘውዲቱ ምኒልክ ዘመን፣ በልዑል አልጋ ወራሽ ንጉሥ ተፈሪ መኰንን አማካይነት በ1921 ዓ.ም. የመጀመርያው አውሮፕላን አዲስ አበባ መድረሱ ይወሳል፡፡ ከአውሮፕላን ጋር የተያያዘው ታሪክ እመርታ ማሳየት የጀመረው በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ሲሆን፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ታኅሳስ 12 ቀን 1938 ዓ.ም. ከተመሠረተ በኋላ የመጀመርያውን በረራ መጋቢት 30 ቀን 1938 ዓ.ም. ወደ ካይሮ በአስመራ በኩል አድርጓል፡፡
ከሰባት አሠርታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ አየር መንገድ በተለይ በ1950ዎቹና በ1960ዎቹ ወደ ጄት ዘመን ሲሸጋገር ከፋና ወጊ አብራሪዎች ተጠቃሹ ካፒቴን ዓለማየሁ አበበ ነበሩ፡፡ ከ55 ዓመት በፊት የመጀመርያው ቦይንግ 720B አውሮፕላን በካፒቴንነት ያበረሩት ካፒቴን ዓለማየሁ የመጀመርያው አፍሪካዊም አሰኝቷቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የሥራ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሊቀመንበር የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም እንደሚያስታውሱት፣ ቦይንግ ጄት ከአሜሪካ ሲያትል ከቦይንግ ፋብሪካ አውሮፕላኑን እንዲያመጡ የተደረጉት ካፒቴን ዓለማየሁ አበበና ካፒቴን አዳሙ መድኃኔ ነበሩ፡፡
ከስድሳ ዓመት በፊት በ1950 ዓ.ም. የመጀመርያውን የንግድ አውሮፕላን አዛዥ በመሆንና ብቻቸውን ዲሲ-3/ሲ47 አውሮፕላን በማብረር ነበር ካፒቴን ዓለማየሁ ዓቢይ ተግባራቸውን ማከናወን የጀመሩት፡፡
በ1952 ዓ.ም. አየር መንገዱ ወደ ጄት አውሮፕላኖች ለመግባት ሲዘጋጅና ቦይንግ 720B ለማስመጣት ሲወሰን መሠረታዊ መሥፈርቱን ለማሟላት የልደታ ኤርፖርት (ኦልድ ኤርፖርት) መለወጥ ነበረበት፡፡ በ1928 ዓ.ም. የተቋቋመው የልደታ ኦልድ ኤርፖርት ጄቶችን ለማሳረፍና ለማስተናገድ ምቹ ባለመሆኑ፣ አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ (ኤርፖርት) በሁለት ዓመት ውስጥ በቦሌ እንዲታነፅ ተደረገ፡፡ በኅዳር 1955 ዓ.ም. በካፒቴን ዓለማየሁ አበበና ካፒቴን አዳሙ መድኃኔ አማካይነት ጄት አውሮፕላኑ ገባ፡፡
የበረራ ትውስታ
ካፒቴን ዓለማየሁ ‹‹ሕይወቴ በምድርና በአየር›› በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ትውስታቸውን እንዲህ አስፍረዋል፡፡ ‹‹. . . የአብራሪነት ኃላፊነቱን ከተረከብኩ በኋላ አንዳንድ መንገደኞች አብራሪው ነጭ ባለመሆኑ ከሚያሳዩት መደናገጥ በቀር ምንም እንከን ሳያጋጥመኝ አየር መንገዱ በሚገለገልባቸው አፍሪካና አውሮፓ መብረር ጀመርኩ፡፡ በስልሳዎቹ አሠርታት መጀመርያ ላይ አብዛኛዎቹ የአፍሪካ አገሮች ከቅኝ ገዥዎች ቀንበር ነፃ ለመውጣት የሚታገሉበት ወቅት ስለነበር ጥቁር ፓይለት በሚያበረው ዘመናዊ ጄት ለመሳፈር እንኳን ለባዕዳን ለወገኖቻችንም ቢሆን መደናገጥን ፈጥሮ ነበር፡፡ ይኸው የመጀመርያ ዓለም አቀፍ በረራ አብቅቶ መሬት እንዳረፍን መንገደኞቹ ሲሰናበቱን ከልብ የመነጨ ምሥጋና ያቀርቡልን ነበር፡፡ አንዳንዶች ኢትዮጵያውያንማ ማመኑም እየቸገራቸው ሳይሆን አይቀርም በአድናቆት ይመለከቱንና ያነጋግሩን ነበር፡፡ በተከታታይ በረራዎች የመንገደኞቼ ሥጋትና ጥርጣሬ ወደ መተማመን ተለውጦ ባየሁትና በሰማሁት ቁጥር የሥራ ባልደረቦቼም ሆኑ እኔ ደስታ ይሰማን ነበር፡፡ በሥራ ውጤት እምነት ከማግኘት የበለጠ ምን ነገር ይኖራል? እርግጥ ነው ስንት ፈተና በትዕግሥት አልፌ ለዚያ ደረጃ እንደበቃሁ መንገደኞቼ አያውቁም ነበር፡፡ ቢያውቁስ ኑሮአፍሪካዊ ጄት ሲያበር ለመጀመርያ ጊዜ በማየታችሁ ለምን ትፈራላችሁ? ለምንስ ትጠራጠራላችሁ?› ብሎ መጠየቅስ ይቻል ነበር? በእኔ ላይ የደረሰው ዓይነት በተከታዮቹ አብራሪዎች ላይም ደርሶ እነሱም በትዕግሥትና በጽናት አልፈውታል፡፡››
የአየር ኃይሉ ዓለማየሁ አበበ
ካፒቴን ዓለማየሁ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ለመቀላቀል የቻሉት በኢትዮጵያ አየር ኃይል በኩል በማለፍ ነው፡፡ በከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸው ለከፍተኛ ውጤት የበቁ ተማሪዎች ወደ አቪዬሽን ትምህርት እንዲገቡ ሲደረግ የዕድሉ ተጠቃሚ ነበሩ፡፡ ገጸ ታሪካቸው እንደሚያመለክተው በአየር በነበራቸው የሥልጠና ጊዜ ከስዊድን የበረራ አሠልጣኞች የቀሰሙትን ሙያ በመጠቀም የመጀመርያውን የብቻ በረራ በ1938 ዓ.ም. ለማድረግ ችለዋል፡፡ በዚያው ዓመት ለተጨማሪ የበረራ ትምህርት ስዊድን በመሄድ በዓመቱ አጠናቀው ተመልሰዋል፡፡ ከስዊድን መልስም በደብረ ዘይት (ቢሾፍቱ) ከተማ በሚገኘው የአየር ኃይል ውስጥ በምክትል መቶ አለቃነት ማዕረግ የበረራ ክንፍ (ዊንግ) አግኝተዋል፡፡
በ1943 ዓ.ም. ከአየር ኃይል ወደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ ምርጥ የሆኑ አብራሪዎች እንዲዛወሩ በተወሰነው መሠረት፣ ከተመራጮቹ አንዱ የነበሩት ካፒቴን ዓለማየሁ ናቸው፡፡ ከሦስት አሠርታት የአገልግሎት ዘመናቸውም ከ1948 እስከ 1960 ዓ.ም. ከመጀመርያ የበረራ መኰንንነት እስከ ካፒቴንነት፣ ከመጀመርያው የቦይንግ 720B ጄት ካፒቴንነት እስከ አየር መንገዱ የበረራ ዘርፍ ምክትልና ዋና ኃላፊነት ሠርተዋል፡፡ ከ1961 እስከ 1972 ዓ.ም. ድረስ የኢንተርናሽናል በረራዎች ዳይሬክተር፣ የበረራ ኦፕሬሽን ረዳት ጄኔራል ማኔጀር ሆነው ሲሠሩ፣ በ1968 ዓ.ም. የመጀመርያው አፍሪካዊ የቦይንግ 707 ጄት ካፒቴን ሆነው ሲሾሙ፣ በ1972 የጄት ካፒቴኖች ፈታኝ በመሆን አገልግለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራ አገልግሎታቸውን በ1974 ዓ.ም. ፈጽመው ከተሰናበቱ በኋላ፣ በኡጋንዳና በየመን አየር መንገዶች ውስጥ በአሠልጣኝነትና በአማካሪነት ለአምስት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ የበረራ ምዕራፋቸውን ቋጭተዋል፡፡
ከአባታቸው ከአቶ አበበ ደስታና ከእናታቸው ከወ/ሮ ጥሩነሽ ጎበና በቀድሞ የሐረር ጠቅላይ ግዛት ጨርጨር አውራጃ የካቲት 16 ቀን 1916 ዓ.ም. የተወለዱት ካፒቴን ዓለማየሁ፣ በሐረር ራስ መኰንን ትምህርት ቤት በአማርኛና በፈረንሣይኛ የሚሰጠውን የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት የተከታተሉ ሲሆን፣ ቀሪውን የአንደኛና መካከለኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በካቶሊክ ሚሲዮን አጠናቀዋል፡፡
በጣሊያን ወረራ (1928-1933) ምክንያት ትምህርታቸውን በማቋረጥ በፖስታ ቤት ተቀጥረው ጣሊያን እስከወጣበት ጊዜ ድረስ ቆይተዋል፡፡ ከድል በኋላ በአዲስ አበባ በቀድሞው የባላባት በኋላም መድኃኔ ዓለም ትምህርት ቤት ገብተው ያቋረጡትን ትምህርት በመቀጠል፣ የሁለተኛ ደረጃ በኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል፡፡ ባስመዘገቡት ከፍተኛ ውጤትም ከንጉሠ ነገሥቱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ እጅ ሽልማት ተቀብለዋል፡፡
በሦስቱ መንግሥታት ዘመን በከፍተኛ የአገርና የሙያ ፍቅር አገራቸውን ያገለገሉት ካፒቴን ዓለማየሁ፣ ባለትዳርና የአራት ሴቶችና የአራት ወንዶች ልጆች አባት፣ እንዲሁም የአራት የልጅ ልጆች አያት ነበሩ፡፡ ዕውቅትና ልምድን ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በማሰብ በ1997 ዓ.ም. ‹‹ሕይወቴ በምድርና በአየር›› የሚል መጽሐፍም አሳትመዋል፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በሕክምና ሲረዱ የቆዩት ካፒቴን ዓለማየሁ፣ ታኅሳስ 26 ቀን 2010 ዓ.ም. በተወለዱ በ94 ዓመታቸው አርፈው ታኅሳስ 28 ቀን በጴጥሮስ ወጳውሎስ የካቶሊክ መካነ መቃብር ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡
በኢትዮጵያ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ሊቀ ጳጳሳት ብፁዕ ካርዲናል አቡነ ብርሃነየሱስ መሪነት በለገሀር መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን ጸሎት ፍትሐት ሲከናወን፣ ከወዳጅ ዘመድ ውጪ በቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ በሥርዓተ ቀብሩ የመንግሥት ከፍተኛ ሹማምንትም ሆኑ የአየር መንገዱ ከፍተኛ ኃላፊዎች አለመገኘታቸው ታይቷል፡፡
በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት የሥራ ሚኒስትርና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ቦርድ ሊቀመንበር የነበሩት ልዑል ራስ መንገሻ ሥዩም፣ ልዕልት ሳራ ግዛው፣ ልዑል በዕደ ማርያም መኰንን ኃይለ ሥላሴ የመጀመርያው ኢትዮጵያዊ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስኪያጅ ኮሎኔል ስምረት መድኃኔ በሥርዓተ ቀብሩ ተገኝተዋል፡፡
ከኢትዮጵያ አየር ኃይል እስከ አየር መንገድ ለአፍሪካም ጭምር ያኮሩ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ሥርዓተ ቀብር በክብር ዘብና በማርሽ ባንድ አለመፈጸሙም ቅሬታ አሳድሯል፡፡
No comments:

Post a Comment