Friday, January 26, 2018

በመስቀል በዓል የዩኔስኮ ምዝገባ የተፈጠረው ‹‹ስህተት›› በጥምቀቱም ላለመድገም


በሔኖክ ያሬድ
መሰንበቻውን የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት ከሳቡ በዓላት አንዱ ዓመታዊው የጥምቀት በዓል ነው፡፡ በኢትዮጵያ በአደባባይ ከሚከበሩት በአውራነትም ይጠቀሳል፡፡ ሃይማኖት ከባህል ጋር የነበረውና ያለው የሚኖረው ቁርኝት አሳይነቱም ይጎላል፡፡ ድንበርን አልፎ ባሕርን ተሻግሮ ባዕዶችን ጭምር የማረከ መሆኑም ሌላው ገጽታው ነው፡፡
የኢትዮጵያን ሃይማኖታዊና ባህላዊ ትውፊቶችን መሠረት አድርጎ ከትውልድ ወደ ትውልድ እየተላለፈ የመጣው የጥምቀት ክብረ በዓል ማኅበራዊ አንድነትን፣ መስተጋብርንና ብዝኃነትን በመላ አገሪቱ ያስተሳሰረ መሆኑ ይነገርለታል፡፡ ይህም ገጽታው ነው በመንግሥታቱ ድርጅት የባህል ክንፍ ዩኔስኮ በማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስና ወካይ መዝገብ ውስጥ የመግባት ዕድሉ ከፍተኛ ነው የሚያሰኘው፡፡
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ጉባዔ በ1996 ዓ.ም. የፀደቀውን የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ጥበቃ ስምምነትን በየካቲት 1998 ዓ.ም. ከፈረመች በኋላ ነው ለዘርፉ ትኩረት መስጠት የጀመረው፡፡ በዩኔስኮ መዝገብ በሚዳሰሱ ቅርሶች ብቻ ትታወቅ ከነበረችበት አልፋ የማይዳሰሰውን ባህላዊ ቅርስ ለማስመዝገብ የቻለችው ስምምነቱን በፈረመች በስምንት ዓመቷ የመስቀል በዓልን በዓለም ወካይ ቅርስ መዝገብ ውስጥ ማስገባቷ ነው፡፡
 በተከታታይ ዓመታትም የፊቼ ጫምባላላና የገዳ ሥርዓት በመመዝገባቸው ቁጥሩን ወደ ሦስት አድርሶታል፡፡
በዓለም አቀፍ የፌስቲቫሎች መድበል ‹‹የአፍሪካ ኤጲፋንያ›› (The African Epiphany) እየተባለ የሚሞካሸው፣ ከአገሬው ባለፈ የውጭ ቱሪስቶች እየመጡ የሚያደንቁት፣ አንዳንዶችም ‹‹በዓለም ወካይ ቅርስ ውስጥ ጥምቀትን ለምን በቅርስነት አላስመዘገባችሁትም?›› እየተባለ የተጠየቀለት በዓለ ጥምቀት እስካሁን ለዩኔስኮ ‹‹ወግ ማዕረግ›› ለመብቃት አልታደለም፡፡
በዓሉ በ2006 ዓ.ም. በተለይ በአዲስ አበባና በጎንደር ሲከበር የቤተክህነትም ሆነ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሮችን ጨምሮ ከፍተኛ ሹማምንት ‹‹ክብረ በዓሉን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየሠራን ነው›› ሲሉ በቴሌቪዥን መስኮት፣ በሬዲዮ ሞገድ መደመጣቸው ይታወሳል፡፡ ከዜና ፍጆታ ባለፈ ተጨባጭ እንቅስቃሴ ከተጀመረ ግን ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የመንፈቀ ዓመቱን አፈጻጸም ሪፖርቱን ባለፈው ታኅሣሥ ለፓርላማው ባቀረበበት ወቅት፣ በጥምቀት ክብረ በዓል ላይ እየተሠራ ያለው ሥራ 70 ከመቶ መጠናቀቁን መግለጹ ይታወቃል፡፡
ይህም ሆኖ የፎክሎርም ሆነ የአንትሮፖሎጂ ባለሙያዎች እንደሚገልጹት፣ የጥምቀት በዓል እንደ መስቀል በዓል ሁሉ በዩኔስኮ ወካይ ቅርስ መዝገብ ውስጥ ለመስፈር የሚያዳግተው አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ ለዩኔስኮ የሚቀርበው ሰነድ በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ጥናት መደረግ እንዳለበት ሳይጠቅሱ አያልፉም፡፡ እዚህ ላይ ለዕውቀት ክፍተት ማሳያነት በዩኔስኮ የመስቀል ክብረ በዓል አመዘጋገብ ላይ የተከሰተው ይነሳል፡፡
በዩኔስኮ የመስቀል በዓል ቀን ተብሎ የተመዘገበው የቱ ነው?
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት መሠረት የመስቀል በዓል በየዓመቱ የሚከበረው መስከረም 17 ቀን (በግብፅ ኮፕቲክ ካሌንደር ቲቶ 17 ቀን) እንደ ጎርጎርዮሳዊ ዘመን አቆጣጠር ደግሞ ሴብቴምበር 27 ቀን ነው፡፡
ይህ በቤተ ክርስቲያኒቱም ሆነ በውጭ ባሉም መዝገቦች ይታወቃል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ትውፊት የመስቀል በዓል ዋዜማው ደመራ ይባላል፡፡ መሠረቱ ይህ ሆኖ ሳለ ግን የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ክብረ በዓሉን በ2006 ዓ.ም. በዩኔስኮ ውሳኔ ሲያስመዘግብ በዋናነት የተጠቀሰው ቀን ‹‹ሴብቴምበር 26›› ተብሎ መስፈሩ ነው ስህተቱ፡፡ በዩኔስኮ ድረ ገጽ የተመለከተው ‹‹The Festival of Maskel is Celebrated across Ethiopia on the 26th of September to commemorate the unearthing of Truth Holy Cross of Christ›› በማለት ነበር፡፡
በግርድፉ ሲተረጎም የመስቀል ክብረ በዓል በመላ ኢትዮጵያ ሴብቴምበር 26 ቀን [ማለትም መስከረም 16 ቀን] ይከበራል ይሆናል፡፡
የመስቀል ዋዜማው መስከረም 16 ቀን አዲስ አበባን በመሰሉ ከተሞች ምሽት ላይ ደመራ የሚለኮስበት እንጂ የመስቀሉ በዓል መስከረም 17 ቀን ነው፡፡ በሰሜን፣ በሰሜን ምዕራብና ሰሜን ምሥራቅ አካባቢዎች ደግሞ የመስቀል ደመራው የሚለኮሰው በዕለቱ (17) ንጋትና ረፋድ ላይ ነው፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በባሕረ ሐሳቧ መሠረት ሁለት ዓይነት አቆጣጠር አላት፡፡ አንደኛው ፀሐያዊ ቀን (Solar day) ሲሆን፣ ሁለተኛው ሊጡሪጊያዊ ቀን (Liturgical day) ከጨረቃ ጋር የሚያያዘው ነው፡፡ በሊጡሪያጊያዊ ቀን ዕለቱ የሚጀመረው በዋዜማው ከ12 ሰዓት ምሽት በኋላ ነው፡፡ ኦሪቱ እንደሚለው ‹‹ማታም ሆነ ጠዋትም ሆነ አንደኛ ቀን›› ሲል፣ የመስከረም 17 መነሻው መስከረም 16 ማታ ሆኖ ከመስከረም 17 እስከ ማታ 24 ሰዓቱ ይሞላል፡፡ በሊጡሪጊያዊ ቀን ስሌት መሠረት በሁሉም የኢትዮጵያ አካባቢዎች የመስቀል ደመራው የሚለኮሰው ‹‹መስከረም 17 ቀን›› ነው፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ መስከረም 16 ቀን ማታ ሲለኮስ ‹‹በመስከረም 17›› የመጀመርያ ክፍል የሌሊቱ ሰዓት ላይ ሲሆን፣ በጎንደር መስከረም 17 ቀን ረፋድ ላይ የሚለኮሰው ‹‹በመስከረም 17›› ሁለተኛው ክፍል የመዓልቱ (የቀኑ) ብርሃን ላይ ነው፡፡
ይህ በቅጡ ባለመታወቁ፣ የማስመዝገቢያው ሰነድ ሲዘጋጅ ባሕረ ሐሳቡን ማዕከል ባለመድረጉና በዕውቀት ላይ ባለመመሥረቱ በዓሉ ‹‹ሴብቴምበር 26 ቀን በመላ ኢትዮጵያ ይከበራል›› ተባለ፡፡ እንዲህ ዓይነት ክፍተት በጥምቀት በዓል ምዝገባ ላይ እንዳይፈጠር ትኩረት መስጠት ያስፈልጋል፡፡
የጥምቀት ክብረ በዓል
በየዓመቱ ጥር 11 ቀን (ጃንዋሪ 19 ቀን) የሚከበረው የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ የጥምቀት በዓል ዋዜማውን ከተራ ጥር 10 ቀን፣ ማግስቱን ጥር 12 እና 13 ቀን አማክሎ የያዘ መሆኑ ሊቃውንት ይገልጻሉ፣ መጻሕፍት ያመለክታሉ፡፡
በዓሉ ‹‹Commemoration of Jesus Christ’s baptism in river Jordan›› (የእግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ የተጠመቀበት መታሰቢያ በዓል) ከሚባለው በተጨማሪ ‹‹Ethiopian Orthodox Celebration of Epiphany›› የአስተርእዮ፣ የመገለጥ በዓል በመባልም ይታወቃል፡፡የሁለቱ ስያሜዎች ምንነትና ይዘት በቅጡ መገለጽ አለበት፡፡ ዕለተ ጥምቀት ጥር 11 ቀን ሆኖ ኤጲፋንያ (አስተርእዮ) ከበዓለ ጥምቀቱ እስከ ጸመ ነነዌ መያዣ ዋዜማ ድረስ የሚያጠቃልል እንደሆነ ይገለጻል፡፡ የምር ምሁራንን ማነጋገር ከሰሞነኛም መጠበቅ ያስፈልጋል፡፡
አንዱ ማሳያ ባለሥልጣኑ በአማራ ክልል በሠራው የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ኢንቬንቶሪ የታየው ተጠቃሽ ነው፡፡ በተለይ በሰሜን ወሎ ዞን በላስታ ላሊበላና አካባቢ ስላለው የጥምቀት በዓል አከባበር በ2009 ዓ.ም. ያሳተመው መድበል ላይ  የሚታይ ክፍተት አለ፡፡ ስለ ቅርሱ ምንነት ማብራሪያ ሲሰጥ ‹‹የተለያዩ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ጥምቀት የሚለው ቃል በግእዝ አስተርእዮ፣ በአማርኛ መጠመቅ፣ መገለጥ (መታየት) እንደማለት ነው፤›› ይላል፡፡
ስለሆነም የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ሙያተኞች ከስያሜ፣ ከይዘትና ከበዓሉ ዕለታት ጋር በተያያዘ ክፍተትም ሆነ ስህተት እንዳይፈጠር ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
የኢትዮጵያን የጥምቀት በዓል አከባበር ልዩ ገጽታ ከላሊበላ እስከ ጎንደር፣ ከአክሱም እስከ ዝዋይ ተነቅሶ በሰነዱ ውስጥ ማካተት አስፈላጊነት አለው፡፡ ክርስቶስ ኢየሱስ ከ1979 ዓመታት በፊት የተጠመቀበት ዕለትና ዓመት ልዩ በሆነው የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር (ባሕረ ሐሳብ) መሠረት መቼ እንደሆነ መገለጽ አለበት፡፡ ይህም ጥር 11 ቀን 31 ዓ.ም. (2010-31=1979)፣ 5531 ዓመተ ዓለም (በስድስተኛው ሺሕ) መሆኑን፣ እግረ መንገዱንም የዘመን ቀመሩን ማሳየት ያሻል፡፡
የዘንድሮ በዓል በተለይ በአዲስ አበባ፣ በጎንደርና በመለ ሲከበር በተለያዩ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን አግኝቷል፡፡ ከጎንደር ሲተላለፍ አንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ ሊቅ በዓሉ ‹‹1980ኛ ዓመት›› መሆኑን ሲናገሩ ተደምጠዋል፡፡ ይህን የሰማ የኢቢሲ ጋዜጠኛ ስለ በዓሉ ሲዘግብ ‹‹በጎንደር ለ1980ኛ ጊዜ›› መከበሩን አስተላልፎ ነበር፡፡ የጥምቀትን አከባበር ለመሰነድ ወደ ጎንደር ያቀናው የባለሙያዎች ቡድን ለዚህ ስህተት ጆሮ እንደማይሰጥ ይታመናል፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የገዳ ሥርዓትን በዩኔስኮ ለማሰመዝገብ ሰነዶቹን ከመላኩ በፊት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ዕውቀት ተኮር ምክክር እንዳደረገው ሁሉ፣ ስለ ጥምቀት ክብረ በዓል የተሰነዱት ጓዞች ወደ ዩኔስኮ ከመላካቸው በፊት ለምክክር መድረክ እንደሚያቀርበው ይጠበቃል፡፡

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ቭላድሚር ፑቲን በ70 ዓመታት ውስጥ


ከአርባ ሦስት ዓመት በፊት ያረፉት የኢትዮጵያ ዘውዳዊ ሥርዓት የመጨረሻው ንጉሠ ነገሥት (1923-1967) የነበሩት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ኦርቶዶክሳዊ ክርስቲያን ስለነበሩ፣ ሉልና ዘውድንም የጨበጡት በቤተ ክርስቲያን ሥርዓትም ስለነበረ ከቤተ ክርስቲያን በዓላት አልተለዩም፡፡ ይህም አልጋወራሽ ልሁል ራስ ተፈሪ መኰንን ከሚባሉበት ዘመን አንሥቶ መሆኑ ነው፡፡
አልጋወራሹ ከነገሡም በኋላ እስከ ወረዱበት ድረስ ከቤተ ክርስቲያን ልዩ ልዩ በዓላት ሌሊትም ሆነ ቀን ተለይተው አያውቁም፡፡ ከነዚህም አንዱ በጥምቀት በዓል ከከተራው እስከ ቃና ዘገሊላ በሦስቱ ቀናት ከቤተ ክርስቲያን እስከ ጃንሜዳ ታቦታቱን ከማጀብ አልተለዩም፡፡ አንዱ ማሳያ ይኼ ፎቶ ነው፡፡ ጥር 11 ቀን 1939 ዓ.ም. ጃንሜዳ ከመሳፍንቱ መኳንንቱ ጋር ሆነው በዓለ ጥምቀቱን ሲያከብሩ፣ እንዲሁም ከከብር ዘበኛ ሠራዊታቸው ጋር ሆነውም ታቦታቱን ሲያጅቡ ይታያሉ፡፡
ይኼ ታሪክ ከተመዘገበ ከሰባት አሠርታት በኋላ የሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምዕመን የሆኑት ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን እንደ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁሉ ከቤተ ክርስቲያናቸው በዓላት ልደት ሆነ ፋሲካ በሌሊቱ፣ ጥምቀትን በቀትሩ እየተገኙ ከማክበር ቸል ያሉበት ጊዜ የለም፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በሞስኮም በዓለ ጥምቀቱ ጥር 11 ቀን ሲከበር በሩሲያ ኦርቶዶክስ ትውፊት መሠረት ከዜሮ በታች 6 ዲግሪ ሴንቲግሪድ በሆነ በረዷማ ቅዝቃዜ ውስጥ እየጠለቁ ሲጠመቁ ታይተዋል፡፡
ሔኖክ መደብር

ነጋሪት ያጀበው በዓለ ጥምቀት
‹‹አታሞውን ምታው
አርገው ደምቧ ደምቧ
እንደወለደች ላም
አታሰኘው እምቧ፡፡›› ይባላል ለበዓል ክብር፣ ለክተት ስሪት ነጋሪት፣ አታሞ ሲመታ:: መቺውን ለማትጋት የሚወረወር ቃል ነው፡፡ የዘንድሮው የጥምቀት በዓል በአዲስ አበባ ጥር 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲከበር ከባሕረ ጥምቀት አንዱ በነበረው ጃንሜዳ በአራት ኪሎ በኩል ወደየአጥቢያቸው ያለፉትን የመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ፣ የታዕካ ነገሥት በዓታ ለማርያምና የመንበረ መንግሥት ቅዱስ ገብርኤል ታቦተ ሕግ በታላቅ አጀብ ከዘለቁት ምዕመናን ጋር ከተሰለፉት ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች አንዱ ነጋሪት ሲሆን፣ ሌሎቹ እነ በገና፣ እምቢልታ፣ አታሞ፣ ጥሩምባ ወዘተ
በዐውደ ጉዞው ታይተዋል፡፡


ሔኖክ መደብር

የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ የማስመዝገብ ማመልከቻ ‹‹በመጋቢት›› ይገባል

 

21 January 2018 (ጥር 13, 2010)
በወርኃ ጥር የኢትዮጵያ አደባባዮች በበዓላት ደምቀው ይታዩበታል ከሚያሰኘው አንዱ የጥምቀት በዓል የሚከበርበት መሆኑ ነው፡፡ የውጭ ጸሐፍት ‹‹የአፍሪካው ኤጲፋኒያ›› (African Epiphany) በመባል በልዩ ልዩ ድርሳኖች የሚታወቀው የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት) በሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ (Representative List of Intangible Cultural Heritage of Humanity)  የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በይፋ እንቅስቃሴ ከጀመረ ከርሟል፡፡
ዓመታዊው ክብረ በዓል በአገሪቱና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን (ዘኦርቶዶክስ ተዋሕዶ) በምትገኝበት የዓለም ክፍሎች የዋዜማውን ከተራ ጨምሮ ጥር 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ተከብሯል፡፡ በማግስቱም የቃና ዘገሊላ በዓልም እንዲሁ ተከብሯል፡፡ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በቅርቡ ለፓርላማው ባቀረበው የመንፈቅ ዓመቱ የአፈጻጸም ሪፖርቱ የሦስት ቀናት በዓል የሆነውን በዓለ ጥምቀትን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ቅድመ ዝግጅቱ እየተገባደደ መሆኑንና እስከ ኅዳር መገባደጃ ድረስ 70 በመቶ መጠናቀቁን ገልጿል፡፡
ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከተው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የባህል አንትሮፖሊጂስቱ አቶ ገዛኸኝ ግርማ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ሥራው ከሞላ ጎደል መጠናቀቁና አንዳንድ ቀሪ ነገሮች ቢኖሩም ሁሉም ነገር በሁለት ወር ውስጥ ተጠናቆ በዩኔስኮ ቀነ ገደብ መሠረት ከመጋቢት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. በፊት ማመልከቻው ይላካል፡፡
ዋዜማውን ከተራ (ጥር 10) እና ማግስቱን (ጥር 12) ቃና ዘገሊላን ይዞ በዓለ ጥምቀት በልዩ ድምቀት ከሚከበርባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነውና ጎንደር ከተመሠረተችበት ከ17ኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በልዩ አገባብ እየተከበረ ያለውን ሒደት ለመሰነድ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባለሙያዎች ቡድን እንደ ዓምናው ሁሉ ዘንድሮም በአቶ ገዛኸኝ መሪነት ቀሪ ሥራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡
የጥምቀት በዓልን ለማስመዝገብ ከባለሥልጣኑ ጋር ተባብረው እየሠሩ መሆኑን የሚገልጹት በመንበረ ፓትርያርክ የቅርስ ጥበቃና የቤተ መጻሕፍት የሙዚየም መምሪያ ኃላፊው መልአከ ሰላም ሰሎሞን ቶልቻ ናቸው፡፡ አንዱ መሥፈርት የይመዝገብልን ፊርማ በመሆኑ የምዕመናንና የካህናት ፊርማ ከነማመልከቻው ተያይዞ መቅረቡን ኃላፊው አስረድተዋል፡፡
መልአከ ሰላም ሰሎሞን የክብረ በዓሉን አንድምታ እንዲህ ይገልጹታል፡-  ‹‹ብዙ በዓላት አሉን፤ ጥምቀት የሚለይበት ከሃይማኖታዊ መሠረትነቱ ባሻገር የአደባባይ በዓል መሆኑ ነው፡፡ ሕፃንና አዋቂ፣ ሽማግሌም ደካማውና ብርቱው የሚታይበት ሃይማኖታዊና ባህላዊ መገለጫዎቹም ለየት ያሉ ናቸው፡፡ ከማኅበረሰቡ ጋር የሚያስተሳስሩ፣ የኢትዮጵያዊነት ወዝ ያላቸው፣ ጠቀሜታቸው የጎላና እኛነታችንን የሚገልጹ ብዙ ባህሎች አሉበት፡፡ በሃይማኖታዊነቱ የጌታ መጠመቅ ለአኛ አርአያ የሆነ ጌታችን ኢየሱስ መጠመቁን የምናይበት ትልቁ በዓላችን ነው፡፡ ለክርስትና ሕይወት የጥምቀት በዓል መሠረታዊ በዓል ነው፡፡ ››
የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ የዓለም ቅርስነት ማስመዝገብ ከበዓሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች ውስጥ አንዱ ነው የሚሉት አቶ ወርቁ፤ መረጃዎች የማሰባሰብና ለመዝጋቢ አካላት ባህሉን የማሳየት ብሎም የማሳመን ሥራዎች በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በኩል ከፍተኛ ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ ይጠቁማሉ፡፡
በጎንደር ከሚሰነደው አከባበር በተጨማሪ በጠቅላይ ቤተክህነትና በሌሎችም አማካይነት የአኩስምን የንግሥት ሳባ መዋኛ ማይ ሹም፤ የላስታ ላሊበላን፣  የአዲስ አበባ ጃንሜዳን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በየባሕረ ጥምቀቱ የሚኖረውን ሥርዓት ስነዳ ይከናወናል፡፡ የማስመረጫ ሰነዱ ለዩኔስኮ የሚላክ ሲሆን፣ እ.ኤ.አ. ለ2019 በዕጩነት ለማቅረብ እስከ መጋቢት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. ሰነዱን አሟልቶ መላክ ይጠበቃል፡፡
በዓለ ጥምቀቱ ሲገለጽ
በኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ጥር 11 ቀን 31 ዓ.ም. (5531 ዓመተ ዓለም) በአጥማቂው ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውስ ነው፡፡ ‹‹ኤጲፋንያ›› በመባልም ይታወቃል፡፡ ጥር 10 ቀን በከተራ፣ በገጠርም ሆነ በከተማ ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወደየባሕረ ጥምቀቱ የሚያደርጉት ጉዞና መንፈሳዊ አዳር በማግስቱ የጥምቀት ዕለት ‹‹ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ›› ሰማያዊው በመሬታዊው እጅ ተጠመቀን ይዞ የሚኖረው ያሬዳዊ ዝማሬ የበዓሉ ገጽታ ነው፡፡
ሥዕላዊ ከሆነው ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ አከባበሩ በተጓዳኝም ባህላዊ ገጽታው ይታያል፡፡ ወጣቶች የሚተጫጩበት የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት አጋጣሚዎችን ከመፍጠሩም ባለፈ በከተማም ሆነ በገጠር ሰውን የሚያገናኝ ድልድይ ነው፡፡
በየዓመቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው፣ በየባሕረ ጥምቀቱ የሚከበሩ በመሆናቸው፣ አገሬውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብነትን በመጎናጸፉ፣ ቱሪስቶችን እንደሳበ ነው፡፡ ከአዲስ አበባ እስከ ላሊበላ፣ ከአክሱም እስከ ጎንደር፣ ከሐዋሳ እስከ ጅማ፣ ከአሶሳ እስከ ጋምቤላ በሁሉም ሥፍራዎች በዚሁ ዓይነት ደምቆ ይከበራል። የምእመናኑም ሆነ የካህናትና ዲያቆናት አለባበስ  በሚማርኩ ባህላዊ አልባሳት የተዋበ በመሆኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሁልጊዜ አዲስ ነው።
ከሃይማኖታዊው ሥነ ሥርዓት በኋላ ካህኑ በሃሌታ፣ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ እንደያመጣጣቸው ወደየአጥቢያቸው ይመለሳሉ።
ሊቃውንቱ እንደሚናገሩት፣ ዘመነ አስተርእዮ የሚባለው፣ ከጥር 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ (ለዘንድሮ እስከ ጥር 21 ቀን 2010 ዓ.ም.) ያለው ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ ‹‹አምላክ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡ፣ በዮርዳኖስ በተጠመቀ ጊዜ የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር መታወቁ፣ በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሠርግ ላይ የመጀመሪያው ተዐምር በመፈጸሙ፣ አምላካዊ ኃይሉ መገለጡ›› እየታሰበ ምስጋና ይቀርባል። ይህ ኩነት ኢትዮጵያ ብሂልን ከባህል ጋር አዛምዳ ከሌላው የክርስቲያን ዓለም በተለየ አከባበር በዓሉን ማክበሯ፣ አያሌ ቱሪስቶችን ለመሳብ አስችሏታል።
ያኔ የሎሚ ውርወራው፣ የከተራው ሽልምልም ዱላ አሁን አሁን በከፊል ሎሚው ወደ ፕሪም፣ ሽልምልሙ ዱላ ወደ ረዥም ቄጠማ (ጨፌ ላይ የሚበቅል) ተለውጦ መታየቱ፣ ከባህላዊ ጭፈራው በተጓዳኝ ወጣቱ በአመዛኙ ከመንፈሳዊ ማኅበራት (ሰንበት ትምህርት ቤቶች) መዘምራን ጋር ወደ ዝማሬ አዘንብሏል፡፡
በዓለም አቀፍ የፌስቲቫሎች መድበል የአፍሪካ ኤጲፋኒያ/ጥምቀት (The African Epiphany) እየተባለ የጎንደሩ፣ የላሊበላው፣ የአዲስ አበባው… የጥምቀት አከባበር በዓለም የክብረ በዓላት (Festivals) ድርሳን ላይ በየጊዜው የሚተዋወቀው፣ ቱሪስቶችም እየመጡ የሚያደንቁት አንዳንዶችም ‹‹ጥምቀትን ለምን በቅርስነት አላስመዘገባችሁም?›› እያሉ ሠርክ መጠየቃቸው አልቀረም፡፡  የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ከሁለት ዓመት ወዲህ ትኩረት ሰጥቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡
የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ በግዙፍ ቅርስነት ከተመዘገቡት ከአክሱም፣ ላሊበላ የጎንደሩ ፋሲል ግቢ ጋር በጥብቅ ተሳስሮ የሚከበር የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ መሆኑ፣ እንዲሁም በዓሉ ከ1,500 ዓመታት በላይ በተከታታይ የአገሪቱ ትውልዶችና ሥልጣኔዎች እየተከበረ ያለ ሕያው ቅርስ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በዓሉ መቼ ይመዘገብ ይሆን?
ኢትዮጵያ እስካሁን ሦስት የማይዳሰሱ ቅርሶቿን (የመስቀል በዓል፣ ፊቼ ጫምባላላና የገዳ ሥርዓት) በዩኔስኮ አስመዝግባለች፡፡ የገዳ ሥርዓት በኅዳር 2009 ዓ.ም. አዲስ አበባ በተደረገው የዩኔስኮ ጉባኤ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡
ዓምና ስምንት የአፍሪካ አገሮች አልጀሪያ፣ ማላዊ፣ ቦትስዋና፣ አይቮሪኮስት፣ ግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያና ሞሪሸስ ለዩኔስኮ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርሶቻቸው እንዲመዘገቡላቸው ቢያመለክቱም ዕድሉን ያገኙት ማላዊ፣ ኒስማ (Nsima, culinary tradition of Malawi) በሚባለው ባህላዊ ምግቧ፤ ሞሪሸስ ሙዚቃ፣ ዳንኪራና ዝማሬን ባካተተው ‹‹ሰጋ ታምቡር›› (Sega Tambour) በሚባለው ባህላዊ ሙዚቃዋ፤ አይቮሪኮስት ዛዑሊ በሚባለው የጉሮ ማኅበረሰብ ባህላዊ ሙዚቃና ዳንኪራ (Zaouli, popular music and dance of the Guro communities in Côte d’Ivoire) አማካይነት መሆኑን የዩኔስኮ ድረ ገጽ ያሳያል፡፡
ኢትዮጵያ ለመወዳደር ያለፏትን ተከታታይ ዓመታት ዳግም እንዳያልፋት የምታደርገው የጥምቀት በዓልን እንዲመዘገብ የሚያስችለውን የማስመዝገቢያ ሰነዷን አዘጋጅታ እስከ መጋቢት 22 ቀን 2010 ዓ.ም. (ማርች 31 ቀን 2018) በፓሪስ ሰዓት አቆጣጠር እስከ እኩለ ሌሊት ስትልክ ብቻ ነው፡፡Friday, January 12, 2018

ልሂቁ ሐኪም ፕሮፌሰር እደማርያም ጸጋ (1929 - 2010)

በሔኖክ ያሬድ
በኢትዮጵያ የዘመናዊ ሕክምና ታሪክ ሉዓላዊ ሥፍራ ከሚሰጣቸው ጠበብት ሐኪሞች አንዱ ነበሩ፡፡ የማከም ጸጋ፣ የማስተማር ክሂል የተጎናፀፉት ፕሮፌሰር እደማርያም ጸጋ ስኬታማ ሙያዊ ሕይወታቸውን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ በኋላ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተባለው በ1960ዎቹና 1980ዎቹ በሕክምና ትምህርት ቤት የውስጥ ደዌ ሕክምና ክፍለ ትምህርት ውስጥ አሳልፈዋል፡፡
ሊቅ መምህር፣ ሐኪምና ተመራማሪው ፕሮፌሰር እደማርያም በዓለም ደረጃ ገናና ስም ያጎናፀፋቸው በጉበት በሽታ ላይ በተለይ የሄፒታይተስ ቫይረስ ከኢትዮጵያ አንፃር የሠሩትና ለኅትመት የበቃው ጥናት ቀዳሚው ተጠቃሽ ነው፡፡ ሌሎች ምርምሮቻቸውም ታትመውላቸዋል፡፡ ሌላው እያንዳንዱ የኢትዮጵያ የሕክምና ትምህርት ተማሪ የሕመምተኛ የጤና ገጽታ አመዘጋገብን (medical case report) ሀሁ የቀሰመው የፕሮፌሰር ዕደማርያም ጸጋ ትሩፋት ከሆነው አረንጓዴው መጽሐፍ “A GUIDE TO WRITING MEDICAL CASE REPORTS” መሆኑም ይጠቀሳል፡፡ 

ፕሮፌሰር እደማርያም የሕክምና ከፍተኛ ትምህርታቸውን በካናዳ ሞንትሪያል በሚገኘው ማክጊል ዩኒቨርሲቲ ተከታትለው በ1950ዎቹ መገባደጃ በውስጥ ደዌ እና በሆድ ዕቃ ሕክምና በምሉዕ ብቃት ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ላቅ ያለ አገልግሎትን ሰጥተዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የውስጥ ደዌ ሕክምና ትምህርት ክፍል ለ16 ዓመታት በመምራትና በማስተማር እንዲሁም ክፍሉ ልዩ ልዩ ዘርፎች ያሉት የአካዴሚክ ዘርፍ እንዲሆንና የቅድመ ምረቃና የሬዚዳንስ ሥልጠና ፕሮግራሞችን በመዘርጋትም ይጠቀሳሉ፡፡
በእርሳቸው አመራርም በ1971 ዓ.ም. ትምህርት ክፍሉ ከመጀመሪያዎቹ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ትምህርት ክፍሎች የድኅረ ምረቃ ትምህርትን ማስተማር ጀምሯል፡፡
የላቀ አገልግሎታቸውን የተገነዘበው ዩኒቨርሲቲውም በ1973 ዓ.ም. ሙሉ ፕሮፌሰርነት አቀዳጅቷቸዋል፡፡ ከረዥም ዘመን አገልግሎታቸው አንዱ የሕክምና ትምህርት ቤቱ ዲን ሆነው ማገልገላቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕክምና ባለሙያዎች ማኅበርንም በ1970ዎቹ በፕሬዚዳንትነት በመሩበት ወቅት በማኅበሩ አጋፋሪነት በርካታ የጥናትና ምርምር ሥራዎች መከናወናቸው ዓመታዊ ጉባዔዎችም መካሄዳቸው ይወሳል፡፡
ፕሮፌሰር እደማርያም በ1980ዎቹ አጋማሽ ወደ ካናዳ በማምራት ኑሮና ሥራቸውን በዚያው ቢያደርጉም የአገር ቤት ግንኙነታቸውን አላቋረጡም፡፡ በተለይ በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የቅድመ ምረቃ ተማሪዎችን በማስተማር፣ የኢንዶስኮፒ ሥልጠናን በውስጥ ደዌና በቀዶ ሕክምና ለተካኑ (ስፔሻሊስቶች) ሐኪሞች ሲሰጡ ነበር፡፡
ከ1986 ዓ.ም. ጀምሮ ለሰባት ዓመታት በካናዳ በግራንድ ፎልስ-ዊንድሶር ኒውፋውንድላንድ በጠቅላላ ሕክምና፣ ከ1993 ዓ.ም. ጡረታ እስከወጡበት 2006 ዓ.ም. ድረስ በሃሚልቶን ሄልዝ ሳይንስ/ማክ ማስተር ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር ኤሚሪተስ ሆነው አገልግለዋል፡፡
ከአባታቸው ሊቀ ካህናት አለቃ ጸጋ ተሻለና ከእናታቸው / የተመኝ መኰንን ሰኔ 30 ቀን 1929 ዓ.ም. በጎንደር ከተማ ልዩ ስሙ ባዕታ በተባለ ሥፍራ የተወለዱት ፕሮፌሰር እደማርያም የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸውን በጎንደር ከተማ፣ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ከተማ ተከታትለዋል።
ከፍተኛ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባችለር ኦፍ ሳይንስ ካገኙ በኋላ ሜዲካል ዶክተርነትን ጨምሮ ሁለተኛና ሦስተኛ ዲግሪያቸውን ከማክጊል እና ከሉንድ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በለንደን የትሮፒካል በሽታዎች ሕክምና ትምህርት ቤት በመከታተል በሰነቁት የተለያዩ ትምህርቶች በጠቅላላ ሐኪምነት፣ በውስጥ ደዌና በሆድ ዕቃ ልዩ ሕክምና ሞያዎች የላቀ አገልግሎት እንደሰጡ ገጸ ታሪካቸው ያመለክታል።
ለ23 ዓመት አገልግሎት በሰጡበት አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ቤት ዲን በነበሩበት ጊዜ ከስዊድኑ ሉንድ ዩኒቨርሲቲ የፒኤችዲግሪ ያገኙት በክሊኒካል ቫይሮሎጂ (Clinical Virology) ነው፡፡
ነፍስ ኄር ፕሮፌሰር እደማርያም ጸጋ ከአገር ውስጥና ከውጭ አገሮች ካገኗቸው ክብሮችና ሽልማቶች መካከል፣ ከለንደን የትሮፒካል ሜዲስንና ሃይጂን ትምህርት ቤት The Frederick Mergatroyed Prize” ከኢትዮጵያ በሳይንሳዊ ምርምር ስኬት የብሉ ናይል ብሔራዊ ሽልማት (Blue Nile Medal)፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ንዑድ ሳይንቲስት (Distinguished Scientist) ከዓለም ጤና ድርጅት የተጋባዥ ሳይንቲስት ሽልማት (Visiting Scientist Award) ያገኟቸው ይጠቀሳሉ፡፡
ፕሮፌሰር እደማርያም ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በ80 ዓመታቸው ታኅሣሥ 23 ቀን 2010 .. ለ23 ዓመታት በኖሩባትና በሞያቸው ባገለገሉባት ሃሚልተን ከተማ አርፈው፣ ሥርዓተ ቀብራቸው ታኅሣሥ 28 ቀን በዚያው በምትገኘው በቅድስት ሥላሴ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተፈጽሟል።
ፕሮፌሰር እደማርያም ጸጋ፣ ከካናዳዊቷ ባለቤታቸው ፍራንሲስ ጸጋ ሌስተር ሦስት ሴቶችና አንድ ወንድ ልጅ አፍርተዋል
በአሜሪካ ከሚገኙት ከቀድሞ ተማሪዎቻቸው አንዱ የሙያ አጋራቸው / አሰፋ ጄጃው ለአሜሪካ ድምፅ ስለሳቸው ልዕልና እንዲህ በማለት ነበር የገለጹት፡-
‹‹በሕክምና ሞያ እጅግ የተወጣላቸው ሐኪም፣ ለሕመምተኛና ለተማሪ ከፍ ያለ ክብር የሚሰጡ፤ ጥሩ ተማሪ የሚያፈሩና ከእርሳቸው የተሻሉ እንዲሆኑ የሚያደርጉ፣ ተማሪ ሆነን ተሳስተሃል ብለን ደፍረን እንድንናገራቸው የሚያበረታቱን ፕሮፌሰር፣ ለሞያቸው የረቀቀ ክብር ያላቸው ሐኪም የሚለው መጠሪያ ለእርሳቸው የተጻፈ የሚመስል ባለሞያ ነበሩ።››