Wednesday, December 26, 2018

የአገር አውራ ስንብት


‹‹ሥርዓቶች ቢለዋወጡ ፖለቲካ ፓርቲዎች በሥልጣን ላይ ቢቀያየሩ መሪ ቢመጣ ቢሄድ ይህ ሁሉ ኃላፊ እንደሆነ ሥርዓትና አገር የተለያዩ እንደሆኑ መተኪያ የሌላት አገር ግን ትናንትና ዛሬ ነገ እንደምትኖር ቀጣይነት እንዳላት በዚህ ላይ መቀለድ እንደማይቻል ይህንንም ርዕሰ ብሔር ሆነው ለ12 ዓመታት ባገለገሉበት ወቅት በንግግራቸው፣ በሁኔታቸው በአስተሳሰባቸው አሳይተዋል፡፡››
ስለቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በሥርዓተ ቀብራቸው ላይ ይህንን ዓቢይ ምስክርነት የሰጡት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ ናቸው፡፡
94ኛ ዓመታቸውን ለማክበር የሁለት ሳምንታት ጊዜ ሲቀራቸው ያረፉት አቶ ግርማ ሥርዓተ ቀብራቸው ለርዕሰ ብሔር በሚመጥን አገራዊ ክብር ታኅሣሥ 10 ቀን 2011 ዓ.ም. በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ከዘጠኝ ሰዓት በኋላ ተፈጽሟል፡፡ ከፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ጋር ርዕሰ መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ፣ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄኔራል ሰአረ መኰንን ተገኝተዋል፡፡
ሺሕ ሰማንያ አካባቢ ከሚገኘው ስፍራ ለክብራቸው 21 ጊዜ መድፍ ተተኩሷል፡፡ ረፋዱ ላይ በሚሌኒየም አዳራሽ በተከናወነው የሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ ዲስኩር ያሰሙት ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ፣ ‹‹ክቡር ፕሬዚዳንት ረጅሙን ጉዞ ጨርሰዋል፤ የእርስዎ ከዚህ ዓለም መለየት የቤተ መጻሕፍት መዘጋት ነው፤›› ብለዋል፡፡ የቀድሞው ፕሬዚዳንት አብዛኛውን የዕድሜያቸውን ጊዜ ኢትዮጵያን በተለያየ የሥልጣንን እርከን ከወታደርነት እስከ ርዕሰ ብሔርነት በቅንነት ማገልገላቸውን ጠቅሰው፣ በኅልፈታቸው የተሰማቸውን ጥልቅ ሐዘን ገልጸዋል።
በሚሌኒየም አዳራሽ የነበረው ፕሮግራም ከተጠናቀቀ በኋላ በክብር ሰረገላና በፈረሰኞች እንዲሁም በወታደራዊ ማርሽ ባንድ ታጅቦ በአፍሪካ ጎዳና እና በዳግማዊ ምኒልክ ጎዳና በመጓዝ አስክሬናቸው ካረፈበት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በማምራት ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለአንድ ቀን ብሔራዊ የሐዘን ቀን እና ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብ ያወጀላቸው የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ሥርዓተ ቀብር የተፈጸመው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ፣ ፓትርያርክ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ መሪነት ጸሎተ ፍትሐት ከተደረገ በኋላ ነው፡፡
የቀብር ሥነ ሥርዓት አስተባባሪ ብሔራዊ ኮሚቴ ባወጣው መርሐ ግብር መሠረት፣ ማክሰኞ ታኅሣሥ 9 ቀን በመኖሪያ ቤታቸው ከፍተኛ የፌዴራልና የክልል ሹማምንትና የውጭ አገሮች ዲፕሎማቶች በተዘጋጀው መዝገብ ላይ የሐዘን መልዕክቶቻቸውን ማስፈራቸው ታውቋል። ብሔራዊ የሐዘን ቀን መታወጁን ተከትሎ በሁሉም የኢትዮጵያ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች፣ እንዲሁም በውጭ በሚገኙ የኢትዮጵያ ኤምባሲዎችና ቆንስላ ጽሕፈት ቤቶች ለአንድ ቀን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ ዝቅ ብሎ እንዲውለበለብምደርጓል።
በሦስት መንግሥታት ከፓርላማ ፕሬዚዳንትነት እስከ ርዕሰ ብሔርነት ኢትዮጵያን የመሩት፡፡ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ በሰባት አሠርታት የሥራ ጉዟቸው፣ በዕውቀታቸውና በሙያቸው በተሰማሩባቸው የተለያዩ መስኮች ጉልህ ሚና እንደተጫወቱ ይነገርላቸዋል፡፡ ከበጎ ፈቃድና በጎ አድራጎት አገልግሎት ጋር ስማቸው ይያያዛል፡፡ ከመንግሥታዊ ተግባራቸው ጡረታም ቢወጡ፣ በተፈጥሮ ጥበቃና አካባቢ ክብካቤ ዙሪያ በለም ኢትዮጵያ ያደረጉት ልጨኛ ተግባር ይጠቀሳል፡፡
ለሁለት ተከፍለው የቆዩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶሶችን ወደ አንድነት ለማምጣት፣ በኢትዮ ኤርትራ መካከል ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ ለማድረግ ጥረት ካደረጉ ታዋቂዎች መካከልም ይገኙበታል፡፡
የስድስት ቋንቋዎች ኦሮሚኛ፣ አማርኛ፣ ትግርኛ፣ ጣሊያንኛ፣ እንግሊዝኛና ፈረንሣይኛ ተናጋሪ የነበሩት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ቀደም ባሉት ስድስት አሠርታት ውስጥም በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥትና በኅብረተሰብዓዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት በተለያዩ ኃላፊነት ቦታ ላይ አገልግለዋል፡፡
በዘውዳዊው ሥርዓት በአዲስ አበባ ከተማ የልደታ ወረዳ እንደራሴ በመሆን በ1954 ዓ.ም. ለፓርላማ በመመረጥ የሕግ መምርያ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትም ነበሩ፡፡ በ52ኛው የዓለም ፓርላማዎች ኅብረት ጉባዔ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ሠርተዋል፡፡
በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ዘመን በ1992 ዓ.ም. በተደረገው አገራዊ ምርጫ በምዕራብ ሸዋ ዞን በቾ ወረዳ በግል ተወዳድረው በማሸነፍ፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ፕሬዚዳንት እስከሆኑበት 1994 ዓ.ም. ድረስ አገልግለዋል፡፡
ከአባታቸው ከግራዝማች ወልደ ጊዮርጊስ ሉጫና ከእናታቸው ከወ/ሮ ወሰንየለሽ መኩሪያ ቅዳሜ ታኅሣሥ 19 ቀን 1917 ዓ.ም የተወለዱት መቶ አለቃ ግርማ፣ ከሁለት ዓመት በፊት ካረፉት ባለቤታቸው ወ/ሮ ሳሌም ጳውሎስ መንአመኖ አምስት ልጆችን ያፈሩ ሲሆን፣ የልጅ ልጆችም አይተዋል፡፡
94 ዓመታቸው ቅዳሜ ታኅሣሥ 6 ቀን ያረፉት አቶ ግርማ ወልደ ጊዮርጊስ ኢትዮጵያን ከ1994 እስከ 2006 ዓ.ም. መምራታቸው ይታወቃል፡፡

Monday, July 23, 2018

የሥነ ልሳንና የትምህርት ባለሙያው ዶ/ር ብቅአለ ሥዩም (1943-2010)


በሔኖክ ያሬድ
ከአራት አሠርታት ለበለጠ ዘመን በመምህርነትና በሥነ ልሳን ባለሙያነት እንዲሁም በትምህርት ቢሮ ኃላፊነት በኢትዮጵያ ትምህርት ሕዋ ውስጥ ብቅ ያሉት ዶ/ር ብቅአለ ሥዩም ባበረከቱት አስተዋጽኦ ይጠቀሳሉ፡፡
ዶ/ር ብቅአለ ከልጅነታቸው ጀምሮ ቀልባቸውን የሰረቀውን ያስተማሪነት ሙያ እጅግ ከመውደዳቸው የተነሳ ለ30 ዓመታት በአንደኛ ደረጃና በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች፣ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ (የአሁኑ ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርሲቲ) እና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አገልግለዋል፡፡ በተለይ በኮተቤ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ከማስተማሩ ባሻገር ኮሌጁን በዲንነት መርተዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በሥነ ልሳን የትምህርት ክፍል በረዳት ፕሮፌሰርነት በመምህርነትና በተመራማሪነት አገልግለዋል፡፡
ዶ/ር ብቅአለ ከማስተማሩ ወደ አስተዳደር በገቡበት ከ1985 እስከ 1993 ዓ.ም. ባለው ጊዜ የአማራ ብሔራዊ ክልል የትምህርት ቢሮ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል፡፡
በተለይ በዚህ ዘመን የኢትዮጵያ ተማሪዎች ሕፃናትና ወጣቶች በሥነ ምግባር ተኮትኩተው እንዲያድጉ ዓይነተኛ መሣሪያ እንደሆነ የታመነበት ‹‹የኢትዮጵያ ተረቶች ፕሮጀክት›› በአማራ ክልል እውን እንዲሆን ካደረጉት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ የፕሮጀክቱ ዋና ዓላማ በቀላል እንግሊዝኛ መጻሕፍትን በማዘጋጀት በእያንዳንዱ የኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሕፃናት ተማሪዎች እንግሊዝኛን ማንበብ እንዲለማመዱና እግረ መንገዳቸውንም ባህላዊ እሴቶቻቸውን የሚያንፀባርቁትን ተረቶች እንዲያውቁ ማድረግ ነው፡፡
 በአማርኛ የተሰበሰቡትና በጽሑፍና በድምፅ ከተሰነዱት ተረቶች መካከል የተወሰኑት ወደ እንግሊዝኛ ተተርጉመው እንዲታተሙ ያስተባበሩት ዶ/ር ብቅአለ ሥዩም ናቸው፡፡ የተረቶቹ መጻሕፍት ለእንግሊዝኛ ቋንቋ ማስተማሪያነት ከመዋላቸው በላይ ከሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ከተሰበሰቡ ተረቶች ጋር በአንድነት በድረ ገጽ ውስጥ ለአገልግሎት ውለዋል፡፡
ከእናታቸው ከወ/ሮ አበበች በንቲና ከአባታቸው ከአቶ ሥዩም ተፈሪ በቀድሞው ጋሞጎፋ ጠቅላይ ግዛት፣ ጋርዱላ አውራጃ ጊዶሌ ከተማ ታኅሣሥ 3 ቀን 1943 ዓ.ም. የተወለዱት ዶ/ር ብቅአለ ሥዩም፣  የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን  በጊዶሌ ከተማ በሚገኘው ፈታውራሪ ገበየሁ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በጨንቻ ከተማ ደጃዝማች ወልደማርያም፣ በአርባ ምንጭ ከተማ፣ በአምቦ ማዕረገ ሕይወት ዘቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና በወቅቱ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ሥር በሚገኘው ልዑል በዕደ ማርያም ትምህርት ቤት አጠናቀዋል፡፡ ለሦስት ዓመታት በመምህርነት ተቀጥረው ካስተማሩ በኋላ፣ በአዲስ አበባ መምህራን ኮሌጅ ገብተው በሁለተኛ ደረጃ መምህርነት በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡
በተለያዩ ዓመታትም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያና የሁለተኛ፣ እንዲሁም የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ያገኙት ዶ/ር ብቅአለ በተጨማሪም እንግሊዝ  ከሚገኘው ኦፕን ዩኒቨርሲቲ በቢዝነስ አስተዳደር ተመርቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባዔ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ሥነ ልሳንን በተመለከቱ በርካታ ጥናታዊ ጽሑፎችን አቅርበዋል፡፡
ዶ/ር ብቅአለ ሥዩም ከረዥም ዘመን አገልግሎት በኋላ በ2005 ዓ.ም. በጡረታ ቢሰናበቱም ባደረባቸው ሕመም ምክንያት በአሜሪካ በተለያዩ ሆስፒታሎችና በአገር ውስጥ በሕክምና ሲረዱ ቆይተው ሐምሌ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በተወለዱ 67 ዓመታቸው አርፈው በማግስቱ በጴጥሮስ ወጳውሎስ ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡
የፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ ታላቅ እህት የወ/ሮ ቦካ ዲነግዴ የልጅ ልጅ የሆኑት ዶ/ር ብቅአለ  ከወ/ሮ ዕፀ ገነት ጽጌ ጋር ትዳር መሥርተው ሁለት ወንዶችና ሁለት ሴቶች ልጆች አፍርተዋል፡፡ 
                            (ሪፖተር፣ እሑድ ሐምሌ 15 ቀን 2010 ዓ.ም.)

Friday, May 25, 2018

የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነትና ቅድመ ታሪክ ከቋንቋ አንፃር እንዴት ይታያል?
በሔኖክ ያሬድ
መጋቢት ወር በሀገረ አሜሪካ ለንባብ ካበቁት አካዴሚያዊ መጻሕፍት ተጠቃሹ ‹‹ቋንቋና ነገድ በኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነትና ቅድመ ታሪክ›› የሚል ርዕስ ያለው የዶ/ር ግርማ አውግቸው ደመቀ መጽሐፍ ነው፡፡ ዶ/ር ግርማ የሥነ ልሳንና የኢትዮጵያዊ ቋንቋዎች ባለሙያ ሲሆኑ፣ የምርምር ትኩረታቸው በአብዛኛው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ታሪክና ሥነ መዋቅር ላይ ነው፡፡ በቅርቡ በእንግሊዝኛ ካሳተሟቸው መጽሐፎች መካከል የአማርኛ ጥንተ አመጣጥ፣ ሰዋስዋዊ ለውጥ በሴሜቲክ የአማርኛ ሰዋሰው በዘመን፣ ሒደትና የአርጎባ ንግግር ዓይነቶች/ቋንቋዎች ይገኙባቸዋል፡፡
ስለአዲሱ መጽሐፋቸው በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን እንደተገለጸው፣ መጽሐፉ ስለኢትዮጵያ ቋንቃዋችና ቤተሰቦቻቸው የታሪካዊ ሥነ ልሳን ጥናት መውሰድ እስከሚችለው ጊዜ ገደብ ድረስ በመጓዝ መሠረታዊ መረጃ ያቀርባል፡፡ ቋንቋና ተናጋሪው የሚለያይ አይደለምና፣ ከቋንቋዎቹ አንፃር በመነሳት የኢትዮጵያን ሕዝብ ማንነትና ቅድመ ታሪክ ይዳስሳል፡፡ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ከተወሰኑ ብቸኛ ቋንቋዎች በስተቀር አፍሮ ኤሽያቲክና ናይሎሰሀራን ከሚባሉ ታላቅ ቤተሰቦች ይመደባሉ፡፡ ከጥቂት የናይሎሰሃራን ቋንቋዎች በስተቀር ሌሎቹ ለረዥም ጊዜ በኢትዮጵያ የነበሩ ናቸው፡፡ መጽሐፉ የአፍሮኤሽያቲክ ቋንቋዎች ከኤሽያ በተለያየ ወቅት ወደ ኢትዮጵያ ገቡ የሚለውን መላምት በስፋት መርምሮ ይህ ስለመሆኑ አሁን ያለው መረጃ ማረጋገጫ  እንደሌለው ያሳያል፡፡ ከዚህም በላይ በኅብረተሰብ መካከል ስላለው ውህደትና ልዩነት በስፋት ይረዝራል፡፡
የመጽሐፉ አዘጋጅ ዶ/ር ግርማ ‹‹መሠረታዊ መነሻ የቅጾች ማስታወቂያ›› በሚለው ምዕራፋቸው እንደገለጹት መጽሐፉ አራት ቅጾች ይኖሩታል፡፡ ለኅትመት የበቃው ቅጽ አንድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ማንነትና ቅድመ ታሪክ፤ ቅጽ ሁለት ኦሞቲክ፣ ናይሎሰሀራንና ምድባቸው ያልለየላቸው ቋንቋዎች፤ ቅጽ ሦስት ኩሽና ኩሽቲክ፤ ቅጽ አራት ሴማዊ ቋንቋና ሕዝብ ናቸው፡፡
ቀዳሚው ቅጽ በስድስት ምዕራፎች በ248 ገጾች የተደራጀ ሲሆን፣ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ማንነትና ታሪካዊ አመጣጥ ከቋንቋ አንፃር ተተንትኖ መረጃዎቹም በታሪካዊና ንፅፅራዊ ሥነ ልሳን ዘዴ መቅረቡ ተወስቷል፡፡  
ዶ/ር ግርማ በመቅድማቸው ያነሷቸው ዐበይት ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዱ ‹‹የሴሜቲክ ሕዝብ ከዓረብ ወደኢትዮጵያ ገባ›› የሚለው መላምት፣ ሌላው ስለ ኩሽቲክ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚቀርበው ሐሳብና የኩሽ ምንነትን ፈትሸዋል፡፡ እንዲሁም የሀበሻን ምንነትንም መርምረውታል፡፡ በቅጽ አንድ መጽሐፋቸው ላይ ያነሷቸውን ነጥቦች እዚህ ላይ እንደወረደ ማቅረብ ወደድን፡፡  
መቅድማዊው ሐሳብ  
‹‹በትምህርት ዓለም መፍትሔና ማብራሪያ ያገኙ ጉዳዮች ወደ ኅብረተሰቡ ሳይወርዱ ይቀሩና መረጃ የሌለው ‹‹አፈ ታሪክ›› ነግሦ የሚታይበት አጋጣሚ ብዙ ነው፡፡ ከእነዚህ ውስጥ የሴሜቲክ ሕዝብ ከዓረብ ወደ ኢትዮጵያ የገባ ነው የሚለው መላምት አንዱ ነው፡፡ ሌላኛው በሥነ ልሳን ጥናት ኩሽቲክ ቋንቋዎች የሚባሉትንና የእነዚህ ተናጋሪዎችን የሚመለከት ነው፡፡ የኩሽቲክ ቋንቋ ተናጋሪዎች ላይ የሚቀርበው ታሪካዊ ትንታኔ በአንዳንድ ሥራዎች ከጥንታዊ ኩሽ መንግሥት ሕዝብና ከመጽሐፍ ቅዱስ ኩሽ አጠቃቀም ጋር እየተምታታ ሲቀርብ ይስተዋላል፡፡ በተለይ ትንሽ በተማረው ዘንድ አንዱ የወሬ መክፈቻ የሴሜቲክ - ኩሽቲክ ጉዳይ እስከመሆን ደርሷል፡፡
‹‹ኩሽቲክና ሴሜቲክ ከቋንቋ ዘር ግንድ አንፃር ምንጫቸው አንድ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙትን ኦሞቲክ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉትን እነ ጥንታዊ ግብፅን፣ በርበርን፣ ቻዲክ ቋንቋዎችን ጨምሮ የእነዚህ ወላጅ/ልዕለ ቋንቋ በአሁኑ ጊዜ አፍሮኤስያዊ/አፍሮኤሽያቲክ በመባል የሚታወቀው ነው፡፡ ከአፍሮኤሽያቲክ ቋንቋዎች በተጨማሪ በኢትዮጵያ የናይሎሰሃራን ቋንቋዎችና የተወሰኑ በቋንቋ ዘር ዝምድና ምደባቸው ያልየላቸው ቋንቋዎች አሉ፡፡
‹‹ኩሽ የሚለው ቃል (ወይም የዚህ ዝርያ ቃል) በጥንታዊ ሥራዎች ነገድን፣ ሕዝብንና አገርን ሲያመለክት፣ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ሕዝብንና የቋንቋ ቤተሰብን ያመለክታል፡፡ በዘመናችን በትምህርታዊ ዐውድ አሁን በዚህ ቃል የሚገለጹትን የቋንቋ ቤተሰቦችም ሆኑ እነዚህን ቋንቋዎች የሚናገሩ ሕዝቦች ጥንት በቅድመ - ክርስቶስ ከሁለት ሺሕ ዓመት በፊት ጀምሮ በነበረው ኩሽ በሚባለው አገር ከሚኖሩ ነገዶችም ሆነ በሌላ ከተጠቀሱት ሕዝቦች በቀጥታ የወረዱ ናቸው ማለት አይደለም፡፡ የመጽሐፍ ቅዱሱ ኩሽም አሁን በሥነ ልሳን ጥናት ካለው አጠቃቀም ጋር ቀጥተኛ ግንኙነት የለውም፡፡ የምርምር ዕውቀት ሁልጊዜ ወደ ሕዝብ አይወርድምና በኅብረተሰባችን በተለይም በፖለቲከኞና ትንሽ ፊደል በቆጠሩት ዘንድ የጥንቱ አጠቃቀምን አሁን ካለው ጋር እያገናኙ ለሙገሳም፣ ለወቀሳም ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡
‹‹ቀደምት በአገራችን ሊቃውንት በቀረቡ ሥራዎች፣ ለምሳሌ በእነ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያና ኅሩይ ወልደ ሥላሴ የጥንቱ አጠቃቀም ከአሁኑ ጋር እየተጋጨ ብዙም ግልጽ ሳይሆን ቀርቷል፡፡ በአብዛኛዎቹ ቀደም ባሉት ጊዜያት በተለይ በስልሳዎቹና በሰባዎቹ ዘመናዊ የታሪክ ጸሐፊዎች ሥራዎችም ቢሆን ያለው የሕዝብ ታሪክ/ቅድመ ታሪክ ትንታኔ ቀደምት የሥነ ልሳን ሥራዎች ላይ የተመሠረተ በመሆኑ አሁን ስለቋንቋዎቹና ስለሕዝቡ ያለን ዕውቀት የሚያንፀባርቅ አይደለም፡፡
‹‹በውጭ ጸሐፊዎችም ሆነ በአገራችን በተለይ ቀደምት ጸሐፊዎች፣ በኩሽ ላይ ብቻ ሳይሆን፣ ስለኢትዮጵያ ሕዝብ ማንሳት፣ ባህና ታሪክ/ቅድመ ታሪክ በስፋት የተሠራጨው ትረካ የተስተካከለ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ይልቁንም በኢትዮጵያዊያን ጸሐፍት በተደረጉ ሥራዎች በከፊል የሚታየው የእርስ በርስ የመጣረስ ችግር ነገሩን በውል ሳያጤኑ ከተዛባና አንዳንዴም በዘረኝነት መርዝ ከተቀባ የውጭ ሥራዎች ከመገልበጥ የመጣ ነው፡፡
‹‹ከላይ የጠቀስናቸው ሥራዎች ከወጡ በኋላ፣ በሥነ ልሳን ዘርፍ በርካታ እመርታዎች ተካሂደዋል፡፡ በሥነ ሰብ፣ ሥነ ማኅበረሰብና በታሪክ ዘርፎችም እንዲሁ፡፡ በእነዚህ ዘርፎች የተደረጉ ምርምሮች አመርቂ ደረጃ ላይ የደረሱ ናቸው ባይባልም፣ ከበፊቱ በተሻለ ስለቋንቋዎቹና ስለሕዝቡ ግንዛቤ አሁን አለን፡፡ ይሁን እንጂ፣ በአገራችን ከዘመናችን ባሉት አዳዲስ ጥናቶች የታዩ ግኝቶች ጋር እኩል በመሄድ የማስተማሪያ መጻሕፍቶቻችን ሲታደሱ ብዙም አይስተዋልም፡፡ ይህ የሚከተለውን የኪዳነ ወልድ ክፍሌን ቃል ያስታውሰናል፤
‹‹ሀገራችንና ቋንቋችን ያረገዙትን ለመውለድ፣ ወልዶም ለማሳደግ፣ ሐኪምና ጊዜ አላገኙም፤ የተወለደውም ትምርታችን ወላጆቹና ሞግዚቶቹ ታርደው፣ ተሰደው ስላለቁ እንደ ሙት ልጅ ሆኖ ከመጫጨትና ከመመሥጨት በቀር እያደገና እየሰፋ፣ እየፋፋ መሄድ አልቻለም፡፡
‹‹አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ከዛሬ ምዕት ዓመት በፊት አካባቢ ያሉት አሁንም የተለወጠ አይመስልም፡፡ በየሙያው በአገራችን ያለን የሰው ኃይል ከቁጥር የማይገባ ብቻም ሳይሆን፣ ያለው የኢኮኖሚክ ሁኔታና የምሁሮቻችን ዝግጅት በሰል ያለ ጥናት ለማድረግ የሚያስችል ደረጃ ላይ አይደለም፣ ያሉት ከኢኮኖሚክ ችግሩ በላይ በፖለቲካው እየተገፉ በየሰው አገር ተበትነው ለመኖር የተገደዱበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ይህን ሥራ ያዘጋጀነው ከላይ ያሉትን ችግሮች በማሰብ ነው፡፡ የታሪካዊ ሥነ ልሳንና የዓይነታዊ ሥነ ልሳን ሥራዎችን፣ እንዲሁም ወቅታዊ የታሪክና የሥነ ሰብ ግንዛቤዎችን ከሥር ከሥሩ እየተከታተሉ የማስተማሪያ መጽሐፎቻችን መታደስ እስከሚችሉ ለመነሻ ግንዛቤ እንዲሆን በማሰብ ነው፡፡
ሀበሻ
‹‹ሀበሻ ኢትዮጵያዊ ከሚለው ቃል ይልቅ በአጠቃቀም በኅብረተሰቡ ዘንድ ሥር የሰደደ ነው፡፡ በርካታ አገራዊ (ቁሳዊና ሐሳባዊ) ባህሎች በዚህ ቃል ቅፅልነት ሲገልጹ ይስተዋላል፡፡ ለዚህ አስረጅ፣ የሀበሻ ዶሮ፣ የሀበሻ ጎመን፣ የሀበሻ መድኃኒት፣ የሀበሻ ኩራት፣ የሀበሻ ተንኮል፣ የሀበሻ ምቀኝነት፣ ወዘተ የሚሉትን አጠቃቀሞች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ሀበሻ የሚለው ቃል ከህንድ እስከ አውሮፓ መላው ዓለም ኢትዮጵያን ለመግለጽ ሲጠቀሙበትም ቆይቷል፡፡ በህንድ፣ በፓኪስታንና በአጎራባች አገሮች ሀበሽ የሚባሉ በጀግንነታቸው የተመሰገኑ ከአካባቢያችን የሄዱ ሕዝቦችም አሉ፡፡
‹‹በአሁኑ ወቅት በውጭው አገር ኢትዮጵያዊውና ኤርትራዊው መሰሉን ሲያይ ‹‹ሀበሻ ነህ?›› የሚል ጥያቄ ያቀርባል፡፡ ይህን ቃል ኢትዮጵያዊ የመሰለውን ሰው ለመተዋወቅ ከአጎራባች አገሮች በተለይ ከሶማሊያ የመጡም ሲጠቀሙበት ይስተዋላል፡፡ ይሁን እንጂ ሀበሻ የሚለው ቃል የተለየ ፖለቲካዊ ትርጉም ሰጥቶትም ይገኛል፡፡  
ሀበሻና ሴም
‹‹ሀበሻ የሚለውን ቃል ከሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪዎች ጋር የማገናኘት ሁኔታ ታሪካዊ መረጃ እንደሌለው ቢገለጽም፣ በአሁኑ ጊዜ በተለይ በአገራችን ተደጋግሞ ሲሰማ ይስተዋላል፡፡ በእግረ መንገድ ይህን ቃል የሚያነሱ ሥራዎችም ይህንኑ ሲደግሙት ይስተዋላል፡፡ ለምሳሌ ሚረን የቀይ ባህር ዜጎች በሚለው መጽሐፉ ሀበሻ የሚለውን ቃል በሙዳየ ቃላት የበየነው በኢትዮጵያና በኤርትራ ደጋማ ቦታዎች የሠፈሩ ሴማዊ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦችን የሚመለከት እንደሆነ ነው፡፡
‹‹ሀበሻና ሴምን የማገናኘት ጉዳይ በኅብረተሰቡ ዘንድ በስፋት እንዲሠራጭ ያስቻለው በየትምህርቱ ቤቱ ሲሰጥ የነበረ ታሪክ ይመስላል፡፡ ከዚህ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ሲሰጥ የነበረው በጣም የተለመደው መላምት ሴማዊ ሕዝቦች ከደቡብ ዓረቢያ ወደ ኢትዮጵያ ተሻግረው መጡ የሚል ነው፡፡
‹‹በዚህ ጉዳይ ቀደምት ሥራዎች ውስጥ ኢዮብ ሉዶልፍ ሊጠቀስ ይችላል፡፡ የመጡበትም ጊዜ በአብዛኛው ከ1,000 እስከ 500 ቅጋአ (ቅድመ የጋራ አቆጣጠር) ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ለዚህ መላምት ሥር መስደድ በግንባር ቀደምትነት ከሉዶልፍ በማስከተል ከሚጠቀሱት ውስጥ አንደኛው ኮንቲ ሮሲኒ ናቸው፡፡ እነ ተክለ ፃዲቅ መኩሪያ በዚሁ በወቅቱ አሳማኝ መስሎ በታየው መላምት ላይ ተመርኩዘው የማስተማሪያ መጻሕፍት በማዘጋጀት፣ ሐሳቡን ወደ ትምህርት ቤት አወረዱት፡፡ ታደሰ ታምራትም ታላቅ ናቸው ብሎ ያሰባቸውን እነ ኮንቲ ሮሲኒን ሐሳብ እንዳለ ተቀብሎ አጠቃላይ የኢትዮጵያን ታሪክ የሴማዊ ሕዝቦች መስፋፋት አድርጎ ማቅረቡ ለአመለካከቱ ሥር መስደድ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጓል ማለት ይቻላል፡፡ በቀዳሚዎቹ ምዕራፎች እንደገለጽነው፣ እንደእነዚህ ጸሐፊዎች እምነት ወደ ኢትዮጵያ መጡ ከሚባሉት የሴም ነገዶች ውስጥ ዋና ዋናዎቹ ነገደ ሐበሽትና ነገደ አግዓዚ የተሰኙ ናቸው፡፡ ነገደ ሐበሸት ስሙን ለሕዝቡ መጠሪያ ሲያሳልፍ ነገደ አግዓዚ ደግሞ ቋንቋውን ተወልን፡፡
  ‹‹በዚህ ሥር በሰደደ መላምት ሀበሻ ከሀበሸት፣ ግዕዝ ደግሞ ከአግዓዚ ከሚሉት ቃላት የመጡ ናቸው፡፡ ግዕዝም ከሳባ በቀጥታ የመጣ ነው የሚለውን የግምት አነጋገር የእኛዎቹ እንዳለ ተቀብለውት በትምህርት ቤት ማስተማሪያዎች ውስጥ ይሰጥ ነበር፤ ‹‹ይህ ግዕዝኛ አነጋገር የመጣ ከክርስትና በኋላ ነው እንጂ የፊተኛው አነጋገርና ጽሑፍ ቀድሞ በደቡብ ዓረብ ሳሉ የሚጽፉበትና የሚነጋገሩበት የሳባ ቋንቋ ነው፡፡ ይኼም የሳባ ፊደልና ቋንቋ ለግዕዝ እንደ አባት የሚቆጠር ነው፡፡ የዚህ መላምት ቅርሻ እስካሁን ላለው በኅብረተሰቡ ዘንድ ለተስፋፋው የተሳሳተ አስተያየት መሠረት የሆነ ይመስላል፡፡
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነልሳን ፕሮፌሰር ዘለዓለም ልየው ስለ መጽሐፉ በሰጡት አስተያየት፣ ዶ/ር ግርማ የኢትዮጵያን ሕዝቦች ማንነትና ታሪካዊ አመጣጥ ከቋንቋ አንፃር ተንትኖ ያቀረቡባቸው መረጃዎች በታሪካዊና ንጽጽራዊ ሥነልሳን ዘዴዎች ተቀነባብረው በመቅረባቸው ስለ ኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ተናጋሪዎቻቸው ያለንን ዕውቀት ለማሳደግ በእጅጉ ይረዳል ብለዋል።
‹‹ከበቂ መረጃ ጋር አብዛኛዎቹ የኢትዮጵያ ሕዝቦችና ቋንቋዎች ምንጫቸው አንድ መሆኑን እንረዳለን። የተናጋሪዎች ለብዙ ዘመናት ተራርቆ መኖር ከአንድ ቤተሰብ የተገኙ ቋንቋዎችን ሊያለያይ እንደሚችል ሁሉ፣ ለብዙ ዘመናት አብሮ በመኖር የተነሳ ከተለያዩ የቋንቋ ቤተሰቦች የተገኙ ቋንቋዎች ደግሞ በቋንቋ ባህርያትና በሌሎችም እሴቶች እየተመሳሰሉ ሊሄዱ እንደሚችሉ በውል ያስገነዝባል፤›› በማለትም በመጽሐፉ ላይ አስፍረዋል፡፡


Friday, May 18, 2018

ልሂቅ ፕሮፌሰር ዓቢይ ፎርድ (1927- 2010)

በሔኖክ ያሬድ
በ1920ዎቹ ዓመታት በማርክስ ጋርቬይ መሪነት ተራማጅ አስተሳሰብ ያራምድ በነበረው የሐርለም ፓን አፍሪካዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ንቁ ተሳታፊ ከነበሩት አንዱ ራባይ አርኖልድ ጆሹዋ ፎርድ ይጠቀሳሉ፡፡ በማርከስ ጋርቬይ የተመሠረተው ዩኒቨርሳል ኔግሮ ማኅበርም የሙዚቃ ዳይሬክተር ሆነው ከማገልገላቸው ባሻገር ‹‹ወደ አፍሪካ እንመለስ›› በተሰኘው ንቅናቄ መሠረት ወደ ኢትዮጵያ በማቅናት ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም. የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የንግሥ በዓል ሲከበር የሙዚቃ ሥራቸውን አቅርበዋል፡፡
በዓመቱ በ1924 ዓ.ም. ሚኞን ፎርድ የራባይ ፎርድን ዳና ተከትለው ኢትዮጵያ በመምጣት የራባይ ፎርድ ፕሮጀክቶች ጸሐፊ ሆነው በሚያገለግሉበት አጋጣሚ ነበር ትዳር መሥርተው ጎጆ ቀልሰው የኋለኛው ባለታሪክ ፕሮፌሰር ዓቢይ ፎርድ የተወለዱት፡፡ ይሁን እንጂ በ1928 ዓ.ም. በጣልያን ወረራ መባቻ ላይ ራባይ ፎርድ በፅኑ በመታመማቸው ሕይወታቸው ከማለፉ አስቀድሞ ራባይ ፎርድ የአዲሲቱን አገራቸውን ዕጣ ፈንታ በጋራ ለመቋቋም ባለቤታቸው ሚኛን ፎርድ ኢትዮጵያን ጥለው እንዳይሄዱ አደራ ብለው ነበር፡፡
በዚህም መሠረት ሚስስ ፎርድ ወረራውን በመቃወም ተሳታፊ የነበሩ ሲሆን፣ ከድል በኋላም ከካረቢያን ጓደኞቻቸው ጋር በመተባበርም ልጃቸው ትምህርት ሀሁን የጀመረበት ‹‹ቤተ ኡራኤል›› ቆይቶ ልዕልት ዘነበ ወርቅ የተሰኘውን ትምህርት ቤት ኢትዮጵያ ድል በኋላ ለማቋቋም ሚስስ ፎርድ የትውልድ ሰንሰለት በትምህርት፣ በሥነ ምግባር፣ በሥራ ወዳድነት እንዲታነፅ ያላሰለሰ ጥረት ያደረጉና ትውልድ የገነቡ እናት ነበሩ፡፡ ሁለቱም ወንድ ልጆቻቸው ዮሴፍና ዓቢይም ይህንኑ የሕይወት ቅርስ በማንገብ ሕይወታቸውን በሙሉ ለማስቀጠል ችለዋል፡፡
የፎርድ ቤተሰብ መሠረታዊ እምነት የአፍሪካን ባህሎችና ማንነቶችን ከሁሉም አንፃር አጉልቶ ማንፀባረቅ ማክበር ነው፡፡ ቤተሰቡ በዘመናት ውስጥ ዓይነተኛ አስተዋጽዖን በትውልዶች መካከል አበርክተዋል፡፡ ሚኞን፣ አርኖልድ፣ ዮሴፍና ዓቢይ በማኅበረሰብ ውስጥ ያበረከቱት ተግባር ሕያው ሆኖ ቀጥሏል፡፡
ፕሮፌሰር ዓቢይ እንደ ሊቅነታቸውና ምሁርነታቸው በትሁት ሰብእና በአስተዋይ ህሊና ልምዳቸውን አካዴሚያዊ ተቋማት እንዲመሠረቱ፣ እንዲሁም ልዩ ልዩ የትምህርት ፕሮግራሞች እንዲከፈቱ በማድረግ ለአፍሪካውያን በአገራቸውም ሆነ በድዮስጶራ ባሉበት ዐቢይ ተግባርን አከናውነዋል፡፡ ለተማሪዎች አርአያ በመሆን ኪነ ጥበባዊ ተግባራትን ለፊልም ሠሪዎች፣ ለሙዚቀኞች፣ ገጣሚዎችና ሠዓሊያን አጋርተዋል፡፡ ፕሮፌሰር ዓቢይ የፓን አፍሪካኒዝም ውርስን (ሌጋሲ)  ለማስቀጠል ለዚህም የሚኞን ፎርድ ፋውንዴሽን በመመሥረት የእናታቸውን የሚስስ ፎርድ ሕይወትና በኢትዮጵያ ያከናወኑት ሥራዎች እንዲታወስ በማድረግ ዓቢይ ተግባር አከናውነዋል፡፡
ፕሮፌሰር ዓቢይ በክርስትና ስማቸው ‹‹ወልደ አብርሃም›› መንፈሳዊ፣ ምሁራዊና የፈጠራ ሕይወታቸው የብዙ ዓለማት ሰው እንደነበሩ ይመሰክራሉ፡፡ ከባርቤዶስ የዘር ግንድ ከተመዘዙትና የፓን አፍሪካዊ ታጋይ ከነበሩት ወላጃቸው በአዲስ አበባ ከተማ ማክሰኞ የካቲት 26 ቀን 1927 ዓ.ም. የተወለዱት ዓቢይ ፎርድ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን የተከታተሉት በሊሴ ገብረማርያም ሲሆን፣ ከፍተኛ ትምህርታቸውን በአሜሪካ አጠናቀዋል፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ አየር ኃይል በአውሮፕላን አብራሪነት ሠልጥነው አገልግሎት መስጠታቸውንም ገጸ ታሪካቸው ያስረዳል፡፡

በይቀጥላልም ኒውዮርክ ከሚገኘው ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ከጋዜጠኝነት ትምህርት ክፍል ሲመረቁ፣ ወደ ሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ በማምራትም የራዲዮ፣ የቴሌቪዥንና የፊልም ትምህርት ዘርፍን በማቋቋምና መሥራች የፋካልቲ አባል በመሆን በአካዴሚያዊ ልቀታቸውና በአስተማሪነት ብቃታቸውምፕሮፌሰርነትን አግኝተዋል፡፡ በርካታ ዘጋቢ ፊልሞችን ከመሥራት ባሻገር በተጨማሪም ዕውቅና በተቸራቸው የጥናትና ምርምር ኅትመቶች ላይም አሻራቸውን አሳርፈዋል፡፡ ከሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ በ1998 ዓ.ም. ከጡረታ እስተገለሉበት ድረስ ዓቢይ ሁለት ጊዜ የፉልብራይት ስኮላር በመሆን  በኢትዮጵያና በቡርኪናፋሶና ምርምር ሠርተዋል፡፡ አርባ ዓመታት የዘለቀው የሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ ቆይታቸው ቢያበቃም ልሂቅ ፕሮፌሰር (ፕሮፌሰር ኤሚራይተስ) ዓቢይ ፎርድ ግን ፊታቸውን ወደ ኢትዮጵያ በማዞር አዲሱን የሕይወታቸውን ምዕራፍ ያጠናከሩት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ኮሙዩኒኬሽን ድኅረ ምረቃ ፕሮግራም እንዲቋቋም ትልቅ ሚና በመጫወት ነው፡፡ የፋኩሊቲው ዲን በመሆንም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ማሠልጠኛ ተቋም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር እንዲቀላቀል በትጋት ሠርተዋል፡፡
 የፕሮፌሰር ዓቢይ ፎርድ ሌላው ላቅ ያለው ተግባራቸው ገጸ ታሪካቸው እንደሚያስረዳው፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን የሥነ ጥበባት ኮሌጅ ለማዋቀር እንዲያግዝ ወደ ተለያዩ ተቋማት የተደረጉትን የጉብኝት ጉዞዎች የልዑካን መሪ በመሆን መሥራታቸው፣ በ2000 ዓ.ም. ደግሞ በጓደኛቸውና የሐዋርድ ዩኒቨርሲቲ ባልደረባቸው በነበረው በስኩንዱር ቦጎሰያን ስም የተሰየመውን የኪነ ጥበባት ኮሌጅ እንዲቋቋም የመማክርት ጉባዔውንም ሆነ የማኔጅመንት ቡድኑን ሲመሩ መቆየታቸው ነው፡፡ በመቀጠልም ኵቤክ ከሚገኘው የካናዳ ፊልም ተቋም ጋር ያላሰለሰ ጥረትና ግንኙነት በመፍጠር ዘለቄታማ የሆነና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለፊልም ፕሮግራም መከፈት ተቋማዊ ሽርክና ለመክፈት እንዲቻል አድርገዋል፡፡
በ2004 ዓ.ም. ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አለ የሥነ ጥበባትና ዲዛይን የትምህርት ዘርፍ ሥር የመጀመሪያው የፊልም ፕሮዳክሽን ድኅረ ምረቃ ፕሮግራም እንዲቋቋም ፋና ወጊ ብቻ ሳይሆኑ ተጋባዥ ፕሮፌሰር በመሆንም የተለያዩ ኮርሶችን በመስጠት ለበርካታ ፊልም ሠሪዎች ተፅዕኖ ፈጣሪ ለመሆን መቻላቸውም ይወሳል፡፡
ሊቀ ጠበብቱ ዓቢይ ከሙያዊ ሕይወታቸውና ካበረከታቸው ሥራዎች ባሻገር የተዋጣላቸው የሙዚቃ ሰውም ነበሩ፡፡ በዚህም የተነሳ አዲስ አበባ ውስጥ ሙዚቃ በሚደገስበት ቦታ ሁሉ ዓቢይን ማግኘት የሠርክ ተግባር ነበር ይባላል፡፡ ዕውቅናን ካተረፉት ሙዚቀኞች ከነአበጋዙ ክብረ ወርቅ ሺዮታና ሔኖክ ተመስገን ጋር ሙዚቃ መጫወት ለልሂቁ ዓቢይ የሚዘወተር ነበር፡፡ በአሜሪካ ቆይታቸውም ትላልቅ ከበሮዎችን ጭነው ዋሽንግተን ዲሲ ከተማ በሚገኘው ማልኮም ኤክስ መናፈሻ  በኩባውያን ካሪቢያውያን እንዲሁም በምዕራብ አፍሪካውያን ሙዚቀኞች የታጀበ የሙዚቃ ድግስ ላይ መሳተፍም ለሙዚቃ ሰው ዓቢይ የዘወትር ልማድ እንደነበር ይነገራል፡፡
ዕውቀትን ልምድን ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ እንዲቻል ዋሽንግተን በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸውም ሆነ በአዲስ አበባ ባለው ስቱዲዮአቸው ሙዚቀኞችን፣ ገጣሚዎችንና አርቲስቶችን ለበርካታ ዓመታት በመጋበዝና መድረክ በማዘጋጀትም ይታወቃሉ፡፡ ‹‹ፒያኖ በመጫወት የሚያገኘው እርካታው እንዲሁም ኩንጋ እና ጀምቤ በመምታት የሚያወጣው ዜማ ፍጹም የሆነ ደስታን ያጎናፅፉት ነበር፤›› የሚሉት አድናቂዎቻቸው፡-
‹‹ረቂቋ ድምፅ ውቢቷ ሙዚቃ
 ዓቢይ ነው ጌጧ›› ብለው ገጥመውላቸዋል፡፡
የፕሮፌሰር ዓቢይ ልጅ ሚኒ ዓቢይና ልጇ ፋሲል እንዲሁም ኤልሳቤጥ ፎርድና ሌሎቹም የቤተሰቡን ውርስ በማስቀጠል ሕይወታቸውን ሙሉ ያከናወኑት ሠናይ ተግባር ሕያው ሆኖ እንዲዘልቅ የበኩላቸውን እንደሚያደርጉ ይታመናል፡፡
በግል ሕይወታቸውም ሆነ በሙያቸው የኢትዮጵያንና የካሪቢያን ሕዝቦችን ባህላዊ ማንነት ክብርና አንድነትን ያለማቋረጥ ሲያራምዱ የቆዩት ፕሮፌሰር ዓቢይ ፎርድ፣ በ83 ዓመታቸው በሀገረ አሜሪካ ያረፉት ረቡዕ ግንቦት 1 ቀን 2010 ዓ.ም. ነበር፡፡
ሥርዓተ ቀብራቸውም በካቶሊክ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ፍትሐት ከተደረገላቸው በኋላ በቅዱሳን ጴጥሮስ ወጳውሎስ የካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን መካነ መቃብር፣ ሐሙስ ግንቦት 9 ቀን በክብር ሲፈጸም የቀድሞው የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴና በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ ተወካይን ጨምሮ ታላላቅ ምሁራን፣ የጥበብ ሰዎችና አድናቂዎቻቸው ተገኝተዋል፡፡በተለያዩ ሥርዓተ ቀብሮች ላይ ሲገኙ የሚታዩት የመንግሥት ከፍተኛ ሹማምንት በዘጠና ዓመታት ውስጥ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ባለውለታ ከሆኑት የፎርድ ቤተሰቦች አንዱ በሆኑት ነፍስ ኄር ዓቢ ፎርድ ሥርዓተ ቀብር ለምን ሳይገኙ ቀሩ በማለት አስተያየት ከመሰንዘር ያልተመለሱም አሉ፡፡
‹‹እንግዲህ መቃብር ተግተህ ተማር
አፍሪቃና ሙዚቃን ጋዜጠኝነትና ፊልምን
ይዞልህ መጥቷልና ዓቢይ መምህር፤›› አሰኝቷል፡፡