Friday, November 10, 2017

ሰሎሞን ዴሬሳ! ሰሎሞን ዴሬሳ! ሰሎሞን ዴሬሳ!




በቅርቡ በ80 ዓመቱ ዜና ዕረፍቱ የተሰማው፣ በዘርፈ ብዙ ዕውቀቱ ተጠቃሽ የነበረው ዕውቁ ገጣሚና ጸሐፊ፣ ጋዜጠኛና የፍልስፍና መምህር ሰሎሞን ዴሬሳ ሥርዓተ ቀብሩ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚኔሶታ ከተማ በግብአተ እሳት መፈጸሙ ይታወሳል፡፡ ነፍስ ኄር ሰሎሞን ዴሬሳ ከ19 ዓመታት በፊት (መስከረም 1991 ዓ.ም.) ከሪፖርተር መጽሔት ከፍተኛ ሪፖርተር (በወቅቱ) ገዛኸኝ ጌታቸው ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር፡፡ በዚያ ቆይታው ስለትምህርቱ፣ ስለጓደኞቹ፣ ስለግጥሞቹ፣ ስለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፣ ስለመንፈሳዊነት፣ ስለኢትዮጵያውያንና ስለብሔረሰቦች፣ እንዲሁም ስለጋዜጠኝነት ሰፊ ሐተታ ሰጥቷል፡፡ ለዝክረ ነገር ይሆን ዘንድ በመጀመርያው ክፍል (በረቡዕ እትም) የሰሎሞን ዴሬሳ ዐውደ ሕይወት፣ የፈረንሳይ ሥነጽሑፍና እኔ፣ የሥነ ጽሑፍ አቋምና ጓደኛሞች የሚሉት መስተናገዳቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ እትም የመጨረሻው ክፍል ይቀርባል፡፡ 


ስለአሁኑ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ
የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ብዙ አልተከታተልኩትም፡፡ አንዳንድ እየተላከልኝ አነባለሁ፡፡ በቅርብ ያነበብኩት ‹‹እኛ›› የሚል የሴቶች ግጥም የወጣበትን መጽሐፍ ነው፡፡ አንዳንዶቹ በጣም በጣም ውብ የሆኑ ናቸው፤ ለኔ ማለቴ ነው፡፡ አንድ ወጣት የአጫጭር ልቦለድ ጸሐፊ የጻፈውንም አንብቤያለሁ፡፡
ጥሩውንም ብቻ ላለመናገር ያሰለቹኝንም ልንገርህ፡፡ በኮሎኔል መንግሥቱ ዘመነ መንግሥት ‹‹ጽጌረዳ ብዕር›› ርዕሱ ራሱ መልአክ ያወጣው ሳይሆን ከዚያ በታች ያወጣው እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡ እስኪ በሌላ ቋንቋ አስበው ‹‹The Rose Pen›› ስትል ምን አለው? የሚጻፈው በነጭ ብራና ላይ በጥቁር ቀለም ነው፡፡ ‹‹ጥቁር ብዕር›› ብለው ቢያወጡት ይሻላቸው ነበር፡፡ የማውቃቸው የነ አቶ ፀጋዬ ገብረመድኅን የነመንግሥቱ ለማ ግጥምም ነበረበት፡፡ ግን በዚያ ውስጥ የማስታውሰው አንድ መቶ አለቃ የጻፈውን ግጥም ብቻ ነው፡፡
የኔ ተቺነት ይህን ያህል ዋጋ ላይኖረው ይችላል፡፡ ይኼን ይኼን አንብበህ አልወደድኩትም ብትለኝ እቀበልሀለሁ፡፡ አንብቤው ግን ትምህርት የማትማርበት እዚህ ላይ ነው ስትለኝ እንለያያለን፡፡ እኔ አቋሜ ድሮም አሁንም እንደዚህ ነው፡፡ አንድ ጊዜ አንዲት ትንሽ መጽሐፍ እንደ አጋጣሚ ገዛኋትና አነበብኳት፣ ጸሐፊዋ መቅደስ ናት፤ የመጽሐፏን ስም ሳይሆን ግጥሞቹን ነው የማስታውሰው፡፡ እሷ ውስጥ ያሉ ግጥሞች በጣም ነኩኝ፡፡ አሁን ስናገር ከዚያ ወዲህ የተጻፉትን የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፎች አንብቤ አስቤበት እነዚህን መርጫለሁ ማለቴ አይደለም፤ ካጋጠሙኝ ማለቴ ነው፡፡ ‹‹Ethiopian Review›› ውስጥ አንዳንድ ግጥሞች ይወጣሉ፡፡ እስካሁን ድረስ ይህን ያህል የነሸጠኝ አላጋጠመኝም፡፡ አንደኛ ብዙዎቹ ግጥሞች ኢትዮጵያ እናቴ፣ እወዳታለሁ ዓይነት ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ኢትዮጵያን መውደድ ምን እንደሆነ ጥያቄ አነሳለሁ፡፡ ኢትዮጵያን መውደድ አይቻልም ማለቴ አይደለም፡፡ አዲስ እና ‹‹እንዴ ይኼም አለ እንዴ?›› አስብሎ ከተቀመጥኩበት ብድግ ያደረገኝ አላጋጠመኝም፡፡
አንዳንድ ዘፈኖች ላይ ግጥም የሚመስሉ የሰማኋቸው አሉ፡፡ ብዙ አላውቃትም በቅርብ ነው የሰማሁዋት የኩኩ ሰብስቤን፡፡ ግጥሞቹ የሷ ይሁኑ አይሁኑ አላውቅም ግን አንዳንዶቹ ስበውኛል፡፡ አንድ በገና የሚጫወት ዓለሙ አጋ የሚሉት አለ፤ የሱም ስበውኛል፡፡
በአጠቃላይ ለመናገር ከኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ጋር ያለኝ ግንኙነት ይኼንን ያህል አይደለም፤ ከአሜሪካም ጋር ያለኝ እንዲሁ ይኼንን ያህል አይደለም፡፡ ከዓለም ላይ የሚመጣውን እንደ አጋጣሚ ያገኘሁትን አነባለሁ፡፡ ግን የኢትዮጵያን ሥራዬ ብዬ አልተከታተልኩትም፡፡ የተከታተልኩት የራሴን በመጻፍ ብቻ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ በሚመለከት ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር አይታየኝም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የተጓደለ ነገር አለ፡፡ ተስፋ የሚያስቆርጥ ግን አይደለም፡፡ አንድ ማስታውሰውና አንዳንድ ጽሑፎችን ሳይ የተሰማኝ ነገር አለ፡፡ አሁን እንኳ ‹‹ብሌን›› የምትባል የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርን መጽሔት ሳነብ ስለመንግሥቱ ለማ በግድ ጎትቶ ማርክሲዝምና ሌኒንዝምን እንደሚከተል አድርጎ እንዲህ እንዲህ ተብሎ ወጥቷል፡፡ እኔ መንግሥቱ ለማ ስለማርኪስዝምና ሌኒንዝም ሲናገር ሰምቼ አላውቅም፡፡
በአጠቃላይ ለጥበብ ሰው መንግሥቱ ከላይ ዓላማ ሰጥቶት የሚሠራ ከሆነ የትም አይደርስም፡፡ ያን ጊዜ እንደዚያ ነበር፡፡ አንተ ወይም እኔ የምጽፈው መንገድ ላይ ስንሄድ፣ ዘመድ ሲሞት፣ ፍቅር ሲይዝ፣…ከዚያ ውስጥ ከሕይወት የሚወጣው ጽሑፍ ጽሑፍ ይሆናል፡፡ መንግሥት ከላይ ሆኖ በዚህ ነው የምሄደውና በዚህ ጻፍ ሲባል ሥነጽሑፍ ወደቀ ማለት ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ድሮ እንደዚህ ብዬ አንድ ችግር ደርሶ ነበር፡፡ አሁንም ደግሞ እንደገና እደግመዋለሁ፡፡ የግዕዝ ከዚያ ቀጥሎ የአማርኛ ምናልባት አላውቅም የትግርኛም ሳስበው ቅኔ ትምህርት ቤት መማር ስለተቻለ ለመጀመርያው ሃምሳ ዓመት ጠቅሞ ይሆናል፡፡ ከዚያ በኋላ የሚመጣው ሰንሰለት ነው የሚሆነው፡፡ እና በግምት በኮሎኔል መንግሥቱ ዘመን በማርክሲዝም ጊዜ ማርክሲዝምን እንደ ፍልስፍና አድርገው ቢያቀርቡት እሱ ራሱን የቻለ ነገር ነው፡፡ ግጥም፣ ሙዚቃና ሥዕል ውስጥ እናስገባው ሲሉ የመንፈስና የስሜት መደህየትን ነው የሚያስከትለው፡፡ በአንድ በኩል ደግሞ በአንዳንድ ቦታ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር በተለየ በድብቅ እየተፈናቀለ የሚወጣ አለ፡፡ እሱ ደግሞ በተለየ ለጸሐፊና ለባለኪነጥበብ ትልቅ ዕድለ ነው፡፡ ለሕይወቱ ሳይሆን ለሥራው፡፡ ለሕይወቱ ችግር ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሳያቸው ትንሽ እንደፈለጉ ለመጻፍ የተከፈተ ይመስለኛል፡፡ ይኼ በግምት ነው፡፡ እና እንደገና ሊያንሰራራ ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡
ሌላው ጥሩ መስሎ የሚታየኝ በቴሌቪዥንና በራዲዮ ሦስት ቋንቋ እሰማለሁ፡፡ ሌሎቹ ትንንሾቹም ቢሰሙ ጥሩ ነበር፡፡ ለጊዜው መተሻሸትንና ትንሽ አለመሰማማትን የሚያመጣ ይመስላል፡፡ ወደፊት ከቀጠለ ግን መዳቀል ይጀመራል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሁልጊዜ ደግሞ አዲስ ነገር የሚመጣው ከመዳቀል ነው፡፡ አዲስም የምንለው ድሮ የምናውቀው ስዳቀል ነው፡፡ ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ምንድነው የማያጽፈኝ? በሚሊዮን የሚቆጠሩ የግጥም መጽሐፎች አሉ፡፡ ይኔ እዚህ ውሰጥ ተጨምራ ጊዜ ማባከን ነው የሚል ስሜት ይመጣብኛል፡፡ ምክንያቱም አዲስ የሚባል ነገር የለም፡፡
እዚያ ላይ በጣም ተስፋ ያለ መስሎ ነው የሚታየኝ፡፡ ቋንቋዎች የግዳቸውን ይቀላቀላሉ፡፡ ከአሁን ወዲያ ጥሩ የሆነ አማርኛ፣ ጥሩ የሆነ ትግርኛ፣ ጥሩ የሆነ ኦሮምኛ ሳያስቸግር አይቀርም፡፡ ለጊዜው በመፋጠጥና በመሻኮት ይተያዩ ይሆናል፡፡ እሱ የፖለቲካዊና የመንግሥት ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ኃላፊ ነው፡፡ እንኳን የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ የኮሎኔል መንግሥቱ፣ የአፄ ኃይለሥላሴ፣ የዮሐንስ፣ የቴዎድሮስ መንግሥት ከአክሱምና ላሊበላም አልፏል፡፡ የማያልፈው የሕዝቡ ሕይወት ነው፡፡ ነገ ኢትዮጵያዊ መባል ይቀርና ለአገሩ አንድ ሌላ ስም ይወጣ ይሆናል፡፡ ይህ ምንም የሚለውጠው ነገር የለም፡፡ እዚህ ያለው ሕዝብ ከ100 ሺሕ ዓመት ጀምሮ የነበረ ሕዝብ ነው፡፡ ከውጭ እየመጣ ይዳቀልበታል፡፡ ግን መሠረቱ ያ ሕዝብ ነው፡፡ ያ ሕዝብ እስካሉ ድረስ መገናኝትና መተላለፍ፤ አንዱ አንዱ ጋር ፍቅር ወድቆ መኖር አለ፡፡ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ያሉት ጭብጦች ከአሥር ከአሥራ ሁለት አይበልጡም፡፡ በነርቨስ ሲስተማችን ውስጥ ኮረንቲ ሽቦ ካልኖረ እንደሌለ በፍጥረታችን ሽቦ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ለቅሶ፣ ፉከራ፣ ፍቅር፣ አድናቆት፣…እስካሉና የሰው ባህርይ እስካልተለወጠና ተገናኝተው የማያውቁ ወይም ደግሞ ግንኙነታቸው ቀረብ ያለም ሕዝቦች ተገናኝተው ተስማሙም ተሻኮቱም አዲስ ነገር ማውጣቱ አይቀርም፡፡
እኔ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውሰጥ በጣም ትልቅ ተስፋ ነው የሚታየኝ፡፡ በተለይ ለወጣቶች ከተጠቀሙበት፡፡ ከተጠቀሙበት ስልህ የሚጽፉት ከነሱ የሚጠበቀውን ሳይሆን እነሱ የሚፈልጉትን ከሆነ ማለቴ ነው፡፡ የሰው ፊት እየታየ ይኼ ይወደድልናል፣ ይኼ ይሸጥልናል ብለው የሚጽፉ በዓለም ላይ አሉ፡፡ ይበጀናል ካሉ ይቅናቸው፤ የሚያገኙትን ገንዘብ እግዜር ይመርቅላቸውና ይክበሩበት፡፡
ሌላ ሥነ ጽሑፍ የምለው የቴክኒክ፣ የስታይል፣ የተሰጥኦ ሳይሆን ያንተን ሳነበው አንተን ይመስለኛል ወይ? እንደዚህ ማድረግ ከቻሉ ትናንት ከወጣበት ዛሬና ነገ በብዛትና በበለጠ የማይወጣበት ምንም ምክንያት አይታየኝም፡፡ እኛንና ከኛ በኋላ የሚመጡትን፣ ከኛ በፊት የነበሩትን ምን ይለየናል? እኔ ለነበሩትም የማይገባ አድናቆት የለኝም፤ ለሚመጡትም ከነሱ ያነሰ አድናቆት የለኝም፡፡ እንደዚህ ነው የሚታየኝ፡፡
 አንዳንዶቹ ትንሽ በቆሙበት ከረር የሚሉ ነበሩ፡፡ አንዱ ዳኛቸው ወርቁ ነበር፡፡ እሱ በማርክሲዝም ጊዜ ይቀበል አይቀበል አላውቅም፡፡ ካልተቀበለ አደጋ ይደርስበታል ብዬ እፈራ ነበር፡፡ ተስፋዬ ደግሞ በአቋሙ ሳይሆን በቀልድ ችግር ይገጥመዋል ብዬ እፈራ ነበር፡፡ በጠቅላላው እነሱ ምልክቶች ይሁኑ እንጂ ለኢትዮጵያውያን ጸሐፊዎችና ሠዓሊዎች ችግር ይደርስባቸዋል ብዬ እገምት ነበር፡፡ ገብረክርስቶስ ደረሰበት፤ መጨረሻው ላይ ስለ አወጣጡ የሰማሁት ነገር አለ፡፡ እሱን አላጣራሁምና አልደግመውም፡፡ ችግር ደርሶበት ወጥቶ ታሞ በሚያሳዝን ሁኔታ አንድ ኢትዮጵያዊ በሌለበት ማንም በማያውቀው አገር ኦኮላሆማ በተባለ ቦታ ሞተ፡፡ አሜሪካ መሆኑንም አላውቅም ነበር፡፡ እኔ ያለሁት ሜኒሶታ እሱ ያለው ኦኮላሆማ ነበር፡፡ ብሰማና ባወቅ ኖሮ ቢያንስ ቢያንስ ሲሞት የሚያውቀው ፊት እያየ ይሞት ነበር፡፡ አሁን ሳስታውሰው በጣም ሆዴን ይበላኛል፡፡ የሰው ልጅ ዋና ስጦታው ከመጣው ማዕበል ጋር መውረድና መውጣት መቻል ነው፡፡ ብዙዎቹ ተረፉ፡፡ ይመስገን፡፡
ዮሐንስ አድማሱ በኔ ግምት የራሱ የከረረ አቋም ስለነበረው እፈራለት ነበር፡፡ እሱ ወደ ሶሻሊዝም ድሮውንም ዝንባሌ ነበረው፤ እነ ኃይሌ ፊዳ፣ እነመንግሥቱ ኃይለማርያም ገና ስማቸው ሳይሰማ፡፡ ግን የሁሉም ሰው ሶሻሊዝም አንድ አይደለም፡፡ እንደ ዮሐንስ ያለ ሰው ማርክስን ወይም ኤንግልስን አንብቦ እራሱ ውሳኔ ላይ የሚደርስ ሰው ነው ብዬ ነው የምገምተው፡፡ እና ከኋላ የመጡት ሁልጊዜ አጠቃላይ (Totalitarian) የሆነ አቋም በማንኛውም ፍልስፍና ወይም ሃይማኖት ላይ ያሰፍናሉ፡፡ ለምሳሌ በእስልምና ፋንዳመንታሊስት እንደሚባለው፣ እኔም አንተም ሙስሊሞች ሆነን እኔ ፋንዳሜንታሊስት ከሆንኩኝ ያንተ ተቀባይነት የለውም፡፡ እስልምናን እኔ እንደማምነው ብቻ ነው፤ ካላመንክ ግን እንገትህን ስጥ እልሃለሁ፡፡ ስለዚህ ለዮሐንስም እንደዚህ ዓይነት ነገር ይደርስበታል ብዬ እፈራ ነበር፡፡
እኔ እድለኛ ነኝ፡፡ ቀድሜ የትምህርት ዕድል በማግኘቴ ወጣሁ፡፡ እንዲያውም ችግሩ እንደዚህ ይሆናል ብዪ አልገመትኩም ነበር፡፡ እኔ ችግር ቢደርስብኝ ኖሮ በፖለቲካው ሳይሆን በጓደኞቼ ምክንያት ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ከሰው ጋር ያለኝን ግንኙነት እኔና አንተ ወደፊት ተገናኝተን ወዳጆች ከሆን ወዳጅነታችን ከኔ እምነት ይቀድማል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ ምክንያቱም የኔ እምነት የዛሬ 20 ዓመት የነበረውና ዛሬ ያለው በጣም ተራርቆ ሄዷል፡፡ እምነት ኃላፊ ነገር ነው፡፡ የአባቶቼ ነው ብለህ የክርስትናን ወይም የእስልምናን ሃይማኖት ልታጠብቅ ትችላለህ፡፡ ሃይማኖቶቹ ያልፋሉ ማለቴ አይደለም፤ አንተ ስለሃይማኖቶቹ ያለህ አስተያየትና የአስተማመን ባህርይ ካልሞትክ ይለወጣል፡፡ ሳይለወጥ ደግሞ 50 ዓመት 60 ዓመት ከደረሰ ሞተህ ነው የቆየኸው ማለት ነው፤ በኔ ግምት፡፡ ስለዚህ በጓደኞቼ ምክንያት ችግር ይደርስብኝ እንደሆነ ብዬ እገምት ነበር፡፡


 ስለመንፈሳዊነት
መንፈሳዊነት አሁን ያለውን የአገራችንን ማኅበራዊ ችግር ለመፍታት ሊጠቅመን ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ እንደሚታየኝ ለኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስና እስልምና እንደ ሃይማኖት ሆኖ አይታየኝም፡፡ ለኔ ማንነት (Identity) ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የማንነት መለያ የሆነ ሃይማኖት አለን፤ አይጎድለንም፡፡ ነገር ግን መንፈሳዊነት ይጎድለናል፡፡
መንፈሳዊነት ለእኔ የእምነት ጉዳይ አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር የማመንና ያለማመን አይደለም፡፡ መንፈሳዊነት መጨረሻው ራስን ማወቅና አንድ መሆን ነው፡፡ የሰው ልጅ አንድ ሆኖ አይፈጠርም፡፡ በቤተሰብ ውስጥ ትወለዳለህ፤ በአንድ በኩል ያባትህን በአንድ በኩል የናትህን ይዘህ ትወለዳለህ፡፡ በሌላ በኩል አሳዳጊዎችህን፣ ወንድሞችህን፣ ጓደኞችህን ሁሉ ትመስላለህ፡፡ መምህራንህን ትመስላለህ፡፡ ስለዚህ እኔ ከነዚህ ሁሉ እንደቡትቱ ጨርቅ ተሰብስቤ ተጣፍኩኝ፡፡ እና ለኔ መንፈሳዊነት የእምነት ነገር ሳይሆን ሳልሞት ምናልባት አንድ ሰሎሞን ሊፈጠር ይችላል ወይ? ይህ ሁልጊዜ የራስህ ፈንታ የራስህ ተግባር የራስህ ግዴታ ነው፡፡ መንፈሳዊነት በመጨረሻው ከብትንትኑ የተጣጣፈ ሰው አንድ ሆኖ ተሰብስቦ ይሞታል ወይ ነው? ይህ ደግሞ በእምነት ሳይሆን በጥረት ነው የሚገኘው፡፡ ለምሳሌ ዛሬ ስንገኛኝ ይህን ነገርኩህ፡፡ ምንያህል እውነት እንደነገርኩህ ማታ ሳስብበት ነው የማውቀው፡፡ የዛሬ ዓመት ስንገናኘና ስንነጋገር ከአሁኑ የበለጠ እውነተኛ ካልሆንኩኝ የቀረው ሁሉ እንዲሁ ለይሉኝታ ሆኖ ይታየኛል፡፡
ይሉኝታ አንድን ኅብረተሰብ አብሮ ለመኖር እንዲያስችል የግድ ያስፈልጋል፡፡ መከባበር የግድ ያስፈልጋል፡፡ ማኅበረሰቡን የሚያይዝ አንድ ነገር ነው፡፡ እዚያ ውስጥ መገኘት አለብኝ፡፡ የራሰን መንፈሳዊነትና ሐቀኝነት አግኝቻለሁና ካንተ ጋር ስንገኛኝ አንተ ሳትፈቅድልኝ እዘረጥጥሃለሁ ማለት አይደለም፡፡ እዚያ ውስጥ መገኘት አለብኝ፡፡ እሱ ውጭ ያለው ሰሎሞን ነው፡፡ ሰሎሞን ብቻውን ሲሆን ደግሞ አብሮት የሚሆን፣ ዋናው ሥራዬ ግዴታዬ ወደሞት እየተቃረብኩኝ ስሄድ (አይቀርምና) መንፈሳዊ ብዬ የምገምተው አንድ ሰሎሞን ሲገኝ ነው፡፡ እናቴ ንፁህ ብራና ወለደች፤ ያልተጻፈበት፡፡ እዚያ ብራና ላይ ሕይወት እንዳጋጠመኝ ተጻፈበት፡፡ በየቦታው በመዞር እኔነቴ ተበታተነ፡፡ የኔ ብቻ አይደለም፤ የሁሉም ሰው ነው፡፡ እና አንድ ሰሎሞንን ለመፍጠር በምጓዝበት ጊዜ ሐቀኝነት እየወጣ ይሄዳል፤ እያደገ ይሄዳል፡፡ መንገድ ላይ ስሄድ የማየውን ነገር ካለሁበት አየዋለሁ፡፡
እምነት አንድ ነገር ነው፤ ብዙ ጊዜ ካሳደጉ ካስተማሩን ሰዎች የተወረሰ፡፡ ወደ መንፈሳዊነት መሄድ ሌላ ነገር ነው፡፡ ግን በማንም እመን በማን የአንተን አንድ መሆን፣ መሰብሰብ፣ ሐቀኝነት እያሳደገ የሚሄድ መንገድ ነው፡፡ እኔ ወደ መንፈሳዊነት አዘነብላለሁ፡፡
በመንፈሳዊነት ደረጃ በተለይ የአይሁድ፣ የክርስቲያንና የእስላም የተያያዘ ይመስለኛል፡፡ አይሁዶች በእስላምም በክርስቲያንም ላይ ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ የሁሉም መጀመሪያዎች ግን የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ተከታዮች ሆነው ግብፅ ውስጥ መንነው የሚኖሩ መነኮሳት ናቸው ዋናዎቹ መምህራን፡፡ አንድ አካባቢ ስለነበሩ በዚያ ላይ ክርስቲያኖች ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ ወደ መጨረሻው ደግሞ የእስልምና ተፅዕኖ በግዴታ ሳይሆን በፍላጎት በክርስትናና በአይሁድ ላይ አርፏል፡፡ እንደሚባለው የነኢበን ዓረቢ የሱፌዎች ጽሑፍ ባይኖር ኖሮ የዳንቴ ዲቪና ኮሜዲያ አይጻፍም ነበር ተብሎ ይገመታል፡፡


ስለግጥሞቼ
በአጭሩ ለኔ እንደሚሰማኝ በስድ ንባብ የተጻፈው እንዲገባህ፣ በግጥም የተጻፈው እንዲሰማህ ነው፡፡ ገባህ አልገባህ ሁለተኛ ነገር ይመስለኛል፡፡ ግጥምን የማነበው እንዲገባኝ ሳይሆን እንድመሰጥበት ብቻ ነው፡፡
እኔ በተለይ በወጣትነቴ የጻፍኳቸው ለምሳሌ የዚህን ኮት እጀጌ አውልቄ ብስበው ውስጡ ወደ ውጭ ይገለበጣል፡፡ ልክ እንደዚያ ውስጤን ወደ ውጭ ለመገልበጥ ነው የሞከርኩት፡፡ አንዳንድ ወጣት ፊት ለፊት ይበጠብጣል፤ አንዳንድ ደግሞ ልዝብ ጥጋብ አለበት፡፡ እኔ ድሮ ልዝብ ጥጋብ ነበረብኝ፡፡
ለምሳሌ ‹‹ጉማላሎ››ን የጻፍኩት በዚያን ጊዜ ስለአማርኛ ዕድገት ብዙ የሚያወሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ እኔ ቋንቋን ላሳድግ ብሎ መነሳት ዛፍ ቶሎ አላደገምና እስቲ ጠዋት ጠዋት እየተነሳሁ ቶሎ ቶሎ ልሳበው እንደማለት ነው፡፡ እንደርሱ ስትስበው ሥሩ ከአፈር ይላቀቅና ይደርቃል እንጂ አያድግም፡፡ ውኃ አጠጥተኸው ፀሐይ ካገኘ ያድጋል፤ ያንተ ግዴታ የለበትም፡፡ እና ይህን ግጥም እንደ ቀልድና እንደ አመጽ ነበር የጻፍኩት፡ አዲስ አበባ ውስጥ ኖረህ በአማርኛ ግጥም ለመጻፍ ግፅዝ ማወቅ አያስፈልግህም፤ በግዕዝ አልጽፍም እኔ፡፡ እንግሊዝኛ ማወቅ አያስፈልግህም፡፡ አካባቢዬ ያለውን አማርኛ መስማት፣ አካባቢዬ ያለውን የሚታይ ነገር ማየት፣ ማየት ብቻ ሳይሆን ቆም ብዬ ምን ተሰማኝ? ብዬ መጠየቅን ይጨምራል፡፡ ብዙ ጊዜ የተሰማኝን ለመግለጽ እንኳን ያኔ አሁንም ይቸግረኛል፡፡ አሁንም ከተመቸኝ ይወጣል ብዬ የምገምተው ‹‹ብስለት›› የሚል የግጥም መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ያሉት ግጥሞች ደግሞ በኔ አኳኋን አንዳንዶቹ ይከራሉ፡፡ አንዳንዶቹ ግን የሚከሩት እንደነዚህ በስሜት ሳይሆን በሐሳብ ስፋት ነው፡፡ የድሮዎቹን የምወዳቸው አንተና እኔ አንድ ላይ ቁጭ ብለን እኔ አንብቤልህ ስትሰማቸው ነው፡፡ ደግሞ የተጻፉት በዓይን እንዲነበቡ ሳይሆን በድምፅ እንዲጋነኑ ነው፡፡ በድምፅ ተጋነው ሲወጡ፣ የኔ ምኞት ግን ያን ጊዜ እየሰማኝ ልለው የማልችለውን አንተ ከተሰማህ ካንተ የሚወጣው ስሜት ለኔ ምላሽ ይሆናል፡፡ እና ከአንባቢ ጋር እንደ አውራጅና እንደተቀባይ ይሆናል ብዬ ነበር የምገምተው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከፈረንጅ የተማርኩት ሳይሆን በራሴ ያለኝ ተሰጥኦ የአዋቂነት፣ የቋንቋ ችሎታ ሳይሆን ቆሜ ማየት መቻሌ ነው፡፡ ያየሁትን አምናለሁ፡፡
በአጠቃላይ ‹‹ጉማላሎ›› የተፃፈችው ማጣቀሻ /reference point/ ወደኋላ ተመልሶ ማግኘት ይህን ያህል ትልቅ ቁም ነገር ከሆነ እኔ እዚሁ እፈጥርልሃለሁ፤ ቀባጥሬ እንደማለት ነው፡፡ የነበረው ዋጋ የለውም ማለቴ አይደለም፡፡
በባህላችን አባቶችን ማክበር አንድ ነገር ነው፡፡ የተባልነውን ሁሉ ነገር መቀበል ግን ራስን እንደመካድ አድርጌ ነው የምቆጥረው፡፡ የግዕዝ ቅኔዎች እንዳሉ እንደ ግዕዝ ቅኔ ተማራቸው፣ ልክ የእንግሊዝኛውን እንደምታነበው አንብባቸው፡፡ ወደ አማርኛው ስትመጣ ግን እነሱ መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ማጠሪያና ማሰሪያ ከሆኑ ግን ነገር ተበላሸ ማለት ነው፡፡
የኔ ግጥሞች ምናልባት የሚያስቸግሩት አንደኛ ለአነባበቡ የኔን ድምፅ መፈለጉ እና እኔ እንዴት ነው የምሰማቸው በማለት መነሻው እኔ ስለሆንኩኝ ነው፡፡ ለዚህ ትንሽ ያስቸግሩ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የምስል ፈጠራው (Imagery) ጉዳይ ነው፡፡ የተጻፉት ታይተው እንዲያልፉ ነው፡፡ እኔ ሁሉም ነገር ኃላፊ መሆኑን በጣም አምናለሁ፡፡ ሁሉም ነገር ኃላፊ ነው፡፡
ሌላ ነገር ደግሞ ስለግጥም ስንነጋገር እኔ ላሊበላን በድንጋይ እንደተጻፈ ቅኔ ነው ያየሁት፡፡ በጣም ያስገረመኝና ለረዥም ሰዓት በቆምኩበት አድርቆ ያስቀረኝ ሥራው መሠራቱ አይደለም፡፡ ይሄ ላሊበላ የሚሉት ሰው (እንደኔና እንዳንተ አድርገህ ያየኸው እንደሆነ) ምን ሲያደርግ አሰበው? ከአንድ ተራራ ላይ ቆመህ ከሌላኛው ተራራ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ቆፍሬ አወጣለሁ ብሎ ማሰብን እንደ እብደት ነው ያየሁት፡፡ ይኼን ጤና ያለው ሰው አያስብም፡፡ በተለይ ጤና ያለው ኢትዮጵያዊ የሚያስበው እንዴት መሥራት እንደማይቻል ነው፡፡ እና ግጥም (ቅኔ) ፀሐፊው ዕድለኛ ከሆነ ከእንዲህ ያለ እብደት ነው የሚወጣው እንጂ ታዲያማ ማን ፈቅዶልኝ ምን አውቄ ነው የአማርኛ ግጥም የምጽፈው? ትንሽ ጥጋብ ያስፈልጋል፣ ትንሽ ልበ ደንዳናነትና ትንሽ እብደት ያስፈልገዋል፡፡ ላሊበላ የድንጋይ ቅኔ ነው ስልህ መሠረቴ ይኼ ነው፡፡
የአክሱምን ሐውልት ስታየው የሚያስገርመኝ መሠራቱ አይደለም፡፡ ሐሳቡ ነው እንጂ የሚጎላው ኢትዮጵያ ተነስታ፣ እኔ እንደ አሜሪካ ጨረቃ ላይ ሰው አወርዳለሁ ብትል ከባድ አይመስለኝም፡፡ ትንሽ ማቲማቲክስና ትንሽ ፊዚክስ ቢበዛ ለሰባት ዓመታት መማር ነው፡፡ እኔን የሚገርመኝ ምን ሲያደርጉ እንደ አሰቡት ነው፡፡ የአክሱምን ሐውልቶች ስታያቸው ማነው እዚያ ቆሞ መጀመሪያ ያሰበው? ምን አሳሰበው? አንድ ጊዜ ከታሰበ በኋላ ምንም ቁም ነገር አይደለም፤ ይኼን ያህልም አይጨፈርበትም፡፡ ማርስ መሄድ ሆነ፣ ህዋን ሰንጥቆ ማለፍ ወይም የአክሱምን ሐውልት ማቆም ወይም የላሊበላን አቢያተ ክርስቲያናት መጥረብ ምንም አይደለም፣ ይኼን ያህል ትልቅ ነገር አይደለም፡፡ መዶሻና መጥረቢያ ይዘህ መነሳት ብቻ ነው፡፡ የሚገርመው የመጀመሪያው እዚህ ድንጋይ አቆማለሁ ብሎ ያሰበው ሰውዬ ምን ሲያደርግ አሰበው? የሚለው ነው፡፡
እኔ ሁሉንም ግጥም ስፅፍ ይህን ሐሳብ ያስተላልፍልኝ ብዬ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ ‹‹ተዛወር ማኪና›› የምትል ግጥም አለች፡፡ የወንድሜ ልጅ ተወለደች፡፡ ግጥሙ ‹‹ለአይዳ›› ይላል፡፡ የተወለደችው ልጅ ባንድ በኩል ትግሬ ናት፡፡ ባንድ በኩል የወለጋ ኦሮሞ ነች፡፡ የተሰማኝ ስሜት የተራራቁ ባህሎች ድንገት አንድ ላይ ተወሳስበው በሷ ሥጋ ለበሱ፡፡ ያ ስሜት በቃል የሚሰማ አልነበረም፡፡ ድርሰት መፃፍ እችል ነበር፡፡ ታሪኩን ብፅፈው ምንም የምናገረው አዲስ ነገር የለም፡፡ አንድ ነገር እንዲሰማህ ለማድረግ ነበር፡፡ እና ታሪኩን ትቼው ስሜቱን ብቻ ብፅፈው ብዬ ታሪኩ ቀርቶ ስሜቱ ብቻ የቀረለት ግጥም ሆነ፡፡
አንዳንዶቹን ግጥሞች ስፅፍ ቃላት አልሰማም፤ ሐሳብም የለኝም፡፡ ከዚያ ነው የሚወጡት፡፡ እነሱን እንደዚያው እለቃቸዋለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ልክ እንደዚያች እንደ ለ2 ሺሕ 1 ዓ.ም. ፀሎት ያሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ አወራረድ የያዘ ሲሆን አወራረዱ ግን ትንሽ ለየት ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ስንል እኛ ሁላችንም መስጊድ እንደገባ ሰው እንስገድ የሚል ነው፡፡ ለኔ እንደሚታየኝ ለኢትዮጵያ ታሪክ መስገድ ለሰሎሞን ዴሬሳ እንደመስገድ ነው፡፡ ከውጭ የመጣ ሰው ይስገድለት እንጂ የራሴ ነው ምን አሰገደኝ፡፡ ከዚህ ታሪክ ነው የመጣሁት፤ አወራረዱ እንደሱ እንዲሆን ነው፡፡ ጥያቄ - የከበርንበትን ሳይሆን የተውነውን መጠየቅ፡፡ ምን ተፈጠረና ነው ላሊበላ ላስታ ውስጥ ብቻ ተፈጥሮ ሌላ ቦታ የቀረው? ለምን ርዝራዡ ቴክኒኩ ወጥቶ ለሰው መኖሪያ ቤት አልዋለም? እንዴት ነው ርዝራዥ ሳይደርሰን የቀረው? አክሱም ያን ያህል ተሠርቷል፡፡ የማያልፍ የለም፡፡ ከዚያ ከርዝራዡ እንዴት ለትግራይ ሕዝብ አልተረፈም? እንደሚመስለኝ ቁጭ ብለን ከማየት፣ ከማተኮር፣ ከመመሰጥ አብልጠን ትምህርት እንፈልጋለን፡፡ ሁልጊዜ ትምህርት የምትፈልግ ከሆንክ ተማሪ ሆነህ ነው የምትቀረው፡፡ ዘላለም ወጣትነትን ከፈለግህ አባት ሳትሆን ታልፋለህ፡፡ ይህን ለመቋቋም ጥያቄ መጠየቅ፡፡ ታሪክን፣ የአገርህን ባህል ዳኛ ሆነህ ቁጭ ብለህ ማንም ሳይሰይምህ ‹‹ተጠየቅ›› ካላልከው የእንጨት ሽበት ይለዋል አበሻ፡፡
ወደ መንፈሳዊው ልዙርና እኔ መንፈሳዊነት የምለው Mysticism የሚለውን ነውና ከዕለት ኃይማኖት ጋር ግንኙነትም ልዩነትም አለው፡፡ በሳይንሱም ያው ነው፡፡ ምሳሌዬን በሳይንሱ ላድርገው፤ አይንሽታይን እስኪመጣ ድረስ ዓለም (ፍጥረት) የስዊስ ሰዓት ሠሪ እንደሚሠራው ተሠርቶ አንድ ጊዜ ተጠምዝዞ ተለቋል፣ ከዚያ በኋላ ምንም የሚጨመር ነገር የለም ብሎ ተቀምጦ ነበር፡፡ ‹‹ከኒውተን ወዲያ እውቀት ንፍጥ ለመለቅለቅ ነው›› ብለው ቁጭ ያሉ ነበሩ፡፡ እንዲያውም አንድ የፈረንሳይ ፊዚስስት እንደዚህ ብሎ ጽፏል፡፡ አውሮፓውያን ጨርሰናል በቃ ብለው ቁጭ ብለው ነበር፡፡ አይንሽ ታይን ስዊትዘርላንድ ወስጥ የአንድ ቢሮ ተራ ፀሐፊ ነበር፤ መዝገብ አመላላሽ፡፡ ይህ ጊዜ ሰጥቶት ቁጭ ብሎ ራሱን መጠየቅ ጀመረ፡፡ እና Theory of Relativity እና በመጠኑም ቢሆን Quantum Mechanics ራሱን ከመጠየቅ ከሱው ነው የመጡት፡፡ አይንሽታይን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አልነበረም፡፡ የኒውተን ፊዚክስ ሚቶሎጂ (እምነት) ሆኖ ነበር እምነቱን ተጠየቅ የሚል ሰው መጣ፡፡ አይንሽታይን ተጠየቅ ባይለው ኖሮ ጨረቃ ላይ መሄድ አይታሰብም ነበር፡፡ አሁን ስለዩኒቨርስ የምናውቀው አይታሰብም ነበር፡፡ ነገ ደግሞ አይንሽታይንን ተጠየቅ የሚለው ሰው ካልመጣና ሳይንቲስቶች የሱ ተማሪ ብቻ ሆነው የቀሩ እንደሆነ ‹‹በአፄ ምኒልክ ጊዜ የደነቆረ ምኒልክ ይሙት እንዳለ ይሞታል›› እንደሚባለው ይሆናል፡፡


ስለኢትዮጵያውያን
እኔ ብዙ ቦታ ዞሬያለሁ፡፡ አፍሪካ፣ አሜሪካና አውሮፓ፡፡ ዘረኝነት እንዲመስልብኝ አልፈልግም፤ እኔ ዘረኛ አይደለሁም፡፡ ግን እንደ ኢትዮጵያውያን ብሩህ አዕምሮ ያለው ብዙ ቦታ አላጋጠመኝም፡፡ ዋጋ ከፍለን ነው ያ ብሩህ አዕምሮ የመጣው፡፡ በአማርኛ ምን እንደምንለው አላውቅም፡፡ Imagination በጣም ያንሰናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ለምንድነው በዓይናችን የምንጠቀመው? ደብረ ብርሃን ሥላሴ ስገባ የሥዕሎቹን ታሪክ ጥሩ አድርገው ነገሩኝ፡፡ ግን ሥዕሎቹን የሚያዩ እኔንም ለማየት ጊዜ የሰጡኝ አልመሰለኝም፡፡ የጊዮርጊስ ሥዕል ደራጎኑን ሲገድል ታሪክ አለው፤ እሱ ራሱን የቻለ የሚስብ ነገር ነው፡፡ ግን እሱን በአማርኛ ድርሰት በአንድና በሁለት ገጽ ማጠቃለል ይቻላል፡፡ እፊቴ ያለው ግን (ሥዕሉን ማን እንደሣለው ባላውቅም) ራሱን የቻለ ዓለም ነው፡፡ ከተጻፈም በኋላ ለማየት፣ ሳይጻፍም በፊት ለማተኮር የአዕምሮን ብሩህነት ከዓይን ማየት እናስቀድማለን፡፡ ይህ በጠቅላላው ትልቅ ችግር ይመስለኛል፤ ለሁላችንም፡፡
አክሱም ውስጥ የተሠሩት ከዚያ በኋላ አልተደገሙም፤ አልፎ ጎንደር ውስጥ ተሠሩ አልተደገሙም፤ ከዚያ በፊት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ተሠሩ አልተደገሙም፡፡ አይቀጥልም፡፡ እዚህ በየትኛውም ዓለም ቢሆን የሚደነቁ ከአንድ ተራራ የተቆረጡ 11 አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ አጠገቡ ያልተመረገ ቤት ታያለህ፡፡ የድህነት ጉዳይ አይደለም፡፡ ጭቃም አለ ሳርም አለ አንድ ላይ አቡክቶ ወር አስቀምጦ አንስቶ መምረግ ነው፡፡ ምክንያቱ የዓይን አለማየት ነው፡፡ ላሊበላ ያለ ሰው ሁሉ (ሌላውም) ቆም ብሎ (ታሪኩ በሚገባ ያውቀዋል) ላሊበላ ምን ነክቶት ነው ይኼን ያሰበው አይልም፡፡ እንደዚያ ሳስበው ከዕውቀት አልፎ ለኔ ምሰጣ ገባ፡፡ ምሰጣ ገባ ስልህ እንደሱ ዓይነት ስሜት ተሰምቶኝ ከሆነ በ19 ዓመቴ ፍቅር የያዘኝ ጊዜ ነው፡፡ አሁን የምጽፋቸው አንዳንድ ግጥሞች ስለሱም የሚያነሱ አሉ፡፡ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን እኔንም ጭምር ሳስበው (እኔ ደግሞ መላቀቅ የምፈልገው) ከተወለድኩበት ባህል ይኼ አዕምሮን ከዓይን ማስቀደም፤ አዕምሮን ከስሜት ማስቀደም ነው፡፡ አዕምሮማ ብቻ ብንሆን ኖሮ ሥጋ አንለብስም ነበረ፡፡ ኢቮሉሽን አራት ሚሊዮን ዓመት ታግሎ ዓይንን አይፈጥርም ነበር፡፡ ዓይን ማየቱ በጣም ስፔሻላይዝድ የሆነ የሚገርም ነገር ነው፡፡ ቆዳ እኮ ነው ምንም የለውም፡፡ ቆዳ ብርሃንን ማየቱና በዚያ አለመመሰጥ ምን ያህል ሳይንስ፣ ታሪክ ብንማር ተማሪዎች አድርጎ ያስቀረናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በተለይ በዚህ በኪነ ጥበብና በመንፈስ በኩል ትንሽ እብደት ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ ብዬ አምናለሁ፣ ማበድ ያስፈልጋል፡፡
ስለኢትዮጵያ ብሔረሰቦች
ስለዚህ ጉዳይ ከውጭ መጥቼ በአንድ ሳምንት ውስጥ ስለኢትዮጵያ ኤክስፐርት መሆን አልፈልግም፡፡ ግን ካየሁትና ከምሰማው አንድ የሚታየኝ ትግርኛ የሚናገሩ፣ አማርኛ የሚናገሩና ኦሮምኛ የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን እዚህ ያሉት እነሱ ብቻ ሆነው እንደሚናገሩ ይመስላል፡፡ በርካታ ቁጥራቸው ትንሽ የሆኑ ሕዝቦች መኖራቸውን የረሳነውና ውይይቱ በኛ መካከል ብቻ የሚካሄድ ይመስላል፡፡ እኔ ይኼ ጥጋብ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በቁጥር ብዛት እውነት አይቆምም፡፡ እውነቱ ደግሞ ቀላል ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ሕዝቦች አሉ፡፡
የኢትዮጵያን ታሪክ ያየኸው እንደሆነ በአንድ በኩል ያስገርማል ያሰኛል፡፡ ባንድ በኩል ደግሞ ያሳዝናል፡፡ ሥልጣኗን ተፈራርቀንባታል፡፡ ጎንደርን ኦሮሞዎች ገብተው ንጉሥ አንግሠው የሚገዘቡበት ጊዜ ነበር፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከተነሱ በኋላ ግዛቱ ወደ ጎንደር ሕዝብ ተመለሰ፡፡ አፄ ዮሐንስ ሲመጡ የትግራይ ዘመን ሆነ፡፡ ምኒልክ ሲመጡ የመሀል አገር የአማራው ግዛት ሆነ፡፡ አሁን ደግሞ ሥልጣኑን የያዙት ከውጭ እንደሚታየው ከትግራይ የመጡ ሰዎች ይመስላሉ፡፡ ሁሉም ኃላፊዎች ናቸው፡፡ መፈራረቅ አይቀርም፡፡ ነገ ማን እንደሚመጣ አላውቅም፡፡ ወይ አማራው ይሆናል ወይ ኦሮሞው ይሆናል፡፡ የሚመጣበትን መንገድ ደግሞ ልንገምት አንችልም፡፡ የማያልፈው ይኼ ግንኙነት ነው፡፡ የማያልፈው ደግሞ የኛ ግንኙነት ትልቅ ሆኖ፤ ከሌላው ዓለም የበለጠ የሚያምር ነገር ሆኖ ሳይሆን የመልክዓ ምድር አቀማመጣችን ነው፡፡
በአንድ በኩል ስታስበው ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጦ እኔ የትግራይ ሰው ነኝ፣ እኔ አማራ ነኝ ብሎ አፍ ሞልቶ መናገሩም አለማወቅ ይመስለኛል፡፡ በሴት አያቶቻችን በራፍ ላይ ማን እንዳለፈ ስንቶቻችን ነን የምናውቀው? የኔን ጥሩ ኦሮሞነት እግዚአብሔርና የሴት አያቶቼ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ የሁሉንም እንዲሁ፡፡ ጦር ባለፈ ቁጥር በመዋለድ፣ በንግድ በመገናኘት፤ ተቸግሮ ከአገር ወጥቶ ሌላ ቦታ በመኖር ይቀላቀላል፡፡
እኔ እናቴ ወለጋ ነበር የሚኖሩት፡፡ ያደግሁት ጋሼ መሐሪ፣ አባባ ደሳለኝ እያልኩኝ ከትግራይ፣ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከሸዋ፣ ከጉራጌ የመጡና እዚያ የሠፈሩትን እየጠራሁ ነው፡፡
ቅድም ስለግጥም እንደተናገርኩት የተባለውን ነገር በዚያው መደጋገም ሰውን ማሰልቸት፣ ራስንም መሰልቸት ነው፡፡ ሕይወትንም ጣዕምና ትርጓሜ ማሳጣት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የመጣው ሁሉ አማራ የገዛ እንደሆነ ሌላውን ቁልቁል ይዞ፣ ትግሬ የመጣ እንደሆነ ሌላውን ቁልቁል ይዞ እያልን ይህንን ስንት ሺሕ ዓመት ነው የምንደጋግመው፡፡ ምን ያህል እንለያያለን? ዘር በመቁጠር ደረጃ እኔ ምንም ችግር አይታየኝም፡፡ ምክንያቱም በራስህ ለመኩራት መጀመርያ በአባትህና በናትህ መኩራት አለብህ፡፡ እሱን እንደ ምግብ በልተኸው ነው ያንተ በራስህ መተማመን የሚመጣው፡፡ ለምሳሌ እኔ ከትግራይ ሰው ጋር ተገናኝቼ የማጫውትህ የትግራይን ትልቅነት ነው ቢለኝ በል ቁጭ በልና እንጨዋወት ነው የምለው፡፡ ከዚህ በላይ ምን ያጫውተኝ? የወለጋውን እንዲያጫውተኝ የሱ አይደለም፡፡ ከጎንደር የመጣ ሰው የጎንደርን ትልቅነት ላጫውትህ ሲለኝ ሌላ ምን ያጫውተኝ፡፡ ጎንደር የሄድኩት የዘመዶቼን ትልቅነት ለመስማት አይደለም፡፡ የነሱን ትልቅነት ለማየትና ለመስማት ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ስንት ኦሮሞ ከብት በነዳበት አገር እኔ የጠራሁ አማራ ነኝ፣ ወይም ንፁህ ትግሬ ነኝ ቢል አነጋገሩ ‹‹ለማያውቅሽ ታጠኝ›› ነው፡፡
በባህል በኩል፣ በጥበብ በኩል ምንም ዋጋ ያለው አይመስለኝም፡፡ አንዱ አንዱን መጫን ከየት ነው የመጣው ያልከኝ እንደሆነ ከድንጋጤ ነው፡፡ የሰው ልጅ ለሕይወት ያለውን መልስ ያየህ እንደሆነ ከድንጋጤ ነው የሚመጣው፡፡ ሁልጊዜ ጠዋት ተነስተን ዛሬ ምን እበላለሁ? ምን ለብሼ አድራለሁ? ብለህ መወራጨቱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በታሪካችን ሲጻፍ ያየኸው እንደሆነ ሁል ጊዜ እንደጀግንነት የሚታየው ጦርነት ብቻ ነው፡፡ እኔ ደግሞ የጦረኝነት ድፍራት ከድንጋጤ የሚመጣ ነው የሚመስለኝ፡፡ የጦርነት ጀግንነት ከድንጋጤ፣ ሞትን ከመሸሽ የተነሳ ነው፡፡ ወደፊት ለኢትዮጵያ የምመኝላት ካለ የማይደነግጡ፣ የሚያልፉ መሆናቸውን የሚቀበሉ ሰዎችን ነው፡፡ ለራሴ የምመኘውን ነው ለኢትዮጵያ ወይም ለኢትዮጵያዊ የምመኘው፡፡ ለራሴ የማልመኘውን አልመኝም፡፡ ለራሴ የምመኘው ፍርሃቴን፣ ኃላፊ መሆኔን ምንም አለመሆኔና መሬት፣ አፈር መሆኔን መቀበል መቻሌ ነው፡፡ የሰውን ልጅ የሚመራው በፍርሃትና ድንጋጤ ነው፡፡ ዕድገት ደግሞ ከዚያ ማለፍ ነው፡፡ በእኛ በኢትዮጵያውያን ታሪክ ጀግንነት ከጦርነት አልፎ በሕይወቴ ባየው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግድ ከሆነ ጊዜዬና ዕድሜዬ ቢሆን እዚያ ውጪ እንደተሠለፉ ልጆች መሠለፍና መሞት እችላለሁ፡፡ ይህ አንድ ዓይነት ግዴታን መቀበል ነው፤ ከዚያ የባሰ ጀግንነት ወይም አለመፍራት የእኔ ኃላፊ መሆን መቀበል ነው፤ በደራሲነትም ሆነ የሰው ልጅ በመሆን፡፡
ስለኢትዮጵያዊነት ሌላ ልናገር የምፈልገው ነገር አለ፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስመጣ ሰላምታ የሚል መጽሔት ተሰጠኝና አገላበጥኩ፡፡ እዚያ ውስጥ ካለማየት የመጣ አንድ ችግር ታየኝ፡፡ አዘጋጆቹም ጽሑፍ የሚያቀርቡትም ፈረንጆች ናቸው፡፡ እጅግ በጣም ገረመኝ፡፡ ለምሳሌ በዚያ ባነበብኩት መጽሔት ላይ ስለቡና ሥነ ሥርዓት የተጻፈ አለ፡፡ በእንግሊዛዊት የተጻፈ፡፡ ለምን አገራችንን ወደዱ አይደለም፡፡ ግን ስለቡና ሥነ ሥርዓት ከእነፍፁም መንፈሱ ቁርሱ ለማን እንደሚረጭ ጭምር የምናውቀው አገሬዎቹ ነን፡፡ ለእንግሊዛዊው ደግሞ አቀላጥፎ የሚጽፍ ሞልቷል፡፡ አሁን እንዲያውም አዲስ ትሪቢዩን፣ ዘሞኒተር፣ ዘሪፖርተር የሚሉ የግል ጋዜጦችም አያለሁ፡፡ እንግሊዝኛቸው ጥሩ ነው፡፡ ስለዚህ ቋንቋ ምክንያት አይሆንም፡፡ የእኔ የተቃውሞ ምንጭ ግን መጽሔቱ እንግዳ መቀበያ ኢትዮጵያን ማስተዋወቂያ በመሆኑ፣ እንግዳ ሲመጣ ኢትዮጵያውያንን የባህል ልብስ አልብሰህ እንዲቀበሉ ታደርጋለህ እንጂ፣ ፈረንጅን የባህል ልብስ አልብሰህ እንግዳ ተቀባይ አታደርግምና ስለአገሩ ለእንግዳ መቀበያ የሚፈጸመው አገሬው መሆኑ የግድ ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡ 


ስለ ጋዜጠኛነት
በእኛ ጊዜ ጋዜጠኛ ጉጉ ነው አዲስ ነገር ቆፍሮ ለማውጣት መንግሥትን የሚያስቆጣ ነገር ቢሠራም አለቆቹ አሳልፈው አይሰጡትም፡፡ ባለሥልጣናቱም በወቅቱ ጥፋት የተባለን ነገር የሠራ ሠራተኛን በኋላ ጥሩ ነገር ከሠራ በደስታ ይቀበሉታል፡፡ አንድ ጊዜ አሳምነው ገብረ ወልድ ንጉሡን የሚያበሳጭ ሥራ ይሠራል፤ በአስቸኳይ እንዲባረር ይወሰንበታል፡፡ በወቅቱ ግን ተጨቃጭቀን በግማሽ ደመወዝ እኔ ቢሮ እንዲቀመጥ አደረግን፡፡
ያን ጊዜ የማስታወቂያ ቱሪዝም ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ጌታቸው መካሻ ቢሮዬ መጥተው ንጉሡ ወደ አሜሪካ ሊሄዱ ነውና አብሯቸው የሚሄድ ጋዜጠኛ መድብ ሲሉኝ ከአሳምነው ገብረ ወልድ በላይ ብቁ የለምና እሱ ነው መሄድ ያለበት አልኩ፡፡ ሁኔታው ቢያስቸግራቸውም ከብዙ መነጋገር በኋላ ዶ/ር ጌታቸው ሐሳቡን ተቀብለው ለንጉሡ ነገሩ፡፡ ንጉሡም አልተቃወሙም፡፡ ሲመለስ ጥሩ ፕሮግራም ሠራ፣ ንጉሡም ወደዱት፡፡ ስለዚህ ወዲያው ወደ ሥራው እንዲመለስ አዘዘ፡፡ የዚህ ዓይነት ነገር በብርሃኑ ዘርይሁን ላይ ተከስቷል፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ስለ አፄ ቴዎድሮስ ሲጽፍ፣ ‹‹አፄ ቴዎድሮስ የሰሎሞን ዘር ነኝ፡፡ እስራኤላዊ ነኝ አይሉም፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ነው የሚሉት፤›› የሚል ሐሳብ አሠፈረ፡፡ ንጉሡም ሹማምንቶቹም በዚህ ተቆጥተው ብርሃኑ ይባረር ተባለ፡፡ እኛ ግን አይሆንም ብለን ብዕሩ ጥሩ ስለሆነ ሬዲዮ ይሥራ አልንና አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሥር ደበቅነው አይታይም ብለን አይደለም ግን ሰው የሚንቀሳቀሰው በቅንነት ስለነበረ የሚያሳጣ አልነበረም፡፡
ሌላም ጉዳይ አለ፤ ነፃነት፡፡ ያን ጊዜ ንጉሡን ላለማበሳጨት ራሳችንን ሳንሱር እናደርጋለን እንጂ ሌላ የለም፡፡ ባለሥልጣናትንም ለማግኘት አያስቸግርም፤ ጋዜጠኛ የታፈረ የተከበረ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ወደ ቤተ መንግሥት ለሥራ ስንሄድ የቤተ መንግሥት ዘበኛ ቁሙ፣ ተፈተሹ ሲለን መኪናችንን አዙረን ወደ መጣንበት ሄድን፡፡ ትንሽ ተጨዋውተን ወደ ቤተ መንግሥት ስልክ ደውለን ለሥራ መጥተን ነበር የቤተ መንግሥት ጠባቂዎች ስላንገላቱን ተመልሰናል አልናቸው፡፡ ኑ ተባልንና ስንሄድ የቤተ መንግሥቱ በር ተከፍቶ ጠበቀን፣ ሳንፈተሽ ገባን ሳንፈተሽ ወጣን፡፡ ይኼ ዛሬ ሊሆን አይችልም፡፡ ግን ይህን ያህል ለመጥገብ አቅም ያላችሁ አይመስለኝም፡፡
ማሳረጊያ
በዚህ በእስካሁኑ ሕይወቴ ቁልቁልም ወደ ላይ የማየው፤ ከቀረብኩት ደግሞ የማላፈቅረው ሰው እንደሌለ ተረድቻለሁ፡፡ በተጨማሪም ሰውን ሳትዳኘው ስለራሱ ሲያወራ ብታዳምጠው ስለአንተ እያወራ ነው የሚመስልህ፡፡ ሲሆን የሠራሁትን አለዚያም ባልሠራውም ያሰብኩትን ነው የሚያወራኝ፡፡




No comments:

Post a Comment