ከ150 ዓመታት በፊት በአለቃ ዘነብ የተጻፈው ‹‹መጽሐፍ ጨዋታ›› ከማብራሪያና ከቃላት መፍቻ ጋር ታተመ፡፡
የኅትመት ብርሃኑን ነሐሴ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ያየው አዲሱ እትም የአለቃ ዘነብን የሕይወት ታሪክ፣ የድርሰቱን ይዘት፣ የመረጃ ምንጮች፣ የቃላት መፍቻና የጨዋታ ማጣቀሻዎችን  በ79 ገጾች ይዟል፡፡  
አፄ ቴዎድሮስ ዘመን በ1856 ዓ.ም. የተጻፈው መጽሐፈ ጨዋታ፣     ‹‹ውብ የአማርኛ ወግ መጽሐፍ ነው›› ይለዋል አንድምታ መጻሕፍት፡፡ ከወጉ ለዓይነት በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን እንዲህ አሥፍሯል፡፡
‹‹ገበሬ በቅልጥሙ ቅባቱን ይዞት ይኖራል፡፡ ገና ኋላ ለቁርበቱ ማልፊያ ይሆነኛል ብሎ ነውን? ያዳምም ልጆች እንደዚሁ ለተዝካራቸው ያኖራሉ፡፡ ምነው ዓይናቸው ሲያይ ቢሰጡት ይኰነኑ ይሆን?››
በአንድምታ መጻሕፍት አዘጋጅነትና አሳታሚነት የቀረበው መጽሐፈ ጨዋታ፣   ቀደም ባሉት 75 ዓመታት ውስጥ በተለያዩ አሳታሚዎች ‹‹መጽሐፍ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ›› በሚል መጠርያ መታተሙ ይታወቃል፡፡
አዲሱ ‹‹መጽሐፈ ጨዋታ›› ዋጋው ሃምሳ ብር ነው፡፡