Friday, September 15, 2017

ሁለት ሺሕ አሥር እንዴት ገባ? በ‹‹ኢትዮጵያ ቀን›› ኢትዮጵያ በማታውቀው ከሌሊቱ 6 ሰዓት አዲሱ ዓመት ‹‹ገባ›› ተብሏል

  • በ‹‹ኢትዮጵያ ቀን›› ኢትዮጵያ በማታውቀው ከሌሊቱ 6 ሰዓት አዲሱ ዓመት ‹‹ገባ›› ተብሏል
  • በሚሌኒየም ስሌት መደነጋገሩ ቀጥሏል
  • https://www.ethiopianreporter.com
 13 Sep, 2017 (3/1/10)
በሔኖክ ያሬድ
‹‹መስከረም ጠባ፡፡ የመስከረም ጮራ ዕንቁጣጣሽ ብላ ተግ አለች፡፡ ልጃገረዶች ሳዱላቸውን አሳመሩ፡፡ አደስ ተቀቡ፡፡ እንሶስላ ሞቁ፡፡ ወንዝ ወረዱ፡፡ ቄጤማ ለቀሙ፡፡ ፀአዳ ልብሳቸውን ለብሰው፣ አሽንክታባቸውን አጥልቀው፣ ‹አበባዬ ሆይ - ለምለም› በማለት ተሰብስበው ብቅ አሉ - እንደ ጮራይቱ፡፡ የወርሀ መስከረም ብሩህ ተስፋና ስሜት በምድሪቱ አስተጋባ፡፡ ጠፍ እያለ መጣ ምድሩ፡፡ ወንዙም እየጠራ፡፡ ኩል መሰለ ሰማዩ፡፡ ሜዳው፣ ጋራው፣ ሸንተረሩ ወርቃማ የአደይ አበባ ካባ ለበሰ፡፡ ደመራ ተደመረ፡፡ ተቀጣጠለ ችቦ፡፡ ‹ኢዮሃ አበባዬ - መስከረም ጠባዬ› ተባለ፡፡››
ይህ ሥዕላዊ ሐተታ ደራሲው በዓሉ ግርማ ከ38 ዓመት በፊት፣ በ1972 ዓ.ም. ባሳተመው ‹‹ደራሲው›› በተሰኘው ልቦለዱ የመስከረምን ድባብ የገለፀበት ነበር፡፡ አዲሱ ዓመት በመጣ ቁጥር  የሚታወስ ነው፡፡
የዘንድሮውን 2010 ዓመት አቀባበል ከወትሮው የተለየ ነበር፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ከነሐሴ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዋዜማው ጳጉሜን 5 ቀን ድረስ በልዩ ልዩ ስያሜዎችና መሪ ቃላት ተከብሮ አልፏል፡፡ በቅድሚያ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት ነን›› የሚል መሪ ቃል የነበረውና መጨረሻ ላይ  ‹‹መጪው ዘመን ለኢትዮጵያ ከፍታ ነው›› በሚል የተከበረው ‹‹የኢትዮጵያ ቀን›› የአሠርቱ ቀናት ማሠሪያ መቋጫ ነበር፡፡
ዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ የባህል ድርጅት)  ልዩ ስለሆነው የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር፣ አዲሱ ዓመት ዘመን የሚለወጥበት ንጋት 12 ሰዓት ላይ እንጂ እንደ ምዕራባውያን እኩለ ሌሊት (6 ሰዓት) ስላለመሆኑ፣ ያመቱ መነሻ መስከረም 1 ቅዱስ ዮሐንስ- ዕለተ ዮሐንስ መባሉንና ሌሎች የቀመር ጓዞችን የያዘውን ጥንታዊ የባሕረ ሐሳብ ብራናን (መጽሐፍ) በዓለም ጽሑፍ ቅርስነት ለመመዝገብ በሚመክርበት ጊዜ ላይ ተደርሶ፣ ሚዲያዎችና የሚመለከታቸው አካላት ያለዕውቀት ቅርሱንና ውርሱን እየጣሉት ይገኛሉ፡፡
ከኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ ጋር የማይተዋወቁት፣ እኩለ ሌሊት ላይ ‹‹አዲስ ዓመት ገባ›› እያሉ ማደናገራቸውን ዓመት ዓመት መቀጠላቸውን ሃይ የሚልም ጠፍቷል፡፡ አዲሱን 2010 ዓ.ም. ለመቀበል በዋዜማው ጳጉሜን 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚሌኒየም አዳራሽ የኢትዮጵያ ቀንና የአሥሩ ቀናት አከባበር ማጠቃለያ ጭምር ሲከበር፣ ከባሕረ ሐሳብ ጋር የማይተዋወቁት ‹‹አርቲስቶቹ›› እኩለ ሌሊት ላይ አዲሱ ዓመት ያለ ዕውቀት በድፍረት ‹‹ገባ›› ብለዋል፡፡ ርችትም ተተኩሷል፡፡ እነርሱን የተከተለው በአዲስ አበባ በሚገኝ አንድ የሬዲዮ ጣቢያም ‹‹የራሷን የቀን አቆጣጠር የምትከተለው ኢትዮጵያ፣ የ2010 አዲስ ዓመቷን እኩለ ለሊት 6:00 ሰዓት ላይ ተቀብላለች፤›› ብሎ በድምፅም በጽሑፍም አስፍሮታል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አዲሱ ዓመት የሚገባው የገባው ማለዳ 12 ሰዓት መሆኑን ለማብሰር እንደሁሌው 21 ጊዜ መድፉን ተኩሷል፡፡
የሚሌኒየሙ ነገር
ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ የ2010 ዓ.ም. አዲስ ዓመት አቀባበልን አስመልክቶ በዋዜማው ጳጉሜን 5 ቀን በብሔራዊ ቤተመንግሥት መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ፣ ኢትዮጵያ ‹‹ሁለተኛውን ሚሌኒየም ከተቀበለች 10 ዓመት›› እንደሆናት ሲገልጹ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሚሌኒየም አዳራሽ በዋዜማው በተዘጋጀው መሰናዶ ዓመቱ በሦስተኛው የኢትዮጵያ ሚሌኒየም ላይ እንደሚገኝ እንዲህ አውስተዋል፡፡
‹‹ሦስተኛው ሚሌኒየም ከተጀመረ አሥረኛ ዓመት ለሆነው የዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል እንኳን አደረሳችሁ››፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ሦስተኛው ሚሌኒየም ከገባበት 2000 ዓ.ም. ጀምሮ…›› ብለው 10 ዓመት 2009 ዓ.ም. እንዳበቃ ተናግረዋል፡፡ ሦስቱም ርዕሰ ብሔሩና ርዕሰ መስተዳድሩ ከሚኒስትሩ ጋር ሦስት ዓይነት መረጃዎችን አስተላልፈዋል፡፡  ነገር ግን ከኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ አንፃር ትክክሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አገላለጽ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ያመለከቱት ሁለተኛው የኢትዮጵያ ሚሌኒየም የገባው ግን በ1001 ዓ.ም. ከአንድ ሺሕ ዓመት በፊት ነበር፡፡
ትንሣኤ ያገኘው የእንግጫ ነቀላና የከሴ አጨዳ
እንግጫ የሣር ዓይነት ነው፡፡ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ልጃገረዶች መስክ ወርደው የሚነቅሉት ነው፡፡ የእንቁጣጣሽ ብሥራት ነጋሪ ነው፡፡ በዘመን መለወጫ ዋዜማ እንግጫ ሳር በልጆች እየተነቀለ እንደቋጨራ እየተጎነጎነ ጣራ ላይ ተወርውሮ ያድርና ጠዋት ላይ ለዘመን መለወጫ እየተጎነጎነ ራስ ላይ፣ ቡሃቃ አንገት ላይና ሌማት ክዳን ላይ ይታሰራል፡፡ ቡሃቃ እና ሌማት ላይ የመታሰሩ ምልክትነት ለረድኤትና ለበረከት ሲባል የሚደረግ ነው፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባሳተመው ‹‹በሰሜን ሸዋ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች የተመዘገቡ የኢንታጀብል ባህላዊ ቅርሶች›› መድበል ላይ እንደተገለጸው፣ እንግጫ ነቀላ ዘመን ሲለወጥ የሚከወን ባህላዊ ሥራት ነው፡፡ በዋዜማው ያላገቡ ሴቶች ወደ መስክ ወርደው እንግጫ ይቆርጣሉ፡፡ ምሽቱን ደግሞ እንግጫውን ሲጎነጉኑ ይቆያሉ፡፡ ሲነጋ ደግሞ በጠዋት ተጠራርተው በመሰባሰብ በየሰው ቤት እየዞሩ የተጎነጎነው እንግጫ ከቤቱ ምሰሶ ላይ ያስራሉ፡፡
እስከ ዓምና ድረስ በከተሞች አካባቢ እንግጫ ነቀላው እየቀረ አበባዮሽ የሚለው ጨዋታ በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ የጎጃም ኅብረተሰብ ነባሩ ትውፊት በከተሞች ቀረብን፣ ተረት ሊሆንብን ነው የሚለው አባባል የሚቀይር ድርጊት በ2010 ዓ.ም. ዋዜማ አስተናግደዋል፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አማካይነት ነባሩ የእንግጫ ነቀላና የከሴ አጨዳ የልጃገረዶች ባህላዊ ክዋኔ  በደብረ ማርቆስ ከተማ በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አደባባይ ጳጉሜን 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በታላቅ ሥነ ሥርዓት አከናውነዋል፡፡
የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ውድ ዓለም አልማው፣ በዞኑ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ቢኖሩም ጠብቆና ተንከባክቦ ለትውልድ ከማስተላለፍ ረገድ ውስንነት እንዳለ አመልክተዋል፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ ብለው የጠቀሱት ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ የሚከበረው የእንግጫ ነቀላና የከሴ አጨዳ ባህል ከጥቂት የገጠር ቀበሌዎች በስተቀር እየተረሳ መምጣቱን ነው።
እንደሳቸው አገላለጽ፣ የእንግጫ ለቀማና የከሴ አጨዳ ክዋኔዎች እስከ መስከረም አንድ ድረስ ጎረምሶችና ልጃገረዶች ተሰባስበው ልዩ ልዩ ዘፈኖችን በመዝፈን በየቤቱ እየተዘዋወሩ ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልክት የሚያስተላልፉባቸው ናቸው። ኢዜአ በዘገበው ገለፃቸውም፣ እንግጫ ለቀማ በወንድ ወጣቶች የሚከወን ሲሆን፣ ከሴ ደግሞ በልጃገረዶች ታጭዶ ከአደይ አበባ ጋር አብሮ ተጎንጉኖ በጭፈራ ታጅቦ ለኅብረተሰቡ የሚሰጥበት ክዋኔ ነው።
የአዲስ ዓመት የምሥራች ምልክት የሆነው እንግጫ ነቀላው በዜማ የሚታጀብ ነው፡፡ 
‹‹እቴ አበባዬ ነሽ
አደይ ተክለሻል
አደይ ተቀምጠሻል
ባሶና ሊበን
አዋጋው ብለሻል
ቦሶና ሊበን
ምነው ማዋጋትሽ
አንዱ አይበቃም ወይ››
በዚህ ጊዜ ወንዶች ደግሞ ያዘጋጁትን ዳቦት (የችቦ ስም) በእሳት ለኩሰው እያበሩ በመምጣት እንግጫ ለሚጎነጉኑት ሴቶች ያበሩላቸዋል፡፡ ዳቦታቸውን እያበሩ ወደ ሴቶቹ በሚያመሩበት ጊዜ የሚያዜሙት ዜማ አላቸው፡፡
‹‹ኢዮሃ ኢዮሃ
የቅዱስ ዮሐንስ
የመስቀል የመስቀል
አሰፉልኝ ሱሪ
ኢዮሃ›› በማለት ያዜማሉ፡፡
ልጃገረዶቹ ወደየሰው ቤት ሲሄዱ ሎሚ ይሰጣቸው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን የእንግጫው ሴቶች ራሳቸው ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› እያሉ ሎሚ ሲሰጡ ገንዘብ ይሰጣቸዋል ይላል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን መድበል፡፡
የዘመን አዋጅ
መስከረም አንድ ቀን ያለው ልዩ ነገር የዘመኑን መለወጥ አስመልክቶ የባሕረ ሐሳብ አዋጁ ይነገራል፡፡ በዓመቱ ውስጥ በዓል የሚውልበት፣ ጾም የሚገባባትን ቀን መምህራኑ እያሰሉ ይናገሩታል፡፡ ዓመቱን በፀሐይና በጨረቃ፣ በዓመተ ዓለም ለምዕመናኑ ይገልጹታል፡፡ ማህሌቱ ካበቃ በኋላ መምህሩ ካባ ደርቦ መስቀል ይዞ ዘመኑን ያውጃል፣ የባሕረ ሐሳቡን ጥንተ ታሪክ ይናገራል፡፡ የዘንድሮው አዲስ ዓመት 2010 ዓ.ም.  በአራት ዓመቱ የሚመላለሰውና ‹‹ዐውደ ጳጉሜን››/ ‹‹ዐውደ ወንጌላውያን›› የሚባለው ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡  2010 ለ4 ተካፍሎ 502 ደርሶ ቀሪው 2 መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዘመኑ የማርቆስ መሆኑ ያመለክታል፡፡ (1 ከቀረ ማቴዎስ፣ 3 ከቀረ ሉቃስ፣ እኩል ከሆነ ዮሐንስ ይሆናል፡፡ ዘንድሮ የዓለም ፍጥረት መነሻ በሆነው በዓመተ ዓለም ሲቆጠር 7510 ዓመተ ዓለም መሆኑና ስምንተኛው ሺሕ ከገባ 509 ዓመት ማለፉንና 510ኛ ዓመት ላይ መገኘቱን ስሌቱ ያሳያል፡፡
እንቁጣጣሽ በምን ወቅት ላይ ትገኛለች?
መስከረም 1 በክረምት ውስጥ የምትገኝ ያመት መነሻ ናት፡፡ ሰኔ 26 ቀን የገባው ክረምት የሚወጣው መስከረም 25 ቀን ላይ ነው፡፡ የስድስተኛው ምታመት የነገረ መለኮት ሊቁ (ቲኦሎጊያን)፣ መዝሙረኛውና ዜማ ቀማሪው ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፈ ድጓው ‹‹ኀለፈ ክረምቱ ጸገዩ ጽጌያት ቆመ በረከት!›› - ክረምቱ አለፈ አበቦችም ፈኩ፣ በረከትም ቆመ ይለናል፡፡
የዛሬው ቀን መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በክረምት ውስጥ ይገኛል፡፡  እንደ ቅዱስ ያሬድ አመዳደብ፣ በውስጡም ልዩ ልዩ ንኡሳን ክፍሎች አሉት፡፡ ከነሱም መካከል የነሐሴ መጨረሻና የጳጉሜን ሳምንት ‹‹ጎሕ፣ ጽባሕ››- ወጋገን፣ ንጋት ይለዋል፡፡ ይህም ያዲስ ዘመን መስከረም የሚጠባበት ጊዜ መድረሱን አመላካች ነው፡፡
ሌላው ንኡስ ክፍል ከዓመት አውራ መነሻ (ርእሰ ዐውደ ዓመት) መስከረም 1 ቀን እስከ መስከረም 7 (8) ቀን ያለው ‹‹ዮሐንስ›› ሲባል፣ ከመስከረም 9 እስከ 15 ዘመነ ፍሬ ይባላል፡፡ ‹‹ዮሐንስ›› የሚለው ቃል የተወሰደው በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ከሚገኘውና ኢየሱስ ክርስቶስን ካጠመቀው የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ ነው፡፡
መስከረም 1 ቀን ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕለተ ዮሐንስ መባሉ በተምሳሌታዊ ፍች የመጣ ነው፡፡ ከአሮጌው ብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን፣ ወደ ዓመተ ምሕረት መሸጋገሪያ ላይ የመጣው መንገድ ጠራጊው ዮሐንስ ስለሆነ፤ ባህሉ/ ትውፊቱ ካሮጌው ዓመት ወዳዲሱ መሸጋገሪያዋን ዕለት፣ መስከረም 1 ቀንን በዘይቤ ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› ‹‹ዕለተ ዮሐንስ›› እያለ ይጠራዋል፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ ባገልግሎት ላይ ይገኛል፡፡ ዩኔስኮ የባሕረ ሐሳባችሁን ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› አውቄዋለሁ፣ አክብሬዋለሁ ሲል እዚህ ግን ቦታ እያጣ ነው፡፡

No comments:

Post a Comment