08 Sep, 2017
በኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር/ ባሕረ ሐሳብ መሠረት 2010 ዓመተ ምሕረትና 7510 ዓመተ ዓለም በፀሐይ
አቆጣጠር፣ 2018 በፀሐይና በጨረቃ ጥምር አቆጣጠር ሰኞ፣ መስከረም 1 ንጋት 12 ሰዓት ላይ ይገባል፡፡ ባህሉንና
ትውፊቱን የሚጠብቀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንደሁሌው በዕለቱ በአዲስ አበባ ንጋት 12 ሰዓት ላይ ዘመኑ
መለወጡን 12 ጊዜ መድፍ በመተኮስ እንደሚያበስር ይጠበቃል፡፡ (እኩለ ሌሊት ላይ የሚለወጥ የኢትዮጵያ ዘመን
እንደሌለን ልብ ይሏል)::
እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትም ከዘመነ ማቴዎስ (2009) ወደ ዘመነ ማርቆስ (2010)፣ ዕለተ
ዮሐንስ በሚባለው መስከረም 1 ቀን ሽግግር ይደረጋል፡፡ ሌሊቱ 16 በጨረቃም መስከረም 20 ቀን 2018 ዓ.ም.፣
እንደ ኢትዮጵያ እስልምና ትውፊትም ዕለቱ በዙልኻጅ 19 ቀን 1438 ዓመተ ሒጅራ፣ እንደ ኢትዮጵያ አይሁድ (ቤተ
እስራኤል) ትውፊትም በኢሉል 20 ቀን 5777 ዓመተ ፍጥረት አዲሱ ዓመት ገብቷል፡፡
በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ መሠረት የፀሐይ ዓመት ሰኞ ይግባ እንጂ ዓመቷን በ354 ቀናት የምትፈጽመው የኢትዮጵያ
የጨረቃ አዲስ ዓመት ‹‹መስከረም 1 ቀን›› የገባው ጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ በ2010 ዓ.ም.
ፋሲካ መጋቢት 30 ቀን የሚከበረው፣ የአይሁድ አዲስ ዓመት ሮሽ ሃሻናኅ (በዓለ መጥቅዕ) መስከረም 11 ቀን
የሚከበረው፣ የኢስላም ኢድ አል ፈጥር፣ ኢድ አል አድሃ (አረፋ) እና መውሊድ የሚከበሩት ከዓመተ ሒጅራም ከኢትዮጵያ
የጨረቃ አዲስ ዓመት በመነሣት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ አቆጣጠር ነው፡፡ ባሕረ ሐሳባችን በፀሐይ
(Solar)፣ በጨረቃና በፀሐይ (Luni-solar) እና በጨረቃ (Lunar) የሚቆጥር የሁሉንም አብርሃማውያንና
ሌሎች ሃይማኖቶች አቈጣጠር የያዘ ነው፡፡
ዐደይ አበባ
የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት መስከረም ባተ፡፡ ሰኔ ግም ብሎ የሐምሌን ጨለማ አልፎ፣ ዕኝኝ ብላን (ከነሐሴ 28 ቀን
እስከ 30 ባለማቋረጥ የሚዘንበው) ጎርፍ በጳጉሜን በኩል ክረምቱ ሲሻገር፣ መስከረምን የምታደምቀው ዐደይ አበባ
ትከሰታለች፡፡ በመስከረም የምትፈነዳውና ለኢትዮጵያ ምድር ጌጧ ሽልማቷም የሆነችው ዐደይ አበባ እንደ አለቃ ደስታ
ተክለወልድ ‹‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት›› ዐደይ ሲፈታ የበጨጨ፣ ብጫ የሆነ አበባ ነው፡፡ ግሱ ‹‹ዐደየ››
በጨጨ፣ ብጫ መሰለ፤ ነጣ፣ ነጭ ሆነ ሲሉም ይፈቱታል፡፡ በኦሮምኛ ነጭን ዐዲ፣ ፀሐይን ዐዱ የሚለው ከዚህ የወጣ ነው
ሲሉም ያክሉበታል፡፡
ስለዐደይ አበባ ተክል ምንነት ሳይንሳዊ መግለጫ ያዘጋጁት ከበደ ታደሰ (ዶ/ር) ‹‹የኢትዮጵያ ወፍ ዘራሽ
አበቦች (Wild Flowers for Ethiopia) በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ ስለዐደይ አበባ ከምትበቅልበት ከተለያዩ
ከፍታዎች አንፃር በሁለት መልክ እንዲህ ጽፈዋል፡፡
የተከፋፈሉ ሰፊ ላይዶ ቅጠሎችና ስምንት የተበተኑ መልካበቦች ያሉት ዓመታዊ ሃመልማል፣ ከመንገድ ዳር ዳርና
ከቃሊም እንዲሁም በከፍተኛና ድንጋያማ ተዳፋት፣ ከ400 እስከ 2,700 ሜትር ከፍታ ላይ ይበቅላል፤ ከመስከረም
እስከ ታኅሣሥም ያብባል፡፡ በሌላ በኩልም እስከ ኅዳር ድረስ የሚያብበው የሚገኘው ከ2,000 እስከ 3,600 ሜትር
ከፍታ ላይ ነው፡፡ ይህንንም ዶ/ር ከበደ ሲገልጹት፣ ዐደይ አበባ ረጃጅም ግንድና ሰፋ ያለ ላይዶ ቅርጽ ያላቸው
ቅጠሎች ያሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚበቅል ከረም ሃመልማል ነው ይሉታል፡፡ መሀላቸው ብርቱካንማ የሆነ ብጫ አበቦች
በግንዱ ጫፍ ሰብሰብ ብለው ይታያል፡፡
ድሮ ድሮ ‹‹ዐደይ ዐደይ የመስከረም፤ ሱስንዮስ ንጉሠ ሮም›› ይባል ነበር፡፡ ‹‹ዐደይ ዐደይ የመስከረም፤
እንዳንቺ ያለ የለም››ም ተብሏል፡፡ ‹‹መስከረም መስከረም የወራቱ ጌታ፤ አበቦች ተመኙ ካንተ ጋር ጨዋታ››
እየተባለም ድሮ በመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ቤት ተማሪዎች ሲዘምሩ እንደነበር መጽሐፋቸው ይናገራል፡፡
ከ55 ዓመታት በፊት በ1955 ዓ.ም. የዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ በአዲስ አበባ ራዲዮ ጣቢያ ስለ ዘመናት
መለወጥ ወይም የታሪክ ዘይቤ ዲስኩር ያሰሙት የፍልስፍና፣ የታሪክና የነገረ ኢትዮጵያ ምሁሩ እጓለ ገብረዮሐንስ
(ዶ/ር) መቋጫ ያደረጉት በምክራዊ ሐሳብ ነበር፡፡
እንዲህ ይነበባል፡- ‹‹በዘመን መለወጫ በዓል አሮጌው አልፎ አዲስ ሲተካ የክረምት ጭለማ አልፎ ብርሃን ሲመጣ ሁሉም በተውሳከ መብልዕ ወመስቴ
[መብልና መጠጥ በመጨመር] እየተደሰተ ከአንዱ ዘመን ወደሌላው መሻገሩን በሚያከብርበት ዕለት ትንሽ ጊዜ አስተርፎ
ስለጠቅላላው የሕይወት ጉዞ ለሚያስበው ረድኤት ይሆን ዘንድ፣ ለማያስበው ደግሞ እንዲያስብ ምክንያት ይሆን ዘንድ፣
እሊህን ሐሳቦች ለማቅረብ ደፈርን፡፡ የዚያ ሰው ይበለን እንጂ ለከርሞ በተሻለ ለማቅረብ እያሰብን ለሰሚዎቻችን
መልካም በዓል እንመኛለን፡፡››
- ሔኖክ ያሬድ's blog
- 56 reads
No comments:
Post a Comment