በበሪሁን ተሻለ
እነሆ የ2008 ዓ.ም. የመጀመሪያው ሳምንት ውስጥ ነን፡፡ ያሳለፍነው ዓመት የመጨረሻ ሳምንት የ2007 ዓ.ም.
አካል መሆኑና ሆኖ መቆጠሩ የተዘነጋ እስኪመስል ድረስ፣ ለሁሉም ዘርፍ የአዲሱ ዓመት መቀበያና መዘጋጃ ሆኖ ተሾሞና
ነግሶ አልፏል፡፡ የመምሰልና የማስመሰል ነገር ደግሞ ልብ ላለው የአገር “ብሔራዊ ስፖርት” ሆኖ ቁልጭ ብሎ
የሚታየው እንዲህ ባለ የበዓል ግርግርና ሆያ ሆዬ ጊዜ ነው፡፡
እጅግ በጣም ጠቃሚ የምግብ ምንጭና ለአገር ጠቅላላ የኢኮኖሚ ዕድገት ዓይነተኛ ካፒታል መሆን ባለበት በኢትዮጵያ
የቀንድ ከብት ሀብት በዓለም አሥረኛ በአፍሪካ አንደኛ ነን ሲባል ነፍስ ካወቅሁ ጀምሮ እሰማለሁ፡፡ በቀደም
በ2007 ዓ.ም. ነሐሴ መጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የቢዝነስ ዘገባ ሳይቀር በኢትዮጵያውያን የሥጋ ዓመታዊ
የነፍስ ወከፍ ፍጆታ አነስተኛነት ሲያፍርና ማፈሩንም መደበቅ ሲያቅተው አይቻለሁ፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ
ወቅት ለመንገደኞች ለሚያቀርበው ምግብ የሥጋ ግብዓት የሚገዛው ከብራዚል መሆኑን፣ በመላው ዓለም ገበያ ውስጥ
በርካሽነቱ የሚታወቀው የዶሮ ሥጋ ኢትዮጵያ ትላልቅ ሆቴሎች ሚኑ ዝርዝር ውስጥ ግን ከውድነቱ የተነሳ ማካተት
አለመቻሉን፣ በዜና መልክ እኛ ኢትዮጵያውያን ከኢትዮጵያ ኦፊሴል የዜና ምንጭ ሰማን፡፡
በዚህ የዘመን መለወጫ በዓል ደግሞ በኪሎ 200 ብር የተጠጋው ሥጋ በታላላቅ ዓመት በዓላት እንኳ ሥጋ መብላትን
የጥቂቶች ሲያደርገው አየን፡፡ በሊትር 74 ብር የገባው የኑግ ዘይት ከደሃ ጓዳ እየወጣ መሆኑን በዓይናችንም
በሆዳችንም አየን፡፡
የሽሮ ክክ በኪሎ 25 ብር፣ ምስር ከ50 ብር በላይ መሆኑ፣ ኪሎ በርበሬ 180 ብር መድረሱ፣ በሽሮ
መብላትንና በበርበሬ ማጥቀስን የድህነት ምልክት መሆኑን ሲሽረው በዓይናችን በብረቱና በሆዳችን በወስፋቱ መሰከርን፡፡
የሚገርመው ደግሞ የዓውደ ዓመቱ “ዘፈን” ሁሉ የምግብና የመጠጥ የዕርድ መሆኑ ነው፡፡
የአዲሱ ዓመት መቀበያ ሆኖ ሌላውን ሐሳባችንንና ሰቀቀናችንን ሁሉ ወደ “ጉያ”ችን የደበቀው የጳጉሜን ወቅት
ከሌላው ጊዜ በከፋ ሁኔታ የዘመን አቆጣጠራችን ለአደጋ የተጋለጠ ቢያንስ ቢያንስ ባለቤት አልባ የሆነ፣ የማንም
የዘፈቀደ አሠራር እንደፈለገ ሊያሾረው የሚችል መሆኑን ሌላ ተጨማሪ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶን ሲያልፍ ጭምር አየን፡፡
ይህን ጉዳይ እሑድ ሰኔ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. የወጣው የሪፖርተር ጋዜጣ (ቁጥር 1580) ካጋጠመው አንድምታና
ችግር ጋር አመላክቶን ነበር፡፡
ፓርላማው ዘንድሮም ጳጉሜን ስድስትን የት አደረሰው በሚል ርዕስ ሥር የቀረበው ጽሑፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር
ቤት ያሳተመው የ2007 ዓ.ም. አጀንዳ (የቀን መቁጠሪያ) የ2007 ዓ.ም. መሰናበቻን ጳጉሜን 5 እንደሚያደርግ፣
ስለዚህም መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚጀምረው (የሚውለው) ዓርብ ነው እንደሚል፣ ይህ ስህተት የሕዝብ
ተወካዮች ምክር ቤት አጀንዳ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ጭምር ነግሮናል፡፡ ጽሑፉ ይህን ስህተት የሠራው ፓርላማው
ያሳተመው የ2007 ዓ.ም. አጀንዳ ብቻ አለመሆኑንም ይገልጻል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ፣ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ
ኃይል፣ ሸገር ሬዲዮ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ባሳተሟቸው የቀን መቁጠሪያዎችም ተመሳሳይ ስህተት እንደሠሩ ነግሮናል፡፡
እንዲህ ያለ የካሌንደር ስህተት ምን ዓይነት ችግር ማስከተል እንደቻለ ለጊዜው የምናውቀው ማወቅ የተፈቀደልንን ያህል ብቻ ነው፡፡
በሪፖርተር ጋዜጣ የሰኔ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. ጽሑፍ መሠረት 2003 ዓ.ም. ቅዳሜ ጳጉሜን 5 ያበቃል
የሚለውን የፓርላማውንና የራሱን አጀንዳ በመከተል ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነሐሴ 14 ቀን (ኢዜአ
እንደዘገበው) በወጣው መግለጫ፣ “መስከረም 9 ቀን 2004 ዓ.ም. የሚከበረውን በዓል በልዩ ድምቀት ለማክበር”
ተብሎ ዝርዝሩ መቅረቡ በዓሉ ከሰኞ ወደ ማክሰኞ ተቀየረ ወይ አስብሎ ነበር፡፡
እንደ 2003ቱ አጀንዳ ጳጉሜን 5 ቅዳሜ አብቅቶ የ2004 ዓ.ም. መስከረም 1 ቀን እሑድ ሆነ፡፡ መስከረም 2
ሰኞ ብሎ በማስላት ሁለተኛውን ሰኞ መስከረም 9 ላይ አመላከተ፡፡ ይሁን እንጂ ጉዱ የታወቀው ቆይቶ ነው፡፡ “ኧረ
ጳጉሜን 6 ነች፣ መስከረም 1ም ሰኞ ነው የሚለው ተሰምቶ ማስተካከያ የተደረገው በዓሉን ከአዋጅ ውጪ ወደ ሦስተኛ
ሰኞ በመውሰድ መከበሩ ነበር፡፡ ሰበብ የተደረገውም፣ “የቀኑ መተላለፍም በቂ ዝግጅት [ለ] ማድረግ” በሚል ነበር፡፡
ስህተቱን ተቀባብለውና አባዝተው የሚሠሩት አጀንዳ አሳታሚዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ዓርብ ጳጉሜን 6 ቀን 2007
ዓ.ም. የጎበኘሁት የፋና (ኤፍቢሲ) ዌብ ሳይት “ዓርብ መስከረም 1 ቀን 2008 ዓ.ም. “Friday,
September 11 2015 GC” ይል ነበር፡፡
የበለጠ ችግር ደርሶ ሳናይ ጉዳዩን የናቁትና ከሥልጣንና ተግባራቸው ውጪ ያራቁት የሥልጣን አካላት መላ
ሊያበጁለት ይገባል፡፡ በመሠረቱ የካሌንደር ጉዳይ በኢትዮጵያ ውስጥ የፌዴራሉ መንግሥት ሥልጣን ነው፡፡ በዚህ ውስጥ
የአገር ደንበኛ (ስታንዳርድ) ሰዓት የበዓላት የሚዛንና የመስፈሪያ (ስታንዳርድ)፣ የጊዜ ቀመር ጉዳይ በዋነኛነት
በንግድና በኢንዱስትሪው ዘርፍ ውስጥ የሚታቀፉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ የፌደራሉ መንግሥት ጉዳዩ የሚመለከተው አካል ይህን
ባለቤት የለውም ተብሎ በየ“ማንም” እጅ የገባውንና የ“ማንም” መጫወቻ የሆነውን ጉዳይ ደንገጥ ብሎ በተነሳ፣
ኃላፊነት በሚሰማውና ተጠያቂነትንም በሚያካትት ስሜት ቢዘገይም “አለሁ!” ሊለው ይገባል፡፡
በእኛ በኩል ይህንን ሥራ ለማገዝ ቢያንስ ቢያንስ ደግሞ በየአራት ዓመቱ ብቻ ሳይሆን፣ በየጊዜው የኢትዮጵያን
የዘመን አቆጣጠር ወደ አውሮፓውያን፣ የአውሮፓውያኑን ወደ ኢትዮጵያ በመለወጥ አሠራር ውስጥ የሚፈጠረውን ችግር
ውዥንብርና ሽብር ጭምር ለመገንዘብ ያስችል ዘንድ፣ ይህንን የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር መግለጫ ሲሆን ለቀጣይ ዕርምጃ
መነሻ እንዲሆን፣ አለዚያም ለ“ንባብ” እንኳን ቢሆን ብለን አቅርበናል፡፡
መግለጫው የተገኘው ከ“የተጠቃለሉ የኢትዮጵያ ሕጎች” ነው፡፡ የተጠቃለሉ የኢትዮጵያ ሕጎች
ማለት ፀንተው የሚሠራባቸውን ሕጎችና ደንቦች በማጠቃለል በጊዜ ሒደትም ውስጥ የወጡትን ማሻሻያዎችና ለውጦች
ከእያንዳንዱ ሕግና ደንብ ጋር በማዋሀድ የታተመ መጽሐፍ ነው፡፡ የመጀመሪያው የተጠቃለሉ የኢትዮጵያ ሕጎች የወጣው
እስከ 1961 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ወጥተው በመላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራባቸውን (ከኮዶች በስተቀር) ሕጎችና
ደንቦች አጠቃልሎ በመያዝ ነው፡፡ የእንደዚህ ያለ የተጠቃለሉ የኢትዮጵያ ሕጎች ጠቃሚነትና ፋይዳ ይቀጥል ዘንድ
በየጊዜው የማሟያ ሥራ መሠራት አለበት፡፡ የተጠቃለሉ ሕጎች የመጀመሪያውና (አለመታደል ሆኖ የመጨረሻው) ማሟያ
የወጣው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፡፡ አንደኛው የተጠቃለሉ የኢትዮጵያ ሕጎች ማሟያ የወጣው ከ1962 ዓ.ም. መጀመሪያ
እስከ 1965 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ ያሉትን ሕጎች ይዞ ነው፡፡ የታተመውም በ1967 ዓ.ም. በደርግ ጊዜ ነው፡፡
ከዚያ በኋላ ማለትም ከ1965 ዓ.ም. መጨረሻ በኋላ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚሠራባቸው ሕጎች ሌላ ሕግ ሽረው ወይም
አሻሽለው ቢወጡም፣ ወይም ራሳቸው ቢሻሩም ቢሻሻሉም ይህን እያዋሀደና እያጠቃለለ የሄደ የተጠቃለሉ የኢትዮጵያ ሕጎችን
ዓላማ የቀጠለ ሥራ በጭራሽ አልታየም፡፡ የኢትዮጵያን የሕግ ሥርዓት ካጎደሉት ሥራዎች አንዱ ይኼው 42 ዓመት ሙሉ
ተዳፍኖ የቀረው የኢትዮጵያን ሕጎች የማጠቃለል ጅምር ሥራ በአጭሩ መቀጨት ነው፡፡
ወደ ካሌንደሩ ጉዳይ ስንመለስ የተጠቃለሉ የኢትዮጵያ ሕጎች የ1965 ዓ.ም. የመጀመሪያ ዕትምና የ1967
ዓ.ም. የመጀመሪያ ማሟያ በሁለቱም የዘመን አቆጣጠር መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ “የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር መግለጫ
የተሰጠው አልፎ አልፎ በእንግሊዝኛው የሕግ ቅጅ ውስጥ ቀኖቹ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር መሠረት በመሰጠታቸው
በአንዳንድ ሰዎች ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ለማስወገድ ነው፡፡”
መግለጫው ግን ከዚህ የበለጠ ፋይዳ አለው፡፡ ለምሳሌ ብዙዎቹን የ2007 ዓ.ም. የቀን መቁጠሪያ አጀንዳዎች
(አንቱ በሚባሉ ድርጅቶችና እኔ ነኝ በሚሉ ተቋማት ጭምር የወጡትን) በገጽ ያወጣቸው አንዱ ጉዳይ የጳጉሜን ጉዳይ
ነው፡፡ ጳጉሜን በአራት ዓመት አንድ ጊዜ 6 ቀናት ይኖሩታል፡፡ ከዚያ ውጪ የጳጉሜን ወር ባለ አምስት ቀን ወር
ነው፡፡ ጥያቄውና ብዙዎቹን “እኔ ነኝ” ባይ የመንግሥት ተቋማት ጭምር እጀ ሰባራ ወይም ምሥጋና ቢስ ያደረገው
ጳጉሜን 6ኛ ቀን የሚኖረው መቼ ነው የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ ብቻውን መልስ አይደለም፡፡
ጳጉሜን 6 የሚሆንበት የአራተኛው ዓመት ራሱ መቼ ነው?
የተጠቃለሉ የኢትዮጵያ ሕጎች ከ42 ዓመት በፊት ያወጣው የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር መግለጫ ፎርሙላ መሰል ነገር ያቋቁማል፡፡ ጳጉሜን ወር ላይ ስድስተኛ ቀን የሚጨመረው የአራት ብዜት ቁጥር ካለው አንድ ዓመት ቀደም ብሎ ባለው ዓመት መጨረሻ ላይ ነው፡፡
ለምሳሌ 1984 የ“አራት ብዜት ቁጥር” ያለው ዓመት ነው፡፡ 1984 ለአራት ሲካፈል ያለምንም ትርፍና ቀሪ
ይከፈላል ማለት ነው፡፡ ከ1984 በፊት ያለው ዘመን 1983 ነው፡፡ ስለዚህም ጳጉሜ ወር ላይ 6ኛው ቀን የሚጨመረው
1983 ላይ ነው፡፡ በዚህ መሠረት የ1983፣ የ1987፣ የ1995፣ የ1999፣ የ2003፣ የ2007 ጳጉሜዎች
ባለስድስት ቀናት ናቸው፡፡ ወደፊትም የ2011፣ የ2015፣ የ2019፣ የ2023፣ የ2027 እንዲሁም የ2031፣
ወዘተ ጳጉሜዎችን ከመደበኛው የጳጉሜን ወር በተጨማሪ ስድስት ቀን ይኖራቸዋል፡፡
ይህን ማወቅ ብቻ ሳይሆን ቀምሮ ማኅበራዊ ዕውቀት ማድረግ አንድ ነገር ነው፡፡ ያቃተንና ያስቸገረንም ተራ ነገር
ይኼው ነው፡፡ እያንዳንዱ ይህን ማድረግ የሚችል ማተሚያ ቤት፣ ከዚያ ካለፈም የእያንዳንዱ “አሳታሚ” ተቋም
የጠቅላላ አገልግሎት፣ ወይም የሕዝብ ግንኙነት፣ ወይም የኮሙዩኒኬሽን መምርያ ወይም ዳይሬክቶሬት እንደመሰለው
የሚወስነው ጉዳይ፣ ባለቤት የሌለው ሥራ መሆኑም፣ የትልቁ ችግራችን ማሳያ ምልክት ነው፡፡
ጳጉሜን እንደተለመደው አምስት መሆኑ ቀርቶ በየአራት ዓመቱ ባለስድስት ቀናት ወር የሚሆንበተን ጊዜ ለይቶ ማወቁ
ሌላም አንድምታና ውጤት አለው፡፡ በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠርና በአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር መካከል ያለው
የተለመደው አጣማጅ አቻ ቁርኝነት ይለወጣል፡፡
ጳጉሜን 6 ቀን ከሚሆንበት የኢትዮጵያ ዘመን በስተቀር መስከረም 1 ማለት ሁልጊዜም ሴፕቴምበር 11 ነው፡፡ ይህ
ግን በየአራት ዓመቱ ይለወጣል፡፡ ስለዚህም የ1959፣ የ1979፣ የ1999 መስከረም አንድ የዋለው በአውሮፓውያን
ዘመን አቆጣጠር እንደ ቅደም ተከተላቸው ሴፕቴምበር 12 ቀን 1967፣ 1987፣ 2007 ነበር፡፡
ለማንኛውምና ለሁሉም ከ42 ዓመት በፊት የነበሩ የከፍተኛ የመንግሥትና የትምህርት ተቋማት ተባብረው ያዘጋጁትና
እየተሟላና እየታደሰ ይሄዳል ብለው እምነት የጣሉበት የኢትዮጵያ ሕጎችን የማጠቃለል ቋሚ ተግባር በአጭር ቢቀጭም፣
በዚያ ታላቅና ወደር የለሽ ሥራ ውስጥ በተጨማሪነት (አባሪነት) የተያያዘው የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር መግለጫ
ጠቃሚነት የሚካድ አይደለም፡፡
የኢትዮጵያ የቀን አቆጣጠር መግለጫ
የሚከተለው የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር መግለጫ የተሰጠው አልፎ አልፎ በእንግሊዝኛው የሕግ ቅጂ ውስጥ ቀናቱ
በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር መሠረት በመስጠታቸው፣ በአንዳንድ ሰዎች ላይ ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ለማስወገድ
ነው፡፡
በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ፩ ዓመት እያንዳንዱ ወር ፴ ቀናት ያሉት ፲፪ ወራትን የያዘ ሲሆን፣ በአሥራ
ሁለተኛው ወር መጨረሻ አምስት ቀናት (በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ፮ ቀኖች) የያዘ አንድ ተጨማሪ የጳጉሜን ወር
አለ፡፡ የዓመቱ የመጀመሪያ ቀን መስከረም አንድ ቀን ነው፡፡ ይኼውም ቀን በአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር መስከረም
፲፩ ቀን ነው፡፡ ነገር ግን በየአራቱ ዓመት የጳጉሜ ወር ስድስት ቀናት በሚሆንበት ጊዜ መስከረም ፲፪ ቀን
ይሆናል፡፡ ይህም ልዩነት የሚሆነው በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የዓመት የመጀመሪያ ቀን (መስከረም ፩ ቀን) ጀምሮ
እስከ የአውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር የዓመት መጨረሻ ባለው ጊዜ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህም በአውሮፓውያን ዘመን
አቆጣጠር በ፲፱፸፩ ዓ.ም. በኅዳር ውስጥ ያለ ቀን በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር የተባለው ቀን ፲፱፻፺፬ ዓ.ም.
ሲሆን፣ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር ከጥር ፩ ቀን ጀምሮ የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ከአውሮፓውያን ዘመን
አቆጣጠር ስምንት ዓመት ይቀንሳል፡፡
No comments:
Post a Comment