የዘንድሮን ፋሲካ በዓለም ዙሪያ በአንድ ቀን ሁሉም ክርስቲያኖች እያከበሩት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በራሷ ባሕረ ሐሳብ መሠረት ሚያዝያ 8 ቀን 2009 ዓ.ም. ስታከብር፣ ምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን በሚከተሉት የጁሊያን አቆጣጠር መሠረት አፕሪል 3 ቀን 2017፣ የምዕራብ ክርስቲያኖችም በጎርጎርዮሳዊው ቀመር አፕሪል 16 ቀን 2017 ሦስቱ በአንድ ቀን ፋሲካን እያከበሩት ይገኛሉ፡፡
ለወትሮው ኢትዮጵያና የምሥራቅ ኦርቶዶክሶች በተመሳሳይ ቀን ሁሌም ቢያከብሩትም  የምዕራቦቹ ግን አልፎ አልፎ ከምሥራቆቹ ጋር ይገጥማል፡፡ ለምሳሌ በ2002 ዓ.ም.፣ በ2003 ዓ.ም. እና በ2006 ዓ.ም. የምሥራቁም የምዕራቡም ፋሲካ ባንድ ቀን መከበሩ ይታወሳል፡፡
ይህም የሆነው ፋሲካ የሚውለው፣ ቀን ሌሊት እኩል 12፣12 ሰዓት ከሚሆንበት (Equinox) ከመጋቢት 25 ቀን በኋላ ከምትታየው የመጀመሪያዋ ሙሉ ጨረቃ ቀጥሎ ባለው እሑድ ነው፡፡ በአጋጣሚ በኢትዮጵያና በጎርጎርዮሳዊ አቆጣጠሮች ሙሉ ጨረቃዋ የታየችው በተመሳሳይ ዕለት በመዋሉ ፋሲካው በአንድ ቀን መዋል ችሏል፡፡
ፋሲካና አከባበሩ
የፋሲካ (ትንሣኤ) በዓል በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች ኅብረተሰቡ መሠረተ እምነቱን ሳይለቅ እንደየባህሉና ትውፊቱ ያከብረዋል፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የፎክሎርና የአትሮፖሎጂ ባለሙያዎች እንደሰነዱት፣ በሰሜን ሸዋ የሚገኙት የምንጃሮች የበዓሉ አከባበር በዕለተ ሐሙስ  ሲጀመር  በዕለቱ ጉልባን፣ ዳቦና ጠላ ተዘጋጅቶ በመብላትና በመጠጣት ይታለፋል፡፡ በማግስቱ ደግሞ የስቅለት ወይም የስግደት ዕለት በዋናነት የአካባቢው ሽማግሌዎችና አዛውንቶች በመስገድ የሚሳተፉበት ዕለት ነው፡፡ ቅዳም ስዑር (የቅዳሜ ስዑር ዕለት) ማታ ዶሮ ይታረዳል፡፡ የዶሮ ወጥ የጾም መፍቺያ በመሆኑ የሚበላው ሌሊት ዶሮ ሲጮህ ሲሆን፣ በዚህ ሰዓት ከትንሽ እስከ ትልቅ ያሉ የቤተሰብ አባላት ከእንቅልፉ ተቀስቅሶ እንዲገድፍ ወይም ጾሙን እንዲፈታ በማድረግ ይሆናል፡፡
በደቡብ ክልል ሸካ ዞን የሚገኙት ሸከቾዎችም ፋሲካን በራሳቸው ባህላዊ መለያ ያከብሩታል፡፡ በዓሉ ሐሙስ የሚጀምር  ሲሆን ዕለቱ ‹‹ዳጲ ማዮ ማዮ›› ይባላል፡፡ ይህም የንፍሮ ቀን ማለት ሲሆን፣ ቀኑን በጾም በማሳለፍ ወደማታ የሚበላው ምግብ ንፍሮ ብቻ ነው፡፡ በሌሎች ቦታዎችም በጸሎተ ሐሙስም ጸዋሚዎቹ ጉልባንና ንፍሮ ቀምሰው እስከ ትንሣኤ ሌሊት ሳይመገቡ ያከፍላሉ፡፡ ባቄላ፣ ስንዴና ጥራጥሬ ተቀላቅሎበት የሚዘጋጅ የምግብ ዓይነት ጉልባን  ነው፡፡ ዓርብ ስቅለት ከስግደት መልስም ጉልባን ይበላል፡፡ የሐዘን መግለጫ ሆኖ የተወከለ ነውና፡፡
በሸከቾዎች ዓርብ ስቅለት ‹‹አኪላቶስ›› ሲባል በዚህ ቀን በተለይ እናቶች ቀኑን በልዩ ሁኔታ ያከብሩታል፡፡ እናቶች ጠንካራ የፈትል ገመድ አዘጋጅተው የሁለቱን እጃቸውን ክንድ ባንድ ላይ የኋሊት በማሰር ይውላሉ፡፡ ወደማታ ሲሆን እጃቸውን ከፈቱ በኋላ በሠፈሩ ያሉ ሴቶች በኅብረት ‹‹ዮዲ›› በሚባል በደንና በዕፅዋት በተከበበና በተከበረ ቦታ በመሰባሰብ ቅጠል አንጥፈው ድምፃቸውን ከፍ  አድርገው ዘለግ ባለ ድምፀትና ተመስጦ ‹‹እቶማራማራ እቶስ›› ‹‹ዮሻ ዮሻ ኢቶስ›› እያሉ ለረዥም ሰዓታት ይሰግዳሉ፡፡ ‹‹መሐሪ የሆነው ክርስቶስ ተይዞ ለሞት ተሰጠ›› የሚል ትርጉም ያለው ሲሆን፣ በየሁሉም ሠፈር የሚከናወነው ስግደት ከሠፈር ሠፈር የሚሰማ ነው፡፡
በላሊበላ ከተማም የፋሲካ በዓል ሲከበር ከሚከናወኑት ድርጊቶች አንዱ፣ የአካባቢው ልጃገረዶች የሚጫወቱት ሹላሌ የተሰኘ ጨዋታ ነው፡፡ እንደ አካባቢው ተወላጅ አቶ ዓለሙ ኃይሌ አገላለጽ፣ ሹላሌ ከትልቅ ዛፍ ላይ ጠፍር ታስሮ ልጃገረዷ በጠፍሩ ላይ ተቀምጣ የምትጫወተው ነው፡፡ ሌሎች እየገፏት እየዘፈኑ ዥዋዥዌውን ይጫወታሉ፡፡
‹‹ሽው ሽው ላሌ
እሰይ ለዓመት በዓሌ…››
ታተይ ከቋቱ ላይ ያለው እንቁላል ድመት በላው
አንቺ የት ሄደሽ? እኔማ ለገብርዬ ያን እሰጥ ብዬ
አግባኝ ሳልለው አግብቶኝ ነጋዴ
ሲያበላኝ ከረመ ነጭ ጤፍ ከስንዴ›› እያሉ እየተመላለሱ ይጫወታሉ፡፡
ሹላሌ የተሰኘው ጨዋታ ከፋሲካ (ትንሣኤ) እስከ ዳግማይ ትንሣኤ ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ ልጃገረዶቹ በጠፍር ላይ ሆነው መወዛወዛቸው ኢየሱስ ክርስቶስ አይሁዶች የክስ አደባባይ ከሔሮድስ ወደ ጲላጦስ፣ ከጲላጦስ እንደገና ወደ ሔሮድስ መመለሳቸውን ምሳሌ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡
 ስለሸካቾ ብሔረሰብ የሚያወሳ አንድ ድርሳን እንደሚያመለክተው፣ ‹‹በስቅለት ዕለት (ዓርብ) ምዕመናኑ ሙሉ ቀን ጹመው ‹የሺ-ቅቶሶች›ን ይለምናሉ፡፡ ‹የሺ-ቅቶሶች› ማለት ከሥረ መሠረቱ ከእኛ ጋር ያለን ጌታ፤ ተይዞ ለእኛ የተሰቀለው፤ ለእኛ ብሎ የሞተ፤…›› የሚለውን ቃል ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም የጸሎት አዝማቹ ‹‹እቶ ማራማራ እቶስ!›› የሚለውም የክርስቶስ ተከታዮችን ያመለክታል፡፡
‹‹ፋሲካ መጣ ገበታው ቀና አለ!›› የሚሉት ሸካዎች ናቸው፡፡ በቋንቋቸው ‹‹ማዲካም›› ይሉታል፡፡ በቀጥተኛ ትርጉሙ ቀና ያለ ገበቴ ማለት ነው፡፡ እሑድ ፋሲካ ወይም የዋናው ማዲካም ዕለት በመሆኑ ከብት ይታረዳል፤ እናቶች ገሪግዮ በሚባል ጎምዛዛ ቅጠል አፋቸውን አራት ጊዜ ‹‹ጮሚበቾ›› በማለት ካበሱ በኋላ መመገብ ይጀምራሉ፡፡ በጾሙ ወቅት ተከድነውና ተሰቅለው የቆዩ የምግብ ዕቃዎች ታጥበውና ፀድተው ለምግብ የሚዘጋጁበት፣ ፋሲካ መጣ ገበታው ቀና አለ ማለት እንደሆነ ድርሳናት ያመለክታሉ፡፡
ምንጃሮችም በዕለተ በዓሉ እሁድ ዕለት ጠዋት ሁሉም የቤተሰብ አባላት ይሰበሰቡና ቡና ተፈልቶ ዳቦ ይቆረሳል፡፡ በግም ሆነ ፍየል የተዘጋጀው ይታረዳል፡፡ ከዚህ ባለፈ እንደቤተሰቡ የአቅም ሁኔታ የከብት ቅርጫ ሥጋ ተካፍሎ ለቤተሰቡ በማስገባት በዓሉ ይከበራል፡፡ ‹‹እንኳን ጾሙን ልጓሙን ፈታላችሁ›› የበዓሉ የመልካም ምኞት መግለጫ ነው፡፡
በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትና ሥርዓት መሠረት፣ በእሑድ ፋሲካ ዋዜማ ቀዳም ሥዑር (ቅዳሜ ሹር) ማለዳ ቄጠማ እየታደለ “ገብረ ሰላመ በመስቀሉ ወአግሀደ ትንሣኤሁ” (በመስቀሉ ሰላምን አደረገ፤ ትንሣኤውም ግልጽ ሆነ) ተብሎ ይከበራል፡፡
ምሽት ላይ ምእመናን ወደየአጥቢያ ቤተ ክርስቲያናቸው ጧፍና ሻማ በመያዝ በምሥራቹና በሥርዓተ ቅዳሴው ለመካፈል የሚጓዙበት ነው፡፡ እስከ መንፈቀ ሌሊት ይቆያሉ፤ በፋሲካ ሌሊት የምሥራቹን ጧፍና ሻማ በመለኮስ በቤተ መቅደሱ ዙሪያ የሚደረገው ዑደት “ትንሣኤከ ለእለ አመነ ብርሃነከ ፈኑ ዲቤነ” (ትንሣኤህን ላመንን ለእኛ ብርሃንህን ላክልን) በሚለው ዝማሬ የታጀበ ነው፡፡ ዶሮ ሲጮህ ይፈስካሉ፤ ለምእመናኑ በመንፈሳዊ እርሻ የተመሰለው ሁዳዴው ሲጀመር
“ጀግናው ዐቢይ ጾም ቢታይ ብቅ ብሎ፣
ቅቤ ፈረጠጠ አገር ርስቱን ጥሎ”
ተብሎ በቃል ግጥም የታጀበው ጾም ሲፈታ፣ በተለይ ሌሊት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ከቅባት የተለየው አካል እንዳይጎዳ ልዩ ምግብ ይዘጋጅለታል፡፡ ማለስለሻ እንዲሆን ተልባ ይቀርባል፡፡
እንደየኅብረተሰቡ ባህል የፋሲካ ድፎ ዳቦ፣ ዶሮ ዳቦ፣ ኅብስት፣ የዶሮ ወጥ እንቁላል፣ የዕርድ ከብቶችን ማዘጋጀት ጠጅና ጠላ መጠጥ ማዘጋጀት የክብረ በዓሉ አንዱ ገጽታ ነው፡፡ ከመልካም ምኞቱ እንኳን አደረሳችሁ፣ ጾመ ልጓሙን እንኳን ፈታልዎ በአነጋገር ደረጃ የሚጠቀስ ነው፡፡ ከርቀትም ሆነ ከቅርበት ያሉ ቤተሰቦች የሚሰባሰቡበት ስጦታ ሙክት፣ ድፎ ዳቦና መጠጦች የሚለዋወጡበትም ነው፡፡
ሸከቾች ከዐቢይ ጾምና ከፋሲካ ጋር በተያያዘ ለየት ያለ የወራት አሰያየም አላቸው፡፡   የካቲት፡- ‹‹መዴጉፓ›› የሁዳዴ ጾም በየካቲት ወር ስለሚጀምር፣ እስካሁን በቅበላ ቆይተሃልና ገበታህን አጥበህ ድፋው ወይም ጾም ጀምር የሚል አንድምታ ያለው ነው፡፡ መጋቢት፡- ‹‹ገኤውቆ›› የጾም እኩሌታ የሚደርስበት ወር በመሆኑ በርታ እንደማለት ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የደብረዘይት በዓል የሚከበርበት መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡ ሚያዝያ፡- ‹‹መካሞ›› ጾም ልትፈታ ነው፡፡ ስለዚህ ተደፍቶ (ተቀምጦ) የከረመውን ገጽታህን ቀና አድርገህ ጾምህን ፍታ፣ የፋሲካ በዓልን አክብር ማለት ነው፡፡ በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም አከባበሩ ጉልህ ይሆናል፡፡
የወጣቶች ጨዋታ
የላሊበላ ወንዶች የሚጫወቱት ጨዋታ ደግሞ የጊጤ ጨዋታ ይሰኛል፡፡ ስለዚህ ጨዋታ አቶ ዓለሙ ኃይሌ እንዲህ ይላሉ፡፡
ወንዶች ቁልቋል የሚባል ተክል ቆርጠው ግንዱን መሬት ቆፍረው ይተክሉታል፡፡ ከዚያ የሾላ አንካሴ ይዘው እሱን እየወረወሩ ይወጋሉ፡፡ ውድድር አለው በተራ በተራ ያሸነፈ ይጨበጨብለታል፡፡ ረቺው በተረቺው ላይ ተፈናጦ ይሄዳል፡፡ ይጋልባል፡፡ በአንካሴ ቁልቋሉን ይወጋል፡፡ ይኸው ጨዋታ ኢየሱስ በጦር የመወጋቱ ምሳሌ መሆኑ ይነገራል፡፡ በትውፊት እንደሚነገረው ጨዋታውን የኢየሱስን መቃብር ሲጠብቁ የነበሩት ወታደሮች ይጫወቱት የነበረው ጨዋታ ጋርም ያይዙታል፡፡
አቶ ዓለሙ ከምዕመናኑ ሌላ አገልጋዮችም የራሳቸው ጨዋታ እንዳላቸው ይገልጻሉ፡፡ ነጫጭ ልብስ ለብሰው፣ ጥምጥማቸውን አሳምረው ‹‹ተስዒነነ ዘወንጌል ቃለ››- የወንጌል ቃልን ተጫምተን መስቀልን ተመርኩዘን- እያሉ በየቤቱ በዓሉን የሚመለከት ወረብ እንደሚወርቡ ያስታውሳሉ፡፡
‹‹አማን በአማን ተንሥአ እሙታን›› - እውነት በእውነት ከሙታን ተለይቶ ተነሣ- በማለት ትንሣኤውን ያበስራሉ፡፡ ከፋሲካ በዓል ጋር ተያይዞ በሚኖረው ጨዋታ ማንጎራጎሩም ያለ ነው፡፡
‹‹አብ እየበደለኝ እያዘነ ሆዴ
ለወልድ እነግራለሁ ለሥጋ ዘመዴ
አብን ተዉትና ንገሩት ለወልድ
ተሰቅሏል ተገርፏል እርሱ ያውቃል ፍርድ፡፡››
   የእሽኬ ጨዋታ
የፋሲካ በዓል በተለይ ለወጣት ልጃገረዶችና ወጣት ወንዶች የተለየ ጊዜ በመሆኑ በምንጃሮች አጠራር ‹‹ሸንጎ›› ላይ በመውጣትና በመጫወት የሚተጫጩበት፣ ወጣት ወንዶችም የትግል ጨዋታ የሚጫወቱበትና አሸናፊና ተሸናፊ የሚባባሉበት፣ ‹‹እሽኬ›› የተባለውን ጨዋታ ይጫወቱበታል፡፡
በዓሉ የምቾት፣ የድሎትና የደስታ ጊዜ መሆኑን ለማመልከት ልጃገረዶች እንዲህ እያሉ ያዜማሉ ይላል፤ በሰሜን ሸዋ ላይ የተሠራው የኢንታንጀብል ባህላዊ ቅርሶች ኢንቬንቶሪ ሰነድ፡፡
 ‹‹አወይ ፋሲካ ኮበለለ
         የሽሮ ቅሉን እያንከባለለ
አወይ ፋሲካ ጀግናው
        ሥጋ እንደጎመን የሚበላው
አወይ ፋሲካ የተውሶ
         ይሄዳል ተመልሶ
የፋሲካ ዕለት እነማዬ ቤት እነአባዬ ቤት
          ያለ ደስታ ያለ ድሎት
የስንዴ ቆሎ በገበታ
         አወይ ፋሲካ የኛ ጌታ››
እያሉ በዘፈኖቻው ይገልጻሉ፡፡
በወጣቶች በኩል በተለይ በዕለተ በዓሉ በቡድን የሚከወን የሩጫ ውድድር በአሸናፊና ተሸናፊ ቡድኖች መካከል በዜማ መወራረፍ አለ፡፡
‹‹አምና የፋሲካ ዕለት ሱሪዬን ባውሰው
         እጓሮ ዞረና ቆሻሻ ለወሰው
አስረጂ2፡- ይኼን ግርንቡዱን ከወገቡ ጎርዶ
         አንዱን ለሙቀጫ አንዱን ለማገዶ
አምና ይኼን ጊዜ ሽልጦ
         አላስሮጥም አለው ጎኑ ተሸጦ››
እየተባለ ተሸናፊ ቡድን አለመቻሉን በውረፋ መልክ እየገለጹ ይገጥማሉ፡፡
  • የፋሲካ ቀመር
የፋሲካ (ትንሣኤ) በዓል አከባበር በአቆጣጠር ልዩነት የተነሣ ከ16ኛው ምእት በኋላ ምሥራቆችና ምዕራቦች ከመለያየታቸው በፊት ከ326 እስከ 1582 ድረስ በ325 በተካሄደው ኒቅያ ጉባኤ ውሳኔ መሠረት ክብረ በዓሉ በተመሳሳይ ቀን ይውል ነበር፡፡
በዓሉ ምንግዜም ቀኑና ሌሊቱ እኩል 12፣ 12 ሰዓት ከሚሆንበት መጋቢት 25 (በጁሊያን ማርች 21) በኋላ፣ ከአይሁድ ፍሥሕ (ፋሲካ) በኋላ፣ ባለው እሑድ ሁልጊዜ እንዲውል ይደነግጋል፡፡ ከጥቅምት 1575 ዓ.ም. (1582) በኋላ የጁሊያን አቆጣጠርን ያሻሻለው የጎርጎርዮስ ቀመር በአብዛኛው የአውሮፓ ካቶሊኮች ተቀባይነት በማግኘቱና በተፈጠረው የቀናት መሳሳብ ሌላ የትንሣኤ በዓል ሊፈጠር ችሏል፡፡
የኦርቶዶክስ ፋሲካ የጁሊያንን ቀመር፣ ኢትዮጵያና ኮፕት ደግሞ በራሳቸው ቀመር የኒቅያውን ድንጋጌ ይዘው በመዝለቃቸው ክብረ በዓሉን በአንድ ቀን ያከብራሉ፡፡ በኢትዮጵያና በኮፕት ባሕረ ሐሳብ መሠረት የኢየሱስ ክርስቶስ ስቅለት ዓርብ መጋቢት 27 ቀን 34 ዓ.ም.፣ ትንሣኤው እሑድ መጋቢት 29 ቀን የዋለ ሲሆን፣ በየዓመቱ እነዚህ ዕለታት  የስቅለት መነሻና የትንሣኤ መነሻ ተብለው ይታሰባሉ፡፡
ትንሣኤን ተከትለው ቀናቸው በየዓመቱ የሚዘዋወሩት ጾሞችና በዓሎች የአወጣጥ ሥርዓት መደበኛውን ፀሐያዊ አቆጣጠር ሳይሆን የፀሐይና ጨረቃን ጥምር አቆጣጠር (ሉኒ-ሶላር) ይከተላል፡፡ ይህም በመሆኑ ትንሣኤ በመጋቢት 26 እና በሚያዝያ 30 መካከል ባሉት 35 ቀናት ውስጥ ይመላለሳል፡፡
ጥንታዊ መጽሐፍ ፍትሐ ነገሥት በፍትሕ መንፈሳዊ ክፍሉ ስለ ትንሣኤ በዓል አከባበር እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹… የትንሣኤውን በዓል በዕለተ እሑድ እንጂ በሌላ ቀን አታድርጉ፤ በመንፈቀ ሌሊት ብሉ፤ ያም ባይሆን በነግህ ብሉ. . . ከዚህም በኋላ ፈጽሞ ደስ እያላቸሁ ጾማችሁን በመብል በመጠጥ አሰናብቱ፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሙታን ተለይቶ ተነሥቷልና፡፡››
  • የፋሲካ ቀን ቋሚ ለማድረግ ?
በባሕር ማዶ ከ1920ዎቹ ጀምሮ በየዐረፍተ ዘመኑ የፋሲካ በዓል ቋሚ ቀን ተቆርጦለት እንዲከበር ሐሳብ እየቀረበ ነው፡፡ የሩቁን ትተን ከ2006 ዓ.ም. ወዲህ በአማራጭነት የቀረበውና በካንተርበሪው ሊቀ ጳጳስ ጁስቲን ወልቢ እንደተስተጋባው፣ ‹‹የኤፕሪል ሁለተኛ ወይም ሦስተኛ እሑድ›› ላይ እንዲውል ነው፡፡
እንዲህ ይባል እንጂ የቀረበው ሐሳብ በሌሎች ወገኖች ተቀባይነት እያገኘ አይደለም፡፡ የ325 ዓ.ም. ኒቅያ ጉባኤ ድንጋጌ፣ ምሳሌው በጨረቃ የሚወጣው የአይሁድ ፋሲካ (ፍሥሕ) የሆነለት የክርስቶስ ፋሲካ ስሌቱ በጨረቃ ጭምር የሚገኝ መሆኑ በደነገገበት፣  ተዘዋዋሪነቱን ትቶ እንዴት ቋሚ ይሆናል ብለው ይጠይቃሉ፡፡
የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ፋሲካን የምታከብረው በኒቅያ ድንጋጌ ቀንና ሌሊቱ እኩል 12፣12 ሰዓት ከሚሆንበትና መጋቢት 25 ቀን ላይ ከሚውለው የፀደይ ዕሪና/ እኩሌ (Spring Equinox) ቀጥሎ፣ ከምትታየው ሙሉ ጨረቃ (የአይሁድ ፋሲካ/ፍሥሕ የሚውልበት) በኋላ በሚመጣው የመጀመሪያ እሑድ ስለሚሆን፣ በዓሉ ቋሚ ፈጽሞ አይሆንም ሲሉ ይሞግታሉ፡፡ ይልቅስ ምዕራቦች ከ16ኛው ምእት ዓመት በፊት ከምሥራቆች ጋር በአንድነት ያከብሩት እንደነበረው ወደዚያው እንዲመለሱ ይመክራሉ፡፡