ፋሺስት
ኢጣሊያ በአምስት ዓመቱ ወረራ (1928-1933) ወቅት በእርመኛ አርበኝነት ከተሰለፉት የቁርጥ ቀን ልጆች አንዱ
ሌተና ጄኔራል ጃጋማ ኬሎ (1913-2009) ነበሩ፡፡ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት (1923-1967) እስከ
ጄኔራል ማዕረግ የደረሱትና ‹‹የበጋው መብረቅ›› በሚል መጠሪያ የሚታወቁት ጃጋማ ኬሎ፣ በ96 ዓመታቸው መጋቢት 30
ቀን 2009 ዓ.ም. አርፈው በማግስቱ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈጉባኤ አባዱላ ገመዳና የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ
ተገኝተዋል፡፡
ኦፈን ያ ጃጋማ!!ኦፈን ያ ጃጋማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
ጣሊያን ግራ ገባው መብረቅ አይጨበጥ
ሲያስገመግም እንጂ አይታይ ሲያደፍጥ
ከቶ ምን ፍጥረት ነው እንዲህ የሚያራውጥ!!
ደንዲ አፋፉ ላይ ታይቷል ሲባል ጀግናው
ግንደበረት ወርዶ ጣልያንን አጨደው።
በቡሳ አቋርጦ… በሺ ላይ አድፍጦ
ዱከኖፍቱ አድሮ ጨሊያ ላይ ማልዶ…
ቦዳ አቦን ተሳልሞ ጊንጪ ላይ ብቅ አለ
በጠራራ ፀሐይ መብረቁን ነደለ።
‘ካፒቴኖ ጃጋማ… ካፒቴኖ’ ጣሊያን ቢማፀነው
አገሬን ሳትለቅ ሰላም የለም አለው።
ተመለስ ጃጋማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
ባንዳ ተልከስክሶ ለጠላት ሊሸጣት
አገሬን ሲያስማማት
ክብሬን ሊያዋርዳት
‘ኢንተኡ ፣ ዲዴ’ ብሎ ጃጋማ ካለበት
በቁጣ ገንፍሎ መብረቁን ጣለበት።
ጠላትሽ ኢትዮጵያ ማደሪያ የለውም
የጃጋማ መብረቅ ምቾት አይሰጠውም።
የጠላት ጦር ሰፈር በጭንቅ ተሽመድምዶ
በጠራራ ፀሐይ መብረቅ መጣል ለምዶ
ጃጋማ ጃጋማ ጃጋማ ተወልዶ!!!
ኦፈን ያ ጃጋማ የበረሀው መብረቅ
አንተ ተሸኝተህ ከማን ጋር ሊዘለቅ።
- ከታሪኩ አባዳማ (ሚያዝያ 1 ቀን 2009 ዓ.ም.)
*****
No comments:
Post a Comment