(1913-2009)
የጣሊያን ተስፋፊ ኃይል በ1888 ዓ.ም. ዓድዋ ላይ ድል በተመታ በ40 ዓመቱ  ኢትዮጵያን ዳግም ሲወር፣ ዱር ቤቴ ብለው ከዘመቱት እርመኛ አርበኞች ከግንባር ቀደምቱ ጎራ ይሰለፋሉ፡፡ ‹‹ኧረ ጥራኝ ጫካ ኧረ ጥራኝ ዱሩ…..›› ብለው በተለይ ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. ለአምስት ዓመታት ከፍልሚያው ጎራ በተለይ በምዕራብ ኢትጵያ ከገነኑት የቁርጥ ቀን ልጆች አንዱ ነበሩ፡፡ ሌተና ጄኔራል ጃግማ ኬሎ፡፡ በሽምቅ (ጎሬላ) ውጊያ የተካኑት ‹‹የበጋው መብረቅ›› ጃገማ ገጸ ታሪካቸው እንዲህ ያዘክራል፡፡
ፋሺስቱ የጣሊያን መንግሥት በ1928 ዓ.ም. አገሪቷን በመውረር አዲስ አበባን ሚያዚያ 27 ቀን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ ምዕራቡ የአገሪቷ ክፍሎች በመስፋፋት ጭልሞና ጋጂ አካባቢን ተቆጣጥሮ ይዞታውን ለማስፋፋትና ለሚያደርገው ሙከራ የመሸጋገሪያ ምሽግ ጊንጪ አካባቢ በመሥራት ለመጠቀም ሙከራ ሲያደርግ የነበረ ቢሆንም፣ ሌተና ጄኔራል ጃግማ ኬሎ የመሸጋገሪያ መሥመሮችን በመዝጋትና የደፈጣ ውጊያ በማድረግ የጠላትን ጦር በእንቅስቃሴ ሲገቱ ቆይተዋል፡፡
የበጋው መብረቅ በጦር ሜዳ ውሏቸው በፋሺስቱ የጣሊያን ወራሪ ጦር ላይ ካገኙት አንፀባራቂ ድል አንዱ በኅዳር ወር 1933 ዓ.ም. የተገኘው ነው፡፡ ይህም የአዲስ ዓለምን ጽዮን ማርያም ምሽግ በመሰበር 70 የጣሊያን ወታደሮችን በመግደል፣ 1,500 ጠመንጃ በመማረክ፣ እንዲሁም 80 የወገን እስረኞችን በማስፈታት ከፍተኛ ወታደራዊ ድል ተቀዳጅተዋል፡፡
በመጋቢት 1933 ዓ.ም. በጭልሞ ምሽግና ጊንጪ አካባቢ በተደረገ ከፍተኛ ውጊያም የጠላት ጦር ቅስሙ ስለተመታ መኪና ያገኙት ወደ አምቦ ሲሸሹ ሌሎች ወደ አዲስ ዓለም የሸሹ ሲሆን የሸሹትን እግር በእግር መከታተል፣ በየመንገዱ በመቁረጥና በመበተን የጠላት ጦር ከጥቅም ውጭ እንዳደሩ ራሳቸው የጻፉት የግል የሕይወት ታሪካቸው ያትታል፡፡
የሌተና ጄኔራል የጦር ሜዳ ድል አድራጊነት ዝነኝነት በአገር ሁሉ እየናኘ የመጣ ሲሆን፣ በዚሁ በ1933 ዓ.ም. ወደ ጅማ ከዘመተው የደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ጦር ጋርም  ወታደራዊ ቅንጅት በመፍጠር በደቡብ ምዕራብ የመሸገውን የፋሽስት ጦርን መውጪያና መግቢያ አሳጥተዋል፡፡
በገጸ ታሪካቸው እንደተወሳው፣ በፋሺስት ላይ የፈጸሙት የላቀ ጀብዱና ታላቅ ገድላቸው ‹‹የበጋው መብረቅ›› የሚል የጀግንነት ስያሜ የተሰጣቸው ጄኔራል ጃገማ አገሪቷ ነፃ ከወጣች በኋላና አፄ ኃይለሥላሴ ከእንግሊዝ ስደት እንደተመለሱ ከፍተኛውን ሚና ከተጫወቱት ድንቅ አርበኞች መካከል ስማቸው በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ጄኔራልን ለማየት ካረፉበት ቦታ ሲደርሱ ሠራዊታቸውን በማሰለፍ ብቻ አልተቀበሏቸውም፡፡
‹‹ገዳይ በልጅነቱ
ዶቃ ሳይወጣ ከአንገቱ
ጃጌ ጃገማቸው
እንደገጠመ የሚፈጃቸው
በአባት በእናቱ ኦሮሞ
ፍዳውን አስቆጠረ ከምሮ ከምሮ!›› በማለት በመፎከር ጭምር እንጂ፡፡
የኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ከተረጋገጠ በኋላ ንጉሠ ነገሥቱ አፄ ኃይለ ሥላሴ መንግሥታቸውን ዳግም በየዘርፉ ሲያደራጁ፣ ፍጡነ ረድኤት ሆነው ከተሰለፉት መካከል ጄኔራል ጃገማ አንዱ ነበሩ፡፡ በውትድርናው ዓለም በተለያዩ ክፍለ ጦሮች በተለያዩ የኃላፊነት እርከኖች በመሥራት እስከ ሌተና ጄኔራልነት ደርሰዋል፡፡
በወቅቱ አጠራር ከሐረርጌ ተነጥሎ ራሱን የቻለው የባሌ ጠቅላይ ግዛት፣ እንዲሁም የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ገዢና የግርማዊነታቸው እንደራሴ በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከአራት አሠርታት አገራዊ አገልግሎት በኋላ በ1998 ዓ.ም. ጡረታ ቢወጡም በልዩ ልዩ ማኅበራዊ ተግባራት ውስጥ ከመሳተፍ ወደኋላ አላሉም፡፡
በ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ የኢትዮጵያን አንድነት በሚያቀነቅኑ ፓርቲዎች ውስጥ ተሳታፊ ብቻ ሳይሆኑ ከፍተኛ አመራርነትንም ይዘው ነበር፡፡ ከነዚህም የኢትዮጵያ አንድነት ፓርቲ አባልና ፕሬዚዳንት በመሆን ከ1983-1990 ዓ.ም.፣ በኢትዮጵያዊነት ድርጅት ከ1988 ዓ.ም. ጀምረው ለበርካታ ዓመታት በምክትል ፕሬዚዳንትነት፣ ከሐምሌ 1987 ዓ.ም. ሕይወታቸው እስካለፈበት ጊዜ ድረስ የግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ መታሰቢያ ድርጅት ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት በመሆን  ሠርተዋል፡፡ ከምድር ጦር፣ ከአየር ኃይልና ከባሕር ኃይል የተወጣጡ አንጋፋ መኰንኖች አማካይነት በ1998 ዓ.ም. የተመሠረተው የኢትዮጵያ አገር መከላከያ ቬተራንስ አሶሴሽን የመጀመርያው ሊቀመንበር ሆነው የተመረጡት ሌተና ጄኔራል ጃገማ ኬሎ  ነበሩ፡፡
 በቀድሞው ሸዋ ጠቅላይ ግዛት፣ በጅባትና ሜጫ አውራጃ በደንዲ ወረዳ ዩብዶ በሚባል ሥፍራ፣ ከአባታቸው ከአቶ ኬሎ ገሮና ከእናታቸው ከወ/ሮ ደላንዱ እናቱ ጥር 20 ቀን 1913 ዓ.ም. የተወለዱት ሌተና ጄኔራል ጃገማ ኬሎ፣ በአካባቢው በሚገኘው የቄስ ትምህርት ቤት ፊደል ከቆጠሩ በኋላ ወደ አዲስ አበባ በማቅናት ተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤት ትምህርታቸውን ተከታትለዋል፡፡
ጄኔራል ጃገማ ለአገራቸው ላበረከቱት የላቀ አገልግሎት ከንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና ከተለያዩ አገሮች ኒሻንና ሜዳዮችን ተሸልመዋል፡፡ ከነዚህም መካከል የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ የአንገት ኒሻን፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ የጦር ሜዳ ጀግና ሜዳይ ባለ ሁለት ዘንባባ፣ የዳግማዊ ምኒልክ ኒሻን ከአገር ውስጥ ሲጠቀሱ፣ ከውጭ አገሮችም ከእንግሊዝ፣ ከዩጎዝላቪያና ከላይቤሪያ የተለያዩ ኒሻኖችን አግኝተዋል፡፡
ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ሕክምና ሲከታተሉ የቆዩት ጄኔራል ጃገማ በተወለዱ በ96 ዓመታቸው ዓርብ መጋቢት 30 ቀን 2009 ዓ.ም. አርፈው፣ ሥርዓተ ቀብራቸው በሣልስቱ እሑድ ሚያዝያ 1 ቀን በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በወታደራዊ ሥርዓት ተፈጽሟል፡፡ ለክብራቸውም 21 ጊዜ ሲተኮስ አርበኞችና ወጣት ከያንያን ሽለላና ቀረርት ፉከራም አሰምተዋል፡፡
በመቶዎች የሚቆጠሩ በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ላይ አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳና የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስን ጨምሮ ንጉሣውያን ቤተሰብና የቀድሞ ሹማምንት ተገኝተዋል፡፡
ጄኔራል ጃገማ የአንድ ወንድ ልጅና የአምስት ሴት ልጆች አባት ነበሩ፡፡