አቶ ልዑል ተወልደ መድኅን ካሕሣይ ነዋሪነቱ በካናዳ ቶሮንቶ ከተማ ነው፡፡ ኮምቦልቻ ተወልዶ
አዲስ አበባ ያደገ ሲሆን፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በ1988 ዓ.ም. በአርክቴክቸርና በከተማ ፕላን በመጃመሪያ ዲግሪ ተመርቋል፡፡
ለአምስት ዓመታት የሥራና ከተማ ልማት ሚኒስቴር ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት በሙያው ሠርቷል፡፡ ከ1993 ዓ.ም. ጀምሮ ኑሮውን በካናዳ
በማድረግ በሙያው እየሠራ ሲሆን፣ ባለው የቋንቋ ጥናት ዝንባሌም መሠረት በአማርኛና በትግርኛ ቋንቋዎች ላይ ጥናቱን እያከናወነ ነው፡፡
በቅርቡ “Proposed
Language Reform for Ethiopia” የተሰኘ የጥናት መጽሐፉን በካናዳ ለኅትመት አብቅቷል፡፡ በመጽሐፉና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ አቶ
ልዑልን ሔኖክ ያሬድ አነጋግሮታል፡፡
ሪፖርተር፡- ያዘጋጀኸው መጽሐፍ ምንድን ነው? ይዘቱስ?
አቶ ልዑል፡-
መጽሐፉ የተዘጋጀው በእንግሊዝኛ ነው፡፡ “Proposed Language
Rerform for Ethiopia” የቋንቋ ሕዳሴ ለኢትዮጵያ እንደማለት
ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቋንቋዎቿን ታድስ ዘንድ ጊዜው አሁን ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ በአገሪቱም የቋንቋ አጠቃቀም ተበላሽቷል የሚል እምነት
አለኝ፡፡ እንዲያውም መበላሸት ብቻ ሳይሆን የቋንቋ አጠቃቀም ቀውስ ውስጥ ነች እላለሁ፡፡ መጽሐፉ ውስጥ በዝርዝር ጠቅሼዋለሁ፡፡
ያም የሚያሳድረው ማኅበራዊና ምጣኔ ሀብታዊ ተጽእኖ ይኖራል፡፡ ኢትዮጵያ ለምታልመው ዕድገት እንቅፋት የሚሆኑ ነገሮች በቀውሱ ምክንያት
ይኖራሉ፡፡
ሪፖርተር፡- የቋንቋ አጠቃቀም ቀውስ ውስጥ ነች ሲባል ምንድን ነው ማሳያው?
አቶ ልዑል፡- ቀውስ ያልተጠበቀ ውጤት የሚያስከትል ነገር ነው፡፡ አንድ ሒደት ባንድ
መንገድ እንደሚሄድ ጠብቀኸው ውጤቱ ግን ከዚያ ውጭ ሆኖ ስታገኘው ለያዥ ለገላጋይ ያስቸገረ ነገር ቀውስ ተከስቷል ማለት ነው፡፡
በቋንቋ አጠቃቀማችን ውስጥ ቀውስ ስለመኖሩ እጅግ በርካታ ማሳያዎች አሉ፡፡ ሰዋስዋዊ ጊዜ (ግራማቲካል ቴንስ) አንዱ ነው፡፡ ለምሳሌ
ታምሜ ነበር፣ ታምሜያለሁ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት ስለተከናወኑ ጉዳዮች ይናገራል፡፡ አግባብነት ያለውን ሰዋስዋዊ ጊዜ ካልተጠቀምኩኝ
ግን መልዕክቴ የተዛባ ሊሆን ይችላል፡፡ በመግባባት ውስጥ ሰዋስዋዊ ጊዜ ትልቅ ተጽዕኖ አለው፡፡
ሌላው የሰዋስው ድምፆች አለመስተካከል
በገቢርና ተገብሮ (አክቲቭና ፓሲቭ ቮይስ) የሚታየው ነው፡፡ ‹‹አበበ ጠረጴዛውን ሰበረው››፣ ‹‹ጠረጴዛው ተሰበረ›› ሁለቱ ተመሳሳይ
መልዕክት ስለጠረጴዛው መሰበር አላቸው፡፡ ድርጊት የተፈጸመበት ነገር ጠረጴዛ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ሁለቱ ድምፆች አጠቃቀማቸው ለየቅል
ነው፡፡ ገቢር ድምፅ ድርጊት ፈጻሚው ላይ ሲያተኩር፣ ተገብሮ ግን ድርጊት ተቀባዩ ላይ ነው ትኩረት የሚያደርገው፡፡
በአማርኛና በትግርኛ ላይ የማስተውለው
ሰዎች ድርጊት ፈጻሚውንና ተቀባዩን አዛብተው ያስቀምጣሉ፡፡ ብዙ ናሙናዎች መጥቀስ ይቻላል፡፡ ‹‹ራበኝ›› የሚለውን በምሳሌነት መውሰድ
እንችላለን፡፡ በእንግሊዝኛ እንዳለው ተሸጋጋሪ ግሶች (transitive
verbs) እና ኢተሸጋጋሪ ግሶች (intransitive verbs)
በተጨማሪ በአማርኛና በትግርኛ ውስጥ እኔ እንደደረስሁበት ‹‹ኢተሸጋጋሪ›› በሁለት ይከፈላሉ፤ አክቲቭ ኢተሸጋጋሪና ፓሲቭ ኢተሸጋጋሪ
የሚባሉ አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ገቢርና ተገብሮ ማለት ነው?
አቶ ልዑል፡- እንደዚያ
ሊሆን ይችላል፡፡ የአማርኛውን ስያሜ ቃል ብዙ ስላለመድሁት፡፡ ‹‹ራበኝ›› ስንል ድርጊት ፈጻሚና ድርጊት ተቀባይ ልንከትበት ማለት
ነው፡፡ ይህ የማይሻገር ግስ ስለሆነ መሆን ያለበት ‹‹ተራብሁ›› ነው፡፡ ሌላው ችግር ማብዛት ላይ ነው፡፡ ስሞችን፣ ቅጽሎችን ባጠቃላይ
የቃላት አበዛዝ ላይ ችግሮች አሉ፡፡ አማርኛ የቃላት አበዛዝ ሕግጋት አሉት፡፡ በዢ ቃላትን ሳናበዛ ግን በብዙ ቁጥሮች ብቻ ተጠቅመን
መጥቀስ ተገቢ አይደለም፡፡ ለምሳሌ ‹‹ሁለት በሬ›› ብለን መቆም አንችልም፡፡ ‹‹ሁለት በሬዎች›› እንጂ፤ ረዥም ሰዎች ሳይሆን
ረዣዥም ሰዎች፡፡ ብዜት ላይ የሚታይ ሌላው አንዳንዶች መንግሥታቶች፣ ዓመታቶች ይላሉ፡፡ ይኼ ድርብ ድርብርብ የሆነ የአበዛዝ ነገር
በመሆኑ በሰዋስው አነጋገር ጸያፍ ነው፡፡ ዓመታት ከግእዝ የተወሰደ ነው፡፡ የአማርኛ የማብዣ መንገድ ‹‹ኦች››ን ወስደህ ይህን
ከግእዝ በተወሰደው ብዛት አመልካች ‹‹ኣት›› ጨምሮ ማቅረብ አይገባም፡፡ ከግእዝ የተወረሱት የአበዛዝ መንገዶች ፎርም ከሥነ ጽሑፍ
አንፃር ተወዳጅነት አላቸው፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ አንዱን መጠቀም ተገቢ ነው፡፡
ቀጥሎ
ልጠቅስ የምችለው የቃላት አመራረጥ ነው፡፡ ከዚህ ጋር የሚያያዙ ይፋዊና ይፋዊ ያልሆኑ አነጋገሮች አሉ፡፡ ሊገኙ የማይገባቸው ቦታ
ላይ የሚገኙ መንደርኛ አነጋገሮች አሉ፡፡ የቃላት አመራረጥን ስንመለከት የቃላት እጥረት ወይም ድህነት አለብን፡፡ ከብዙ አሠርታት
በፊት ጀምሮ የታወቀ ድህነት ነገር ነው፡፡ አፄ ኃይለሥላሴ ለአንድ የቋንቋ ባለሙያ በ1920ዎቹ በጻፉት ደብዳቤያቸው ላይ የቋንቋ
ድህነት እንዳለብን ጠቅሰው ነበርና የታወቀ ነው፡፡ ቮካብለሪያችን ወይም የቃላት ብዛት የለንም፤ ሲኖሩንም በአግባቡ አንጠቀምባቸውም፡፡
ለምሳሌ
ሰዎች ‹‹ከእንቅልፌ ተነሳሁ›› ወይም ደግሞ ‹‹ተነሳሁ›› ይላሉ፡፡ ከመኝታ መንቃታቸውን ለማሳየት መሆን ያለበት ነቃሁ ነው፡፡
መነሳት በአካል ብድግ ብሎ መውረድን ያካትታል፡፡ አካላዊ ነገር ነው፡፡ መንቃት ግን አዕምሮአዊ ነገር ነው፡፡ እነኚህ በማኅበራዊ
ሕይወት ብዙ ለውጥ ላያመጡ ይችላሉ፡፡ በሕክምና ወይም በሌሎች ረቂቅ አገባብ ላይ ግን ቁብ አላቸው፡፡ ስናድግ ሮኬት ወደ ሰማይ
ማምጠቃችን፣ የኒኩለር ፊዚክስ፣ የአንጎል ቀዶ ሕክምና መሥራታችን አይቀር ይሆናል፡፡ እነዚህ ነገሮች በራሳችን ቋንቋ ልናከናውን
የምንችልበት ብቃቱን ማዳበር የምንችለው ካሁኑ ነው፡፡
ሌላው
ችግር የባዕዳን ቃላት በብዛት የመጠቀማችን ነገር አሳሳቢው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ሥር ሰዷል፡፡ የባዕዳን ቃላትን ያለመከልከል
የመጠቀማችን ነገር ሰነፎች እንድንሆን አደረገን፡፡ የራሳችንን ቃላት እንዳንፈልግና እንዳናዳብራቸው አደረገን፡፡
ስለዚህ በስንፍና ባዕዳን ቃላት ላይ
ማተኮር ጀመርን፡፡ ባሁን ዘመን ተስፋፍቶ የሚገኘው እንግሊዝኛ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ፈረንሣይኛና ሌሎች ቋንቋዎች ነበሩ፡፡ ያኔ ያሁኑን
ያህል ብርታት አልነበራቸውም፤ ምክንያቱም ቴክኖሎጂው፣ ግሎባላይዜሽንም አልነበረም፡፡ ትምህርትም ብዙም ተስፋፍቶ ስላልነበር ድሮ
ይመጡ የነበሩት ባዕዳን ቃላት ጊዜ ጠብቀው ዓመታትን ፈጅተው ይቀላቀሉ ነበር፡፡ ቋንቋም በቃላት ረገድ በዚያ በኩል ስለሚያድግ ብዙ
አስጊ አልነበረም፡፡ አሁን ያለው ግን ቋንቋዎችን ሊደፈጥጥ ሊጨፈልቅ ሰዋስውንም ሊያበላሽ በሚችል መንገድ እየገቡ ነው፡፡ እንደደረስሁበትና
መጽሐፌ ላይ እንደጠቀስሁት፣ የኛን ቋንቋዎች ሰዋስው የሚጎዱት የእንግሊዝኛ ግሶች ናቸው፡፡ ስሞችና ቅፅሎችም ጉዳት ያደርሳሉ፣ ግሶች
ግን የዐረፍተ ነገሮች መሠረታዊ አካል፣ የዐረፍተ ነገሮችን ቅርፅ (መዋቅር) እና ግንባታ ወሳኝ በመሆናቸው ትኩረት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡
ሪፖርተር፡- ከሥርዓተ ጽሕፈት ጋርስ የሚነሳ ነገር፤
አቶ ልዑል፡- የቋንቋው
አጠቃቀም ቀውስ ሌላው ገጽታ ከጽሕፈት ጋር የሚያያዝ ነው፡፡ ከዚህ ላይ የማያቸው በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ የመጀመሪያው የኛ ፊደል
አልፋቤታዊ አለመሆኑ ነው፤ ሲሌቢክ (ቀለማዊ) ነው፡፡ አልፋቤታዊ ተነባቢና አናባቢ ያሉት ፊደል መሆኑ ነው፡፡ የኛ ፊደል ግን ተነባቢና
አናባቢው በሆሄያት ውስጥ ተቀላቅለው ስላሉ ስላልተነጣጠሉ አልፋቤታዊ አይደሉም፡፡ ቀለማዊ ፊደል ናቸው፡፡ ለ1,700 ዓመታት ያህል
ድንቅ ሥራ የሠራ ሀገራችንን ከሌሎች ሀገሮች ያልተናነሰ የጽሕፈት ባህል ያላት ሀገር ያደረገ ፊደል ነው፡፡ ልንኮራበት ልንመካበት
የሚገባ ፊደል ነው፡፡
ነገር
ግን አሁን ሌላ ወቅት፣ ሌላ ትውልድ፣ ሌላ ቴክኖሎጂያዊ ፍላጎት ላይ ደርሰናል፡፡ ይህንን የደረስንበትን የቴክኖሎጂ ዘመን የመግባቢያ
ፍላጎት እየጎለበተ ለማሳካት የሚበቃ ዓለማቀፋዊ ብቃት ያለው ፊደል ሊኖረን ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ ቀለማዊ ስለሆነ አዲስ ድምፅ
በመጣ ቁጥር አዲስ ቀለም መፍጠር ሊኖርብን ሆነ፡፡ ወይም ድምፆች በተለያየ ሁኔታ ሲዋዋጡ ሌላ መልክ ይሰጧቸዋል፡፡ አንዳንድ የተባዙ
ቃላትን ተመልክቶ መሠረታዊ ቃሉ የቱ እንደነበረ ለማወቅ አስቸጋሪ ይሆናል፡፡ ያ ደግሞ ሌላ የሚያመጣው የስፔሊንግ ወይም የፍደላ
ችግርን ነው፡፡ አንዱን ቃል እንዴት ነው የምፈድለው (ስፔል የማደርገው)፣ አንተ ከምትፈድለው የተለየ ሊሆን ይችላል? በአክሰንትም
ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ቀለሞቹ መሠረታዊ የሆነውን የቃሉን ፊደሎች ስለሚያዛቡ ማለት ነው፡፡
ከሥርዓተ
ጽሕፈት ጋር በተያያዘ ሁለተኛው ችግር ያልኩት የሆሄያት አላግባብ የመብዛት ነገር ነው፡፡ በአማርኛ መሠረታዊ እቅፍ ውስጥ ያሉት
ሆሄያት 33 ናቸው፡፡ እንደገና ሰባት ዐምዶች አሉ፡፡ ሲባዙ 231 ይሆናሉ፡፡ ቅጥያ እቅፍ ውስጥ ያሉ ሆሄያት ሏ፣ ሟ፣ ሯ፣ ሷ፣…
የሚባሉት ሲታከሉበት ቁጥሩ ይጨምራል፡፡ በኦሮምኛና በሌሎች ቋንቋዎች እነሱንና ሌሎች ምልክቶችን ስንደምር ወደ 500 የሚጠጉ ዩኒኮድ
ውስጥ የገቡ የኢትዮጵያ ሆሄያት ወይም ቀለማት አሉ፡፡ ፓንኩቴሽን መብዛቱ ችግር የለውም፡፡ ለጽሑፍ የምንጠቀምባቸው መሠረታዊ ሆሄያት
ግን መብዛት የለባቸውም፡፡ ትምህርት ላይ የሚያሳድሩት አሉታዊ ተጽዕኖ አለ፡፡ ልጆች ፊደልን ለማጥናት የሚፈጅባቸውን ጊዜ የሚወስደው
አሰልቺና አስቸጋሪ መንገድ ሊወገድ ይገባዋል፡፡
ሌላው
የሆሄያቱ መብዛት የሚያስከትለው ችግር መዝገበ ቃላት ውስጥ ቃላትን ስንደረድር ፊደላዊ ቅደም ተከተልን ተከትለው እንዲመጡ ማድረግ
አለብን፡፡ ሆሄያቱ ከበዙ ግን ያንን ቅደም ተከተል እንድንስት ያደርጋሉ፡፡ አብዛኛው ሰው ቅደም ተከተሉን አያስታውሰውም፡፡
ሁሉንም ለማስታወስ አስቸጋሪ ነው፡፡
ምክንያቱም ቅደም ተከተላችን በቁመት አለ፣ እንደገናም በወርድ አለ፡፡ ሀለሐመሠረሰ ካልን በኋላ እንደገና ሁሂሃሄህሆ፡፡ የበለጠ
አስቸጋሪ ያደርጉታል፡፡
ሪፖርተር፡- የሆሄያት መብዛት በተመለከተ አንዳንዶች ‹‹ለአንድ ድምፅ አንድ ምልክት›› የሚል ሥነ
ልሳናዊ እይታ የሚያራምዱ አሉ፡፡ አማርኛ የወረሰው የግእዙን የፊደል ገበታ ነው የሚል ነገር አለ፡፡ አማርኛ የሞክሼ ሆሄያት ነባር
ድምፅ ጠፍቶበታል፡፡ በሌላ በኩል በአገባብ ላይ ትርጉም ሊያመጣ የሚችል ይኖራል፡፡ ሥርዓተ ጽሕፈትን ለማስተካከል ምን መደረግ አለበት
ትላለህ? በመጽሐፍህ የሰጠኸው የመፍትሔ ሐሳብ ምንድን ነው? ለምሳሌ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች አካዴሚ ሞክሼዎቹን ሆሄያት አስወግዶ ያዘጋጀው
መዝገበ ቃላት አለ፡፡
አቶ ልዑል፡- በአማርኛ
ከአንድ በላይ ቀለማት አንድ ድምፅ ወክለው ይገኛሉ፡፡ ወይም ደግሞ ለአንድ ድምፅ ተጠሪ ሆነው ይገኛሉ፡፡ በሌሎች ቋንቋዎች ለምሳሌ
በትግርኛና በግእዝ የየራሳቸው አገባብ አላቸው፡፡ ለምሳሌ ሀሌታው ሀ፣ ሐመሮ ሐ በትግርኛ የተለያየ አገባብ ነው ያላቸው፡፡ ድምፆቻቸውም
እንዲሁ የተለያየ ነው፡፡ በግእዝም እንደዚያ እንደነበር መገመት አያዳግትም፣ የታወቀም ነው፡፡ በኋላ ላይ ግን አማርኛ ድምፆቹን
እየሳተ፣ ድምፆቹን እያቀራረበ ሄደና የተወሰኑ ቀለሞች አንድ ድምፅ ብቻ እንዲተኩ እየሆኑ ሄዱ፡፡ ለምሳሌ አሌፉን አ እና ክቡን
ዐ ብንመለከት በትግርኛ የተለያዩ ድምፆች ነው ያላቸው፤ በግእዝም እንደዛው፡፡ በአማርኛ ግን አንዳይነት ነው፡፡ ሁለቱን ፀ፣ጸ ብንመለከት
ትግርኛ አንዱን ከፊደሉ አውጥቶታል፡፡ አማርኛ ግን ሁለቱን አቅፎ በአንድ ድምፅ ይዟል፡፡ ስለዚህ አሻሚ ናቸው፡፡ ፀሐይን የተለያዩ
ሰዎች በተለያየ መንገድ ነው የሚፈድሉት፡፡ መጽሐፌ ላይ አስፍሬዋለሁ፣ ለፀሐይ ብቻ ዐሥር የተለያዩ የአፈዳደል (ስፔሊንግ) ዓይነቶች
አሉ፡፡ ይኸ ለዕድገት ጠቃሚ አይደለም፡፡ ሥርወ ቃላዊ (ኢቶሞሎጂካል) የሆኑ የቃላት መሠረት ተከትለህ ‹‹ዓይን›› የትኛውን እንደምትከተል
‹‹አሥር›› ወይም ‹‹አንድ›› ለሚለው የትኛውን እንደምትጠቀም ወደ ግእዙ ሄዶ መመልከትና ርሱን አስታከን እንምጣ የሚለውን ነገር
መጠቀም ይቻል ነበር፡፡ ከዚህ ቀደም የተለያዩ ምሁራን ሐሳቡን አቅርበው ተሞክሯል፡፡ ውጤቱ ግን እንደዚያ ሊሆን አልቻለም፡፡
አማርኛ
ድምፆቹን አስቀድሞ ስለረሳቸው የአፈዳደል ችግር እንዲፈጠርብን አድርጓል፡፡ ቃላቱን በመዝገበ ቃላቱ በአግባቡ ካልደረደርናቸው አንድ
ሰው ቋንቋን ለመማርም ሆነ ቋንቋን ለማሳደግ የተቀመጠ ነገር ላይኖረን ማለት ነው፡፡
የማቀርበው
የመፍትሔ ሐሳብ እነኚህ ሆሄያት በመብዛታቸው ምክንያት የተፈጠረብን ችግር እጅግ ብዙ በመሆኑ ከዚህ በፊት ኢቶሞሎጂካሊ የሆነ ዓይነት
ድምፅ የነበራቸውን ቀለማት ችላ ብለን አንድ ዓይነት ሆሄ ብቻ ስለሰጠናቸው የሚመጣው ችግር ብዙ አይደለም፡፡ ከዚያ ይልቅ ቃላቱ
የሆሄያትን ብዛት ቀንሰን በአግባቡ ያሉንን ብንጠቀም የሚመጣው ጥቅም እጅግ በጣም የበዛ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ሰዋስውን (ግራመርን) በተመለከተስ ያነሳኸው ነጥብ አለ? በዘመናችን እንደ ክፍተት የሚነሳው
የአማርኛ ሰዋስው እንደቀደመው ጊዜ እምብዛም ትኩረት እንዳላገኘ ይነገራልና፡፡
አቶ ልዑል፡- ስለሰዋስው
በመጠኑ ጠቅሼያለሁ፡፡ የሚቀጥለው መጽሐፌ ግን ሙሉ በሙሉ ስለሰዋስው የምገልጽ ይሆናል፡፡ ሰዋስው ለአንድ ቋንቋ መሠረታዊ ነገር
ነው፡፡ የመግባቢያ ደንብ የቋንቋን ሕግጋት ይዟል፡፡ ለሒሳብ ሕግጋት እንዳሉት ሁሉ ለቋንቋም አሉት፡፡ ታሪካችን ቋንቋችን ብለን
ለመኩራራት ሳይሆን የሰዋስው ሕግጋት እኛን እንድግባባ መሠረት ስለሚሆኑን ነው፡፡ እኔ የምረዳው የሰዋስው ሕግ ተጠቅመህ አንተ ስታናግረኝ
ሐሳብህ ምን እንደሆነ ያለጥርጥር እረዳሃለሁ፡፡
ሰዋስውን
መማር ተገቢ የሚሆነው ስለዚህ ነው፡፡ በዓመታት ውስጥ ለውጥ እንደሚኖርም ይታወቃል፡፡ ለውጥ ሲከሰት በከተማና በገጠር፣ ወይም በተማረውና
ባልተማረው፣ በውጭ አገርና በአገር ውስጥ ባለው መካከል መግባባት ላይኖር ፍትሕ ሊጠፋ ነው ማለት ነው፡፡ መልካም አስተዳደር ከቋንቋ
ጋር የተያያዘ ነገር እንዳለው በመጽሐፌ ውስጥ አበክሬ ጠቅሻለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በቋንቋ ውስጥ መዋዋስ ያለ ነገር ነው፡፡ እንግሊዝኛ ከላቲን ይወሰዳል፣ አማርኛም ከግእዝ
እንዲሁ፡፡ ለክብረትም ለክብደትም ተብሎ የሚወሰዱ ቃላት አሉ፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ‹‹ሳይቸግር ጤፍ ብድር›› ሆኖ ገላጭ ቃላት እያሉ
ባዕድ ቃላት እየገቡ ነው፡፡ ለምሳሌ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ዳይሬክቶሬት፣ ዳይሬክተር ጄኔራል፣ ትራንስፎርሜሽን ወዘተ እየታዩ ነው፡፡
መምሪያ፣ ዋና ዳይሬክተር፣ ውላጤ ማለት እየተቻለ በመዝገበ ቃላቱ ውስጥም ኖረው አገልግሎት እየሰጡ እያሉ መጠቀም አልተፈለገም፡፡
አቶ ልዑል፡- ለአንዳንድ
ቃላት አቻ ስያሜ መፍጠር ይቻል ነበር፡፡ የትምህርት ቤት ዳይሬክተርን ርዕሰ መምህር ተብሎ እንደተጠራው ማለት ነው፡፡ ጥሩ ቃል
ነው፡፡ የውጭ ቃላትን በመፍቀዳችን ምክንያት ችግር መጥቷል፡፡ አንዴ የከፈትከው በር መልሰህ ለመዝጋት በጣም አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡
ቋንቋው እንዲበከል በማድረጋችን ሰዎች ለተራ ቃላት እንኳ ጠረጴዛ፣ ወንበር፣ ሳጥን፣ መኪና፣ ሕንፃ፣ እናት፣ አባት እንግሊዝኛ መጠቀም
ጀመሩ፡፡ አንዳንዴ ግለሰቦችን መውቀስ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው፡፡ በአፄ ኃይለሥላሴ ቀዳሚ ዘመን ከሁለተኛ ደረጃ ጀምሮ በእንግሊዝኛ
መስጠት የተጀመረው በወቅቱ ብቁ የሆኑ መምህራን ባለመኖራቸው ከእንግሊዝ፣ አሜሪካ፣ ሕንድ መጥተው ያስተምሩ ስለነበር ነው፡፡
እኛ
በቅኝ ሳንገዛ ኖረን አሁን ብዙ የተማረ ኃይል ኖሮ እንዴት በውጭ ቋንቋ ብቻ ትምህርቱ ይሰጣል? ያኔ የነበረው የመምህራን እጥረት
አሁን የለም፡፡ በእንግሊዝኛ እስከ 21ኛው ክፍል ዘመን ዕውቀትን ትምህርትን ለምን እናስተላልፋለን፡፡ ባንድ በኩል ስናየው መንግሥት
የቋንቋ አጠቃቀም ላይ የተዛባ ፖሊሲ ስላለው የመጣ ነገር ነው፡፡ በተለያዩ ጊዜያት እንግሊዝኛ የመማርያ ቋንቋ እንዳይሆን ባለሙያዎች
በወቅቱ መክረው ነበር፡፡ በደርግ ዘመን በትምህርት ሚኒስቴር ተቋቁሞ የነበረ አንድ የጥናት ቡድን እንግሊዝኛው ቀርቶ በአማርኛ እንዲሆን
ሐሳብ አቅርቦ ነበር፡፡ [በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለመጀመሪያ ዓመት የፍልስፍና ትምህርት በአማርኛ ለአንድ ዓመት ተሰጥቶ ነበር]
በወቅቱ ጦርነትና ረሀብ የተለያየ ችግርም ስለነበረ አርቀን ማሰብ አልቻልንም፡፡ የአስተሳሰብ እጥረት ነው፡፡ ማንም ሀገር በባዕድ
ቋንቋ ተጠቅማ ያደገች የለችም፡፡ ቻይና፣ ጃፓን፣ ኮሪያ፣ እስራኤል በራሳቸው ቋንቋ የበለጸጉ ናቸው፡፡ ከየት በመጣ ሞዴል ነው በተውሶ
ቋንቋ እየተንገዳገድን የምንማረው? ይህ ክስተት ያመጣው ከእነዚህ ተቋማት የወጡ ምሁራን ሳይማር ያስተማራቸውን ገበሬውንም ሌላውን
ኅብረተሰብ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መለማመጃ ያደርጉታል፡፡ ኅብረተሰቡ ምን እየተናገሩ እንደሆነ ላይገነዘብ ይችላል፡፡ እንደ ሕዝብ ልናፍር
ይገባል፡፡ ባለሥልጣናት ያለመከልከል የእንግሊዝኛ ቃላትን እየቀላቀሉ ሲናገሩ ይደመጣል፡፡ ይህ የመልካም አስተዳደር እጥረት፣ ጉድለት
ነው፡፡ ኢፍትሐዊ ነው ብዬ የማምነው፡፡ መንግሥት በዓዋጅ ደረጃ የአገሪቱ መማሪያ ቋንቋ ማስተካከል ይገባዋል፡፡
በሌላ በኩል ማስታወቂያዎች በጣም
በሚገርም ሁኔታ በውጭ ቋንቋ ተወረዋል፡፡ ከአገሬ ከመውጣቴ በፊት አብዛኞቹ በየመንገዱ የሚለጠፉም ሆነ በጽሑፍ የሚሠራጩት ባብዛኛው
በአገር ቋንቋ ነበር፡፡ አሁን ግን አንዳንዱ እንዲያውም የአገር ቋንቋ ፈጽሞ የሌለባቸው ማስታወቂያዎችም ተመልክቻለሁ፡፡ በጣም ነው
የማዝነው፤ በዓዋጅ የቋንቋ ፖሊሲ አውጥቶ ማስገደድ አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- የመጽሐፉ ተደራሽነት ለማን ነው? በእንግሊዝኛ ቋንቋ ተዘጋጅቶ በካናዳ ነው የታተመው፤
በአማርኛስ አዘጋጅተኸዋል?
አቶ ልዑል፡-
ተደራሽነቱ ለመንግሥት ሰዎች ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለትምህርት ሚኒስቴርና ለሚመለከታቸው አካላት ነው፡፡ ፊደልን ያለአዋጅ ሕዳሴ
ማድረግ አይቻልም፡፡ ምሁራንም ሊተቹበት ይገባል፡፡ በአማርኛ ያልጻፍኩት በስንፍና በቸልታ ምክንያት አይደለም፡፡ የተለያዩ ምክንያቶች
ነበሩ፡፡ አንደኛው እንዲታደስ ሐሳብ የማቀርብበት ቋንቋ ራሱና ሥርዓተ ጽሑፉን ተጠቅሜ መጽሐፍ ብጽፍ ለማስረዳት እጅግ አድካሚ ይሆናል፡፡
ሌላ እንደምንም ተቸግሬ ልጻፍ ብል
የሚመጣው ችግር ቴክኒካዊ ቃላትን በምን ልተካቸው እችላለሁ? በዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተሠሩትን አላየኋቸውም፤ አቻ ቃላትን ለማምጣት
የራሴን ትርጉም ከሰጠሁት ሌሎች ላይረዱ ይችላሉ፡፡ መጀመሪያ ትኩረት መስጠት የምፈልገው የቋንቋ ሕዳሴና የፊደላቱ ሕዳሴ ይሆናል፡፡
እዚህ ላይ ቃላት የምፈጥር ከሆነ ሰዎች ስለማይገነዘቡት ለነርሱ ለማስረዳት ሌላ ጣጣ ውስጥ መግባት ይሆናል፡፡ እነኚህ የመሰሉ ምክንያቶች
አስገደዱኝ፡፡ በውጭ ዓለሙ የመታተሙ ነገር ነዋሪነቴ እዚያ በመሆኑ ነው፤ መንግሥት ግን የተወሰኑ መጻሕፍትን ገዝቶ በተለያዩ ቤተ
መጻሕፍት በማስገባት ለተጠቃሚዎች ለአንባቢዎች መድረስ ይችላል፡፡ አነስተኛ ወጪ አውጥቶም ኅብረተሰቡ በሚገባው መልኩ ማስተርጐም
ይችላል፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ የራሷ አኀዝ (ቁጥር) አላት፤ ግን እምብዛም አይታወቅም፡፡ መጻሕፍት ሲታተሙ
ከዋናው ገጽ በፊት ያሉት ገጾች ለማመልከት ከግእዝ ቂጥር ይልቅ የሮማን ቁጥር ይጠቀማሉ፡፡ ከዚህስ አንፃር የምትለው ምንድን ነው?
አቶ ልዑል፡- የቁጥር
ምልክቶቻችንን አለማወቅ እጅግ አሳዛኝ ነው፡፡ እንዲያውም በኢትዮጵያ የቋንቋ አጠቃቀም ቀውስ ስለመኖሩ ከሚያሳየን ነገር አንዱ የቁጥራችን
ጉዳይ ነው፡፡ አንድ ሰው የሮማን ቁጥርን ተጠቅሞ Ⅲ አሳይቶ፣ የግእዙን ፫ ላያሳይ መፍቀዱ
ከአዕምሮዬ በላይ ልገነዘበው በፍጹም አልችልም፡፡ ኢንዶ አረቢክ የሚባለው ከ0 እስከ 9 ያለው የቁጥር ምልክት ዓለማቀፋዊ መግባቢያ
ሆኗል፡፡ ስሌትን ያለነርሱ መሥራት አይቻልም፡፡ የሮማንም ሆነ የግእዝ ቁጥሮች ለረቀቀ የዴሲማል ሒሳብ ሊሆኑ እንደማይቻል ይታወቃል፡፡
ነገር
ግን ታሪካዊ የሆኑ የሮማን ቁጥሮችን ለመጠቀም በሚያስችል አቻ መልክ ላሉ ቦታዎች ሁሉ የራሳችንን የግእዝ ቁጥሮች መጠቀም የማንችልበት
ምንም ምክንያት የለም፡፡ የግእዝ ቁጥሮችን ልንጠቀምበት የሚገባው ቦታ የመኪና ታርጋዎች ላይ ነው፡፡ እዚያ መደመር መቀነስ የለም፡፡
ቋሚ ነገር ሰለሆኑ ኅብረተሰቡም ሊያጠናቸው ይችላል፡፡ የመንገድ አመልካችና የቤት ቁጥሮችም ላይም መጠቀም ይገባል፡፡
ችግሩ የግለሰቦች ድክመት አይደለም፡፡
የመንግሥት ድክመት ነው የቋንቋ ራዕይ ስለሌለን ነው፡፡ ግለሰብ እስከተወሰነ ድረስ ነው የሚጥረው፤ ከዚያ በኋላ ይደክማል፡፡ ችግሩ
መቀረፍ ያለበት ከሥርዓተ ትምህርቱ ጀምሮ ነው፡፡ እነዚህ ያገራችን ቁጥሮች በትምህርት ቤት ይሰጣሉ ወይ? መታየት አለበት፡፡ የመማርያ
ቋንቋ በእንግሊዝኛ እስካደረግን ድረስ ከግድግዳ ጋር እንደመጣላት ነው፡፡ የመማርያ ቋንቋ ቢያንስ ቢያንስ እስከ 12ኛ ክፍል ድረስ
በአማርኛ መሰጠት አለበት፡፡ ክልሎች የራሳቸው ቋንቋ እንዳላቸው እናውቃለን፡፡ የአገሪቱ የሥራ ቋንቋ አማርኛ ስለሆነ እስከተወሰነ
ድረስ መሰጠት አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- ቋንቋና ፊደል በተመለከተ መነገር አለበት የምትለው ለየት ያለ ሐሳብ ምንድን ነው?
አቶ ልዑል፡- የቋንቋን
ሕዳሴ አስመልክቶ የተለያዩ አገሮች በተለያዩ ዘመኖችና ትውልዶች የቋንቋን ሕዳሴ አድርገዋል፡፡ እኛም ራሳችን ከዚህ በፊት አድርገን
ነበር፡፡ በመጽሐፌ ላይ እንደጠቀስኩት በንጉሥ ኢዛና ዘመነ መንግሥት ፊደላችን የመጀመሪያው የግእዙ ዐምድ ብቻ ሆይ፣ ሎይ፣ ሐውት፣
ማይ፣ ዛት… ነበር፡፡ በኋላ በዒዛና ከካዕብ እስክ ሳብዕ ዐምዶች ተጨመሩ፡፡ እና ትልቁ የፊደል ሕዳሴ የተደረገው በንጉሥ ዒዛና
ዘመን ነበር፡፡ ከዚያ ወዲህ በተለያዩ ዘመናት አነስተኛ ሕዳሴዎችም ተደርገዋል፡፡ ለምሳሌ ግእዙን እንደ ቋንቋ መጠቀም ካቆምንና
አማርኛ ብሔራዊ ቋንቋ መሆን ከጀመረ በኋላ፣ ከኩሽ ቋንቋዎች ከኦሮምኛ፣ አገውኛ የገቡ ድምፆች ነበሩ፡፡ እንደነጨ፣ ጀ እና ቨ ገብተዋል፡፡
ይኼ የአሁኑ መጽሐፌ የዚያ ተከታይ ነው፡፡ ቱርክ የቋንቋና የፊደላት ሕዳሴ ነበር ያደረገችው፡፡ ብዙ አገሮች የፊደል ሕዳሴ የአንድ
ያፈዳደል (ስፔሊንግ) ወይም የአንድ ሆሄ ሕዳሴ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡
ላስተላልፍ
የምፈልገው መልዕክት ይህ ትውልድ መስዋዕትነት ከፍሎ ለሚቀጥለው ትውልድ የተለየች ኢትዮጵያን ይፈጥር ዘንድ አሁን የጀመርነውን ምጣኔ
ሀብታዊና ማኅበራዊ ዕድገት በበለፀገ መንገድ ይቀጥል ዘንድ ማስቻል አለብን፡፡ እስካሁን ያሉት የረቀቀ የቋንቋ መግባቢያ መንገድን
አልጠየቁንም፡፡ ከአሁን በኋላ የሚመጡት የረቀቀ የመግባቢያ ቋንቋ መጠየቃቸው አይቀርም፡፡ የኒኩለርና ሌሎች ሥራዎችን መጥቀስ ይቻላል፡፡
እነዚህንና ሌሎችን ለማድረግ መሠረቱን ካሁኑ መጣል አለብን፡፡ አባቶቻችን ከራቀው የጥንት ዘመን ተነስቶ፣ ከቅርቡም ከአፄ ምኒልክ
ጊዜ ጀምሮ የቋንቋ አጠቃቀማችን ለማደስ ብዙ ደክመዋል፡፡ እኛም በዚህ ትውልድ ስኬታማ እንዲሆን ሁላችንም የተቻለንን እናድርግ፡፡
No comments:
Post a Comment