አፍሪካ ፖለቲካዊ አንድነት ከመመሥረቷ በፊት በእግር ኳስ አንድነትን የጀመረችው በ1949 ዓ.ም. በሱዳን ካርቱም ከተማ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ፣ ሱዳን፣ ግብፅና ደቡብ አፍሪካ ተወካዮቻቸውን በመላክ ባደረጉት መሥራች ጉባኤ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) እውን ሆኗል፡፡
በመሥራች ጉባኤው ላይ የተሳተፉት ኢትዮጵያውያን አቶ ይድነቃቸው ተሰማና ሻለቃ ገበየሁ ዱቤ (በኋላ ኮሎኔል) ሲሆኑ፣ ግንባር ቀደሙ አቶ ይድነቃቸው የመጀመሪያው ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው ለ15 ዓመታት ካገለገሉ በኋላ፣ ከ1964 ዓ.ም. ጀምሮ አራት ጊዜ በመመረጥ ሕይወታቸው እስካለፈበት 1979 ዓ.ም. ድረስ መርተዋል፡፡
አቶ ይድነቃቸው ፕሬዚዳንታዊ ሥልጣናቸውን ለሁለተኛ ጊዜ ያስቀጠሉት 10ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ኢትዮጵያ በ1968 ዓ.ም. ባስተናገደችበት ጊዜ ነበር፡፡ በየካቲት 1968 ዓ.ም. በአዲስ አበባው የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ 12ኛው የካፍ ጉባኤ ሲካሄድ በከፍተኛ ድምፅ መመረጣቸው ይታወሳል፡፡
ይህ የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡ ፀሐይ የሞቀው፣ ዓለም ያወቀው ክንውን ነው፡፡ ይሁን እንጂ በሳምንቱ አጋማሽ ኢትዮጵያ ያስተናገደችው 60ኛው ዓመት የካፍ አልማዝ ኢዮቤልዩ በዓልና 39ኛው የካፍ ጉባኤ ሲካሄድ፣ የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሹማምንት ርዕሰ ብሔሩ ጭምር በይፋ በአፍሪካ ኅብረት አደባባይ ጉባኤው በአዲስ አበባ የተዘጋጀው ‹‹ከ51 ዓመታት በኋላ›› ነው ብለዋል፡፡
እንዴት ነው ነገሩ? ታሪክ በዘፈቀደ ሆነሳ?
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ በዋዜማውና በምርጫው ዕለት በተደጋጋሚ ‹‹ከ51 ዓመታት በኋላ›› ጉባኤውን ለመጀመሪያ ጊዜ አዘጋጀን አሉ፡፡
ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የታሪካዊ ሰነድ ድሃ መሆኑን ያመላከተ ነው፡፡ ወቅትን ከክስተት፣ ነውን ከነበር የሚያጣቅስ የኢትዮጵያና የአፍሪካ የእግር ኳስ ትስስራዊ ታሪክ በአግባቡ ሰንዶ አለመያዙን ያወጀበት መድረክ ነው፡፡
የዕለት እንጂ የዓመታት ጉዳይ ከቁብ አልተቆጠረም እንዴ? እንዴት ነው ነገሩ?
የካፍ ጉባኤን መጋቢት 7 ቀን 2009 ዓ.ም. በአፍሪካ ኅብረት ኒልሰን ማንዴላ አዳራሽ በይፋ የከፈቱት ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ፣ ጉባኤው ‹‹ከአምስት አሠርታት በኋላ›› (after five decades) በአዲስ አበባ መካሄዱን ተናግረዋል፡፡ ለርሳቸው ንግግር ምንጩ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ በተለይም የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር መሆኑ ይታመናል፡፡ ሚኒስቴሩ ታሪክ እንዳይዛባ አገርም ከግምት ውስጥ እንዳትገባ የሚጠብቅ ቃፊር የለውም እንዴ?
የሚኒስቴሩ መዝገብ ቤት (የማኅደር ክፍል) ቀደምት ሰነዶችስ የሉትም እንዴ እንዴት ነው ነገሩ?
ሌላው ቢቀር ‹‹የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ሊቀመንበር ጽሕፈት ቤት›› በቁጥር 3690/6የ/68፣ ሰኔ 23 ቀን 1968 ዓ.ም. የላከው ደብዳቤ ከመዝገብ ቤት ቢያይ ኖሮ ‹‹ከአምስት አሠርታት፣ ከ51 ዓመታት›› በኋላ የተካሄደው ጉባኤ ተብሎ ባልተነገረ ነበር፡፡
ከ41 ዓመታት በፊት፣ ብርጋዲየር ጄኔራል ተፈሪ ባንቴ፣ የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ሊቀመንበር፣ በወቅቱ የስፖርትና የአካል ማሰልጠኛ ድርጅት ኮሚሽነር ለነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ በጻፉት ደብዳቤ፣ እንደገና የካፍ ፕሬዚዳንት ሆነው መመረጣቸው ኢትዮጵያን ያኮሩ መሆናቸውን ያመለከቱት በዚህ መልኩ ነበር፡፡
‹‹በየካቲት ወር 1968 ዓ.ም. አዲስ አበባ በተደረገው የአፍሪቃ ፉትቦል ኮንፌዴሬሽን 12ኛ ጠቅላላ ጉባኤ እንደገና ለአራት ዓመት የድርጅቱ ፕሬዚዳንት ሆነው በመመረጥዎና ለዚህ ድርጅት ከሃያ ዓመት በላይ የሰጡት አገልግሎት ሲታይ የአፍሪካ ስፖርት ድርጅቶች የጣሉብዎት እምነት ከፍ ያለ መሆኑን ያስረዳል፡፡
‹‹ላንድ ኢትዮጵያዊ ይህን የመሰለ ከባድ ኃላፊነት ተደጋግሞ ሲሰጥ የሚያኮራው ሰውየውን ብቻ ሳይሆን አገሩን ጭምር መሆኑ የታወቀ ነው፡፡››
እነዚህን አንቀጾች የያዘው የርዕሰ ብሔሩ ደብዳቤ በግልባጭ ለባህል፣ ስፖርትና ወጣቶች ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር አክሊሉ ሀብቴ ተልኮ ነበር፡፡ የአሁኑ ወጣቶች ሚኒስቴር ከመዝገብ ቤቱ ይህን ደብዳቤ ቢያገኝ፣ ወይም ከሌሎች ምንጮች እውን ጉባኤው ከ51 ዓመታት በኋላ ነው የተካሄደው ብሎ ቢያጣራ እሱም ተሳስቶ ያገሪቱ ሚዲያዎችም ባልተሳሳቱ ነበር፡፡
እንዴት ነው ነገሩ?
ነገርን ነገር ቢያነሳው አይደንቅምና ለአፍሪካ እግር ኳስ ልዕልና የአንበሳውን ድርሻ የሚወስዱት የታላቁ ይድነቃቸው ተሰማን ስፖርታዊ፣ እግር ኳሳዊ ልዕልና ባዕዳኑ ሲያወድሱ፣ የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንትም ሆኑ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር አንድ ቃል ሳይናገሩ እንዴት አለፉት?
የዓለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ ባስተናገደችበት አጋጣሚ ዋንጫው ኢትዮጵያ መጥቶ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በብሔራዊ ቤተ መንግሥት ከፊፋ ሲቀበሉ ባደረጉት ንግግር፣ የአቶ ይድነቃቸው ተሰማን ታላቅነት በይፋ ያወጁበት፣ ባቀባበሉም ይድነቃቸውን ያነገሡበት እንደነበር የቅርብ ዘመን ትውስታ ነው፡፡
ዘንድሮ የሚያማክር ጠፍቶ ነው?  ወይስ… ‹‹ነቢይ በአገሩ…›› የሚለው ብሂል እውን ሆኖ ነው? 
እንዴት ነው ነገሩ?