በባሕር ማዶ ‹‹የአፍሪካው ኤጲፋኒያ›› (African Epiphany) በመባል በልዩ ልዩ ድርሳኖች የሚታወቀው
የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት) በሰው ልጅ ወካይ
የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በይፋ እንቅስቃሴ መጀመሩን አብስሯል፡፡
ዓመታዊው ክብረ በዓል በአገሪቱና የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን በምትገኝበት የዓለም ክፍሎች ጥር 11 ቀን 2009
ዓ.ም. ተከብሯል፡፡ በተለይ በአዲስ አበባ በጃንሜዳ ሲከበር በሥነ በዓሉ ላይ የተገኙት አዲሷ የባህልና ቱሪዝም
ሚኒስትር ዶ/ር ሒሩት ወልደማርያም እንዳበሰሩት፣ የጥምቀት በዓልን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ቅድመ ዝግጅት እየተደረገ
ነው፡፡ ሚኒስትሯ አያይዘውም የጥምቀት በዓል ‹‹ከጥንት ጀምሮ የሰላምና የፍቅር ተምሳሌት በመሆን የሚከበር፣
የኩራታችንና የማንነታችን መገለጫ ሃይማኖታዊ በዓል ከመሆኑ ባሻገር የበርካታ ባህላዊ እሴቶች ማሳደጊያ ነው፤››
ሲሉ፣ ቡራኬ የሰጡት ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ወፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊም፣ ‹‹በዓለ ጥምቀቱ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አንድነት መጠበቂያ ጠንካራ ዘዴ በመሆኑ ኢትዮጵያውያኑ ሊጠብቁትና ለዓለም ሊያስተዋውቁት ይገባል፤›› ብለዋል፡፡
ዋዜማውን ከተራ (ጥር 10) እና ማግስቱን (ጥር 12) ቃና ዘገሊላን ይዞ በዓለ ጥምቀት በልዩ ድምቀት
ከሚከበርባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነውና ጎንደር ከተመሠረተችበት ከ17ኛው ምታመት ጀምሮ በልዩ አገባብ እየተከበረ
ያለውን ሒደት ለመሰነድ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባለሙያዎች ቡድን ሥራውን እያከናወነ ይገኛል፡፡ የጥናት
ቡድኑ አስተባባሪና የባህል አንትሮፖሊጂስቱ አቶ ገዛኸኝ ግርማ ለሪፖርተር እንደገለጹት ቡድኑ ከጥር 1 ቀን 2009
ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ ነው፡፡
እንደ አቶ ገዛኸኝ አገላለጽ፣ በጎንደር ከሚሰነደው አከባበር በተጨማሪ በቤተክህነት አማካይነት በተለያዩ
አካባቢዎች በየባሕረ ጥምቀቱ የሚኖረውን ሥርዓት ስነዳ ይከናወናል፡፡ የማስመረጫ ሰነዱ ለዩኔስኮ የሚላክ ሲሆን፣
እ.ኤ.አ. ለ2018 በዕጩነት ለማቅረብ እስከ መጋቢት 22 ቀን 2009 ዓ.ም.¸ሰነዱን አሟልቶ መላክ ይጠበቃል፡፡
በዓለ ጥምቀቱ ሲገለጽ
በኦርቶዶክሳዊቷ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ በ30 ዓመቱ
በመጥምቁ ዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ባሕር የተጠመቀበትን ዕለት የሚያስታውስ ነው፡፡ ‹‹ኤጲፋንያ›› በመባልም
ይታወቃል፡፡ ጥር 10 ቀን በከተራ፣ በገጠርም ሆነ በከተማ ታቦታት ከየአብያተ ክርስቲያናቱ ወደየባሕረ ጥምቀቱ
የሚያደርጉት ጉዞና መንፈሳዊ አዳር በማግስቱ የጥምቀት ዕለት ‹‹ተጠምቀ ሰማያዊ በእደ መሬታዊ፤›› ሰማያዊው
በመሬታዊው እጅ ተጠመቀን ይዞ የሚኖረው ያሬዳዊ ዝማሬ የበዓሉ ገጽታ ነው፡፡
ሥዕላዊ ከሆነው ከሃይማኖታዊና መንፈሳዊ አከባበሩ በተጓዳኝም ባህላዊ ገጽታው ይታያል፡፡ ወጣቶች የሚተጫጩበት
የትዳር አጋራቸውን የሚመርጡበት አጋጣሚዎችን ከመፍጠሩም ባለፈ በከተማም ሆነ በገጠር ሰውን የሚያገናኝ ድልድይ
ነው፡፡
በየዓመቱ በመላ ኢትዮጵያ የሚከበረው የጥምቀት በዓል፣ ታቦታት ከመንበራቸው ወጥተው፣ በየባሕረ ጥምቀቱ የሚከበሩ
በመሆናቸው፣ አገሬውን ብቻ ሳይሆን ዓለም አቀፋዊ መስህብነትን በመጎናጸፉ፣ ቱሪስቶችን እንደሳበ ነው፡፡ ከአዲስ
አበባ እስከ ላሊበላ፣ ከአክሱም እስከ ጎንደር፣ ከሐዋሳ እስከ ጂማ፣ ከአሶሳ እስከ ጋምቤላ በሁሉም ሥፍራዎች በዚሁ
ዓይነት ደምቆ ይከበራል። የምእመናኑም ሆነ የካህናትና ዲያቆናት አለባበስ ፍፁም በሚማርክ ባህላዊ አልባሳት የተዋበ
በመሆኑ ከውጭም ሆነ ከአገር ውስጥ ለሚመጡ ጎብኚዎች ሁልጊዜ አዲስ ነው።
ከሃይማኖታዊው ሥነ ሥርዓት በኋላ ካህኑ በሃሌታ፣ ወንዱ በሆታ፣ ሴቱ በእልልታ ታቦተ ሕጉን አጅበው፣ እንደያመጣጣቸው ወደየአጥቢያቸው ይመለሳሉ።
‹‹እዩት ወሮ ሲመለስ
መድኃኔ ዓለም በፈረስ
ወሮ ሲመለስ
የሚካኤል አንበሳ
ሎሌው ሲያገሳ።
ማር ይፈሳል ጠጅ
በእመቤቴ ደጅ፤» እያሉ ምእመናኑ ታቦታቱን በዝማሬቸው ያጅቡታል።
ታቦተ ሕጉም ቅጽር ግቢው ሲደርስ ሁሉም ምኞታቸውን በፍሡሕ ገጽ እንዲህ እያሉ ይገልጻሉ።
«በሕይወት ግባ በዕልልታ
የዚህ ሁሉ አለኝታ
በሕይወት ግቢ እምዬ
እንድበላ ፈትዬ››
ሊቃውንቱ እንደሚናገሩት፣ ዘመነ አስተርእዮ የሚባለው፣ ከጥር 11 ቀን ጀምሮ እስከ ጾመ ነነዌ (ለዘንድሮ እስከ
ጥር 28 ቀን 2009 ዓ.ም.) ያለው ጊዜ ነው። በዚህ ጊዜ ውስጥ አምላክ ሰው ሆኖ በሥጋ መገለጡ፣ በዮርዳኖስ
በተጠመቀ ጊዜ የአንድነትና የሦስትነት ምሥጢር መታወቁ፣ በቃና ዘገሊላ በተደረገው ሠርግ ላይ የመጀመሪያው ተዐምር
በመፈጸሙ፣ አምላካዊ ኃይሉ መገለጡ፣ እየታሰበ ምስጋና ይቀርባል። ይህ ኩነት ኢትዮጵያ ብሂልን ከባህል ጋር አዛምዳ
ከሌላው የክርስቲያን ዓለም በተለየ አከባበር በዓሉን ማክበሯ፣ አያሌ ቱሪስቶችን ለመሳብ አስችሏታል።
ያኔ የሎሚ ውርወራው፣ የከተራው ሽልምልም ዱላ አሁን አሁን በከፊል ሎሚው ወደ ፕሪም፣ ሽልምልሙ ዱላ ወደ ረዥም
ቄጠማ (ጨፌ ላይ የሚበቅል) ተለውጦ መታየቱ፣ ከባህላዊ ጭፈራው በተጓዳኝ ወጣቱ በአመዛኙ ከመንፈሳዊ ማኅበራት
(ሰንበት ትምህርት ቤቶች) መዘምራን ጋር ወደ ዝማሬ አዘንብሏል፡፡
በዓለም አቀፍ የፌስቲቫሎች መድበል የአፍሪካ ኤጲፋኒያ/ጥምቀት (The African Epiphany) እየተባለ
የጎንደሩ፣ የላሊበላው፣ የአዲስ አበባው… የጥምቀት አከባበር በዓለም የክብረ በዓላት (Festivals) ድርሳን ላይ
በየጊዜው የሚተዋወቀው፣ ቱሪስቶችም እየመጡ የሚያደንቁት አንዳንዶችም ‹‹ጥምቀትን ለምን በቅርስነት
አላስመዘገባችሁም?›› እያሉ ሠርክ እየጠየቁ ባሉበት፣ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ለከተራ ጥምቀት አከባበር
ምዝገባ ለዓመታት ትኩረት ሳይሰጥ መክረሙ ይነገራል፡፡
በ2006 ዓ.ም. የጥምቀት በዓል በአዲስ አበባም ሆነ በጎንደር ሲከበር የቤተክህነትም ሆነ የባህልና ቱሪዝም
ሚኒስቴር ከፍተኛ ሹማምንት ክብረ በዓሉን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየሠራን ሲሉ ቢደመጡም፣ በተግባር ግን
የሚታይ እንቅስቃሴ እንዳልነበረ ገሐድ ነበር፡፡ ዘንድሮ ግን ተግባራዊ እንቅስቃሴ መጀመሩ ይበል አሰኝቷል፡፡
የጥምቀት በዓል በዩኔስኮ በግዙፍ ቅርስነት ከተመዘገቡት ከአክሱም፣ ላሊበላ የጎንደሩ ፋሲል ግቢ ጋር በጥብቅ
ተሳስሮ የሚከበር የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ መሆኑ፣ እንዲሁም በዓሉ ከ1,500 ዓመታት በላይ በተከታታይ የአገሪቱ
ትውልዶችና ሥልጣኔዎች እየተከበረ ያለ ሕያው ቅርስ መሆኑ ይታወቃል፡፡
በዓሉ መቼ ይመዘገብ ይሆን?
ኢትዮጵያ እስካሁን ሦስት የማይዳሰሱ ቅርሶቿን (የመስቀል በዓል፣ ፊቼ ጫምባላላና የገዳ ሥርዓት) በዩኔስኮ አስመዝግባለች፡፡ የገዳ ሥርዓት ባለፈው ኅዳር አዲስ አበባ በተደረገው ጉባኤ መመዝገቡ ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያ ለዘንድሮው 2017 ለዩኔስኮ ያቀረበችው አንድም የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ የለም፡፡ ስምንት የአፍሪካ
አገሮች አልጀሪያ፣ ማላዊ፣ ቦትስዋና፣ አይቮሪኮስት፣ ግብፅ፣ ሞሮኮ፣ ናይጄሪያና ሞሪሸስ እንዲመረጡላቸው የተለያዩ
ባህላዊ ቅርሶችን ማቅረባቸው ዩኔስኮ ይፋ አድርጓል፡፡ ከነዚህም መካከል ቦትስዋና ዶኮፔሎ የሚሰኘውን ባህላዊ ሙዚቃ፣
ግብፅ የላዕላይ ግብፅን የታሊ ዕደ ጥበብና ሥነ ጥበብ፣ ማላዊ ባህላዊ ምግቧን፣ ናይጄሪያ የዮሩባን ቃል ግጥም
ይገኙባቸዋል፡፡
በመጪው ኅዳር 2010 ዓ.ም. በሚደረገው የዩኔስኮ የዘርፉ ኮሚቴ ጉባኤ ለውሳኔ እንዲታይላቸው ማመልከቻቸውን
ያስገቡት በሕገ ደንቡ መሠረት ማርች 31 ቀን 2016 (መጋቢት 22 ቀን 2008 ዓ.ም.) ነበር፡፡
ኢትዮጵያ ለመወዳደር ያለፋትን ዘንድሮ (2017)፣ በ2018 (2011 ዓ.ም.) ለማግኘት ዕድል የሚኖራት
የጥምቀት በዓልን እንዲመዘገብ የሚያስችለውን የኖሚኔሽን ሰነዷን አዘጋጅታ እስከ መጋቢት 22 ቀን 2009 ዓ.ም.
(ማርች 31 ቀን 2017) በፓሪስ ሰዓት አቆጣጠር እስከ እኩለ ሌሊት ስትልክ ብቻ ነው፡፡
በሁለት ወር ውስጥ የመጀመሪያውን ተግባር ካላከናወነች ማመልከቻው የሚገባው ባመቱ መጋቢት 22 ቀን 2010
ዓ.ም. (ማርች 31 ቀን 2018) ሲሆን፣ ውሳኔውም በሦስተኛው ዓመት ኅዳር 2012 ዓ.ም. ይከናወናል፡፡
- ሔኖክ ያሬድ's blog
- 157 reads
No comments:
Post a Comment