ዶ/ር ሐሰን ሰዒድ የቅድመ ዘመን አርኪዮሎጂስት ናቸው፡፡ ላለፉት 15 ዓመታት በሙዚየም ኃላፊነት እያገለገሉ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአርኪዮሎጂና ቅርስ አስተዳደር ክፍለ ትምህርት የሙዚየም ሳይንስን ያስተምራሉ፡፡ በኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋምም የሙዚየም በኩሬተርት ያገለግላሉ፡፡ የኢትዮጵያ አርኪዮሎጂ ባለሙያዎች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባልም ናቸው፡፡ የከፋውን የቡና ሙዚየም በማቋቋም ይጠቀሳሉ፡፡ ብሔራዊ የቤተ መንግሥት ወደ ሙዚየም እንዲቀየር እየተደረገ ባለው ጥረት በግብረ ኃይሉ ውስጥ ሠርተዋል፡፡ በሙዚየምና ቅርስ ዙሪያ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙት ዶ/ር ሐሰን ቀደም ሲል የአርኪዮሎጂ እንግሊዝኛ አማርኛ መዝገበ ቃላት ያዘጋጁ ሲሆን፣ በቅርቡ ደግሞ ‹‹እስላማዊ ቅርሶች ዓይነትና ስርጭት ከሰሜን ሸዋ እስከ ደቡብ ወሎ›› በሚል ርዕስ ከአቶ ሐሰን ሙሐመድ ጋር አዘጋጅተው ለኅትመት አብቅተዋል፡፡ በመጽሐፉና በተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ሔኖክ ያሬድ ዶ/ር ሐሰንን አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡‑ ቅርሶችን የተመለከተው መጽሐፍ የማዘጋጀት መነሻችሁ ምንድን ነው?
ዶ/ር ሐሰን፡‑ በኢትዮጵያ ሚሌኒየም ብሔራዊ ሴክሬታሪያት ውስጥ ቅርስን እንወክል በተባለበትና በምክትል ዳይሬክተርነት ተመድቤ በምሠራበት ጊዜ በአገራችን የቅርስ አፈላለግ፣ አስተዳደርና ልማት ላይ ፍንትው ብለው የሚታዩ ክፍተቶች ነበሩ፡፡ የኢትዮጵያን ብዝኃነት ባማከለ ሁኔታ የሚሠራ ሳይሆን ወደ አንድ ወገን ያጋደለ ነበር፡፡ አገር በቀል የእምነት ሥርዓትን አንሰበስብም፣ የቤተ እስራኤልን፣ የሙስሊሙን ቅርሶች አንሰበስብም ለልማት የምናደርገው ጥረት ደካማ ነበር፡፡ በቱሪዝም ረገድ የሰሜን መስመር ከሚባለው በስተቀር ወደ ምሥራቅ፣ ወደ ደቡብ አልሄደ፣ ይኼ ክፍተት ትንሽ ጠገነንና ምን አስተዋጽኦ እናድርግ ብለን ተነሳን፡፡ ለኢትዮጵያ ሚሌኒየም የምንቆየው አንድ ዓመት ተኩል ቢሆንም ክፍተቱንም ማሳየት አንድ ነገር ነው ብለን አንድ ፕሮጀክት ቀርጸን፣ ፕሮጀክቱን አማራጭ የቱሪስት መዳረሻዎችን ለማመላከት አልንና በሰሜን ሸዋና በደቡብ ወሎ ያሉትን ነገሮች መረጥን፡፡ አመራረጣችንም ለአዲስ አበባ ቅርበት ያላቸውና በውሎ ገባ መመለስ የሚቻልበት አጋጣሚ ስላላቸው ነው፡፡ ሁለተኛ የሰሜን ሸዋ ከደቡብ ወሎ አካባቢ በጥንት ጊዜ ወደ ቀይ ባሕር የሚሄደው የምሥራቅ የንግድ መስመር አንኮበር፣ አልዩ አምባ ጫፍ ይዞ ይገኛል፡፡ በብሔረሰቦች ደረጃም ኦሮሞ፣ አማራ፣ አርጎባ፣ አፋር በአንድነት በገበያ፣ በበዓል፣ በጋብቻ የሚገናኙበት ትልቅ ማዕከል ነው፡፡ ከሃይማኖት አኳያም የቤተ እስራኤል ትልቁ ክንፍ ያለው በሰሜን ሸዋ ነው፡፡ ክርስትናና እስልምና ያሉበት እንዲያውም ለ200 ዓመት የእስልምና ሱልጣኔት አስተዳደር ያለበት ነበር፡፡
እነዚህ አንኳር ነጥቦች ምክንያት ሆነው ደረጃውን የጠበቀ ሰነድ እንሥራ ብለን መነሳታችን ይህ መጽሐፍ እንዲወለድ ምክንያት ሆኗል፡፡ በዚህ በኩል ያለውን ክፍተት ይሞላል፡፡ ጥናቱና ስነዳው ስምንት ዓመት ወስዷል፡፡ የኅትመት ገንዘብ አጥተን የቆየ ቢሆንም አሁን ግን የአርጎባ ልዩ ወረዳ አስተዳደር፣ አብዛኛው መጽሐፉ ውስጥ ያሉት ቅርሶች የሚያስተዋውቁት፣ አካባቢዬን ነው በማለት በአጋርነት (ስፖንሰርነት) እንዲታተም አድርጎታል፡፡
ሪፖርተር፡‑ የመጽሐፉ ይዘት ምንድን ነው?
ዶ/ር ሐሰን፡‑ በመጽሐፉ ውስጥ ለማሳየት የፈለግነው አንዱ የእስላማዊ ቅርስ ምንነት ነው፡፡ አንዳንዱ እስላማዊ ቅርስ ምን ማለት ነው? ብሎ ይጠይቃል፤ ለምንስ የእስላም የክርስቲያን ይባላል፡፡ ቅርስ ቅርስ ነው እንጂ ይላል፡፡ የበለጠ ቀርበን እንድናጠናው፣ እንድናውቀውና እንድንጠብቀው ለይተን እናጠናለን፡፡ ለምሳሌ በዩኒቨርሲቲ ውስጥ ባይብል ከለር አርኪዮሎጂ የሚባል አለ፡፡ ዓላማው በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተተረኩት ታሪኮች እውን ነበሩ? ተብሎ የሚጠናበት ነው፡፡ ኢያሪኮን በከተማነት፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ተቸነከረበት የተባለውን ምስማር፣ እንጨት ማግኘት፣ ወዘተ የሚመረምር መጽሐፍ ቅዱሳዊ አርኪዮሎጂ ተፈጥሯል፡፡ በተመሳሳይ መልኩም እስላማዊ አርኪዮሎጂ ተፈጥሯል፡፡ ይህን ወደ አገራችን ስናመጣ እስላማዊ አርኪዮሎጂ፣ ቅርስ ለማለት ሰው የሚፈራው አገራዊ አይደለም ወይ በማለት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በተግባር ላይ ያሉ 44 ሙዚየሞች አሉ፡፡ ይዘታቸውም ከቤተክርስቲያን ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ የአገር ቅርስም ናቸው፡፡ እንዲሁም በእስላማዊ ቅርስ ረገድ በኢትዮጵያ ውስጥ ከሰባተኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በነበረው ሒደት ምን ቅርስ አፍርቷል? ከሥነ ሕንፃ፣ ከሥነ ጽሑፍ፣ ከአዋቂዎች (ኡላማዎች) አንፃር እነማን ተነስተዋል የሚለውን ጉዳይ ለማሳየት መጽሐፉ ይሞክራል፡፡ መጽሐፉ በውስን መልክአ ምድር ሰሜን ሸዋና ደቡብ ወሎ ላይ ያተኩራል፡፡ የእስላማዊ ቅርሶች ብያኔን ከማስፈር ባለፈ፣ በየዘርፉ መድበናል፡፡ እስላማዊ መንደሮች የሚመሠረቱበትን መልክ ከሌሎች ጋር በማነፃፀር ሠርተናል፡፡
እስልምና ከእምነት ባለፈ የሕይወት የአኗኗር ስልት ዘይቤ ነው፡፡ ሃይማኖቱ በሚፈቅደው መልክ መኖር ማለት ነው፡፡ በአርኪዮሎጂ የቤቶችን ክብነት ወይም ሌላው ዓይነት እናገኛለን፡፡ በመንደር፣ በመስጊድ፣ በእስላማዊ ሥነ ጽሑፍ በአጀቢ ጽሕፈት (ቋንቋው አማርኛና ሌላ የአገር ቋንቋ ሆኖ ፊደሉ ዐረቢኛ ሆኖ ሥነ ፈለክ፣ ቁጥር፣ ሕክምና፣ ወዘተ ይዘት ያላቸው የያዘ)፣ የዑላማዎች አስተዋጽኦ (በእግራቸው በሱዳን በኩል ግብፅና የመን ሄደው ተምረው የተመለሱ፣ በቃልና በኪታብ ሲያስተምሩ የኖሩት) ይህ ሁሉ የኢትዮጵያ ታሪክ ነው፡፡
መሠረታዊ የሚባሉትን የእስላማዊ ቅርሶችን በየዘርፉ የተሰነደበት መጽሐፍ ነው፡፡ እስላማዊ ሥነ ጽሑፎች፣ ግጥሞች፣ መንዙማዎችና ውዳሴዎች ባለመፈለጋቸው፣ ባለመሰብሰባቸውና ባለመጠናታቸው ስንኳን ስለሀገር ሥነ ጥበብ ያበረከቱትን ለመለየት ቀርቶ ለዛና ጣዕማቸውን ለማጣጣም አልታደልንም፡፡ ከዚህ ሌላ እስላማዊ ቅርሶች በውስጣቸው ቀርቅበው የያዟቸውን ቁም ነገሮች ባለማየታችን አያሌ የታሪክ መረጃዎች ተደብቀው እንዲቀሩ ፈርደንባቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡‑ ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ሦስተኛውን የማይዳሰስ ቅርሷን የገዳ ሥርዓት አስመዝግባለች፡፡ ከሃይማኖታዊና ባህላዊ ቅርሶች አኳያ ለማስመዝገብ ብዙ ሥራ እንዳልተሠራ ይነገራል፡፡
ዶ/ር ሐሰን፡‑ በአገሪቱ በቤተእስራኤልም፣ በክርስትናም፣ በእስልምናም ብዙ መንፈሳዊ ቅርሶች አሉ፡፡ የመውሊድ በዓል ገታ ላይ የሚከበረው ዠማ ንጉሥ ሳምንት ድረስ የሚዘልቀው ልዩ ነው፡፡ በመርካቶ 24 ሰዓት ሳምቡሳ እየተበላ ጫትም ኖሮ የበዓሉ መገለጫ መንዙማው ልዩ ድባብ አለው፡፡ በዓለም ቅርስነት ማስመዝገቡ ቆይቶ በአገር ደረጃ ለምን እንዲሰነድ አይደረግም? ሁሉንም የሚወክል የቅርስ አሰባሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሙዚየሙ የተቋቋመለትን ዓላማ ግቡን ይመታ ዘንድ በቅርስ አሰባሰብ ላይ ፖሊሲ ሊኖር ይገባል፡፡ ውክልናውን ማስጠበቀ ይገባል፡፡ የሁሉንም ማቀፍ አለበት፡፡
ሪፖርተር፡‑ ቅርስ ባለሥልጣን የቅርስ ማስመዝገብ ጥያቄ ሲቀርብለት ነው የሚንቀሳቀሰው ይባላል?
ዶ/ር ሐሰን፡‑ አሠራሩ ጥያቄ ሲቀርብለት ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ብሔራዊ ተቋሙ በወካይነት ሊቀመጡ የሚችሉ ቅርሶችን አስቦና ተጨንቆ የመመዝገብ የማስተባበር ሥራ መሥራት አለበት፡፡ ለሙስሊሙ ዓለም ልናበረክት የምንችለው ነጋሽ ላይ ቅርስ አለ፡፡ ድሬ ሼህ ሁሴን ለዩኔስኮ የዕጩነት (ኖሚኔሽን) ፋይል ቀርቦ እንዴት ስምንት ዓመት ይፈጃል፡፡ ዛሬ ስለርሱ የሚያነሳ የለም፡፡ ወረዳም ሆነ ዞን ተነስቶ ቅርስ አስመዘግባለሁ ይላል፡፡ ማነው የሚያደርገው? አገር ነው የሚጠይቀው አገር ሲጠይቅ ግን ተዘጋጅቶ ነው፡፡ ኢትዮጵያን ሊያስተዋውቁ ብዝኃነቷን ሊያሳዩ የሚችሉ ቅርሶች ማስመዝገብ ያለበት ይኼ ተቋም ነው፡፡
በሌላ በኩል በዩኔስኮ ቅርስን ማስመዝገብ ተጨማሪ ኃላፊነትን መውሰድ ማለት ነው፡፡ አክሱምን ተመልከት ባለው አያያዝ በአደጋ ላይ ያለ ቅርስ ወደሚባለው መዝገብ ውስጥ ሊገባ ነው፡፡ ተቋማዊ ብቃትን ሳናጠናክር ሕጋዊ መስመርን ሳናሲዝ ማስመዝገብ ጥያቄ ውስጥ ያስገባል፡፡
ሪፖርተር፡‑ ከእስላማዊ ቅርሶች ጋር የተያያዘ ዕውቀት ያለው ባለሙያ አለ?
ዶ/ር ሐሰን፡‑ በብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትም (ወመዘክር) ሆነ በቅርስ ተቋም እንደሌለ ነው የማውቀው፡፡ በዓረቢኛ የተጻፉት የክርስትና ይሁን የእስልምና ጽሑፎች መሆናቸውን የሚለይ የለም፡፡ ስለዚህ ይህ ብሔራዊ ተቋም እስላማዊ ቅርሶችን መሰብሰብ ግዴታዬ ነው እንዲህ ዓይነት ባለሙያ ላፍራ ማለት የለበትም?!
ሪፖርተር፡‑ የአገሪቱን ምልዐተ ቅርሶች በስፋት እንዲታወቁ እንዲጠበቁ ለማድረግ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሥር የተቋቋመው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ኃላፊነት እምን ድረስ ነው?
ዶ/ር ሐሰን፡‑ ተቋሙ ባደረጃጀት ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ የመጀመሪያው የቅርስ ተቋም በ1936 ዓ.ም. የተቋቋመው ብሔራዊ ሙዚየም ነው፡፡ ባለሥልጣኑ ብሔራዊ ሙዚየሙን አፈረሰው፡፡ ከዚህ ቀደም ከአሠርታት በፊት ሙዚየም እንዲያድግ አይፈለግም ነበር፡፡ ለምን ሌሎች ዲፓርትመንቶች ሙዚየሙ ገኖ ከወጣ ዝቅ ይላሉ፡፡ ያ ገጽታ (ስታተስ) እንዳይኖር ሙዚየሙ ከነርሱ ጋር እኩል እንዲራመድ ገድበውት ቆዩ፡፡ ይባሱኑም ገደሉት፡፡ በአሁን ጊዜ በሕግ አቋም ‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየም›› ተብሎ የሚጠራ ተቋም የለም፡፡
እንዲያውም የቅርስ ባለሥልጣኑ የፌዴራል ፖለቲካዊ አደረጃጀቱንኳ ከግምት ያላስገባ ነው፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ቅርንጫፎች በየክልሉ አሉ እንዴ? ሁለተኛ ባለሥልጣኑ አሁን የሚመራበት አዋጅ መታየት ያለበት ነው፡፡ ይህም የምልበት አንዱ ማሳያ በአዋጁ ቅርስ ጥናትና ጥበቃን የሚመራ የመማክርት ምክር ቤት ይመሠረታል እንጂ ቅርንጫፍ አቋቁሞ ሥራውን ይመራል የሚል የለውም፡፡ ከክልል ጋር የሚሠራው በመግባባት እንጂ የሕግ አስገዳጅ ነገር የለውም፡፡ ስለዚህ ከአደረጃጀትም ከሥልጣንም አንፃር ትልቅ ችግር አለበት፤ ከባጀትም አንፃር ውስን ነው፡፡ አገሪቱ በአሁን ጊዜ ሰፊ መሠረተ ልማት እያከናወነች ግዙፍ ተቋማት በየአካባቢው እየተንቀሳቀሱ ነው፡፡ እነዚህም በቅርሶች ላይ የሚያሳድሩት ተጽእኖ ይኖራል፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከክልሎች 27 ጥያቄዎች መጥተውለታል፡፡ አብዛኛው ከቤተክርስቲያን ‹‹ጠግንልን›› ብለው ላኩ፡፡ በጀቱና ፍላጎቱ ቢኖረውም ያሉት ባለሙያዎች ሰባት ናቸው፡፡ መሥሪያ ቤቱ መሥራት ያለበት ሬጉላቶሪ የሱፐርቪዥን ሥራ እንጂ ኦፕሬሽን ላይ አይችልም፡፡ ይህ ዝበት ስላለ ነው የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ሥራችን የቆመው፡፡
ሁለተኛ ነገር በሌላው አገር ምርምር የሚሠራው መጀመሪያ በራሷ የሰው ኃይል ነው፡፡ ያለውን ዕምቅ ሀብት ማወቅ ይገባል፡፡ ይህ ባለመታወቁ የምርምር አካሄዳችን ተጣርሷል፡፡ ከውጭ ተመራማሪዎች ጋር ተቧድኖ የሚሠራው ምርምር በተወሰነ አካባቢ ሆኗል፡፡ ምርምሩን የሚተልሙት የውጭ አጥኚዎች እንጂ በእኛ ተቋማት አይደለም፡፡
ተቋማዊ ተክለ ሰውነቱ ራሱ ልዩ ነው፡፡ ላቦራቶሪ ለመሆን ቴክኒሻኖች ማፍራት፣ ቴክኖሎጂ ማስገባት አለብህ፡፡ ቢያንስ ቻርኮል እዚህ ዘመኑ መለየት (ዴት) መቻል አለበት፡፡ የብራና መጻሕፍት፣ አይቮሪ፣ ቴክስታይል፣ ወዘተ መጠገን መቻል አለብህ፡፡ አሁን ጽሕፈት ቤትና ግምጃ ቤት (ስቶር) ነው የሆነው፡፡ ስለዚህ አካሄዳችንም አሠራራችንም ትንሽ የጎደለው ነገር አለ፡፡
ሪፖርተር፡‑ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካሄድስ?
ዶ/ር ሐሰን፡‑ በኒዮሌቲክ፣ በብረት ዘመን፣ በቅድመ ታሪክ አርኪዮሎጂ ሰው የለንም፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን የሚሰጡን ሥርዓተ ትምህርት አንድ ዓይነት ነው፡፡ ዶ/ር ካሳዬ የዛሬ አሥር ዓመት የቀረፀውን ሥርዓተ ትምህርት ፎቶ ኮፒ እያደረግን እንደጨረር በአዳዲስ ዩኒቨርሲቲዎች ሁሉ ያቺኑ ነው የምናስተምረው፡፡ የወጡት ልጆች ግን ሁሉን ነገር ያሟላሉ? ራሳቸውን ችለው የመስክ ምርምር ማድረግ የሚችሉ ናቸው? ስፔሻላይዜሽን እንኳ የለንም፡፡ ሐዋሳ ቅድመ ታሪክ አርኪዮሎጂን ከሚያስብ ኢትኖ አርኪዮሎጂን ለምን አያስተምርም፡፡ የብሔር ብሔረሰቦች አካባቢ ነውና ከ50 በላይ ብሔረሰቦች ይሠራል፡፡ በአፋርስ እንደ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለምን ተመሳሳይ ትምህርት ያስተምራል፡፡ ፊዚካል አርኪዮሎጂ እያለለት፡፡ አክሱምስ እንደማንኛውም ቅርስ ማስተማር አለበት? አኩሱሞሎጂ ነው ነጥሮ መውጣት  ያለበት፡፡ ስለዚህ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ሌላ ቀርቶ ስፔሻላይዜሽን እንኳን አይሞክሩም፡፡ እስቲ ቆም ብለን እንመልከት፡፡ በአሥር ዓመት ውስጥ እያፈራን ያለነው የአገሪቱ ፍላጎት ላይ ተመሥርተን ነው?
ከዐሥር ዓመት በፊት የቀረፅነው ሥርዓተ ትምህርት ዛሬም ሊያገለግለን ይገባል? ለምን አናሻሽለውም፡፡ ለዚህ ነገር ተነሳሽነቱን መውሰድ ያለበት ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ነው፡፡ የሰው ኃይል የሚፈልገው ከዩኒቨርሲቲ በመሆኑ የሚፈልገውን እያገኘ ነው ወይ? ይህን ዞር ብሎ ማየት ያስፈልጋል፡፡ መወቀስ ካለም ባለሥልጣኑ ብቻ ሳይሆን የአርኪዮሎጂና ሙዚየም ባለሙያዎች ማኅበራትም ጭምር ናቸው፡፡
ማኅበራት ያለውን ክፍተት ለመሙላት ምን ያህል ተንቀሳቅሰዋል? ለመንግሥትም ሆነ ለተቋም ምን ያሳየነው ነገር አለ? አቅጣጫ ለማሳየት በቁርጠኝነት ምን ያህል ሄደናል?
ሪፖርተር፡‑ ምን መደረግ አለበት?
ዶ/ር ሐሰን፡‑ ከአርኪዮሎጂ አንፃር ሥርዓተ ትምህርታችንን መፈተሽ አለብን፡፡ የትኛው ዩኒቨርሲቲ አንፃራዊ ጠቀሜታ አለውና በየትኛው ነገር ስፔሻላይዝ ያድርግ ማለት አለብን፡፡ ሁለተኛ አዳዲስ የሚወጡ ተመራቂዎች መተማመን ኖሯቸው ወደየምርምር ቦታዎች ራሳቸውን ችለው እንዲሄዱ ማድረግ፣ 19 ኢንተርናሽናል የምርምር አካሎች እዚህ ሲንቀሳቀሱ ከእኛ ፈቃድ አግኝተው ነው፡፡ በፈቃዱ ፎርማት ላይ በአጭር በመካከለኛና በረዥም ጊዜ የአቅም ግንባታ ለተቋሙ ለማድረግ ፈቅደን ፈርመናል ይላል፡፡ ምን ያህል ተጠቅመንበታል፡፡
ወጣቱን ልከን አቅማቸውን የሚያሳድጉበት መንገድ ለምን አንፈጥርም፡፡ የሚመጡ ሰዎች የየዘርፉ ኃላፊዎች በበጀት፣ በሥርዓተ ትምህርት የሚያዙ ናቸው፡፡ አላደረግንም፡፡ ለምንድን ነው ያላደረግነው፡፡ ተቋማዊ ርዕይ ኖሮት የሚመጣ የለም፡፡ ስለዚህ እኛ የፈረንጆች አገልጋይ ሆነን ነው እንጂ የምንመለሰው፣ ራሳችንን ችለን በራስ መተማመን ቦታ እንዲኖረን አያደርግም፡፡ ርግጥ ራሳቸውን ችለው የሚሠሩ አሉ፡፡ ጥቂት እነ ዶ/ር ዘርዐ ሠናይ፣ ዶ/ር ዮሐንስ ኃይለሥላሴ ዶ/ር ዮናስና ስለሺ አሉ፡፡ ስለዚህ የእኛ ተቋም ርዕይ ሊኖረው ይገባል፡፡ እንግዲህ ሱፐርቪዥን፣ ቁጥጥር፣ አመራር ላይ የሰው ኃይል ሥልጠና ስትራቴጂ ላይ ራሴን ላድርግ ማለት አለበት፡፡ ­