Friday, November 10, 2017

ሰሎሞን ዴሬሳ! ሰሎሞን ዴሬሳ! ሰሎሞን ዴሬሳ!
በቅርቡ በ80 ዓመቱ ዜና ዕረፍቱ የተሰማው፣ በዘርፈ ብዙ ዕውቀቱ ተጠቃሽ የነበረው ዕውቁ ገጣሚና ጸሐፊ፣ ጋዜጠኛና የፍልስፍና መምህር ሰሎሞን ዴሬሳ ሥርዓተ ቀብሩ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚኔሶታ ከተማ በግብአተ እሳት መፈጸሙ ይታወሳል፡፡ ነፍስ ኄር ሰሎሞን ዴሬሳ ከ19 ዓመታት በፊት (መስከረም 1991 ዓ.ም.) ከሪፖርተር መጽሔት ከፍተኛ ሪፖርተር (በወቅቱ) ገዛኸኝ ጌታቸው ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር፡፡ በዚያ ቆይታው ስለትምህርቱ፣ ስለጓደኞቹ፣ ስለግጥሞቹ፣ ስለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፣ ስለመንፈሳዊነት፣ ስለኢትዮጵያውያንና ስለብሔረሰቦች፣ እንዲሁም ስለጋዜጠኝነት ሰፊ ሐተታ ሰጥቷል፡፡ ለዝክረ ነገር ይሆን ዘንድ በመጀመርያው ክፍል (በረቡዕ እትም) የሰሎሞን ዴሬሳ ዐውደ ሕይወት፣ የፈረንሳይ ሥነጽሑፍና እኔ፣ የሥነ ጽሑፍ አቋምና ጓደኛሞች የሚሉት መስተናገዳቸው ይታወሳል፡፡ በዚህ እትም የመጨረሻው ክፍል ይቀርባል፡፡ 


ስለአሁኑ የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ
የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ብዙ አልተከታተልኩትም፡፡ አንዳንድ እየተላከልኝ አነባለሁ፡፡ በቅርብ ያነበብኩት ‹‹እኛ›› የሚል የሴቶች ግጥም የወጣበትን መጽሐፍ ነው፡፡ አንዳንዶቹ በጣም በጣም ውብ የሆኑ ናቸው፤ ለኔ ማለቴ ነው፡፡ አንድ ወጣት የአጫጭር ልቦለድ ጸሐፊ የጻፈውንም አንብቤያለሁ፡፡
ጥሩውንም ብቻ ላለመናገር ያሰለቹኝንም ልንገርህ፡፡ በኮሎኔል መንግሥቱ ዘመነ መንግሥት ‹‹ጽጌረዳ ብዕር›› ርዕሱ ራሱ መልአክ ያወጣው ሳይሆን ከዚያ በታች ያወጣው እንደሆነ ነው የሚሰማኝ፡፡ እስኪ በሌላ ቋንቋ አስበው ‹‹The Rose Pen›› ስትል ምን አለው? የሚጻፈው በነጭ ብራና ላይ በጥቁር ቀለም ነው፡፡ ‹‹ጥቁር ብዕር›› ብለው ቢያወጡት ይሻላቸው ነበር፡፡ የማውቃቸው የነ አቶ ፀጋዬ ገብረመድኅን የነመንግሥቱ ለማ ግጥምም ነበረበት፡፡ ግን በዚያ ውስጥ የማስታውሰው አንድ መቶ አለቃ የጻፈውን ግጥም ብቻ ነው፡፡
የኔ ተቺነት ይህን ያህል ዋጋ ላይኖረው ይችላል፡፡ ይኼን ይኼን አንብበህ አልወደድኩትም ብትለኝ እቀበልሀለሁ፡፡ አንብቤው ግን ትምህርት የማትማርበት እዚህ ላይ ነው ስትለኝ እንለያያለን፡፡ እኔ አቋሜ ድሮም አሁንም እንደዚህ ነው፡፡ አንድ ጊዜ አንዲት ትንሽ መጽሐፍ እንደ አጋጣሚ ገዛኋትና አነበብኳት፣ ጸሐፊዋ መቅደስ ናት፤ የመጽሐፏን ስም ሳይሆን ግጥሞቹን ነው የማስታውሰው፡፡ እሷ ውስጥ ያሉ ግጥሞች በጣም ነኩኝ፡፡ አሁን ስናገር ከዚያ ወዲህ የተጻፉትን የኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፎች አንብቤ አስቤበት እነዚህን መርጫለሁ ማለቴ አይደለም፤ ካጋጠሙኝ ማለቴ ነው፡፡ ‹‹Ethiopian Review›› ውስጥ አንዳንድ ግጥሞች ይወጣሉ፡፡ እስካሁን ድረስ ይህን ያህል የነሸጠኝ አላጋጠመኝም፡፡ አንደኛ ብዙዎቹ ግጥሞች ኢትዮጵያ እናቴ፣ እወዳታለሁ ዓይነት ናቸው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ኢትዮጵያን መውደድ ምን እንደሆነ ጥያቄ አነሳለሁ፡፡ ኢትዮጵያን መውደድ አይቻልም ማለቴ አይደለም፡፡ አዲስ እና ‹‹እንዴ ይኼም አለ እንዴ?›› አስብሎ ከተቀመጥኩበት ብድግ ያደረገኝ አላጋጠመኝም፡፡
አንዳንድ ዘፈኖች ላይ ግጥም የሚመስሉ የሰማኋቸው አሉ፡፡ ብዙ አላውቃትም በቅርብ ነው የሰማሁዋት የኩኩ ሰብስቤን፡፡ ግጥሞቹ የሷ ይሁኑ አይሁኑ አላውቅም ግን አንዳንዶቹ ስበውኛል፡፡ አንድ በገና የሚጫወት ዓለሙ አጋ የሚሉት አለ፤ የሱም ስበውኛል፡፡
በአጠቃላይ ለመናገር ከኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ጋር ያለኝ ግንኙነት ይኼንን ያህል አይደለም፤ ከአሜሪካም ጋር ያለኝ እንዲሁ ይኼንን ያህል አይደለም፡፡ ከዓለም ላይ የሚመጣውን እንደ አጋጣሚ ያገኘሁትን አነባለሁ፡፡ ግን የኢትዮጵያን ሥራዬ ብዬ አልተከታተልኩትም፡፡ የተከታተልኩት የራሴን በመጻፍ ብቻ ነው፡፡
የኢትዮጵያን ሥነ ጽሑፍ በሚመለከት ተስፋ የሚያስቆርጥ ነገር አይታየኝም፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ የተጓደለ ነገር አለ፡፡ ተስፋ የሚያስቆርጥ ግን አይደለም፡፡ አንድ ማስታውሰውና አንዳንድ ጽሑፎችን ሳይ የተሰማኝ ነገር አለ፡፡ አሁን እንኳ ‹‹ብሌን›› የምትባል የኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበርን መጽሔት ሳነብ ስለመንግሥቱ ለማ በግድ ጎትቶ ማርክሲዝምና ሌኒንዝምን እንደሚከተል አድርጎ እንዲህ እንዲህ ተብሎ ወጥቷል፡፡ እኔ መንግሥቱ ለማ ስለማርኪስዝምና ሌኒንዝም ሲናገር ሰምቼ አላውቅም፡፡
በአጠቃላይ ለጥበብ ሰው መንግሥቱ ከላይ ዓላማ ሰጥቶት የሚሠራ ከሆነ የትም አይደርስም፡፡ ያን ጊዜ እንደዚያ ነበር፡፡ አንተ ወይም እኔ የምጽፈው መንገድ ላይ ስንሄድ፣ ዘመድ ሲሞት፣ ፍቅር ሲይዝ፣…ከዚያ ውስጥ ከሕይወት የሚወጣው ጽሑፍ ጽሑፍ ይሆናል፡፡ መንግሥት ከላይ ሆኖ በዚህ ነው የምሄደውና በዚህ ጻፍ ሲባል ሥነጽሑፍ ወደቀ ማለት ነው፡፡
ከዚህ ቀደም ድሮ እንደዚህ ብዬ አንድ ችግር ደርሶ ነበር፡፡ አሁንም ደግሞ እንደገና እደግመዋለሁ፡፡ የግዕዝ ከዚያ ቀጥሎ የአማርኛ ምናልባት አላውቅም የትግርኛም ሳስበው ቅኔ ትምህርት ቤት መማር ስለተቻለ ለመጀመርያው ሃምሳ ዓመት ጠቅሞ ይሆናል፡፡ ከዚያ በኋላ የሚመጣው ሰንሰለት ነው የሚሆነው፡፡ እና በግምት በኮሎኔል መንግሥቱ ዘመን በማርክሲዝም ጊዜ ማርክሲዝምን እንደ ፍልስፍና አድርገው ቢያቀርቡት እሱ ራሱን የቻለ ነገር ነው፡፡ ግጥም፣ ሙዚቃና ሥዕል ውስጥ እናስገባው ሲሉ የመንፈስና የስሜት መደህየትን ነው የሚያስከትለው፡፡ በአንድ በኩል ደግሞ በአንዳንድ ቦታ እንዲህ ዓይነት ችግር ሲፈጠር በተለየ በድብቅ እየተፈናቀለ የሚወጣ አለ፡፡ እሱ ደግሞ በተለየ ለጸሐፊና ለባለኪነጥበብ ትልቅ ዕድለ ነው፡፡ ለሕይወቱ ሳይሆን ለሥራው፡፡ ለሕይወቱ ችግር ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሳያቸው ትንሽ እንደፈለጉ ለመጻፍ የተከፈተ ይመስለኛል፡፡ ይኼ በግምት ነው፡፡ እና እንደገና ሊያንሰራራ ይችላል ብዬ እገምታለሁ፡፡
ሌላው ጥሩ መስሎ የሚታየኝ በቴሌቪዥንና በራዲዮ ሦስት ቋንቋ እሰማለሁ፡፡ ሌሎቹ ትንንሾቹም ቢሰሙ ጥሩ ነበር፡፡ ለጊዜው መተሻሸትንና ትንሽ አለመሰማማትን የሚያመጣ ይመስላል፡፡ ወደፊት ከቀጠለ ግን መዳቀል ይጀመራል ብዬ እገምታለሁ፡፡ ሁልጊዜ ደግሞ አዲስ ነገር የሚመጣው ከመዳቀል ነው፡፡ አዲስም የምንለው ድሮ የምናውቀው ስዳቀል ነው፡፡ ምንም አዲስ ነገር የለም፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ጊዜ ተስፋ ያስቆርጣል፡፡ ምንድነው የማያጽፈኝ? በሚሊዮን የሚቆጠሩ የግጥም መጽሐፎች አሉ፡፡ ይኔ እዚህ ውሰጥ ተጨምራ ጊዜ ማባከን ነው የሚል ስሜት ይመጣብኛል፡፡ ምክንያቱም አዲስ የሚባል ነገር የለም፡፡
እዚያ ላይ በጣም ተስፋ ያለ መስሎ ነው የሚታየኝ፡፡ ቋንቋዎች የግዳቸውን ይቀላቀላሉ፡፡ ከአሁን ወዲያ ጥሩ የሆነ አማርኛ፣ ጥሩ የሆነ ትግርኛ፣ ጥሩ የሆነ ኦሮምኛ ሳያስቸግር አይቀርም፡፡ ለጊዜው በመፋጠጥና በመሻኮት ይተያዩ ይሆናል፡፡ እሱ የፖለቲካዊና የመንግሥት ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ኃላፊ ነው፡፡ እንኳን የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ የኮሎኔል መንግሥቱ፣ የአፄ ኃይለሥላሴ፣ የዮሐንስ፣ የቴዎድሮስ መንግሥት ከአክሱምና ላሊበላም አልፏል፡፡ የማያልፈው የሕዝቡ ሕይወት ነው፡፡ ነገ ኢትዮጵያዊ መባል ይቀርና ለአገሩ አንድ ሌላ ስም ይወጣ ይሆናል፡፡ ይህ ምንም የሚለውጠው ነገር የለም፡፡ እዚህ ያለው ሕዝብ ከ100 ሺሕ ዓመት ጀምሮ የነበረ ሕዝብ ነው፡፡ ከውጭ እየመጣ ይዳቀልበታል፡፡ ግን መሠረቱ ያ ሕዝብ ነው፡፡ ያ ሕዝብ እስካሉ ድረስ መገናኝትና መተላለፍ፤ አንዱ አንዱ ጋር ፍቅር ወድቆ መኖር አለ፡፡ ሥነ ጽሑፍ ውስጥ ያሉት ጭብጦች ከአሥር ከአሥራ ሁለት አይበልጡም፡፡ በነርቨስ ሲስተማችን ውስጥ ኮረንቲ ሽቦ ካልኖረ እንደሌለ በፍጥረታችን ሽቦ ውስጥ ያሉ ናቸው፡፡ ለቅሶ፣ ፉከራ፣ ፍቅር፣ አድናቆት፣…እስካሉና የሰው ባህርይ እስካልተለወጠና ተገናኝተው የማያውቁ ወይም ደግሞ ግንኙነታቸው ቀረብ ያለም ሕዝቦች ተገናኝተው ተስማሙም ተሻኮቱም አዲስ ነገር ማውጣቱ አይቀርም፡፡
እኔ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ውሰጥ በጣም ትልቅ ተስፋ ነው የሚታየኝ፡፡ በተለይ ለወጣቶች ከተጠቀሙበት፡፡ ከተጠቀሙበት ስልህ የሚጽፉት ከነሱ የሚጠበቀውን ሳይሆን እነሱ የሚፈልጉትን ከሆነ ማለቴ ነው፡፡ የሰው ፊት እየታየ ይኼ ይወደድልናል፣ ይኼ ይሸጥልናል ብለው የሚጽፉ በዓለም ላይ አሉ፡፡ ይበጀናል ካሉ ይቅናቸው፤ የሚያገኙትን ገንዘብ እግዜር ይመርቅላቸውና ይክበሩበት፡፡
ሌላ ሥነ ጽሑፍ የምለው የቴክኒክ፣ የስታይል፣ የተሰጥኦ ሳይሆን ያንተን ሳነበው አንተን ይመስለኛል ወይ? እንደዚህ ማድረግ ከቻሉ ትናንት ከወጣበት ዛሬና ነገ በብዛትና በበለጠ የማይወጣበት ምንም ምክንያት አይታየኝም፡፡ እኛንና ከኛ በኋላ የሚመጡትን፣ ከኛ በፊት የነበሩትን ምን ይለየናል? እኔ ለነበሩትም የማይገባ አድናቆት የለኝም፤ ለሚመጡትም ከነሱ ያነሰ አድናቆት የለኝም፡፡ እንደዚህ ነው የሚታየኝ፡፡
 አንዳንዶቹ ትንሽ በቆሙበት ከረር የሚሉ ነበሩ፡፡ አንዱ ዳኛቸው ወርቁ ነበር፡፡ እሱ በማርክሲዝም ጊዜ ይቀበል አይቀበል አላውቅም፡፡ ካልተቀበለ አደጋ ይደርስበታል ብዬ እፈራ ነበር፡፡ ተስፋዬ ደግሞ በአቋሙ ሳይሆን በቀልድ ችግር ይገጥመዋል ብዬ እፈራ ነበር፡፡ በጠቅላላው እነሱ ምልክቶች ይሁኑ እንጂ ለኢትዮጵያውያን ጸሐፊዎችና ሠዓሊዎች ችግር ይደርስባቸዋል ብዬ እገምት ነበር፡፡ ገብረክርስቶስ ደረሰበት፤ መጨረሻው ላይ ስለ አወጣጡ የሰማሁት ነገር አለ፡፡ እሱን አላጣራሁምና አልደግመውም፡፡ ችግር ደርሶበት ወጥቶ ታሞ በሚያሳዝን ሁኔታ አንድ ኢትዮጵያዊ በሌለበት ማንም በማያውቀው አገር ኦኮላሆማ በተባለ ቦታ ሞተ፡፡ አሜሪካ መሆኑንም አላውቅም ነበር፡፡ እኔ ያለሁት ሜኒሶታ እሱ ያለው ኦኮላሆማ ነበር፡፡ ብሰማና ባወቅ ኖሮ ቢያንስ ቢያንስ ሲሞት የሚያውቀው ፊት እያየ ይሞት ነበር፡፡ አሁን ሳስታውሰው በጣም ሆዴን ይበላኛል፡፡ የሰው ልጅ ዋና ስጦታው ከመጣው ማዕበል ጋር መውረድና መውጣት መቻል ነው፡፡ ብዙዎቹ ተረፉ፡፡ ይመስገን፡፡
ዮሐንስ አድማሱ በኔ ግምት የራሱ የከረረ አቋም ስለነበረው እፈራለት ነበር፡፡ እሱ ወደ ሶሻሊዝም ድሮውንም ዝንባሌ ነበረው፤ እነ ኃይሌ ፊዳ፣ እነመንግሥቱ ኃይለማርያም ገና ስማቸው ሳይሰማ፡፡ ግን የሁሉም ሰው ሶሻሊዝም አንድ አይደለም፡፡ እንደ ዮሐንስ ያለ ሰው ማርክስን ወይም ኤንግልስን አንብቦ እራሱ ውሳኔ ላይ የሚደርስ ሰው ነው ብዬ ነው የምገምተው፡፡ እና ከኋላ የመጡት ሁልጊዜ አጠቃላይ (Totalitarian) የሆነ አቋም በማንኛውም ፍልስፍና ወይም ሃይማኖት ላይ ያሰፍናሉ፡፡ ለምሳሌ በእስልምና ፋንዳመንታሊስት እንደሚባለው፣ እኔም አንተም ሙስሊሞች ሆነን እኔ ፋንዳሜንታሊስት ከሆንኩኝ ያንተ ተቀባይነት የለውም፡፡ እስልምናን እኔ እንደማምነው ብቻ ነው፤ ካላመንክ ግን እንገትህን ስጥ እልሃለሁ፡፡ ስለዚህ ለዮሐንስም እንደዚህ ዓይነት ነገር ይደርስበታል ብዬ እፈራ ነበር፡፡
እኔ እድለኛ ነኝ፡፡ ቀድሜ የትምህርት ዕድል በማግኘቴ ወጣሁ፡፡ እንዲያውም ችግሩ እንደዚህ ይሆናል ብዪ አልገመትኩም ነበር፡፡ እኔ ችግር ቢደርስብኝ ኖሮ በፖለቲካው ሳይሆን በጓደኞቼ ምክንያት ነው የሚሆነው፡፡ ምክንያቱም ከሰው ጋር ያለኝን ግንኙነት እኔና አንተ ወደፊት ተገናኝተን ወዳጆች ከሆን ወዳጅነታችን ከኔ እምነት ይቀድማል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ ምክንያቱም የኔ እምነት የዛሬ 20 ዓመት የነበረውና ዛሬ ያለው በጣም ተራርቆ ሄዷል፡፡ እምነት ኃላፊ ነገር ነው፡፡ የአባቶቼ ነው ብለህ የክርስትናን ወይም የእስልምናን ሃይማኖት ልታጠብቅ ትችላለህ፡፡ ሃይማኖቶቹ ያልፋሉ ማለቴ አይደለም፤ አንተ ስለሃይማኖቶቹ ያለህ አስተያየትና የአስተማመን ባህርይ ካልሞትክ ይለወጣል፡፡ ሳይለወጥ ደግሞ 50 ዓመት 60 ዓመት ከደረሰ ሞተህ ነው የቆየኸው ማለት ነው፤ በኔ ግምት፡፡ ስለዚህ በጓደኞቼ ምክንያት ችግር ይደርስብኝ እንደሆነ ብዬ እገምት ነበር፡፡


 ስለመንፈሳዊነት
መንፈሳዊነት አሁን ያለውን የአገራችንን ማኅበራዊ ችግር ለመፍታት ሊጠቅመን ይችላል ብዬ አምናለሁ፡፡ እኔ እንደሚታየኝ ለኢትዮጵያውያን ኦርቶዶክስና እስልምና እንደ ሃይማኖት ሆኖ አይታየኝም፡፡ ለኔ ማንነት (Identity) ነው፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የማንነት መለያ የሆነ ሃይማኖት አለን፤ አይጎድለንም፡፡ ነገር ግን መንፈሳዊነት ይጎድለናል፡፡
መንፈሳዊነት ለእኔ የእምነት ጉዳይ አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር የማመንና ያለማመን አይደለም፡፡ መንፈሳዊነት መጨረሻው ራስን ማወቅና አንድ መሆን ነው፡፡ የሰው ልጅ አንድ ሆኖ አይፈጠርም፡፡ በቤተሰብ ውስጥ ትወለዳለህ፤ በአንድ በኩል ያባትህን በአንድ በኩል የናትህን ይዘህ ትወለዳለህ፡፡ በሌላ በኩል አሳዳጊዎችህን፣ ወንድሞችህን፣ ጓደኞችህን ሁሉ ትመስላለህ፡፡ መምህራንህን ትመስላለህ፡፡ ስለዚህ እኔ ከነዚህ ሁሉ እንደቡትቱ ጨርቅ ተሰብስቤ ተጣፍኩኝ፡፡ እና ለኔ መንፈሳዊነት የእምነት ነገር ሳይሆን ሳልሞት ምናልባት አንድ ሰሎሞን ሊፈጠር ይችላል ወይ? ይህ ሁልጊዜ የራስህ ፈንታ የራስህ ተግባር የራስህ ግዴታ ነው፡፡ መንፈሳዊነት በመጨረሻው ከብትንትኑ የተጣጣፈ ሰው አንድ ሆኖ ተሰብስቦ ይሞታል ወይ ነው? ይህ ደግሞ በእምነት ሳይሆን በጥረት ነው የሚገኘው፡፡ ለምሳሌ ዛሬ ስንገኛኝ ይህን ነገርኩህ፡፡ ምንያህል እውነት እንደነገርኩህ ማታ ሳስብበት ነው የማውቀው፡፡ የዛሬ ዓመት ስንገናኘና ስንነጋገር ከአሁኑ የበለጠ እውነተኛ ካልሆንኩኝ የቀረው ሁሉ እንዲሁ ለይሉኝታ ሆኖ ይታየኛል፡፡
ይሉኝታ አንድን ኅብረተሰብ አብሮ ለመኖር እንዲያስችል የግድ ያስፈልጋል፡፡ መከባበር የግድ ያስፈልጋል፡፡ ማኅበረሰቡን የሚያይዝ አንድ ነገር ነው፡፡ እዚያ ውስጥ መገኘት አለብኝ፡፡ የራሰን መንፈሳዊነትና ሐቀኝነት አግኝቻለሁና ካንተ ጋር ስንገኛኝ አንተ ሳትፈቅድልኝ እዘረጥጥሃለሁ ማለት አይደለም፡፡ እዚያ ውስጥ መገኘት አለብኝ፡፡ እሱ ውጭ ያለው ሰሎሞን ነው፡፡ ሰሎሞን ብቻውን ሲሆን ደግሞ አብሮት የሚሆን፣ ዋናው ሥራዬ ግዴታዬ ወደሞት እየተቃረብኩኝ ስሄድ (አይቀርምና) መንፈሳዊ ብዬ የምገምተው አንድ ሰሎሞን ሲገኝ ነው፡፡ እናቴ ንፁህ ብራና ወለደች፤ ያልተጻፈበት፡፡ እዚያ ብራና ላይ ሕይወት እንዳጋጠመኝ ተጻፈበት፡፡ በየቦታው በመዞር እኔነቴ ተበታተነ፡፡ የኔ ብቻ አይደለም፤ የሁሉም ሰው ነው፡፡ እና አንድ ሰሎሞንን ለመፍጠር በምጓዝበት ጊዜ ሐቀኝነት እየወጣ ይሄዳል፤ እያደገ ይሄዳል፡፡ መንገድ ላይ ስሄድ የማየውን ነገር ካለሁበት አየዋለሁ፡፡
እምነት አንድ ነገር ነው፤ ብዙ ጊዜ ካሳደጉ ካስተማሩን ሰዎች የተወረሰ፡፡ ወደ መንፈሳዊነት መሄድ ሌላ ነገር ነው፡፡ ግን በማንም እመን በማን የአንተን አንድ መሆን፣ መሰብሰብ፣ ሐቀኝነት እያሳደገ የሚሄድ መንገድ ነው፡፡ እኔ ወደ መንፈሳዊነት አዘነብላለሁ፡፡
በመንፈሳዊነት ደረጃ በተለይ የአይሁድ፣ የክርስቲያንና የእስላም የተያያዘ ይመስለኛል፡፡ አይሁዶች በእስላምም በክርስቲያንም ላይ ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ የሁሉም መጀመሪያዎች ግን የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ተከታዮች ሆነው ግብፅ ውስጥ መንነው የሚኖሩ መነኮሳት ናቸው ዋናዎቹ መምህራን፡፡ አንድ አካባቢ ስለነበሩ በዚያ ላይ ክርስቲያኖች ተፅዕኖ ነበራቸው፡፡ ወደ መጨረሻው ደግሞ የእስልምና ተፅዕኖ በግዴታ ሳይሆን በፍላጎት በክርስትናና በአይሁድ ላይ አርፏል፡፡ እንደሚባለው የነኢበን ዓረቢ የሱፌዎች ጽሑፍ ባይኖር ኖሮ የዳንቴ ዲቪና ኮሜዲያ አይጻፍም ነበር ተብሎ ይገመታል፡፡


ስለግጥሞቼ
በአጭሩ ለኔ እንደሚሰማኝ በስድ ንባብ የተጻፈው እንዲገባህ፣ በግጥም የተጻፈው እንዲሰማህ ነው፡፡ ገባህ አልገባህ ሁለተኛ ነገር ይመስለኛል፡፡ ግጥምን የማነበው እንዲገባኝ ሳይሆን እንድመሰጥበት ብቻ ነው፡፡
እኔ በተለይ በወጣትነቴ የጻፍኳቸው ለምሳሌ የዚህን ኮት እጀጌ አውልቄ ብስበው ውስጡ ወደ ውጭ ይገለበጣል፡፡ ልክ እንደዚያ ውስጤን ወደ ውጭ ለመገልበጥ ነው የሞከርኩት፡፡ አንዳንድ ወጣት ፊት ለፊት ይበጠብጣል፤ አንዳንድ ደግሞ ልዝብ ጥጋብ አለበት፡፡ እኔ ድሮ ልዝብ ጥጋብ ነበረብኝ፡፡
ለምሳሌ ‹‹ጉማላሎ››ን የጻፍኩት በዚያን ጊዜ ስለአማርኛ ዕድገት ብዙ የሚያወሩ ሰዎች ነበሩ፡፡ እኔ ቋንቋን ላሳድግ ብሎ መነሳት ዛፍ ቶሎ አላደገምና እስቲ ጠዋት ጠዋት እየተነሳሁ ቶሎ ቶሎ ልሳበው እንደማለት ነው፡፡ እንደርሱ ስትስበው ሥሩ ከአፈር ይላቀቅና ይደርቃል እንጂ አያድግም፡፡ ውኃ አጠጥተኸው ፀሐይ ካገኘ ያድጋል፤ ያንተ ግዴታ የለበትም፡፡ እና ይህን ግጥም እንደ ቀልድና እንደ አመጽ ነበር የጻፍኩት፡ አዲስ አበባ ውስጥ ኖረህ በአማርኛ ግጥም ለመጻፍ ግፅዝ ማወቅ አያስፈልግህም፤ በግዕዝ አልጽፍም እኔ፡፡ እንግሊዝኛ ማወቅ አያስፈልግህም፡፡ አካባቢዬ ያለውን አማርኛ መስማት፣ አካባቢዬ ያለውን የሚታይ ነገር ማየት፣ ማየት ብቻ ሳይሆን ቆም ብዬ ምን ተሰማኝ? ብዬ መጠየቅን ይጨምራል፡፡ ብዙ ጊዜ የተሰማኝን ለመግለጽ እንኳን ያኔ አሁንም ይቸግረኛል፡፡ አሁንም ከተመቸኝ ይወጣል ብዬ የምገምተው ‹‹ብስለት›› የሚል የግጥም መጽሐፍ ነው፡፡ በዚህ ውስጥ ያሉት ግጥሞች ደግሞ በኔ አኳኋን አንዳንዶቹ ይከራሉ፡፡ አንዳንዶቹ ግን የሚከሩት እንደነዚህ በስሜት ሳይሆን በሐሳብ ስፋት ነው፡፡ የድሮዎቹን የምወዳቸው አንተና እኔ አንድ ላይ ቁጭ ብለን እኔ አንብቤልህ ስትሰማቸው ነው፡፡ ደግሞ የተጻፉት በዓይን እንዲነበቡ ሳይሆን በድምፅ እንዲጋነኑ ነው፡፡ በድምፅ ተጋነው ሲወጡ፣ የኔ ምኞት ግን ያን ጊዜ እየሰማኝ ልለው የማልችለውን አንተ ከተሰማህ ካንተ የሚወጣው ስሜት ለኔ ምላሽ ይሆናል፡፡ እና ከአንባቢ ጋር እንደ አውራጅና እንደተቀባይ ይሆናል ብዬ ነበር የምገምተው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ከፈረንጅ የተማርኩት ሳይሆን በራሴ ያለኝ ተሰጥኦ የአዋቂነት፣ የቋንቋ ችሎታ ሳይሆን ቆሜ ማየት መቻሌ ነው፡፡ ያየሁትን አምናለሁ፡፡
በአጠቃላይ ‹‹ጉማላሎ›› የተፃፈችው ማጣቀሻ /reference point/ ወደኋላ ተመልሶ ማግኘት ይህን ያህል ትልቅ ቁም ነገር ከሆነ እኔ እዚሁ እፈጥርልሃለሁ፤ ቀባጥሬ እንደማለት ነው፡፡ የነበረው ዋጋ የለውም ማለቴ አይደለም፡፡
በባህላችን አባቶችን ማክበር አንድ ነገር ነው፡፡ የተባልነውን ሁሉ ነገር መቀበል ግን ራስን እንደመካድ አድርጌ ነው የምቆጥረው፡፡ የግዕዝ ቅኔዎች እንዳሉ እንደ ግዕዝ ቅኔ ተማራቸው፣ ልክ የእንግሊዝኛውን እንደምታነበው አንብባቸው፡፡ ወደ አማርኛው ስትመጣ ግን እነሱ መነሻ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ማጠሪያና ማሰሪያ ከሆኑ ግን ነገር ተበላሸ ማለት ነው፡፡
የኔ ግጥሞች ምናልባት የሚያስቸግሩት አንደኛ ለአነባበቡ የኔን ድምፅ መፈለጉ እና እኔ እንዴት ነው የምሰማቸው በማለት መነሻው እኔ ስለሆንኩኝ ነው፡፡ ለዚህ ትንሽ ያስቸግሩ ይሆናል፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የምስል ፈጠራው (Imagery) ጉዳይ ነው፡፡ የተጻፉት ታይተው እንዲያልፉ ነው፡፡ እኔ ሁሉም ነገር ኃላፊ መሆኑን በጣም አምናለሁ፡፡ ሁሉም ነገር ኃላፊ ነው፡፡
ሌላ ነገር ደግሞ ስለግጥም ስንነጋገር እኔ ላሊበላን በድንጋይ እንደተጻፈ ቅኔ ነው ያየሁት፡፡ በጣም ያስገረመኝና ለረዥም ሰዓት በቆምኩበት አድርቆ ያስቀረኝ ሥራው መሠራቱ አይደለም፡፡ ይሄ ላሊበላ የሚሉት ሰው (እንደኔና እንዳንተ አድርገህ ያየኸው እንደሆነ) ምን ሲያደርግ አሰበው? ከአንድ ተራራ ላይ ቆመህ ከሌላኛው ተራራ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ቆፍሬ አወጣለሁ ብሎ ማሰብን እንደ እብደት ነው ያየሁት፡፡ ይኼን ጤና ያለው ሰው አያስብም፡፡ በተለይ ጤና ያለው ኢትዮጵያዊ የሚያስበው እንዴት መሥራት እንደማይቻል ነው፡፡ እና ግጥም (ቅኔ) ፀሐፊው ዕድለኛ ከሆነ ከእንዲህ ያለ እብደት ነው የሚወጣው እንጂ ታዲያማ ማን ፈቅዶልኝ ምን አውቄ ነው የአማርኛ ግጥም የምጽፈው? ትንሽ ጥጋብ ያስፈልጋል፣ ትንሽ ልበ ደንዳናነትና ትንሽ እብደት ያስፈልገዋል፡፡ ላሊበላ የድንጋይ ቅኔ ነው ስልህ መሠረቴ ይኼ ነው፡፡
የአክሱምን ሐውልት ስታየው የሚያስገርመኝ መሠራቱ አይደለም፡፡ ሐሳቡ ነው እንጂ የሚጎላው ኢትዮጵያ ተነስታ፣ እኔ እንደ አሜሪካ ጨረቃ ላይ ሰው አወርዳለሁ ብትል ከባድ አይመስለኝም፡፡ ትንሽ ማቲማቲክስና ትንሽ ፊዚክስ ቢበዛ ለሰባት ዓመታት መማር ነው፡፡ እኔን የሚገርመኝ ምን ሲያደርጉ እንደ አሰቡት ነው፡፡ የአክሱምን ሐውልቶች ስታያቸው ማነው እዚያ ቆሞ መጀመሪያ ያሰበው? ምን አሳሰበው? አንድ ጊዜ ከታሰበ በኋላ ምንም ቁም ነገር አይደለም፤ ይኼን ያህልም አይጨፈርበትም፡፡ ማርስ መሄድ ሆነ፣ ህዋን ሰንጥቆ ማለፍ ወይም የአክሱምን ሐውልት ማቆም ወይም የላሊበላን አቢያተ ክርስቲያናት መጥረብ ምንም አይደለም፣ ይኼን ያህል ትልቅ ነገር አይደለም፡፡ መዶሻና መጥረቢያ ይዘህ መነሳት ብቻ ነው፡፡ የሚገርመው የመጀመሪያው እዚህ ድንጋይ አቆማለሁ ብሎ ያሰበው ሰውዬ ምን ሲያደርግ አሰበው? የሚለው ነው፡፡
እኔ ሁሉንም ግጥም ስፅፍ ይህን ሐሳብ ያስተላልፍልኝ ብዬ አይደለም፡፡ ለምሳሌ አንድ ‹‹ተዛወር ማኪና›› የምትል ግጥም አለች፡፡ የወንድሜ ልጅ ተወለደች፡፡ ግጥሙ ‹‹ለአይዳ›› ይላል፡፡ የተወለደችው ልጅ ባንድ በኩል ትግሬ ናት፡፡ ባንድ በኩል የወለጋ ኦሮሞ ነች፡፡ የተሰማኝ ስሜት የተራራቁ ባህሎች ድንገት አንድ ላይ ተወሳስበው በሷ ሥጋ ለበሱ፡፡ ያ ስሜት በቃል የሚሰማ አልነበረም፡፡ ድርሰት መፃፍ እችል ነበር፡፡ ታሪኩን ብፅፈው ምንም የምናገረው አዲስ ነገር የለም፡፡ አንድ ነገር እንዲሰማህ ለማድረግ ነበር፡፡ እና ታሪኩን ትቼው ስሜቱን ብቻ ብፅፈው ብዬ ታሪኩ ቀርቶ ስሜቱ ብቻ የቀረለት ግጥም ሆነ፡፡
አንዳንዶቹን ግጥሞች ስፅፍ ቃላት አልሰማም፤ ሐሳብም የለኝም፡፡ ከዚያ ነው የሚወጡት፡፡ እነሱን እንደዚያው እለቃቸዋለሁ፡፡ አንዳንዶቹ ልክ እንደዚያች እንደ ለ2 ሺሕ 1 ዓ.ም. ፀሎት ያሉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ አወራረድ የያዘ ሲሆን አወራረዱ ግን ትንሽ ለየት ይላል፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ ስንል እኛ ሁላችንም መስጊድ እንደገባ ሰው እንስገድ የሚል ነው፡፡ ለኔ እንደሚታየኝ ለኢትዮጵያ ታሪክ መስገድ ለሰሎሞን ዴሬሳ እንደመስገድ ነው፡፡ ከውጭ የመጣ ሰው ይስገድለት እንጂ የራሴ ነው ምን አሰገደኝ፡፡ ከዚህ ታሪክ ነው የመጣሁት፤ አወራረዱ እንደሱ እንዲሆን ነው፡፡ ጥያቄ - የከበርንበትን ሳይሆን የተውነውን መጠየቅ፡፡ ምን ተፈጠረና ነው ላሊበላ ላስታ ውስጥ ብቻ ተፈጥሮ ሌላ ቦታ የቀረው? ለምን ርዝራዡ ቴክኒኩ ወጥቶ ለሰው መኖሪያ ቤት አልዋለም? እንዴት ነው ርዝራዥ ሳይደርሰን የቀረው? አክሱም ያን ያህል ተሠርቷል፡፡ የማያልፍ የለም፡፡ ከዚያ ከርዝራዡ እንዴት ለትግራይ ሕዝብ አልተረፈም? እንደሚመስለኝ ቁጭ ብለን ከማየት፣ ከማተኮር፣ ከመመሰጥ አብልጠን ትምህርት እንፈልጋለን፡፡ ሁልጊዜ ትምህርት የምትፈልግ ከሆንክ ተማሪ ሆነህ ነው የምትቀረው፡፡ ዘላለም ወጣትነትን ከፈለግህ አባት ሳትሆን ታልፋለህ፡፡ ይህን ለመቋቋም ጥያቄ መጠየቅ፡፡ ታሪክን፣ የአገርህን ባህል ዳኛ ሆነህ ቁጭ ብለህ ማንም ሳይሰይምህ ‹‹ተጠየቅ›› ካላልከው የእንጨት ሽበት ይለዋል አበሻ፡፡
ወደ መንፈሳዊው ልዙርና እኔ መንፈሳዊነት የምለው Mysticism የሚለውን ነውና ከዕለት ኃይማኖት ጋር ግንኙነትም ልዩነትም አለው፡፡ በሳይንሱም ያው ነው፡፡ ምሳሌዬን በሳይንሱ ላድርገው፤ አይንሽታይን እስኪመጣ ድረስ ዓለም (ፍጥረት) የስዊስ ሰዓት ሠሪ እንደሚሠራው ተሠርቶ አንድ ጊዜ ተጠምዝዞ ተለቋል፣ ከዚያ በኋላ ምንም የሚጨመር ነገር የለም ብሎ ተቀምጦ ነበር፡፡ ‹‹ከኒውተን ወዲያ እውቀት ንፍጥ ለመለቅለቅ ነው›› ብለው ቁጭ ያሉ ነበሩ፡፡ እንዲያውም አንድ የፈረንሳይ ፊዚስስት እንደዚህ ብሎ ጽፏል፡፡ አውሮፓውያን ጨርሰናል በቃ ብለው ቁጭ ብለው ነበር፡፡ አይንሽ ታይን ስዊትዘርላንድ ወስጥ የአንድ ቢሮ ተራ ፀሐፊ ነበር፤ መዝገብ አመላላሽ፡፡ ይህ ጊዜ ሰጥቶት ቁጭ ብሎ ራሱን መጠየቅ ጀመረ፡፡ እና Theory of Relativity እና በመጠኑም ቢሆን Quantum Mechanics ራሱን ከመጠየቅ ከሱው ነው የመጡት፡፡ አይንሽታይን ዩኒቨርሲቲ ውስጥ አልነበረም፡፡ የኒውተን ፊዚክስ ሚቶሎጂ (እምነት) ሆኖ ነበር እምነቱን ተጠየቅ የሚል ሰው መጣ፡፡ አይንሽታይን ተጠየቅ ባይለው ኖሮ ጨረቃ ላይ መሄድ አይታሰብም ነበር፡፡ አሁን ስለዩኒቨርስ የምናውቀው አይታሰብም ነበር፡፡ ነገ ደግሞ አይንሽታይንን ተጠየቅ የሚለው ሰው ካልመጣና ሳይንቲስቶች የሱ ተማሪ ብቻ ሆነው የቀሩ እንደሆነ ‹‹በአፄ ምኒልክ ጊዜ የደነቆረ ምኒልክ ይሙት እንዳለ ይሞታል›› እንደሚባለው ይሆናል፡፡


ስለኢትዮጵያውያን
እኔ ብዙ ቦታ ዞሬያለሁ፡፡ አፍሪካ፣ አሜሪካና አውሮፓ፡፡ ዘረኝነት እንዲመስልብኝ አልፈልግም፤ እኔ ዘረኛ አይደለሁም፡፡ ግን እንደ ኢትዮጵያውያን ብሩህ አዕምሮ ያለው ብዙ ቦታ አላጋጠመኝም፡፡ ዋጋ ከፍለን ነው ያ ብሩህ አዕምሮ የመጣው፡፡ በአማርኛ ምን እንደምንለው አላውቅም፡፡ Imagination በጣም ያንሰናል፡፡ እንዲህ ዓይነት ጥያቄ ማንሳት እፈልጋለሁ፡፡ ለምንድነው በዓይናችን የምንጠቀመው? ደብረ ብርሃን ሥላሴ ስገባ የሥዕሎቹን ታሪክ ጥሩ አድርገው ነገሩኝ፡፡ ግን ሥዕሎቹን የሚያዩ እኔንም ለማየት ጊዜ የሰጡኝ አልመሰለኝም፡፡ የጊዮርጊስ ሥዕል ደራጎኑን ሲገድል ታሪክ አለው፤ እሱ ራሱን የቻለ የሚስብ ነገር ነው፡፡ ግን እሱን በአማርኛ ድርሰት በአንድና በሁለት ገጽ ማጠቃለል ይቻላል፡፡ እፊቴ ያለው ግን (ሥዕሉን ማን እንደሣለው ባላውቅም) ራሱን የቻለ ዓለም ነው፡፡ ከተጻፈም በኋላ ለማየት፣ ሳይጻፍም በፊት ለማተኮር የአዕምሮን ብሩህነት ከዓይን ማየት እናስቀድማለን፡፡ ይህ በጠቅላላው ትልቅ ችግር ይመስለኛል፤ ለሁላችንም፡፡
አክሱም ውስጥ የተሠሩት ከዚያ በኋላ አልተደገሙም፤ አልፎ ጎንደር ውስጥ ተሠሩ አልተደገሙም፤ ከዚያ በፊት የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ተሠሩ አልተደገሙም፡፡ አይቀጥልም፡፡ እዚህ በየትኛውም ዓለም ቢሆን የሚደነቁ ከአንድ ተራራ የተቆረጡ 11 አብያተ ክርስቲያናት አሉ፡፡ አጠገቡ ያልተመረገ ቤት ታያለህ፡፡ የድህነት ጉዳይ አይደለም፡፡ ጭቃም አለ ሳርም አለ አንድ ላይ አቡክቶ ወር አስቀምጦ አንስቶ መምረግ ነው፡፡ ምክንያቱ የዓይን አለማየት ነው፡፡ ላሊበላ ያለ ሰው ሁሉ (ሌላውም) ቆም ብሎ (ታሪኩ በሚገባ ያውቀዋል) ላሊበላ ምን ነክቶት ነው ይኼን ያሰበው አይልም፡፡ እንደዚያ ሳስበው ከዕውቀት አልፎ ለኔ ምሰጣ ገባ፡፡ ምሰጣ ገባ ስልህ እንደሱ ዓይነት ስሜት ተሰምቶኝ ከሆነ በ19 ዓመቴ ፍቅር የያዘኝ ጊዜ ነው፡፡ አሁን የምጽፋቸው አንዳንድ ግጥሞች ስለሱም የሚያነሱ አሉ፡፡ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን እኔንም ጭምር ሳስበው (እኔ ደግሞ መላቀቅ የምፈልገው) ከተወለድኩበት ባህል ይኼ አዕምሮን ከዓይን ማስቀደም፤ አዕምሮን ከስሜት ማስቀደም ነው፡፡ አዕምሮማ ብቻ ብንሆን ኖሮ ሥጋ አንለብስም ነበረ፡፡ ኢቮሉሽን አራት ሚሊዮን ዓመት ታግሎ ዓይንን አይፈጥርም ነበር፡፡ ዓይን ማየቱ በጣም ስፔሻላይዝድ የሆነ የሚገርም ነገር ነው፡፡ ቆዳ እኮ ነው ምንም የለውም፡፡ ቆዳ ብርሃንን ማየቱና በዚያ አለመመሰጥ ምን ያህል ሳይንስ፣ ታሪክ ብንማር ተማሪዎች አድርጎ ያስቀረናል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በተለይ በዚህ በኪነ ጥበብና በመንፈስ በኩል ትንሽ እብደት ያላቸው ሰዎች ያስፈልጋሉ ብዬ አምናለሁ፣ ማበድ ያስፈልጋል፡፡
ስለኢትዮጵያ ብሔረሰቦች
ስለዚህ ጉዳይ ከውጭ መጥቼ በአንድ ሳምንት ውስጥ ስለኢትዮጵያ ኤክስፐርት መሆን አልፈልግም፡፡ ግን ካየሁትና ከምሰማው አንድ የሚታየኝ ትግርኛ የሚናገሩ፣ አማርኛ የሚናገሩና ኦሮምኛ የሚናገሩ ኢትዮጵያውያን እዚህ ያሉት እነሱ ብቻ ሆነው እንደሚናገሩ ይመስላል፡፡ በርካታ ቁጥራቸው ትንሽ የሆኑ ሕዝቦች መኖራቸውን የረሳነውና ውይይቱ በኛ መካከል ብቻ የሚካሄድ ይመስላል፡፡ እኔ ይኼ ጥጋብ ይመስለኛል፡፡ ምክንያቱም በቁጥር ብዛት እውነት አይቆምም፡፡ እውነቱ ደግሞ ቀላል ነው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ሕዝቦች አሉ፡፡
የኢትዮጵያን ታሪክ ያየኸው እንደሆነ በአንድ በኩል ያስገርማል ያሰኛል፡፡ ባንድ በኩል ደግሞ ያሳዝናል፡፡ ሥልጣኗን ተፈራርቀንባታል፡፡ ጎንደርን ኦሮሞዎች ገብተው ንጉሥ አንግሠው የሚገዘቡበት ጊዜ ነበር፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ከተነሱ በኋላ ግዛቱ ወደ ጎንደር ሕዝብ ተመለሰ፡፡ አፄ ዮሐንስ ሲመጡ የትግራይ ዘመን ሆነ፡፡ ምኒልክ ሲመጡ የመሀል አገር የአማራው ግዛት ሆነ፡፡ አሁን ደግሞ ሥልጣኑን የያዙት ከውጭ እንደሚታየው ከትግራይ የመጡ ሰዎች ይመስላሉ፡፡ ሁሉም ኃላፊዎች ናቸው፡፡ መፈራረቅ አይቀርም፡፡ ነገ ማን እንደሚመጣ አላውቅም፡፡ ወይ አማራው ይሆናል ወይ ኦሮሞው ይሆናል፡፡ የሚመጣበትን መንገድ ደግሞ ልንገምት አንችልም፡፡ የማያልፈው ይኼ ግንኙነት ነው፡፡ የማያልፈው ደግሞ የኛ ግንኙነት ትልቅ ሆኖ፤ ከሌላው ዓለም የበለጠ የሚያምር ነገር ሆኖ ሳይሆን የመልክዓ ምድር አቀማመጣችን ነው፡፡
በአንድ በኩል ስታስበው ኢትዮጵያ ውስጥ ተቀምጦ እኔ የትግራይ ሰው ነኝ፣ እኔ አማራ ነኝ ብሎ አፍ ሞልቶ መናገሩም አለማወቅ ይመስለኛል፡፡ በሴት አያቶቻችን በራፍ ላይ ማን እንዳለፈ ስንቶቻችን ነን የምናውቀው? የኔን ጥሩ ኦሮሞነት እግዚአብሔርና የሴት አያቶቼ ብቻ ናቸው የሚያውቁት፡፡ የሁሉንም እንዲሁ፡፡ ጦር ባለፈ ቁጥር በመዋለድ፣ በንግድ በመገናኘት፤ ተቸግሮ ከአገር ወጥቶ ሌላ ቦታ በመኖር ይቀላቀላል፡፡
እኔ እናቴ ወለጋ ነበር የሚኖሩት፡፡ ያደግሁት ጋሼ መሐሪ፣ አባባ ደሳለኝ እያልኩኝ ከትግራይ፣ ከጎጃም፣ ከጎንደር፣ ከሸዋ፣ ከጉራጌ የመጡና እዚያ የሠፈሩትን እየጠራሁ ነው፡፡
ቅድም ስለግጥም እንደተናገርኩት የተባለውን ነገር በዚያው መደጋገም ሰውን ማሰልቸት፣ ራስንም መሰልቸት ነው፡፡ ሕይወትንም ጣዕምና ትርጓሜ ማሳጣት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክ የመጣው ሁሉ አማራ የገዛ እንደሆነ ሌላውን ቁልቁል ይዞ፣ ትግሬ የመጣ እንደሆነ ሌላውን ቁልቁል ይዞ እያልን ይህንን ስንት ሺሕ ዓመት ነው የምንደጋግመው፡፡ ምን ያህል እንለያያለን? ዘር በመቁጠር ደረጃ እኔ ምንም ችግር አይታየኝም፡፡ ምክንያቱም በራስህ ለመኩራት መጀመርያ በአባትህና በናትህ መኩራት አለብህ፡፡ እሱን እንደ ምግብ በልተኸው ነው ያንተ በራስህ መተማመን የሚመጣው፡፡ ለምሳሌ እኔ ከትግራይ ሰው ጋር ተገናኝቼ የማጫውትህ የትግራይን ትልቅነት ነው ቢለኝ በል ቁጭ በልና እንጨዋወት ነው የምለው፡፡ ከዚህ በላይ ምን ያጫውተኝ? የወለጋውን እንዲያጫውተኝ የሱ አይደለም፡፡ ከጎንደር የመጣ ሰው የጎንደርን ትልቅነት ላጫውትህ ሲለኝ ሌላ ምን ያጫውተኝ፡፡ ጎንደር የሄድኩት የዘመዶቼን ትልቅነት ለመስማት አይደለም፡፡ የነሱን ትልቅነት ለማየትና ለመስማት ነው፡፡ ከዚያ ባለፈ ግን ስንት ኦሮሞ ከብት በነዳበት አገር እኔ የጠራሁ አማራ ነኝ፣ ወይም ንፁህ ትግሬ ነኝ ቢል አነጋገሩ ‹‹ለማያውቅሽ ታጠኝ›› ነው፡፡
በባህል በኩል፣ በጥበብ በኩል ምንም ዋጋ ያለው አይመስለኝም፡፡ አንዱ አንዱን መጫን ከየት ነው የመጣው ያልከኝ እንደሆነ ከድንጋጤ ነው፡፡ የሰው ልጅ ለሕይወት ያለውን መልስ ያየህ እንደሆነ ከድንጋጤ ነው የሚመጣው፡፡ ሁልጊዜ ጠዋት ተነስተን ዛሬ ምን እበላለሁ? ምን ለብሼ አድራለሁ? ብለህ መወራጨቱ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ በታሪካችን ሲጻፍ ያየኸው እንደሆነ ሁል ጊዜ እንደጀግንነት የሚታየው ጦርነት ብቻ ነው፡፡ እኔ ደግሞ የጦረኝነት ድፍራት ከድንጋጤ የሚመጣ ነው የሚመስለኝ፡፡ የጦርነት ጀግንነት ከድንጋጤ፣ ሞትን ከመሸሽ የተነሳ ነው፡፡ ወደፊት ለኢትዮጵያ የምመኝላት ካለ የማይደነግጡ፣ የሚያልፉ መሆናቸውን የሚቀበሉ ሰዎችን ነው፡፡ ለራሴ የምመኘውን ነው ለኢትዮጵያ ወይም ለኢትዮጵያዊ የምመኘው፡፡ ለራሴ የማልመኘውን አልመኝም፡፡ ለራሴ የምመኘው ፍርሃቴን፣ ኃላፊ መሆኔን ምንም አለመሆኔና መሬት፣ አፈር መሆኔን መቀበል መቻሌ ነው፡፡ የሰውን ልጅ የሚመራው በፍርሃትና ድንጋጤ ነው፡፡ ዕድገት ደግሞ ከዚያ ማለፍ ነው፡፡ በእኛ በኢትዮጵያውያን ታሪክ ጀግንነት ከጦርነት አልፎ በሕይወቴ ባየው ደስ ይለኝ ነበር፡፡ ግድ ከሆነ ጊዜዬና ዕድሜዬ ቢሆን እዚያ ውጪ እንደተሠለፉ ልጆች መሠለፍና መሞት እችላለሁ፡፡ ይህ አንድ ዓይነት ግዴታን መቀበል ነው፤ ከዚያ የባሰ ጀግንነት ወይም አለመፍራት የእኔ ኃላፊ መሆን መቀበል ነው፤ በደራሲነትም ሆነ የሰው ልጅ በመሆን፡፡
ስለኢትዮጵያዊነት ሌላ ልናገር የምፈልገው ነገር አለ፡፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ስመጣ ሰላምታ የሚል መጽሔት ተሰጠኝና አገላበጥኩ፡፡ እዚያ ውስጥ ካለማየት የመጣ አንድ ችግር ታየኝ፡፡ አዘጋጆቹም ጽሑፍ የሚያቀርቡትም ፈረንጆች ናቸው፡፡ እጅግ በጣም ገረመኝ፡፡ ለምሳሌ በዚያ ባነበብኩት መጽሔት ላይ ስለቡና ሥነ ሥርዓት የተጻፈ አለ፡፡ በእንግሊዛዊት የተጻፈ፡፡ ለምን አገራችንን ወደዱ አይደለም፡፡ ግን ስለቡና ሥነ ሥርዓት ከእነፍፁም መንፈሱ ቁርሱ ለማን እንደሚረጭ ጭምር የምናውቀው አገሬዎቹ ነን፡፡ ለእንግሊዛዊው ደግሞ አቀላጥፎ የሚጽፍ ሞልቷል፡፡ አሁን እንዲያውም አዲስ ትሪቢዩን፣ ዘሞኒተር፣ ዘሪፖርተር የሚሉ የግል ጋዜጦችም አያለሁ፡፡ እንግሊዝኛቸው ጥሩ ነው፡፡ ስለዚህ ቋንቋ ምክንያት አይሆንም፡፡ የእኔ የተቃውሞ ምንጭ ግን መጽሔቱ እንግዳ መቀበያ ኢትዮጵያን ማስተዋወቂያ በመሆኑ፣ እንግዳ ሲመጣ ኢትዮጵያውያንን የባህል ልብስ አልብሰህ እንዲቀበሉ ታደርጋለህ እንጂ፣ ፈረንጅን የባህል ልብስ አልብሰህ እንግዳ ተቀባይ አታደርግምና ስለአገሩ ለእንግዳ መቀበያ የሚፈጸመው አገሬው መሆኑ የግድ ያስፈልጋል ባይ ነኝ፡፡ 


ስለ ጋዜጠኛነት
በእኛ ጊዜ ጋዜጠኛ ጉጉ ነው አዲስ ነገር ቆፍሮ ለማውጣት መንግሥትን የሚያስቆጣ ነገር ቢሠራም አለቆቹ አሳልፈው አይሰጡትም፡፡ ባለሥልጣናቱም በወቅቱ ጥፋት የተባለን ነገር የሠራ ሠራተኛን በኋላ ጥሩ ነገር ከሠራ በደስታ ይቀበሉታል፡፡ አንድ ጊዜ አሳምነው ገብረ ወልድ ንጉሡን የሚያበሳጭ ሥራ ይሠራል፤ በአስቸኳይ እንዲባረር ይወሰንበታል፡፡ በወቅቱ ግን ተጨቃጭቀን በግማሽ ደመወዝ እኔ ቢሮ እንዲቀመጥ አደረግን፡፡
ያን ጊዜ የማስታወቂያ ቱሪዝም ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ጌታቸው መካሻ ቢሮዬ መጥተው ንጉሡ ወደ አሜሪካ ሊሄዱ ነውና አብሯቸው የሚሄድ ጋዜጠኛ መድብ ሲሉኝ ከአሳምነው ገብረ ወልድ በላይ ብቁ የለምና እሱ ነው መሄድ ያለበት አልኩ፡፡ ሁኔታው ቢያስቸግራቸውም ከብዙ መነጋገር በኋላ ዶ/ር ጌታቸው ሐሳቡን ተቀብለው ለንጉሡ ነገሩ፡፡ ንጉሡም አልተቃወሙም፡፡ ሲመለስ ጥሩ ፕሮግራም ሠራ፣ ንጉሡም ወደዱት፡፡ ስለዚህ ወዲያው ወደ ሥራው እንዲመለስ አዘዘ፡፡ የዚህ ዓይነት ነገር በብርሃኑ ዘርይሁን ላይ ተከስቷል፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ስለ አፄ ቴዎድሮስ ሲጽፍ፣ ‹‹አፄ ቴዎድሮስ የሰሎሞን ዘር ነኝ፡፡ እስራኤላዊ ነኝ አይሉም፤ ኢትዮጵያዊ ነኝ ነው የሚሉት፤›› የሚል ሐሳብ አሠፈረ፡፡ ንጉሡም ሹማምንቶቹም በዚህ ተቆጥተው ብርሃኑ ይባረር ተባለ፡፡ እኛ ግን አይሆንም ብለን ብዕሩ ጥሩ ስለሆነ ሬዲዮ ይሥራ አልንና አቡነ ጴጥሮስ ሐውልት ሥር ደበቅነው አይታይም ብለን አይደለም ግን ሰው የሚንቀሳቀሰው በቅንነት ስለነበረ የሚያሳጣ አልነበረም፡፡
ሌላም ጉዳይ አለ፤ ነፃነት፡፡ ያን ጊዜ ንጉሡን ላለማበሳጨት ራሳችንን ሳንሱር እናደርጋለን እንጂ ሌላ የለም፡፡ ባለሥልጣናትንም ለማግኘት አያስቸግርም፤ ጋዜጠኛ የታፈረ የተከበረ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ወደ ቤተ መንግሥት ለሥራ ስንሄድ የቤተ መንግሥት ዘበኛ ቁሙ፣ ተፈተሹ ሲለን መኪናችንን አዙረን ወደ መጣንበት ሄድን፡፡ ትንሽ ተጨዋውተን ወደ ቤተ መንግሥት ስልክ ደውለን ለሥራ መጥተን ነበር የቤተ መንግሥት ጠባቂዎች ስላንገላቱን ተመልሰናል አልናቸው፡፡ ኑ ተባልንና ስንሄድ የቤተ መንግሥቱ በር ተከፍቶ ጠበቀን፣ ሳንፈተሽ ገባን ሳንፈተሽ ወጣን፡፡ ይኼ ዛሬ ሊሆን አይችልም፡፡ ግን ይህን ያህል ለመጥገብ አቅም ያላችሁ አይመስለኝም፡፡
ማሳረጊያ
በዚህ በእስካሁኑ ሕይወቴ ቁልቁልም ወደ ላይ የማየው፤ ከቀረብኩት ደግሞ የማላፈቅረው ሰው እንደሌለ ተረድቻለሁ፡፡ በተጨማሪም ሰውን ሳትዳኘው ስለራሱ ሲያወራ ብታዳምጠው ስለአንተ እያወራ ነው የሚመስልህ፡፡ ሲሆን የሠራሁትን አለዚያም ባልሠራውም ያሰብኩትን ነው የሚያወራኝ፡፡
ሰሎሞን ዴሬሳ! ሰሎሞን ዴሬሳ! ሰሎሞን ዴሬሳ!


8 November 2017
ጥቅምት 29፣ 2010 ዓ.ም.
በቅርቡ በ80 ዓመቱ ዜና ዕረፍቱ የተሰማው፣ በዘርፈ ብዙ ዕውቀቱ ተጠቃሽ የነበረው ዕውቁ ገጣሚና ጸሐፊ፣ ጋዜጠኛና የፍልስፍና መምህር ሰሎሞን ዴሬሳ ሥርዓተ ቀብሩ ጥቅምት 25 ቀን 2010 ዓ.ም. በሚኔሶታ ከተማ በግብአተ እሳት መፈጸሙ ይታወሳል፡፡
ነፍስ ኄር ሰሎሞን ዴሬሳ ከ19 ዓመታት በፊት (መስከረም 1991 ዓ.ም.) ከሪፖርተር መጽሔት ከፍተኛ ሪፖርተር (በወቅቱ) ገዛኸኝ ጌታቸው ጋር ቃለ ምልልስ አድርጎ ነበር፡፡ በዚያ ቆይታው ስለትምህርቱ፣ ስለጓደኞቹ፣ ስለግጥሞቹ፣ ስለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ፣ ስለመንፈሳዊነት፣ ስለኢትዮጵያውያንና ስለብሔረሰቦች፣ እንዲሁም ስለጋዜጠኝነት ሰፊ ሐተታ ሰጥቷል፡፡ ለዝክረ ነገር ይሆን ዘንድ በዚህ እትም የመጀመርያው ክፍል ሲቀርብ ቀሪው በእሑዱ እትም ይስተናገዳል፡፡

ዐውደ ሕይወት
በወለጋ ክፍለ አገር ጩታ በተባለች መንደር በ1929 ወይም በ1930 ዓ.ም. [1937] ተወለድኩ፡፡ በጣሊያን ጊዜ፡፡ አራት ዓመት ሲሞላኝ ዘመዶቼ ወደ አዲስ አበባ ይዘውኝ ስለመጡ አገሬ አዲስ አበባ ነው ማለት ይቀለኛል፡፡
ትምህርት አልገባ ብሎታል ተብዬ ያልገባሁበት ትምህርት ቤት የለም፡፡ በመጨረሻ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በ16 ዓመቴ ገባሁ፡፡ እዚያም ከትምህርቱ ይልቅ ልጅ ሁሉ እንደሚያደርገው ጨዋታና መበጥበጥ ይበልጥብኝ ነበር፡፡ ክፍል ውስጥ የሚገኘውን ትምህርት አላጠናቅኩትም፡፡ ነገር ግን ዩኒቨርሲቲው ውስጥ ከሚገኙት ልጆች መጻሕፍት ቤቱን እንደኔ የተጠቀመበት ብዙ ተማሪ ያለ አይመስለኝም፡፡ ከዚያ ለሦስት ወራት የእንግሊዝኛ ዜና አንባቢ ሆኜ በአሁኑ ራዲዮ ኢትዮጵያ በቀድሞው ራዲዮ አዲስ አበባ ተቀጠርኩ፡፡ ከአለቃዩ ጋር በልጅነቴ የተነሳ አልተስማማንም፡፡ ወዲያው እንዳጋጣሚ ፈረንሣይ አገር ስኮላርሺፕ አገኘሁ፡፡ በዩኒቨርሲቲው ታሪክ በፈረንሣይኛ ቋንቋ ትምህርት የጅማሪ ክፍሎን ሦስት ጊዜ በተደጋጋሚ የወደቀ ቢኖር እኔ ብቻ ሳልሆን አልቀርም፡፡
ፈረንሣይኛ ይህን ያህል አላስቸገረኝም፡፡ ተማሪ ቤት ተመዘገብኩ፡፡ ፈረንሣይ አገር የዩኒቨርሲቲ ፈተና በዓመት አንድ ጊዜ ነው የምትፈተነው፡፡ የምማረው ቱሉዝ ነበርና እኔ አውሮፓ ውስጥ ስዞር ከርሜ አንድ ሦስት ወር ሲቀረው መጥቼ አጥንቼ አልፋለሁ፡፡ በኋላ ሰዓሊው እስክንድር በጎስያን ጥቁር አሜሪካዊት አላባማ ሊያገባ ስለነበር ለሱ ሚዜ ሆኜ አሜሪካ ሄድኩኝ፡፡ ሁለተኛ ወደ አውሮፓ አልተመለስኩም፡፡
ወደ ካሊፎርኒያ ሄጄ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ ሥራ አገኘሁ፡፡ በቴፕ እየቀረፁ ቋንቋ ማስተማር የመጀመሪያውን ክፍላቸውን ከጌታሁን አምባቸው ጋር እኔ ነበርኩ ያቋቋምኩት፡፡ ያላየሁት ገንዘብ እጄ ገባ፡፡ አማርኛ አስተምር ነበር፣ ይህን አሠራ ነበር፣ በኋላ ላይ ደግሞ ዎልፍ ሌስላው ‹‹ኢትዮጵያን ዲክሽነሪ›› ብሎ ያወጣትን አንድ አሥራ አንድ ኢትዮጵያውያን ሆነን ስንሠራ እሱ ሱፐርቫይዘር ነበር፤ በዚህ ሁሉ የማገኘው ገንዘብብ ኪሴን ሞላው፡፡
ከዚያ ወደ ኒዮርክ ሄድሁና ለአንድ ለሁለት ቀን ሉካንዳ ውስጥ ሥራ እሠራለሁ ብዬ ገባሁ፡፡ ገንዘቡ ጥሩ ነበር፤ ግን የሥጋው ሽታ ስለበዛ እሱን ጥዬ ወጣሁ፡፡ ግራና ቀኝ ስል በተባበሩት መንግሥታት ሥራ አገኘሁ፡፡ እዚያ እየሠራሁ አንድ ማስታወቂያ አየሁ፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ ሠራተኛ ይፈልጋል›› የሚል ሲሆን፣ አሜሪካኖችም ሌሎችም ሲያመለክቱ እኔም አመለከትኩ፡፡ በቋንቋ ማወቅ ስለሆነ እኔ አማርኛ፣ ኦሮምኛ፣ ፈረንሣይኛ፣ እንግሊዝኛ እናገራለሁ፡፡ ትግርኛም ትንሽ ትንሽ እሰማ ነበር፡፡ በዚህ አሜሪካኖቹን አሸንፌ ተቀጥሬ መጣሁ፡፡
በእውነት ያደግሁት ራዲዮ ኢትዮጵያ ውስጥ ነው፤ ነፍሴን ያወቅሁት፡፡ ወደ መጨረሻ ከዚያ ስወጣ የራዲዮ የቴሌቪዥን ምክትል ሥራ አስኪያጅ ነበርኩ፤ ለአዲስ ሪፖርተር እንግሊዝኛ መጽሔት እሠራ ነበር ግጥም እፃፅፍ ነበር፡፡
እውነቱን ለመናገር እኔ ገጣሚ ነኝ ብዬ አስቤ አላውቅም ነበር፡፡ እንዲሁ በየቦታው እየተጻፈ (አሁንም እንዲሁ ነው) የጠፋው ጠፍቶ የተገኘውን ባለቤት ስብሰባ ካስቀመጣቸው ውስጥ ‹‹ልጅነት›› ወጣች፡፡ የቀሩትን እዚሁ ትቻቸው ሄድኩኝ፡፡ እንደ ሦስት ጅምር ተውኔቶች፣ የአጫጭር ልቦለድ ስብስቦችና ግጥሞች እዚሁ ቀረሁ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ጽሑፍ አስተምር ስነበር ለብዙ ጊዜ አልጽፍም ነበር፡፡ ለእኔ ሁለቱ አንድ ላይ አልሄደም፤ አስቸገረ፡፡
የማስተምረው Critical Thinking እና Creative Writing አንድ ላይ በማንኛውም አቅጣጫ ነው፡፡ Wrting for the sciences writng for literature writing for the fin arts writing for the social sciences አስተምር ነበር፡፡ ለማስተማር ኳሊፊኬሽን ኖሮኝ አያውቅም፡፡ ሳመለክት እንዳጋጣሚ እቀጠራለሁ ከዚያ ከተማሪዎቹ ጋር እየተማርኩ ነው የማስተምረው፡፡ የዛሬ አምስት ነው ስድስት ዓመት ገደማ ከዩኒቨርሲቲ ወጣሁ፡፡ ምክንያቱም የተማሪዎቼን ጽሑፍ ማረም ስለሰለቸኝ ነበር፡፡ ከዚያ training and consulting in communication ጀመርኩኝ፡፡ አሁንም የምሠራው ይህንኑ ነው፡፡ ከየትኛውም ተቋም ጋር ግንኙነት የለኝም፡፡ የማስተምረው በአንድ ቦታ ሳይሆን እየተዘዋወርኩ ነው፡፡ ተማሪዎቼን የማሰባስበው በአፍ ማስታወቂያና እርስ በርሱ እየተስማማ ከሚመጣው ነው፡፡
ያለኝ የባችለር ዲግሪ ነው የመጀመሪያ ዲግሪ ብቻ ነገር ግን የድህረ ምረቃ ተማሪዎችንም አስተምር ነበር፡፡ መጀመሪያ በዩኒቨርሲቲው ፕብሊክ ሄልዝ ኮሌጅ ውስጥ ከዚያ ደግሞ ገሽታልት ኢንስቲትዩት (የሳይኮሎጂ) ውስጥ በሳይኮሎጂ ለፒኤችዲ የሚሠሩትንም፣ ሶሻል ወርከሮችንም፣ ሳይካትሪስቶችንም አስተምር ነበር፡፡ አሁንም እንደዚህ ያሉ የግል ተሪማዎች አሉኝ፡፡
የባችለር ዲግሪዬን አዲስ አበባ ሳልጨርሰው ነው የሄድኩት፡፡ አሜሪካ ሄጄ የጨረስኩት Oriental Philosophy and American literature ነው፡፡ እዚህ ዩኒቨርሲቲ ሳልጨርሰው ሳይሆን ዲግሬዬን ሳላገኝ የወጣሁት Literature and western philosophy ነበረ፡፡ የምዕራባውያን ፍልስፍናን ክፍል ውስጥ በመማር ሳይሆን በማንበብ ምናልባት ኮሌጅ ለማስተርስ ከሚሠሩት ጋር እኩል ሳላነብ የቀረሁ አይመስለኝ፡፡ ስላልተፈተንኩበት ሳለማር ልል አልችልም፡፡ እዚያ ብሄድ አዲስ ነገር ካጋጠመኝ ብዬ በአንድ ስምንት ወር ውስጥ ጨረስኳት፡፡
ከሦስት ወር በኋላ እዚያው ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ መልሰው ለማስተማር ቀጠሩኝ፡፡ መጀመሪያ ስቀጠር ሳስተምረው የነበረ ኮርስ ‹‹ሥነ ጥበብና ቴክኖሎጂ›› የሚል የራስ ፈጠራ የሆነ ነበር፡፡ ቴክኖሎጂው እየተሻሻለ ሲሄድ ሥነ ጥበቡን ይለውጠዋል፡፡ ሥነ ጥበቡ ደግሞ እየተሻሻለ ሲሄድ ለቴክኖሎጂው አዲስ መንገድ ይከፍታል፡፡ እና በዓለም ታሪክ ውስጥ ሥነ ጥበብና ቴክኖሎጂ የት የት ቦታ ነው የተገናኙት የሚለውን ማስተማር ጀመርሁ፡፡
የፈረንሳይ ሥነጽሑፍና እኔ
የፈረንሳይን ሥነ ጽሑፍ አነብም አጠናም ነበር፡፡ የደረሱበትን አላውቅም እንጂ በፈረንሣይኛ የጻፍኳቸው፣ ታትመው የወጡም ግጥሞች ነበሩኝ፡፡ አሁን ፈረንሣይኛው እየጠፋ ሄዷል፡፡ የቀሩኝ አማርኛ፣ እንግሊዝኛ ኦሮምኛ ናቸው፡፡ በኦሮምኛ እስካሁን አልጻፍኩም፡፡
በኔ ላይ ተፅዕኖ ያሳደረብኝ የፈረንሳይ ሥነ ጽሑፍ ሳይሆን ፓሪስ መኖሬ ነው፡፡ ፓሪስ ስደርስ 20 ዓመቴ ነበር፡፡ ፓሪስ ነፃ ክፍት ከተማ ስለነበርና ልጅ ስለበርኩ ቁልፉን የከተማው ከንቲባ እንደሰጠኝ ነው ያየሁት፡፡ በኋላ ትልልቅ የሆኑ ጸሐፊዎች፣ የሙዚቃ ሰዎች ሠዓሊዎች ነበሩ፡፡ እንዲያውም ላንድ አቫን ጋርድ የፈረንሣይ ጋለሪ ማንም ሳይሾመኝ ሥዕል አውቃለሁ ብዬ ገብቼ አንድ አማካሪ ሆኜ ያኔ የመረጥኳቸው ሠዓሊዎች አሁን በዓለም የታወቁ አሉ፤ ኢትዮጵያውያን ማለቴ አይደለም፡፡ ዋናው ተፅዕኖ ከነሱ ጋር መዋል መቻሌ ነው፡፡ ከጥቁር አሜሪካዎች ጋርም በጣም በጣም ቅርብ ነበርኩኝ በተለይ ከጃዝ ሙዚቀኞች ጋር፡፡ አሁንም በብዛት የምሰማው ሙዚቃ የኢትዮጵያ፣ ጃዝና ክላሲካል ሙዚቃ ነው፡፡ ከፈረንሣይ ጸሐፊዎች ጋርም ያለ ዕድሜዬና ያለ ዕውቀቴ እኩል ገብቼ ዋልኩኝ፡፡ በማንበብ ሳይሆን አብሮ በመዋል እንዳባቶች ሆነው አሳድገውኛል፡፡ ከፈረንሣይ፣ ከእንግሊዝ ከአሜሪካን ጸሐፊዎች ውስጥ ሪቻርድ ሪይት ለትንሽ አመለጠኝ፡፡ ግን የእሱ ጓደኞች ከሚውሉበት ነበር የምውለው፡፡ እነ ቸስተር ሃየምስ፣ ጀምስ ቦልድዊንና ስማቸውን ከማላስታውሳቸው ጸሐፊዎች ጋር አብሮ መዋል እኔንም ጸሐፊ ያደረገኝ መስሎኝ ነበር፡፡ ያሳደጉኝ እነሱ እንጂ የፈረንሣይ ዩኒቨርሲቲ አይደለም፡፡ በተጨማሪም ፓሪስ ከተማ አለች ከኢትዮጵያውያን ጓደኞቼ ጋር እየዋልኩኝ ወደ ሙዚየም፣ ቤተ መጻሕፍት፣ ቲያትር ቤት፣ ኮንሰርት እሄድ ነበር፡፡ ገንዘብ ብዙ አልነበረበኝም፡፡ በተለይ መጨረሻው ላይ ምንም አልነበረኝም፡፡ ከትሬንታ ላይ ሌሊት ሌሊት አትክልት እያወረድኩ ነበረ የምኖረው፡፡ ግን አንድ ሳንቲም ኪሴ ሳይኖር እንደ ሚሊየነር ልጅ ነው ፓሪስን የኖርኩባት፡፡ ከአዲስ አበባ ቀጥላ የትውልድ ከተማዬ የምትመስለኝ ፓሪስ ነች፡፡

የሥነ ጽሑፍ አቋም
ከብዙ ወጣት ደራስያን ጋር ከዮሐንስ አድማሱ፣ ብርሃኑ ዘርይሁን ጋር የተለየ አቋም ነበረኝ፡፡ ከዮሐንስ ጋር ከሥነ ጽሑፍ ይልቅ የጓደኝነት ግንኙነት ነበረን፡፡ በጣም በጣም አደንቀው የነበረና አሁንም የማደንቀው የአማርኛ ባለቅኔ ብዬ የምገምተው ገብረክርስቶስ ደስታ ነው የተረሳ፡፡ የተረሳ ስል ግጥሞቹ ተሰብስበው በመጽሐፍ መልክ አልወጡም፡፡ ከአቶ መንግሥቱ ለማ ጋርም ጓደኞች ነን፡፡ አንዳንዶቹን ግጥሞቹን በጣም አደንቃቸው ነበር፡፡ እሱ እኔ ላይ ተፅዕኖ ሳይኖረው አይቀርም ብዬ እገምታለሁ፡፡ ምክንያቱም መጻፍ ሳልጀምር ነው የሱን ግጥም እሱ ሲያነብ መስማት የጀመርኩት፡፡ እንዲያውም ልጅነት ውስጥ ‹‹ቱሉዝ ገምቤላ›› የምትል አንድ ግጥም አለች፡፡ እሷ ያለጥርጥር የመንግሥቱ ተፅዕኖ አለባት፡፡
አንዳንድ ጸሐፊዎች ወይም ገጣሚዎች አካባቢያቸው ያለውን የሰው ሕይወት ሆነ፣ የማኅበራዊ ሆነ፣ የመሬት አቀማመጥ፣ ቅጠላ ቅጠሉን ይጽፋሉ፡፡ አንዳንድ ደግሞ ከሐሳብ ነው የሚጽፉት ግብ አላቸው፡፡ ወይ የማስተማር ወይ የመቀስቀስ (እንደ ፉከራ) ወይ ሕይወት ከበደኝ ብሎ እሮሮ የማሰማት ዓለማ አለው፡፡ ሌላው መንገድ የሰው ልጅ ውጪው ብቻ ሳይሆን ውስጡም ሕይወት አለውና የውስጡ ብዙ ጊዜ እውጪ አንፀባርቆ አይታይም፡፡ እኔን በተለይ የሚስበኝ ይኼ ነው፡፡ ነገር ግን ወስኜ ‹‹ጥበብ ለጥበብነቱ ሲባል›› ብዬ ተነስቼ አላውቅም፡፡ ልጅም ሆኜ ወደዚያ ይስበኝ ነበር፡፡ እንዳጋጣሚ በልጅነቴ የመጀመሪያዬን ግጥም 10 ሳንቲም ነበር ሸጥኳት፡፡ ጎረቤታችን የነበረች አንድ ወጣት ሴት ከአንድ ወጣት ጋር ፍቅር ይዟት 10 ሳንቲም ከፍላ እሷ ናት ግጥም ያጻፈችኝ፡፡ የግጥሙም አለመወደድ ይሁን ወይም የሷ የትም አልደረሰም፡፡ እና እሱ ተፅዕኖ አሳደረብኝ፣ ግብ ለማጣት አይለም፡፡ ግብ መጀመሪያ ላይ ወስኜ እንዲህ ይሁን ብዬ አልነበረም የምጽፈው፡፡ ውስጤ ያለውን እንደመጣም ነበር የምጽፈው፡፡
አሁን ደግሞ ለኔ እንደሚመስለኝ ዛሬ የምጽፈው ግጥም ሳየው ግጥሙን አንብቤ የሚለው ሁሉ ዛሬ ካወቅሁት ባይታተም ግዴለኝም፡፡ አሜሪካ እንድ አሥራ ሦስት ግጥሞች አንድ የግጥም መድበል ውስጥ ወጥተዋል፡፡ እንግሊዝ አገርም አንድ ሁለት ወጥተዋል፡፡ ካናዳም ወጥተዋል፡፡ እና እንዳጋጣሚ ወዳጅ አግኝቷቸው ፎቶ ኮፒ ልኮልኝ ሳያቸው ያኔ ምን እንደሆኑ አላውቃቸውም ነበር፡፡ አሁን ነው የምረዳቸው፡፡ አንብቤው ግጥሙ በሙሉ ለራሴ ግልጽ ሆኖ ከታየኝ የትናንትናውን፣ ያለፈውን እንደማወራ መስሎ ስለሚሰማኝ አላስቀምጣቸውም፡፡ ግጥም እንደዚህ መጻፍ ጥሩ አይደለም ማለቴ አይደለም፡፡ እያንዳንዱ አናፂ ሆነ ጸሐፊ የየራሱ ባህርይ ስላለው የኔ ባህርይ ወደ ውጭው አይደለም ማለቴ ነው፡፡ ግብ በሚመለከት ግን እኔ ባልወስነውም ያገኛል፡፡

ጓደኛሞች
ከስብሐት ገብረእግዚአብሔርና ከተስፋዬ ገሰሰ ጋር አብሮ አደጎች ነበርን፤ ዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ፡፡ ውጭ ሁላችንም የራስ የራሳችን ጓደኞች ነበርን፡፡ ሲመሽ ሁላችንም አንድ ሰፈር ነበር የምንሄደው ውቤ በረሃ፡፡ አንዳንዴ አብረን እንሄዳለን እንጂ የውቤ በረሃ ጓደኞቼ እነስብሐት አልነበሩም፡፡ ሦስታችን ስንገናኝ ሥነ ጽሑፍ በብዛት እናነብ ነበር፡፡ ስብሐት ያን ጊዜም ቢሆን ግጥም አልነበረም የሚጽፈው፣ አጫጭር ልቦለዶች ነው፡፡ ተስፋዬ ግጥምም ይሞካክር ነበር፡፡ እኔ ወደ ግጥም ነበር የማደላው፡፡
ስብሐት መጀመሪያ ጽፎ አስደንቆኝ ያየሁት ኤክስ አን ፕሮቫንስ ሆኖ የጻፈውን ነው፡፡ እኔ ፓሪስ ነበርኩ፡፡ ላየው ስለፈለኩ መንገድ ላይ መኪና እየለመንኩ ደረስኩ፡፡ ይች ትኩሳት ተብላ የወጣችው ያኔ ስትጻፍ ነበረች አጀማመሯን አየሁት፡፡ ከዚያ ደግሞ እዚህ መጥቼ በእጅ ተገልብጠው ቀበና በላይ እንግሊዝ ተማሪ ቤት በታች ሲኖር አስነበበኝ፡፡ የኔንም አብረን እናነብ ነበር፡፡ በኋላ ደግሞ እህቴን አገባ፤ ሃና ይልማን፡፡ ከመንገድ ወዲህና ከመንገድ ወዲያ ስለምንኖር ሁልጊዜ ማታ ማታ እንገናኝ ነበር፡፡ ስብሐትና ተስፋዬ በወንድምነትም በጓደኝነትም እንደ ወንድሞቼ የሚቀርቡኝ ናቸው፡፡
ከነገብረክርስቶስ ደስታ፣ መንግሥቱ ለማ፣ ዳኛቸው ወርቁ፣ ዮሐንስ አድማሱ ጋር ያገናኘን ሥነ ጽሑፍ ነው፡፡ ከዚያ ተነስቶ ነው ጓደኞች የሆነው፡፡ ከዮሐንስ ጋር ትንሽ እንዳንቀራረብ ያደረገን የሥነ ሐሳብ መለያየት ሳይሆን ሐረር ሊያስተምር መሄዱ ነው፤ የምንገናኘው ሲመጣ ነበር፡፡ የሚገርመኝ ነገር እኔ የሱን ግጥም ሳነብ በሐሳብ ተለያየን ብዬ አልነበረም የማስበው፤ ‹‹ይኼ ዮሐንስ አድማሱ ነው›› ነው የምለው እሱም አንስቶት በዚህ ስንከራከር አላውቅም፡፡ ሲያነብ ግን ይኼ ሰሎሞን ነው ይላል፡፡ ሳናነብበት መለያየታችንን ተቀብለን የምንናበብ ይመስለኛል፡፡
ገብረክርስቶስ ዊንጌት አብረን ስንማር እሱ ሥዕል ነበር የሚሠራው፤ ጀርመን አገር ሲማርም ሄጄ ጎብኜቸዋለሁ፤ ከእስክንድር ጋር፡፡ መጀመሪያ ግጥም ያነበበልኝ እዚያ ነው፤ ኮለን አጠገብ ይኖር ነበር፡፡ ምንም እንኳ ሥዕሎቹ ቆንጆ ቢሆኑም የሚያስደንቁኝ የአማርኛ ግጥሞቹ ነበሩ፡፡ ከዚያ መጥተን እዚህ ቀጠልን፡፡
ያን ጊዜ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያምም ይጻጽፍ ነበር፤ አሁን ትቶ እንደሆነ አላውቅም፡፡ እሱም አንዱ ባለጠበል ነበር፡፡ ዳኛቸው አይመጣም፡፡ ተጎትቶ ካልሆነ ከሰው አይቀርብም ነበር፡፡ ከኔ ጋር ግን ውጭም ወዳጆች ነበርን፡፡
‹‹ልጅነት›› ታትማ ስትወጣ በመጠኑ ቁጣ ወረደባት፡፡ የኢትዮጵያን የግጥም አወራረድ አበላሽ፤ ከፈረንጅ ያመጣው ነው፤ አንዳንዶቹ ደግሞ ሱሪያሊስቶቹን ገልብጦ ነው ምናምን ይባል ነበር፡፡ የማስታውሰው የምስጋና ጽሑፍ ያገኙሁት ከዳኛቸው ወርቁ ብቻ ነው፡፡ የደረሰኝ የምስጋና ጽሑፍ የቄስ ጽሕፈት ይመስል ነበርና የሱ መሆኑን ያወቅሁት በኋላ ስንቀራረብ ነው፤ አልፈረመባትም ነበር፡፡ እንደ አጋጣሚ ደግሞ እኔ ‹‹አደፍርስ››ን አግኝቼ ሳነብ ‹‹ማነው ልጅነትን የጻፈው?›› ብሎ ሲፈልግ ነው የተገናኘነው፡፡ በጣም በጣም ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ ሳይሆን የትም ቦታ ከማደንቃቸው ጸሐፊዎች ዳኛቸው አንዱ ነው፡፡ በሁሉም ሳይሆን በአደፍርስና በ The Thirteenth Sun:: በአጠቃላይ ግን አንድ ጸሐፊ አንደ ደህና ነገር ከጻፈ በኋላ ሕይወቱ ካልተለወጠ ድግግሞሽ ነው የሚጽፈው፡፡
እነ ዳኛቸው ለአማርኛ ሥነ ጽሑፍ ያደረጉት አስተዋፅኦ ከሁሉ የበለጠ ስታይል (አማርኛ ምን እንደምለው አላውቅም) ይመስለኛል፡፡ ይኸውም የስብሐትን የአማርኛ አጻጻፍ የትም ባየውና ባይፈርምበትም የስብሐት መሆኑን አውቃለሁ፡፡ መጀመሪያ መቅለሏ፣ የአረፍተ ነገሩ ማጠር፣ ቁጭ ብለህ የምትነጋገር ነው የሚመስልህ፡፡ አማርኛ አሁንም ብሶበታል፤ ገመድ ሆኗል፡፡ የዳኛቸው ደግሞ የስብሐት ተቃራኒ የሆነ ነው፡፡ ግን ገመድ አለበትም፡፡ የመንግሥቱ ለማ ሌላው ቢቀር ‹‹ማን ያውቃል›› የምትል ግጥም አለች፡፡
የመስቀል ወፍና የአደይ አበባ
ቀጠሮ እንዳላቸው መስከረም ሲጠባ
ማን ያውቃል?
የምትል፡፡
አንድ ጸሐፊ ሁልጊዜ ተነባ የምትታወስና የሰውን መንፈስ ፍላጎት የምትቀሰቅስ ከጻፈ ዕድለኛ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ እና የመንግሥቱ ለማ ይኼ ግጥም አለ፤ ሌሎችም አሉት፡፡ ትያትሮችም አሉ፡፡ መንግሥቱ ለማ ፌዘኛና ተሰጥኦ ነበረው፡፡ ሌላ እንደሱ ተሰጥኦ የነበረውም አቶ ነጋሽ ገብረማርያም ነው፤ አሁንም ይጽፍ እንደሆነ አላውቅም፡፡ በጣም ለማሳቅ ስጦታ ያለው፡፡
እስክንድር አሁን በቅርብ ‹‹Ethiopian Birr›› በሚል መጽሔት አንድ ረዘም ያለ ድርሰት ስለሱ በእንግሊዝኛ ጽፌ ነበር፡፡ ያው እዚያ ያልኩትን ነው የምደግመው፡፡ እስክንድር በኢትዮጵያ ሥነ ሥዕል ውስጥ የተለየ ቦታ ያለው ይመስለኛል፡፡ የተለየ ቦታ ያለው ስል ከሌሎቹ ሁሉ ይልቃል ለማለት ሳይሆን ጨክኖ መንገድ ክፍቷል ብዬ ነው የምገምተው፡፡ መንገድ ሲከፍት ደግሞ ፓሪስና ሎንደን አሥር ዓመት ከተማረ በኋላ (እውነቱን ለመናገር አልተማረም ከሠዓሊዎች ጋር በመዋል፤ ሙዚየሙም ውስጥ ጊዜ ከማሳለፍ፣ ከማጠንጠን ተነስቶ) ከፈረንጆቹ ተፈናቅሎ ወደ አፍሪካ ትራዲሽን በጠቅላላው፣ በተለይ ደግሞ የምዕራብ አፍሪካ ቅርፆች ተፅዕኖ አሳደሩበት፡፡ የነ ኤምስጋርቱቶላ ጽሑፍ ተፅዕኖ አሳደረበት፡፡ ከዚያ ተላቆ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ፡፡ ወደ ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ1966 እንደገና መንገድ ለመለወጥ በጣም ዝግጁ ሆኖ መጣ፡፡ መጥቶ የአክሱምን፣ የጎንደርን፣ የላሊበላን፣ የወላይታ ቅርፃ ቅርፆችን፣ ኦሮሞ መቃብር ላይ የሚቆሙትን፣ ሐረር ዋሻ ውስጥ ያሉትን አየና አንድ ጊዜ ጭንቅላጹን በረገደው፡፡ ተመልሶ ያንን ሊሠራ ሲችል ተላቀቀና ወደዚህ ዞረ፡፡ አሁን የኢትዮጵያን ሥዕሎች ዞሬ አላሁም እንጂ ለብዙ ጊዜ ተፅዕኖው ይታይ ነበር፡፡ አንዳንዶቹ ሰንፈው ነው፡፡ ባትሰንፍም የአንዳንድ ሰው ሥዕል አንድ ጊዜ ካየኸው አይለቅህም፡፡ የእስክንድር ሥዕሎች ሲታዩ አዲስ ነገር ይመስላሉ፤ ደግመህ ስታየው አብረኸው ያደግኸው ይመስላል፡፡ የኢትዮጵያን ሥዕሎች ጥንት የነበሩት ጎንደር ደብረብረሃን ሥላሴ ያሉት ሥዕሎች የሚያስደንቁ ናቸው፡፡ ከዚያ ወዲህ ጨክኖ ዓይኑን ወደዚህ ዞር ያደረገና ታይቶት የሠራ ነው፡፡ በቅርብ ካሉት ውስጥ በጣም የማደንቀው ሠዓሊ እሱ ነው፡፡ ይልቃል አይደለም አደንቀዋለሁ ነው የምለው፡፡

Friday, September 15, 2017

‹‹መጽሐፈ ጨዋታ›› ከነማብራሪያው ታተመ

30 Aug, 2017

ከ150 ዓመታት በፊት በአለቃ ዘነብ የተጻፈው ‹‹መጽሐፍ ጨዋታ›› ከማብራሪያና ከቃላት መፍቻ ጋር ታተመ፡፡
የኅትመት ብርሃኑን ነሐሴ 22 ቀን 2009 ዓ.ም. ያየው አዲሱ እትም የአለቃ ዘነብን የሕይወት ታሪክ፣ የድርሰቱን ይዘት፣ የመረጃ ምንጮች፣ የቃላት መፍቻና የጨዋታ ማጣቀሻዎችን  በ79 ገጾች ይዟል፡፡  
አፄ ቴዎድሮስ ዘመን በ1856 ዓ.ም. የተጻፈው መጽሐፈ ጨዋታ፣     ‹‹ውብ የአማርኛ ወግ መጽሐፍ ነው›› ይለዋል አንድምታ መጻሕፍት፡፡ ከወጉ ለዓይነት በመጽሐፉ የጀርባ ሽፋን እንዲህ አሥፍሯል፡፡
‹‹ገበሬ በቅልጥሙ ቅባቱን ይዞት ይኖራል፡፡ ገና ኋላ ለቁርበቱ ማልፊያ ይሆነኛል ብሎ ነውን? ያዳምም ልጆች እንደዚሁ ለተዝካራቸው ያኖራሉ፡፡ ምነው ዓይናቸው ሲያይ ቢሰጡት ይኰነኑ ይሆን?››
በአንድምታ መጻሕፍት አዘጋጅነትና አሳታሚነት የቀረበው መጽሐፈ ጨዋታ፣   ቀደም ባሉት 75 ዓመታት ውስጥ በተለያዩ አሳታሚዎች ‹‹መጽሐፍ ጨዋታ ሥጋዊ ወመንፈሳዊ›› በሚል መጠርያ መታተሙ ይታወቃል፡፡
አዲሱ ‹‹መጽሐፈ ጨዋታ›› ዋጋው ሃምሳ ብር ነው፡፡

ሰኞ የሚብተው የኢትዮጵያ 2010 እና 2018 ዘመን

08 Sep, 2017

በኢትዮጵያ  ዘመን አቈጣጠር/ ባሕረ ሐሳብ መሠረት 2010 ዓመተ ምሕረትና 7510 ዓመተ ዓለም በፀሐይ አቆጣጠር፣ 2018 በፀሐይና በጨረቃ ጥምር አቆጣጠር ሰኞ፣ መስከረም 1 ንጋት 12 ሰዓት ላይ ይገባል፡፡ ባህሉንና ትውፊቱን የሚጠብቀው የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት እንደሁሌው በዕለቱ በአዲስ አበባ ንጋት 12 ሰዓት ላይ ዘመኑ መለወጡን 12 ጊዜ መድፍ በመተኮስ እንደሚያበስር ይጠበቃል፡፡ (እኩለ ሌሊት ላይ የሚለወጥ የኢትዮጵያ ዘመን እንደሌለን ልብ ይሏል)::
እንደ ኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊትም ከዘመነ ማቴዎስ (2009) ወደ ዘመነ ማርቆስ (2010)፣ ዕለተ ዮሐንስ በሚባለው መስከረም 1 ቀን ሽግግር ይደረጋል፡፡ ሌሊቱ 16 በጨረቃም መስከረም 20 ቀን 2018 ዓ.ም.፣ እንደ ኢትዮጵያ እስልምና ትውፊትም ዕለቱ በዙልኻጅ 19 ቀን 1438 ዓመተ ሒጅራ፣ እንደ ኢትዮጵያ አይሁድ (ቤተ እስራኤል) ትውፊትም በኢሉል 20 ቀን 5777 ዓመተ ፍጥረት አዲሱ ዓመት ገብቷል፡፡
በኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ መሠረት የፀሐይ ዓመት ሰኞ ይግባ እንጂ ዓመቷን በ354 ቀናት የምትፈጽመው የኢትዮጵያ የጨረቃ አዲስ ዓመት ‹‹መስከረም 1 ቀን›› የገባው ጳጉሜን 3 ቀን 2009 ዓ.ም. ነበር፡፡ በ2010 ዓ.ም. ፋሲካ መጋቢት 30 ቀን የሚከበረው፣ የአይሁድ አዲስ ዓመት ሮሽ ሃሻናኅ (በዓለ መጥቅዕ) መስከረም 11 ቀን የሚከበረው፣ የኢስላም ኢድ አል ፈጥር፣ ኢድ አል አድሃ (አረፋ) እና መውሊድ የሚከበሩት ከዓመተ ሒጅራም ከኢትዮጵያ የጨረቃ አዲስ ዓመት በመነሣት መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ሁሉም የኢትዮጵያ አቆጣጠር ነው፡፡ ባሕረ ሐሳባችን በፀሐይ (Solar)፣ በጨረቃና በፀሐይ (Luni-solar) እና በጨረቃ (Lunar) የሚቆጥር የሁሉንም አብርሃማውያንና ሌሎች ሃይማኖቶች አቈጣጠር የያዘ ነው፡፡
ዐደይ አበባ
የኢትዮጵያ አዲስ ዓመት መስከረም ባተ፡፡ ሰኔ ግም ብሎ የሐምሌን ጨለማ አልፎ፣ ዕኝኝ ብላን (ከነሐሴ 28 ቀን እስከ 30 ባለማቋረጥ የሚዘንበው) ጎርፍ በጳጉሜን በኩል ክረምቱ ሲሻገር፣ መስከረምን የምታደምቀው ዐደይ አበባ ትከሰታለች፡፡ በመስከረም የምትፈነዳውና ለኢትዮጵያ ምድር ጌጧ ሽልማቷም የሆነችው ዐደይ አበባ እንደ አለቃ ደስታ ተክለወልድ ‹‹ዐዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት›› ዐደይ ሲፈታ የበጨጨ፣ ብጫ የሆነ አበባ ነው፡፡ ግሱ ‹‹ዐደየ›› በጨጨ፣ ብጫ መሰለ፤ ነጣ፣ ነጭ ሆነ ሲሉም ይፈቱታል፡፡ በኦሮምኛ ነጭን ዐዲ፣ ፀሐይን ዐዱ የሚለው ከዚህ የወጣ ነው ሲሉም ያክሉበታል፡፡
ስለዐደይ አበባ ተክል ምንነት ሳይንሳዊ መግለጫ ያዘጋጁት  ከበደ ታደሰ (ዶ/ር) ‹‹የኢትዮጵያ ወፍ ዘራሽ አበቦች (Wild Flowers for Ethiopia) በተሰኘው መጽሐፋቸው፣ ስለዐደይ አበባ ከምትበቅልበት ከተለያዩ ከፍታዎች አንፃር በሁለት መልክ እንዲህ ጽፈዋል፡፡   
የተከፋፈሉ ሰፊ ላይዶ ቅጠሎችና ስምንት የተበተኑ መልካበቦች ያሉት ዓመታዊ ሃመልማል፣ ከመንገድ ዳር ዳርና ከቃሊም እንዲሁም በከፍተኛና ድንጋያማ ተዳፋት፣ ከ400 እስከ 2,700 ሜትር ከፍታ ላይ ይበቅላል፤ ከመስከረም እስከ ታኅሣሥም ያብባል፡፡ በሌላ በኩልም እስከ ኅዳር ድረስ የሚያብበው የሚገኘው ከ2,000 እስከ 3,600 ሜትር ከፍታ ላይ ነው፡፡ ይህንንም ዶ/ር ከበደ ሲገልጹት፣ ዐደይ አበባ ረጃጅም ግንድና ሰፋ ያለ ላይዶ ቅርጽ ያላቸው ቅጠሎች ያሉት ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ የሚበቅል ከረም ሃመልማል ነው ይሉታል፡፡ መሀላቸው ብርቱካንማ የሆነ ብጫ አበቦች በግንዱ ጫፍ ሰብሰብ ብለው ይታያል፡፡
ድሮ ድሮ ‹‹ዐደይ ዐደይ የመስከረም፤ ሱስንዮስ ንጉሠ ሮም›› ይባል ነበር፡፡ ‹‹ዐደይ ዐደይ የመስከረም፤ እንዳንቺ ያለ የለም››ም ተብሏል፡፡ ‹‹መስከረም መስከረም የወራቱ ጌታ፤ አበቦች ተመኙ ካንተ ጋር ጨዋታ›› እየተባለም ድሮ በመጀመሪያ ደረጃ ተማሪ ቤት ተማሪዎች ሲዘምሩ እንደነበር መጽሐፋቸው ይናገራል፡፡
ከ55 ዓመታት በፊት በ1955 ዓ.ም. የዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ በአዲስ አበባ ራዲዮ ጣቢያ ስለ ዘመናት መለወጥ ወይም የታሪክ ዘይቤ ዲስኩር ያሰሙት የፍልስፍና፣ የታሪክና የነገረ ኢትዮጵያ ምሁሩ እጓለ ገብረዮሐንስ (ዶ/ር) መቋጫ ያደረጉት በምክራዊ ሐሳብ ነበር፡፡
እንዲህ ይነበባል፡- ‹‹በዘመን መለወጫ በዓል አሮጌው አልፎ አዲስ ሲተካ የክረምት ጭለማ አልፎ ብርሃን ሲመጣ ሁሉም በተውሳከ መብልዕ ወመስቴ [መብልና መጠጥ በመጨመር] እየተደሰተ ከአንዱ ዘመን ወደሌላው መሻገሩን በሚያከብርበት ዕለት ትንሽ ጊዜ አስተርፎ ስለጠቅላላው የሕይወት ጉዞ ለሚያስበው ረድኤት ይሆን ዘንድ፣ ለማያስበው ደግሞ እንዲያስብ ምክንያት ይሆን ዘንድ፣ እሊህን ሐሳቦች ለማቅረብ ደፈርን፡፡ የዚያ ሰው ይበለን እንጂ ለከርሞ በተሻለ ለማቅረብ እያሰብን ለሰሚዎቻችን መልካም በዓል እንመኛለን፡፡››

ሁለት ሺሕ አሥር እንዴት ገባ? በ‹‹ኢትዮጵያ ቀን›› ኢትዮጵያ በማታውቀው ከሌሊቱ 6 ሰዓት አዲሱ ዓመት ‹‹ገባ›› ተብሏል

  • በ‹‹ኢትዮጵያ ቀን›› ኢትዮጵያ በማታውቀው ከሌሊቱ 6 ሰዓት አዲሱ ዓመት ‹‹ገባ›› ተብሏል
  • በሚሌኒየም ስሌት መደነጋገሩ ቀጥሏል
  • https://www.ethiopianreporter.com
 13 Sep, 2017 (3/1/10)
በሔኖክ ያሬድ
‹‹መስከረም ጠባ፡፡ የመስከረም ጮራ ዕንቁጣጣሽ ብላ ተግ አለች፡፡ ልጃገረዶች ሳዱላቸውን አሳመሩ፡፡ አደስ ተቀቡ፡፡ እንሶስላ ሞቁ፡፡ ወንዝ ወረዱ፡፡ ቄጤማ ለቀሙ፡፡ ፀአዳ ልብሳቸውን ለብሰው፣ አሽንክታባቸውን አጥልቀው፣ ‹አበባዬ ሆይ - ለምለም› በማለት ተሰብስበው ብቅ አሉ - እንደ ጮራይቱ፡፡ የወርሀ መስከረም ብሩህ ተስፋና ስሜት በምድሪቱ አስተጋባ፡፡ ጠፍ እያለ መጣ ምድሩ፡፡ ወንዙም እየጠራ፡፡ ኩል መሰለ ሰማዩ፡፡ ሜዳው፣ ጋራው፣ ሸንተረሩ ወርቃማ የአደይ አበባ ካባ ለበሰ፡፡ ደመራ ተደመረ፡፡ ተቀጣጠለ ችቦ፡፡ ‹ኢዮሃ አበባዬ - መስከረም ጠባዬ› ተባለ፡፡››
ይህ ሥዕላዊ ሐተታ ደራሲው በዓሉ ግርማ ከ38 ዓመት በፊት፣ በ1972 ዓ.ም. ባሳተመው ‹‹ደራሲው›› በተሰኘው ልቦለዱ የመስከረምን ድባብ የገለፀበት ነበር፡፡ አዲሱ ዓመት በመጣ ቁጥር  የሚታወስ ነው፡፡
የዘንድሮውን 2010 ዓመት አቀባበል ከወትሮው የተለየ ነበር፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ከነሐሴ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዋዜማው ጳጉሜን 5 ቀን ድረስ በልዩ ልዩ ስያሜዎችና መሪ ቃላት ተከብሮ አልፏል፡፡ በቅድሚያ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት ነን›› የሚል መሪ ቃል የነበረውና መጨረሻ ላይ  ‹‹መጪው ዘመን ለኢትዮጵያ ከፍታ ነው›› በሚል የተከበረው ‹‹የኢትዮጵያ ቀን›› የአሠርቱ ቀናት ማሠሪያ መቋጫ ነበር፡፡
ዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ የባህል ድርጅት)  ልዩ ስለሆነው የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር፣ አዲሱ ዓመት ዘመን የሚለወጥበት ንጋት 12 ሰዓት ላይ እንጂ እንደ ምዕራባውያን እኩለ ሌሊት (6 ሰዓት) ስላለመሆኑ፣ ያመቱ መነሻ መስከረም 1 ቅዱስ ዮሐንስ- ዕለተ ዮሐንስ መባሉንና ሌሎች የቀመር ጓዞችን የያዘውን ጥንታዊ የባሕረ ሐሳብ ብራናን (መጽሐፍ) በዓለም ጽሑፍ ቅርስነት ለመመዝገብ በሚመክርበት ጊዜ ላይ ተደርሶ፣ ሚዲያዎችና የሚመለከታቸው አካላት ያለዕውቀት ቅርሱንና ውርሱን እየጣሉት ይገኛሉ፡፡
ከኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ ጋር የማይተዋወቁት፣ እኩለ ሌሊት ላይ ‹‹አዲስ ዓመት ገባ›› እያሉ ማደናገራቸውን ዓመት ዓመት መቀጠላቸውን ሃይ የሚልም ጠፍቷል፡፡ አዲሱን 2010 ዓ.ም. ለመቀበል በዋዜማው ጳጉሜን 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚሌኒየም አዳራሽ የኢትዮጵያ ቀንና የአሥሩ ቀናት አከባበር ማጠቃለያ ጭምር ሲከበር፣ ከባሕረ ሐሳብ ጋር የማይተዋወቁት ‹‹አርቲስቶቹ›› እኩለ ሌሊት ላይ አዲሱ ዓመት ያለ ዕውቀት በድፍረት ‹‹ገባ›› ብለዋል፡፡ ርችትም ተተኩሷል፡፡ እነርሱን የተከተለው በአዲስ አበባ በሚገኝ አንድ የሬዲዮ ጣቢያም ‹‹የራሷን የቀን አቆጣጠር የምትከተለው ኢትዮጵያ፣ የ2010 አዲስ ዓመቷን እኩለ ለሊት 6:00 ሰዓት ላይ ተቀብላለች፤›› ብሎ በድምፅም በጽሑፍም አስፍሮታል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አዲሱ ዓመት የሚገባው የገባው ማለዳ 12 ሰዓት መሆኑን ለማብሰር እንደሁሌው 21 ጊዜ መድፉን ተኩሷል፡፡
የሚሌኒየሙ ነገር
ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ የ2010 ዓ.ም. አዲስ ዓመት አቀባበልን አስመልክቶ በዋዜማው ጳጉሜን 5 ቀን በብሔራዊ ቤተመንግሥት መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ፣ ኢትዮጵያ ‹‹ሁለተኛውን ሚሌኒየም ከተቀበለች 10 ዓመት›› እንደሆናት ሲገልጹ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሚሌኒየም አዳራሽ በዋዜማው በተዘጋጀው መሰናዶ ዓመቱ በሦስተኛው የኢትዮጵያ ሚሌኒየም ላይ እንደሚገኝ እንዲህ አውስተዋል፡፡
‹‹ሦስተኛው ሚሌኒየም ከተጀመረ አሥረኛ ዓመት ለሆነው የዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል እንኳን አደረሳችሁ››፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ሦስተኛው ሚሌኒየም ከገባበት 2000 ዓ.ም. ጀምሮ…›› ብለው 10 ዓመት 2009 ዓ.ም. እንዳበቃ ተናግረዋል፡፡ ሦስቱም ርዕሰ ብሔሩና ርዕሰ መስተዳድሩ ከሚኒስትሩ ጋር ሦስት ዓይነት መረጃዎችን አስተላልፈዋል፡፡  ነገር ግን ከኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ አንፃር ትክክሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አገላለጽ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ያመለከቱት ሁለተኛው የኢትዮጵያ ሚሌኒየም የገባው ግን በ1001 ዓ.ም. ከአንድ ሺሕ ዓመት በፊት ነበር፡፡
ትንሣኤ ያገኘው የእንግጫ ነቀላና የከሴ አጨዳ
እንግጫ የሣር ዓይነት ነው፡፡ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ልጃገረዶች መስክ ወርደው የሚነቅሉት ነው፡፡ የእንቁጣጣሽ ብሥራት ነጋሪ ነው፡፡ በዘመን መለወጫ ዋዜማ እንግጫ ሳር በልጆች እየተነቀለ እንደቋጨራ እየተጎነጎነ ጣራ ላይ ተወርውሮ ያድርና ጠዋት ላይ ለዘመን መለወጫ እየተጎነጎነ ራስ ላይ፣ ቡሃቃ አንገት ላይና ሌማት ክዳን ላይ ይታሰራል፡፡ ቡሃቃ እና ሌማት ላይ የመታሰሩ ምልክትነት ለረድኤትና ለበረከት ሲባል የሚደረግ ነው፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባሳተመው ‹‹በሰሜን ሸዋ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች የተመዘገቡ የኢንታጀብል ባህላዊ ቅርሶች›› መድበል ላይ እንደተገለጸው፣ እንግጫ ነቀላ ዘመን ሲለወጥ የሚከወን ባህላዊ ሥራት ነው፡፡ በዋዜማው ያላገቡ ሴቶች ወደ መስክ ወርደው እንግጫ ይቆርጣሉ፡፡ ምሽቱን ደግሞ እንግጫውን ሲጎነጉኑ ይቆያሉ፡፡ ሲነጋ ደግሞ በጠዋት ተጠራርተው በመሰባሰብ በየሰው ቤት እየዞሩ የተጎነጎነው እንግጫ ከቤቱ ምሰሶ ላይ ያስራሉ፡፡
እስከ ዓምና ድረስ በከተሞች አካባቢ እንግጫ ነቀላው እየቀረ አበባዮሽ የሚለው ጨዋታ በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ የጎጃም ኅብረተሰብ ነባሩ ትውፊት በከተሞች ቀረብን፣ ተረት ሊሆንብን ነው የሚለው አባባል የሚቀይር ድርጊት በ2010 ዓ.ም. ዋዜማ አስተናግደዋል፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አማካይነት ነባሩ የእንግጫ ነቀላና የከሴ አጨዳ የልጃገረዶች ባህላዊ ክዋኔ  በደብረ ማርቆስ ከተማ በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አደባባይ ጳጉሜን 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በታላቅ ሥነ ሥርዓት አከናውነዋል፡፡
የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ውድ ዓለም አልማው፣ በዞኑ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ቢኖሩም ጠብቆና ተንከባክቦ ለትውልድ ከማስተላለፍ ረገድ ውስንነት እንዳለ አመልክተዋል፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ ብለው የጠቀሱት ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ የሚከበረው የእንግጫ ነቀላና የከሴ አጨዳ ባህል ከጥቂት የገጠር ቀበሌዎች በስተቀር እየተረሳ መምጣቱን ነው።
እንደሳቸው አገላለጽ፣ የእንግጫ ለቀማና የከሴ አጨዳ ክዋኔዎች እስከ መስከረም አንድ ድረስ ጎረምሶችና ልጃገረዶች ተሰባስበው ልዩ ልዩ ዘፈኖችን በመዝፈን በየቤቱ እየተዘዋወሩ ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልክት የሚያስተላልፉባቸው ናቸው። ኢዜአ በዘገበው ገለፃቸውም፣ እንግጫ ለቀማ በወንድ ወጣቶች የሚከወን ሲሆን፣ ከሴ ደግሞ በልጃገረዶች ታጭዶ ከአደይ አበባ ጋር አብሮ ተጎንጉኖ በጭፈራ ታጅቦ ለኅብረተሰቡ የሚሰጥበት ክዋኔ ነው።
የአዲስ ዓመት የምሥራች ምልክት የሆነው እንግጫ ነቀላው በዜማ የሚታጀብ ነው፡፡ 
‹‹እቴ አበባዬ ነሽ
አደይ ተክለሻል
አደይ ተቀምጠሻል
ባሶና ሊበን
አዋጋው ብለሻል
ቦሶና ሊበን
ምነው ማዋጋትሽ
አንዱ አይበቃም ወይ››
በዚህ ጊዜ ወንዶች ደግሞ ያዘጋጁትን ዳቦት (የችቦ ስም) በእሳት ለኩሰው እያበሩ በመምጣት እንግጫ ለሚጎነጉኑት ሴቶች ያበሩላቸዋል፡፡ ዳቦታቸውን እያበሩ ወደ ሴቶቹ በሚያመሩበት ጊዜ የሚያዜሙት ዜማ አላቸው፡፡
‹‹ኢዮሃ ኢዮሃ
የቅዱስ ዮሐንስ
የመስቀል የመስቀል
አሰፉልኝ ሱሪ
ኢዮሃ›› በማለት ያዜማሉ፡፡
ልጃገረዶቹ ወደየሰው ቤት ሲሄዱ ሎሚ ይሰጣቸው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን የእንግጫው ሴቶች ራሳቸው ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› እያሉ ሎሚ ሲሰጡ ገንዘብ ይሰጣቸዋል ይላል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን መድበል፡፡
የዘመን አዋጅ
መስከረም አንድ ቀን ያለው ልዩ ነገር የዘመኑን መለወጥ አስመልክቶ የባሕረ ሐሳብ አዋጁ ይነገራል፡፡ በዓመቱ ውስጥ በዓል የሚውልበት፣ ጾም የሚገባባትን ቀን መምህራኑ እያሰሉ ይናገሩታል፡፡ ዓመቱን በፀሐይና በጨረቃ፣ በዓመተ ዓለም ለምዕመናኑ ይገልጹታል፡፡ ማህሌቱ ካበቃ በኋላ መምህሩ ካባ ደርቦ መስቀል ይዞ ዘመኑን ያውጃል፣ የባሕረ ሐሳቡን ጥንተ ታሪክ ይናገራል፡፡ የዘንድሮው አዲስ ዓመት 2010 ዓ.ም.  በአራት ዓመቱ የሚመላለሰውና ‹‹ዐውደ ጳጉሜን››/ ‹‹ዐውደ ወንጌላውያን›› የሚባለው ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡  2010 ለ4 ተካፍሎ 502 ደርሶ ቀሪው 2 መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዘመኑ የማርቆስ መሆኑ ያመለክታል፡፡ (1 ከቀረ ማቴዎስ፣ 3 ከቀረ ሉቃስ፣ እኩል ከሆነ ዮሐንስ ይሆናል፡፡ ዘንድሮ የዓለም ፍጥረት መነሻ በሆነው በዓመተ ዓለም ሲቆጠር 7510 ዓመተ ዓለም መሆኑና ስምንተኛው ሺሕ ከገባ 509 ዓመት ማለፉንና 510ኛ ዓመት ላይ መገኘቱን ስሌቱ ያሳያል፡፡
እንቁጣጣሽ በምን ወቅት ላይ ትገኛለች?
መስከረም 1 በክረምት ውስጥ የምትገኝ ያመት መነሻ ናት፡፡ ሰኔ 26 ቀን የገባው ክረምት የሚወጣው መስከረም 25 ቀን ላይ ነው፡፡ የስድስተኛው ምታመት የነገረ መለኮት ሊቁ (ቲኦሎጊያን)፣ መዝሙረኛውና ዜማ ቀማሪው ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፈ ድጓው ‹‹ኀለፈ ክረምቱ ጸገዩ ጽጌያት ቆመ በረከት!›› - ክረምቱ አለፈ አበቦችም ፈኩ፣ በረከትም ቆመ ይለናል፡፡
የዛሬው ቀን መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በክረምት ውስጥ ይገኛል፡፡  እንደ ቅዱስ ያሬድ አመዳደብ፣ በውስጡም ልዩ ልዩ ንኡሳን ክፍሎች አሉት፡፡ ከነሱም መካከል የነሐሴ መጨረሻና የጳጉሜን ሳምንት ‹‹ጎሕ፣ ጽባሕ››- ወጋገን፣ ንጋት ይለዋል፡፡ ይህም ያዲስ ዘመን መስከረም የሚጠባበት ጊዜ መድረሱን አመላካች ነው፡፡
ሌላው ንኡስ ክፍል ከዓመት አውራ መነሻ (ርእሰ ዐውደ ዓመት) መስከረም 1 ቀን እስከ መስከረም 7 (8) ቀን ያለው ‹‹ዮሐንስ›› ሲባል፣ ከመስከረም 9 እስከ 15 ዘመነ ፍሬ ይባላል፡፡ ‹‹ዮሐንስ›› የሚለው ቃል የተወሰደው በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ከሚገኘውና ኢየሱስ ክርስቶስን ካጠመቀው የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ ነው፡፡
መስከረም 1 ቀን ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕለተ ዮሐንስ መባሉ በተምሳሌታዊ ፍች የመጣ ነው፡፡ ከአሮጌው ብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን፣ ወደ ዓመተ ምሕረት መሸጋገሪያ ላይ የመጣው መንገድ ጠራጊው ዮሐንስ ስለሆነ፤ ባህሉ/ ትውፊቱ ካሮጌው ዓመት ወዳዲሱ መሸጋገሪያዋን ዕለት፣ መስከረም 1 ቀንን በዘይቤ ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› ‹‹ዕለተ ዮሐንስ›› እያለ ይጠራዋል፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ ባገልግሎት ላይ ይገኛል፡፡ ዩኔስኮ የባሕረ ሐሳባችሁን ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› አውቄዋለሁ፣ አክብሬዋለሁ ሲል እዚህ ግን ቦታ እያጣ ነው፡፡

ሁለት ሺሕ አሥር እንዴት ገባ? በ‹‹ኢትዮጵያ ቀን›› ኢትዮጵያ በማታውቀው ከሌሊቱ 6 ሰዓት አዲሱ ዓመት ‹‹ገባ›› ተብሏል

  • በ‹‹ኢትዮጵያ ቀን›› ኢትዮጵያ በማታውቀው ከሌሊቱ 6 ሰዓት አዲሱ ዓመት ‹‹ገባ›› ተብሏል
  • በሚሌኒየም ስሌት መደነጋገሩ ቀጥሏል
  • https://www.ethiopianreporter.com
 13 Sep, 2017 (3/1/10)
በሔኖክ ያሬድ
‹‹መስከረም ጠባ፡፡ የመስከረም ጮራ ዕንቁጣጣሽ ብላ ተግ አለች፡፡ ልጃገረዶች ሳዱላቸውን አሳመሩ፡፡ አደስ ተቀቡ፡፡ እንሶስላ ሞቁ፡፡ ወንዝ ወረዱ፡፡ ቄጤማ ለቀሙ፡፡ ፀአዳ ልብሳቸውን ለብሰው፣ አሽንክታባቸውን አጥልቀው፣ ‹አበባዬ ሆይ - ለምለም› በማለት ተሰብስበው ብቅ አሉ - እንደ ጮራይቱ፡፡ የወርሀ መስከረም ብሩህ ተስፋና ስሜት በምድሪቱ አስተጋባ፡፡ ጠፍ እያለ መጣ ምድሩ፡፡ ወንዙም እየጠራ፡፡ ኩል መሰለ ሰማዩ፡፡ ሜዳው፣ ጋራው፣ ሸንተረሩ ወርቃማ የአደይ አበባ ካባ ለበሰ፡፡ ደመራ ተደመረ፡፡ ተቀጣጠለ ችቦ፡፡ ‹ኢዮሃ አበባዬ - መስከረም ጠባዬ› ተባለ፡፡››
ይህ ሥዕላዊ ሐተታ ደራሲው በዓሉ ግርማ ከ38 ዓመት በፊት፣ በ1972 ዓ.ም. ባሳተመው ‹‹ደራሲው›› በተሰኘው ልቦለዱ የመስከረምን ድባብ የገለፀበት ነበር፡፡ አዲሱ ዓመት በመጣ ቁጥር  የሚታወስ ነው፡፡
የዘንድሮውን 2010 ዓመት አቀባበል ከወትሮው የተለየ ነበር፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ከነሐሴ 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ዋዜማው ጳጉሜን 5 ቀን ድረስ በልዩ ልዩ ስያሜዎችና መሪ ቃላት ተከብሮ አልፏል፡፡ በቅድሚያ ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን የጥቁር ሕዝቦች ተምሳሌት ነን›› የሚል መሪ ቃል የነበረውና መጨረሻ ላይ  ‹‹መጪው ዘመን ለኢትዮጵያ ከፍታ ነው›› በሚል የተከበረው ‹‹የኢትዮጵያ ቀን›› የአሠርቱ ቀናት ማሠሪያ መቋጫ ነበር፡፡
ዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስ የባህል ድርጅት)  ልዩ ስለሆነው የኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር፣ አዲሱ ዓመት ዘመን የሚለወጥበት ንጋት 12 ሰዓት ላይ እንጂ እንደ ምዕራባውያን እኩለ ሌሊት (6 ሰዓት) ስላለመሆኑ፣ ያመቱ መነሻ መስከረም 1 ቅዱስ ዮሐንስ- ዕለተ ዮሐንስ መባሉንና ሌሎች የቀመር ጓዞችን የያዘውን ጥንታዊ የባሕረ ሐሳብ ብራናን (መጽሐፍ) በዓለም ጽሑፍ ቅርስነት ለመመዝገብ በሚመክርበት ጊዜ ላይ ተደርሶ፣ ሚዲያዎችና የሚመለከታቸው አካላት ያለዕውቀት ቅርሱንና ውርሱን እየጣሉት ይገኛሉ፡፡
ከኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ ጋር የማይተዋወቁት፣ እኩለ ሌሊት ላይ ‹‹አዲስ ዓመት ገባ›› እያሉ ማደናገራቸውን ዓመት ዓመት መቀጠላቸውን ሃይ የሚልም ጠፍቷል፡፡ አዲሱን 2010 ዓ.ም. ለመቀበል በዋዜማው ጳጉሜን 5 ቀን 2009 ዓ.ም. በሚሌኒየም አዳራሽ የኢትዮጵያ ቀንና የአሥሩ ቀናት አከባበር ማጠቃለያ ጭምር ሲከበር፣ ከባሕረ ሐሳብ ጋር የማይተዋወቁት ‹‹አርቲስቶቹ›› እኩለ ሌሊት ላይ አዲሱ ዓመት ያለ ዕውቀት በድፍረት ‹‹ገባ›› ብለዋል፡፡ ርችትም ተተኩሷል፡፡ እነርሱን የተከተለው በአዲስ አበባ በሚገኝ አንድ የሬዲዮ ጣቢያም ‹‹የራሷን የቀን አቆጣጠር የምትከተለው ኢትዮጵያ፣ የ2010 አዲስ ዓመቷን እኩለ ለሊት 6:00 ሰዓት ላይ ተቀብላለች፤›› ብሎ በድምፅም በጽሑፍም አስፍሮታል፡፡ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አዲሱ ዓመት የሚገባው የገባው ማለዳ 12 ሰዓት መሆኑን ለማብሰር እንደሁሌው 21 ጊዜ መድፉን ተኩሷል፡፡
የሚሌኒየሙ ነገር
ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ የ2010 ዓ.ም. አዲስ ዓመት አቀባበልን አስመልክቶ በዋዜማው ጳጉሜን 5 ቀን በብሔራዊ ቤተመንግሥት መልዕክታቸውን ሲያስተላልፉ፣ ኢትዮጵያ ‹‹ሁለተኛውን ሚሌኒየም ከተቀበለች 10 ዓመት›› እንደሆናት ሲገልጹ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ በሚሌኒየም አዳራሽ በዋዜማው በተዘጋጀው መሰናዶ ዓመቱ በሦስተኛው የኢትዮጵያ ሚሌኒየም ላይ እንደሚገኝ እንዲህ አውስተዋል፡፡
‹‹ሦስተኛው ሚሌኒየም ከተጀመረ አሥረኛ ዓመት ለሆነው የዘንድሮው የዘመን መለወጫ በዓል እንኳን አደረሳችሁ››፡፡ የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ኃላፊ ሚኒስትር ነገሪ ሌንጮ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ‹‹ሦስተኛው ሚሌኒየም ከገባበት 2000 ዓ.ም. ጀምሮ…›› ብለው 10 ዓመት 2009 ዓ.ም. እንዳበቃ ተናግረዋል፡፡ ሦስቱም ርዕሰ ብሔሩና ርዕሰ መስተዳድሩ ከሚኒስትሩ ጋር ሦስት ዓይነት መረጃዎችን አስተላልፈዋል፡፡  ነገር ግን ከኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ አንፃር ትክክሉ የጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አገላለጽ ነው፡፡ ፕሬዚዳንቱ ያመለከቱት ሁለተኛው የኢትዮጵያ ሚሌኒየም የገባው ግን በ1001 ዓ.ም. ከአንድ ሺሕ ዓመት በፊት ነበር፡፡

ትንሣኤ ያገኘው የእንግጫ ነቀላና የከሴ አጨዳ
እንግጫ የሣር ዓይነት ነው፡፡ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ልጃገረዶች መስክ ወርደው የሚነቅሉት ነው፡፡ የእንቁጣጣሽ ብሥራት ነጋሪ ነው፡፡ በዘመን መለወጫ ዋዜማ እንግጫ ሳር በልጆች እየተነቀለ እንደቋጨራ እየተጎነጎነ ጣራ ላይ ተወርውሮ ያድርና ጠዋት ላይ ለዘመን መለወጫ እየተጎነጎነ ራስ ላይ፣ ቡሃቃ አንገት ላይና ሌማት ክዳን ላይ ይታሰራል፡፡ ቡሃቃ እና ሌማት ላይ የመታሰሩ ምልክትነት ለረድኤትና ለበረከት ሲባል የሚደረግ ነው፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባሳተመው ‹‹በሰሜን ሸዋ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች የተመዘገቡ የኢንታጀብል ባህላዊ ቅርሶች›› መድበል ላይ እንደተገለጸው፣ እንግጫ ነቀላ ዘመን ሲለወጥ የሚከወን ባህላዊ ሥራት ነው፡፡ በዋዜማው ያላገቡ ሴቶች ወደ መስክ ወርደው እንግጫ ይቆርጣሉ፡፡ ምሽቱን ደግሞ እንግጫውን ሲጎነጉኑ ይቆያሉ፡፡ ሲነጋ ደግሞ በጠዋት ተጠራርተው በመሰባሰብ በየሰው ቤት እየዞሩ የተጎነጎነው እንግጫ ከቤቱ ምሰሶ ላይ ያስራሉ፡፡
እስከ ዓምና ድረስ በከተሞች አካባቢ እንግጫ ነቀላው እየቀረ አበባዮሽ የሚለው ጨዋታ በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ የጎጃም ኅብረተሰብ ነባሩ ትውፊት በከተሞች ቀረብን፣ ተረት ሊሆንብን ነው የሚለው አባባል የሚቀይር ድርጊት በ2010 ዓ.ም. ዋዜማ አስተናግደዋል፡፡
በምሥራቅ ጎጃም ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ አማካይነት ነባሩ የእንግጫ ነቀላና የከሴ አጨዳ የልጃገረዶች ባህላዊ ክዋኔ  በደብረ ማርቆስ ከተማ በንጉሥ ተክለ ሃይማኖት አደባባይ ጳጉሜን 4 ቀን 2009 ዓ.ም. በታላቅ ሥነ ሥርዓት አከናውነዋል፡፡
የዞኑ ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ ውድ ዓለም አልማው፣ በዞኑ በርካታ የሚዳሰሱና የማይዳሰሱ ቅርሶች ቢኖሩም ጠብቆና ተንከባክቦ ለትውልድ ከማስተላለፍ ረገድ ውስንነት እንዳለ አመልክተዋል፡፡ ለዚህም አንዱ ማሳያ ብለው የጠቀሱት ከነሐሴ አጋማሽ ጀምሮ የሚከበረው የእንግጫ ነቀላና የከሴ አጨዳ ባህል ከጥቂት የገጠር ቀበሌዎች በስተቀር እየተረሳ መምጣቱን ነው።
እንደሳቸው አገላለጽ፣ የእንግጫ ለቀማና የከሴ አጨዳ ክዋኔዎች እስከ መስከረም አንድ ድረስ ጎረምሶችና ልጃገረዶች ተሰባስበው ልዩ ልዩ ዘፈኖችን በመዝፈን በየቤቱ እየተዘዋወሩ ለአዲሱ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልክት የሚያስተላልፉባቸው ናቸው። ኢዜአ በዘገበው ገለፃቸውም፣ እንግጫ ለቀማ በወንድ ወጣቶች የሚከወን ሲሆን፣ ከሴ ደግሞ በልጃገረዶች ታጭዶ ከአደይ አበባ ጋር አብሮ ተጎንጉኖ በጭፈራ ታጅቦ ለኅብረተሰቡ የሚሰጥበት ክዋኔ ነው።
የአዲስ ዓመት የምሥራች ምልክት የሆነው እንግጫ ነቀላው በዜማ የሚታጀብ ነው፡፡ 
‹‹እቴ አበባዬ ነሽ
አደይ ተክለሻል
አደይ ተቀምጠሻል
ባሶና ሊበን
አዋጋው ብለሻል
ቦሶና ሊበን
ምነው ማዋጋትሽ
አንዱ አይበቃም ወይ››
በዚህ ጊዜ ወንዶች ደግሞ ያዘጋጁትን ዳቦት (የችቦ ስም) በእሳት ለኩሰው እያበሩ በመምጣት እንግጫ ለሚጎነጉኑት ሴቶች ያበሩላቸዋል፡፡ ዳቦታቸውን እያበሩ ወደ ሴቶቹ በሚያመሩበት ጊዜ የሚያዜሙት ዜማ አላቸው፡፡
‹‹ኢዮሃ ኢዮሃ
የቅዱስ ዮሐንስ
የመስቀል የመስቀል
አሰፉልኝ ሱሪ
ኢዮሃ›› በማለት ያዜማሉ፡፡
ልጃገረዶቹ ወደየሰው ቤት ሲሄዱ ሎሚ ይሰጣቸው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን የእንግጫው ሴቶች ራሳቸው ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› እያሉ ሎሚ ሲሰጡ ገንዘብ ይሰጣቸዋል ይላል የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን መድበል፡፡
የዘመን አዋጅ
መስከረም አንድ ቀን ያለው ልዩ ነገር የዘመኑን መለወጥ አስመልክቶ የባሕረ ሐሳብ አዋጁ ይነገራል፡፡ በዓመቱ ውስጥ በዓል የሚውልበት፣ ጾም የሚገባባትን ቀን መምህራኑ እያሰሉ ይናገሩታል፡፡ ዓመቱን በፀሐይና በጨረቃ፣ በዓመተ ዓለም ለምዕመናኑ ይገልጹታል፡፡ ማህሌቱ ካበቃ በኋላ መምህሩ ካባ ደርቦ መስቀል ይዞ ዘመኑን ያውጃል፣ የባሕረ ሐሳቡን ጥንተ ታሪክ ይናገራል፡፡ የዘንድሮው አዲስ ዓመት 2010 ዓ.ም.  በአራት ዓመቱ የሚመላለሰውና ‹‹ዐውደ ጳጉሜን››/ ‹‹ዐውደ ወንጌላውያን›› የሚባለው ሁለተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡  2010 ለ4 ተካፍሎ 502 ደርሶ ቀሪው 2 መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዘመኑ የማርቆስ መሆኑ ያመለክታል፡፡ (1 ከቀረ ማቴዎስ፣ 3 ከቀረ ሉቃስ፣ እኩል ከሆነ ዮሐንስ ይሆናል፡፡ ዘንድሮ የዓለም ፍጥረት መነሻ በሆነው በዓመተ ዓለም ሲቆጠር 7510 ዓመተ ዓለም መሆኑና ስምንተኛው ሺሕ ከገባ 509 ዓመት ማለፉንና 510ኛ ዓመት ላይ መገኘቱን ስሌቱ ያሳያል፡፡
እንቁጣጣሽ በምን ወቅት ላይ ትገኛለች?
መስከረም 1 በክረምት ውስጥ የምትገኝ ያመት መነሻ ናት፡፡ ሰኔ 26 ቀን የገባው ክረምት የሚወጣው መስከረም 25 ቀን ላይ ነው፡፡ የስድስተኛው ምታመት የነገረ መለኮት ሊቁ (ቲኦሎጊያን)፣ መዝሙረኛውና ዜማ ቀማሪው ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፈ ድጓው ‹‹ኀለፈ ክረምቱ ጸገዩ ጽጌያት ቆመ በረከት!›› - ክረምቱ አለፈ አበቦችም ፈኩ፣ በረከትም ቆመ ይለናል፡፡
የዛሬው ቀን መስከረም 3 ቀን 2010 ዓ.ም. በክረምት ውስጥ ይገኛል፡፡  እንደ ቅዱስ ያሬድ አመዳደብ፣ በውስጡም ልዩ ልዩ ንኡሳን ክፍሎች አሉት፡፡ ከነሱም መካከል የነሐሴ መጨረሻና የጳጉሜን ሳምንት ‹‹ጎሕ፣ ጽባሕ››- ወጋገን፣ ንጋት ይለዋል፡፡ ይህም ያዲስ ዘመን መስከረም የሚጠባበት ጊዜ መድረሱን አመላካች ነው፡፡
ሌላው ንኡስ ክፍል ከዓመት አውራ መነሻ (ርእሰ ዐውደ ዓመት) መስከረም 1 ቀን እስከ መስከረም 7 (8) ቀን ያለው ‹‹ዮሐንስ›› ሲባል፣ ከመስከረም 9 እስከ 15 ዘመነ ፍሬ ይባላል፡፡ ‹‹ዮሐንስ›› የሚለው ቃል የተወሰደው በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ከሚገኘውና ኢየሱስ ክርስቶስን ካጠመቀው የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ ነው፡፡
መስከረም 1 ቀን ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕለተ ዮሐንስ መባሉ በተምሳሌታዊ ፍች የመጣ ነው፡፡ ከአሮጌው ብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን፣ ወደ ዓመተ ምሕረት መሸጋገሪያ ላይ የመጣው መንገድ ጠራጊው ዮሐንስ ስለሆነ፤ ባህሉ/ ትውፊቱ ካሮጌው ዓመት ወዳዲሱ መሸጋገሪያዋን ዕለት፣ መስከረም 1 ቀንን በዘይቤ ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› ‹‹ዕለተ ዮሐንስ›› እያለ ይጠራዋል፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ ባገልግሎት ላይ ይገኛል፡፡ ዩኔስኮ የባሕረ ሐሳባችሁን ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› አውቄዋለሁ፣ አክብሬዋለሁ ሲል እዚህ ግን ቦታ እያጣ ነው፡፡

መስከረም 5- የኢትዮጵያ ንጉሥ [1501-1533] ልብነ ድንግል አረፈ

በዚችም ቀን (መስከረም 5) እግዚአብሔርን የሚወድ፣ ሃይማኖቱ የቀና ደግ ጻድቅ የኢትዮጵያ ንጉሥ [1501-1533] ልብነ ድንግል አረፈ። በረከቱ ከኛ ጋራ ትኑር ለዘላለሙ አሜን።
 ስንክሳር ዘመስከረም ፭።
- On this day also is commemorated Lebna Dengel, or Dawit (David) II Wanag Sagad,
King of Ethiopia from Aug. 15, 1508, to Sept. 2, 1540. [Julian Calendar]
Glory be to God Who is glorified in His Saints. Amen.

Friday, July 21, 2017

ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴና የአፍሪካ አንድነትበሔኖክ ያሬድ
‹‹ሐምሌ ሐምሌ ሐምሌ 16 ተወለደ ጠቅል›› ከ42 ዓመታት በፊት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ልደት አስመልክቶ የሚዜም ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት ከብሔራዊ በዓላት አንዱ ሆኖ መሥሪያ ቤቶች ሁሉ ዝግ የሚሆኑበት ንጉሠ ነገሥቱ በሐረርጌ ኤጀርሳ ጎሮ ሐምሌ 16 ቀን መወለዳቸውን በማመልከት ነበር፡፡
ለስድስት አሠርታት ግድም (ከ1909 እስከ 1967 ዓ.ም.) ከአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንንነት እስከ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴነት ኢትዮጵያን የመሩት አፄ ኃይለ ሥላሴ በአፍሪካ አንድነት መሥራችነትና አባትነትም ይታወቃሉ፡፡ ከ16 ዓመታት በፊት አፍሪካ አንድነት ድርጅትን (አአድ) የተካው የአፍሪካ ኅብረት በቅርቡ ባካሄደው 29ኛው የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ በሚገኘው የኅብረቱ ጽሕፈት ቤት ሐውልታቸው እንዲቆም መወሰኑ ይታወሳል፡፡  
ከዓመታት በፊት የጋናው ፕሬዚዳንት ለነበሩት ክዋሜ ንኩሩማ ብቻ ሐውልት መቆሙ በተለያዩ መልክ ትችት ሲቀርብበት የነበረው ኅብረቱ ለተነሳበት ጥያቄ ዘንድሮ ምላሹን ሰጥቷል፡፡  
‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባት››
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (ቀኃሥ) በ1955 ዓ.ም. የአአድ መሥራችና አባቱም የሆኑለት ከድርጅቱ ዋናዎቹ አንቀሳቃሾች አንዱ እንደነበሩ ምስክርነት የሰጠው የጋናው ዘጋኔያን ታይምስ በጁላይ 24፣ 1972 (ሐምሌ 17 ቀን 19614 ዓ.ም.) ዕትሙ ነበር፡፡
የናይጄሪያው ሳንዴይ ኦብዘርቨር ቀኃሥ 80ኛ ዓመታቸውን ባከበሩበት ሐምሌ 16 ቀን 1964 ዓ.ም. (ጁላይ 23፣ 1972) ባወጣው ዕትሙ ‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅት አባት ኢትዮጵያዊው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ›› (Haile Selassie I of Ethiopia: Father of The O.A.U.) በሚል ርዕስ ሐተታ አውጥቶ ነበር፡፡
እንደ ሰንዴይ ኦብዘርቨር አገላለጽ፣ ቀኃሥ ስለ አፍሪካ ያላቸው ውጥን እጅግ በጣም የተዋጣና የተቃና መሆኑን ጠቅሶ፣ አዲስ አበባ ‹‹የፓን አፍሪካን መዲና›› (የአፍሪካ አንድነት ከተማ) ለመባል የበቃችበትን ምክንያት አስታውሶ ነበር፡፡
‹‹የዚህ ምክንያት አስቀድሞ የአፍሪካ አገሮች በሞላ የተገኙበትና እንዲሁም ጊዜያዊ ጽሕፈት ቤት ለማቋቋም ውሳኔ የተላለፈበት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መልካም ፈቃድ በ1955 ዓ.ም. የተያዘው አዲስ አበባ ላይ ስለነበር ነው፡፡ ከዚህም በላይ በይበልጥ ጠቃሚ የሆነው ኢትዮጵያ የእንግሊዝኛን ወይም የፈረንሣይኛን ቋንቋ ዓይነተኛ አድርጋ አለመውሰዷ ነው፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ከአፍሪካ ውስጥ እጅግ ረዥም የሆነ የነፃነት ዘመናት ያላት አገር ናት፡፡ እንዲሁም ደግሞ ከአፍሪካ አንድነት ድርጅት በፊት የአፍሪካ ኤኮኖሚክ ኮሚሽን አዲስ አበባ ውስጥ ተቋቀሞ ነበር፡፡ ዳሩ ግን በራሴ አስተያየት ንጉሠ ነገሥት የመናገሻ ከተማቸው የአፍሪካ አንድነት ከተማ እንድትሆን ባይተጉበት ኖሮ እነዚህ የተዘረዘሩት ጉዳዮቸ ምንም ለውጥ ባላስከተሉም ነበር፡፡
‹‹የአፍሪካ አንድነት ድርጅትም የአፍሪካ ኃይሎች ራሳቸውን ለመከላከል ይተባበሩ ዘንድ ግርማዊ ጃንሆይ ባላቸው እምነት መሠረት ፈቃዳቸውን ከግቡ ማድረሳቸው የሚያስደንቅ ነው፡፡ በዚህም እምነት መሠረት፣ በየትኛም የአህጉሩ ክፍል አምባጓሮ ቢነሳ ተገቢው ስምምነት እንዲፈጸም ግርማዊነታቸው ዓይነተኛ መድኅን ሆነዋል፡፡ በዚህም መሠረት የናይጄሪያ ችግር በተፈጠረበት ጊዜ የአስታራቂነት ዕርምጃ የወሰዱ ሲሆን ይህም ፍጻሜ እንዳገኘ በችግሩ ምክንያት አለመግባባት የተፈጠረባቸውን አፍሪካውያን መሪዎችን ፈጥነው ለማስማማት ችለዋል፡፡ ከዚህ በስተቀር ጃንሆይ ከዓለም አብያተ ክርስቲያናት ድርጅት ጋር በመተባበር የወጠኑት ከባድ ሥራ 16 ዓመታት የፈጀውን የሱዳንን ችግር በማስወገድ በቅርቡ አንድ ታሪካዊ ስምምንት እንዲፈጸም አስችሏል፡፡
ግርማዊነታቸው ሴኔጋልና ጊኒ አለመግባባታቸውን ለማስወገድ በተስማሙበት ይኸውም በላይቤሪያ ዋና ከተማ በሞንሮቪያ ውስጥ በተደረገው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ስብሰባ ሊቀ መንበር ሆነው መርተዋል፡፡ በዚህ መሠረት ግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቀደም ሲል ጀምሮ የታሪክ ሥፍራቸውን መያዛቸው ጉልህ ነው፡፡
‹‹በውጩም ዓለም ቢሆን አፍሪካ ግንባራቸው ሳይታጠፍ ከአውሮፓ፣ ከአሜሪካና ከእስያ መሪዎች ጋር ለመቋቋም የሚችሉ ከፍተኛ መሪዎች ያላት መሆኑን ግርማዊ ጃንሆይ በሚገባ አስመስክረዋል፡፡ ይልቁንም የግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መፈጠር፣ ቀደም ብለው እንደነበሩት እንደቸርችል፣ ኔህሩ፣ ቶማስ ጀፈረሰንና እንደሌኒንን ሁሉ የሰውን ልጅ ዕድል ለማሳደግ የረዳ መሆኑ አሁን ጃንሆይን ሊያረካ የሚችል ነው፡፡
ኢትዮጵያ በዓለም ጋዜጦች በሚል ርዕስ በእንግሊዝኛ፣ ፈረንሣይኛና ጣሊያንኛ በግርማዊ ንጉሠ ነገሥት ልዩ ካቢኔ ፕሬስ ክፍል ከ1957 እስከ 1966 ዓ.ም. ይታተም የነበረው መጽሔት የቀኃሥን ተግባሮች መዘከሩ ይታወቃል፡፡ አንዱ የጠቀሰው ለንደን ታይምስ (The Times London) በጁላይ 22፣ 1972 (ሐምሌ 15 ቀን 1965 ዓ.ም.) ዕትሙ፣ ‹‹የንጉሠ ነገሥቱ ጽኑ ሥልጣን በአፍሪካ መሪዎች ዘንድ ታፋሪነትን አትርፎላቸዋል›› (Emperor’s firm authority earns respect among the Leaders of Africa) በሚል ርዕስ ሐተታውን አስፍሮ ነበር፡፡
‹‹ኢትዮጵያን ከግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሰውነትና ክብር ጋር የተያያዘ በአፍሪካ ውስጥ ከሁሉም ልቆ የሚገኝ አቋም አላት፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ የአፍሪካ መሪዎች ተቀዳሚ መሪ ብቻ ሳይሆኑ ኢትዮጵያን ከኢጣሊያውያን ወራሪዎች ነፃ ለማውጣት ያደረጉት ተጋድሎም የዘመናዊቷን አፍሪካ ልደት የሚያበስር ነው፡፡ አዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫ እንድትሆን ተመርጣለች፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ኢትዮጵያ ስለአፍሪካ ሕዝብ የፖለቲካ ደኅንነት ላላት ተቆርቋሪነት ጉልህ ምልክት ነው፡፡ ድርጅቱ የተቃቋመውም በድንገት ከተፈጠረ ስሜት አልነበረም፡፡ ንጉሠ ነገሥቱ በእርጋታና አንዳንድ ጊዜም በግላቸው የአፍሪካ አገሮች ገና ነፃነታቸውን ሳይጎናጸፉ የወደፊት መሪዎች ለሚሆኑት ሰዎች የትምህርትን ዕድል በመስጠት ረድተዋል፡፡ ግርማዊነታቸው በአፍሪካ አህጉር ያላቸው ተሰሚነት አገራቸው ከድንበሮቿ ውጭ ካላት ተሰሚነት የተገኘ ሳይሆን ንጉሠ ነገሥቱ ካተረፉት የመከበር ዕድል ነው፡፡
‹‹የብሔራዊና የኢንተርናስዮናል መሪ መሆን ጥቅም ሊኖረው ይችላል፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሊቀመንበርነት በየዓመቱ የሚለወጥ ነው፤ ነገር ግን የፈረስ ኮቴ በሚመስለው የጉባዔ ጠረጴዛ አባል አገሮች ሲቀመጡ የኢትዮጵያ ሥፍራ ከጠረጴዛው ጫፍ በመጀመሪያ ላይ ሲሆን፤ ንጉሠ ነገሥቱም በጉባዔዎቹ ሁሉ በሰፊው ይሳተፋሉ፡፡ በሰሜንና ደቡብ ሱዳን ግዛቶች መካከል ለብዙ ዓመታት የቆየውን ግጭት ከፍጻሜ ለማድረስ በቅርቡ ለተደረገው የሰላም ንግግር የተመረጠችው አዲስ አበባ ነበረች፡፡
‹‹በአብዛኛው የአፍሪካ ክፍል የጎረቤት አገሮች ግንኙነቶች ውስብስብ ከሆነ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ለኡጋንዳ፣ ኬንያና ታንዛኒያ የጋራ አገልግሎት የሚውለው በእንግሊዝ አስተዳደር የተጀመረው የምሥራቅ አፍሪካ ኮሚኒቲ አንዱ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሁኔታ ደግሞ ከዚሁ የተለየ ራሱን የቻለ ነው፡፡
‹‹እንደዚሁም ኢትዮጵያ በአፍሪካ ፖለቲካ የተከፋፈሉ ሁለት ወገኖች ከሆኑት የእንግሊዝኛና የፈረንሣይኛ ተናጋሪ አገሮች ከቶውንም ወገን ለይታ አባል ሆና ስለማታውቅም ከሌሎቹ የምትለይበት ራሱን የቻለ አቋም አላት፡፡ ስለዚህም ኢትዮጵያ በማንኛውም አከራካሪ ጉዳይ ገለልተኛነቷን ጠብቃ መሸምገል ትችላለች፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በአዲስ አበባ የሆነበትም ምክንያት የአገሪቱ ከማንኛውም ወገን ነፃ የሆነ ይዞታ ነው፡፡
‹‹ንጉሠ ነገሥቱ በአፍሪካ የፖለቲካ ንቅናቄ ግንባር ቀደም ሆነው እንዳሉ ናቸው፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ባለፉት አሥር ዓመታት [ከ1955 እስከ 1965 ዓ.ም.] በሚገባ ከመርዳታቸውም በስተቀር በአፍሪካ የቀረውን የአውሮፓውያን የቅኝ አገዛዝ ርዝራዥ በተለይም የፖርቱጋልን የአፍሪካ አገሮች ቅኚ ገዥነት በጥብቅ ተቃውመዋል፡፡
ከ45 ዓመት በፊት ለፊጋሮ-ፓሪስ (Le Figaro-Paris) የተሰኘ የፈረንሣይ ጋዜጣ በፈረንሣይኛ በነሐሴ 1 ቀን 1964 ዓ.ም. (8 Aout, 1972) ዕትሙ ‹‹ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሰማንያኛ የልደት በዓላቸውን ያከብራሉ›› (Hailé Sélassié, Vient de fêter ses 80 ans.) በሚለው ርዕሱ መንደርደርያ ያደረገው እንዲህ ነበር፡፡
 ‹‹ትልቁ አንበሳ ደስ ስላለው አገሳ፡፡ ጠባቂው ልዩ የተቆረጠ ሙዳ ሥጋ በአሉሚኒዬ ሣህን አመጣለት፣ ግርማዊ ጃንሆይ ከዚህ አንድ አንዱን እያነሱ ሰጡት፡፡ ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቀጥለው በእጆቻቸው ጎፈሩን ደባበሱት፡፡ የፊታቸው ገጽ ብሩህ ነው፡፡ አንበሳውን ተናግረውት ድምፃቸውን አሰሙት፡፡ በመጨረሻም ግርማዊነታቸው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትራቸው መለስ ብለው አጭር መሪ ቃል ነገሯቸው፡፡
‹‹ግርማዊ ጃንሆይ፣ እነዚህ አንበሶች በቤተ መንግሥትዎ መዝናኛ አትክልቶች ውስጥ፣ የግርማዊነትዎ በሆኑ አርማዎች ውስጥ፣ ለክብር ዘበኞች እንደ መልካም ዕድል፣ ለብሔራዊ የአየር መንገድ ኩባንያ ደግሞ ሕያው ማስታወቂያ እየሆኑ በኢትዮጵያ ውስጥ በየቦታው እንዲህ የሚታዩበት ምሳሌ ትርጉሙ ምንድር ነው?
-    እንደሚያስረዳውም ድል አድራጊ አንበሳ የአገራችን አምሳል የነፃነት ምስያ ነው፡፡››