28 Dec, 2016 By ሔኖክ ያሬድ   Comments

ለገድለኛው (ሌጀንድ) ኢትዮጵያዊ ሯጭ ምሩፅ ይፍጠር፣ ባረፈበት የካናዳዋ ቶሮንቶ ከተማ፣ ትናንት ማክሰኞ ታኅሣሥ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ጸሎተ ፍትሐት ተደረገለት፡፡ ‹‹ይፍጠር ዘሺፍተር›› (ማርሽ ቀያሪው ምሩፅ ይፍጠር)፣ ‹‹ይፍጠር ዘማስተር›› (የሩጫ ጌታው ምሩፅ ይፍጠር) በመባል የዐቢይ አድናቆት ባለቤት ለነበረው ምሩፅ ይፍጠር ጸሎተ ፍትሐቱ የተደረገው፣ በቶሮንቶ በምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን ሲቢሲ ኒውስ በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ካህናትና ምዕመናን መገኘታቸው ታውቋል፡፡ በ1972 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1980) በሞስኮ ኦሊምፒክ ሁለት ወርቆችን በ10ሺሕና በ5ሺሕ ሜትር፣ በ1964 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1972) በሙኒክ ኦሊምፒክ በ10ሺሕ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያሸነፈው ምሩፅ ይፍጠር በሳምባ ጽኑ በሽታ በ72 ዓመቱ ያረፈው ታኅሣሥ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. መሆኑ ይታወሳል፡፡ የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ምሩፅ አስክሬን፣ በዚህ ሳምንት አዲስ አበባ እንደሚገባና ሥርዓተ ቀብሩም ከተለያዩ አካላት ተውጣጥቶ በተቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት በክብር እንደሚፈጸም ይጠበቃል፡፡ በዐሥራ ሦስት ዓመታት የሩጫ ሕይወቱ ከመካከለኛ ርቀት ማለትም ከ1,500 ሜትር እስከ ረዥም ርቀት (5,000 እና 10,000 ሜትር)፣ እንዲሁም ግማሽ ማራቶንን ጨምሮ ባሉት ርቀቶች በመወዳደርና ከ250 በላይ ተሳትፎ በማድረግ በአንደኛነት ያጠናቀቀው ምሩፅ ይፍጠር፣ ከኦሊምፒክ ድርብ ድሎቹ በተጨማሪ አህጉሮች በሚካፈሉበት የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫ በ1969 እና በ1971 ዓ.ም. በ5,000 እና በ10,000 ሜትር ለአፍሪካ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች ማስገኘቱ ይታወቃል፡፡