በ1950ዎቹ መጨረሻ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ በአውሮፓና በአሜሪካ መቀጣጠል ሲጀምር ግንባር ቀደም ከነበሩት መካከል ይገኙበታል፡፡ በ1960 ዓ.ም. በአገር ቤት ውስጥ በነበረው የንጉሠ ነገሥት መንግሥቱን ሥርዓት በመቃወም አድማ የመቱ ተማሪዎች በታሠሩበትና በተፈረደባቸው ጊዜ፣ የእነርሱን ሁኔታ በአሜሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስታወቅና እንዲፈቱም ለማድረግ በተወሰደው በዋሽንግተን የሚገኘውና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከተቆጣጠሩት ተማሪዎች አንዱ ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰር ዓለም ሀብቱ፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር በሰሜን አሜሪካ (ኢሳና) ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር ዓለም፣ በመጋቢት 1961 ዓ.ም. ተማሪዎች የኢትዮጵያን ኤምባሲ እንዲቆጣጠሩና በወቅቱ ሚሊተሪ አታሼ የነበሩትን ጄኔራል ተፈሪ በንቲን ‹‹በተጨቆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም›› ለተወሰነ ጊዜ በቁም እስር እንዲውሉ ያደረጉትን ተማሪዎች ከፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ጋር በመሆን መርተዋል፡፡
‹‹The Ethiopian Student Movement (ESM): My Experiences in ESUNA, 1964-1971›› በሚለው ወረቀታቸው እንደገለጹት፣ በፊላዴልፊያ ከተማ በነሐሴ 1961 ዓ.ም. በተካሄደው የኢሱና ጉባኤ በአገሪቱ ያሉትን ችግሮች የተመለከቱት ‹‹The Problem of Regionalism in Ethiopia›› በሚል ነበር፡፡ ዋለልኝ መኰንን ‹‹The Question of Nationalities›› (የብሔረሰቦች ጥያቄ) የሚለውን ወረቀቱን ከማውጣቱ ሦስት ወራት በፊት ነበር የአካባቢ/ክልል (ሪጅንስ) ጉዳይ የሚመለከተው ጽሑፍ የወጣው፡፡
ፕሮፌሰር ዓለም ከአምስት ወራት በፊት ለአውስትራሊያው ኤስቢኤስ ሬዲዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ የጽሑፉ ይዘት የሚያመለክተው ‹‹ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ሪጅንስ አላት፣ በእነሱ መካከል ያሉትን ልዩነቶች ገዥ መደቦች እየተጠቀሙ ሕዝቡን ከፋፍለው ይገዙ ነበር፤ በፀረ ፊውዳልና ፀረ ኢምፔሪያሊዝም አቋም መሠረት ኢትዮጵያውያን ለአንድ ሕዝብ መሠረታዊ ለውጥ እንዲታገሉ ነበር፡፡››
እነ ፕሮፌሰር አንድርያስ፣ መለሰ አያሌውና ሐጎስ ገብረ ሕይወትም ያራመዱት ይኼ ሐሳብ ከዋለልኝ መኰንን ሐሳብ የተለየ ነበር፡፡
‹‹በዚያን ጊዜ እኛ የተጠቀምነው ቃል ሪጅናሊዝም ነበር እንጂ ናሽናል ኮስችን አልነበረም፡፡ ናሽናል ኮስችን በማርክሲስት ሌኒኒስት መስመር ሲታይ ነው፤ በዚያ መስመር አላየነውም፤›› ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ የኤርትራ ብቻ ሳይሆን በአሁን ጊዜ ብሔር ብሔረሰብ የሚባለው ጥያቄ መጀመርያ የተነሳው ከሪጂናሊዝም አንፃር ያቀረቡት ከ48 ዓመታት በፊት ነበር፡፡
ፕሮፌሰር ዓለም ሪጅናሊዝም የሚመለከተውን ጽሑፍ ያዘጋጁት የኢትዮጵያን ኤምባሲ ለሁለተኛ ጊዜ በሐምሌ 1961 ዓ.ም. ንጉሡ አሜሪካን በጎበኙበት አጋጣሚ ስምንት ሆነው በተቆጣጠሩበትና ለእስር በተዳረጉት አጋጣሚ ነበር፡፡
‹‹ስለአገራችን በቂ ዕውቀት የለንም፡፡ የሌላ አገር ታሪክና ቲየሪ ብቻ ሳይሆን የራሳችን ታሪክና መማር አለብን፤›› በማለት ይመሩት በነበረው የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበር የብሔረሰቦች ጥያቄ ወደፊት የመራውና ዋና ጥያቄ እንዲሆን ያደረገው፣ በማኅበሩ ውስጥ የተማሪው ማኅበር ሳያውቃቸው በነበሩ በኅቡዕ የተቋቋሙ የፖለቲካ ድርጅቶች አማካይነት ነበር፡፡ ይህን አቋም እሳቸውና ጓደኞቻቸው ባለመደገፋቸው የሐሳብ ልዩነት መፈጠሩን ተመልክቷል፡፡
የ1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አብዮት መፈንዳት ተከትሎ በሐምሌ ወር በአቶ ተክለጻድቅ መኩሪያ የሚመራው የሕገ መንግሥት ኮሚሽን ያረቀቀው ሕገ መንግሥት፣ ኢትዮጵያን በሕገ መንግሥታዊ ዘውድ ሥርዓት እንደ እንግሊዝና ስዊድን የሚያደርገው በወቅቱ በጣም መደገፍ እንደነበረበት ያምኑ የነበሩት ፕሮፌሰር ዓለም፣ ተማሪውም ተራማጁም ለተለያዩ አማራጮች በቂ ትኩረት ባለመስጠታቸው ከመጀመርያውኑ ተጨናግፎ ወታደሩ ሥልጣን እንዲይዝ አድርጎታል፣ አገሪቱ ለጉዳትም መዳረጓን ያምኑ ነበር፡፡
በኢሱና ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ውስጥ ለአምስት ዓመታት (ከ1957 ዓ.ም.-1962 ዓ.ም.) በመጀመርያ በረዳት ዋና ጸሐፊነት (1957-1959 ዓ.ም.) ቀጥሎም በፕሬዚዳንትነት (1959-1960)፣ እንዲሁም የማኅበሩ ልሳን በነበረው ቻሌንጅ (Challenge) ዋና አዘጋጅነት (1960-1962) ያገለገሉት ፕሮፌሰር ዓለም፣ ባለፉት የትግል ዘመናት መለስ ብለው የተመለከቱትን በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፡፡
‹‹ያጠፋነውም ያለማነውም ይኖራል፡፡ አቅማችን በፈቀደ ግን የተማሪው ንቃተ ኅሊናም ከፍ እንዲል ማኅበራዊ እሴቶች እንዲኖሩ ጥረት አድርገን ነበር፡፡ ሁላችንንም ባይመለከትም ግን ከኛ በኋላ የመጣው የሰሜን አሜሪካ ተማሪዎች ማኅበር የተማሪን ሚና ከአቅሙ በላይ አድርጎ አይቶ፣ ተማሪ በትጥቅ ትግል ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብሎ ለብዙ ጥፋቶችና ስህተቶች ተዳርጓል፡፡ ‹‹የተማሪው ንቅናቄ በሙሉ በአንድ በኩል እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ላለው አጀንዳ ያዘጋጀ ይመስላል፡፡ ለደጉም ለክፉም የተማሪዎች ንቅናቄ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ላይ ትልቅ ምልክት ትቶ ነው የሚያልፈው፡፡››
ፋሺስት ኢጣሊያ በ1933 ዓ.ም. ድል ከተመታ በኋላ በነበሩት ተከታታይ ትውልዶች ለውጥ ለማምጣት ለየት ያለ ትግል ያደረገው የ1950ዎቹ ትውልድ እንደሆነ እምነት ነበራቸው፡፡ ‹‹የኛ ትውልድ ነው ለውጥ ለማምጣት የታገለው፡፡ እኔ ‹ሥር ነቀል› የሚለውን ቃል አልወድም፡፡ ምክንያቱም ሥር ውስጥ አንዳንድ በጎም መጥፎም ነገሮች አሉ፡፡ ሁለቱን ሳይለዩ ሥር መንቀል ታጥቦ ጭቃ ሊሆንም ይችላል፤›› የሚልም አተያይ ነበራቸው፡፡
ከ1966 ዓ.ም. አብዮት ወዲህ የኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበራዊ እሴቶች እያጡ መምጣታቸውን፣ ድሮ የነበረው በባህል ላይ የተመሠረተው ማኅበራዊ እሴት ፈሪኃ እግዚአብሔርና ይሉኝታ እየተዘነጋ የግል ጥቅምን ማስቀደምና ገንዘቡ ማምለክ ዓይነት እሴቶች ማምራቱ በጣም እንደሚያሳስብ ይናገሩ የነበሩት ፕሮፌሰር ዓለም ዜና ዕረፍት ከአሜሪካ የተሰማው ነሐሴ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ነበር፡፡
ከ45 ዓመታት በላይ በሲቲ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒውዮርክ የሶሲዮሎጂ መምህር የነበሩት ፕሮፌሰር ዓለም፣ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ያረፉት ኒውዮርክ ሲቲ ሜሞሪያል ሆስፒታል ውስጥ ነው፡፡
የሶሲዮሎጂ ፕሮፌሰሩ ዓለም ሀብቱ በርካታ የጥናትና ምርምራ ሥራዎች ያከናወኑ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል ጥልቅ ትንተና የሰጡበት ‹‹Ethinc Federalism in Ethiopia Background Present Conditions and Future Prospects›› የሚለው ይገኝበታል፡፡
‹‹Books on the Ethiopian Revolution A Review Essay – Socialism and Democracy›› ሌላው ነው፡፡
በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በ2002 ዓ.ም. በተካሄደው አምስተኛው ኢንተርናሸናል የፌዴራሊዝም ጉባዔ ካቀረቡት ጥናት በተጨማሪ የጥናቱ መድበል ኤዲተር ነበሩ፡፡
በቀድሞው አጠራር በትግራይ ጠቅላይ ግዛት በእንደርታ አውራጃ በሐረቆ አምባ በግንቦት 1936 ዓ.ም. የተወለዱት ፕሮፌሰር ዓለም፣ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ከተማ በአሰፋ ወሰንና በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤቶችና ሁለተኛ ደረጃን በኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል፡፡
ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በማምራትም የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በፔንስሊቪያና ዲክሰን ኮሌጅ የማስትሬትና የፒኤችዲ ትምህርታቸውን በሲቲ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒውዮርክ አጠናቀዋል፡፡ ለሦስተኛው ዲግሪያቸው የመመረቂያ ድርሳን (ዲዜርቴሽን) የሠሩት ‹‹Ethiopian Women’s Literacy in Ethiopia›› በሚል ነበር፡፡
ፕሮፌሰር ዓለም ሀብቱ የቅርብ ወዳጃቸው የነበሩትን ታላቁ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁን ሕይወትና ሥራ በተመለከተ ከ30 ሰዓታት በላይ ኢንተርቪው አድርገው ታሪካቸውን በድምፅ ሰንደዋል፡፡
ባለትዳርና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት የነበሩት ፕሮፌሰር ዓለም ሥርዓተ ቀብር እዚያው ኒውዮርክ ሲቲ ጳጉሜን 1 ቀን 2008 ዓ.ም. መፈጸሙ ታውቋል፡፡
- ሔኖክ ያሬድ's blog
- 2172 reads
No comments:
Post a Comment