Saturday, December 31, 2016

የገናናው አትሌት ምሩፅ ይፍጠር ሥርዓተ ቀብር በሀገራዊ ክብር ዛሬ ይፈጸማል


የኦሊምፒክና የዓለም ዋንጫ በ5,000 ሜትርና በ10,000 ሜትር ሻምፒዮን የነበረው የገናናው አትሌት ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ሥርዓተ ቀብር ዛሬ እሑድ ታኅሣሥ 23 ቀን 2009 ዓ.ም. ከቀኑ ስምንት ሰዓት በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል፡፡
በመተንፈሻ አካል ችግር ምክንያት ሕክምናውን ሲከታተልበት በነበረው ካናዳ ታኅሣሥ 13 ቀን በቶሮንቶ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ 3 ሰዓት 05 ደቂቃ ያረፈው ሻምበል ምሩፅ፣ አስክሬን አዲስ አበባ የሚደርሰው፣ በዛሬው ዕለት ከጧቱ አንድ ሰዓት ከሩብ መሆኑን የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አስታውቋል፡፡
የኮሚቴው ዋና ዳይሬክተር አቶ ታምራት በቀለ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በታላቅ ሀገራዊ ክብር በሀገር መከላከያ ሠራዊት የክብር ዘብ ታጅቦ ሥርዓተ ቀብሩ ይፈጸማል፡፡ በቤተሰቡና በከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት አቀባበል ከተደረገ በኋላ አስክሬኑ ቦሌ መድኃኔ ዓለም ቤተ ክርስቲያን አካባቢ በሚገኘው መኖሪያ ቤት ቆይታ ያደርጋል፡፡ ስንብትና በክብር መዝገብ ላይ አስተያየት የሚሰጥበት ሥነ ሥርዓት ከተከናወነም በኋላ በታላቅ ወታደራዊ አጀብ በቦሌ ዋናው መስመር፣ በዳግማዊ ምኒልክ ጎዳና ከመስቀል አደባባይ ሽኝት በኋላ ወደ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሲያመራ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አካባቢ እንደደረሰ በማርሽ ባንድ መሪነት በሐዘን ዜማ ታጅቦ ከማረፊያው ይደርሳል፡፡
በቤተ ክርስቲያኒቱ ከሚኖረው ሃይማኖታዊ ሥርዓት ባሻገር፣ የአገሪቱ ርእሰ መንግሥት፣ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መልዕክቶች እንደሚተላለፉ ታውቋል፡፡
ለገድለኛው (ሌጀንድ) ኢትዮጵያዊ ሯጭ ምሩፅ ይፍጠር፣ ባረፈበት የካናዳዋ ቶሮንቶ ከተማ፣ ማክሰኞ ታኅሣሥ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. በዚያው በምትገኘው ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ፍትሐት መደረጉ ይታወሳል፡፡
 ‹‹ይፍጠር ዘሺፍተር›› (ማርሽ ቀያሪው ምሩፅ ይፍጠር)፣ ‹‹ይፍጠር ዘማስተር›› (የሩጫ ጌታው ምሩፅ ይፍጠር) በመባል የዐቢይ አድናቆት ባለቤት የነበረው ምሩፅ ይፍጠር  በ1972 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1980) በሞስኮ ኦሊምፒክ ሁለት ወርቆችን በ10,000 ሜትርና በ5,000 ሜትር፣ በ1964 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1972) በሙኒክ ኦሊምፒክ በ10,000 ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያሸነፈ ሲሆን፤ አህጉሮች በሚወዳደሩበትና በ1969 እና በ1971 ዓ.ም. በተከታታይ በተካሄዱት የዱዞልዶርፍና የሞንትሪያል የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫ ምሩፅ ይፍጠር አራት ወርቆችን በ10,000 ሜትርና  በ5,000 ሜትር ለአፍሪካ ማስገኘቱ ይታወቃል፡፡
ገድለኛው ምሩፅ በዐሥራ ስድስት ዓመታት የሩጫ ሕይወቱ፣ ከመካከለኛ ርቀት ማለትም ከ1,500 ሜትር እስከ ረዥም ርቀት (5,000 እና 10,000 ሜትር)፣ እንዲሁም ግማሽ ማራቶንን ጨምሮ ባሉት ርቀቶች በመወዳደርና ከ250 በላይ በመወዳደር በአንደኛነት ማጠናቀቁ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡
የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ምሩፅ ሥርዓተ ቀብሩን በክብር ለማስፈጸም ከወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር፣ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ፣ ከብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ከቤተሰቡ የተወጣጡ አባላት ያሉት ኮሚቴ እየሠራ መሆኑ ይታወሳል፡፡
ከአባቱ አቶ ይፍጠር ተክለሃይማኖትና ከእናቱ ወ/ሮ ለተገብርኤል ገብረአረጋዊ በ1937 ዓ.ም. በትግራይ፣ ዓዲግራት የተወለደውና በ72 ዓመቱ ያረፈው ምሩፅ ይፍጠር የሰባት ልጆች አባት ነበር፡፡


Wednesday, December 28, 2016

ፍሬ ከናፍር ዘምሩፅ ይፍጠር

‹‹ሰዎች ዶሮዎቼን ሊሰርቁ ይችላሉ፤ ሰዎች በጎቼን ሊሰርቁ ይችላሉ፤ ዕድሜዬን ግን ሊሰርቁ አይችሉም፡፡››
በቅርቡ ያረፈው የረዥም ርቀት ንጉሡ፣ ‹‹ይፍጠር ዘሺፍተር››- ማርሽ ቀያሪው ምሩፅ ይፍጠር፣ ‹‹ይፍጠር ዘማስተር››- ጌታው ይፍጠር፣ ከሦስት አሠርታት በፊት ለዜና አውታሮች የተናገረው፡፡ በ1972 ዓ.ም. በተካሄደው የሞስኮ ኦሊምፒክ በሁለት ርቀቶች በ5 ሺ እና 10 ሺ ሜትር ድርብ ወርቅ ማግኘቱን ተከትሎ፣ ምሩፅ በኦሊምፒክ ሲያሸንፍ ዕድሜው 36? ፣ 40?፣ ወይስ 42? ተብሎ የተለያዩ መረጃዎች መውጣታቸውን ተከትሎ በዘይቤ የሰጠው ምላሽ፣ በተለያዩ የኦሊምፒክና የአትሌቲክስ ታሪካዊ ድርሳናት ሰፍሮ ይገኛል፡፡ የሻምበል ምሩፅ ዜና ዕረፍት ከካናዳ ቶሮንቶ ታኅሣሥ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. መሰማቱን ተከትሎ የሐዘን መግለጫ ካስተላለፉት መካከል፣ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴና ኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ይገኙበታል፡፡ በኢትዮጵያም ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ካወጡት የሐዘን መግለጫ ባሻገር፣ ብሔራዊ እግር ኳስ ፌዴሬሽኑ ሰባተኛው ሳምንት የፕሪሚየር ሊጉ ጨዋታዎች በተካሄዱባቸው የአገሪቱ ከተሞች ምሩፅ ይፍጠርን በኅሊና ጸሎት ዘክረዋል፡፡ ስለ ምሩፅ በኩር አትሌትነት የሚያስታውሱ መግለጫዎችም ቀርበዋል፡፡

ፕሮፌሰር ዓለም ሀብቱ (1936-2008)


በ1950ዎቹ መጨረሻ በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ በአውሮፓና በአሜሪካ መቀጣጠል ሲጀምር ግንባር ቀደም ከነበሩት መካከል ይገኙበታል፡፡ በ1960 ዓ.ም. በአገር ቤት ውስጥ በነበረው የንጉሠ ነገሥት መንግሥቱን ሥርዓት በመቃወም አድማ የመቱ ተማሪዎች በታሠሩበትና በተፈረደባቸው ጊዜ፣ የእነርሱን ሁኔታ በአሜሪካም ሆነ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስታወቅና እንዲፈቱም ለማድረግ በተወሰደው በዋሽንግተን የሚገኘውና የኢትዮጵያ ኤምባሲ ከተቆጣጠሩት ተማሪዎች አንዱ ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰር ዓለም ሀብቱ፡፡
የቀድሞው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ማኅበር በሰሜን አሜሪካ (ኢሳና) ፕሬዚዳንት የነበሩት ፕሮፌሰር ዓለም፣ በመጋቢት 1961 ዓ.ም. ተማሪዎች የኢትዮጵያን ኤምባሲ እንዲቆጣጠሩና በወቅቱ ሚሊተሪ አታሼ የነበሩትን ጄኔራል ተፈሪ በንቲን ‹‹በተጨቆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ስም›› ለተወሰነ ጊዜ በቁም እስር እንዲውሉ ያደረጉትን ተማሪዎች ከፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ጋር በመሆን መርተዋል፡፡
‹‹The Ethiopian Student Movement (ESM): My Experiences in ESUNA, 1964-1971›› በሚለው ወረቀታቸው እንደገለጹት፣ በፊላዴልፊያ ከተማ በነሐሴ 1961 ዓ.ም. በተካሄደው የኢሱና ጉባኤ በአገሪቱ ያሉትን ችግሮች የተመለከቱት ‹‹The Problem of Regionalism in Ethiopia›› በሚል ነበር፡፡ ዋለልኝ መኰንን ‹‹The Question of Nationalities›› (የብሔረሰቦች ጥያቄ) የሚለውን ወረቀቱን ከማውጣቱ ሦስት ወራት በፊት ነበር የአካባቢ/ክልል (ሪጅንስ) ጉዳይ የሚመለከተው ጽሑፍ የወጣው፡፡
ፕሮፌሰር ዓለም ከአምስት ወራት በፊት ለአውስትራሊያው ኤስቢኤስ ሬዲዮ በሰጡት ቃለ ምልልስ እንደተናገሩት፣ የጽሑፉ ይዘት የሚያመለክተው ‹‹ኢትዮጵያ ልዩ ልዩ ሪጅንስ አላት፣ በእነሱ መካከል ያሉትን ልዩነቶች ገዥ መደቦች እየተጠቀሙ ሕዝቡን ከፋፍለው ይገዙ ነበር፤ በፀረ ፊውዳልና ፀረ ኢምፔሪያሊዝም አቋም መሠረት ኢትዮጵያውያን ለአንድ ሕዝብ መሠረታዊ ለውጥ እንዲታገሉ ነበር፡፡››
እነ ፕሮፌሰር አንድርያስ፣ መለሰ አያሌውና ሐጎስ ገብረ ሕይወትም ያራመዱት ይኼ ሐሳብ ከዋለልኝ መኰንን ሐሳብ የተለየ ነበር፡፡
‹‹በዚያን ጊዜ እኛ የተጠቀምነው ቃል ሪጅናሊዝም ነበር እንጂ ናሽናል ኮስችን አልነበረም፡፡ ናሽናል ኮስችን በማርክሲስት ሌኒኒስት መስመር ሲታይ ነው፤ በዚያ መስመር አላየነውም፤›› ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ የኤርትራ ብቻ ሳይሆን በአሁን ጊዜ ብሔር ብሔረሰብ የሚባለው ጥያቄ መጀመርያ የተነሳው ከሪጂናሊዝም አንፃር ያቀረቡት ከ48 ዓመታት በፊት ነበር፡፡
ፕሮፌሰር ዓለም ሪጅናሊዝም የሚመለከተውን ጽሑፍ ያዘጋጁት የኢትዮጵያን ኤምባሲ ለሁለተኛ ጊዜ በሐምሌ 1961 ዓ.ም. ንጉሡ አሜሪካን በጎበኙበት አጋጣሚ ስምንት ሆነው በተቆጣጠሩበትና ለእስር በተዳረጉት አጋጣሚ ነበር፡፡
‹‹ስለአገራችን በቂ ዕውቀት የለንም፡፡ የሌላ አገር ታሪክና ቲየሪ ብቻ ሳይሆን የራሳችን ታሪክና መማር አለብን፤›› በማለት ይመሩት በነበረው የቀድሞ ተማሪዎች ማኅበር የብሔረሰቦች ጥያቄ ወደፊት የመራውና ዋና ጥያቄ እንዲሆን ያደረገው፣ በማኅበሩ ውስጥ የተማሪው ማኅበር ሳያውቃቸው በነበሩ በኅቡዕ የተቋቋሙ የፖለቲካ ድርጅቶች አማካይነት ነበር፡፡ ይህን አቋም እሳቸውና ጓደኞቻቸው ባለመደገፋቸው የሐሳብ ልዩነት መፈጠሩን ተመልክቷል፡፡
የ1966 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አብዮት መፈንዳት ተከትሎ በሐምሌ ወር በአቶ ተክለጻድቅ መኩሪያ የሚመራው የሕገ መንግሥት ኮሚሽን ያረቀቀው ሕገ መንግሥት፣ ኢትዮጵያን በሕገ መንግሥታዊ ዘውድ ሥርዓት እንደ እንግሊዝና ስዊድን የሚያደርገው በወቅቱ በጣም መደገፍ እንደነበረበት ያምኑ የነበሩት ፕሮፌሰር ዓለም፣ ተማሪውም ተራማጁም ለተለያዩ አማራጮች በቂ ትኩረት ባለመስጠታቸው ከመጀመርያውኑ ተጨናግፎ ወታደሩ ሥልጣን እንዲይዝ አድርጎታል፣  አገሪቱ ለጉዳትም መዳረጓን ያምኑ ነበር፡፡
በኢሱና ሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት ውስጥ ለአምስት ዓመታት (ከ1957 ዓ.ም.-1962 ዓ.ም.) በመጀመርያ በረዳት ዋና ጸሐፊነት (1957-1959 ዓ.ም.) ቀጥሎም በፕሬዚዳንትነት (1959-1960)፣ እንዲሁም የማኅበሩ ልሳን በነበረው ቻሌንጅ (Challenge) ዋና አዘጋጅነት (1960-1962) ያገለገሉት ፕሮፌሰር ዓለም፣ ባለፉት የትግል ዘመናት መለስ ብለው የተመለከቱትን በአንድ ወቅት እንዲህ ብለው ነበር፡፡
‹‹ያጠፋነውም ያለማነውም ይኖራል፡፡ አቅማችን በፈቀደ ግን የተማሪው ንቃተ ኅሊናም ከፍ እንዲል ማኅበራዊ እሴቶች እንዲኖሩ ጥረት አድርገን ነበር፡፡ ሁላችንንም ባይመለከትም ግን ከኛ በኋላ የመጣው የሰሜን አሜሪካ ተማሪዎች ማኅበር የተማሪን ሚና ከአቅሙ በላይ አድርጎ አይቶ፣ ተማሪ በትጥቅ ትግል ለውጥ ማምጣት ይቻላል ብሎ ለብዙ ጥፋቶችና ስህተቶች ተዳርጓል፡፡ ‹‹የተማሪው ንቅናቄ በሙሉ በአንድ በኩል እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ ላለው አጀንዳ ያዘጋጀ ይመስላል፡፡ ለደጉም ለክፉም የተማሪዎች ንቅናቄ በኢትዮጵያ ዘመናዊ ታሪክ ላይ ትልቅ ምልክት ትቶ ነው የሚያልፈው፡፡››
ፋሺስት ኢጣሊያ በ1933 ዓ.ም. ድል ከተመታ በኋላ በነበሩት ተከታታይ ትውልዶች ለውጥ ለማምጣት ለየት ያለ ትግል ያደረገው የ1950ዎቹ ትውልድ እንደሆነ እምነት ነበራቸው፡፡ ‹‹የኛ ትውልድ ነው ለውጥ ለማምጣት የታገለው፡፡ እኔ ‹ሥር ነቀል› የሚለውን ቃል አልወድም፡፡ ምክንያቱም ሥር ውስጥ አንዳንድ በጎም መጥፎም ነገሮች አሉ፡፡ ሁለቱን ሳይለዩ ሥር መንቀል ታጥቦ ጭቃ ሊሆንም ይችላል፤›› የሚልም አተያይ ነበራቸው፡፡  
ከ1966 ዓ.ም. አብዮት ወዲህ የኢትዮጵያ ወጣቶች ማኅበራዊ እሴቶች እያጡ መምጣታቸውን፣ ድሮ የነበረው በባህል ላይ የተመሠረተው ማኅበራዊ እሴት ፈሪኃ እግዚአብሔርና ይሉኝታ እየተዘነጋ የግል ጥቅምን ማስቀደምና ገንዘቡ ማምለክ ዓይነት እሴቶች ማምራቱ በጣም እንደሚያሳስብ ይናገሩ የነበሩት ፕሮፌሰር ዓለም ዜና ዕረፍት ከአሜሪካ የተሰማው ነሐሴ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ነበር፡፡
ከ45 ዓመታት በላይ በሲቲ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒውዮርክ የሶሲዮሎጂ መምህር የነበሩት ፕሮፌሰር ዓለም፣ ባደረባቸው ሕመም ምክንያት ያረፉት ኒውዮርክ ሲቲ ሜሞሪያል ሆስፒታል ውስጥ ነው፡፡
የሶሲዮሎጂ ፕሮፌሰሩ ዓለም ሀብቱ በርካታ የጥናትና ምርምራ ሥራዎች ያከናወኑ ሲሆን፣ ከነዚህም መካከል ጥልቅ ትንተና የሰጡበት ‹‹Ethinc Federalism in Ethiopia Background Present Conditions and Future Prospects›› የሚለው ይገኝበታል፡፡
‹‹Books on the Ethiopian Revolution A Review Essay – Socialism and Democracy›› ሌላው ነው፡፡ 
በኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ በ2002 ዓ.ም. በተካሄደው አምስተኛው ኢንተርናሸናል የፌዴራሊዝም ጉባዔ ካቀረቡት ጥናት በተጨማሪ የጥናቱ መድበል ኤዲተር ነበሩ፡፡
በቀድሞው አጠራር በትግራይ ጠቅላይ ግዛት በእንደርታ አውራጃ በሐረቆ አምባ  በግንቦት 1936 ዓ.ም. የተወለዱት ፕሮፌሰር ዓለም፣ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርታቸውን በአዲስ አበባ ከተማ በአሰፋ ወሰንና በተፈሪ መኰንን ትምህርት ቤቶችና ሁለተኛ ደረጃን በኮተቤ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት አጠናቀዋል፡፡
ወደ ዩናይትድ ስቴትስ በማምራትም  የመጀመርያ ዲግሪያቸውን በፔንስሊቪያና ዲክሰን ኮሌጅ የማስትሬትና የፒኤችዲ ትምህርታቸውን በሲቲ ዩኒቨርሲቲ ኦፍ ኒውዮርክ አጠናቀዋል፡፡ ለሦስተኛው ዲግሪያቸው የመመረቂያ ድርሳን (ዲዜርቴሽን) የሠሩት ‹‹Ethiopian Women’s Literacy in Ethiopia›› በሚል ነበር፡፡
ፕሮፌሰር ዓለም ሀብቱ የቅርብ ወዳጃቸው የነበሩትን ታላቁ ኢትዮጵያዊ ደራሲ ሐዲስ ዓለማየሁን ሕይወትና ሥራ በተመለከተ ከ30 ሰዓታት በላይ ኢንተርቪው አድርገው ታሪካቸውን በድምፅ ሰንደዋል፡፡
ባለትዳርና የሁለት ሴቶች ልጆች አባት የነበሩት ፕሮፌሰር ዓለም ሥርዓተ ቀብር እዚያው ኒውዮርክ ሲቲ ጳጉሜን 1 ቀን 2008 ዓ.ም. መፈጸሙ ታውቋል፡፡

የ‹‹ማርሽ ቀያሪው›› ምሩፅ ይፍጠር ስንብት


ከሠላሳ ሰባት ዓመት በፊት የተካሄደው የሞስኮ ኦሊምፒክ ሲነሣ ቀድሞ የሚመጣው የሚወሳው ረዥም ርቀት ሯጩ ምሩፅ ይፍጠር ነው፡፡ የድል ቁርጠኝነት የተሞላበት አሯሯጡ የመላው ዓለምን ምናብ ሰንጎ መያዙ አይረሳም፡፡
በሞስኮ ኦሊምፒክ በሁለቱ ርቀቶች በ5,000 ሜተርና በ10,000 ሜትር ለተቀናቃኞቹ ዕድል ሳይሰጥ ተፈትልኮ የሮጠበትና ያሸነፈበት መንገድ ‹‹ይፍጠር ዘ ሺፍተር›› (ማርሽ ለዋጩ ምሩፅ - አካለ ማርሹ ምሩፅ) የተባለበትን ዳግም ያረጋገጠበት ነበር፡፡ በሞስኮ ድሉ ከተመሰጡና አርአያ ከሆነላቸው መካከል በወቅቱ የሰባት ዓመት ልጅ የነበረው ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ውድድሩን በትራንዚተር ሬዲዮ ጆሮውን ደቅኖ ሲከታተል አንድ ቀን የርሱን ዱካ እንደሚከተል አልሞ ነበር፡፡
ኢትዮጵያን የኦሊምፒክ ብርሃን ከዘጠና ሦስት ዓመት በፊት የዳሰሰው በፓሪስ ኦሊምፒክ አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንንና የክብር ተከታዮቻቸው በታደሙበት ቢሆንም፣ መወዳደር የጀመረችው ግን ከስድሳ ዓመት በፊት ሜልቦርን ላይ ነበር፡፡ የኦሊምፒክ የድል ጮራ የበራውም በሮም ኦሊምፒክ አበበ ቢቂላ በማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ሲያጠልቅ ነው፡፡ ከአበበ ቢቂላ ጋር ማሞ ወልዴ፣ ምሩፅ ይፍጠር፣ ኃይሌ ገብረ ሥላሴና ቀነኒሳ በቀለ የኢትዮጵያ የምንጊዜም የረዥም ርቀት ዝነኞች ሆነው ተከስተዋል፡፡
ፋና ወጊው አበበ ቢቂላ የኦሊምፒክ ማራቶንን በ1952 ዓ.ም. (1960) እና 1957 ዓ.ም. (1964) ኦሊምፒኮች ድል ሲመታ፣ ምሩፅ ግን በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ታሪክ ሁነኛ ሥፍራ ያሰጠውን አስደናቂ ድርብ ድል በሞስኮ በ1972 ዓ.ም. (1980) ተቀዳጅቷል፡፡
የሞስኮ ኦሊምፒክ የምሩፅ አስደናቂው ድርብ ድል እስከሚከሰትበት ድረስ የሚዲያ መድረኩን ተቆጣጥረውት የነበሩት ሁለት እንግሊዛውያን የ1,500 ሜትርና የ800 ሜትር ባለድሎቹ ሰባስቲያን ኮ እና ስቲቭ ኦቬት ነበሩ፡፡  በአስደናቂ አሯሯጡና በልዩ ችሎታው ማርሽ ቀይሮ ያሳየው ብልጫ ሩጫውን ሕይወት ሰጠው፡፡ ሐምሌ 22 ቀን 1972 ዓ.ም. በተካሄደው የ10 ሺሕ ፍጻሜ ከምሩፅ ይፍጠር ጋር አብረው የተሰለፉ መሐመድ ከድርና ቶሎሳ ቆቱ በሁለት ኦሊምፒክ የበላይ የነበረችው ፊንላንድ በሻምፒዮኑ ላሲ ሸረን መሪነት ካርሎ ማኒንካን ይዞ የታየው የ25 ዙር ታክቲካዊ ትግል የተቋጨው፣ ውድድሩ ሊያበቃ 300 ሜትር ሲቀረው ምልዓተ ኃይሉን ተጠቅሞ ባፈተለከው ምሩፅ ይፍጠር ድል አድራጊነት ነበር፡፡ ምሩፅ የመጨረሻውን 200 ሜትር በ26.8 ሰከንድ በመሮጥ መስመሩን በጥሶ ያለፈው በ27 ደቂቃ 42.69 ሰከንድ ነበር፡፡ ማኒንካ ብር፣ መሐመድ ነሐስ ሲያገኙ ቶሎሳና ቬረን ተከታዮቹን ቦታ ይዘው ፈጽመዋል፡፡
ይህ በሁለቱ በኢትዮጵያና በፊንላንድ መካከል የነበረውን ፉክክር ለማየት በወቅቱ የፊንላንድ ፕሬዚዳንት የነበሩት በስፍራው መገኘታቸው ይታወሳል፡፡ በ5,000 ሜትርም ምሩፅ የመጨረሻውን 200 ሜትር በ27.2 ሰከንድ በማለፍ ድሉን ያጣጣመው በ13፡20.91 ሲሆን፣ ያስከተላቸውም ታንዛኒያውን ሱሌይማን ንያምቡና ፊንላንዳዊውን ማኒካን ነበር፡፡
ምሩፅ ስለ ሞስኮ ድሉ ከ12 ዓመት በፊት ላናገረው የኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ድረ ገጽ እንዳወጋው፣ ያኔ ከአሠልጣኞቻቸው ጋር የተነጋገሩት ርሱም የተለማመደው በሁለቱም ርቀቶች 300 ሜትር ሲቀር አፈትልኮ ለመሮጥ ነበር፡፡ ‹‹አምስት ዙር እንደቀረው የተቀናቃኞቼን እንቅስቃሴና ትርታ ማዳመጥ ጀመርሁ፤  ውጥረት የሚሰፍነው ደወሉ ሲደወል በመሆኑና አቅማቸውን አሰባስበው ከመነሳታቸው በፊት 300 ሜትር ሲቀር ማምለጥ እንዳለብኝ ወሰንሁ፤ ድሉንም ጨበጥኩ፡፡›› 
የምሩፅ ይፍጠር የሩጫ ጉዞ
መስከረም 1961 ዓ.ም. አበበ ቢቂላና ማሞ ወልዴን የያዘው የሜክሲኮ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ ተሳታፊ አትሌቶች የመጨረሻ ጉዟቸውን ወደ ሜክሲኮ ሲቲ ከማድረጋቸው በፊት ለልምምድ ያረፉት አስመራ ከተማ ነበር፡፡ በአስመራ ንግሥተ ሳባ ስታዲየም ልምምድ ሲያደርጉ የተመለከተው የከተማዋ ነዋሪ ምሩፅ ይፍጠር ለወደፊት ሕይወቱ በር ከፋች አጋጣሚ ፈጠረለት፡፡ በልምምድ ሩጫ ውድድርም ከነማሞ ወልዴ ጋር ተወዳድሮ መጨረሻ ቢወጣም አሯሯጡንና አቅሙን ያስተዋሉት አሠልጣኝ ንጉሤ ሮባ በአየር ኃይል ስፖርት መምሪያ እንዲያዝና ልምምድ እንዲያደርግ አደረጉ፡፡ ቅጥሩንም ፈጸመ፡፡ ለ20 ዓመታት በአየር ኃይል ሲያገለግል እስከ ሻምበልነት ደርሷል፡፡
በአዲስ አበባው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ስታዲየም፣ ንብ የሚባለውን የአየር ኃይል ስፖርት ክለብን እየወከለ በብሔራዊ ሻምፒዮናና በጦር ኃይሎች ውድድር ውጤታማ መሆን የጀመረው ምሩፅ፣ የመጀመሪያው ኢንተርናሽናል ውድድሩ በ1962 ዓ.ም. በምሥራቅ አፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታንዛኒያ ውስጥ በ1,500 ሜትር ከኦሊምፒክ ባለወርቁ ኬፕቾግ ኬይኖ ጋር ተወዳድሮ ሦስተኛ የወጣበት ውድድሩ ነበር፡፡
በ1963 ዓ.ም. በአሜሪካ በተካሄደው የአፍሮ አሜሪካን ውድድር በ10 ሺሕ ወርቅ፣ በ5 ሺሕ ሜትር ብር ሜዳሊያ በማግኘት ድሉን አሐዱ ብሎ ጀምሯል፡፡
የመጀመሪያው የኦሊምፒክ መድረኩ በሆነው 20ኛው ኦሊምፒያድ በሙኒክ ሲካሄድ ምሩፅ በ5 ሺሕና በ10 ሺሕ ሜትር ለመወዳደር ነበር ወደ ሥፍራው ያመራው፡፡ በ10 ሺሕ ሜትር በማጣሪያው አንደኛ ወጥቶ በፍጻሜው ሦስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያን አግኝቷል፡፡ በ5 ሺሕ ሜትር ማጣሪያ ‹‹አሠልጣኞቹ በፈጠሩት ችግር›› ምክንያት በጊዜ ባለመድረሱ የተነሳ ሳይወዳደር በመቅረቱ ሌላ ሜዳሊያ የማግኘት ዕድሉ ተጨናግፎበታል፡፡
በ1965 ዓ.ም. በሌጎስ (ናይጄሪያ) በተካሄደው የመላው አፍሪካ ጨዋታዎች በ10 ሺሕ ወርቅ በ5 ሺሕ ብር አሸንፏል፡፡ በዚያው ዓመት ከሁሉም የስፖርት ዓይነቶች ከተውጣጡት መካከል የኢትዮጵያ ስፖርት ኮከብ አትሌት ተብሎ የተመረጠው ምሩፅ፣ በ1968 ዓ.ም. በሞንትሪያል (ካናዳ) በተካሄደው 21ኛው ኦሊምፒያድ ያለ ጥርጥር በ5,000 እና በ10,000 ሜትር ሁለት ወርቅ ያገኛል ተብሎ ቢጠበቅም፣ ከደቡብ አፍሪካ ጋር ስፖርታዊ ግንኙነት የነበራት ኒውዚላንድ ከሞንትሪያል ኦሊምፒክ ባለመታገዷ ምክንያት አፍሪካውያን አንካፈልም በማለታቸው ሳይወዳደር ተመልሷል፡፡
በሙኒክ ኦሊምፒክ ምሩፅን ያሸነፈው ፊንላንዳዊው ላሲ ቨረን ዳግመኛ ድሉን ምሩፅ በሌለበት አጣጣመ፡፡
ምሩፅ የኦሊምፒክ ወርቅ ሕልሙን ያሳካው በ1972 ዓ.ም. ሞስኮ ባስተናገደችው 22ኛ ኦሊምፒያድ ሲሆን በሁለቱም ርቀቶች ወርቁን ያጠለቀው ፊንላንዳዊውን ላሲ ቨረንን ድል በመምታት ነበር፡፡
በሞስኮ ኦሊምፒክ ሲሮጥ ዕድሜው የገፋው (በፓስፖርት ዕድሜው 36 ዓመቱ በተለያዩ ሚዲያዎች እስከ 42 የሚያደርሱት) ምሩፅ፣ በ1969 ዓ.ም. እና በ1971 ዓ.ም. በተካሄዱት የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫዎች አፍሪካን በመወከል አራት ወርቅ ሜዳሊያ ሲያገኝ ተወዳዳሪዎቹን በቀደመበት ርቀት ያህል በሞስኮ አልደገመውም፡፡ ዕድሜው ገፍቷልና፡፡
በሁለቱ የዓለም ዋንጫዎች በ5,000 ሜትር ውድድሩ ሊያበቃ 500 ሜትር ሲቀር፣ በ10 ሺሕ 600 ሜትር ሲቀር ነበር ማርሽ ቀይሮ በማፈትለክ ያሸነፈው፡፡ በሞስኮ ኦሊምፒክ ግን በሁለቱ ርቀቶች እንደ ቅደም ተከተላቸው 200 ሜትርና 300 ሜትር ሲቀረው ነበር፣ ማርሽ ቀይሮ ድል የመታው፡፡ ምሩፅ በ1971 ዓ.ም. በዓለም ዋንጫ አፍሪካን ወክሎ ለመካፈል የበቃው የመጀመሪያው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በዳካር (ሴኔጋል) ሲካሄድ ሁለት ወርቅ (በ5 ሺሕና 10 ሺሕ) በማግኘቱ ነበር፡፡
ምሩፅ 1971 ዓ.ም. ወርቃማ ዓመቱ ነበር፡፡ እጅግ የገነነበት ታላቅ ክብርንም የተቀዳጀበት፡፡ በዚያው ዓመት በቼኮዝሎቫኪያ በተዘጋጀው የዓለም ኮከብ አትሌቶች ምርጫ ዘጠኝ አትሌቶች ሲመረጡ አንዱ ምሩፅ ሲሆን፣ ‹‹የኮከቦች ኮከብ›› ተብሎ መመረጡ በተዘጋጀው የተሸላሚዎች መድረክ ራሱ ከመሀል በከፍታ መቀመጡ ይታወሳል፡፡ የወርቅ ጫማም ተሸላሚ ነበር፡፡ ምሩፅ ድርብ ድሎቹን በዳካር፣ በሞስኮና ሞንትሪያል በተደረጉ አህጉራዊና ዓለማዊ ውድድሮች ስድስት ወርቅ ይዞ አዲስ አበባ በደረሰ ጊዜ ጋዜጠኛ ኃይሉ ልመንህ እንዲህ ገጥሞለት ነበር፡፡
‹‹አብዮቱ ፈካ አበባው አማረ
ያለም ሻምፒዮና በምሩፅ ሠመረ፡፡
ሞስኮ ላይ ቀደመ ዳካር ላይ ድል መታ
ሞንትሪያል ደገመ እንዳመሉ ረታ
ዓለም ይሁን አለ ድሉን ተቀበለ
እየደጋገመ ምሩፅ ምሩፅ አለ፡፡››
የመጀመሪያ ዓለም ዋንጫ በዱዞልዶርፍ (ምዕራብ ጀርመን) ሲካሄድ አፍሪካን ወክሎ ለመሳተፍ የበቃው የቅርብ ተቀናቃኙን ኬንያዊውን የዓለም ሪከርድ ባለቤት ሔንሪ ሮኖን በመርታት ነበር፡፡
የኢትዮጵያ መንግሥት (በወቅቱ ኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ) ሻምበል ምሩፅ በቅድመ ሞስኮ ኦሊምፒክ ባገኛቸው አህጉራዊና ኢንተርናሽናል ድሎች ኢትዮጵያን ለታላቅ ግርማ ሞገስ በማብቃት ለፈጸመው አኩሪ ተግባር አምስተኛው የአብዮት በዓል ሲከበር፣ ‹‹የጥቁር ዓባይ ኒሻን››ን ከርዕሰ ብሔሩ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እጅ መቀበሉ ይታወሳል፡፡
በ1,500 ሜትር መወዳደር የጀመረው ምሩፅ 5 ሺሕና 10 ሺሕ መደበኛ ውድድሮቹ ቢሆኑም በጎዳና ላይ ሩጫዎችም ተደጋጋሚ ድሎች ማግኘቱ አይሳትም፡፡
በተለይ በተከታታይ ዓመታት ድል የተጎናፀፈበት የፖርቶ ሪኮ ግማሽ ማራቶን ውድድር ለዓለም ክብረ ወሰን የበቃበት ነበር፡፡ ጥር 29 ቀን 1969 ዓ.ም. በፖርቶ ሪኮ ኮዓሞ የ21 ኪሎ ሜትር (ግማሽ ማራቶን) ውድድር ምሩፅና መሐመድ ከድር ተከታትለው ሲያሸንፉ ምሩፅ የገባበት 1 ሰዓት 02 ደቂቃ 57 ሰከንድ ያለም ክብረ ወሰን ሆኖ ተመዝግቦለታል፡፡
በ1972 በፖርቶ ሪኮ ግማሽ ማራቶን አሸንፎ እንደተመለሰ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫም ‹‹የማተኩረው በሞስኮ ኦሊምፒክ ስለሆነ በፖርቶ ሪኮው ድሌ አልኮራም›› ማለቱ አይዘነጋም፡፡
በሞስኮ ኦሊምፒክ ለሦስተኛ ጊዜ ድሉን ለማጣጣም ቋምጦ የነበረው ፊንላንዳዊ ላሲ ቬረን በሞስኮ አየሩ ጥሩ ከሆነ እንደሚያሸንፍ መናገሩን ተከትሎ ምሩፅ በሰጠው አፀፋ ‹‹ሐሩርም ይሁን በረዶ እኔ ከማሸነፍ የሚገታኝ አንዳች ኃይል የለም›› ማለቱ ልበ ሙሉነቱን ያሳየበት አጋጣሚ ነበር፡፡
ከሞስኮ ኦሊምፒክ ድሉ በኋላ ጥንታዊ ኦሊምፒክ በተመሠረተባት ግሪክ ለኦሊምፒያዊ ሽልማት ከተመረጡ አምስት አትሌቶች ቀዳሚ ሆኖ የኦሊምፒክ ሎሬት አክሊልን ከርዕሰ ብሔሩ የተቀበለው ምሩፅ ይፍጠር ነበር፡፡
በዓለም ገናና ለሆነው ኃይሌ ገብረሥላሴ፣ ለሞሮኮው ሰዒድ አዊታና ለሌሎችም አርአያ የሆነው ምሩፅ፣ ኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር በ1973 ዓ.ም. በምዕራብ ጀርመን ባደን ባደን ጉባኤውን ሲያካሂድ የዓለም አትሌቶችን ከወከሉ አትሌቶች አንዱ ርሱ ነበር፡፡ ሌላኛው ተወካይ እንግሊዛዊው ያሁኑ የኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ፕሬዚዳንት የያኔው የሞስኮ ኦሊምፒክ የ1,500 ሜትር ባለድል ሰባስቲያን ኮ ነበር፡፡
ጀንበሯ ስትጠልቅ
ከሁለት አሠርታት ወዲህ በአብዛኛው መቀመጫውን በካናዳ አድርጎ የነበረው ምሩፅ፣ ከዓመት ወዲህ ባደረበት ጽኑ የሳምባ ሕመም ምክንያት ሕክምናውን እየተከታተለ ቢቆይም፣ ከሐሙስ ታኅሣስ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. ወዲህ መሻገር አልቻለም፡፡ በቶሮንቶ ሰዓት አቆጣጠር ከምሽቱ ሦስት ሰዓት ከአምስት ደቂቃ ሕይወቱ ማለፉ በካናዳ ለቤተሰቡ ቅርብ የሆነው አድናቂና ወዳጁ አቶ ታምሩ ተስፋዬ በስልክ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ዜና ዕረፍቱን ተከትሎ ቤተሰቡ በካናዳ ከኢትዮጵያ ኤምባሲ እንዲሁም ጥልቅ ሐዘናቸውን ከገለጹት ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጋር መገናኘቱንና አስክሬኑን በክብር ወደ አገሩ ለመመለስ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
‹‹ምሩፅ አገሬ ወስዳችሁ ነው የምትቀብሩኝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለውለታዬ ነው›› ይል እንደነበረ ያስታወሱት አቶ ታምሩ፣ በገና በዓል ምክንያት መሥሪያ ቤቶች ዝግ በመሆናቸው ሒደቱን ማፋጠን ባለመቻሉ ሰነዶቹ ተሟልተው እንዳበቁ በቀናት ውስጥ አስክሬኑ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚጓጓዝ ተናግረዋል፡፡
የሻምበል ምሩፅ ይፍጠር ሥርዓተ ቀብር በክብር ለማስፈጸም በወጣቶችና ስፖርት ሚኒስቴር የተሰየመ ኮሚቴ መኖሩንና የብሔራዊ  አትሌቲክስ ፌዴሬሽን መሪዎች ኃይሌ ገብረሥላሴና ገብረ እግዚአብሔር እየተንቀሳቀሱ መሆኑን በአዲስ አበባ የሚገኘው ልጁ ቢንያም ምሩፅ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አስክሬኑን ለማጓጓዝ መጠየቁን ያወሳው ቢንያም፣ ለምሩፅ የጀግና ሽኝት እንደሚደረግለት እምነቱ መሆኑን ተናግሯል፡፡
ያ ስመ ገናና ‹‹ይፍጠር ዘ ሺፍተር››፣ በደዌ ዳኛ በአልጋ ቁራኛ ተይዞ ከካናዳ ሆኖ በባዕድ መንግሥት እየታገዘ በነበረበት ሰዓት ምሩፅ፣ እጅግ ውድና በገንዘብ የማይተመኑት ሽልማቶቹ በጨረታ ተሸጠው ለሕክምና እንዲውሉ ሲጠየቅ ‹‹ሽልማቶቼ የኢትዮጵያ ሕዝብ ናቸው፤ ለሽያጭ አይታሰቡም›› ማለቱ አይዘነጋም፡፡
ከአባቱ አቶ ይፍጠር ተክለሃይማትና ከእናቱ ወ/ሮ ለተገብርኤል ገብረአረጋዊ ጥቅምት 5 ቀን 1937 ዓ.ም. በትግራይ፣ ዓዲግራት የተወለደውና በ72 ዓመቱ ያረፈው ምሩፅ ይፍጠር የሰባት ልጆች አባት ነበር፡፡
የምሩፅ ይፍጠር ዓበይት ድሎች
ኢትዮጵያን በመወከል
ሜዳሊያ
እ.ኤ.አ.
ኦሊምፒክ ጨዋታዎች
ወርቅ
1980
ሞስኮ
5,000 ሜትር
ወርቅ
1980
ሞስኮ
10,000 ሜትር
ነሐሰ
1972
ሙኒክ
10,000 ሜትር
መላ አፍሪካ ጨዋታዎች
ወርቅ
1973
ሌጎስ
10,000 ሜትር
ብር
1973
ሌጎስ
5,000 ሜትር
አፍሪካን በመወከል 
የአይኤኤፍ ዓለም ዋንጫ (የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫ)
ወርቅ
1977
ዱዘልዶርፍ
5,000 ሜትር
ወርቅ
1977
ዱዘልዶርፍ
10,000 ሜትር
ወርቅ
1979
ሞንትሪያል
5,000 ሜትር
ወርቅ
1979
ሞንትሪያል
10,000 ሜትር

         


ለገድለኛው ሯጭ ምሩፅ ይፍጠር በቶሮንቶ ጸሎተ ፍትሐት ተደረገለት

28 Dec, 2016 By ሔኖክ ያሬድ   Comments

ለገድለኛው (ሌጀንድ) ኢትዮጵያዊ ሯጭ ምሩፅ ይፍጠር፣ ባረፈበት የካናዳዋ ቶሮንቶ ከተማ፣ ትናንት ማክሰኞ ታኅሣሥ 18 ቀን 2009 ዓ.ም. ጸሎተ ፍትሐት ተደረገለት፡፡ ‹‹ይፍጠር ዘሺፍተር›› (ማርሽ ቀያሪው ምሩፅ ይፍጠር)፣ ‹‹ይፍጠር ዘማስተር›› (የሩጫ ጌታው ምሩፅ ይፍጠር) በመባል የዐቢይ አድናቆት ባለቤት ለነበረው ምሩፅ ይፍጠር ጸሎተ ፍትሐቱ የተደረገው፣ በቶሮንቶ በምትገኘው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መሆኑን ሲቢሲ ኒውስ በድረ ገጹ ዘግቧል፡፡
በሥነ ሥርዓቱ ላይ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ ካህናትና ምዕመናን መገኘታቸው ታውቋል፡፡ በ1972 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1980) በሞስኮ ኦሊምፒክ ሁለት ወርቆችን በ10ሺሕና በ5ሺሕ ሜትር፣ በ1964 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1972) በሙኒክ ኦሊምፒክ በ10ሺሕ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያሸነፈው ምሩፅ ይፍጠር በሳምባ ጽኑ በሽታ በ72 ዓመቱ ያረፈው ታኅሣሥ 13 ቀን 2009 ዓ.ም. መሆኑ ይታወሳል፡፡ የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ምሩፅ አስክሬን፣ በዚህ ሳምንት አዲስ አበባ እንደሚገባና ሥርዓተ ቀብሩም ከተለያዩ አካላት ተውጣጥቶ በተቋቋመው ኮሚቴ አማካይነት በክብር እንደሚፈጸም ይጠበቃል፡፡ በዐሥራ ሦስት ዓመታት የሩጫ ሕይወቱ ከመካከለኛ ርቀት ማለትም ከ1,500 ሜትር እስከ ረዥም ርቀት (5,000 እና 10,000 ሜትር)፣ እንዲሁም ግማሽ ማራቶንን ጨምሮ ባሉት ርቀቶች በመወዳደርና ከ250 በላይ ተሳትፎ በማድረግ በአንደኛነት ያጠናቀቀው ምሩፅ ይፍጠር፣ ከኦሊምፒክ ድርብ ድሎቹ በተጨማሪ አህጉሮች በሚካፈሉበት የዓለም አትሌቲክስ ዋንጫ በ1969 እና በ1971 ዓ.ም. በ5,000 እና በ10,000 ሜትር ለአፍሪካ አራት የወርቅ ሜዳሊያዎች ማስገኘቱ ይታወቃል፡፡