ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ሆነው ጳጉሜን 5 ቀን 2005 ዓ.ም. በቦነስ አይረስ፣ አርጀንቲና በተመረጡበት ዕለት ከወቅቱ ፕሬዚዳንት ዣክ ሩገ ጋር፤ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን፣ የአፍሪካ ስፖርት ኮንፌዴሬሽኖች ማኅበር ፕሬዚዳንት፣ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ የፊፋ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ፤ የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የአፍሪካ ስፖርት ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ፀጋው አየለና አዲሱ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴ፡፡
19 Nov, 2016 ከሦስት አሠርታት በፊት በወቅቱ የዓለም እግር ኳስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር-ፊፋ ፕሬዚዳንት ለነበሩት ብራዚላዊው ጆኦዎ ሃቨላንጅ (1908-2008) ጋዜጠኞች ‹‹ከርስዎ በኋላ የፊፋ ፕሬዚዳንት ማን ይሆናል? እርስዎን የሚተካው ማነው?›› ብለው ለጠየቋቸው የሰጡት ምላሽ ባጭር ቋንቋ ‹‹ሚስተር ተሰማ ነዋ!›› ብለው በወቅቱ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) ፕሬዚዳንት፣ እንዲሁም የአፍሪካ ስፖርት ኮንፌዴሬሽኖች ማኅበር ፕሬዚዳንትና የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ (1914-1979) ለቦታው እንደሚመጥኑ ተናግረው ነበር፡፡
ሃቨላንጅ ያለምክንያት አልነበረም እኚህን ታላቅ ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ የስፖርትና የኦሊምፒክ ግንባር ቀደም መሪ ይድነቃቸው ተሰማን ያጩት፡፡ የኢትዮጵያን ዘመናዊ ስፖርት ያደራጁ ልዩ ልዩ ሕጎችንና መተዳደሪያ ደንቦችን በአማርኛ ያዘጋጁ ለአፍሪካም የተረፉ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴን ትክክለኛ መስመር ያስያዙ፣ የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖካ) ብቻ ሳይሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ብሔራዊ ኢሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖክ) ህልውና የተጉ፣ የአፍሪካን የተለያዩ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን ያስተሳሰረው የአፍሪካ ስፖርት ኮንፌዴሬሽኖች ማኅበር የቆረቆሩ በመሆናቸው ሥራዎቻቸው ‹‹ፕሮዤ ተሰማ›› ለመባል የበቁ ነበር፡፡
ሃቫላንጅ ያኔ ይድነቃቸውን ለፊፋ ፕሬዚዳንትነት ሲያስቧቸው ለጥቆማቸው አክብሮታቸውን የገለጹት አቶ ይድነቃቸው፣ በጤና ምክንያት እንደማያስቡት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ኢትዮጵያውያን በአህጉራዊ ስፖርት አመራር
በመጨረሻው የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት (1923-1967) ሆነ በኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ መንግሥት (1967-1979) ዘመኖች፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የስፖርት ፌዴሬሽኖች፣ በአፍሪካ የተለያዩ ኮንፌዴሬሽኖች፣ በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) የአመራርነት እንዲሁም በተለያዩ ኮሚቴዎች በአባልነት ተሳትፎዋ ትታወቅ ነበር፡፡
በዘመነ ይድነቃቸው በአህጉሪቱ የተለያዩ ኮንፌዴሬሽኖች ኢትዮጵያውያን በአህጉራዊው አመራር ውስጥ ነበሩ፡፡ ለምሳሌ አቶ ታደለ መለሰ የአፍሪካ አትሌቲክስ ኮንፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ አቶ ሰሎሞን በቀለ የአፍሪካ ብስክሌት ኮንፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንትና የምሥራቅና መካከለኛው አፍሪካ ብስክሌት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡ ከአቶ ይድነቃቸው ቀጥሎ የአካል ማሠልጠኛና ስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ ፀጋው አየለ፣ የአፍሪካ ስፖርት ከፍተኛው ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ፣ የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖካ) ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት ነበሩ፡፡
አቶ ፀጋው በስፖርትና በኦሊምፒክ መድረኮች ላበረከቱት የላቀ አስተዋጽዖ፣ በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይሁንታ አግኝተው በወቅቱ ፕሬዚዳንት ጁዋን ኦቶንዮ ሳማራንሽ አማካይነት፣ የአገሪቱ ርእሰ ብሔር ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም በተገኙበት የኦሊምፒክ ኦርደር ሜዳይ መሸለማቸው ይታወቃል፡፡ አቶ ፀጋው በአህጉር ደረጃ የአመራር ቦታ መያዝና የአይኦሲ ቀልብም እሳቸው ላይ ማረፍ ሲጀምር፣ እንደ አቶ ይድነቃቸው፣ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል ሆነው ለመታጨት በሩ የሚከፈትላቸው ጊዜ ሩቅ እንደማይሆን ተስፋ ያደረጉ ጥቂት አልነበሩም፡፡
ይሁን እንጂ ደርግ፣ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክን (ኢሕዲሪ) በ1980 ዓ.ም. ሲመሠርት፣ ቀደም ብሎ በአደረጃጀት ራሱን ችሎ የነበረው ስፖርት ኮሚሽን ፈርሶ ከባህል ጋር ሲቀላቀልና ባህልና ስፖርት ጉዳይ ሚኒስቴር ሲባል፣ ኮሚሽነር ፀጋው አየለ ከቦታው ተነስተው የአካባቢ ጉዳዮች ሚኒስትርነት በመሾማቸው ከስፖርቱና ከኦሊምፒኩ ተፋቱ፡፡
በአህጉር ደረጃ በስፖርቱም ሆነ በኦሊምፒክ አመራርነት ለመመረጥ በቀላሉ የማይገኘውን ክብር ያገኘችው ኢትዮጵያ መንበሩን አጣች፡፡ ሌሎች ያሰፈሰፉት ጨበጡት፡፡
በስፖርት ተወልዶ በስፖርት ውስጥ ያለፈን፣ በወወክማ ኢትዮጵያ በልዩ ልዩ ተግባሮች የተሳተፈና እስከ ዋና ጸሐፊነት የደረሰ፣ የኢትዮጵያ ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ፣ በስፖርት ኮሚሽን የውድድር ስፖርቶች መምሪያ ኃላፊ የነበረ፣ በኋላም ኮሚሽነርና ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንትነት ደረጃ የደረሰን ኢትዮጵያዊ፣ ለአህጉር አመራርነት ብሎም ለዓለም በሚንደረደርበት ጊዜ ማቆም ለምን? አሰኝቶ ነበር፡፡
ከሩብ ምታመት በፊት የተደረገውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ፣ የስፖርት ፌዴሬሽኖችን የሚመሩት አባላት የሚመርጡበት ሒደት፣ ስፖርቱን በተለይም ክለቦችን ማዕከል ያደረገ ባለመሆኑና ባመዛኙ ከስፖርቱ ጋር ትውውቅ የሌላቸው መሆኑ፣ ባለፉት ዓመታት የታዩት ውጣ ውረዶች፣ በተለይ በእግር ኳስ ፌዴሬሽን ውስጥ ተፈጥሮ የነበረው ቀውስ በፊፋ እስከ መታገድ የተደረሰበት ገጽታ ይነሳል፡፡
በእግር ኳስና በአትሌቲክስ በምሥራቅና መካከለኛ አፍሪካ ደረጃ ለአመራርነት በቅተው የነበሩት ዶ/ር አሸብር ወልደጊዮርጊስና ወ/ሮ ብስራት ጋሻውጠና ይጠቀሳሉ፡፡ ዶ/ር አሸብር የካፍ ምክትል ፕሬዚዳንትነት ሊበቁ የሚችሉባቸው አጋጣሚዎች ቢፈጠርላቸውም በአገር ቤት የተፈጠረው ውዝግብ እንዲያመልጣቸው ማድረጉ ይነገራል፡፡
ብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንን ለስምንት ዓመታት በመምራት ልምድ ያካበቱትና ለክፍለ አህጉራዊው ኮንፌዴሬሽን መሪነት በቅተው የነበሩት ወ/ሮ ብሥራት ጋሻው ጠና፣ በአህጉራዊው ኮንፌዴሬሽን በተለይም ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ምክር ቤት አባልነት ታጭተው፣ የውድድር ጊዜውን እየጠበቁ ሳለ ከብሔራዊው ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንትነት እንዲነሱ መደረጉ ዋጋ አስከፍሏል፡፡
ከርሳቸው ጋር ተፎካካሪ የነበሩት የሌሎች አገሮች ዕጩዎች በቀላሉ ለመመረጥ አስችሏቸዋል፡፡ ኢትዮጵያ በአትሌቲክስ በተለይም በረዥም ርቀትና በማራቶን ገናና ስም ያላት መሆኑ ሥጋት ፈጥሮባቸው ነበር፡፡ ‹‹ባለቤቱ ያቀለለውን…›› እንዲሉ የኢትዮጵያ ዕድል አምልጧል፡፡
በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴና በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን፣ እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት በልዩ ልዩ ቦታዎች ያገለገሉትና እያለገሉ ያሉት የቀድሞው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ፣ ሃቻምና (2007 ዓ.ም.) ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ በወ/ሮ ብሥራት ላይ የተፈጸመውን ድርጊት ተችተው ነበር፡፡ እንዲህ ሲሉ፡-
‹‹በኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተደረገውን ብንመለከት፣ ወ/ሮ ብሥራት ለትልልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት አመራርነት የሚያበቃቸውን መንገድ ሲጀምሩ ነው እንዲነሱ የተደረገው፡፡ ከአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ጀምሮ በየደረጃው በሚገኙ ዓለም አቀፍ የስፖርት ተቋማት ውስጥ፣ ኢትዮጵያውያን የሚገቡበትን ሁኔታ ተነስቶ ውይይት ሲደረግ፣ ቋሚ ሰው እንደማያገኙ ነው ድምዳሜ ላይ የሚደርሱት፤ ለኔም ተደጋግሞ የሚነገረኝ ይኸው ነው፡፡ ይኼ ችግር ሥር የሰደደ ነው፡፡›› ይሄ ሥር የሰደደው ችግር አቶ ፀጋው አየለ ከተነሱበት ከ1980 ዓ.ም. የጀመረ ነው፡፡ ወ/ሮ ብሥራት በምን ምክንያት እንደተነሱ እንኳ አልተነገረም፡፡ ‹‹ክልሉ ውክልናዬን አንስቻለሁ፤›› ማለቱ ብቻ ነበር የተሰማው፡፡
‹‹ብቸኛዋ ኢትዮጵያዊት››
ኢትዮጵያ በአሁን ወቅት በዓለም አቀፍና በአህጉር፣ እንዲሁም በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ በአመራርነትና በአባልነት ያላት ወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ባድሚንተን ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ ዳግማዊት፣ የአፍሪካ ባድሚንተን ኮንፌዴሬሽን ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖክ) ሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ናቸው፡፡ ከጳጉሜን 5 ቀን 2005 ዓ.ም. ወዲህ ደግሞ የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ በግል አባል ሆነዋል፡፡ (ጳጉሜን 5 ቀን በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ ልዩ ቦታ አላት፤ አበበ ቢቂላ በሮም ኦሊምፒክ ማራቶን ድል ያደረገው ጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም. ነበር)፡፡ ቀደም ሲልም በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊነታቸው በኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባልነት ሲሠሩ ነበር፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያን ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንት፣ ፕሬዚዳንትና ዋና ጸሐፊነት ከማገልገላቸው በተጨማሪ፣ አቶ ፀጋው አየለ በተቀዳሚ ምክትል ፕሬዚዳንትነት መርተውት በነበረው የአፍሪካ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴዎች ማኅበር (አኖካ)፣ የሥራ አስፈጻሚ ቦርድ አባል ሆነው አገልግለዋል፡፡
የነ ኃይሌ ገብረሥላሴ አብዮት ይቀጥል ይሆን?
በብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ለዘመናት የአመራርነት ቦታን ያጡት አትሌቶች ዘንድሮ ባስነሱት ‹‹አብዮት›› መንበሩን ጨብጠውታል፡፡ ፌዴሬሽኖች የክለቦች መሆኑን ያሳየው 20ኛ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ጉባኤ፣ ሻለቃ ኃይሌ ገብረሥላሴን ፕሬዚዳንት፣ ገብረእግዚአብሔር ገብረማርያምን ምክትል ፕሬዚዳንት አድርጎ መርጧል፡፡ ሁለቱም በአትሌቲክሱ ውስጥ ያለፉና የላቀ ደረጃ ላይ የደረሱ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ለበርካታ ዓመታት በብሔራዊ ፌዴሬሽን አመራር ውስጥ የአዲስ አበባ አትሌቲክስ ክለቦች ሳይኖራቸው ቆይቶ ለመጀመሪያ ጊዜ ሁለት ባለሙያዎችን ሻለቃ ኃይሌና ዶ/ር በዛብህ ወልዴን በዘንድሮው ምርጫ አስገብተዋል፡፡ ዶ/ር በዛብህ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የቀድሞ ዋና ጸሐፊ የነበሩ ሲሆን፣ በተሰናባቹ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ በአባልነት የተሰየሙት ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት ዘብጥያ በመውረዳቸው ነበር፡፡
እነ ሻለቃ ኃይሌ ወደ አመራርነት መምጣት ባላቸው ገናና ስም አማካይነት ወደ አህጉራዊና ዓለማቀፋዊ የስፖርትና ኦሊምፒክ ተቋማት የመግባት የመመረጥ ዕድላቸው እንደሚሰፋ ይታመናል፡፡
የብሔራዊ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የምርጫ ሒደት ፋና ወጊ ሆኖ በሌሎችም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች እንዲንፀባረቅ የሚፈልጉ ለየስፖርቱ ልዕልና ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ በተለየ ታዋቂ በሆነችባቸውና በአህጉር ደረጃ ኮንፌዴሬሽንን በመመሥረት ከታወቀችባቸው የአህጉርና የዓለም አመራርነት ለመመለስ በር እንደሚከፍትላት ነው፡፡