ኢትዮጵያን ከ1928 እስከ 1933 ዓ.ም. ድረስ ወርሮ የነበረው የኢጣሊያ ፋሺስት ሠራዊት፣ ድል የተመታበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ የድል በዓል ምክንያት በማድረግ ሦስት የውጭ አገር ዜጎችን ጨምሮ ለ25 ታላላቅ አርበኞች የመታሰቢያ ቴምብር ታተመላቸው፡፡
የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ድርጅት ‹‹የኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች 75ኛ ዓመት መታሰቢያ የድል በዓል›› በሚል ርእስ ያሳተመው ስድስት ዓይነት ቴምብሮችን ኅዳር 1 ቀን 2009 ዓ.ም. በመላ አገሪቱ አሠራጭቷል፡፡
አምና በሚያዝያ 2008 ዓ.ም. የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር የድሉን አልማዛዊ ኢዮቤልዩ በብሔራዊ ደረጃ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ሲያከብር አንዱ እቅዱ የአርበኞች መታሰቢያ ቴምብር ማሳተም ነበር፡፡
እንደ ማኅበሩ መግለጫ፣ በቴምብሮቹ ላይ እነማን ይካተቱ በሚለው ጉዳይ ዙሪያ የማኅበሩ የሥራ አመራር ምክር ቤት መክሮና ዘክሮበት በስማቸው ቴምብር እንዲታተምላቸው ከብዙዎቹ መካከል የመረጣቸው 25 ናቸው፡፡ በአንድ ቴምብር ላይ ከአራት እስከ ስድስት አርበኞችን የሚወክሉ ምስሎችን ወጥተዋል፡፡
በመስፈርቶቹ መሠረት ከተመረጡት አርበኞች መካከል ከሃይማኖታዊ ታላቅ ተልዕኮአቸው በተጨማሪ የአርበኝነት ግዳጅን በመወጣት በጀግንነት የሕይወት መስዋዕትነት የከፈሉት የምዕራብ ኢትዮጵያ ጎሬ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሚካኤልና የምሥራቅ ኢትዮጵያ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስ በመታሰቢያው ቴምብር ተካትተዋል፡፡
እንዲሁም ጠላትን ፊት ለፊት ተጋፍጠው የሕይወትና የአካል መስዋዕትነት እየከፈሉ ካርበደበዱት መካከል ራስ ደስታ ዳምጠው፣ ደጃዝማች ኃይሉ ከበደ፣ ልዕልት ከበደች ሥዩም መንገሻ (እመቤት ሆይ)፣ ደጃዝማች በላይ ዘለቀ፣ ደጃዝማች ኃይለማርያም ማሞ፣ ደጃዝማች ገረሡ ዱኪ፣ ደጃዝማች ባልቻ አባ ነፍሶ፣ ደጃዝማች አፈወርቅ ወልደሰማያት፣ ፊታውራሪ ዓለማየሁ ጎሹ፣ ሼህ ሆጄሌ አልሃሰን፣ ደጃዝማች ፍቅረማርያም አባተጫንና ኮሎኔል በላይ ኃይለአብ ይገኙበታል፡፡
በጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዚዳንትነት ካገለገሉት መካከል፣ ሁለቱ ቀዳሚዎች ራስ አበበ አረጋይና ራስ መስፍን ስለሺ፤ በፋሺስቱ ሩዶልፍ ግራዚያኒ ላይ የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም. አደጋ የጣሉት አብርሃ ደቦጭ፣ ሞገስ አስገዶምና ስምዖን አደፍርስ፣ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በፋሺስቶች ሲዋረድ፣ መቀበል አቅቷቸው በሮም አደባባይና በኢጣሊያ በረሃዎች ታላቅ ገድል የፈጸሙት ደጃዝማች ዘርዓይ ድረስና ኮሎኔል አብዲሳ አጋ በየቴምብሮቹ ምስላቸው ታትሟል፡፡
የፋሺስቶች ወረራ አስቆጥቷቸው በአርበኝነት ተጋድሎ ከኢትዮጵያ ጐን ለቆሙ የውጭ ዜጐች እንግሊዛውያኑ ሲልቪያ ፓንክረስት፣ ሜጀር ጀነራል አርዲ ቻርለስ ዊንጌትና አሜሪካዊው ኮሎኔል ሲ ሮቢንሰንም የመታሰቢያ ቴምብሮቹ አካሎች ናቸው፡፡
በወቅቱ በነበረው የመንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) መቀመጫ ጄኔቭ በመገኘት፣ ለዓለም መንግሥታት አቤቱታቸውን ያሰሙት ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923-1967) ዲስኩር ሲያሰሙ የተነሱት ፎቶም የኅትመቱ አካል ነው፡፡ ከ80 ዓመታት በፊት፣ ሰኔ 23 ቀን 1928 ዓ.ም. ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በሸንጎው ላይ ካደረጉት ዲስኩር የሚከተለው ኃይለ ቃል ይገኝበታል፡፡
‹‹… ከእግዚአብሔር መንግሥት በቀር የፍጡር መንግሥት ሁሉ አንዱ ከአንዱ የማይበልጥ ሥራ የለውም፡፡ ነገር ግን በምድር ላይ ኃይለኛ የሆነው መንግሥት ምንም በደል የሌለበትን የሌላውን መንግሥት ሕዝብ ለማጥፋት የሚገባው መስሎት በተነሳበት ጊዜ ተጠቂው ወገን ለመንግሥታት ማኅበር የተበደለውን የሚያቀርብበት ሰዓት ነው፡፡ እግዚአብሔር ታሪክ ለምትሰጡት ፍርድ ለመንግሥት ማኅበርም ምስክር ሆነው ይመለከታሉ…››
የጥንታዊት ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ‹‹እኔ ለሀገሬ›› በሚል ርእስ ባዘጋጀው፣ የ75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ የድል በዓል መታሰቢያ ቴምብሮች መግለጫው ላይ እንደተወሳው፣ በመታሰቢያ ቴምብሩ ላይ ምስሎቻቸው እንዲወጣ የተደረጉት አርበኞች አመራረጥ፣ ‹‹በተቻለ መጠን ሚዛናዊ የሆነ ኅብረ ብሔራዊና የጾታ ስብጥርን ከግንዛቤ ውስጥ ያስገባ ነው፡፡››
ይሁን እንጂ ከ25ቱ አርበኞች መካከል ሴት አርበኛ አንድ ብቻ መሆናቸው ለምን? ያሉ አልታጡም፡፡ በአምስቱ ዘመን በተለያዩ ግንባሮች በውጊያው አውድማ ውስጥ ከዘመቱት በሺዎች ከሚቆጠሩት ሴቶች መካከል አንዲት አርበኛ ልዕልት ከበደች ሥዩም ብቻ ለቴምብሩ በቅተዋል፡፡
ሌላው ቢቀር ማኅበሩ ለአልማዝ ኢዮቤልዩ መታሰቢያ ባሳተመው ‹‹እኔ ለሀገሬ›› መጽሔት ጀግንንታቸው የተዘረዘረላቸው ፊታውራሪ በላይነሽ ገብረ አምላክ ሁለተኛዋ ለመሆን ለምን አልታደሉም?
በ1928 ዓ.ም. በምሥራቅ ግንባር ሰርጎ የገባው የፋሺስት ወራሪን ፊታውራሪ በላይነሽ ገብረ አምላክ ሱሪ ታጥቀው፣ ዝናር ታጥቀው ብረት አንግተው ተፋልመዋል፡፡ ከፊታውራሪ በላይነሽ ጋር ከ15 ዓመታት በፊት ቃለምልልስ ባደረገው ‹‹እኔ ለሀገሬ›› መጽሔት አገላለጽ፣ ከወረራው 10 ዓመት በፊት ያረፉትን የአባታቸውን ፊታውራሪ ገብረአምላክ ውብነህ ማዕረግን የያዙት ፊታውራሪ በላይነሽ፣ ከድል በኋላ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘንድ በቀረቡበት ጊዜ፣ ጃንሆይ ‹‹ጄኔቭ በነበርንበት ጊዜ፣ በላይነሽ የምትባለው ሴት ትዋጋለች እየተባለ የምንሰማው እሷን ነው?› ብለው ጠየቁ፡፡ ደጃዝማች ይገዙም ‹አዎ› ብለው አቀረቡኝ፡፡ ጃንሆይም በፈገግታ ተቀበሉኝ፡፡ ‹አለሽ እንዴ! ማን ትባያለሽ?› አሉኝ፡፡ እኔም፣ ‹ፊታውራሪ በላይነሽ ነኝ› አልኳቸው፡፡ ‹በስምሽ ተጠሪበት› ብለው ሹመቱን አፀደቁልኝ፡፡››
ፋሺስት ኢጣሊያ ኢትዮጵያን ሲወር ባለቤታቸው በጅጅጋ በኩል ወደ ጂቡቲ ለስደት እንዲሄዱ ቢገፋፏቸው አገራቸውን ትተው እንደማይሄዱና ተጋድሏቸውን እንደሚቀጥሉ ነግረዋቸው የተለዩዋቸውን እኚህን እርመኛ አርበኛ የቴምብሩ ገበታ ሊረሳቸው ባልተገባ ነበር፡፡
አደራ ተረካቢ ወካይ የሆኑ ወጣቶችን ጨምሮ በስድስት ዓይነት የታተሙት 600 ሺሕ ቴምብሮች ሲሆኑ፣ የያንዳንዱ ዋጋም ከ1 ብር እስከ 1.50 ብር መሆኑ ታውቋል፡፡   
በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን (1888 ዓ.ም.) ዓድዋ ላይ ድል የተመታው የኢጣሊያ ወራሪ ሠራዊት፣ ከ40 ዓመት ቆይታ በኋላ በፋሺስቱ ቤኔቶ ሙሶሎኒ አማካይነት ኢትዮጵያን መውረሩና በተለይ በዓለም የተከለከለው የመርዝ ጋዝ በመጠቀም የኢትዮጵያን ሠራዊት በ1928 ዓ.ም. መፈታቱ ይታወሳል፡፡
እርመኛ አርበኞች የአገሪቱን ነፃነት ለማስከበር የሕዝቡን ልዕልና ለማስጠበቅ መራር ተጋድሎ ማድረጋቸውም ባይዘነጋም የፋሺስት ወንጀለኞች በታኅሣሥ 1928 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ሠራዊት የፈቱበት፣ በተምቤንና በሐሸንጌ በመርዝ ጋዝ ያደረሱት እልቂት ይጠቀሳል፡፡
ከሰባ አምስት ዓመታት በፊት የድሉን ብሥራት አስመልክተው ባለቅኔው የእንጦጦ ራጉኤሉ ብርሃኑ ድንቄ (ከስድስት አሠርታት በፊት በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩ) ግእዝ ከአማርኛ አጣቅሰው እንዲህ ተቀኝተው ነበር፡-
‹‹ኢትዮጵያ ከማር ለሚጣፍጥ ለስምሽ አጠራር ሰላም ይገባል፡፡
ባምላክ እጅ ለተሠራ ለራስ ፀጉርሽም ሰላምታ ይገባል፡፡
ምሳሌ የሌለሽ መቅደስ ኢትዮጵያ፤
ጠላት ኢጣሊያ ስላረከሰሽና መሠዊያሽን ስላጠፋ ፈንታ፣
ከእንግዲህ ወዲህ ተቀደሽ፣ ኃይልንም ገንዘብ አድርጊ፡፡››
እኚሁ ሊቀ ሊቃውንት ብርሃኑ ድንቄ እንዲህ እያሉም ዘመሩላት፡፡
‹‹እናታችን ኢትዮጵያ ሆይ
ለታረዙ ልብስ ነሽና
በባንዲራሽ ጥላ ሰብስቢ ልጆችሽን!››