አዲሱ የ2009 ዓ.ም. እንደ ቀደሙት ዓመታት በዓል በዓል በሚሉ ዘፈኖች አልደመቀም? ይልቁንም አምና የተጀመረውን ሕዝባዊ ተቃውሞ የሚያስተጋቡ ሙዚቃዎች ተደመጡ፡፡ በሕዝባዊው ተቃውሞ ሕይወታቸውን ባጡ ሰዎች ሐዘን ምክንያት ለዕንቁጣጣሽ የታቀዱ ኮንሰርቶች ተሰርዘዋል፡፡ ድምፃውያን ትኩረታቸውን ከኮንሰርቱ ይልቅ በአገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ወደሚያሳስቡ ዘፈኖች ያዞሩ ይመስላል፡፡ ከሙዚቃዎቹ የይሁኔ በላይ ‹‹ሰከን በል›› ይጠቀሳል፡፡
‹‹ተው በለው
ማንነቴን ብሎ አደባባይ ወጥቶ
ባዶ እጁን እያየው
ሲያልፍ ለሚያልፍ ቀን
ወንድሙን ወንድሙ አልሞ ገደለው. . .
ሰከን በል. . .
ሰከን ማለት መውጫ አላት
ሰከን ማለት ነው ጀግንነት
ወታደሩ ሰከን በል
አፈሙዙን ሰከን አርገው
ባዶ እጁን ነው የሚጮኸው
ሰላማዊ ወንድምህ ነው…››
ዘፈኑ የሕዝብ ጥያቄ እንዲመለስና ነገሮች በመግባባት እንዲካሄዱ ይጠይቃል፡፡ በዘርና ቋንቋ መለያየት ቀርቶ፣ ፍቅርና መተሳሰብ እንዲነግሥም ያሳስባል፡፡ ዘፈኑ የተለቀቀው አዲስ ዓመት አካባቢ እንደመሆኑ ድምፃዊው የዘንድሮ ዓመት የተረጋጋ እንዲሆን ይመኛል፡፡ የናትናኤል አያሌው (ናቲ ማን) ‹‹አሁን ተነካሁ›› ተመሳሳይ ይዘት አለው፡፡ በሕዝቡ መካከል አንድነት እንዲኖርና ዜጎች እንዲከበሩ በሙዚቃው ይጠይቃል፡፡
‹‹. . .ወገኔን ሲከፋው አሁን ተነካሁ
የኔ ቤት ሲንኳኳ ካንተ ቤት ይዘልቃል
አፍንጫ ሲነካ ዓይንኮ ያነባል
ሰብስቦ ያቆየን፤ ይህ ነበር ወጋችን
ዛሬም በአንድ ይሁን ሐዘንም ደስታችን. . .››
የአገሪቱን ፖለቲካዊ ሁኔታ ያማከሉ ዘፈኖች ለኢትዮጵያ ታሪክ አዲስ አይደሉም፡፡ ሙዚቃ መነሻውን ማኅበራዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ እውነታ ያደርጋልና የኢትዮጵያ ሙዚቃዎችም የየዘመኑ መስታወት ናቸው፡፡ ሙዚቃን ጨምሮ በሌሎችም ኪነ ጥበባዊ ሥራዎች ዘመንን አሻግሮ መመልከት ይቻላል፡፡ የየወቅቱን ሥርዓት የሚተቹ ወይም የሚደግፉ ዘፈኖች ተደምጠዋል፡፡ ሙዚቀኞች ያሉበትን ወቅት ከመግለጽ ባሻገር ለወደፊት ሊሆን የሚችለውን እንደ ርዕይ ያስቀመጡበትም ጊዜ አለ፡፡
ድምፃውያን በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የሕዝብን ድምፅ አስተጋብተዋል፡፡ እያስተጋቡም ነው፡፡ ሙዚቃ ሕዝብን ለማስተባበር እንዲሁም አንዳች አቅጣጫ ለማመላከትም ይውላል፡፡ ከድምፃውያን ጀርባ ያሉ የግጥምና ዜማ ደራሲዎች በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በሙዚቃ መልዕክት ያስተላልፋሉ፡፡ ሙዚቀኞች የግል  አቋማቸውንና የሕዝቡንም የልብ ትርታ ሲያሰሙ ድጋፍና ተቃውሞም ያገኙባቸው አጋጣሚዎችን ታሪክ ያስነብባል፡፡ መወደድና መሞገስ እንዳለ ሁሉ መታሰር፣ ከአገር መሰደድና መገደልም የደረሰባቸው አሉ፡፡ ባለፉት ሁለት ሥርዓቶችና በአሁኑም ፖለቲካውና መዚቃ ያላቸውን መስተጋብር እንዲሁም ከሕዝቡና ከመንግሥት የተሰጣቸውን ምላሽ መመልከት ይቻላል፡፡
በዘፈን ግጥምና ዜማ እንዲሁም በተውኔት ድርሰትና ዝግጅት የሚታወቀው ተስፋዬ አበበ (ፋዘር) በየዘመኑ ፖለቲካና ሙዚቃ ሲዋሃዱ የሚሰጣቸው ምላሽ ተመሳሳይነት እንዳለው ይናገራል፡፡ መንግሥታት መተቸት ስለማይፈልጉ ሙዚቃውን በተለያየ መንገድ ለመቆጣጠር ሲሞክሩ፣ በተቃራኒው ሕዝቡ በሙዚቃዎቹ ይደሰታል፡፡
በንጉሡ ጊዜ፣ ንጉሡን ከሚያወድሱ ሥራዎች ውጪ ያሉት በቅድመ ምርመራ እንዲወድቁ ይደረጋል፡፡ ‹‹ቅድመ ምርመራ አድራጊዎቹ ቅኔ አዋቂዎች በመሆናቸው በወርቅና ሰም መልክም መልዕክት ማስተላለፍ አይቻልም፤›› ይላል ባለሙያው፡፡ ሕዝቡን ይቀሰቅሳሉ የሚባሉ ሙዚቃዎችን የማስቆም ሒደት በፖሊስ ሠራዊት፣ ክብር ዘበኛና የምድር ጦር ሙዚቃ ክፍልም ተመሳሳይ እንደነበር ይናገራል፡፡
የሶሻሊዝም ርዕዮት በሚራመድበት የደርግ ሥርዓት ነገሮች ቢሻሻሉም፣ መንግሥትን የሚነኩ ሙዚቃዎች ተቀባይነት አልነበራቸውም፡፡ ‹‹ሥርዓቱ ኅብረተሰቡን ስለሚያቅፍ ሙዚቃው ያደገበት ዘመን ቢሆንም ምንጊዜም ገዥዎች የራሳቸው ዕድፍ ሲነካ ስለማይወዱ ያኔም ችግር ነበር፤›› ይላል፡፡
ወደ ኢሕአዴግ ሲመጣ በቀደሙት ጊዜያት የነበረው ቅድመ ምርመራ መልኩን ለውጦ በግምገማ መልክ ቢመጣም፣ ጥቂት ሙዚቃዎች ይህን አልፈው ሲወጡ ይታያል፡፡ በዚህ ወቅት የመናገርና የመጻፍ ነፃነት በሕገ መንግሥቱ ቢሰጥም ይዘታቸው የማይፈለግ ሙዚቃዎች ጫና ይደረግባቸዋል፡፡ ‹‹ጥበብና ፖለቲካ እስከመጨረሻው እየተናቆሩ ይኖራሉ፤›› የሚለው ተስፋዬ፣ ሙዚቀኞች የሚያስተላልፉት መልዕክት መደመጥ እንዳለበት ‹‹መንግሥታት ራሳቸውን ለኪነ ጥበብ ማስገዛት አለባቸው፤›› ብሎ ይገልጻል፡፡ በሙዚቃ የሕዝቡን ስሜት መረዳት እንደሚቻልና የለውጥ መሣሪያ ማድረግ እንደሚቻል ያክላል፡፡
በሙዚቃ ግጥሞቹና በቴአትር ጽሑፎቹ የታሰረባቸውና ሥራዎቹ የታገዱባቸው ወቅቶች ብዙ ቢሆኑም፣ የሕዝብን ድምፅ ለማስተጋባት በሠራቸው ሙዚቃዎች ደስተኛ ነው፡፡ ‹‹ሙዚቃን ተዋግተንበታል›› ይላል ዘመኑን ሲገልጽ፡፡ በ1957 ዓ.ም. ለጦር ሠራዊቱ የሚከፈለው ደመወዝና የሥራ ጫናው አለመመጣጠኑን ለመግለጽ ዓለማየሁ እሸቴ የተጫወተውን ዘፈን ደረሰ፡፡
‹‹. . .የእዬዬ ወሸኔ የዋኔ ጭፋሮ
በእከክ መሰንቆ ውርደት እንጉርጉሮ
የፎከት ዳንኪራ የስቃይ ከበሮ
እዛ ሞላ ሞላ ለአምና ዘንድሮ. . .››
በወቅቱ ይህ ዘፈን ግጥሙ ካልተቀየረ ለጦር ሠራዊቱ እንደማይቀርብ ተገለጸለት፡፡ ለመቀየር ተስማማና መድረክ ሲመራ የተቀየረውን ግጥም አስተዋወቀ፡፡ ዓለማየሁ አንዴ መድረኩን ካገኘ በኋላ የመጀመርያውን ግጥም እንደሚዘፍን ተመካክረው ነበር፡፡ ዓለማየሁ መዝፈን ከጀመረ በኋላ ዘፈኑ የተቀየረው ግጥም አለመሆኑን ያስተዋሉት የፀጥታ ኃይሎች፣ ተስፋዬን ወዲያው እስር ቤት አስገቡት፡፡ ሦስት ወር ታስሮ ተለቋል፡፡ የእሱን መሰልና የከፋም አጋጣሚ የነበራቸው ሙዚቀኞች ብዙ ናቸው፡፡
ሚውዚኮሎጂስቷ ዶ/ር ትምክህት ተፈራ ከ1967 እስከ 1983 ዓ.ም. የነበረውን ፖለቲካዊ ሁኔታና የሙዚቃውን ሚና በዳሰሱበት ጥናታቸው፣ በዘመኑ የፊውዳል ሥርዓትን የሚቃወሙ ፀረ ኢምፔሪያሊስት ሙዚቃዎች በሕዝቡ ተወዳጅ እንደነበሩ ይገልጻሉ፡፡ የሕዝብ ጭቆናን የሚቃወሙና የሠርቶ አደሩን ድምፅ የሚያሰሙ ሙዚቃዎችን መንግሥትም ይጠቀምባቸው ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በቀይ ሽብር ወቅት ገጽታውን ለውጦ ሥርዓቱን የሚደግፍ ሙዚቃ ለመሥራት ፈቃደኛ ያልሆኑ ሙዚቀኞች ይነጣጠርባቸው ጀመር፡፡
በጥናታቸው፣ ሙዚቃ በአገር ውስጥና በውጭም የነበረውን ሁኔታ ይከተል እንደነበር አመልክተዋል፡፡ ለምሳሌ በ1969ኙ የኢትዮጵያና ሶማሊያ ጦርነት ወቅት የኢትዮጵያ የጦር ሠራዊትን የሚያነሳሳ ሙዚቃ ጦር ግንባር ድረስ ሄደው ካሰሙት ድምፃውያን መካከል ጥላሁን ገሰሰ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ መሀሙድ አሕመድ፣ ዓለማየሁ እሸቴና ታምራት ሞላ ይጠቀሳሉ፡፡
በአገሪቱ ውስጣዊ ሁኔታ ረገድ በሕወሓት ንቅናቄ ሙዚቃ የነበረውን ሚና ሚውዚኰሎጂስቷ ይገልጻሉ፡፡ ኪሮስ ዓለማየሁና ገብረጻድቅ ወልደዮሐንስን የመሰሉ የትግርኛ ዘፋኞች ይጠቀሳሉ፡፡ ኪሮስ በሙዚቃዎቹ ለእስር ቢዳረግም፣ ቅኔ አዘል የተቃውሞ ዘፈኖቹን ከተፈታ በኋላም ቀጥሏል፡፡
የተቃውሞም ይሁን የድጋፍ ዘፈኖች በተለያዩ ቋንቋዎችም ተሠርተዋል፡፡ የሕዝብን ጭቆና በመቃወም ለለውጥ የሚያነሳሱ ዘፈኖች ከሚያቀነቅኑ የኦሮምኛ ዘፋኞች አሊ ቢራ ተጠቃሽ ነው፡፡ ከቀድሞቹ ኡስማዩ ሙሳና እልፍነሽ ኬኖ አሁን ደግሞ ሀዊ ተዘራና ጫላ ቡቱሜን ማንሳት ይቻላል፡፡ ከእነዚህ ድምፃውያን በተጨማሪ ሌሎችም የየአካባቢያቸውን ባህልና እሴት በማንፀባረቅ ቀስቃሽ ሙዚቃዎችን ያስደምጣሉ፡፡ በሌላ በኩል በአሁኑ ወቅት ከፍተኛ ቦታ ከሚሰጣቸው የመንግሥት ፕሮጀክቶች መካከል የሕዳሴ ግድብ ግንባታን ለመደገፍ የተሠሩ ሙዚቃዎች ይገኛሉ፡፡ የሰንደቅ ዓላማና የብሔር ብሔረሰቦች ቀንም በኅብረ ዝማሬዎች ታጅበው የሚከበሩ ናቸው፡፡ የሙሉ ገበየሁ ቅንብር የሆነው ‹‹ብሔር ብሔረሰቦች›› እና ‹‹ዓባይ ዓባይ›› ይጠቀሳሉ፡፡ ከ‹‹ዓባይ ዓባይ›› ስንኞች የሚከተለው ይገኝበታል፡፡
‹‹… እንጉርጉሮ ይብቃ፤ ይገባል ውዳሴ
ጉዞውን ጀምሯል ዓባይ በሕዳሴ
ትውልድ እንደ ጅረት የተቀባበለው
ቁጭት ፀፀት ሥጋት ዛሬ ሊቋጭ ነው
ቁጭት ፀፀት ሥጋት ሀይ ባይ ሊያገኝ ነው…››
የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፕሬዚዳንት የሙዚቃ አቀናባሪና ኪቦርዲስት ዳዊት ይፍሩ፣ በየዘመኑ የተሠሩ ፖለቲካዊ ይዘት ያላቸው ሙዚቃዎች ሰምና ወርቅ ይዘታቸውን የሚገነዘቡ በደፈናው የሚሰሙም እንዳሉ ይገልጻል፡፡ እንደ ምሳሌ የሚያነሳው የጥላሁን ገሠሠን ሙዚቃዎች ነው፡፡ ማስተላለፍ የፈለገውን መልዕክት የሚረዱም የማይረዱም አድማጮች አሉ፡፡ ‹‹ለአንዳንድ ሙዚቃዎች ሕዝቡ የራሱን ትርጉም እየሰጠ ያደምጣል፤›› ይላል፡፡ የጥላሁን ‹‹አልማዝን አይቼ› በሰምና ወርቅ ይዘቱ ይጠቀሳል፡፡
‹‹. . .አልማዝን አይቼ አልማዝን ባያት
ሦስተኛዋ አልማዝ ስትመጣ ድንገት
ሁለቱን አልማዞች ስላስረሳችኝ
ምርጫዬ በምርጫሽ ተበላሸብኝ. . .››
ሙዚቃው አልማዝ ስለተባለች ሴት ይምሰል እንጂ፣ በሌተና ጄኔራል አማን አምዶም፣ ብርጋዴዬር ጄኔራል ተፈሪ በንቲና ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም መካከል የነበረውን የሥልጣን ሽኩቻ የሚወርፍ ነው፡፡
ሙዚቀኛው አሁን የሚሠሩ ሙዚቃዎችን ከቀድሞዎቹ ጋር ሲያነፃፅር፣ ጥልቅ መልዕክት ያላቸው ሥራዎች ቁጥር እየቀነሰ መጥቷል ይላል፡፡ ይህ ደግሞ ሙዚቃው ለነባራዊው ፖለቲካዊ ሁኔታ ያለውን አስተዋጽኦ ውስን ያደርገዋል፡፡ የቀድሞ ሙዚቃዎች ይዘታቸው የየወቅቱን ሥርዓት መደገፍም ይሁን መንቀፍ ጠንካራ ነበሩ፡፡ በዳዊት እምነት፣ ዛሬ ከሚሠሩ ሙዚቃዎች አብላጫው ንግድ ተኮር ናቸው፡፡ በኅብረተሰቡ ዘንድ መልዕክት አዘል ሙዚቃ የሚሠሩ ድምፃውያንን በየጎራው የመፈረጅ ሁኔታም አለ፡፡ የሚደግፉትና የሚተቹት በተለያዩ ፓርቲዎች ጐራ ይፈረጃሉ፡፡ ‹‹ሙዚቀኛው ሐሳቡን በነፃነት የሚያስተላልፍበትና የማይፈረጅበት ሁኔታ መፈጠር አለበት፤›› ይላል፡፡
ሐሳቡን የሚጋራው በዜማ ማህሌት የሬዲዮ መርሐ ግብር የሙዚቃ ትንተናዎቹ የሚታወቀውና የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ፀሐፊ ማኅተመ ኃይሌ፣ ዛሬ ዛሬ ሙዚቀኞች የሕዝብን ስሜት የሚያንፀባርቁ ሥራዎች በብዛት የማይሠሩት ስለሚፈሩ ነው ብሎ ያምናል፡፡ ሙዚቀኞቹ በዘፈናቸው ሊደርስባቸው የሚችለውን በመገመት ግለ ቅድመ ምርመራ ያደርጋሉ፡፡ ‹‹የዘመኑ ሙዚቀኛ ራሱ በራሱ ላይ ቅድመ ምርመራ ያደርጋል፡፡ የቀድሞ ሙዚቀኞች በሥራዎቻቸው የደረሰባቸውን ጫና በማየትም ሊሆን ይችላል፤›› ሲል ይገልጻል፡፡
በባለሙያው ገለጻ፣ አንዳንዴ ከሙዚቃው መልዕክት ይልቅ ዘፋኙ ሥራውን ያቀረበበት ቦታ ላይ ሲተኮርበት ሁሉ ይስተዋላል፡፡ የት ቦታ ተገኝቶ ዘፈነ? በሚል ሙዚቀኞች ይመዘናሉ፡፡ ነገሩም ትርጉም ይሰጠዋል፡፡ ሙዚቀኞች ከኅብረተሰቡ ጋር ላለመጋጨት ራሳቸውን የሚያቅቡበት ጊዜም አለ፡፡ ማኅተመ ‹‹ሙዚቃ ብቻ ሳይሆን ኪነ ጥበብ ከፍርኃት ነፃ መሆን አለበት፡፡ መንግሥትም ሙዚቃም ከሕዝብ እንደመውጣታቸው የሕዝብን ስሜት መጋራት አለባቸው፤›› ይላል፡፡ ብልህ መሪ ሙዚቃ ከሚያስተጋባው የሕዝብ ድምፅ ትምህርት እንደሚወስድም ያክላል፡፡
የኢትዮጵያን ባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃ ከታሪካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ ዐውድ አንፃር የሚያትተው የስሜነህ በትረዮሐንስ ጥናት ላይ ከአዝማሪዎች ጀምሮ በዘመናዊው ሙዚቃ የሚጠቀሱ ሥራዎች ተዳሰዋል፡፡ በኢትዮጵያ የዘመናት የውስጥና የውጭ ጦርነት ቀረርቶ፣ ሽለላና ፉከራ የነበራቸውን ቦታ ይገልጻል፡፡ ‹‹አዝማሪ ምን አለ?›› የሚለው አባባል አዝማሪ የሕዝቡን ስሜት በማንፀባረቅ ያለውን ትልቅ አስተዋጽኦ ይጠቁማል፡፡ ያስተዋሉትን ኢፍትሐዊነትና የአስተዳደር ችግርን በቅኔ አዘል ሙዚቃ ያሰማሉ፡፡
‹‹አርሜ ኮትኩቼ ያሳደኳትን
መልከኛ ወሰዳት የሎሚ ዘንጌን
ወይ አለመታደል አይ ገባር መሆን››
የፊውዳል ሥርዓትን በመቃወም ከተቀነቀኑ አንዱ ነው፡፡ አዝማሪዎች በፋሺስት ጣልያን ወረራ ወቅት ለጦርነቱ የነበራቸው አስተዋጽኦም ቀላል አልነበረም፡፡ ጣልያኖችም አዝማሪዎች በሰምና ወርቅ ግጥማቸው ሕዝብን ያነሳሳሉ በሚል ሥጋት ይገድሏቸው ነበር፡፡
አጥኚው፣ በወቅቱ በየትምህርት ቤቱ፣ በፖሊስና በጦር ሠራዊት እንዲሁም በየቴአትር ቤቶቹ ሙዚቃዊ እንቅስቃሴ ማንሰራራቱን ያነሳል፡፡ በወቅቱ ምርታማነትን የሚያበረታቱ እንደ ‹‹እህል ዝሩ ቡና አብቅሉ›› ያሉ ዘፈኖች ይደመጡ ነበር፡፡ ከቀደምቱ ተሰማ እሸቴ፣ ፈረዳ ጎላና ንጋቷ ከልካይ ይጠቀሳሉ፡፡ የአሁኖቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር፣ ራስ ቴአትርና ሀገር ፍቅር ቴአትር አገራዊ መልዕክት ያላቸው ሙዚቃዎች ምንጭ ናቸው፡፡
ኪነቶች ሙዚቃ በፖለቲካው ያለውን ቦታ ከሚያሳዩ ምሳሌዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ በደርግ ወቅት የተስፋፉት ኪነቶች ከሚሠሩት ሙዚቃ አንፃር በፖለቲካው የነበራቸውን ተፈላጊነት ማንሳት ይቻላል፡፡ ‹‹ኪነት ለአብዮት፣ ኪነት ለትግል፣ ኪነት ለንቃት፣ ኪነት የሰፊው ሕዝብ መሣሪያ ነው፤›› የሚሉ መሪ ቃሎች በማስረጃነት ተቀምጠዋል፡፡ ከጥናቱ የመንግሥታት መለዋወጥ ለሙዚቀኞች ያለው አስተዋጽኦና ተፅዕኖውም በሙዚቃው እንደሚታይ መረዳት ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ሙዚቃና ፖለቲካዊ እውነታው ከተጠቀሱት የአገር ውስጥ ተመራማሪዎች በተጨማሪ የውጭ አጥኚዎችንም ትኩረት ሲስብ ይታያል፡፡ የኦስሎ ዩኒቨርሲቲ መምህርት ዶ/ር ክርስቲን ስካር ኦርገርት፣ በሙዚቃ ቅድመ ምርመራ ላይ የሠሩት ጥናት መነሻ ያደረገው የቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) ‹‹ያስተስርያል›› ዘፈንን ነው፡፡ ሙዚቃው ከ1997 ዓ.ም. ምርጫ በኋላ በሕዝቡ ላይ ስለፈጠረው ስሜት ገልጸዋል፡፡ ሙዚቃው በይፋ ባይታገድም በመገናኛ ብዙኃን እንዳይተላለፍ የተደረገ ጫና መኖሩም ተጠቅሷል፡፡ በዚህ ረገድ የፋሲል ደሞዝ ‹‹አለ ነገር››ንም ማንሳት ይቻላል፡፡ አንዳንድ ሙዚቃዎች በሚለቀቁበት ጊዜ ከሚሰጡት ትርጉም በላይ ቆየት ብሎ በሚፈጠር ሁኔታ ተደማጭነታቸው ሊጐላ ይችላል፡፡
ሙዚቃ ላይ ዕገዳ መጣል ወይም ቅድመ ምርመራ ማድረግ የብዙ አገሮች እውነታ መሆኑን ዶ/ር ክርስቲን ይናገራሉ፡፡ የፈጠራ ነፃነትን በሚፃረር መልኩ ሙዚቃዎች ሲታገዱ የሕዝቡ የማዳመጥ ፍላጎት ይጨምራል፡፡ ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት ሥጋት በሚል ምክንያት ብዙ መንግሥታት ማዕቀብ የሚጥሉባቸው ሙዚቃዎች በዓለም ተወዳጅ እንደሆኑም በጥናቷ አስቀምጠዋል፡፡
በተመሳሳይ በኬይ ኩፍማን ሾልሚ ለ16ኛው የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባኤ የተሠራው ጥናት በኢትዮጵያውያን ዳያስፖራዎች ሙዚቃ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ጥናቱ የሚያተኩረው አሜሪካ በሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ሲሆን፣ ሙዚቃ የአገሪቱን እውነታ በማንፀባረቅ በመካከላቸው ያለውን ትስስር ያጠናከረ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ በተለያየ ወቅት በፖለቲካው ምክንያት ከአገር የወጡ ሙዚቀኞች በያሉበት አቋማቸውን የሚገልጹ ዘፈኖች ይለቃሉ፡፡ አንድ ሥርዓት በሌላው ሲተካ ወደ ትውልድ አገራቸው የሚመለሱም አሉ፡፡
በጥቅሉ ሙዚቃ በየአገሩ ፖለቲካ የራሱን ሚና መጫወቱን ማየት ይቻላል፡፡ ኢፍትሐዊነት፣ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ሙስናና የመሪዎች ገደብ የለሽ ሥልጣን ተነቅፏል፡፡ ለሕዝባዊ ንቅናቄ መነሻና ማፋፋሚያ ውሏል፡፡ በደቡብ አፍሪካ ፀረ አፓርታይድ እንዲሁም በመላው አፍሪካ የፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል ሙዚቃ ሚና ነበረው፡፡ የነጮች የበላይነትን በመቃወም በአሜሪካው ሲቪል ራይትስ ሙቭመንት (የሰብአዊ መብት ንቅናቄ) ሙዚቃ መሣሪያ ነበር፡፡ ብሉዝና ሂፕ ሀፕም በዚህ ረገድ ይጠቀሳሉ፡፡ ቢሊ ሆሊደይ፣ ሳም ኩክና ኒና ሲሞን ዘረኝነትን ተቃውመው ዘፍነዋል፡፡ ሙዚቀኞች አቀንቃኝ (አክቲቪስት) የሆኑባቸው የኢትዮጵያም ይሁን የተቀረው ዓለም ሙዚቃ አገዝ ትግሎች ሙዚቀኞቹን ያስከፈለው መስዋዕትነት ከአስተዋፅኦው ተያይዞ በታሪክ ሰፍሯል፡፡