Saturday, October 8, 2016

የሰላም ግብረ ኃይል በማቋቋም ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ለመንግሥት ጥያቄ ቀረበ




በታምሩ ጽጌ
መንግሥት በአገራቸው ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ ወገኖች ጋር በመነጋገር የሕዝቡን ብሶትና ጥያቄ በአግባቡ በማዳመጥ ምላሽ እንዲሰጥና የሰላም ግብረ ኃይል በማቋቋም ብሔራዊ መግባባት እንዲፈጠር ተጠየቀ፡፡
ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የአገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና የንግዱ ማኅበረሰብ የሚሳተፉበት የሰላም ግብረ ኃይል እንዲቋቋም የጠየቁት፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ጉባዔ መሪዎችና የበላይ ጠባቂዎች ናቸው፡፡
የጉባዔው መሪዎችና የበላይ ጠባቂዎች መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት ብሔራዊ መግባባት፣ ዕርቅና የሕሊና ፈውስ እንዲፈጠር መንግሥትና ሕዝብ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረግ አለባቸው፡፡ ከሁሉም በላይ በኢትዮጵያ ያለውን ግጭት ወደ ሰላም የመለወጥ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ነው ብለው፣ መንግሥት ተገቢውን ሁሉ እንዲያደርግና ሕዝቡም አገራዊ ኃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ አሳስበዋል፡፡
በአገሪቱ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር መወያየታቸውን ያስታወሱት መሪዎቹና የበላይ ጠባቂዎቹ የሕዝቡ ጥያቄ በአግባቡ ተደምጦ አስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጠው የተስማሙ ቢሆንም፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ የአገሪቱ ሰላም እየደፈረሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎችም በተከሰተው ግጭት ምክንያት ሕይወት መጥፋቱን፣ የአካል ጉዳት መድረሱን፣ ሀብትና ንብረት መውደሙንም አስረድተዋል፡፡
መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም. በኦሮሚያ ቢሾፍቱ ከተማ የኢሬቻ ዓመታዊ በዓል ለማክበር የወጡ ወገኖች ሕይወታቸው ማለፉ እንዳሳዘናቸው የተናገሩት የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ መሪዎችና የበላይ ጠባቂዎች፣ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የተከሰቱትን ግጭቶች ለማርገብም ሆነ ሐሳብን ለመግለጽ በሚደረገው ጥረት፣ ማንኛውም አካል ከምንም ነገር በላይ ለሰው ሕይወት ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡ በተለያዩ አካባቢዎች ሕይወታቸውን ያጡና ንብረቶቻቸው የወደሙባቸው ወገኖች የሚቋቋሙበት ሁኔታ እንዲመቻችም መንግሥትን ጠይቀዋል፡፡
የተለያዩ እምነቶች ተከታይ የሆኑ ኢትዮጵያውያን በይቅርታና በምሕረት እርስ በርሳቸው ተከባብረው ለሰላምና ለልማት በጋራ እንዲቆሙ፣ ወንድምና እህት በመሆን ከጥላቻ፣ ከአድማና ከሁከት በመራቅ ያላቸውን ጥያቄ ሁሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲያቀርቡም ጠይቀዋል፡፡ በተለይ መሠረተ ልማቶች የአገር ሀብት በመሆናቸው፣ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲጠብቃቸውና እንዲንከባከባቸው ጠይቀዋል፡፡
የኢትዮጵያ የሃይማኖቶች ጉባዔ መሪዎችና የበላይ ጠባቂዎች የመገናኛ ብዙኃንን በሚመለከት እንደተናገሩት ማኅበራዊ ድረ ገጾችና ግለሰቦች ሕዝብን ወደ ጥላቻ፣ ግጭትና ሁከት ወይም የሰው ሕይወት ወደ ማጥፋት ከሚመራ ዘገባና መልዕክት ማስተላለፍ እንዲታቀቡ አሳስበዋል፡፡

No comments:

Post a Comment