‹‹መስከረም ጠባ፡፡ የመስከረም ጮራ ዕንቁጣጣሽ ብላ ተግ አለች፡፡
ልጃገረዶች ሳዱላቸውን አሳመሩ፡፡ አደስ ተቀቡ፡፡ እንሶስላ ሞቁ፡፡ ወንዝ ወረዱ፡፡ ቄጤማ ለቀሙ፡፡ ፀአዳ ልብሳቸውን ለብሰው፣ አሽንክታባቸውን አጥልቀው፣ ‹አበባዬ ሆይ - ለምለም› በማለት ተሰብስበው ብቅ አሉ - እንደ ጮራይቱ፡፡ የወርሀ መስከረም ብሩህ ተስፋና ስሜት በምድሪቱ አስተጋባ፡፡
ጠፍ እያለ መጣ ምድሩ፡፡ ወንዙም እየጠራ፡፡ ኩል መሰለ ሰማዩ፡፡ ሜዳው፣ ጋራው፣ ሸንተረሩ ወርቃማ የአደይ አበባ ካባ ለበሰ፡፡ ደመራ ተደመረ፡፡ ተቀጣጠለ ችቦ፡፡ ‹ኢዮሃ አበባዬ - መስከረም ጠባዬ› ተባለ፡፡››
ይህ ሥዕላዊ ሐተታ በዓሉ ግርማ ከሠላሳ ሰባት ዓመት በፊት ባሳተመው ‹‹ደራሲው›› በተሰኘው ልቦለዱ የመስከረምን ድባብ የገለፀበት ነበር፡፡ አዲሱ ዓመት በመጣ ቁጥር ሁሌ የሚታወስ ነው፡፡
የዘንድሮው 2009 ዓመት እንደወትሮው ሰዉ በፍካትና በሐሴት ላለመቀበሉ በተለያዩ አካባቢዎች የተከሰተው አመፅ ሰበብ ሆኖ ያስከተለው ኅልፈተ ሕይወትና ጉዳት ሐዘንና ብካይ መፍጠሩም አይዘነጋም፡፡
ይህም ሆኖ ‹‹ኢዮሃ አበባዬ . . . መስከረም ጠባዬ›› ዘመን በተሞሸረ ዓመት በተቀመረ ቁጥር ሰው መልካም ምኞት የሚለዋወጥበት ሐረግ ነው፡፡ ድምፃውያንም ያቀነቅኑታል፡፡ እንግዲህ ኃያሉ ክረምት ሊያበቃ፣ መሰስ እያለ ወጥቶ ለከርሞ ሊመለስ ከመስቀል በዓል በኋላ አንድ ሳምንት (መስከረም 25 ቀን 2009 ዓ.ም.) ቢቀረው ነው፡፡ ግን ኢዮሃ እየተባለ የመዘመሩ፣ የማቀንቀኑ ምስጢር ምንድን ነው? ኢዮሃስ ምን ማለት ነው? ሊቁ አለቃ ደስታ ተክለወልድ ዘብሔረ ወግዳ፣ በታላቁ ‹‹አዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት›› ሥራቸው ያወሱትን እዚህ ላይ ይወሳል፡፡ ሥርወ ቃሉ (የቃሉ ሥር መገኛ) ‹‹ኢዩ››- እይ፣ ‹‹ሃ››- ውሃ ማለት ሲሆን፣ ሲናበብ ደግሞ ‹‹ውሃ ያደረገውን እይ ተመልከት›› የሚል ፍች ይኖረዋል፡፡ ኢዮሃ አበባዬ የደስታ ቃል ነው፡፡ ወንዶች የደመራ ለት እየዘፈኑ ድምሩን የሚዞሩበት ያበባ ዘፈን ነው፡፡ ሰኔ ግም ብሎ፣ ያምሌን ጨለማ አልፎ፣ የነሐሴን ጎርፍ ሙላትን በእኝኝ ተሻግሮና ተንተርሶ በጠንካራው ዝናብ (ውሃ) ምክንያት ብቅ የምትለዋ ያደይ አበባ ናትና፤ ውሃ ያደረገውን ታምር፣ ያስበቀለውን አበባ አደያዊን ተመልከት ለማለት ‹‹ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ›› ይባላል፡፡
ዶ/ር ሀብተማርያም አሰፋ ‹‹የኢትዮጵያ ታሪክ ጥያቄዎችና ባሕሎች›› በሚሉት መጽሐፋቸው መስከረምን እንዲህ ገልጸዋታል፡፡
መስከረም ‹‹ምስ-ከረም›› ከከረመ በኋላ ወይም ክረምት ካለፈ በኋላ ማለት ነው፡፡ የመስከረም ወር ዝናብ የሚቆምበት ፀሐይ የምትወጣበት ወንዞች ንጹሕ ውሃ ጽሩይ ማይ የሚጎርፍበት፣ አፍላጋት የሚመነጩበት፣ አዝርዕት ማለት የተዘሩት አድገው ማሸት የሚጀምሩበት፣ ሜዳዎችና ተራራዎች ሸለቆዎችም በአበባ የሚያሸበርቁበትና የሚቆጠቆጡበት ነው ይሉታል፡፡
እንዲህም በመሆኑ የጨለማ የችግርና የአፀባ ጊዜ የሚያበቃበት የብርሃን፣ የደስታ የሸት፣ የፍሬና የጥጋብ ጊዜ የሚጀምርበትና የሚተካበት ነው ብሎ ሕዝቡ ስለሚያምንበትም የዕንቁጣጣሽ በዓልን ከሁሉ አብልጦ ግምት ስለሚሰጠው በእሳት ብርሃንና በእሳት ቡራኬ በየቤቱ እንደ ሁኔታው እንስሳ አርዶ ደም አፍስሶ ይቀበለዋል፡፡ ያከብረዋል ሲሉም አክለውበታል፡፡
በወርኃ መስከረም መሬቷ በአደይ አበባ አሸብርቃ ስለምትታይና በተለይም ዕንቁ የመሰለ አበባ ስለምታወጣ መሬቷን ዕንቁጣጣሽ፣ ዕንቁ የመሰለ አበባ አስገኘሽ ለማለት ዕንቁጣጣሽ መባሏን የቅርስ ባለሙያው መምህር ዓለሙ ኃይሌ ይገልጻሉ፡፡ አያይዘው አቧራ፣ ቡላ የነበረው መሬት በዝናቡ ኃይል ለምልሞ ተመልከቱኝ፣ ተመልከቱኝ የምትል ያሸበረቀች፣ አበባ የተንቆጠቆጠች ሆነች የሚል ለዕንቁጣጣሽ ስያሜ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ይጠቁማሉ፡፡
እንግጫ
እንግጫ የሣር ዓይነት ነው፡፡ በአዲስ ዓመት ዋዜማ ልጃገረዶች መስክ ወርደው የሚነቅሉት ነው፡፡ የዕንቁጣጣሽ ብሥራት ነጋሪ ነው፡፡ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባሳተመው ‹‹በሰሜን ሸዋ በምሥራቅና ምዕራብ ጎጃም ዞኖች የተመዘገቡ የኢንታጀብል ባህላዊ ቅርሶች›› መድበል ላይ ስለ እንግጫ እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡
በዘመን መለወጫ ዋዜማ እንግጫ ሳር በልጆች እየተነቀለ እንደቋጨራ እየተጎነጎነ ጣራ ላይ ተወርውሮ ያድርና ጠዋት ላይ ለዘመን መለወጫ እየተጎነጎነ ራስ ላይ፣ ቡሃቃ አንገት ላይና ሌማት ክዳን ላይ ይታሰራል፡፡ ቡሃቃ እና ሌማት ላይ የመታሰሩ ምልክትነት ለረድኤትና ለበረከት ሲባል የሚደረግ ነው፡፡
ራስ ላይ የታሰረው ደግሞ ለመስቀል በዓል ተቀምጦ ይቆይና ደመራው ላይ ይታሰርና እንዲቃጠል ይደረጋል፡፡ ለራስ ምታትና ለጤንነት ሲባል በማኅበረሰቡ የሚከወን ነው፡፡
እንግጫ ነቀላ ዘመን ሲለወጥ የሚከወን ባህላዊ ሥራት ነው፡፡ በዋዜማው ያላገቡ ሴቶች ወደ መስክ ወርደው እንግጫ ይቆርጣሉ፡፡ ምሽቱን ደግሞ እንግጫውን ሲጎነጉኑ ይቆያሉ፡፡ ሲነጋ ደግሞ በጠዋት ተጠራርተው በመሰባሰብ በየሰው ቤት እየዞሩ የተጎነጎነው እንግጫ ከቤቱ ምሰሶ ላይ ያስራሉ፡፡ እንግጫ የአዲስ ዓመት የምሥራች ምልክት ነው፡፡ በመድበሉ እንደተወሳው፣ እንግጫው ነቀላ በዜማ የታጀበ ነው፡፡
‹‹እቴ አበባዬ ነሽ
አደይ ተክለሻል
አደይ ተቀምጠሻል
ባሶና ሊበን
አዋጋው ብለሻል
ቦሶና ሊበን
ምነው ማዋጋትሽ
አንዱ አይበቃም ወይ››
በዚህ ጊዜ ወንዶች ደግሞ ያዘጋጁትን ዳቦት (የችቦ ስም) በእሳት ለኩሰው እያበሩ በመምጣት እንግጫ ለሚጎነጉኑት ሴቶች ያበሩላቸዋል፡፡ ዳቦታቸውን እያበሩ ወደ ሴቶቹ በሚያመሩበት ጊዜ የሚያዜሙት ዜማ አላቸው፡፡
‹‹ኢዮሃ ኢዮሃ
የቅዱስ ዮሐንስ
የመስቀል የመስቀል
አሰፉልኝ ሱሪ
ኢዮሃ›› በማለት ያዜማሉ፡፡
በከተሞች አካባቢ እንግጫ ነቀላው እየቀረ አበባዮሽ የሚለው ጨዋታ በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡ ልጃገረዶቹ ወደየሰው ቤት ሲሄዱ ሎሚ ይሰጣቸው የነበረ ሲሆን፣ አሁን ላይ ግን የእንግጫው ሴቶች ራሳቸው ‹‹እንኳን አደረሳችሁ›› እያሉ ሎሚ ሲሰጡ ገንዘብ ይሰጣቸዋል፡፡
የዘመን አዋጅ
መስከረም አንድ ቀን ያለው ልዩ ነገር የዘመኑን መለወጥ አስመልክቶ የባሕረ ሐሳብ አዋጁ ይነገራል፡፡ በዓመቱ ውስጥ በዓል የሚውልበት፣ ጾም የሚገባባትን ቀን መምህራኑ እያሰሉ ይናገሩታል፡፡ ዓመቱን በፀሐይና በጨረቃ፣ በዓመተ ዓለም ለምዕመናኑ ይገልጹታል፡፡ መምህር ዓለሙ ኃይሌ በምሳሌነት በላሊበላ ያለውን ሥርዓት ሲገልጹ የአሥሩም ቤተ መቅደስ ካህናት ቤተ ማርያም ይሰበሰቡና ማህሌቱ ካበቃ በኋላ ካህኑ ሻሹን ጠምጥሞ፣ ካባ ደርቦ መስቀል ይዞ ዘመኑን ያውጃል፣ የባሕረ ሐሳቡን ጥንተ ታሪክ ይናገራል፡፡ የዘንድሮው አዲስ ዓመት 2009 ዓ.ም. አዲስነቱ ለአንድ ዓመት ብቻ አይደለም፡፡ የአዲስ አራት ዓመት መባቻም ነው፡፡ በአራት ዓመቱ የሚመላለሰውና ‹‹ዐውደ ጳጉሜን››/ ‹‹ዐውደ ወንጌላውያን›› የሚባለው አንደኛ ዓመቱ ዘንድሮ ተጀምሯል፡፡ 2009 ለ4 ተካፍሎ 502 ደርሶ ቀሪው 1 መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ይህም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ትውፊት ዘመኑ የማቴዎስ መሆኑ ያመለክታል፡፡ (2 ከቀረ ማርቆስ፣ 3 ከቀረ ሉቃስ፣ እኩል ከሆነ ዮሐንስ ይሆናል፡፡ 2008 የአራት ዓመቱ ዑደት/ ሳይክል ማብቂያ ነበር) ዘንድሮ የዓለም ፍጥረት መነሻ በሆነው በዓመተ ዓለም ሲቆጠር 7509 ዓመተ ዓለም መሆኑና ስምንተኛው ሺሕ ከገባ 508 ዓመት ማለፉንና 509ኛ ዓመት ላይ መገኘቱን ስሌቱ ያሳያል፡፡
‹‹ተቀጸል ጽጌ›› (አበባን ተቀዳጅ)
‹‹ተቀጸል ጽጌ›› አበባን ተቀዳጅ ማለት ሲሆን፣ በዘመነ አክሱም በስድስተኛው ምታመት በነበሩት አፄ ገብረ መስቀል ዘመን የክረምት መውጫ በሆነው መስከረም 25 ቀን የሚከበር የወቅት ሽግግር በዓል ነበር፡፡ ለንጉሠ ነገሥቱ የአበባ አክሊል/ጉንጉን ይበረከትለት ስለነበር ‹‹ተቀጸል ጽጌ፤ ገብረ መስቀል ሐፄጌ›› (አፄ ገብረ መስቀል አበባን ተቀዳጅ) እየተባለ ይዘመር ነበር፡፡ ከ15ኛው ምታመት በኋላ ኢየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ግማሽ ክፍሉ (ግማደ መስቀል) መምጣቱን ተከትሎ በዓሉ ወደ መስከረም 10 ቀን ዞሯል፡፡ እስከ መጨረሻው ንጉሠ ነገሥት አፄ ኃይለ ሥላሴ (1923 - 1967) ድረስ በዓሉ በኢዮቤልዩ ቤተ መንግሥት ሲከበር ቆይቷል፡፡ ከ1983 ዓ.ም. የመንግሥት ለውጥ ወዲህ በዓሉ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ዐውደ ምሕረት በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ አማካይነት የአበባውን በዓል ማክበሩና ለበዓሉ ታዳሚዎችም አበባን ማደሉ ቀጥሏል፡፡
የመስከረም ወቅት
መስከረም 1 በክረምት ውስጥ የምትገኝ ያመት መነሻ ናት፡፡ ሰኔ 26 ቀን የገባው ክረምት የሚወጣው መስከረም 25 ቀን ላይ ነው፡፡ የስድስተኛው ምታመት የነገረ መለኮት ሊቁ (ቲኦሎጊያን)፣ መዝሙረኛውና ዜማ ቀማሪው ቅዱስ ያሬድ በመጽሐፈ ድጓው ‹‹ኀለፈ ክረምቱ ጸገዩ ጽጌያት ቆመ በረከት!›› - ክረምቱ አለፈ አበቦችም ፈኩ፣ በረከትም ቆመ ይለናል፡፡
የዛሬው ቀን መስከረም 8 ቀን 2009 ዓ.ም. በክረምት ውስጥ ይገኛል፡፡ እንደ ቅዱስ ያሬድ አመዳደብ፣ በውስጡም ልዩ ልዩ ንኡሳን ክፍሎች አሉት፡፡ ከነሱም መካከል የነሐሴ መጨረሻና የጳጉሜን ሳምንት ‹‹ጎሕ፣ ጽባሕ››- ወጋገን፣ ንጋት ይለዋል፡፡ ይህም ያዲስ ዘመን መስከረም የሚጠባበት ጊዜ መድረሱን አመላካች ነው፡፡
ሌላው ንኡስ ክፍል ከዓመት አውራ መነሻ (ርእሰ ዐውደ ዓመት) መስከረም 1 ቀን እስከ መስከረም 7 (8) ቀን ያለው ‹‹ዮሐንስ›› ሲባል፣ ከመስከረም 9 እስከ 15 ዘመነ ፍሬ ይባላል፡፡ ‹‹ዮሐንስ›› የሚለው ቃል የተወሰደው በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ከሚገኘውና ኢየሱስ ክርስቶስን ካጠመቀው የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ ነው፡፡ መስከረም 1 ቀን ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕለተ ዮሐንስ መባሉ በተምሳሌታዊ ፍች የመጣ ነው፡፡ ከአሮጌው ብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን፣ ወደ ዓመተ ምሕረት መሸጋገሪያ ላይ የመጣው መንገድ ጠራጊው ዮሐንስ ስለሆነ፤ ባህሉ/ ትውፊቱ ካሮጌው ዓመት ወዳዲሱ መሸጋገሪያዋን ዕለት፣ መስከረም 1 ቀንን በዘይቤ ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› ‹‹ዕለተ ዮሐንስ›› እያለ ይጠራዋል፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ ባገልግሎት ላይ ይገኛል፡፡ እንዳለመታደል፣ ምስጢሩን ባለመረዳት ሚዲያዎች በተለይም መንግሥታዊዎቹ በመናገሻ ከተማይቱንም ሆነ በየክልሉ የሚገኙት ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› የሚለውን የመስከረም 1 ቀን ልዩ መጠርያ ሲያነሱት አይሰማም፡፡ ሃይማኖታዊ ብሎ በመደምደም፡፡
ዩኔስኮ ልዩ ስለሆነው የኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር (ካሌንደር/ ቀለንቶን)፣ አዲሱ ዓመት ዘመን የሚለወጥበት ንጋት 12 ሰዓት ላይ እንጂ እንደ ምዕራባውያን እኩለ ሌሊት (6 ሰዓት) ስላለመሆኑ፣ ያመቱ መነሻ መስከረም 1- ቅዱስ ዮሐንስ- ዕለተ ዮሐንስ መባሉንና ሌሎች የቀመር ጓዞችን የያዘውን ጥንታዊ የባሕረ ሐሳብ ብራናን (መጽሐፍ) በጽሑፍ ቅርስነት ለመመዝገብ በሚመክርበት ጊዜ ላይ ተደርሶ ሚዲያዎችና የሚመለከታቸው አካላት ያለዕውቀት ቅርሱንና ውርሱን እየጣሉት ይገኛሉ፡፡
ከኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ ጋር የማይተዋወቁት፣ እኩለ ሌሊት ላይ ‹‹አዲስ ዓመት ገባ›› እያሉ ማደናገራቸውን ዓመት ዓመት መቀጠላቸውን ሃይ የሚልም ጠፍቷል፡፡ ለነገሩ የዘመን መለወጫ እንቁጣጣሽ ዜማዎች ውስጥ፣ ድምፃውያኑ ቅዱስ ዮሐንስን ፈጽሞ አልረሱትም፡፡ (ሁለት የዘመን መለወጫ በዓል የሚከበርባት ኤርትራ መስከረም 1 ቀንን ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› እያለች ዳር እስከ ዳር እያከበረችው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡) ዩኔስኮ የባሕረ ሐሳባችሁን ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› አውቄዋለሁ፣ አክብሬዋለሁ ሲል እዚህ ግን እየተጣለ ነው፡፡
ሊቁ ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ የዛሬ 54 ዓመት በአዲስ አበባ ራዲዮ ጣቢያ የዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ ላይ፣ ባደረጉት ንግግር ማሰሪያቸውን እንዲህ ገልጸውት ነበር፡፡ ‹‹በዘመን መለወጫ በዓል አሮጌው አልፎ አዲስ ሲተካ የክረምት ጭለማ አልፎ ብርሃን ሲመጣ ሁሉም ‹በተውሳከ መብልዕ ወመስቴ› [ምግብና መጠጥን በመጨመር] እየተደሰተ፣ ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላው መሻገሩን በሚያከብርበት ዕለት ትንሽ ጊዜ አስተርፎ ስለጠቅላላው የሕይወት ጉዞ ለሚያስበው ረድኤት ይሆን ዘንድ፣ ለማያስበው ደግሞ እንዲያስብ ምክንያት ይሆን ዘንድ፣ እሊህን ሐሳቦች ለማቅረብ ደፈርን፡፡›› እንዳሉት፣ ያሁኑ ትውልድም ይህን የሊቁን እጓለ መርሐ ሐሳብ ለምን አይሰንቅም? ነገ፣ ሰኞ መስከረም 9 ቀን 2009 ዓ.ም. ከዮሐንስ ወደ ፍሬ ሽግግር የሚደረግበት ሲሆን፣ ከነገ ወዲያ፣ መስከረም 10 ቀን ተቀጸል ጽጌ (አበባን ተቀዳጅ) ይውላል፡፡ ዘመነ ፍሬ የኢትዮጵያ ፍሬዎች የሚታወቁበትና የሚከበሩበት ይሆናል ተብሎ ይታመናል፡፡ ተቀጸል ጽጌ፡፡

- ሔኖክ ያሬድ's blog
- 203 reads
No comments:
Post a Comment