![]() |
የአሹራ በዓል በነጋሽ ከተማ ጥቅምት 2 ቀን 2009 በተከበረበት ጊዜ |
በሔኖክ ያሬድ
አሹራ
በእስላማዊው የዘመን አቆጣጠር የመጀመርያው ወር በሆነው ሙሀረም በተጀመረ በ10ኛው ቀን በየዓመቱ የሚከበር በዓል ነው፡፡
በዓሉ
በተለያዩ የዓለም ክፍል በሚገኙ ሙስሊሞች ይከበራል፡፡ ዓመቱን 354 (355) ቀኖች በያዘውና በጨረቃ አቆጣጠርን መሠረቱ ባደረገው
እስላማዊ ካሌንደር መሠረት፣ አዲሱ ዓመት 1438 ዓመተ ሒጅራ (ዓ.ሒ.) የገባው ሙሀረም 1 ቀን (በፀሐይ መስከረም 22 ቀን
2009 ዓ.ም.) ሲሆን የአሹራ በዓልም ሙሀረም 10 ቀን 438 ዓ.ሒ. (ጥቅምት 2 ቀን) ተከብሯል፡፡
የኢስላም ካሌንደር
ከሁለት
ሳምንት በፊት የእስላማዊ አዲስ ዓመት 1438 ዓመተ ሒጅራ የባተበት ነበር፡፡ ዕለቱም የሙሀረም ወር አንደኛ ቀን የእስላሚክ የጨረቃ
ካሌንደር የመጀመርያ ወር ነው፡፡ የሙስሊም ዘመን የሚሰላው ከጨረቃ መውጣትና መግባት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ እስላማዊ የጨረቃ ካሌንደር
(ሉናር ካሌንደር) የዓመቱ ቀኖች 354 (355) ሲሆን ከፀሐይ 365 ቀኖች በ11 ቀን ያንሳል፡፡ የ12 ወራት የእስላሚክ/ሒጅራ
ካሌንደር የተጀመረው በሁለተኛው ከሊፋ ዑመር በ16 ዓ.ሒ. (637 ዓ.ም.) ነበር፡፡ የዓመቱ የመጀመርያ ወር፣ ሙሀረም የመታሰቢያ
ወር በመባል የሚታወቅና በሙስሊም ካሌንደር ውስጥ ልዩ ስፍራ ከሚሰጣቸው ወራት አንዱ ነው፡፡
በዴይሊ
ትረስት እንደተጻፈው፣ ሙሀረም ‹‹የተከለከለ›› የሚል ፍች አለውና በርካታ ሙስሊሞች በፈቃዳቸው በዚህ ወቅት ይጾማሉ፡፡ የዓመቱ
መባቻ የኢድ አልአድሃና ኢድአልፈጥር ዓይነት ከፍታ ባይኖረውም፣ ነቢዩ መሐመድ የመጀመርያውን ኢስላማዊ አስተዳደር በመዲና ከተማ
(ባንድ ወቅት ያትሪብ ትባል ነበር) የመሠረተበት ዕለት በመሆኑ ይወሳል፡፡
ነቢዩ
መሐመድ በ622 ዓ.ም. ከመካ ወደ መዲና የተሰደዱበት ስደት ሒጅራ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ይህም የሙስሊም ካሌንደር መጀመርያና መጠርያ
ሆኗል፡፡
የአሹራ በዓል
የአሹራ በዓል ረቡዕ ሙሀረም 10 ቀን 1438 ዓ.ሒ. (ጥቅምት 2 ቀን
2009 ዓ.ም.) በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ተከብሯል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ በዓሉ በየዓመቱ ከሚከበርባቸው መስጊዶች መካከል አንዱ
በሆነው በትግራይ ክልል ነጋሽ ከተማ በሚገኘው ጥንታዊ መስጊድ በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተከብሯል፡፡
ነጋሺ
በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከመካ መዲና ተሰደው የመጡ ሰሃቦች የተስተናገዱበት ቦታ ነበር፡፡ ‹‹አሹራ በእስልምና ዓለም›› በሚለው
መጣጥፋቸው አቶ አህመድ ዘካሪያ እንደጻፉት፣ በአሹራ ዕለት ከነቢዩ አደም ጀምሮ የታወቁት ነቢያት በሙሉ ተአምራታቸው የታየበት ቀን
ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
የአደምና
የሐዋ መፈጠር፣ የነቢዩ ኢብራሂም ከእሳት ቃጠሎ መዳን፣ ሙሳ ቀይ ባሕርን ከተከታዮቻቸው ጋር ማቋረጥ፣ ኑህ ከጥፋት ውኃ መዳንና
የሌሎቹም ነቢያት ተአምራት የተመዘገበበት ቀን ነው፡፡
በሰሜን
ኢትዮጵያ (በትግራይ፣ በወሎና በጎንደር) ደግሞ አህመድ ነጋሽ የነቢዩ ሙሀመድ ቤተሰቦችን ተቀብለው ከማስተናገዳቸው፣ ከአደጋ ከመከላከላቸውና
ታላቅ መሪ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ይከበራል፡፡ በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከሐጅ ሲመለሱ ነጋሺ መስጊድ ተገናኝተው ጸሎት ያደርሱ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜም ይህ ልማድ ቀጥሎ ወደ ሐጅ ያልሄዱ የወሎ፣
የትግራይ፣ አልፎ አልፎ ይሁን እንጂ የጎንደር እስልምና እምነት ተከታዮች ወደዚያው በመሄድ የአሹራን በዓል ያከብራሉ፡፡ በሐረሪም
በተለየ አካባበር ይከበራል፡፡
መሰንበቻውን
ነጋሽ ከተማ በተገኘንበት አጋጣሚ ያነጋገርናቸው የነጃሺ መስጊድ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር ሐጂ መሐመድ አልኑር፣ የሙሀረም ወር
10ኛ ቀን የሚከበርባት አሹራ ብዙ ትርጉም እንዳላት ያወሳሉ፡፡
‹‹ሰማይና
ምድር የተሆለቁት (የተፈጠሩት) በአሹራ ቀን ነው፡፡ አዳምና ሐዋ የተሆለቁት በአሹራ ነው፡፡ ጥሩ ጥሩ ሥራ የሚሠራበት ፍርድም የሚደረግበት
በአሹራ ነው፡፡››
ከ65
ዓመት በፊት በነጋሽ መስጊድ ቅጥር ግቢ በአዝማች መሐመድ ሐጂ አብዱ (የቀድሞው የአገር አቋራጭ አውቶቡሶች ማኅበር የሰሜናዊ ትራንስፖርት
መሥራችና ባለቤት) በተሠራው ታላቅ አዳራሽ ምግብ በማዘጋጀት ሰደቃ ሲደረግበት ኖሯል፡፡ ለዘንድሮው አሹራ በዓል ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ
መስከረም 19 ቀን 2009 ዓ.ም. የተገኙት ወ/ሮ ብርሃን ናሥራይ በየዓመቱ እንደሚያደርጉት ሁሉ ለሚመጣው እንግዳ ከብት በማረድ
ምግብ እንደሚያዘጋጁ ገልጸውልን ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያና በቱርክ መንግሥታት ትብብር የዕድሳትና ተጨማሪ መሠረተ
ልማት እየተሠራበት በሚገኘው ነጋሽ መስጊድ ቅጥር ግቢ የሚገኘው ነባሩና ሰደቃ የሚደረግበት አዳራሽ፣ በግንባታ ሥራውም ምክንያት
በመያዙ ሌላ አማራጭ እንዲሰጣቸው በጠየቁበት አጋጣሚ ነበር ያገኘናቸው፡፡
![]() |
ወ/ሮ ብርሃን ናሥራይ |
‹‹በየዓመቱ
ሰደቃ ማብላቱን አዝማች መሐመድ አብዱ ጀመሩት፡፡ ወንድማቸው እነ ባሻ ሁሴን ይሠሩት ነበር፡፡ በሞት ሲለዩ ልጆቻቸው ቀጠሉት፤ የአሥመራ
መንገድ ከተዘጋ በኋላ ተውት፡፡ ከዚያ በኋላ እኔ ተተክቼ በየዓመቱ አስተናግዳለሁ፤›› የሚሉት ወ/ሮ ብርሃን፣ ‹‹ዓመት ዓመት የሚመጣ
እንግዳ መንገላታት የለበትም፡፡ እንደሌላው አካባቢ ሆቴል የለምና በየዓመቱ የምናስተናግድበት ቦታ ማጣት የለብንም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ዓመት
ዓመት እንግዳ መቀበያ መሥራታችን ትንሽ ነገር አይደለም፡፡ ብዙ እንግዳ በልቶ ጠጥቶ የሚያድርበት ቦታ ነው፡፡ አሁን ሌላ ቦታ ተቀይሮ
ቢሰጠንም ለወደፊቱ ልንሠራው እንችላለን፤›› ላሉት ወ/ሮ ብርሃን ለጥያቄያቸው እድሳቱንና ግንባታውን እያካሄደ ያለው ተቋም ቀና
ምላሽ ሰጥቷቸዋል፡፡ ሰደቃ ይደረግበት የነበረው አዳራሽ መጋዘን በመሆኑ በምትኩ አዲስ በታነፁት ቤቶች ውስጥ መሰናዶን እንዲያዘጋጁ
ማድረጉን ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
እድሳትና ግንባታ
ክፍለ
ዘመናትን ያሳለፈው ነጋሽ መስጊድ ነባሩንና ታሪካዊ ይዞታው ሳይለወጥ የማደስና የመጠገን እንዲሁም በተንጣለለው ቅጥር ግቢ ውስጥ
የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች በቱርክ መንግሥት ድጋፍ እየተሠራ ነው፡፡ ሥራውን የቱርክ ኩባንያ እያከናወነው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል
የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሺበሺ ጫካ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመጀመርያው ዙር ፕሮጀክት አምስት ሚሊዮን ዶላር የተበጀተለት
ሲሆን፣ ከመስጊዱ እድሳት በተጨማሪ ከተከናወኑት አዳዲስ ግንባታዎች
የእንግዶች ማረፊያ፣ ምግብ ቤት፣ መፀዳጃ ቤት ሲገኙበት፣ የቅጥር ግቢ አጥርና የመስጊዱን በረንዳ የማስፋት ሥራም እየተከናወነ
ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ለመስጊዱም ሆነ ለአካባቢው ኅብረተሰብ የሚያገለግል የከርሰ ምድር ውኃ የወጣ ሲሆን፣ 120 ሺ ሜትር ኪዩብ
የሚይዝ በርሚል (ሮቶ) ተደርጎለታል፡፡
![]() |
የነጋሽና የ15ቱ ሱሃቦች ስም የሚጻፍበት የድንጋይ ምሰሶዎች 8 በግራ 8 በቀኝ ቆመዋል |
በአሁን
ጊዜ 75 በመቶ ብቻ የተጠናቀቀው ፕሮጀክቱ፣ እንደ ሥራ አስኪያጁ አነጋገር የማጠናቀቂያ ሥራው በአራት ወራት ውስጥ ያበቃል፡፡ ከአዳዲስ
ግንባታ መካከል ከዋናው በር እስከ ቀደምቱ ሱሃቦች መካነ መቃብር የሚወሰደው መንገድ በዘመናዊ መልክ የተገነባና በመተላለፊያው የነጋሽና
የ15ቱ ሱሃቦች ስም የሚጻፍበት የድንጋይ ምሰሶዎች 8 በግራ 8 በቀኝ ቆመዋል፡፡ የያንዳንዱ ስም በአማርኛ፣ በቱርክኛና በእንግሊዝኛ
ቋንቋዎች እንደሚጻፍና ሰዎች በሚገቡበት ሰዓት ስሞቹን እያነበቡ ወደ ታሪካዊ ቦታ እንዲገቡ ለማድረግ የታሰበ እንደሆነ ሥራ አስኪያጁ
ተናግረዋል፡፡
የአል
ነጃሺ ቅዱስ ስፍራን ለማደስ፣ ለመጠገንና መልክአ ምድራዊ ገጽታውን ለማሳመር በቱርክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው የቱርክ
ኩባንያ ቲካ፣ ከትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ከክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጋር በመሆን ሥራውን እያከናወነ ነው፡፡
እንደ ኢንጂነር ሺበሺ መግለጫ የመጀመርያው ፕሮጀክት ከተጠናቀቀ በኋላ በሁለተኛው እቅድ በነጋሽ ከተማ የዕደ ጥበባት ማዕከል፣ ሆቴሎች፣
ካፌና የእንግዳ ማረፊያዎች ይሠራሉ፡፡ ይህም የቱሪስቱን ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድገዋል የሚል ተስፋም አላቸው፡፡
No comments:
Post a Comment