Saturday, October 8, 2016

ብርጋዴየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ‹‹በራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና››




ብርጋዴየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ
‹‹በራሪው የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና››
በሔኖክ ያሬድ
በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግሥት (1967-1983) ዘመን ሶማሊያ ኢትዮጵያን በወረረችበት (1969-1970) ወቅት በተዋጊ ጄት አብራሪነት ወደር የሌለው ጀግንነት በመፈጸማቸው፣ ‹‹የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ›› ተሸላሚ የነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ አረፉ፡፡
ላለፉት 27 ዓመታት በኖሩበት አሜሪካ በሕክምና ሲረዱ የቀዩት ብርጋዴየር ጄኔራል ለገሠ ያረፉት፣ ሐሙስ መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም. መሆኑን ዘገባዎች አመልክተዋል፡፡
ሶማሊያ ከ1956 ዓ.ም. የመጀመርያው ወረራዋ በኋላ ለሁለተኛ ጊዜ በ1969 ዓ.ም. ኢትዮጵያን በምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ በወረረችበት ጊዜ በተደረገው ዘመቻ፣ በኢትዮጵያ አየር ኃይል የዘጠነኛው ስኳድሮን ባልደረባ የነበሩት በወቅቱ ሌተና ኮሎኔል ማዕረግ የነበራቸው ጄኔራል ለገሠ፣ በአየር ላይ ውጊያ አምስት ተዋጊና አንድ የማጓጓዣ አውሮፕላኖችን፣ የጠላትን መደበኛ ሠራዊት ድርጅቱንም ጭምር ማጋየታቸው ገጸ ታሪካቸው ያመለክታል፡፡
በምሥራቅ ጦር ግንባር ወደር የሌለው ጀግንነት በመፈጸማቸው፣ በዘመኑ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ከነበሩት ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ‹‹የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ›› ተሸልመዋል፡፡
በጳጉሜን 1979 ዓ.ም. የታተመው ‹‹ትግልና ጀግና›› የሜዳይ፣ ኒሻንና ሽልማት መጽሔት ስለ ጄኔራል ለገሠ ተጋድሎ ሲገልጽ፣ ‹‹በተዋጊ አውሮፕላን አብራሪነታቸው የታወቁ የምድር ዒላማን አነጣጥሮ በመምታትና አየር ለአየር በሚደረግ ውጊያ ለማንኛውም ቆራጥ አብራሪ አርአያነትን ያተረፉ ታላቅ ጀግና ናቸው፤›› ብሏቸዋል፡፡
ሐምሌ 9 ቀን 1969 ዓ.ም. የድሬዳዋ አየር ጣቢያ በተጠናከረ የሶማሊያ ጦር የተወረረበት የድሬዳዋ ከተማ ሕዝብም ከሠራዊቱ ጎን በመሠለፍ ከጠላት ጋር ግብ ግብ በገጠመበት ጊዜ፣ ጄኔራል ለገሠ ከሐረር ሜዳ በመወርወር የጠላትን ይዞታ እያደኑ በሚደበድቡበት ጊዜ ድንበር ጥሰው ከገቡት የሶማሊያ አራት የአየር ኃይል ተዋጊ አውሮፕላኖች ሁለቱን ‹‹ዶግ ፋይቲንግ›› በሚባለው ውጊያ ሥልት እርስ በርሳቸው ተላትመው እንዲወድቁ ማድረጋቸው ይነገርላቸዋል፡፡
ጄኔራል ለገሠ በሶማሊያ ከ11 ዓመታት የጦር እስረኝነት ቆይተው ነፃ ከወጡ በኋላ በአየር ኃይል በበረራ አስተማሪነት ያገለገሉ ሲሆን፣ ከ1981 ዓ.ም. የግንቦት መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ከከሸፈ በኋላ መኖሪያቸውን በአሜሪካ አድርገዋል፡፡
ከሐረር የጦር አካዴሚ በ1959 ዓ.ም. የተመረቁት፣ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት የነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ አስከሬን መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. አዲስ አበባ እንደሚገባ፣ ሥርዓተ ቀብራቸውም በማግሥቱ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል እንደሚፈጸም የቅርብ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

No comments:

Post a Comment