በሔኖክ ያሬድና በነአምን አሸናፊ
ከሩብ ምዕት ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ
መድረክ በተለይም በተቃውሞው ጎራ ግንባር ቀደም መሪዎች ከነበሩት አንዱ የነበሩት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል አረፉ፡፡
የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ምክትል
ሊቀመንበርና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መሥራችና ሊቀመንበር፣ እንዲሁም የቀድሞው የቅንጅት
ለአንድነትና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት) ሊቀመንበር የነበሩት ኢንጂነር ኃይሉ በ80 ዓመታቸው መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ያረፉት
የስኳር ሕመም ሕክምና ሲከታተሉበት በነበረው በባንኮክ ታይላንድ ነው፡፡
በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ወቅት
ከጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ የነበረውን ቅንጅትን በምርጫው ዋዜማ የመሠረቱት መኢአድ፣ ኢዴፓ (የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ
ፓርቲ)፣ ኢዲሊ (የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሊግ) እና ቀስተ ዳመና ሲሆኑ ኢንጂነር ኃይሉ በሊቀመንበርነት መርተውታል፡፡ ከምርጫው
ውጤት በኋላ በተነሳው ተቃውሞ ከቅንጅት መሪዎች ጋር ለእስር ከተዳረጉ በኋላ፣ ከሌሎች 23 የቅንጅት መሪዎች ጋር በአገር ክህደትና
በዘር ማጥፋት ክስ ተመሥርቶባቸውና ተፈርዶባቸው ነበር፡፡
በታኅሳስ 2000 ዓ.ም. የፓርቲው አመራሮች
ባቀረቡት የይቅርታ ጥያቄ መሠረት በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ምሕረት ተደርጎላቸው መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡ በፖለቲካ ተሳትፏቸውም መኢአድን
ለአሥር ዓመታት፣ ቅንጅትን ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ በሊቀመንበርነት የመሩት ኢንጂነር ኃይሉ የተወለዱት በሰሜን ሸዋ አንኮበር በ1928
ዓ.ም. ሲሆን፣ ከፍተኛ ትምህርታቸውን በአሜሪካ ዌይን ስቴት ዩኒቨርሲቲ (Wayne State
University) በሲቪል ምሕንድስና አጠናቀዋል፡፡ በ1950 ዓ.ም. ከተመለሱ በኋላ ሥራ የጀመሩት በአሜሪካኖች
በሚመራው የዓባይ ሸለቆ ጥናት ፕሮጀክት በኃይድሮሎጂስትነት በመቀጠር ነበር፡፡
በሼል ኢንተርናሽናል የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች
ካገለገሉ በኋላ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በ1963 ዓ.ም. የቀድሞው የአውራ ጎዳና ባለሥልጣን (የአሁኑ የኢትዮጵያ መንገዶች
ባለሥልጣን)፣ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ተሹመው ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል፡፡
በኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ
መንግሥት ዘመን የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የወንጂና የመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችም ሥራ አስኪያጅ ነበሩ፡፡
በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙ እርሻዎችን የሚመራው
የመንግሥት እርሻዎች ልማት ሚኒስትር ሆነው ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ሠርተዋል፡፡
በ1975 ዓ.ም. የመንግሥት ሥልጣናቸውን ትተው
የራሳቸውን ሻውል አማካሪ የተሰኘ ድርጅት መሥርተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ልጃቸው ዶ/ር ሻውል ኃይሉ እየመሩት ይገኛል፡፡
ባለትዳርና የአምስት ወንድና የአንዲት ሴት ልጅ
አባት የነበሩት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል አስከሬን፣ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. አዲስ አበባ እንደሚገባ መኢአድ አስታውቋል፡፡
No comments:
Post a Comment