Friday, October 28, 2016

ኢትዮጵያዊው የዕፀዋት ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው ዓለም አቀፍ ተሸላሚ ሆኑ - በጥር ወር በለንደን ዲስኩር ያሰማሉ


-
ታዋቂው ኢትዮጵያዊ የዕፀዋት ሳይንቲስት ፕሮፌሰር ሰብስቤ ደምሰው የዘንድሮ የእንግሊዝ የሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ ኪው (Royal Botanic Garden, Kew) ዓለም አቀፍ ሽልማት ተሸላሚ ሆኑ፡፡
ኪው ኢንተርናሽናል ሜዳልያ በያመቱ ለግሰለቦች የሚሰጥ ሽልማት ሲሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ የታወቀ ሥራን ላከናወነና ከሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ፣ ኬው ተልዕኮ ጋር ስምም የሆነ ተግባር ለፈጸሙ የሚበረከት ነው፡፡
የኢትዮጵያን ብዝኃ ሕይወትን ለረዥም ጊዜ በማጥናትና በመመርመር ኅብረተሰቡም ሆነ አገሪቱም ከዘርፉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ በዓለምም እንዲታወቅ ለማድረግ ያከናወኑት ተግባር ፕሮፌሰር ሰብስቤን ለሽልማቱ አብቅቷቸዋል፡፡
በሥነ ዕፀዋት (Botanic Science) ምርምርና ጥናት ግንባር ቀደም እንደሆኑ የሚነገርላቸው ፕሮፌሰር ሰብስቤ የኢትዮጵያ ፍሎራ ፕሮጀክትን ከ1988 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ 2001 ዓ.ም. ድረስ ከ17 የአፍሪካና የአውሮፓ አገሮች የተወጣጡ የዕፀዋት ተመራማሪዎችን በመምራት ስኬታማ ተግባር ማከናወን ችለዋል፡፡
የሽልማት ሥነ ሥርዓቱ አዲስ አበባ በሚገኘው የእንግሊዝ ኤምባሲ ጥቅምት 11 ቀን 2009 ዓ.ም. የተከናወነ ሲሆን፣ የሜዳሊያ ክብሩን የሚቀበሉት በለንደን ከተማ በመጪው ጥር ወር እንደሚሆንና ዲስኩር እንደሚያሰሙ ታውቋል፡፡ የሮያል ቦታኒክ ጋርደን ኪው የሳይንስ ዳይሬክተር ፕሮፌሰር ካቲ ዊልስ በአዲስ አበባው ሥነ ሥርዓት ላይ መልዕክታቸውን ያስተላለፉት ‹‹ፕሮፌሰር ሰብስቤ በሥነ ዕፀዋት መስክ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪና የላቁ መሪ በመሆናቸው እንደሳቸው ዓይነት ሰብእና ያለውን እውቅናና ሽልማት መስጠት እንሻለን፤›› በማለት ነበር፡፡
ፕሮፌሰር ሰብስቤ ባካሄዱት ሳይንሳዊ ምርምር ዕፀዋት በሰዎች ሕይወት ላይ ያላቸውን ሚዛናዊ ሚናና ጥቅም ማሳየት መቻላቸው ውጤታማ እንዳደረጋቸውና በአገር በቀል ዕፀዋት ላይ ያዘጋጁት ሥራ ለየአካባቢው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚኖረውም ዳይሬክተሩ አክለው ገልጸዋል፡፡
በሥነ ዕፀዋት ምርምር ላከናወኑት ተግባር ለዓለም አቀፍ እውቅናና ሽልማት መብቃታቸው እንዳስደሰታቸው የገለጹት ፕሮፌሰር ሰብስቤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዕፀዋት መልክአ ምድራዊ ሥርጭት፣ ዓይነትና መጠንን በጥልቀት የሚፈትሽ ጥናት ሠርተዋል፡፡
ፕሮፌሰሩ በግላቸው በጋራ ከሠሯቸው ከብዝኃ ሕይወት ጋር የተያያዙ የምርምር መጻሕፍት መካከል “Aloes and Other Lilies of Ethiopia and Eritrea”፣ “Aromatic Plants of Ethiopia”፣ “Atlas of the Potential Vegetation of Ethiopia”፣ “Ethiopian Orchids”፣ “Field Guide to Ethiopian Orchids” ይገኙበታል፡፡    
ፕሮፌሰር ሰብስቤ በቀጣይ ከሚሠሯቸው ምርምሮች በተጓዳኝ በኢትዮጵያ የሚገኙ ዕፀዋትን በድረ ገጾች በማስተዋወቅ ረገድ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጋር በቅንጅት ለመሥራት ፍላጎቱ አላቸው፡፡
ሽልማቱ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ገጽታ ግንባታ ዓይነተኛ ሚና እንደሚጫወት የተናገሩት የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶ/ር አድማሱ ፀጋዬ፣ ፕሮፌሰር ሰብስቤ ለብዝኃ ሕይወት ልማት ያበረከቱት አስተዋጽዖ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪቃ ጭምር ነው ብለዋል፡፡
በደቡባዊ ምዕራብ ለንደን የሚገኘውና የተለያዩ ዕፀዋትን ያሰባሰበው ሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ (ብሔረ ጽጌ) እ.ኤ.አ. በ2003 በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በ1759 የተመሠረተውና በአበቦችና ዕፀዋት መናኸርያነቱ (ብሔረ ጽጌ) እንዲሁም በቱሪስት መዳረሻነቱ የሚታወቀው ሮያል ቦታኒክ ጋርደንስ ከ18ኛው እስከ 20ኛው ምእት ዓመት ድረስ የነበሩና ያሉ አትክልትና ዕፀዋት ተሰባስበው ይገኙበታል፡፡  

Saturday, October 15, 2016

‹‹የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና›› የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመበሔኖክ ያሬድ
ሶማሊያ ኢትዮጵያን በምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ ግንባሮች በወረረችበት ወቅት (1969-1970) በተዋጊ ጄት አብራሪነት ወደር የሌለው ጀግንነት በመፈጸማቸው ከቀድሞው መንግሥት ‹‹የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ›› እና የ‹‹የካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን›› ተሸላሚ የነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ሥርዓተ ቀብር መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ፡፡ በሥርዓተ ቀብራቸው በተነበበው የሕይወት ታሪክ እንደተገለጸው፣ ከሶማሊያ ጋር በ1969 ዓ.ም. በነበረው ጦርነት የኢትዮጵያ አየር ኃይል በምዕራፍ አንድ ዘመቻው ጄኔራል ለገሠና ጓዶቻቸውን አሰማርቶ ከሐምሌ 17 ቀን እስከ ነሐሴ 28 ቀን 1969 ዓ.ም. ድረስ በተናጠልና በቡድን ሆነው ከሶማሊያ አየር ኃይል ጋር ባካሄዱት የአየር ለአየር ውጊያ የጠላትን 12 ሚግ 21 እና 13 ሚግ 17 በድምሩ 25 ተዋጊ አውሮፕላኖች ከአየር ላይ በማራገፍ አኩሪ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ ጄኔራል ለገሠ በደቡብ ግንባር መስከረም 11 ቀን 1970 ዓ.ም. በነበረው ውጊያ አውሮፕላናቸው በመመታቱ በፓራሹት በመውረድ ቢተርፉም በሶማሊያ ሠራዊት እጅ በመውደቃቸው ለ11 ዓመት በጦር እስረኝነት ሶማሊያ ውስጥ ቆይተዋል፡፡ ከአባታቸው ከአቶ ተፈራ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ከወይዘሮ ተናኜ ተክለ ወልድ፣ ነሐሴ 13 ቀን 1934 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ሾላ ላም በረት አካባቢ የተወለዱት ብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ፣ የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደጃዝማች ወንድይራድና በኮከበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል፡፡ አገራቸውን በውትድርና ሙያ ለማገልገል በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ፣ ጥቅምት 1 ቀን 1956 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሐረር ጦር አካዴሚ የ7ኛ ጊዜ ተወዳዳሪ ዕጩ መኮንን በመሆን፣ አንጋፋውን የምድር ጦር ሠራዊት ሲቀላቀሉ፣ በሐረር አካዴሚ የአዛዥነትን ትምህርት ሲያጠናቅቁም ወደ አየር ኃይል ተዛውረዋል፡፡ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት የነበሩትና በ75 ዓመታቸው ያረፉት ጄኔራል ለገሠ ሥርዓተ ቀብር በኢትዮጵያ አየር ኃይል እግረኛ ወታደር ታላቅ አጀብና የማርሽ ባንድ የሐዘን ዜማ ታጅቦ ሲፈጸም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፣ የቀድሞዎቹ የኢሕዲሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ፍሥሐ ደስታና ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስን ጨምሮ የቀድሞ መንግሥት ከፍተኛ መንግሥታዊና ወታደራዊ ባለሥልጣናት  እንዲሁም ወዳጅ ዘመድ ተገኝተዋል፡፡

Friday, October 14, 2016

‹‹የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና›› የብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ሥርዓተ ቀብር ተፈጸመ

በሔኖክ ያሬድ
ሶማሊያ ኢትዮጵያን በምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ ግንባሮች በወረረችበት ወቅት (1969-1970) በተዋጊ ጄት አብራሪነት ወደር የሌለው ጀግንነት በመፈጸማቸው ከቀድሞው መንግሥት ‹‹የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጀግና ሜዳይ›› እና የ‹‹የካቲት 1966 1ኛ ደረጃ ኒሻን›› ተሸላሚ የነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ ተፈራ ሥርዓተ ቀብር መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተፈጸመ፡፡ 

በሥርዓተ ቀብራቸው በተነበበው የሕይወት ታሪክ እንደተገለጸው፣ ከሶማሊያ ጋር በ1969 ዓ.ም. በነበረው ጦርነት የኢትዮጵያ አየር ኃይል በምዕራፍ አንድ ዘመቻው ጄኔራል ለገሠና ጓዶቻቸውን አሰማርቶ ከሐምሌ 17 ቀን እስከ ነሐሴ 28 ቀን 1969 ዓ.ም. ድረስ በተናጠልና በቡድን ሆነው ከሶማሊያ አየር ኃይል ጋር ባካሄዱት የአየር ለአየር ውጊያ የጠላትን 12 ሚግ 21 እና 13 ሚግ 17 በድምሩ 25 ተዋጊ አውሮፕላኖች ከአየር ላይ በማራገፍ አኩሪ ተግባር ፈጽመዋል፡፡ ጄኔራል ለገሠ በደቡብ ግንባር መስከረም 11 ቀን 1970 ዓ.ም. በነበረው ውጊያ አውሮፕላናቸው በመመታቱ በፓራሹት በመውረድ ቢተርፉም በሶማሊያ ሠራዊት እጅ በመውደቃቸው ለ11 ዓመት በጦር እስረኝነት ሶማሊያ ውስጥ ቆይተዋል፡፡ ከአባታቸው ከአቶ ተፈራ ወልደ ሥላሴና ከእናታቸው ከወይዘሮ ተናኜ ተክለ ወልድ፣ ነሐሴ 13 ቀን 1934 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ሾላ ላም በረት አካባቢ የተወለዱት ብርጋዲየር ጄኔራል ለገሠ፣ የአንደኛ ደረጃና የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በደጃዝማች ወንድይራድና በኮከበ ጽባሕ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ተከታትለዋል፡፡ አገራቸውን በውትድርና ሙያ ለማገልገል በነበራቸው ጽኑ ፍላጎት የተነሳ፣ ጥቅምት 1 ቀን 1956 ዓ.ም. በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የሐረር ጦር አካዴሚ የ7ኛ ጊዜ ተወዳዳሪ ዕጩ መኮንን በመሆን፣ አንጋፋውን የምድር ጦር ሠራዊት ሲቀላቀሉ፣ በሐረር አካዴሚ የአዛዥነትን ትምህርት ሲያጠናቅቁም ወደ አየር ኃይል ተዛውረዋል፡፡ ባለትዳርና የሦስት ልጆች አባት የነበሩትና በ75 ዓመታቸው ያረፉት ጄኔራል ለገሠ ሥርዓተ ቀብር በኢትዮጵያ አየር ኃይል እግረኛ ወታደር ታላቅ አጀብና የማርሽ ባንድ የሐዘን ዜማ ታጅቦ ሲፈጸም የቀድሞው ፕሬዚዳንት ግርማ ወልደጊዮርጊስ፣ ብፁዕ ሊቀ ጳጳስ አቡነ ገብርኤል፣ የቀድሞዎቹ የኢሕዲሪ ምክትል ፕሬዚዳንት ፍሥሐ ደስታና ጠቅላይ ሚኒስትር ፍቅረ ሥላሴ ወግደረስን ጨምሮ የቀድሞ መንግሥት ከፍተኛ መንግሥታዊና ወታደራዊ ባለሥልጣናት  እንዲሁም ወዳጅ ዘመድ ተገኝተዋል፡፡
በሔኖክ ያሬድ

የአሹራ ክብር የአሹራ በዓል በነጋሽ ከተማ ጥቅምት 2 ቀን 2009 በተከበረበት ጊዜ


በሔኖክ ያሬድ
አሹራ በእስላማዊው የዘመን አቆጣጠር የመጀመርያው ወር በሆነው ሙሀረም በተጀመረ በ10ኛው ቀን በየዓመቱ የሚከበር በዓል ነው፡፡
በዓሉ በተለያዩ የዓለም ክፍል በሚገኙ ሙስሊሞች ይከበራል፡፡ ዓመቱን 354 (355) ቀኖች በያዘውና በጨረቃ አቆጣጠርን መሠረቱ ባደረገው እስላማዊ ካሌንደር መሠረት፣ አዲሱ ዓመት 1438 ዓመተ ሒጅራ (ዓ.ሒ.) የገባው ሙሀረም 1 ቀን (በፀሐይ መስከረም 22 ቀን 2009 ዓ.ም.) ሲሆን የአሹራ በዓልም ሙሀረም 10 ቀን 438 ዓ.ሒ. (ጥቅምት 2 ቀን) ተከብሯል፡፡
የኢስላም ካሌንደር  
ከሁለት ሳምንት በፊት የእስላማዊ አዲስ ዓመት 1438 ዓመተ ሒጅራ የባተበት ነበር፡፡ ዕለቱም የሙሀረም ወር አንደኛ ቀን የእስላሚክ የጨረቃ ካሌንደር የመጀመርያ ወር ነው፡፡ የሙስሊም ዘመን የሚሰላው ከጨረቃ መውጣትና መግባት ጋር ተያይዞ ነው፡፡ እስላማዊ የጨረቃ ካሌንደር (ሉናር ካሌንደር) የዓመቱ ቀኖች 354 (355) ሲሆን ከፀሐይ 365 ቀኖች በ11 ቀን ያንሳል፡፡ የ12 ወራት የእስላሚክ/ሒጅራ ካሌንደር የተጀመረው በሁለተኛው ከሊፋ ዑመር በ16 ዓ.ሒ. (637 ዓ.ም.) ነበር፡፡ የዓመቱ የመጀመርያ ወር፣ ሙሀረም የመታሰቢያ ወር በመባል የሚታወቅና በሙስሊም ካሌንደር ውስጥ ልዩ ስፍራ ከሚሰጣቸው ወራት አንዱ ነው፡፡
በዴይሊ ትረስት እንደተጻፈው፣ ሙሀረም ‹‹የተከለከለ›› የሚል ፍች አለውና በርካታ ሙስሊሞች በፈቃዳቸው በዚህ ወቅት ይጾማሉ፡፡ የዓመቱ መባቻ የኢድ አልአድሃና ኢድአልፈጥር ዓይነት ከፍታ ባይኖረውም፣ ነቢዩ መሐመድ የመጀመርያውን ኢስላማዊ አስተዳደር በመዲና ከተማ (ባንድ ወቅት ያትሪብ ትባል ነበር) የመሠረተበት ዕለት በመሆኑ ይወሳል፡፡
ነቢዩ መሐመድ በ622 ዓ.ም. ከመካ ወደ መዲና የተሰደዱበት ስደት ሒጅራ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ይህም የሙስሊም ካሌንደር መጀመርያና መጠርያ ሆኗል፡፡
የአሹራ በዓል
 የአሹራ በዓል ረቡዕ ሙሀረም 10 ቀን 1438 ዓ.ሒ. (ጥቅምት 2 ቀን 2009 ዓ.ም.) በተለያዩ የዓለም አካባቢዎች ተከብሯል፡፡ በተለይ በኢትዮጵያ በዓሉ በየዓመቱ ከሚከበርባቸው መስጊዶች መካከል አንዱ በሆነው በትግራይ ክልል ነጋሽ ከተማ በሚገኘው ጥንታዊ መስጊድ በልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓት ተከብሯል፡፡
ነጋሺ በሰባተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከመካ መዲና ተሰደው የመጡ ሰሃቦች የተስተናገዱበት ቦታ ነበር፡፡ ‹‹አሹራ በእስልምና ዓለም›› በሚለው መጣጥፋቸው አቶ አህመድ ዘካሪያ እንደጻፉት፣ በአሹራ ዕለት ከነቢዩ አደም ጀምሮ የታወቁት ነቢያት በሙሉ ተአምራታቸው የታየበት ቀን ነው ተብሎ ይታመናል፡፡
የአደምና የሐዋ መፈጠር፣ የነቢዩ ኢብራሂም ከእሳት ቃጠሎ መዳን፣ ሙሳ ቀይ ባሕርን ከተከታዮቻቸው ጋር ማቋረጥ፣ ኑህ ከጥፋት ውኃ መዳንና የሌሎቹም ነቢያት ተአምራት የተመዘገበበት ቀን ነው፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ (በትግራይ፣ በወሎና በጎንደር) ደግሞ አህመድ ነጋሽ የነቢዩ ሙሀመድ ቤተሰቦችን ተቀብለው ከማስተናገዳቸው፣ ከአደጋ ከመከላከላቸውና ታላቅ መሪ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ይከበራል፡፡ በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ከሐጅ ሲመለሱ ነጋሺ መስጊድ ተገናኝተው  ጸሎት ያደርሱ ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜም ይህ ልማድ ቀጥሎ ወደ ሐጅ ያልሄዱ የወሎ፣ የትግራይ፣ አልፎ አልፎ ይሁን እንጂ የጎንደር እስልምና እምነት ተከታዮች ወደዚያው በመሄድ የአሹራን በዓል ያከብራሉ፡፡ በሐረሪም በተለየ አካባበር ይከበራል፡፡
መሰንበቻውን ነጋሽ ከተማ በተገኘንበት አጋጣሚ ያነጋገርናቸው የነጃሺ መስጊድ ኮሚቴ ምክትል ሊቀመንበር ሐጂ መሐመድ አልኑር፣ የሙሀረም ወር 10ኛ ቀን የሚከበርባት አሹራ ብዙ ትርጉም እንዳላት ያወሳሉ፡፡
‹‹ሰማይና ምድር የተሆለቁት (የተፈጠሩት) በአሹራ ቀን ነው፡፡ አዳምና ሐዋ የተሆለቁት በአሹራ ነው፡፡ ጥሩ ጥሩ ሥራ የሚሠራበት ፍርድም የሚደረግበት በአሹራ ነው፡፡››
ሰው መካ መዲና እንደሚሄደው ሁሉ ብዙ ሰው ወደ ነጋሽ እንደሚመጣ ዱኣ የሚደርስበት፣ የሚዘየርበት፣ ሰደቃ የሚደረግበትም ነው ይላሉ፡፡
ሐጂ መሐመድ አልኑር
ከ65 ዓመት በፊት በነጋሽ መስጊድ ቅጥር ግቢ በአዝማች መሐመድ ሐጂ አብዱ (የቀድሞው የአገር አቋራጭ አውቶቡሶች ማኅበር የሰሜናዊ ትራንስፖርት መሥራችና ባለቤት) በተሠራው ታላቅ አዳራሽ ምግብ በማዘጋጀት ሰደቃ ሲደረግበት ኖሯል፡፡ ለዘንድሮው አሹራ በዓል ቅድመ ዝግጅት ለማድረግ መስከረም 19 ቀን 2009 ዓ.ም. የተገኙት ወ/ሮ ብርሃን ናሥራይ በየዓመቱ እንደሚያደርጉት ሁሉ ለሚመጣው እንግዳ ከብት በማረድ ምግብ እንደሚያዘጋጁ ገልጸውልን ነበር፡፡ ከሁለት ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያና በቱርክ መንግሥታት ትብብር የዕድሳትና ተጨማሪ መሠረተ ልማት እየተሠራበት በሚገኘው ነጋሽ መስጊድ ቅጥር ግቢ የሚገኘው ነባሩና ሰደቃ የሚደረግበት አዳራሽ፣ በግንባታ ሥራውም ምክንያት በመያዙ ሌላ አማራጭ እንዲሰጣቸው በጠየቁበት አጋጣሚ ነበር ያገኘናቸው፡፡
ወ/ሮ ብርሃን ናሥራይ
‹‹በየዓመቱ ሰደቃ ማብላቱን አዝማች መሐመድ አብዱ ጀመሩት፡፡ ወንድማቸው እነ ባሻ ሁሴን ይሠሩት ነበር፡፡ በሞት ሲለዩ ልጆቻቸው ቀጠሉት፤ የአሥመራ መንገድ ከተዘጋ በኋላ ተውት፡፡ ከዚያ በኋላ እኔ ተተክቼ በየዓመቱ አስተናግዳለሁ፤›› የሚሉት ወ/ሮ ብርሃን፣ ‹‹ዓመት ዓመት የሚመጣ እንግዳ መንገላታት የለበትም፡፡ እንደሌላው አካባቢ ሆቴል የለምና በየዓመቱ የምናስተናግድበት ቦታ ማጣት የለብንም፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ዓመት ዓመት እንግዳ መቀበያ መሥራታችን ትንሽ ነገር አይደለም፡፡ ብዙ እንግዳ በልቶ ጠጥቶ የሚያድርበት ቦታ ነው፡፡ አሁን ሌላ ቦታ ተቀይሮ ቢሰጠንም ለወደፊቱ ልንሠራው እንችላለን፤›› ላሉት ወ/ሮ ብርሃን ለጥያቄያቸው እድሳቱንና ግንባታውን እያካሄደ ያለው ተቋም ቀና ምላሽ ሰጥቷቸዋል፡፡ ሰደቃ ይደረግበት የነበረው አዳራሽ መጋዘን በመሆኑ በምትኩ አዲስ በታነፁት ቤቶች ውስጥ መሰናዶን እንዲያዘጋጁ ማድረጉን ከክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡
እድሳትና ግንባታ
ክፍለ ዘመናትን ያሳለፈው ነጋሽ መስጊድ ነባሩንና ታሪካዊ ይዞታው ሳይለወጥ የማደስና የመጠገን እንዲሁም በተንጣለለው ቅጥር ግቢ ውስጥ የአገልግሎት መስጫ ሕንፃዎች በቱርክ መንግሥት ድጋፍ እየተሠራ ነው፡፡ ሥራውን የቱርክ ኩባንያ እያከናወነው ሲሆን፣ በኢትዮጵያ በኩል የፕሮጀክቱ ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ሺበሺ ጫካ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የመጀመርያው ዙር ፕሮጀክት አምስት ሚሊዮን ዶላር የተበጀተለት ሲሆን፣ ከመስጊዱ እድሳት በተጨማሪ ከተከናወኑት አዳዲስ ግንባታዎች  የእንግዶች ማረፊያ፣ ምግብ ቤት፣ መፀዳጃ ቤት ሲገኙበት፣ የቅጥር ግቢ አጥርና የመስጊዱን በረንዳ የማስፋት ሥራም እየተከናወነ ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ለመስጊዱም ሆነ ለአካባቢው ኅብረተሰብ የሚያገለግል የከርሰ ምድር ውኃ የወጣ ሲሆን፣ 120 ሺ ሜትር ኪዩብ የሚይዝ በርሚል (ሮቶ) ተደርጎለታል፡፡
የነጋሽና የ15ቱ ሱሃቦች ስም የሚጻፍበት የድንጋይ ምሰሶዎች 8 በግራ 8 በቀኝ ቆመዋል
በአሁን ጊዜ 75 በመቶ ብቻ የተጠናቀቀው ፕሮጀክቱ፣ እንደ ሥራ አስኪያጁ አነጋገር የማጠናቀቂያ ሥራው በአራት ወራት ውስጥ ያበቃል፡፡ ከአዳዲስ ግንባታ መካከል ከዋናው በር እስከ ቀደምቱ ሱሃቦች መካነ መቃብር የሚወሰደው መንገድ በዘመናዊ መልክ የተገነባና በመተላለፊያው የነጋሽና የ15ቱ ሱሃቦች ስም የሚጻፍበት የድንጋይ ምሰሶዎች 8 በግራ 8 በቀኝ ቆመዋል፡፡ የያንዳንዱ ስም በአማርኛ፣ በቱርክኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች እንደሚጻፍና ሰዎች በሚገቡበት ሰዓት ስሞቹን እያነበቡ ወደ ታሪካዊ ቦታ እንዲገቡ ለማድረግ የታሰበ እንደሆነ ሥራ አስኪያጁ ተናግረዋል፡፡
የአል ነጃሺ ቅዱስ ስፍራን ለማደስ፣ ለመጠገንና መልክአ ምድራዊ ገጽታውን ለማሳመር በቱርክ ሪፐብሊክ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሥር የሚገኘው የቱርክ ኩባንያ ቲካ፣ ከትግራይ ባህልና ቱሪዝም ቢሮና ከክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ጋር በመሆን ሥራውን እያከናወነ ነው፡፡ እንደ ኢንጂነር ሺበሺ መግለጫ የመጀመርያው ፕሮጀክት ከተጠናቀቀ በኋላ በሁለተኛው እቅድ በነጋሽ ከተማ የዕደ ጥበባት ማዕከል፣ ሆቴሎች፣ ካፌና የእንግዳ ማረፊያዎች ይሠራሉ፡፡ ይህም የቱሪስቱን ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ ያሳድገዋል የሚል ተስፋም አላቸው፡፡

Saturday, October 8, 2016

ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል (1928 – 2009)


በሔኖክ ያሬድና በነአምን አሸናፊ
ከሩብ ምዕ ዓመት ወዲህ በኢትዮጵያ ፖለቲካ መድረክ በተለይም በተቃውሞው ጎራ ግንባር ቀደም መሪዎች ከነበሩት አንዱ የነበሩት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል አረፉ፡፡
የመላው አማራ ሕዝብ ድርጅት (መአሕድ) ምክትል ሊቀመንበርና የውጭ ግንኙነት ኃላፊ፣ የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) መሥራችና ሊቀመንበር፣ እንዲሁም የቀድሞው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ (ቅንጅት) ሊቀመንበር የነበሩት ኢንጂነር ኃይሉ በ80 ዓመታቸው መስከረም 26 ቀን 2009 ዓ.ም. ያረፉት የስኳር ሕመም ሕክምና ሲከታተሉበት በነበረው በባንኮክ ታይላንድ ነው፡፡
በ1997 ዓ.ም. በተካሄደው አገራዊ ምርጫ ወቅት ከጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች አንዱ የነበረውን ቅንጅትን በምርጫው ዋዜማ የመሠረቱት መኢአድ፣ ኢዴፓ (የኢትዮጵያውያን ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ)፣ ኢዲሊ (የኢትዮጵያ ዲሞክራሲያዊ ሊግ) እና ቀስተ ዳመና ሲሆኑ ኢንጂነር ኃይሉ በሊቀመንበርነት መርተውታል፡፡ ከምርጫው ውጤት በኋላ በተነሳው ተቃውሞ ከቅንጅት መሪዎች ጋር ለእስር ከተዳረጉ በኋላ፣ ከሌሎች 23 የቅንጅት መሪዎች ጋር በአገር ክህደትና በዘር ማጥፋት ክስ ተመሥርቶባቸውና ተፈርዶባቸው ነበር፡፡
በታኅሳስ 2000 ዓ.ም. የፓርቲው አመራሮች ባቀረቡት የይቅርታ ጥያቄ መሠረት በአገሪቱ ፕሬዚዳንት ምሕረት ተደርጎላቸው መለቀቃቸው ይታወሳል፡፡ በፖለቲካ ተሳትፏቸውም መኢአድን ለአሥር ዓመታት፣ ቅንጅትን ደግሞ ለተወሰነ ጊዜ በሊቀመንበርነት የመሩት ኢንጂነር ኃይሉ የተወለዱት በሰሜን ሸዋ አንኮበር በ1928 ዓ.ም. ሲሆን፣ ከፍተኛ ትምህርታቸውን በአሜሪካ ዌይን ስቴት ዩኒቨርሲቲ (Wayne State University) በሲቪል ምሕንድስና አጠናቀዋል፡፡ በ1950 ዓ.ም. ከተመለሱ በኋላ ሥራ የጀመሩት በአሜሪካኖች በሚመራው የዓባይ ሸለቆ ጥናት ፕሮጀክት በኃይድሮሎጂስትነት በመቀጠር ነበር፡፡
በሼል ኢንተርናሽናል የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ካገለገሉ በኋላ በኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት በ1963 ዓ.ም. የቀድሞው የአውራ ጎዳና ባለሥልጣን (የአሁኑ የኢትዮጵያ መንገዶች ባለሥልጣን)፣ ዋና ሥራ አስኪያጅ በመሆን ተሹመው ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል፡፡
በኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ መንግሥት ዘመን የኢትዮጵያ ስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የወንጂና የመተሐራ ስኳር ፋብሪካዎችም ሥራ አስኪያጅ ነበሩ፡፡
በመንግሥት ይዞታ ሥር የሚገኙ እርሻዎችን የሚመራው የመንግሥት እርሻዎች ልማት ሚኒስትር ሆነው ለሁለት ዓመት ከመንፈቅ ሠርተዋል፡፡
በ1975 ዓ.ም. የመንግሥት ሥልጣናቸውን ትተው የራሳቸውን ሻውል አማካሪ የተሰኘ ድርጅት መሥርተዋል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ልጃቸው ዶ/ር ሻውል ኃይሉ እየመሩት ይገኛል፡፡
ባለትዳርና የአምስት ወንድና የአንዲት ሴት ልጅ አባት የነበሩት ኢንጂነር ኃይሉ ሻውል አስከሬን፣ መስከረም 30 ቀን 2009 ዓ.ም. አዲስ አበባ እንደሚገባ መኢአድ አስታውቋል፡፡