Friday, September 2, 2016

ኢሬቻ


በሔኖክ ያሬድ
‹‹አምና በሰላም በጤና 13ቱን ወር አስጨርሰኸናል፡፡ መጪውን ዓመት ደግሞ በሰላም እንድታደርሰን ይሁን፡፡ ይኸንን ለሰው ልጅ ለሁሉም ፍጥረት ብለህ የፈጠርከውን ንፁህ ውኃ በአንተ ኃይል አጣርተህ ያስቀመጥከውን በሐይቅህ ላይ ምስጋናህን እናቀርባለን፡፡ ውኃ ንፁህ ነውና››
ይህ ምርቃት እሑድ መስከረም 25 ቀን 2007 ዓ.ም. በቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ (አርሰዲ ሐይቅ) ዳርቻ አንጋፋው አቶ ስለሺ ዳባ በባህላዊ የኦሮሞ አለባበስ ተውበው የአንበሳ ለምድ አጥልቀው አንፋሮ ደፍተውና ጋሻ ይዘው ነው፡፡
ቡራኬው በየዓመቱ ከመስቀል በዓል በኋላ በሚመጣው እሑድ የሚከበረውን የኢሬቻ በዓል ተከትሎ የመጣ ነው፡፡ ኢሬቻ ከተከበሩትና ከተቀደሱት የኦሮሞ ክብረ በዓሎች አንዱ ሲሆን ከጥንታውያኑ የኦሮሞ አባቶች ሲወርድ ሲዋረድ እንደመጣ ይነገራል፡፡ በዓሉ በቢሾፍቱ ከተማ ባለፈው እሑድ ሲከበር በሚሊዮን የሚቆጠር ሕዝብ በመገኘት ለበዓሉ ድምቀት ሰጥቶታል፡፡
ከተለያዩ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች የመጡ በዓል አክባሪዎች የአካባቢያቸውን ባህል የሚያንፀባርቁ አልባሳት ለብሰው ጫማ ተጫምተው ጌጣጌጥ አጥልቀው ታይተዋል፡፡
‹‹ኢሬቻ እርጥብ ሣር፣ ቅጠል ቄጠማ አበባ ማለት ነው›› የሚሉት የኦሮሞ አባ ገዳ ዋና ሰብሳቢ የሆኑት አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ፣ ኢሬቻው ለእግዚአብሔር ምስጋና የምናቀርብበት ሥርዓት ነው ይላሉ፡፡ ‹‹ኢሬቻ ሣሩን አበባውን እግዚአብሔር ነው ያበቀለው፡፡ ይኸንን አበባውን አብቅለህ ለከብቶች ሣር አብቅለህ፣ ለሰው ልጅ ደግሞ ዘር ሰጥተህ፣ ፍሬ አሰጥተህ ስላደረስከን ለአንተ ኢሬቻ እናቀርባለን፡፡ በክረምቱ መልካው ወንዙ ሞለቶ ዘመድ ከዘመድ ተለያይቶ አሁን ስለተገናኘ እግዚአብሔር ሆየ አንደርስብህምና ለአንተ ኢሬቻ እናቀርባለን፡፡››
በዓሉ በምርቃት ያስጀመሩት ከተለያዩ የኦሮሚያ ዞን የመጡ አባ ገዳዎች እና የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን ናቸው፡፡
እንደ አባ ገዳ በየነ አገላለጽ፣ የመመረቂያው ቦታ አድባር ‹‹ድሬ›› ይባላል፤ የተስተካከለ ቦታ ማለት ነው፡፡ ከዚህ ካልተመረቀ ወደታች ወደ ሐይቁ አይኬድም፡፡ ዱለቻ በሬ ይታረዳል፡፡ ከመልካውም ሲኬድ ኮርማ ይታረዳል፡፡ ምርቃቱም ‹‹እንኳን በሰላም ከክረምቱ ወደ ብርሃኑ አወጣኸን፡፡ ዘመኑን በሰላም ያድርግልን፡፡ የእኛን ሕዝብና አገሪቷን ይባርክልን›› የሚል ነበር፡፡
ሆራ አርሴዲ የክብረ በዓሉ ዋነኛ ስፍራ ነው፡፡ ሰፊና ክብ ነው፡፡ አካባቢው ዙርያው በዛፎች ተሸፍኗል፡፡ ለበዓሉ አክባሪዎችና ሥነ ሥርዓቱ ተከታዮች ምቹ ስፍራ ነው፡፡ ታዳሚዎቹ ለምለም ቅጠል ቀጤማ ርጥብ ሣር አደይ አበባ ይዘው ሐይቁ ውስጥ እየነከሩ ይረጫሉ፤ ወደራሳቸውም ያስነካሉ፡፡ ከሐይቁ ዳርቻም ያስቀምጣሉ፡፡ ክርስቲያኖችም፣ ሙስሊሞችም፣ የዋቄ ፈታ ተከታዮችም አሉበት፡፡ ዝማሬና ምርቃት ልዩ ልዩ ሥነ ሥርዓት በሐይቁ ዳርቻ በሚገኘው ዋርካ ሥር ያደርጉታል፡፡ ዋርካውን ‹‹ኦዳ›› ይሉታል፡፡
በኦዳው ዙሪያ ወንዱና ሴቱ አዋቂውና ሕፃኑ በቡድን በቡድን ተቀምጠዋል፤ እጣኑን ያጨሳሉ፣ ሰንደሉን ይለኩሳሉ፡፡ ለሰንደሎች ማስቀመጫ በተሠራው ክብ ብረት ላይ ያስቀምጡታል፡፡ ቡናውን ያፈላሉ፣ ይቀማምሳሉ፡፡ ኅብረ ዝማሬ ያሰማሉ፡፡ ከተቀመጡት ሌላ በርካታ ቁጥር ያለው ሰው ዙሪያውን ቆሞ በጽሞና ሥነ ሥርዓቱን ይከታተላል፡፡ ጸሎቱን ያደርሳል፡፡ በቅርብ ርቀትም ባህላዊውን ጨዋታ የሚያደርጉ ወንዶችም ሴቶችም ይታያሉ፡፡ ተቀምጠው በዓሉን ከሚያከብሩት መካከል የቢሾፍቱ ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ ዓለምነሽ ተፈራ፣ ‹‹እንኳን ከድፍርሱ ውኃ ወደጠራው ውኃ አሸጋገርከን የምንልበት ኢሬቻ መልካውን የምናከብርበት፣ ሴራውን የምንፈጽምበት ነው፤ መሬሆ የተባለ የምስጋና መዝሙር እናሰማበታለን፤›› ብለዋል፡፡
እጆቻቸው በልዩ ልዩ ቅርፅ የተዘጋጁ በትሮች ይዘው ኢንፋር ራሳቸው ላይ አጥልቀው የሚጨፍሩ ጎረምሶችም ይታያሉ፡፡ በኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማና በኦሮሚያ ክልል ባንዲራ ባሸበረቀው አካባቢ ከተገኙት እድምተኞች የተለያዩ ባህላዊ ልብሶች ቀይ ነጭና ጥቁር ኅብረ ቀለማት ያለውን የባህል አልባሳት ለብሰው ይታያሉ፡፡
ከእነዚህም መካከል ከሰንዳፋ የመጡት አቶ ስለሺ ዳባ ያጠለቁት አንፋሮ የአንበሳ ምልክት፣ የያዙት ጋሻ (ዋንታ) ውኃ ውስጥ ከሚኖረው የጉማሬ ቆዳ የተለበደበት ነው፡፡ ‹‹ወደ ሆራ አርሴዲ ሲወረድ ሴራ (ሥርዓት) አለው፡፡ በዋንታው ውኃ ይቀዳና ይረጭበታል፤›› ብለዋል፡፡
በበዓሉ ላይ ከአባ ገዳዎች ጋር ሲመርቁ ያገኘናቸው ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ዋና ሥራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ ‹‹ኢሬቻ ትርጉሙ እርቅ ማለት ነው፡፡ ሰዎችና ሰዎች የሚታረቁበት እግዜርና ሰው የሚታረቁበት ሰላም፣ ስምምነት አንድነት ምቾት ማለት ነው፡፡ በክረምት ወንዞች ሄደው ሳያልቁ ሳይደርቁ እዚህ ያለውና እዚያ ሳይገናኝ ይቆያል፡፡ ስለዚህ ወደ ወንዙ ይሄድና ከወዲህና ማዶ ያለው ‹አላችሁ ደርሳችኋል እኛ ደርሰናል› እያለ እርስ በርስ ሰላምታ ይለዋወጣል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ኢሬቻውን ፈጽሞ ይሄዳል፡፡››
ኢሬቻ የተከበረበት መስከረም 25 የክረምት ማብቂያ ማግስቱ መስከረም 26 ቀን የመፀው ወቅት የአበባ መግቢያ መሆኑን የሚናገሩት ሊቀ አዕላፍ ቀሲስ በላይ፣  መስከረም 25 ቀን (በኋላ መስከረም 10) ተቀፀል ጽጌ (አበባን ተቀዳጅ) እየተባለ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን ከነበሩት አፄ ገብረ መስቀል ዘመን ጀምሮ እስከ አፄ ኃይለ ሥላሴ ድረስ በቤተ መንግሥት ይከበር እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
በኢሬቻ ላይ በክብር እንግድነት ከተገኙት ከፍተኛ ሹማምንት መካከል የተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ ይገኙበታል፡፡ በክብር ቦታቸው ላይ እንዳሉ ኢሬቻን እንዴት ይገልጹታል? አልናቸው፡፡ ፈገግታ በማይለየው አንደበታቸውም፣ ‹‹ኢሬቻ የገዳ ሥርዓት አንድ አካል መሆኑን ለሺሕ ዓመታት በኦሮሞ ባህል ውስጥ የቆየ፣ ኦሮሞዎች አደይ ሲፈነዳ በጋራ ተሰብስበው አንድ አምላካቸውን የሚያመሰግኑበት፣ ዝናባማ ደመናውን ያሳለፈ፣ አዲሱን ዓመት ደግሞ በሰላም እንድንከርም አድርገን የሚሉበት፣ ያለፈው ታሪክ እንዳይደገም የሚማፀኑበት መሆኑን አወጉን፡፡ ባለፈው የተጣላ ይታረቃል፡፡ ቂም የተያያዘ ይታረቃል፣ ያላገባ እንዲያገባ መጥፎ ሱስ ያለው እንዲተው ብዙዎች ነገሮች አባ ገዳው በሚያውጁት መሠረት ይሄዳልም አሉን፡፡
‹‹የአባ ገዳውን አዋጅ ዓመቱን ሙሉ የሰማው ሁሉ ስለሚያከብረው ትልቅ ነገር ነው፡፡ እኔ ኢሬቻን በጣም ነው የምወደው›› የሚሉት አፈ ጉባኤ አባዱላ፣ ‹‹እንደምታዩት ከተለያየ አካባቢ ሃይማኖት ሳይገድባቸው የተለያየ ክልል ውስጥ መኖራቸው ሳይከልላቸው የሚሰበሰቡበት፣ የሚነጋገሩበትና የሚጨዋወቱበት እዚህ ለመድረሳቸው ምስጋና የሚያቀርቡበት፣ አዲሱን ዓመት በብሩህና በተስፋ ለማሳለፍ የሚመኙበት በዓል ስለሆነ ሁልጊዜ እዚህ መገኘት እፈልጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡
ኢሬቻን ከገዳ ሥርዓት ጋር በማያያዝ በዓለም መንፈሳዊ ቅርስነት ለማስመዝገብ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ከቅርብ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር ከ2005 ዓ.ም. ጀምሮ ጥናት እየሠራ መሆኑን የቢሮው ኃላፊ አቶ መሐሙድ ጅሎ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ (R1507 Culture)

No comments:

Post a Comment