እንዴት ነው ነገሩ?
መሰንበቻውን የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ከአፍሪካ
ኢኮኖሚ ኮሚሽን ጋር በመተባበር ለመጪዎቹ አሥር ዓመታት የቱሪዝም ኢንዱስትሪው የሚመራበትን ማስተር ፕላን ይፋ አድርጓል፡፡ ኢትዮጵያ
ከአፍሪካ አምስት ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻዎች አንዷ እንድትሆን ለማድረግ ራዕይ ሰንቆ የተነሣው ሚኒስቴሩ ከ2006 ዓ.ም. ጀምሮ
እንቅስቃሴ መጀመሩ ይታወሳል፡፡
ሐምሌ 23 ቀን 2006 ዓ.ም. በተካሄደው የግብዓት
ማሰባሰቢያ የምክክር መድረክ ላይ እንደተወሳው ማስተር ፕላኑ የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ካዘጋጀው የቱሪዝም
መሥፈርት ማስተር ፕላን (2013 - 2023) ጋር በተመሳሳይ የሚሠራ ነው፡፡
‹‹The
Federal Democratic Republic of Ethiopia Sustainable Tourism Master Plan
2015-2025›› በሚባል የሚታወቀው ዐቢይ ሰነድ መሠረት በዐሠርት ውስጥ ሊተገበሩ ለታቀዱት ዕቅዶች
5.446 ቢሊዮን ብር ሊያስፈልግ እንደሚችል ተመልክቷል፡፡
ስትራቴጂካዊ ተግባራት ተብለው በ10 ዓይነቶች
ለተዘረዘሩት እንደ መንደርደርያ የአገሪቱን ገጽታ፣ የቱሪዝሟን ጥንተ ታሪክ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ቅርሶችን፣ የኦሊምፒክ በተለይም አትሌቲክሱን
የሚመለከቱ መጣጥፎች የሰነዱ አካል ናቸው፡፡
በተለያዩ ከተሞች በድሬዳዋ፣ መቐለና አዲስ አበባ
ከዞናዊ ባለድርሻ አካላት ጋር ምክክር መደረጉ፣ ረቂቅ ሰነዱም የተለያዩ ሒደቶችን አሳልፎ የመጨረሻው ደረጃ ላይ መድረሱ ያመለክታል፡፡
የመጀመሪያው ረቂቅ ከኅዳር 2006 ዓ.ም. እስከ
መስከረም 2007 ዓ.ም. መከናወኑ በወሩም ለዐውደ ጥናት መቅረቡ፣ በተገኘው ግብዓት መሠረትም በጥቅምትና በኅዳር ሁለተኛው ረቂቅ
መዘጋጀቱ፣ በማግስቱም በሁለተኛው ረቂቅ ላይ በቀረበ መግለጫና ውይይት መሠረት የመጨረሻው ሰነድ ኅዳር 5 ቀን 2007 ዓ.ም. መከናወኑ
ተገልጿል፡፡
ከአንድ ዓመት ከዘጠኝ ወር በኋላ ሰነዱ ይፋ
የሆነው በቅርቡ በኢሊሊ ሆቴል በተዘጋጀው መድረክ ነበር፡፡ የተለያዩ የምክክር መድረኮችን ያለፈው ሰነድ ልብ ያልተባሉ እንደ ክፍተት
የሚቆጠሩ ነጥቦች እዚህ ላይ ይነሳሉ፡፡
ባለ 10 ዓመቱ ማስተር ፕላን የዘመን ማዕቀፍ
ከ2015 እስከ 2025 እንደሆነ ያመለክታል፡፡ መነሻው ጃንዋሪ 2015 መድረሻው ዲሴምበር 2025 ከሆነ የዓመቱ ቁጥር 11 እንጂ
10 አይሆንም፡፡ የሰነዱ ቅድመ ዝግጅት ከኖቬምበር 2013 እስከ ኖቬምበር 2014 ዘልቋልና፡፡ መሆን የሚኖርበት 2015 –
2024 ወይም 2016 – 2025 ነው፡፡
የኢትዮጵያን ቱሪዝም የተሻለ ለማድረግ የተቀረፀው
ማስተር ፕላን የመጨረሻ ምክክሩን በጥቅምት 2007 ሲያደርግ ሚኒስቴሩ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የመጀመሪያ
ዓመት (2008) ተግባራዊ ይደረጋል ማለቱ ይታወሳል፡፡ ማስተር ፕላኑ ይፋ የተደረገው ግን በዕቅዱ ሁለተኛ ዓመት ላይ ነው፡፡
እንዴት ነው ነገሩ?
የመግቢያው
ፎቶ
በማስተር ፕላኑ ገጽ 16 ባለቀለም ፎቶ የሚያሳየው
ሙክታር እድሪስ የተሰኘ አትሌት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ይዞ ነው፡፡ የፎቶው መግለጫ ሙክታር ሐምሌ 7 ቀን 2004 ዓ.ም. በባርሴሎና
በተካሄደው የዓለም ወጣቶች አትሌቲክስ ሻምፒዮና በ5000 ሜትር ማሸነፉን ያሳያል፡፡ ለዚህ ፎቶ መለጠፍ ምክንያቱ ግን ኢትዮጵያ
ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ ጨዋታዎች መሳተፍ የጀመረችበት እ.ኤ.አ. 1956ን ለማጀብ ነው፡፡
የአትሌቲክስ ሻምፒዮና ፎቶ እንዴት የኢትዮጵያ
ኦሊምፒክ ፎቶን ይገልጻል? ከኢትዮጵያ አልፎ በጥቁር አፍሪካውያን ዘንድ በሮም ኦሊምፒክ (1960) የመጀመሪያው የኦሊምፒክ ባለወርቅ
ለዚያውም በባዶ እግሩ ሮጦ ያሸነፈ፣ ከአራት ዓመት በኋላ በቶኪዮ የዓለምንና የኦሊምፒክ ክብረወሰኖች የሰባበረው አበበ ቢቂላ ፎቶግራፍ
ጠፍቶ ነው? ለነገሩ መጣጥፉ አበበ ቢቂላ በቶኪዮ ‹‹የኦሊምፒክ ሪከርድ አሻሻለ›› ብቻ ነው ያለው፡፡ እንዴት ነው ነገሩ?
ሩጫ በኢትዮጵያ (Running
in Ethiopia) የሚለው ንኡስ ምዕራፍ አገሪቱ በርካታ ሻምፒዮኖችን ከበኩሩ አበበ ቢቂላ ጀምሮ ማፍራቷን
በመግለጽ ይጀምራል፡፡ መጣጥፉ ከአበበ ቢቂላ በቀጥታ የተሻገረው ወደ ኃይሌ ገብረሥላሴና ቀነኒሳ በቀለ፤ መሠረት ደፋርና ጥሩነሽ
ዲባባ ነው፡፡ ምሰሶዎቹ አትሌቶች በሜልቦርን (እ.ኤ.አ. 1956) ፋና ወጊዎች መካከል ለስኬት የበቃው በሜክሲኮ ኦሊምፒክ
(1968) በማራቶንና በ10ሺ ሜትር የወርቅና ብር ሜዳሊያ አሸናፊው ማሞ ወልዴ፣ በሞስኮ ኦሊምፒክ (1980) በ5ሺና 10ሺ የሁለት
ወርቅ አሸናፊ በመሆን የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊና አፍሪካዊ የሆነው ‹‹ማርሽ ቀያሪው›› ምሩፅ ይፍጠር፣ የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት በባርሴሎና
ኦሊምፒክ (1992) 10ሺ ሜትር ባለወርቅ ኢትዮጵያዊት ደራርቱ ቱሉ፣ በአትላንታ ኦሊምፒክ (1996) የመጀመሪያዋ አፍሪካዊት የማራቶን
ባለወርቋ ፋጡማ ሮባ ለምን ተረሱ?
ከምክክሩ መድረክ የኦሊምፒክ ኮሚቴ ለምን አልተጋበዘም?
በወቅቱ የነበረው ስፖርት ኮሚሽንስ? እንዴት ነው ነገሩ?
ኢትዮጵያን ለቱሪስት መዳረሻነት ከሚያነቃቁት
ነገሮች መካከል በዩኔስኮ (የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት የሳይንስና የባህል ድርጅት) በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡት ባህላዊና
ተፈጥሯዊ ቅርሶች ይጠቀሳሉ፡፡ ዘጠኝ በማስመዝገብ ከአፍሪካ ቀዳሚ ናት፡፡ የማስተር ፕላን ሰነዱ እነዚህን በአግባቡ ጠቅሷቸዋል፡፡
ጊዜያዊ መዝገብ (ሊስት) ውስጥ የተያዙ አምስት ቅርሶችም ተመልክተዋል፡፡ ለዚህም የረዳው የዩኔስኮ ድረ ገጽ መሆኑም አይሳትም፡፡
ከግዙፍ ቅርሶች ሌላ ረቂቅ/ኢንታንጀብል ባህላዊ
ቅርሶች በሰው ልጅ ወካይ ቅርስነት በ2006 ዓ.ም. የተመዘገበው የመስቀል በዓል በሰነዱ ቢመለከትም፤ በ2008 ዓ.ም. ሁለተኛው
ወካይ ቅርስ ሆኖ የተመዘገበው የሲዳማ ባህላዊ የዘመን መለወጫ ‹‹ፊቼ ጫምባላላ›› በሰነዱ አልተገለጸም፡፡ ሰነዱ ከዓመት በፊት
መጠናቀቁ ቢታወቅም፣ ምናልባት ካልታተመ ማሻሻል አይቻልም ነበር?
እሱም ባይቻል? ጊዜያዊ መዝገብ ውስጥ ያሉት
ለ2015 ፊቼ ጫምባላላ፣ ለ2016 የኦሮሞ ገዳ ሥርዓትና ኢሬቻ ተብሎ መጥቀስ ያልተቻለው ለምንድን ነው? በምክክሩ መድረክ ከቅርስ
ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በተለይ ከዘርፉ ጋር የተያያዙ ባለሙያዎች አስተያየት እንዲሰጡበት ለምን አልተደረገም?
ኢትዮጵያ በዩኔስኮ ያስመዘገበቻቸው ዓይነተኛ
ቅርሶች በሁለቱ ጎራ ብቻ የተመደቡ አይደሉም፡፡ የራሷ ፊደል፣ የራሷ አኀዝና ባለ 13 ወራት የዘመን አቆጣጠር ያላት ኢትዮጵያ መሆኗ
በሰነዱ ለምን አልጎላም?
መጽሐፍ ቅዱስ ከተጻፈባቸውና ከተተረጐመባቸው
ስድስት ቋንቋዎች አንዱ በሆነው በግእዝና በአማርኛ የተጻፉ ልዩ ልዩ ብራናዎች (ሰነዶች) መካከል 12ቱ በዩኔስኮ በዓለም ጽሑፍ
ቅርስነት (Memory
of the world Register) መመዝገባቸው እየታወቀ እንዴት የቱሪዝሙ ማስተር ፕላን ሳያካትተው ቀረ?
እነሱ ብቻም አይደሉም፤ የቀድሞው የመንግሥታት
ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) ጥንታዊ ሰነዶች በዓለም ቅርስነት ሲመዘገቡ አንዱ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ (1923 - 1967) የፋሺስት
ኢጣልያ የ1928 ዓ.ም. ወረራን በመቃወም በጄኔቭ ሸንጎ ፊት ያደረጉት ትንቢታዊና ታሪካዊ ንግግር ጽሑፍ ነበር፡፡ እንኳን ይሄ
ሊካተት በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ የሚታወቁት 12ቱ የሚያስታውስ ከአዘጋጆቹ አንድ እንኳ እንዴት ጠፋ?
እንዴት ነው ነገሩ?
ለዘመናት ሲባል የኖረው የ3,000 ዓመት ታሪክ
እንዴት እልፍ ማለት አቃተው? ባለፉት አሠርታት በተደረጉ ጥናቶችና ይፋ በሆኑ አርኪዮሎጂያዊ ግኝቶች ጥንታዊው የኢትዮጵያ ዘመን
ከ4,000 ዓመታት በላይ መሆኑን በየሃ፣ በመነበይቲ፣ በውቕሮ (ትግራይ) የተገኙት ቁሳዊ ሀብቶች ተረጋግጧል፡፡ ከይሓና ከአክሱም
በፊት የደአማት ሥርወ መንግሥት እንደነበረስ ይህን የሚያመለክት አካል አልተገኘም ይሆን?
አብያተ ክርስቲያናት፣ ገዳማትና መስጊዶች (Timeless
churches, Monasteries and Mosques) በተሰኘው
ንኡስ ክፍሉም በላሊበላና በትግራይ የሚገኙት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከ13ኛው ምታመት ጀምሮ እንደታነፁ ይገልጻል፡፡ የላሊበላው
በ12ኛው ምታመት መገባደጃና በ13ኛው ምታመት በነገሠው ቅዱስ ላሊበላ መሠራቱ ይታወቃል፡፡ የታሪክ ሰነዶች እንደሚያሳዩት በትግራይ
የሚገኙት ከ120 በላይ የሚቆጠሩት ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ከአራተኛው ምታመት ጀምሮ በየምታመቱ መታነፃቸው ይወሳል፡፡
ከአዲስ አበባ ከተማ መስህቦች መካከል የቅርብ
ዘመኑ ከ40 ዓመት በፊት በተደረገው የኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት፣ እንደሰነዱ አገላለጽ በኦጋዴን ጦርነት የኢትዮጵያና ኩባ ወታደሮች
መታሰቢያ የቆመው ትግላችን ሐውልት፣ ፎቶው ከነመግለጫው ታትሟል፡፡ ይሁን እንጂ በፀረ ቅኝ አገዛዝ ትግል የአውሮፓዊቷ ወራሪ ጣሊያንን
በቅድሚያ ዓድዋ (1988 ዓ.ም.) ላይ ላንበረከኩት በኋላም በፋሺስት ጣሊያን ወረራ ጊዜ (1928-1933) ድል ለመቱት የኢትዮጵያ
እርመኛ አርበኞች መታሰቢያ ከቆሙት ሐውልቶች አንዱን መጥቀስ ሳይቻል እንዴት ቀረ?
‹‹ነውን ለማወቅ ነበርን ጠይቅ ነውና!›› እንዴት
ነው ነገሩ?