‹‹ይወስዳል
መንገድ፤ ያመጣል መንገድ፣
አንድም
የሚያስደስት አንድም የሚያሳዝን›› ብል ማን ከልክሎኝ፡፡ እየተጓዝን ነው፡፡ ከአራዳ ጊዮርጊስ በቸርችል ጎዳና ቁልቁል እየወረድን
ነው፡፡ ረዳቱ ‹‹ይወስዳል መንገድ . . .›› እያለ ያዜመውን ያንጎራጎረውን የሰሙት ከጥግ የተቀመጡት ሃምሳዎቹን ያገባደዱት ተሳፋሪ
‹‹አዎ ይወስዳል መንገድ. . . እውነትህን ነው፡፡ ሐሴትና ብካይን ደስታና ሐዘንን እያፈራረቀ ይወስደናል፤›› አሉት፡፡ ግራና
ቀኝ ገልመጥመጥ እያሉ፡፡ ግንቦት መገባደጃ ነው፡፡ ግንቦት የወራት ሁሉ ቁንጮ ያሰኘው መንግሥት የተለወጠበት አጋጣሚ ነው፡፡ ታክሲውም
እያመራ ያለው እያቆለቆለ ያለው ወደ ቦሌ ነው፡፡
አንደኛው
ተሳፋሪ ረዳቱን ‹‹አብዮት ነው የምትጥለኝ›› ይለዋል፡፡ ‹‹ምን እጥልሃለሁ አወርደሃለሁ እንጂ ደርግ እንደወረደው ሳይሆን በክብር
አወርድሃለሁ እንጂ›› ሆነ መልሱ፡፡ ይሄኔ ነው ከጎልማሳነት ያለፉት ተሳፋሪ ትውስታቸውን ማውጋት የጀመሩት፡፡ ‹‹ረዳት ለመሆኑ
ይህ የምንወርድበት ጎዳና ስሙን ታውቀዋለህ? ለነገሩ ብዙዎች አያውቁትም?››
ቀጠለ
ረዳቱ፣ መለሰ የምድር ተሽከርካሪ አጋፋሪው፤ ‹‹ምነው አባቴ ቸርችል ጎዳናን ሁሌ የምንጠራውን ነው እንዴ የሚጠይቁኝ?››
‹‹እሱማ
የአሁን ስሙ ‘ኮ ነው፤ የድሮውን ነው የምልህ ‹አብዮት አብዮት› ትላለህ ከቀረ ዘመን የለውም፤ ‹መስቀል መስቀል› አትልም›› አብዮት
አደባባይ መጠሪያው በግንቦት ከተገረሰሰው ደርግ ጋር መቅረቱን እንዳላጣው የተናገረው ረዳቱ፣ ‹‹መስቀል መስቀል ብል ማንን ልትሰቅል
ነው? ቢሉኝ ምን ልመልስ ነው? ሆሆ ጎመን በጤና አንቀጽ ቢጠቅሱብኝ ማን ያተርፈኛል? ቃሊቲ መውረዴ አይደል፤›› ተሳፋሪው ሁሉ
አውካካ ሳቅ በሳቅ፡፡ ‹‹እውነቱን ነው›› አለች አንዷ መለሎ ተሳፋሪ፤
‹‹የዓይኖቿ
ውበት የአንገቷ ሙስና
ሮብ
ያስገድፋል እንኳን ሐሙስና›› ለሷ ዓይነት የተገጠመ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ቀጠለች ‹‹ታሪካችንን በቅጡ ባለማወቃችን ለአጓጉል ነገር
ይዳርገናል፡፡ ብናውቅም በማያውቁት ላይ ብንወድቅ ለከፋ ነገር እንዳይዳርገን ምን ዋስትና አለ?››
‹‹መስቀል
መስቀል. . . ብሏል ብሎ ዘብጥያ ቢወርድ ነገ አዋቂ ሰው አይጥፋ እንጂ መለቀቁ አይቀርም›› አለ አንድ ፕሮቶኮሉን የጠበቀ ‹ስሪ
ፒስ› የተላበሰ የኮቱ ደረት ላይ ‹‹Rio 2016›› የሚል ጽሑፍ የሰፈረበት ፒን የለጠፈ፡፡ ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ እየጠበቀ
ያለው የሪዮ ኦሊምፒክ የሚጠብቅ ይመስላል፡፡ ‹‹የመስቀሉ ታሪክ እስከሚጣራ ማን ይታሰራል፤ ተረቱን አልሰማህም እንዴ! አለች ውቢቷ
ተሳፋሪ፡፡ ተረቱንም ተረተች፡፡
‹‹አንዲት
ጥንቸል እየሮጠች ነው፤ ማረፍ የለም፤ የሚያውቋት ሁሉ ሰላምታ ሊያቀርቡላት ቢሞክሩም የድንጋጤ ሩጫዋ ማለቂያ አልነበረውም፡፡ ፌቆ
አገኘቻትና ‹ምነው እንዲህ ያስሮጥሻል? ማነው ያስደነበረሽ?› አለቻት፡፡ ‹‹አልሰማሽም እንዴ ታላላቆቹ አራዊት እነ አንበሳ፣ ነብር እንዲያዙ ታዟል ‘ኮ›› ስትላት፣ ‹‹ታዲያ አንቺ ምን ቤት ነሽ? አይመለከትሽ›› ከማለቷ ከአፏ ቀበል አድርጋ ‹‹እስኪጣራ ማን ይያዛል?›› ሆነ መልሷ፡፡››
ተሳፋሪው
ሁሉ አውካካ፣ ሳቁን መቆጣጠር ያቃተው ረዳቱ ‹‹ይሄም አለ ለካ! አፌ ቁርጥ ይበልልሽ፣ በአንድ ሬዲዮ የሰማሁት ‹ነገር በምሳሌ፣
ጠጅ በብርሌ፣ መዝሙር በሃሌ› ተከሰተልኝ፤›› ብሎ ብቻ አላበቃም፡፡ የቀደመ ወጉን አስታውሶ ጠየቀ፤ ‹‹ጌታው ይልቅ የቸርችል ጎዳና የቀድሞ ስሙ
ማን ነበር? ይንገሩን እንጂ?››
ነገር
በነገር ቢወሳ አይደንቅምና ተሳፋሪው የታክሲ ላይ ውይይቱን ተያይዞታል፡፡ የጎዳናው መጠርያ ማን እንደነበረ ማወቅ ሽቷል፡፡ ‹‹ነውን
ለማወቅ ነበርን ጠይቅ›› ነውና፡፡
ከሰባ አምስት ዓመት በፊት ፋሺስት ኢጣሊያ ተጠራርጎ ሲወጣ በአምስት ዓመት
የወረራ ዘመኑ ሰይሟቸው የነበሩ መጠሪያዎችንም ንጉሡ እንዳስወገዱ በስድሳው ዋዜማ ያሉት ተሳፋሪ አወጉ፡፡
‹‹ይኸውልህ
ልጄ ጎዳናው ‹ሙሶሎኒ ጎዳና› ይባል ነበር፡፡ የዚያ የፋሺስት ፓርቲ አውራ የፋሽስት ኢጣሊያ ቁንጮ ቤኔቶ ሙሶሎኒን ስም ይዞ የኖረው፡፡
አርበኞቻችንና ንጉሡ በእንግሊዝ ድጋፍ ድል ካደረጉ በኋላ ነው፤ ስሙ በእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ዊንስተን ቸርችል የተቀየረው፤››
ውቢቷ በአግራሞት እያየች፣ ‹‹ምነው ይሄን ሳናውቀው ለምን ቀረን? ታሪካችንን ከዩኒቨርሲቲ ደጃፍ ገብተን እንኳን በቅጡ ሳንማር
ወጣን፤ ከ25 ዓመት በፊት የነበሩት ተማሪዎች በኮመን ኮርስ ሂስትሪ ይማሩ ነበር፡፡ እኛ ለዚህ ሳንታደል ተመርቀን ወጣን፡፡ መመረቅ
ነው መረገም፤›› በእንጉርጉሮዋ ሲቃ ይዟታል፡፡ ጠየቀች፡፡
‹‹እያንገበገበ
አንጀቱን ሲያጨሰው
ሮሮ አታሰማኝ ይላል ያገሬ ሰው›› ቀጠለ ከጎኗ የተቀመጠው ተሳፋሪ፡፡ በአባባሏ
በመስማማት ራሱን እየነቀነቀ ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪውን ተመርቆ ሲወጣ ስላገሩ ታሪክ ቅኝት አለመቋደሱንም አወጋ፡፡
ረዳቱ
ገርሞታል፤ እህህ እያለ ነው፡፡ የተሳፋሪዎቹ የወግ ለዛ ታሪክን ያጣቀሰ መሆኑ እህህውን ቀጥሎበታል፡፡ ታሪኬን ሳላውቅ እስከመቼ
እህህ የሚል ይመስላል፡፡ የፊቱን ገጽታ ላየ፡፡ ያቺ ታዋቂ አቀንቃኝ ‹‹እህህ እስከመቼ እህህ. . .›› እንዳለችው መሆኑ ነው፡፡
‹‹ይልቅስ
ልጨምርላችሁ ጎበዝ ከአራት ኪሎ ወደ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የድሮው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ወዳለበት ሽቅብ የሚወስደው መንገድም
‹ኪንግ ጆርጅ ስድስተኛ› የተባለውምኮ ፋሺስቶች ከወጡ በኋላ ነው፤ ያኔ ‹ንጉሥ ዑምቤርቶ ጎዳና› እየተባለ በጣሊያኑ ንጉሥ ይጠራ
ነበር፤›› ሲሉ አምባሳደር አካባቢ ታክሲው እየደረሰ ነበር፡፡ የቀድሞው ጦር ሚኒስቴር ያሁኑ መከላከያ ሚኒስቴር ሲደርሱ ሌላ ትዝታ
ቀሰቀሰባቸው፡፡
‹‹እናንተዬ
እኔ ቸርችል ጎዳናን ቁልቁል በወረድሁ ቁጥር ትዝ የሚለኝ ከ42 ዓመት በፊት የሕዝብ ንቅናቄ ሲነሣ፣ አብዮቱ ሲፈነዳ ሥልጣኑን የጠለፈው
ደርግ ጦር ሠራዊቱን በጂፕ አሳፍሮ የወረደበትን ነው፡፡ ‹ቋሚ ተጠሪ› የሚባሉትን መትረየስ የተጠመደባቸውና ‹ኢትዮጵያ ትቅደም›
የሚል ጥቅስ የሰፈረባቸው ተሽከርካሪዎች ይዞ የተሽከረከረበት ነው፤›› ብለው መራር ትዝታቸውን፣ አብዮተ ሕዝብ በአብዮተ ደርግ መነጠቁን
በቁጭት አስታወሱ፡፡
በዘመኑ
ወጣት የነበረው ጎልማሳም ተቀበላቸው፡፡ ‹‹ደርግ ንጉሡን መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ካወረደ በኋላ ባወረደበት መሪ ቃሉ በ‹ኢትዮጵያ
ትቅደም› የሚጠራ በክፍላተ ሀገር መካከል የሚደረግ የእግር ኳስ ውድድር ነበረው፤ ያን ያደረገውም በንጉሡ ዘመን የነበረውን ጥቅምት
23 ቀን 1923 ዓ.ም. በነገሡበት መታሰቢያ የዘውድ ዋንጫ በማስቀረት
ነበር፤›› ብሎ አከለበት፡፡
‹‹ይወስዳል
መንገድ ያመጣል መንገድ›› ነውና ጎልማሳው ሐሳቡን ማሸንሸራሸሩን ተሳፋሪውም ጆሮውን መስጠቱን አላቋረጠም፡፡
አሁንም
እኮ ታሪኩ በተመሳሳይ ቀጥሏል፡፡ የ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› ውድድር ቀርቶ ‹የግንቦት 20› ውድድር ቀጥሏል፡፡ ረዳት፣ ረዳት አብዮት
ወራጅ አለ ይቅርታ መስቀል ወራጅ አለ፤›› አለና ተሳፋሪውን መመረቅ፤ መማጠን ጀመረ፤ ‹‹የከርሞ ሰው ይበለን! ኧረ በፈጠራችሁ
ታሪካችንንም አፋልጉን፣ ተሰርቀናል ‘ኮ! የዝንጆሮ ገበያ ከመሆን አድኑን፡፡››
ብሂሉም
ተከተለ፡፡ ‹‹ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ፣ አንድም የሚያስደስት አንድም የሚያሳዝን፡፡›› መልካም ጉዞ!
No comments:
Post a Comment