Saturday, August 20, 2016

የወንዶች ማራቶን - የሪዮ ኦሊምፒክ ማጠቃለያ -  የኢትዮጵያ አራተኛው ባለድል ይመጣ ይሆን?

በሔኖክ ያሬድ፥ ነሐሴ 15፣ 2008

ከሁለት ሳምንታት በላይ ያስቆጠረው 31ኛው ኦሊምፒያድ ፍፃሜው ላይ ደርሷል፡፡ በመዝጊያው ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሚካሄዱት ውድድሮች ዋነኛው የወንዶች ማራቶን ይጠቀሳል፡፡ ማራቶን ከጥንት እስከዛሬ የብዙዎችን ቀልብ እንደገዛ ነው፡፡ በየኦሊምፒኩ የሚጠበቁ ሯጮች እንደሚያሸንፉ ሁሉ ያልተጠበቁ፣ ያልታሰቡ ክብሩን ሲቀዳጁ ይታያል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ባለፈው የለንደን ኦሊምፒክ አሸናፊው ዑጋንዳዊ ስቴፈን ኪፕሮች ተጠቃሽ ነው፡፡

በዛሬው የሪዮ ኦሊምፒክ ማራቶን በተለይ ምሥራቅ አፍሪካውያኑ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያና ዑጋንዳ የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ ተሰላፊ ሠለስቱ ሯጮች ተስፋዬ አበራ፣ ለሚ ብርሃኑና ፈይሳ ሌሊሳ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ሯጮች ፈጣን ሰዓት ያለው ባለፈው ጥር በዱባይ ማራቶን 2፡04፡24  በመፈጸም ያሸነፈው ተስፋዬ አበራ ነው፡፡ ከኬንያውያኑ ኢሉድ ኪፕችግ (2፡03፡05) እና ስታንሌይ ቢዎት (2፡03፡51) ቀጥሎ ዘንድሮ ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው ተስፋዬ፣ ባለፈው ሚያዝያ ባሸነፈው ሀምቡርግ ማራቶን በ2፡06፡58 መፈጸሙ በጥሩ አቋም ላይ እንደሚገኝ የአይኤኤፍ ዘገባ ያመለክታል፡፡ በሌሎች ታላላቅ ውድድሮች ባይወዳደርም በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሮጧል፡፡

ለሚ ብርሃኑ ከተስፋዬ ቀጥሎ ጥሩ ሰዓት 2፡04፡33 ያስመዘገበ ሲሆን፣ ባለፈው ሚያዝያ የቦስተን ማራቶንን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ማሸነፉ ይነገርለታል፡፡ አምና በቤጂንግ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና በ15ኛነት ካጠናቀቀበት ውድድር ሌላ በታላላቅ ውድድሮች አልተካፈለም፡፡ ሦስተኛው ተወዳዳሪ ፈይሳ ሌሊሳ ዘንድሮ ምርጥ ሰዓት ካላቸው ሁለት ኬንያውያንና ሁለት ኢትዮጵያውያን ተርታ ውስጥ ባይገባም ወቅታዊ ሰዓቱ 2፡06፡56 ነው፡፡

በዓምናው የዓለም ሻምፒዮና በቤጂንግ ሳይጠበቅ ኢትዮጵያዊውን የማነ ፀጋይን አስከትሎ ያሸነፈው ኤርትራዊው ግርማይ ገብረሥላሴ ዘንድሮም ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ በማራቶን የዓለም ሻምፒዮን ሆኖ የኦሊምፒክ ባለድል እስኮሁን አልተመዘገበም፡፡ ቀደም ባሉት ኦሊምፒኮች የሲዲኒው አሸናፊ ገዛኸኝ አበራና የለንደኑ ስቴፈን ኪፕሮች የዓለም ሻምፒዮን የሆኑት ከኦሊምፒክ ድሎቻቸው በኋላ ነበር፡፡ ዘንድሮ ይህን ታሪክ የሚለውጥ ይኖር ይሆን?

ኢትዮጵያና ማራቶን

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ መድረክ ከ60 ዓመታት በፊት ስትገኝ፣ ከተወዳደረችባቸው ስፖርቶች አንዱ የአትሌቲክሱ ማራቶን ነበር፡፡ በኅዳር 1949 ዓ.ም. በተካሄደው ውድድር የሮጡት ባሻዬ ፈለቀና ገብሬ ብርቄ ነበሩ፡፡ ባሻዬ 29ኛ፣ ገብሬ 32ኛ ሆነው ማጠናቀቃቸው እ.ኤ.አ. የ1956 ሜልቦርን ኦሊምፒክ ሰነድ ያወሳል፡፡

ኢትዮጵያ ወርቃዊ ድል ማጣጣም የጀመረችው እ.ኤ.አ. በ1960 በሮም ኦሊምፒክ በማራቶን ነበር፡፡ በደማቅዋ የአውሮፓ በጋ ምሽት፣ ጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም. ጀንበርዋ በሮም ኦሊምፒክ ስታዲየም ጀርባ ባዘቀዘቀችበት አጋጣሚ አንድ ያልታወቀ ጥቁር ገጽታ ያለው አትሌት፣ የማራቶኑን ሩጫ በውራ ጎዳናው በቀዳሚነት ፈፀመ፡፡ በባዶ እግሩ የሮጠው  አበበ ቢቂላ በ2 ሰዓት 16 ደቂቃ 15 ሰከንድ የመጨረሻውን መስመር በጥሶ በማለፍ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከሁሉም በላይ እንድትውለበለብ አደረጋት፡፡ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አበበ ዋቅጅራም እንደ አበበ ቢቂላ ሁሉ በባዶ እግሩ ሮጦ በሰባተኛነት አጠናቅቋል፡፡ አበበ ቢቂላ በሮም በሽልማት ሰገነቱ ላይ እንደወጣ የመጀመሪያው «ጥቁር አፍሪካዊ» የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ አጥላቂ ሆነ፡፡

ከአራት ዓመት በኋላ ለኢትዮጵያ ሦስተኛዋ በሆነው የቶኪዮው የኦሊምፒክ ተሳትፎ፣ አበበ ቢቂላ ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም. ተጫምቶ በመሮጥ ለሁለተኛ ጊዜ የማራቶን ድሉን አዲስ የዓለምና የኦሊምፒክ ክብረ ሰዓትን በ2 ሰዓት 12 ደቂቃ 11.2 ሰከንድ በመፈጸም መስበሩ ብቻ ሳይሆን፣ የትርፍ አንጀት ቀዶ ሕክምና ባደረገ ስድስት ሳምንት ውስጥ ማሸነፉ ገድሉን ልዩ ያደርገዋል፡፡

ከእርሱ በፊት ማንም ያልፈጸመውን፣ ከእርሱም በኋላ ለ16 ዓመታት ማንም ያላደረገውን የኦሊምፒክ ማራቶን ሁለት ጊዜ አከታትሎ የመውሰድ ገድል ፈጸመ፡፡ ይኸም ብቻ አይደለም ባሻናፊነት የገባበት ሰዓትም እጅግ በጣም ፈጣንና በእንግሊዛዊው ባሲል ሔትሌይ በ2 ሰዓት 13 ደቂቃ 55 ሰከንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረወሰን በ1 ደቂቃ 43፡8 ሰከንድ የሰበረበት ነው፡፡

‹‹እንደበረዶ ነጫጭ ጥርስ አብቅሎ፣ ይቆረጣጥማል ሰዓት እንደቆሎ›› ብለው በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ (1914-1979) እንዲቀኙለት አድርጓቸዋል፡፡

ከ52 ዓመታት በፊት አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ጊዜ ታላቁን ሩጫ ማራቶንን አሸንፎ ወርቅ ሲያጠልቅ ‹‹የበርሊን ማራቶን መጽሔት›› ዘጋቢ እንዲህ ነበር የጻፈው፡፡

‹‹አበበ ቢቂላ በ1952 ዓ.ም. የሮም ኦሊምፒክ ማራቶን በባዶ እግሩ ሮጦ ተአምራዊ አሸናፊ ከሆነ ወዲህ የማራቶንን ሩጫ በ2 ሰዓት ከ14 ደቂቃ የሚጨርስ ቢኖር ሻምፒዮን ይባላል፤ በ2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ የሚፈጽም ከተገኘ ደግሞ ድንቅ ሻምፒዮን ይባላል፡፡ አበበ ቢቂላ ግን በቶኪዮ ኦሊምፒክ 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ11፡2 ሰከንድ በማምጣቱ ምን ብዬ እንደምለው ቃላት አጥቼለታለሁ፡፡››

በቀጣዩ አራት ዓመት አበበ ቢቂላ ለሦስተኛው ድል ቢሮጥም፣ 17ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ባጋጠመው የጡንቻ መሸማቀቅ አቋርጦ ወጥቷል፡፡ ቢሆንም ድሉ ከኢትዮጵያ አላፈተለከም፡፡ በመስከረም 1961 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1968) የሜክሲኮ ኦሊምፒክ ማሞ ወልዴ አገሩን ለሦስተኛ ጊዜ አሸናፊ ያደረጋትን ድል አስመዘገበ፡፡ መርዓዊ ገብሩም ስድስተኛ ሆነ፡፡ ማሞ በ10,000 ሜትር ሩጫም ከኬንያዊው ናፍታሊ ቲሙ ጋር እልህ አስጨራሽ ፉክክር አድርጎ የብር ሜዳሊያ ለማጥለቅ ችሏል፡፡ የማሞ የማራቶን ድልም ‹‹ማራቶን ማራቶን ማራቶን ልዕልቷ

 አበበና ማሞ ሆኑ ባለቤቷ›› ተብሎ እንዲዘፈን አደረገ፡፡

20ኛው ኦሊምፒያድ የጀርመኗ ሙኒክ ከተማ በ1964 ዓ.ም (1972) ስታዘጋጅ የተካፈለችው ኢትዮጵያ ለወርቅ ባትታደልም በነሐስ ሜዳሊያ ለመታጀብ ችላለች፡፡ ማሞ ወልዴ በ40 ዓመት ዕድሜው ማራቶንን ሮጦ ሦስተኛ በመሆኑ፣ አንጋፋው የኦሊምፒክ ማራቶን ባለሜዳሊያ ተሰኝቷል፡፡

ከሙኒክ ስምንት ዓመት በኋላ በተደረገው የሞስኮ ኦሊምፒክ ሜዳሊያ ሠንጠረዥ ውስጥ ባትገባም ደረጀ ነዲ ሰባተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ በባርሴሎና እና በአትላንታ ኦሊምፒኮች ውጤት የራቃት ኢትዮጵያ (በአትላንታ በሴቶች የፋጡማ ሮባ ድል ሳይዘነጋ)፣ የወርቅ ሜዳሊያን ያገኘችው ከ32 ዓመት ቆይታ በኋላ ነበር፡፡

በሲድኒ ኦሊምፒክ 27ኛው ኦሊምፒያድ በ1993 ዓ.ም (እ.ኤ.አ. 2000) ሲካሄድ  ገዛኸኝ አበራ ከስምንት ኦሊምፒያድ በኋላ ለኢትዮጵያ በማራቶን የወርቅ፣ ተስፋዬ ቶላ የነሐስ ሜዳሊያዎች ለማስገኘት ችለዋል፡፡ አንፀባራቂ ድልንም ተጎናፅፈዋል፡፡

ከሲድኒ በኋላ በተካሄዱት የአቴንስ፣ የቤጂንግና ለንደን ኦሊምፒኮች ኢትዮጵያ ከወርቁ ጋር ከተፋታች 16 ዓመታት ተቆጥረዋል (በለንደን የፀጋዬ ከበደ ነሐስ ሜዳሊያ ሳይዘነጋ)፡፡ ዘንድሮ ለኢትዮጵያ በወንዶች ማራቶን አምስተኛውን ወርቅ የሚያመጣውና አራተኛው ኢትዮጵያዊ የማራቶን ባለወርቅ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ማን ይሆን?

ስፓርት

Author

ሔኖክ ያሬድ

Amharic News 08/17/2016

No comments:

Post a Comment