06 Aug, 2016
ኢትዮጵያ ለአሥራ ሦስተኛ ጊዜ የተካፈለችበት የኦሊምፒክ ጨዋታዎች ባለፈው ዓርብ (ሐምሌ 29 ቀን 2008 ዓ.ም.) በሪዮ ዲጄኔሮ ከተማ የተከፈተ ሲሆን፣ ለሁለት ሳምንታት እየተካሄደ ይዘልቃል፡፡ ኢትዮጵያ በ31ኛው ኦሊምፒያድ መካፈሏን ተከትሎ በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አማካይነት በጎጆ ክሬኤቲቭ ሚዲያ የተዘጋጀው ‹‹ኦሊምፒክ - ሪዮ 2016›› መጽሔት ታትሞ ተሠራጭቷል፡፡ መጽሔቱ በይዘቱ የተፋለሰና ፈሩን የሳተ መሆኑን በመጥቀስ ሪፖርተር ባለፈው ሳምንት እትሙ ሐተታ አቅርቦበት ነበር፡፡ በብዙዎች ዘንድ በተለይም በስፖርትና ኦሊምፒክ ቤተሰብ ዘንድ አነጋጋሪ ሆኖ ስለሰነበተው መጽሔትና በኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ ዙርያ ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው አቶ ታደለ ይድነቃቸው ተሰማ የሚያነሷቸው ነጥቦች አሉ፡፡ አቶ ታደለ በኢትዮጵያ በዘመናዊ ስፖርትና ኦሊምፒክ አባትነት የሚጠቀሱት፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የመጀመርያ ፕሬዚዳንት፣ የኢንተርናሽናል ኮሚቴ አባል፣ የፊፋ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል፣ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ (1914-1979) ልጅ ናቸው፡፡ አቶ ይድነቃቸው አፍሪካና ደቡብ አሜሪካ በፊፋ ውስጥ የነበረውን የአውሮፓ ፍጹም የበላይነት ለመታገል የመጨረሻ ስምምነት ለማድረግ ከ43 ዓመት በፊት በሪዮ ዲጄኔሮ በተዘጋጀው ስብሰባ ላይ አቶ ታደለ የመካፈል ዕድል አግኝተው ነበር፡፡ የኢትዮጵያን የስፖርት ታሪክ ከኦሊምፒክና ከፊፋ ጋር የተያያዙ ዋና ዋና ጉዳዮች፣ እንዲሁም የአቶ ይድነቃቸው ተሰማ ታሪክን አደራጅተው አሳትመዋል፡፡ በኦሊምፒክ መጽሔት ይዘት፣ በኢትዮጵያ ስፖርትና ኦሊምፒክ ጥንተ ታሪክ ዙርያ አቶ ታደለ ይድነቃቸው ተሰማን ሔኖክ ያሬድ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ‹‹ኦሊምፒክ - ሪዮ 2016›› የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መጽሔትን እንዴት አገኙት?
አቶ ታደለ፡- ሁለት ነገር ነው የታዘብኩት፤ ኢትዮጵያ በኦሊምፒክ መሳተፍ የጀመረችበት 60ኛው ዓመትና የሪዮ ኦሊምፒክ መጽሔት መደባለቅ፡፡
የኦሊምፒክ መጽሔት የአንድ ብሔራዊ ኦሊምፒክ መጽሔት ብቻ አይደለም፡፡ ስታንዳርድ የሆነ እያንዳንዱ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በያንዳንዱ ተሳትፎ የኦሊምፒክ ፍልስፍናዎች የሚያከብርና የተቀበለ መሆኑን የሚያውጅበት፣ የዘመናዊ ኦሊምፒክ መሥራቹን ባሮን ደኩበርቲን ስሙን የሚጠቅስበት፣ ከዚያ በኋላ የራሱን ብሔራዊ ኦሊምፒክ የሚያስተዋውቅበት፣ ከአገሪቱ ስፖርት መሪዎች፣ ከብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴና ከአገሪቱ መሪ መልዕክት የሚተላለፍበት ነው፡፡ እንዲሁም ብሔራዊ ፌዴሬሽኖች አገሪቱ ካሁን በፊት ያደረገቻቸው የኦሊምፒክ ውድድር ታሪኮች፣ ኢትዮጵያዊ ሆነው የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ውስጥ ያገለገሉና አባል የነበሩ ሰዎች የሚታወሱበት ከሌሎች ጋርም ልውውጥ የሚደረግበት ነው፡፡
እንደ ነጋዴ የንግድ ካርዱን ኮክቴል ላይ እንደሚለዋወጠው፣ ስለየ አገሩ በጥቂቱ ለማወቅ፤ እያንዳንዱ አገር የኦሊምፒክ መጽሔቱን ይለዋወጣል፡፡ ለኦሊምፒክ ጨዋታዎች የሚዘጋጀው መጽሔት በማንኛውም መልኩ መደበኛ የታሪክ መጽሐፍ ሊሆን አይችልም፡፡ ኢንፎርሜሽን የሚሰጥበት ነው፡፡ 60ኛ ዓመት፣ 50ኛ ዓመት፣ 25ኛ ዓመት የተለዩ ነገሮች ናቸው፡፡ በነዚህ ጊዜ ከኋላ ከመነሻው ጀምሮ የነበሩ ክንውኖች፣ ሰዎችም የሚታወሱበት፣ ከየት ተነሣን? የት ደረስን? የሚቃኝበት ነው፡፡ ሁለቱ በመቀላቀላቸው የመጀመርያው ስህተት ተሠርቷል፡፡ የኢትዮጵያን የ60 ዓመት ኦሊምፒክ ታሪክ ከኢትዮጵያ የሪዮ ኦሊምፒክ መተዋወቂያ ሰነድ ጋር አትቀላቅለውም፤ እንደ መነሻ ትጠቅሰዋለህ እንጂ፡፡
ሪፖርተር፡- አጻጻፉንስ እንዴት አዩት?
አቶ ታደለ፡- ታሪክን በዘፈቀደ የመጻፍ ነገር ብሔራዊ ውይይት የሚያስፈልገው ነው፡፡ በአገራችን በሁሉም ሴክተር (ዘርፍ) እየተለመደ የመጣ መጥፎ ባህል አለ፡፡ የዛሬውንና ያለፈውን ትውልድ ያለያየ፣ እንዳይተዋወቁ ያደረገ ነው፡፡ በመጽሔቱ ውስጥ የተፈጠሩት ስህተቶች በሪፖርተር ከነዕርማታቸው ተጠቁሟል፡፡ ነገር ግን ከዚህ ከኦሊምፒክ ጋር በተያያዘ ውሸቱ እንዴት ተለመደ? ወደ ሚለው ብንሄድና የተወሰኑ ነገሮች ባነሳ አስፈላጊ ነጥቦች ናቸው፡፡ አንደኛ ታሪክ የሚለወጥበት ምክንያት ምንድን ነው? የሚለወጥበት ምክንያት የአንድ ሰው ታሪክ ለመለወጥ ይሆናል፡፡ በዘመኑ ሁሉም ኢትዮጵያውያን በምሥረታው ጊዜ የነበሩት የሚያውቁት የዘመናዊ ስፖርት መሥራች፣ ዛሬ እሱ አይደለም የሚል ታሪክ ለመፍጠር ሊሆን ይችላል፡፡ እንዳየሁትም ዓላማው ያ ነው፡፡ ለአቴንስ (1996 ዓ.ም.) እና ለአትላንታ (1988 ዓ.ም.) የተዘጋጁትን የኦሊምፒክ መጽሔቶች አግኝቼ በጣም ገርሞኝ ነበር፡፡ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ በስፖርት የዘር አድልዎን የታገለና የከለከለ ድርጅት ነው፡፡ በዘር አድልዎ አያምንም የሚል ነገር አለው፡፡ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ የዘር አድልዎ እየተገበረ፣ መተግበር አትችልም ብላ በቦይኮት ያስቆመች ኢትዮጵያ መሆኗ እየታወቀ፤ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዘረኝነትን አትቀበሉ ብሎ ኢትዮጵያን ያስተማረ ይመስል፣ እንዲህ ያለ ነገር መጽሔት ላይ ጽፎ መሄድ ተገቢ ነው ወይ? ነፍሱን ይማርና ለብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ አሰፋ ማሞ ጠይቄ ነበር፡፡ አስገራሚ መልስ ነበር የሰጠው፡፡ ትክክል ነው፤ ይኼ ታሪክ የኢትዮጵያ መሆኑን እናውቃለን፣ ግን የማሳተሚያው ፈንድ የሚመጣው ከኦሊምፒክ ሶሊዳሪቲ ስለሆነ ብዙ ጊዜ እነሱ የፈለጉትን የመጻፍ ሁኔታ ውስጥ ትገባለህ፤ ይኼ ግን ይታረማል ብሎ ነበር፡፡ ያ ወቅት ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ የገንዘብ ኃይሉን ተጠቅሞ የአገሮችን የኦሊምፒክ መጽሔት ስፖንሰር እያደረገ እርሱን እንዲያወድሱት የሚያጽፍበት ወቅት ነበር፡፡ አንዱ የታሪክ ለውጥ በዚያ ዘመን ነበር፡፡ ሁለተኛው የታሪክ ለውጥ በግምት ላይ የተመሠረተውና የአንድን ግለሰብ ታሪክ ከመለወጥ ጋር የተያያዘው አጠቃላይ የአገሪቱን ስፖርት ታሪክ የመለወጥ አዝማሚያ ነው፡፡ እዚያ ላይ ተጠቂ የሚሆነው በአንደኛ ደረጃ ታሪክ ነው፡፡ ታሪክ ሲሸጥና ሲለወጥ የሚጠቃው ታሪክ ነው፡፡ ሦስተኛ በነዚያ ዓመታት የአገሪቱን ስፖርት የሚያገለግሉት ሰዎች በሙሉ ነፃ አገልጋዮች ናቸው፡፡ ትርፍ ጊዜያቸውን የመኪና ነዳጃቸውን አንዳንዴም ገንዘባቸውን ሁሉ ለአንዳንድ ሥራዎች እያወጡ የኖሩ ሰዎች ናቸው፡፡ የነሱ ታሪክ ነው እየተለወጠ ያለው፡፡
አቶ ታደለ፡- የኢትዮጵያ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ታሪክ አመሠራረት እንዳለ ተለውጧል፡፡ ኦሊምፒክ ኮሚቴው እ.ኤ.አ. በ1954 (1946 ዓ.ም.) ተመሠረተ የሚል ወጣ፡፡ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በ1954 አልተመሠረተም፡፡ ታሪኩ ሌላ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን ተብሎ በመንግሥት ማስታወቂያ የተቋቋመ ከፊል መንግሥታዊ ከፊል ሕዝባዊ የሆነ ተቋም ለጊዜው በተሾመለት ዋና ጸሐፊ ኤድዋርድ ቪርቪሊስ በሚባል ግሪካዊ አማካይነት፣ በ1954 አቴንስ ላይ ለነበረው የኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጉባኤ ቃል ገብቶ፣ ወደፊት አምስት ፌዴሬሽኖችና ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውን እናቋቁማለን፤ እስከዚያው ስፖርት ኮንፌዴሬሽኑ ያንን ሠርቶ እስኪጨርስ ኮንፌዴሬሽኑ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሽግግር ወኪል ሆኖ እንድንካፈል ይፈቀድልን ብሎ ተፈቅዶ የገባንበት እንጂ፣ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተቋቋመበት ጊዜ አይደለም፡፡
የተዘረዘሩት እነዚያ ስፖርቶች ወደ ፌዴሬሽን ተቃርበው የነበሩት የኢትዮጵያ ስፖርት ጽሕፈት ቤት በ1936 ዓ.ም. ሲቋቋም እግር ኳስ፣ ብስክሌትና ቦክስ ነበሩ፡፡ ትራክ ኤንድ ፊልድ (አትሌቲክስ) የሚባለው የሜዳ ሩጫ በኋላ ላይ የስዊድን የጦር አሠልጣኞች ሲመጡ በወታደራዊ ክፍሎች ውስጥ ነው የጀመሩት፡፡ ለዚህም ነው አንድም ጊዜ ከትምህርት ቤቶች ወይም ከሌላ አካባቢ አገሪቱን የወከለ አትሌት ወጥቶ የማያውቀው፡፡ ያ ዘመን ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የተቋቋመበት ዘመን አይደለም፡፡ ወደፊት እናቋቁማለን በሚል ቃልኪዳን የመካፈል ዕድል የተገኘበት ዘመን ነው፡፡ ስህተቱ የሚጀምረው እዚህ ጋ ነው፡፡ ከርሱ ጋር በተያያዘ በደብዳቤ የተደረጉትን ልውውጦች በቁንፅል እየተመለከቱ ብስክሌትና አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከእግር ኳስ ቀድመው ተቋቁመው ነበር የሚሉ አሉ፡፡
እዚህ ላይ የሚነሳ ጥያቄ አለ፡፡ ብስክሌትና አትሌቲክስ ከእግር ኳስ በፊት ተቋቁመዋል ሲባል የት ነበረ ውድድሩ? ውድድር በሌለበት ፌዴሬሽን ከየት ይመጣል? ፌዴሬሽን አወዳዳሪ አካል ነው? አወዳዳሪ አካላቱስ እነማን ነበሩ? ከ1941 ዓ.ም. ጀምሮ አወዳዳሪዎች የነበሩት እነማን ነበሩ? ተወዳዳሪዎችስ? መልስ የለም፡፡ ብስክሌት በጣሊያን ወረራ ጊዜ ነበር፡፡ ጣሊያኖች በአሁኑ ጊዜ ተወዳጅ የሆነው ቱር ደፍራንስን ሁለት ጊዜ አሸንፈው ነበር፡፡ የጣሊያን ብሔራዊ ስሜት የሚንፀባረቅበት ስፖርት ነበርና በቅኝ ግዛት በያዘቻቸው አገሮች ሁሉ ብስክሌት አስገብታ ያገር ተወላጅ ጥቁሩ ተለያይቶ ይጫወት ነበር፡፡ እኛም አገር በዚያን ጊዜ ተስፋፍቷል፡፡ ያ በፌዴሬሽን ሳይሆን በአገር ተወላጆች ስፖርት ጽሕፈት ቤት በሚባለው ውስጥ ነው፡፡ ካሳ ፈዲል ታዋቂ የነበረበት ያ ዘመን ነው፡፡ ‹‹ገኖ ይጠራል ስማቸው በኮርስ ካሳ በኳስ ይድነቃቸው›› ተብሏል፡፡ ያ ዘመን ካሳ ፈዲልና ሌሎችም አሁን ስማቸውን የማላስታውሳቸው ብዙ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች ብስክሌት መወዳደር የጀመሩበት ዘመን ነው፡፡ ያንን የኢትዮጵያ ብስክሌት ፌዴሬሽን ብሎ መመዝገብ አይቻልም፡፡ የቅኝ ግዛት ተቋም ነው፡፡ የአገር ተወላጆች የስፖርት ጽሕፈት ቤት እንጂ ፌዴሬሽን አልነበረም፡፡
ከዚያ በኋላ አባቴ [ይድነቃቸው ተሰማ] እንደሚያስታውሰው፣ ስፖርት ጽሕፈት ቤት የሚለውን ሲያቋቁም የርሱ እምነት እነዚያ በጣሊያን ጊዜ ብስክሌትና ቦክስ ለተጫወቱ ሁሉ ውድድር እናዘጋጃለን የሚል ምኞት ነበረው፡፡ ነገር ግን እነ ካሳ ብስክሌቶቻቸው አርጅተዋል፡፡ ለቦክሰኞቹም ጓንት አልነበረም፡፡ ስለዚህ እግር ኳሱ ብቻ ቀጠለ፡፡ ብስክሌትና ቦክስ ከ1936 እስከ 1941 ዓ.ም. በነበረው ጊዜ በስፖርት ጽሕፈት ቤት ሥር ውድድር አልተደረገላቸውም፡፡ በ1941 ዓ.ም. ላይ የኢትዮጵያ ስፖርት ጽሕፈት ቤት ወደ ኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽን ይለወጥ ሲባል ብስክሌትና ቦክስ በዚያው ተረሱ፡፡ ደግሞም ሁለቱን ማካሄድ እንደ እግር ኳስ በገንዘብ ቀላል አይደለም፡፡
እግር ኳስ ዝም ብለህ ሜዳ ትሰጠዋለህ፤ ቤተሰብ ትጥቅ አቡጀዲ ገዝቶለት ነው የሚወዳደረው፣ ቀላል ነው፣ ብዙ ወጪ የለውም፡፡ ጓንትና ብስክሌት መግዛት ውድ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፉትቦል ፌዴሬሽን መልኩን ነው የለወጠው፡፡ መጀመርያ በስፖርት ጽሕፈት ቤት ውስጥ መቋቋሙ ተመዝግቦለታል፡፡ ነገር ግን ፊፋ በሚፈልገው መልኩ ነፃ ሆኖ የተቋቋመበት ዘመን 1941 ዓ.ም.፣ እነ ሜጄር ጄኔራል ሙሉጌታ ቡሊ (በዚያን ጊዜ የክብር ዘበኛ ዋና አዛዥ የነበሩ)፣ ሌተና ኮሎኔል ከበደ ገብሬ (በኋላ ሌተና ጄኔራል)፣ ሌተና ኮሎኔል ኃይሌ ባይከዳኝ፣ ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉበት ዘመን ነበር፡፡ አቶ ገብረሥላሴ ኦዳ (ከቅዱስ ጊዮርጊስ) እንዲሁ፡፡ እያንዳንዱ ክለብ በሥራ አስፈጻሚ ውስጥ እንዲገባ ተደርጎ የመቻል (የምድር ጦር) ተወካይ ሌተና ኮሎኔል ከበደ ገብሬ ፕሬዚዳንት፣ የጊዮርጊስ ተወካይ ከነበሩት ውስጥ ይድነቃቸው ተሰማ ዋና ጸሐፊ እንዲሆን ተደርጎ የተቋቋመበት ጊዜ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ግሪካዊው ቬርቪሊስ ከኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ ጋር ተያይዞ ሲነሳ ይሰማል፡፡
አቶ ታደለ፡- ይኼ ኤድዋርድ ቬርቪሊስ የሚባለው ሰው ዛሬ እንደሚተርከው ለኦሊምፒክ ተሳትፎ ሲባል ከሌላ ቦታ የመጣ ሰው አይደለም፡፡ ማስታወቂያ ሚኒስቴር ውስጥ በነበረው የስፖርት ጽሕፈት ቤት ውስጥ በአማተር አገልጋይነት የቴክኒክ አማካሪ ሆኖ ይሠራ የነበረ፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ ጃንሜዳ በተደረገው ስብሰባ በኋላ የነ አበበ ቢቂላ አሠልጣኝ በነበረው በኦኒ ኒስካነን በድምፅ ተበልጦ ሳይገባ የቀረ፣ በዚያም አኩርፎ የወጣ ነው፡፡
ከዚያ በኋላ የስፖርት ኮንፌዴሬሽን እንዲቋቋም ለንጉሠ ነገሥቱ ካመለከቱት የመንግሥት ባለሥልጣናት ጋር አብሮ የቀረበና በዚያ ምክንያት ዋና ጸሐፊ የሆነ እንጂ ቀደም ሲል ኢትዮጵያ ውስጥ በስፖርት የማይታወቅ ሰው ሆኖ አይደለም፡፡ አሌክሳንደሪያ ውስጥ የመጀመርያ ደረጃ ትምህርት ቤት ውስጥ የአካል ማጎልመሻ አስተማሪ ነበር፡፡ ከዚያ ኢትዮጵያ መጥቶ ቡና ነጋዴ ሆኖ ሳለ በ1936 ዓ.ም. በተቋቋመው የስፖርት ጽሕፈት ቤት ውስጥ ረዳት የቴክኒክ አማካሪ ሆኖ ገባ፡፡ ከአምስት ዓመት በኋላ ፉትቦል ፌዴሬሽኑ ራሱን ሲችል የክብር ዘበኛ ተወካይ ኦኒ ኒስካነን ከሱ የተሻለ ድምፅ አገኘና ተመረጠ፡፡ አኩርፎ የወጣ እንጂ አዲስ ለስፖርቱ ተብሎ ከግሪክ የመጣ ሰው አይደለም፡፡ ዛሬ እንደሚባለው አይደለም፡፡ የውሸት ታሪክ ነው የሚጻፈው፡፡
የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መነሻ ታሪክ ሰፊ ነው፡፡ ኮንፌዴሬሽኑን በተመለከተ በዚያን ጊዜ የነበሩ ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ሜጀር ጄኔራል መርዕድ መንገሻ (በኋላ ሌተና ጄኔራል) ሌተና ኮሎኔል ታምራት ይገዙ ባንድ በኩል፣ ሌተና ጄኔራል አቢይ አበበ በሌላ በኩል ሆነው ብዙ የተሟገቱበት በኋላ እየተለወጠ የመጣ አደረጃጀት ነው፡፡ የስፖርት ኮንፌዴሬሽን አመሠራረት ራሱን የቻለ ታሪክ ስለሚፈልግ እዚህ ላይ ባንገባበት ጥሩ ነው፡፡ ባጠቃላይ ያ የስፖርት ኮንፌዴሬሽን እንጂ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አይደለም፤ አልነበረም፡፡
ሪፖርተር፡- አትሌቲክስ ፌዴሬሸን መቼ ተቋቋመ?
አቶ ታደለ፡- አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ከፉትቦል በፊት ተቋቋመ ማለት ብቻ ሳይሆን፣ ሌተና ኮሎኔል ጌታሁን ተክለማርያም የመጀመርያው ፕሬዚዳንት ነበሩ የሚል የፈጠራ ታሪክ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴውም ሆነ አትሌቲክስ ፌዴሬሽኑ ዛሬም ድረስ ድረ ገጹ ላይ ለጥፏል፡፡ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡
አንደኛ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን የተቋቋመው በየካቲት 1953 ዓ.ም. ሲሆን፣ እግር ኳስ በ1936 ዓ.ም. ነው የተቋቋመው፤ ልዩነቱ ሩቅ ነው፡፡ ሁለተኛ የአትሌቲክስ ፌዴሬሽን መሥራች አባላት ስም ዝርዝር አለ፡፡ ሌተና ኮሎኔል ብርሃነ ተፈራ (የፖሊስ ሠራዊት አባል) የመጀመርያው ፕሬዚዳንት ሆነው እስከ 1958 ዓ.ም. አገልግለዋል፡፡ አቶ ልዑልሰገድ በቀለ፣ ተቋመ ወልደጻድቅ፣ ብርሃነ ዳሬሳ፣ ለገሠ በየነ፣ ዑስማን መሐመድ፣ ሻምበል ገበየሁ ዱቤ፣ ጥግነህ አስፋው፣ ወልደብርሃን ተስፋማርያም፣ ዝግጁ በልሁ፣ እሸቴ ህለተ ወርቅና መቶ አለቃ ተፈሪ በንቲ (ምናልባትም በኋላ ብርጋዲየር ጄኔራል ሆነው አገሪቱን የመሩት ናቸው) መሥራቹ ትውልድ ይሄ ነው፡፡ ጌታሁን ወይም ጌታነህ ተክለማርያም ማለት የነ ሻምበል ዘላለም ደስታ እኩያ ናቸው፡፡ የነ ሻምበል ዘላለም አለቃ የነበሩ ናቸው፡፡ በደርግ የመጀመርያ ዓመታት የተደረጉትን የጦር ኃይሎች ውድድር አዘጋጅ ኮሚቴ ሊቀመንበር የነበሩ በጣም ወጣት ናቸው፡፡ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ሲመሠረት በዚያ ቦታ የሉም፡፡ ተፈሪ በንቲ ሊቀመንበር ባልነበሩበት ፌዴሬሽን ውስጥ ሊቀመንበር ነበረ ብሎ ማቅረብ በታሪክ ላይ የተሠራ ግፍ ነው፣ ትክክል አይደለም፡፡
እንደዚህ ዓይነቶቹ ነገሮች የሌሎችንም ታሪኮች እየደበቁ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ እንዳልኩህ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ባለሥልጣኖች መካከል ኢትዮጵያ ውስጥ በስፖርት ያላገለገለውን መቁጠር ይቀላል፡፡ አብዛኞቹ ነፃ አገልግሎት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ ሰጥተዋል፡፡ የነርሱንም ስም የመሠረዝ ነው፡፡ ከባለሥልጣኖቹ ውጪ የነጋዴው ኅብረተሰብ በጣም ብዙ አለ፡፡ የነርሱን ሁሉ ታሪክ መሠረዝ ነው፡፡ ለምን እንዲህ ማድረግ እንደተፈለገ ያነሣሁት ነጥብ አለ፡፡ ዓላማው ያ ቢሆንም ጉዳቱ ግን በዚያ ላይ ብቻ አይቆምም፡፡
ሪፖርተር፡- ኮንፌዴሬሽን በተመለከተ በነጋሪት ጋዜጣ 1941 ዓ.ም. የወጣው እንዴት ይታያል?
አቶ ታደለ፡- ስለ ኢትዮጵያ የስፖርት ኮንፌዴሬሽን መቋቋም የወጣ የመንግሥት ማስታወቂያ ነው፤ ያኔ ፉትቦሉ በፊፋ ተመዝግቦ ነበር፡፡ ሌሎቹስ ወዴት ነው የሚመዘገቡት? ከፉትቦል ሌላ፣ ሌላ ፌዴሬሽን የለም፡፡ ኮንፌዴሬሽኑ ሌሎቹን ካቋቋመ በኋላ ዓላማው ምንድን ነው? ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ በዚያን ጊዜ ለማቋቋም የተቸገረው፣ ንጉሠ ነገሥቱም ወዲያውኑ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ይቋቋም ያላሉት፣ ለማቋቋም የሚያስፈልጉ አምስት ፌዴሬሽኖች ስላልነበሩ ነው፡፡ ዛሬ አምስት ፌዴሬሽኖች ነበሯት እየተባለ ነው፡፡ የዛሬው ታሪክ እንደዚያ ነው የሚለው፡፡ እነ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ቀድመው ከተቋቋሙ፣ ኮሚቴው ነበረ ማለት ነው፡፡ ያን ጊዜ ይኼን ያሉት ኮ ፌዴሬሽኖችን ቀድሞ የማደራጀት አስፈላጊነቱን ስለተረዱ ነው፡፡ መሠረታዊ በመሆኑ በሕዝብ ማስታወቂያ ላይ ተጠቅሷል፡፡ ያም ባይኖር ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ አይቀበልም፡፡ ኮሚቴው የሚመዘግብህ በኦሊምፒክ የታወቁ የአምስት ስፖርቶች ፌዴሬሽኖች ሲኖሩ ነው፡፡
በ1941 ዓ.ም. የመንግሥት ማስታወቂያ ቢወጣም ለ19 ዓመታት ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ማቋቋም አልተቻለም፣ ምክንያት አለ፡፡ ፌዴሬሽን መመሥረት ቀላል ነገር አይደለም፡፡ የቅርጫት ኳስ ውድድር አዘጋጅተህ ተሳታፊ ላታገኝ ትችላለህ፡፡ ተወዳጅነትም ላያገኝ ይችላል፡፡ የማስተማር፣ ተመልካች የመሳብ ነገር አለ፡፡ ጊዜ ይወስዳል፡፡ ሒደት ነው፡፡ በ1960 ዓ.ም.ም ቢሆን ኦሊምፒክ ኮሚቴን ያቋቋምነው ተሳክቶልን አምስቱ ተሟልተው ሳይሆን፣ ከኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ጋር በአፓርታይድ ምክንያት የተቀያየምን ስለሆነ ብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የላችሁም ብሎ እንዳያባርረን በጥድፊያ የተደረገ ነው፡፡ ስታዲየሙ ውስጥ ያሉት ቢሮዎች በሙሉ ስም ተጽፎባቸው ፌዴሬሽኖቹ ተቋቁመዋል ተብሎና ማመልከቻ ቀርቦ፣ የአባልነት ክፍያም ተከፍሎ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሳይወድ በግዱ ኢትዮጵያ ከአምስት በላይ ፌዴሬሽኖች አላት ብሎ የተቀበለን በ1960 ዓ.ም. ነበር፡፡ የሕዝብ ክፍል ማስታወቂያ እዚህ ላይ ተንፀባርቋል፡፡ ነገር ግን እርሱ ኖረ አልኖረ ኢንተርናሽናል ኦሊምፒክ ኮሚቴ ለመመዝገብ ግዴታ ነበር፡፡ በ1960 ዓ.ም. ስንመዘገብ እውነቱን እንነጋገር ከተባለ አምስት የሚንቀሳቀሱ ፌዴሬሽኖች ነበሩን? አልነበሩንም፡፡
ዛሬስ? ካሳዛነኝ ነገር አንዱ ከ60 ዓመት መካፈል በኋላ ዛሬ የምንካፈለው በ38 አትሌቶች ነው፡፡ ሁለተኛ የምንካፈልባቸው ስፖርቶች ከማደግ ይልቅ ወደ መውረድ ማዘንበላቸው፡፡ ሦስተኛ ዛሬ በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በሚውልበት ጊዜ አንድ ብስክሌተኛ ብቻ ማካፈል በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ ለሮም ኦሊምፒክ በዚያን ጊዜ የብስክሌት ፌዴሬሽን አልነበረም፡፡ አንድ ግሪክ ነው (ጋሽ ገረመው ደንቦባን ልትጠይቀው ትችላለህ) በ7 ሺሕ ብር ብስክሌት የገዛላቸው፡፡ መንግሥት በጀት ሲለቅ ነው ለግሪኩ የተከፈለው፡፡ ያን ጊዜ ግን ሦስት ተወዳዳሪዎች ነበሩ፡፡ ዛሬ አንድ ለምን? በቶኪዮም በሜክሲኮም በርካታ ነበሩ፡፡ ዞሮ ዞሮ ዕድገት የለም፤ የተለወጠ ነገር የለም፡፡ በስፖርቱም ዓይነት ሆነ በስፖርተኞች ቁጥር የሜዳሊያ ቁጥራችን የጨመረው በዚያን ጊዜ የሌሉ የሴቶች የማራቶን፣ 10ሺ፣ 5ሺ፣ 1,500፣ 3,000 መሠናክል ዛሬ ስለተጀመሩ ነው እንጂ አይጨምርም ነበር፡፡ እኛና ኬንያ በመካከለኛ ርቀትና በማራቶን ጥሩ ውጤት አለን፡፡ ያ በሴቶችም ሲሆን ዕጥፍ ሆነ እንጂ አንድም ዕድገት የለም፡፡ መሸፋፈን አያስፈልግም፡፡ 60 ዓመታት ሙሉ አንድ ቦታ ለምን ቆምን ብሎ በአልማዝ ኢዮቤልዩ አጋጣሚ መነጋገር ይገባ ነበር፡፡ የዛሬ 60 ዓመት ከነበርንበት ቦታ ላይ ለምን ቆምን? ያኔ ገንዘብ የለም፣ ባለሙያ የለም፡፡ በዚያ ሁሉ መወዳደር ከቻልን ዛሬ ከ60 ዓመት በኋላ በዚህ ሁሉ ሚሊዮን ብር ለምን ቆምን? ይኼ ነው መታየት ያለበት፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን መጽሔቶች ላይ የምናየው ስህተት እንዴት ነው ማረም የሚቻለው? ለተፈጠሩት ስህተቶችስ ይቅርታ የሚጠይቅ አካል አይኖርም?
አቶ ታደለ፡- እኔ በዚህ ጉዳይ ላይ ከወ/ሮ ዳግማዊት ግርማይ ጋር አንድ ጊዜ ተወያይቼያለሁ፡፡ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴያችን ታሪክ መለወጥ ተገቢ እንዳልሆነ፡፡ በዚያን ጊዜ የቤጂንግ ኦሊምፒክ (2000 ዓ.ም.) ተቃርቦ ስለነበረ፣ ሩጫ ላይ ስለነበሩ ግዴለም እንደመጣሁ አጣርቼ መልስ እሰጣለሁ ብለው በዚያው ሁኔታዎች ቀሩ፡፡ ዛሬም ታሪኩ ላይ መሰባሰብ ያስፈልጋል፡፡ ሰነዶቹ እዚያው አሉ፡፡ የጠፋው አንብቦ እውነተኛውን የሚዘግብ ነው፡፡ የበረከተው ደግሞ የእውነቶቹን ሸፍኖ አዳዲስ የፈጠራ ታሪክ የሚያጎላው ነው፡፡ አንድ ያየሁት አሳዛኝ ነገር፣ በዚህ ባነሳኸው ነጥብ ላይ ይቅርታ የመጠየቅ ባህል የለንም፡፡ ስህተታቸውን እያወቁ ይቅርታ የመጠየቅ ባህሉ የለም፡፡ ይኼን ነገር በብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴው አይቻለሁ፣ በጣም ነው የገረመኝ፡፡
አንድ ጊዜ የብሔራዊ ኦሊምፒክ ኮሚቴ 50ኛ ዓመት ሲከበር ለይድነቃቸው ተሰማ ሽልማት ተቀበል ብለው በቃል ጋበዙኝ፡፡ ትክክል አለመሆናቸው ነገርኳቸው፡፡ ማንኛውም ሽልማት ሲሰጥ መጀመርያ የሚሸለመው ምን ሠራ ተብሎ ነው? በናንተ ድረ ገጽ ብቁ ስላልነበረ ግሪክ መጥቶ ተሹሟል ነው ያላችሁት፡፡ ብቁ ያልነበረ ሰው ለምን ትሸልማላችሁ? ስለዚህ አብራሩልኝ ብዬ ብጠይቅ መልስ አልመጣም፡፡ ቢሆንም ባይሆንም ተገኝልን አሉ፤ አልገኝም፣ ቤተሰቡም አይቀበልም አልኩ፡፡ ግን በግድ እነሱ ሰጪ፣ እነሱ ተቀባይ ሆኑ፡፡ ማን እጅ ላይ እንዳለ አላውቅም፡፡ እዚያው ተቀባበሉት፡፡ ይቅርታ የጠየቀ ሰው የለም፣ ይቅርታ የመጠየቅ ባህል የለም፣ በጣም አሳፋሪ ነው፡፡ ስህተት መሥራት አንድ ራሱን የቻለ ችግር ሆኖ፤ ስህተቱ ተነግሮ ይቅርታ አለመጠየቅ በማንኛውም መሥፈርት ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ደግሞስ ታሪክህን ራስህ ታዘጋጃለህ እንጂ እንዴት ለውጭ አሳልፈህ (አውት ሶርስ አድርገህ) ትሰጣለህ? ይኸው ነው የሚሰማኝ፡፡
- ሔኖክ ያሬድ's blog
- 548 reads
No comments:
Post a Comment