Saturday, August 20, 2016

የወንዶች ማራቶን - የሪዮ ኦሊምፒክ ማጠቃለያ -  የኢትዮጵያ አራተኛው ባለድል ይመጣ ይሆን?

በሔኖክ ያሬድ፥ ነሐሴ 15፣ 2008

ከሁለት ሳምንታት በላይ ያስቆጠረው 31ኛው ኦሊምፒያድ ፍፃሜው ላይ ደርሷል፡፡ በመዝጊያው ነሐሴ 15 ቀን 2008 ዓ.ም. ከሚካሄዱት ውድድሮች ዋነኛው የወንዶች ማራቶን ይጠቀሳል፡፡ ማራቶን ከጥንት እስከዛሬ የብዙዎችን ቀልብ እንደገዛ ነው፡፡ በየኦሊምፒኩ የሚጠበቁ ሯጮች እንደሚያሸንፉ ሁሉ ያልተጠበቁ፣ ያልታሰቡ ክብሩን ሲቀዳጁ ይታያል፡፡ ከእነዚህ አንዱ ባለፈው የለንደን ኦሊምፒክ አሸናፊው ዑጋንዳዊ ስቴፈን ኪፕሮች ተጠቃሽ ነው፡፡

በዛሬው የሪዮ ኦሊምፒክ ማራቶን በተለይ ምሥራቅ አፍሪካውያኑ ኢትዮጵያ፣ ኤርትራ፣ ኬንያና ዑጋንዳ የሚያደርጉት ፉክክር ይጠበቃል፡፡ የኢትዮጵያ ተሰላፊ ሠለስቱ ሯጮች ተስፋዬ አበራ፣ ለሚ ብርሃኑና ፈይሳ ሌሊሳ ናቸው፡፡ ከኢትዮጵያ ሯጮች ፈጣን ሰዓት ያለው ባለፈው ጥር በዱባይ ማራቶን 2፡04፡24  በመፈጸም ያሸነፈው ተስፋዬ አበራ ነው፡፡ ከኬንያውያኑ ኢሉድ ኪፕችግ (2፡03፡05) እና ስታንሌይ ቢዎት (2፡03፡51) ቀጥሎ ዘንድሮ ፈጣን ሰዓት ያስመዘገበው ተስፋዬ፣ ባለፈው ሚያዝያ ባሸነፈው ሀምቡርግ ማራቶን በ2፡06፡58 መፈጸሙ በጥሩ አቋም ላይ እንደሚገኝ የአይኤኤፍ ዘገባ ያመለክታል፡፡ በሌሎች ታላላቅ ውድድሮች ባይወዳደርም በዓለም አገር አቋራጭ ሻምፒዮና ሮጧል፡፡

ለሚ ብርሃኑ ከተስፋዬ ቀጥሎ ጥሩ ሰዓት 2፡04፡33 ያስመዘገበ ሲሆን፣ ባለፈው ሚያዝያ የቦስተን ማራቶንን በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ማሸነፉ ይነገርለታል፡፡ አምና በቤጂንግ በተካሄደው የዓለም ሻምፒዮና በ15ኛነት ካጠናቀቀበት ውድድር ሌላ በታላላቅ ውድድሮች አልተካፈለም፡፡ ሦስተኛው ተወዳዳሪ ፈይሳ ሌሊሳ ዘንድሮ ምርጥ ሰዓት ካላቸው ሁለት ኬንያውያንና ሁለት ኢትዮጵያውያን ተርታ ውስጥ ባይገባም ወቅታዊ ሰዓቱ 2፡06፡56 ነው፡፡

በዓምናው የዓለም ሻምፒዮና በቤጂንግ ሳይጠበቅ ኢትዮጵያዊውን የማነ ፀጋይን አስከትሎ ያሸነፈው ኤርትራዊው ግርማይ ገብረሥላሴ ዘንድሮም ውጤታማ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል፡፡ በማራቶን የዓለም ሻምፒዮን ሆኖ የኦሊምፒክ ባለድል እስኮሁን አልተመዘገበም፡፡ ቀደም ባሉት ኦሊምፒኮች የሲዲኒው አሸናፊ ገዛኸኝ አበራና የለንደኑ ስቴፈን ኪፕሮች የዓለም ሻምፒዮን የሆኑት ከኦሊምፒክ ድሎቻቸው በኋላ ነበር፡፡ ዘንድሮ ይህን ታሪክ የሚለውጥ ይኖር ይሆን?

ኢትዮጵያና ማራቶን

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በኦሊምፒክ መድረክ ከ60 ዓመታት በፊት ስትገኝ፣ ከተወዳደረችባቸው ስፖርቶች አንዱ የአትሌቲክሱ ማራቶን ነበር፡፡ በኅዳር 1949 ዓ.ም. በተካሄደው ውድድር የሮጡት ባሻዬ ፈለቀና ገብሬ ብርቄ ነበሩ፡፡ ባሻዬ 29ኛ፣ ገብሬ 32ኛ ሆነው ማጠናቀቃቸው እ.ኤ.አ. የ1956 ሜልቦርን ኦሊምፒክ ሰነድ ያወሳል፡፡

ኢትዮጵያ ወርቃዊ ድል ማጣጣም የጀመረችው እ.ኤ.አ. በ1960 በሮም ኦሊምፒክ በማራቶን ነበር፡፡ በደማቅዋ የአውሮፓ በጋ ምሽት፣ ጳጉሜን 5 ቀን 1952 ዓ.ም. ጀንበርዋ በሮም ኦሊምፒክ ስታዲየም ጀርባ ባዘቀዘቀችበት አጋጣሚ አንድ ያልታወቀ ጥቁር ገጽታ ያለው አትሌት፣ የማራቶኑን ሩጫ በውራ ጎዳናው በቀዳሚነት ፈፀመ፡፡ በባዶ እግሩ የሮጠው  አበበ ቢቂላ በ2 ሰዓት 16 ደቂቃ 15 ሰከንድ የመጨረሻውን መስመር በጥሶ በማለፍ የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ከሁሉም በላይ እንድትውለበለብ አደረጋት፡፡ ሌላኛው ኢትዮጵያዊ አበበ ዋቅጅራም እንደ አበበ ቢቂላ ሁሉ በባዶ እግሩ ሮጦ በሰባተኛነት አጠናቅቋል፡፡ አበበ ቢቂላ በሮም በሽልማት ሰገነቱ ላይ እንደወጣ የመጀመሪያው «ጥቁር አፍሪካዊ» የኦሊምፒክ ወርቅ ሜዳሊያ አጥላቂ ሆነ፡፡

ከአራት ዓመት በኋላ ለኢትዮጵያ ሦስተኛዋ በሆነው የቶኪዮው የኦሊምፒክ ተሳትፎ፣ አበበ ቢቂላ ጥቅምት 11 ቀን 1957 ዓ.ም. ተጫምቶ በመሮጥ ለሁለተኛ ጊዜ የማራቶን ድሉን አዲስ የዓለምና የኦሊምፒክ ክብረ ሰዓትን በ2 ሰዓት 12 ደቂቃ 11.2 ሰከንድ በመፈጸም መስበሩ ብቻ ሳይሆን፣ የትርፍ አንጀት ቀዶ ሕክምና ባደረገ ስድስት ሳምንት ውስጥ ማሸነፉ ገድሉን ልዩ ያደርገዋል፡፡

ከእርሱ በፊት ማንም ያልፈጸመውን፣ ከእርሱም በኋላ ለ16 ዓመታት ማንም ያላደረገውን የኦሊምፒክ ማራቶን ሁለት ጊዜ አከታትሎ የመውሰድ ገድል ፈጸመ፡፡ ይኸም ብቻ አይደለም ባሻናፊነት የገባበት ሰዓትም እጅግ በጣም ፈጣንና በእንግሊዛዊው ባሲል ሔትሌይ በ2 ሰዓት 13 ደቂቃ 55 ሰከንድ ተይዞ የነበረውን የዓለም ክብረወሰን በ1 ደቂቃ 43፡8 ሰከንድ የሰበረበት ነው፡፡

‹‹እንደበረዶ ነጫጭ ጥርስ አብቅሎ፣ ይቆረጣጥማል ሰዓት እንደቆሎ›› ብለው በወቅቱ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ የነበሩት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ (1914-1979) እንዲቀኙለት አድርጓቸዋል፡፡

ከ52 ዓመታት በፊት አበበ ቢቂላ ለሁለተኛ ጊዜ ታላቁን ሩጫ ማራቶንን አሸንፎ ወርቅ ሲያጠልቅ ‹‹የበርሊን ማራቶን መጽሔት›› ዘጋቢ እንዲህ ነበር የጻፈው፡፡

‹‹አበበ ቢቂላ በ1952 ዓ.ም. የሮም ኦሊምፒክ ማራቶን በባዶ እግሩ ሮጦ ተአምራዊ አሸናፊ ከሆነ ወዲህ የማራቶንን ሩጫ በ2 ሰዓት ከ14 ደቂቃ የሚጨርስ ቢኖር ሻምፒዮን ይባላል፤ በ2 ሰዓት ከ13 ደቂቃ የሚፈጽም ከተገኘ ደግሞ ድንቅ ሻምፒዮን ይባላል፡፡ አበበ ቢቂላ ግን በቶኪዮ ኦሊምፒክ 2 ሰዓት ከ12 ደቂቃ ከ11፡2 ሰከንድ በማምጣቱ ምን ብዬ እንደምለው ቃላት አጥቼለታለሁ፡፡››

በቀጣዩ አራት ዓመት አበበ ቢቂላ ለሦስተኛው ድል ቢሮጥም፣ 17ኛው ኪሎ ሜትር ላይ ባጋጠመው የጡንቻ መሸማቀቅ አቋርጦ ወጥቷል፡፡ ቢሆንም ድሉ ከኢትዮጵያ አላፈተለከም፡፡ በመስከረም 1961 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. 1968) የሜክሲኮ ኦሊምፒክ ማሞ ወልዴ አገሩን ለሦስተኛ ጊዜ አሸናፊ ያደረጋትን ድል አስመዘገበ፡፡ መርዓዊ ገብሩም ስድስተኛ ሆነ፡፡ ማሞ በ10,000 ሜትር ሩጫም ከኬንያዊው ናፍታሊ ቲሙ ጋር እልህ አስጨራሽ ፉክክር አድርጎ የብር ሜዳሊያ ለማጥለቅ ችሏል፡፡ የማሞ የማራቶን ድልም ‹‹ማራቶን ማራቶን ማራቶን ልዕልቷ

 አበበና ማሞ ሆኑ ባለቤቷ›› ተብሎ እንዲዘፈን አደረገ፡፡

20ኛው ኦሊምፒያድ የጀርመኗ ሙኒክ ከተማ በ1964 ዓ.ም (1972) ስታዘጋጅ የተካፈለችው ኢትዮጵያ ለወርቅ ባትታደልም በነሐስ ሜዳሊያ ለመታጀብ ችላለች፡፡ ማሞ ወልዴ በ40 ዓመት ዕድሜው ማራቶንን ሮጦ ሦስተኛ በመሆኑ፣ አንጋፋው የኦሊምፒክ ማራቶን ባለሜዳሊያ ተሰኝቷል፡፡

ከሙኒክ ስምንት ዓመት በኋላ በተደረገው የሞስኮ ኦሊምፒክ ሜዳሊያ ሠንጠረዥ ውስጥ ባትገባም ደረጀ ነዲ ሰባተኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡ በባርሴሎና እና በአትላንታ ኦሊምፒኮች ውጤት የራቃት ኢትዮጵያ (በአትላንታ በሴቶች የፋጡማ ሮባ ድል ሳይዘነጋ)፣ የወርቅ ሜዳሊያን ያገኘችው ከ32 ዓመት ቆይታ በኋላ ነበር፡፡

በሲድኒ ኦሊምፒክ 27ኛው ኦሊምፒያድ በ1993 ዓ.ም (እ.ኤ.አ. 2000) ሲካሄድ  ገዛኸኝ አበራ ከስምንት ኦሊምፒያድ በኋላ ለኢትዮጵያ በማራቶን የወርቅ፣ ተስፋዬ ቶላ የነሐስ ሜዳሊያዎች ለማስገኘት ችለዋል፡፡ አንፀባራቂ ድልንም ተጎናፅፈዋል፡፡

ከሲድኒ በኋላ በተካሄዱት የአቴንስ፣ የቤጂንግና ለንደን ኦሊምፒኮች ኢትዮጵያ ከወርቁ ጋር ከተፋታች 16 ዓመታት ተቆጥረዋል (በለንደን የፀጋዬ ከበደ ነሐስ ሜዳሊያ ሳይዘነጋ)፡፡ ዘንድሮ ለኢትዮጵያ በወንዶች ማራቶን አምስተኛውን ወርቅ የሚያመጣውና አራተኛው ኢትዮጵያዊ የማራቶን ባለወርቅ የሚሆነው ኢትዮጵያዊ ማን ይሆን?

ስፓርት

Author

ሔኖክ ያሬድ

Amharic News 08/17/2016

‹‹እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ . . .››


በሔኖክ ያሬድ
 ‹‹ስለ ሀገሬ ኢትዮጵያ ባሰብኩ ቁጥር ስለ ጥንታዊቷ አገር ያነበብኳቸው የታሪክ መጻሕፍትና አሁን ያለንበት ሁኔታ አልገጣጠም ይለኝና ‹ለምን ይህ ሆነ?› እያልኩ ብቻዬን እነጋገራለሁ፤ እተክዛለሁ በተመስጦም ዝም ብዬ ቁጭ እላለሁ፡፡ ቀድሞ የነበርንበትን የከበረ ወንበርና አሁን ደግሞ ያለንበትን ከባድ ጉስቁልና ሳስብ ውስጤ በቁጭት ይሞላል፡፡ ብዙ ጊዜ በጥሞና ውስጥ ሆኜ አዲሲቱንና የምንመኛትን አገሬን በዓይነ ሕሊናዬ አያታለሁ፡፡ ታዲያ እንደገና መለስ ብዬ አሁን ያለንበትን ሁኔታ ሳስብ ወደምንመኛት፣ ማርና ወተት ወደምታፈስ አገር ለመድረስ ምን መደረግ አለበት? ብዬ ሳውጠነጥን መያዣ መጨበጫው ይጠፋኛል፡፡ ችግሮቹ እጅግ የበዙ ናቸውና፡፡››


ፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው (በግራ)  1.                                                                                                                                      

     መሰንበቻውን የኅትመት ብርሃን ባየው የፕሮፌሰር ዳንኤል ቅጣው ‹‹እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ . . .›› መጽሐፍ መግቢያ ላይ ደራሲ የተንደረደሩበት እሳቦት ነው፡፡ ቀድሞ ገናና የነበረች አገር በዚህ ዘመን ምን ዱብዳ ወድቆባት ነው ጭራ የሆነችው? የሚለውን የኅብረተሰብ ቁጭት መርምረው መፍትሔ ነው የሚሉትን ሐሳቦች በመጽሐፉ ላይ አስፍረውታል፡፡ 

 
የአስተሳሰብ የማያቋርጥ ዕድገት ለአገሮች ብልፅግና መሠረት መሆኑን  ያመለከቱት ደራሲው፣ ሐሳባቸውን ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ በመነሳት ለአገሪቱ ዕድገት የኢትዮጵያውያን የልቦና ውቅር መለወጥ (ፓራዳይም ሺፍት/Paradigm Shift) እንዳለበት ያመለክታሉ፡፡
መጽሐፉ ባለፈው ሳምንት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሲመረቅ የምሕንድስና ፕሮፌሰሩ እንደተናገሩት፣ ‹‹የምንመኛትን ኢትዮጵያ በማየት እዚያ እንዴት ነው መድረስ የምንችለው? አስተሳሰባችን አመለካከታችን ልንቀይር ይገባል፡፡ አሁን ያለን አመለካከት ድሮ በኖርንበት ከሆነ የትም መድረስ አንችልም፡፡ ዓለም እየተቀየረች ነው፡፡ በፖለቲካ፣ በጂኦግራፊ፣ በኢኮኖሚ በሁሉም አቅጣጫ እየተቀየረች ሲሆን እኛ ደግሞ ሐሳባችንና አመለካከታችን መቀየር አለበት፡፡››
ይህንኑ መሠረተ ሐሳባቸውን በመግቢያቸው እንዲህ አብራርተውታል፡፡  ‹‹ኢትዮጵያን ስናስብ በራቀው የታሪካችን ምዕራፍ ውስጥ ምን ያህል ገናና ታላቅ አገር እንደነበረች እንረዳለን፡፡ ጥቂትም ቢሆኑ ትንግርት መስለው የቆሙ ምስክሮቻችን ለቀድሞ ትውልድ ማንነት ማስታወሻ፣ ለአሁኖቹ የጥያቄዎቻችን ምንጭ፣ ለሌሎቹ ደግሞ የግርምታቸው ዘሀ ሆነው እናገኛቸዋለን፡፡ ታዲያ ከዓለም በፊት ቀድመን፣ ሰው ተኝቶ ሳያልም እኛ ርዕይ አይተን እንዳልነበር ለምን አሁን የሀገራት ጭራ ሆንን? ጥያቄው የሁላችንም፣ ምክንያቱ ፈርጀ ብዙ ይሆናል፡፡
‹‹ይሁን እንጂ አሁንም እንደትውልድ ለቀጣዩ እንድናስተላልፍ ያልተቀበልነው ዱላ፣ እንደታሪክ ያልተሻገርነው ክፍተት አለ ማለት ነው፡፡ አገራችን እጅግ ከባድና መራራ ጊዜ ብታሳልፍም፣ የቱንም ያህል ጠላቶቻችን ቢበዙና ቢያይሉ ከሥራ ለዘብተኛነትና ቸልተኝነት በላይ የሚጎዳን፣ ከፍቅርና ኅብረት ማጣታችን የባሰ የሚያሸንፈን ነገር አይኖርም፡፡ በመሆኑም በአገር ደረጃ ከፍ ብለን ለመታየትና፣ የምንመኛትንም ዓይነት የበለፀገችና ጠንካራ አገር በሁላችንም ጥረትና ሥራ ለማምጣት የጋራ ርዕይ ያስፈልገናል፡፡ ይህን ርዕይ ደግሞ ሁላችንም ልንደርስበት የምንችለው በእያንዳንዳችን ልብ ውስጥ የታተመ ሲሆን ነው፡፡››
ሌላው ተናጋሪ፣ ‹‹አገርን ለመውደድ መጀመርያ ራስን መውደድ ያስፈልጋል የሚል ነገር አለ፡፡ እዚህ ላይ ነው የልቦና ውቅር የሚመጣው፡፡ ኢትዮጵያውያን በየጊዜው ያለፉበት መንገድ አለ፤›› የሚሉት በመጽሐፉ ላይ አስተያየት የሰጡት የሥነ ልቦና ምሁሩ ዶ/ር መስፍን አርአያ ናቸው፡፡  
እንዲሀም አብራሩት፣ በአንድ ወቅት ካሜራ ኢትዮጵያ ሲገባ ለአፄ ምኒልክ እንዴት እንደሚሠራ ሲያሳዩዋቸው በአካባቢያቸው የነበሩት በጣም ነበር የነቀፉት፡፡ ለምን ይህ የሰይጣን ሥራ ነው የሚል አመለካከት ነበራቸውና፡፡ እንዲህ ያለ ነገር አገራችን መግባት የለበትም፤ መኪና ፈቀዱ፣ ሰላቢ የሆነ በሽቦ ውስጥ የሚሄድ ድምፅ እንዲሠራ ፈቀዱ፤ በአገራችን መከራ አሳር ያመጣል፡፡ በዚያን ጊዜ የነበረውን የልቦና ውቅር ያሳያል፡፡ አርቆ አሳቢው መሪ ግን ራሳቸው እንዳሳዩት ካሜራውን መጠቀም፣ መኪናውን መንዳት ነበረባቸው ራሳቸው በስልክ መነጋገር ነበረባቸው፡፡
‹‹እንደዚህ ዓይነቱን ውቅር ለውጥ እስካላመጣን ድረስ በአገሪቱ በአንድ ቦታ ላይ የምንሰቃይ ከሆነ መራመድ አንችልም፤ ወሳኝ የሆነ ነገር ነውና የልቦና አወቃቀር ጽንሰ ሐሳብን ሁላችንም መያዝ እንዳለብን በሚገባ መጽሐፉ ያመለክታል፤›› ያሉት ዶ/ር መስፍን፣ ሙሉ ሰዎችን ለማፍራት ትክክለኛ የልቦና ውቅር ለውጥ መምጣት እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተውበታል፡፡ በየትውልድ ላይ የሚቀየሩ ነገሮች እንደሚስተዋሉ ያመለከቱት አንድ ዘለላ ምሳሌ በማምጣት ነው፡፡
‹‹በአሁን ሰዓት የአሜሪካን ሕዝብ መዝሙር ለማጥናት የሚተጉ ወጣቶችን አስተውላለሁ፡፡ አንፃሩ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ መዝሙር ከ‹ኢትዮጵያ ሆይ› ጀምሮ እስካሁን እስካለው ‹የዜግነት ክብር› ድረስ ያለውን መዝሙር የምናውቀው ስንት ነን? ብንል በጣም ጥያቄ ውስጥ የምንገባ ነው የሚሆነው፡፡ የልቦና ውቅር ሰፊ ነው ወደ ሚለው ይወስደናል፡፡
የምንመኛት ኢትዮጵያን በተመለከተ በልማቱ ዘርፍ ምርታማነትና ጥራት ላይ ብዙ ጽፈዋል፡፡ ወደዚያ ለመድረስ ከፈለክ ግን መጀመርያ ያለውን የልቦና አወቃቀራችንን ለመቀየር መዘጋጀት አለብን የሚለው ከዚህ መጽሐፍ ላይ የምወስደው ነው፡፡››
በዶ/ር መስፍን አርአያ አገላለጽ፣ የልቦና ውቅርን ከሰብእና ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ ሰብእና አንድ ሰውን ሲያመለክት ልቦና ውቅር ደግሞ በዚያ ሰውና በአካባቢው የሚቀረፁ ሒደቶችን ያመላክታል፡፡
‹‹እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ. . .›› መንግሥታዊና ግላዊ ተቋማት እንዲሁም የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ትስስር የተሻለ እንዲሆን ይመክራል፡፡ ምርታማነት እንዲጨምር ያሠራር መንገዶችን በቀጣይነት ስለማሻሻል ያትታል፡፡ በተለይም የሐሳቦች ዋነኛ አትኩሮቱ ጥራት ላይ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ዕድገት ያገልግሎትና ምርት ጥራት ጉዳይ የሁሉም ኃላፊነት መሆኑንም አስረግጦ ይናገራል፡፡ ይህንኑ  ፕሮፌሰር ዳንኤል ሲያመለክቱ፣ ‹‹ጥራት ሒደት ነው፤ ጥራት የዕድገት ደረጃ ነው፡፡ አሜሪካኖቹ አውሮፓውያኑን በሰባት ዓመት ይበልጧቸዋል ይላል ሊትሬቸሩ፤ አውሮፓውያኑ ደግሞ እኛን በብዙ ዓመት ይበልጡናል፡፡ ስለዚህ ይህን የጥራት ባህል የምናመጣው እያንዳንዳችን ከልጅነት ጀምሮ ስንማር ነው፤›› ብለዋል፡፡
በመድረኩ እንደታወሰው፣ አገሪቱ አማካይ ነገር ላይ ነች፡፡ በድህነትና በብልፅግና፡፡ እኩልነት የሰፈነባት ኢትዮጵያን ለማምጣት ‹‹እነሆ መንገድ ለኢትዮጵያ . . .›› አንድ ማሳያ ነው፡፡ ‹‹የመንግሥተ ሰማያት መንገድ ቀጭን ነች፡፡ የኢትዮጵያን ቀጭን መንገድ ሁላችን ልንጓዝበት ይገባል፡፡ በሩ እየሰፋ ይሄዳል፡፡ የኢትዮጵያችን በር መስፋት አለበት፡፡ ጥቂቶች የሚበለፅጉበት ሌሎች መናጢ የሚሆንበት መንገድ መኖር የለበትም፡፡ የልቦና ውቅር ለውጥ መምጣት አለበት፤›› በመድረኩ ተስተጋባ፡፡
በአገሪቱ መተባበርና መወዳደር (Cooperative and Competition) ለዕድገት እንደሚበጅ ደራሲው ያሰመሩበት ቁም ነገር በምሳሌ የታጀበ ነው፡፡ ‹‹አቅርቦት (Delivery)›› በተሰኘው ምዕራፋቸው ያነሱት ነጥብ እዚህ ላይ ይነሳል፡፡
‹‹የጫማ ፋብሪካ የሚጠይቀው የአቅርቦት መጠን እራሱ ካለው የአቅርቦት አቅም በላይ ከሆነ፣ እሱን መሰል ከሆኑ ሌሎች ፋብሪካዎች ጋር በመተባበር የተጠየቀውን የአቅርቦት መጠን ማሟላት ይችላል፡፡ ተመሳሳይ ድርጅቶች በጋራ ሆነው መሥራት፣ ሲያስፈልግም ደግሞ እርስ በርስ መወዳደራቸው ክላስተሪንግ በመባል ይታወቃል፡፡ ይህን ክላስተሪንግ የተሰኘ ጽንሰ ሐሳብ ማስተማሪያ የሚሆን ምሳሌ ሳስብ እ.ኤ.አ. 2003 የተካሄደው የፓሪሱ የዓለም ሻምፒዮና የ10,000 ሜትር ሩጫ ውድድር ወደ አዕምሮዬ ይመጣል፡፡
‹‹በዚያ ፈታኝና እጅግ እልህ አስጨራሽ ውድድር ላይ ኢትዮጵያውያኑ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ቀነኒሳ በቀለና ስለሺ ስሕን ተወዳድረዋል፡፡ ሦስቱ ጀግና አትሌቶቻችን ከመነሻው ጀምሮ በመተባበር ሌሎቹን ተወዳዳሪዎች ካዳከሟቸው በኋላ ሦስቱም ብቻቸውን አፈትልከው ወጥተዋል፡፡ ዓለም በአንድ ሳንባ የሚተነፍስ እስኪመስል ድረስ ትንፋሽ አሳጥቶ የነበረው ውድድር ላይ ተነጥለው የወጡት አትሌቶች ቀሪው ሥራቸው እርስ በርስ መወዳደር ነበር፡፡ እናም ሦስቱ ብርቱዎች እርስ በርስ ተፎካክረው ከአንደኛ እስከ ሦስተኛ ወጡ፡፡
‹‹እነዚህ ጀግኖች ተመሳሳይ ስልት ተጠቅመው እ.ኤ.አ. 2004 በአቴና ኦሊምፒክ ከዚያም እ.ኤ.አ. 2008 በቤጂንግ ኦሊምፒክ የ10,000 ሜትር ሩጫ ውድድሮች ላይ በተደጋጋሚ አስደናቂ ውጤት አግኝተዋል፡፡ ይህ ነው እንግዲህ በመተባበርና በመወዳደር አንፀባራቂ ድል ማስመዝገብ፡፡ ኢንዱስትሪዎቻችንም አንዱ ብቻውን አከናውኖ ማቅረብ የማይችለውን በመተባበር ቢሠሩ በድል አድራጊነት መወጣት ይችላሉ፡፡››Tuesday, August 9, 2016

ኧረ አፋልጉን!
‹‹ይወስዳል መንገድ፤ ያመጣል መንገድ፣
አንድም የሚያስደስት አንድም የሚያሳዝን›› ብል ማን ከልክሎኝ፡፡ እየተጓዝን ነው፡፡ ከአራዳ ጊዮርጊስ በቸርችል ጎዳና ቁልቁል እየወረድን ነው፡፡ ረዳቱ ‹‹ይወስዳል መንገድ . . .›› እያለ ያዜመውን ያንጎራጎረውን የሰሙት ከጥግ የተቀመጡት ሃምሳዎቹን ያገባደዱት ተሳፋሪ ‹‹አዎ ይወስዳል መንገድ. . . እውነትህን ነው፡፡ ሐሴትና ብካይን ደስታና ሐዘንን እያፈራረቀ ይወስደናል፤›› አሉት፡፡ ግራና ቀኝ ገልመጥመጥ እያሉ፡፡ ግንቦት መገባደጃ ነው፡፡ ግንቦት የወራት ሁሉ ቁንጮ ያሰኘው መንግሥት የተለወጠበት አጋጣሚ ነው፡፡ ታክሲውም እያመራ ያለው እያቆለቆለ ያለው ወደ ቦሌ ነው፡፡
አንደኛው ተሳፋሪ ረዳቱን ‹‹አብዮት ነው የምትጥለኝ›› ይለዋል፡፡ ‹‹ምን እጥልሃለሁ አወርደሃለሁ እንጂ ደርግ እንደወረደው ሳይሆን በክብር አወርድሃለሁ እንጂ›› ሆነ መልሱ፡፡ ይሄኔ ነው ከጎልማሳነት ያለፉት ተሳፋሪ ትውስታቸውን ማውጋት የጀመሩት፡፡ ‹‹ረዳት ለመሆኑ ይህ የምንወርድበት ጎዳና ስሙን ታውቀዋለህ? ለነገሩ ብዙዎች አያውቁትም?››
ቀጠለ ረዳቱ፣ መለሰ የምድር ተሽከርካሪ አጋፋሪው፤ ‹‹ምነው አባቴ ቸርችል ጎዳናን ሁሌ የምንጠራውን ነው እንዴ የሚጠይቁኝ?››
‹‹እሱማ የአሁን ስሙ ‘ኮ ነው፤ የድሮውን ነው የምልህ ‹አብዮት አብዮት› ትላለህ ከቀረ ዘመን የለውም፤ ‹መስቀል መስቀል› አትልም›› አብዮት አደባባይ መጠሪያው በግንቦት ከተገረሰሰው ደርግ ጋር መቅረቱን እንዳላጣው የተናገረው ረዳቱ፣ ‹‹መስቀል መስቀል ብል ማንን ልትሰቅል ነው? ቢሉኝ ምን ልመልስ ነው? ሆሆ ጎመን በጤና አንቀጽ ቢጠቅሱብኝ ማን ያተርፈኛል? ቃሊቲ መውረዴ አይደል፤›› ተሳፋሪው ሁሉ አውካካ ሳቅ በሳቅ፡፡ ‹‹እውነቱን ነው›› አለች አንዷ መለሎ ተሳፋሪ፤
‹‹የዓይኖቿ ውበት የአንገቷ ሙስና
ሮብ ያስገድፋል እንኳን ሐሙስና›› ለሷ ዓይነት የተገጠመ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ቀጠለች ‹‹ታሪካችንን በቅጡ ባለማወቃችን ለአጓጉል ነገር ይዳርገናል፡፡ ብናውቅም በማያውቁት ላይ ብንወድቅ ለከፋ ነገር እንዳይዳርገን ምን ዋስትና አለ?››
‹‹መስቀል መስቀል. . . ብሏል ብሎ ዘብጥያ ቢወርድ ነገ አዋቂ ሰው አይጥፋ እንጂ መለቀቁ አይቀርም›› አለ አንድ ፕሮቶኮሉን የጠበቀ ‹ስሪ ፒስ› የተላበሰ የኮቱ ደረት ላይ ‹‹Rio 2016›› የሚል ጽሑፍ የሰፈረበት ፒን የለጠፈ፡፡ ከሁለት ወራት ያነሰ ጊዜ እየጠበቀ ያለው የሪዮ ኦሊምፒክ የሚጠብቅ ይመስላል፡፡ ‹‹የመስቀሉ ታሪክ እስከሚጣራ ማን ይታሰራል፤ ተረቱን አልሰማህም እንዴ! አለች ውቢቷ ተሳፋሪ፡፡ ተረቱንም ተረተች፡፡
‹‹አንዲት ጥንቸል እየሮጠች ነው፤ ማረፍ የለም፤ የሚያውቋት ሁሉ ሰላምታ ሊያቀርቡላት ቢሞክሩም የድንጋጤ ሩጫዋ ማለቂያ አልነበረውም፡፡ ፌቆ አገኘቻትና ‹ምነው እንዲህ ያስሮጥሻል? ማነው ያስደነበረሽ?› አለቻት፡፡  ‹‹አልሰማሽም እንዴ ታላላቆቹ አራዊት እነ አንበሳ፣ ነብር  እንዲያዙ ታዟል ‘ኮ›› ስትላት፣ ‹‹ታዲያ  አንቺ ምን ቤት ነሽ? አይመለከትሽ›› ከማለቷ ከአፏ ቀበል አድርጋ  ‹‹እስኪጣራ ማን ይያዛል?›› ሆነ መልሷ፡፡››
ተሳፋሪው ሁሉ አውካካ፣ ሳቁን መቆጣጠር ያቃተው ረዳቱ ‹‹ይሄም አለ ለካ! አፌ ቁርጥ ይበልልሽ፣ በአንድ ሬዲዮ የሰማሁት ‹ነገር በምሳሌ፣ ጠጅ በብርሌ፣ መዝሙር በሃሌ› ተከሰተልኝ፤›› ብሎ ብቻ አላበቃም፡፡  የቀደመ ወጉን አስታውሶ ጠየቀ፤ ‹‹ጌታው ይልቅ የቸርችል ጎዳና የቀድሞ ስሙ ማን ነበር? ይንገሩን እንጂ?››
ነገር በነገር ቢወሳ አይደንቅምና ተሳፋሪው የታክሲ ላይ ውይይቱን ተያይዞታል፡፡ የጎዳናው መጠርያ ማን እንደነበረ ማወቅ ሽቷል፡፡ ‹‹ነውን ለማወቅ ነበርን ጠይቅ›› ነውና፡፡
 ከሰባ አምስት ዓመት በፊት ፋሺስት ኢጣሊያ ተጠራርጎ ሲወጣ በአምስት ዓመት የወረራ ዘመኑ ሰይሟቸው የነበሩ መጠሪያዎችንም ንጉሡ እንዳስወገዱ በስድሳው ዋዜማ ያሉት ተሳፋሪ አወጉ፡፡
‹‹ይኸውልህ ልጄ ጎዳናው ‹ሙሶሎኒ ጎዳና› ይባል ነበር፡፡ የዚያ የፋሺስት ፓርቲ አውራ የፋሽስት ኢጣሊያ ቁንጮ ቤኔቶ ሙሶሎኒን ስም ይዞ የኖረው፡፡ አርበኞቻችንና ንጉሡ በእንግሊዝ ድጋፍ ድል ካደረጉ በኋላ ነው፤ ስሙ በእንግሊዝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሰር ዊንስተን ቸርችል የተቀየረው፤›› ውቢቷ በአግራሞት እያየች፣ ‹‹ምነው ይሄን ሳናውቀው ለምን ቀረን? ታሪካችንን ከዩኒቨርሲቲ ደጃፍ ገብተን እንኳን በቅጡ ሳንማር ወጣን፤ ከ25 ዓመት በፊት የነበሩት ተማሪዎች በኮመን ኮርስ ሂስትሪ ይማሩ ነበር፡፡ እኛ ለዚህ ሳንታደል ተመርቀን ወጣን፡፡ መመረቅ ነው መረገም፤›› በእንጉርጉሮዋ ሲቃ ይዟታል፡፡ ጠየቀች፡፡
‹‹እያንገበገበ አንጀቱን ሲያጨሰው
 ሮሮ አታሰማኝ ይላል ያገሬ ሰው›› ቀጠለ ከጎኗ የተቀመጠው ተሳፋሪ፡፡ በአባባሏ በመስማማት ራሱን እየነቀነቀ ነበር፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዲግሪውን ተመርቆ ሲወጣ ስላገሩ ታሪክ ቅኝት አለመቋደሱንም አወጋ፡፡
ረዳቱ ገርሞታል፤ እህህ እያለ ነው፡፡ የተሳፋሪዎቹ የወግ ለዛ ታሪክን ያጣቀሰ መሆኑ እህህውን ቀጥሎበታል፡፡ ታሪኬን ሳላውቅ እስከመቼ እህህ የሚል ይመስላል፡፡ የፊቱን ገጽታ ላየ፡፡ ያቺ ታዋቂ አቀንቃኝ ‹‹እህህ እስከመቼ እህህ. . .›› እንዳለችው መሆኑ ነው፡፡
‹‹ይልቅስ ልጨምርላችሁ ጎበዝ ከአራት ኪሎ ወደ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ የድሮው ገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ወዳለበት ሽቅብ የሚወስደው መንገድም ‹ኪንግ ጆርጅ ስድስተኛ› የተባለውምኮ ፋሺስቶች ከወጡ በኋላ ነው፤ ያኔ ‹ንጉሥ ዑምቤርቶ ጎዳና› እየተባለ በጣሊያኑ ንጉሥ ይጠራ ነበር፤›› ሲሉ አምባሳደር አካባቢ ታክሲው እየደረሰ ነበር፡፡ የቀድሞው ጦር ሚኒስቴር ያሁኑ መከላከያ ሚኒስቴር ሲደርሱ ሌላ ትዝታ ቀሰቀሰባቸው፡፡
‹‹እናንተዬ እኔ ቸርችል ጎዳናን ቁልቁል በወረድሁ ቁጥር ትዝ የሚለኝ ከ42 ዓመት በፊት የሕዝብ ንቅናቄ ሲነሣ፣ አብዮቱ ሲፈነዳ ሥልጣኑን የጠለፈው ደርግ ጦር ሠራዊቱን በጂፕ አሳፍሮ የወረደበትን ነው፡፡ ‹ቋሚ ተጠሪ› የሚባሉትን መትረየስ የተጠመደባቸውና ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› የሚል ጥቅስ የሰፈረባቸው ተሽከርካሪዎች ይዞ የተሽከረከረበት ነው፤›› ብለው መራር ትዝታቸውን፣ አብዮተ ሕዝብ በአብዮተ ደርግ መነጠቁን በቁጭት አስታወሱ፡፡  
በዘመኑ ወጣት የነበረው ጎልማሳም ተቀበላቸው፡፡ ‹‹ደርግ ንጉሡን መስከረም 2 ቀን 1967 ዓ.ም. ካወረደ በኋላ ባወረደበት መሪ ቃሉ በ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› የሚጠራ በክፍላተ ሀገር መካከል የሚደረግ የእግር ኳስ ውድድር ነበረው፤ ያን ያደረገውም በንጉሡ ዘመን የነበረውን ጥቅምት 23 ቀን 1923 ዓ.ም. በነገሡበት መታሰቢያ  የዘውድ ዋንጫ በማስቀረት ነበር፤›› ብሎ አከለበት፡፡
‹‹ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ›› ነውና ጎልማሳው ሐሳቡን ማሸንሸራሸሩን ተሳፋሪውም ጆሮውን መስጠቱን አላቋረጠም፡፡
አሁንም እኮ ታሪኩ በተመሳሳይ ቀጥሏል፡፡ የ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› ውድድር ቀርቶ ‹የግንቦት 20› ውድድር ቀጥሏል፡፡ ረዳት፣ ረዳት አብዮት ወራጅ አለ ይቅርታ መስቀል ወራጅ አለ፤›› አለና ተሳፋሪውን መመረቅ፤ መማጠን ጀመረ፤ ‹‹የከርሞ ሰው ይበለን! ኧረ በፈጠራችሁ ታሪካችንንም አፋልጉን፣ ተሰርቀናል ‘ኮ! የዝንጆሮ ገበያ ከመሆን አድኑን፡፡››
ብሂሉም ተከተለ፡፡ ‹‹ይወስዳል መንገድ ያመጣል መንገድ፣ አንድም የሚያስደስት አንድም የሚያሳዝን፡፡›› መልካም ጉዞ!