በደረጀ ጠገናው
ጥንታዊው
የግሪክ ኦሊምፒክ ጌምስ መቼ እንደተጀመረ በውል ባይታወቅም የመጀመርያው ጥንታዊ ኦሊምፒክ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ776 ዓመተ
ዓለም እንደተጀመረ ይነገራል፡፡
ኢፊቶስ
የተሰኘ ንጉስ በስፖርት አማካይነት በግዛቱ ሰላም ለማስፈን ስለፈለገ በጊዜው የነበሩትን ጠንካራ ሰዎች በማሰባሰብ በየአራት ዓመቱ
በኦሊምፒያ ያወዳድር እንደነበርም የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ያሳተመው መጽሔት ያስረዳል፡፡
ንጉሱ
ለውድድር ይመርጣቸው የነበሩ ስፖርቶች የእግር ጉዞ፣ የጦር መሳሪያ ተሸክሞ የእግር ጉዞ ማድረግ፣ ነፃ ትግል፣ ቡጢ፣ የፈረስ ግልቢያና
የጋሪ ፈረስ ሩጫ ነበሩ፡፡ ስፖርቱ በዚህ መልክ ለረዥም ምዕተ ዓመታት ቀጥሎ በ394 ዓ.ም. ሮማያውያን ግሪክን ተቆጣጥረው ስለነበረ
ንጉሰ ነገስቱ ቴዎዶር ወረራውን ምክንያት በማድረግ በዓሉ እንዳይከበር ከልክሎ፣ ማዕቀቡም እ.ኤ.አ. እስከ 1896 ቆይቷል፡፡
በ490
ዓመተ ዓለም የግሪክ ጀነራል የነበሩት ሚቲያዴስ የፐርሽያን ወታደሮች በጦር ስለአሸነፉ ከወታደሮች ፊዲፒደስ የተባለ ወታደር ድሉን
ለማብሰር ወደ አቴንስ 42 ኪሎ ሜትር ያለእረፍት ሮጦ “አሸንፈናል” እንዳለ ሕይወቱ ያልፋል፡፡ ክስተቱም ዛሬ ለምንገኝበት ዘመናዊው
ኦሊፒክ መነሻ እንደሆነም መረጃው ያስረዳል፡፡
ዘመናዊውን
ኦሊምፒክ የፈጠሩት ፈረንሳዊው ባሮን ዴ ኩበርቲን ሲሆኑ፣ እ.ኤ.አ. በ1894 ሐሳባቸውን ለተለያዩ ዓለም አቀፍ ስፖርት ሕብረተሰብ
በማሳወቅ ጨዋታዎቹም ሲካሔዱ አንዱ ሌላውን ለማሸነፍ ሳይሆን፣ የዓለም ሕዝቦች በስፖርት ውድድር ወንድማማችነትን ለማስፈን በሚል
ነበር፡፡
ኩበርቲን
በዚሁ ዓመት የመጀመርያውን ዓለም አቀፍ ጉባኤ በፖሪስ እንዲካሔድ አድርገው በጉባኤው ከ15 አገሮች የተገኙ 79 አባላት ተሰባስበው
በደረሱበት ስምምነት ዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ተመሠረተ፡፡
የዓለም
አቀፉን ኦሊምፒክ ኮሚቴ በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ የተመረጡት ደግሞ ግሪካዊው ዲሚትሪያስ ቪካለስ በ1894 እስከ 1896 ተቋሙን
መርተዋል፡፡ ዋና ፀሐፊ ሆነው የተመረጡት ደግሞ ለዘመናዊው ኦሊምፒክ መፈጠር ተጠቃሽ ሆነው እስከአሁን ስማቸው በክብር መዝገብ ላይ
ሰፍሮ የሚገኘው ኩበርቲን ነበሩ፡፡
ዘመናዊ
ኦሊምፒክ ጌምስ ከ1896 ጀምሮ እንዲካሔድ ተወስኖ አቴንስ የመጀመርያው አስተናጋጅ ሆነች፡፡ ከአቴንስ ኦሊምፒክ ጌምስ ጀምሮ በ1916
በ1ኛው የዓለም ጦርነት፣ በ1940 እና በ1944 በ2ኛው የዓለም ጦርነቶች ከመቋረጡ በቀር 30ኛውን የለንደን ኦሊምፒያድ ጨምሮ
27 ኦሊምፒያዶች ተከናውነዋል፡፡
የሻምላ
ውድድር፣ ፈረስ ግልቢያ፣ ጀልባ ቀዘፋና ቡጢን ያዘወትሩ የነበሩት ኩበርቲን ከ1896 እስከ 1925 የዓለም አቀፉን ኦሊምፒክ ኮሚቴ
በፕሬዚዳንትነት መርተዋል፡፡ ኦሊምፒክ ጌምሶችን በሚመለከት አያሌ መጽሐፎችን በጋዜጦችና በመጽሔቶች አስነብበዋል፡፡
አንድ
ስፖርት የኦሊምፒክ ስፖርት ለመሆን የሚችለው በሴቶችና ወንዶች በሦስት አሕጉሮች ከ35 እስከ 50 የሚሆኑ አገሮች የሚያዘወትሩት
መሆን ይገባዋል፡፡ የክረምት ኦሊምፒክ ጌምስ ስፖርቶች ደግሞ የሚመረጡት በሁለቱም ጾታዎች በሦስት አሕጉሮች በሚገኙ 25 አገሮች
መዘውተር የግድ ይለዋል፡፡
በ1896
የመጀመርያው አቴንስ ኦሊምፒክ ጌምስ ሴቶች ያልተካፈሉ ሲሆን፣ የ14 አገሮች 245 ወንድ ስፖርተኞች በዘጠኝ የውድድር ዓይነቶች
ተካፍለዋል፡፡ የውድድር ዓይነቶቹ አትሌቲክስ፣ ብስክሌት፣ ጅምናስቲክ፣ ክብደት ማንሳት፣ ነፃ ትግል፣ ውኃ ዋና፣ ቴኒስ፣ ኢላማ ተኩስና
ሻምላ ናቸው፡፡
በጥንታዊ
ኦሊምፒክ ለአሸናፊዎች የወይራ ዝንጣፊ እንዲበረከተላቸው ሲደረግ ሽልማቶቹ እንደ ዝናም ስለሚወሩላቸው ይከበራሉ፣ ዝነኛነትን ይጐናጸፋሉ፡፡
በዘመናዊው ኦሊምፒክ ጌምስ ግን አንደኛ ለወጣ የወርቅ፣ 2ኛ ለወጣ የብርና 3ኛ ለወጣ ነሐስ ሜዳሊያዎች ይበረከቱላቸዋል፡፡
No comments:
Post a Comment