Thursday, July 28, 2016

የኢትዮጵያ ድል በንግሥቷ ወርቅ ተጀመረ


በሔኖክ ያሬድ፣ ሐምሌ 27 ቀን 2004

 
እንደተጠበቀው ኢትዮጵያ በኬንያ ላይ ያላትን የኦሊምፒክ የሴቶች የ10,000 ሜትር ሩጫ የበላይነት ዳግም በለንደን ኦሊምፒክ ከትናንት በስቲያ (ሐምሌ 27 ቀን 2004) በንግሥቷ ጥሩነሽ ዲባባ ባስመዘገበችው አስደናቂ ድል አረጋገጠች፡፡
ዓርብ ምሽት ላይ በተካሄደውና ከፍተኛ ፉክክር በታየበት ውድድር ጥሩነሽ የዓመቱን ፈጣን ጊዜ 30 ደቂቃ 20.75 ሰከንድ በማስመዝገብ ያሸነፈችው፣ ኬንያውያቱን ሳሊ ኪፕዬጎና የዴጉ ዓለም ሻምፒዮኗ ቪቪያን ቼሩዮትን አስከትላ በመግባት ነው፡፡
ጥሩነሽ በማሸነፏ በቤጂንግ በ5,000 እና በ10,000 ሜትር ካገኘችው ድሏ ጋር የኦሊምፒክ ወርቆቿን ሦስት በማድረሷ የመጀመርያዋ እንስት አትሌት አድርጓታል፡፡ ለማሸነፍ ፎክራ የነበረችው ኬንያዊቷ ቼሩዮት በወርቅነሽ ኪዳኔ ቡድን ሥራ ዙሩ በመክረሩና ጥሩነሽም ባፈጻጸም ብቃቷ ምልዓተ ኃይሏን ተጠቅማ በማሸነፏ አልተሳካላትም፡፡
ተወዳዳሪዎቹ የመጀመርያውን 4,000 ሜትር ዙሩን በ74 ሰከንድ ጊዜ በሮጡበት አጋጣሚ መሪነቱን ይዛ የነበረችው ኪፕዬጎ ዙሩን ለማክረር ሙከራ ብታደርግም አልሆነላትም፡፡
7,600 ሜትር ላይ መሪነቱን የያዘችው ወርቅነሽ ኪዳኔ ዙሩን በማፍጠኗ ፉክክሩ በእርሷ፣ በቼሩዮት፣ በኪፕዬጎና በጥሩነሽ መካከል ሆኖ ቀጥሎ ከሦስት ዙር በኋላ ኪፕዬጎ ወርቅነሽን አልፋ ለመሄድ ብትሞክርም ጥሩነሽ ዕድሉን አልሰጠቻትም፡፡ 80 ሺሕ ተመልካች ጢም ብሎ በሞላበት ኦሊምፒክ ስታዲየም ውድድሩ ሊያበቃ 600 ሜትር ሲቀር በመወንጨፍና የመጨረሻውን ዙር (400 ሜትር) በ62 ሰከንድ በመሮጥ የድሉን ዘውድ ደፍታለች፡፡ ለሁለት ዓመት በጉዳት ምክንያት ከውድድር ርቃ የነበረችው ጥሩነሽ ከኬንያውያቱ ጋር በተደረገው ከፍተኛ ፉክክር የወርቅነሽ ኪዳኔ አሯሯጥ ለድሏ እንደረዳት ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተናግራለች፡፡
‹‹እስከ መጨረሻው ታግለናል፤ ወርቅነሽ ብዙ ታግላለች፤ ቆንጆ ነገር ሠርታልኛለች፤›› ብላም አወድሳታለች፡፡ ኬንያውያቱ ጎን ለጎን ሲነጋገሩ መስማቷን ለጥሩነሽ በመንገር መሪነቱን መያዟና ለኢትዮጵያ ወርቅ መትጋቷን የተናገረችው ወርቅነሽ፣ ‹‹ስምንቱን ዙር ይዤ የሄድኩት እነርሱን [ኬንያውያቱን] ለማደንዘዝ ነው፤›› ብላለች፡፡ ከቤጂንጉ ድርብ ድሏ በላቀ ሁኔታ መደሰቷን ያልሸሸገችው ጥሩነሽ፣ የመጨረሻው ዙር አሯሯጧ የሲዲኒውን የደራርቱ ወርቃማ ድል የማብቂያውን 400 ሜትር አሯሯጥና ጌጤ ዋሚን በሁለተኛነት በርቀት አስከትላ የገባችበትን ሁነት ያስታወሰ ነው፡፡ ወርቁን ቋምጣ የነበረችው ቼሩዮት በነሐስ ሜዳሊያ ስትወሰን ሳሊ ኪፕዬጎ ብሯን በማጥለቅ የመጀመርያዎቹን የኦሊምፒክ ሜዳሊያዎች አጣጥመዋል፡፡ ሦስተኛዋ ኬንያዊት ጆይስ ዌሊንግስ የውድድሩን ክረት መቋቋም ባለመቻሏ አቋርጣ ወጥታለች፡፡ 
ወርቅነሽን ተከትላ በአምስተኝነት የገባችው በላይነሽ ኦልጂራ ስትሆን፣ ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ የቱርክ ሯጭ ሽታዬ እሸቴ በስድስተኛነት አጠናቃለች፡፡ ያስመዘገበችው 30 ደቂቃ 47.25 ሰከንድ የቱርክ ብሔራዊ ሪከርድ ሆኖላታል፡፡ የኦሊምፒክን 10,000 ሜትር ክብረ ወሰን በ29 ደቂቃ 54.66 ሰከንድ እስካሁን የያዘችው ጥሩነሽ የኦሊምፒክ 10,000  ሜትርን ሁለት ጊዜ በማሸነፏም ከአክስቷ የባርሴሎናና የሲዲኒ ኦሊምፒክ አሸናፊዋ ደራርቱ ቱሉ ጋር እኩል ባለታሪክ ሆናለች፡፡ ለየት የሚያደርጋት ግን አከታትላ ማሸነፏ ነው፡፡  መሠረት ደፋር ወርቅ ባጠለቀችበት የአቴንስ ኦሊምፒክ በ5,000 ሜትር ነሐስ ያገኘችው ጥሩነሽ፣ በለንደኑ በ5,000 ሜትር በተጠባባቂነት ብትያዝም በርቀቱ ለመሮጥ ዝግጁ መሆኗንና ለመወዳደር ግን ውሳኔው የአሠልጣኞቿ መሆኑንም ተናግራለች፡፡
በታላቅ ጥንካሬ ውድድሩን ስታከርና ተወዳዳሪዎችን ስታስጨንቅ የነበረችውና በቡድን ሥራ ውጤታማነቷ ጎልታ የምትታወቀው ወርቅነሽ ኪዳኔ ከስምንት ዓመት በፊት በአቴንስ 10,000 ሜትር ተመሳሳይ ጥረት አድርጋ አራተኛ መውጣቷና እጅጋየሁ ዲባባና ደራርቱ ቱሉ ሁለተኛና ሦስተኛ ሆነው ብርና ነሐስ ማግኘታቸው ይታወሳል፡፡
የሴቶች 10,000 ሜትር ሩጫ በኦሊምፒክ የተካተተው በሴዑል ኦሊምፒክ እ.ኤ.አ በ1988 ሲሆን፣ እስከ ዘንድሮው የለንደን ኦሊምፒክ ሰባት ጊዜ ተካሂዶ ኢትዮጵያ አራቱን አሸንፋለች፡፡ በሴቶች 10,000 ውድድር የተገኙት ሜዳሊያዎች ብዛትም አራት ወርቅ፣ ሁለት ብርና ሁለት ነሐስ ሆነውላታል፡፡No comments:

Post a Comment