በሔኖክ ያሬድ፣ነሐሴ 6 ቀን 2004
“የአምስት ዓመት ልጄን በስልክ አግኝቻት ነበር፡፡
እርሷም ‹ማሚ እባክሽ የወርቅ ሜዳሊያውያን አሸንፊ› ስትል ጠየቀችኝ፡፡ ቃል ገብቼላት ነበር፤ ቃሏን በመጠበቄ ኮርቻለሁ በቃ፣ ዛሬ
እንደገና የተወለድሁ ያህል ከፍተኛ ደስታ ተሰምቶኛል፤” ይህን ቃል መሠረት ደፋር ከ2004 የአቴንስ ኦሊምፒክ በኋላ ሁለተኛውን
የኦሊምፒክ ወርቅ በ5‚000 ሜትር ለንደን ላይ ካሸነፈች በኋላ ለዜና ሰዎች የተናገረችው ነው፡፡ ከፍተኛ ፉክክር የነበረበትን ውድድር
ተቀናቃኟን ኬንያዊት ቪቪያን ቼሪዮትንና የቤጂንግ ኦሊምፒክ አሸናፊዋና የዘንድሮው የ10‚000 ሜትር ባለወርቅ ጥሩነሽ ዲባባን አስከትላ
በ15 ደቂቃ 04.25 ሰከንድ በሆነ ጊዜ በማሸነፍ የወርቅ ሜዳሊያውን አግኝታለች፡፡
ዛሬ መጠናቀቂያው ላይ የደረሰው 30ኛው የለንደን
ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ ሴት አትሌቶችን አይበገሬነት አሳይቷል፡፡ በ56 ዓመት ታሪክ ውስጥ በአንድ ኦሊምፒክ ሦስት ሴት አትሌቶች ሦስት
ወርቅ በማግኘት ታሪክ ሠርተው ድሉን አድምቀውታል፡፡ ሦስተኛውን ወርቅ ባለፈው ዓርብ ምሽት በ5‚000 ሜትር በኢትዮጵያውያትና በኬንያውያት
መካከል በነበረው ከፍተኛ ፉክክር ድሉን የጨበጠችው መሠረት ደፋር ናት፡፡
መሠረት ደፋር በኦሊምፒክ 5‚000 ሜትር ሁለት
የወርቅ ሜዳሊያዎችና አንድ ነሐስን ጨምሮ ሦስት ሜዳሊያዎችን በማግኘት ብቸኛዋ አትሌት ሆናለች፡፡ ደራርቱ ቱሉም በተመሳሳይ በ10‚000
ሜትር በባርሴሎናና በሲዲኒ ኦሊምፒኮች ሁለት የወርቅና በአቴንስ ኦሊምፒክ አንድ የነሐስ ሜዳሊያዎች አግኝታለች፡፡
“ሁለተኛውን ወርቅ ከስምንት ዓመት በኋላ ማግኘቴ
ልዩ እመርታ ነው፤ ዛሬ ዳግም እንደተወለድኩ ነው የምቆጥረው፤” ያለችው መሠረት፣ የድሉን መስመር አልፋ እንደገባች ከጉያዋ ውስጥ
ድንግል ማርያም ከልጇ ጋር ያለችበትን ምስል እያሳየች ስትስም ታይታለች፡፡ “ድሉን ዛሬ ስለሰጠኝ እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ፤ እጅግ
በጣም ተደስቻለሁ፣ ይህ ለእኔ ታላቅ ነው፤” ማለቷን የኢንተርናሽናል አትሌቲክስ ፌዴሬሽኖች ማኅበር ድረ ገጽ አስፍሯል፡፡
ዝግ ብሎ የተጀመረውን የ5,000 ሜትር ሩጫ
ብሪታንያዊቷና ጣሊያናዊቷ የመጀመርያውን ሦስት ሺሕ ሜትር እየተፈራረቁ የመሩት ቢሆንም አልዘለቁበትም፡፡ ኬንያውያቷ ቼሪዮት፣ ኪፒዮጎና
ኪሲዎት ወደፊት ማምራት መጀመራቸውን ያስተዋለችው ጥሩነሽ ቀዳሚነቱን ይዛ ዙሩን ስታከረው መሠረትም ተከትላታለች፡፡ አራቱን ዙር
ያፈጠነችው ጥሩነሽ ለኢትዮጵያ ስኬት በሩን ከፍታለች፡፡ 100 ሜትር ላይ ማለፍ የጀመረችው መሠረት በድንቅ አፈጻጸም አንደኛ ስትሆን
ሦስተኛ ላይ የነበረችው ኬንያዊቷ ቼሩዮት ጥሩነሽን አልፋ ሁለተኛ ሆናለች፡፡
ውድድሩ የምሥራቅ አፍሪካውያት የበላይነት የታየበትና
ሦስት ኢትዮጵያውያትና ሦስት ኬንያውያት ተፈራርቀው የገቡበት ነው፡፡ የመሠረት ድል የኢትዮጵያን የኦሊምፒክ 5‚000 ሜትር የበላይነት
ለ12 ዓመታት እንዲዘልቅ ያደረገ ነው፡፡ በ10‚000 ሜትር ሩጫ በወርቅነሽ ኪዳኔ የታየው የቡድን ሥራ በ5‚000 ሜትር ላይ በጥሩነሽ
ዲባባ መቀጠሉ ታይቷል፡፡ “400 ሜትር ከቀረ ቼሪዮት አስቸጋሪ ነች፡፡ እንዳታመልጠን አራት ዙር ሲቀረው ወጣሁ፤” በማለት ለዜና
ሰዎች የተናገረችው ጥሩነሽ፣ “ወርቁን እኔም አገኘሁት መሠረት ዋናው ለአገር መሆኑ ነው፤” ብላለች፡፡
በ5‚000 ሜትር በተጠባባቂነት ተይዛ የነበረችው
ጥሩነሽ በርቀቱ እንደምትወዳደር በተነገረ ጊዜ እንደ ቤጂንጉ ሁሉ ድርብ ድልን ታስመዘግባለች የሚሉ ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም፡፡
ዓርብ ምሽት ውድድሩ ሊያበቃ 100 ሜትር አካባቢ እስከቀረውና መሠረት እስካለፈቻት ድረስ ትመራ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ሦስተኛውን ወርቅ
በመሠረት በኩል እንድታገኝ ያከናወነችው የቡድን ሥራ በአስደሳችነቱ ሲወሳ ሌላዋ አትሌት ገለቴ ቡርቃ አምስተኛ ሆናለች፡፡
ለባህሬን የሮጡት ትውልደ ኢትዮጵያውያቱ ሽታዬ
እሸቴና ጠጂቱ ዳባ 10ኛ እና 12ኛ ሆነው አጠናቀዋል፡፡ መሠረት የድሉን መስመር እንዳለፈች የተፈጠረባት ደስታ ሲቃና እንባ የተሞላ
ነበር፡፡ ከቤጂንግ በኋላ የዓመታት ጥረቷ ለወርቅ በመብቃቱ እፎይታን ፈጥሮላታል፡፡ በሦስት ኦሊምፒያዶች ሦስት ሜዳሊያዎች ያገኘችውና
እ.ኤ.አ በ2007 የዓለም ምርጥ አትሌት ተብላ የተመረጠችው መሠረት ወደፊት ማራቶን ለመሮጥ ሐሳቡ አላት፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት
ፊላዴልቪያ ላይ ግማሽ ማራቶን ሩጣ በ67 ደቂቃ 45 ሰከንድ ማጠናቀቋ ይታወሳል፡፡
የሴቶች 5‚000 ሜትር ለመጀመርያ ጊዜ ለውድድር
የቀረበው በአትላንታ ኦሊምፒክ (1996) ሲሆን፣ በወቅቱ ያሸነፈችው ቻይናዊቷ ዋንግ ጁኒያ ስትሆን ኬንያዊቷ ፓውሊን ኮንጋ ሁለተኛ
ወጥታ ነበር፡፡ ኢትዮጵያን በ5‚000 ሜትር የመጀመሪያ የሜዳሊያ ባለቤት ያደረገችው ሲድኒ ኦሊምፒክ (2000) የተካፈለችው ጌጤ
ዋሚ ስትሆን ሦስተኛ ወጥታ ነሐስ አግኝታለች፡፡ አየለች ወርቁና ወርቅነሽ ኪዳኔ አራተኛና ሰባተኛ ሆነው ማጠናቀቃቸው ይታወሳል፡፡
ከመሠረት ወርቃማ ድል ግማሽ ሰዓት በኋላ በተካሔደው
የሴቶች 1‚500 ሜትር ፍፃሜ በከፍተኛ ደረጃ ለወርቅ ተጠብቃ የነበረችው አበባ አረጋዊ ባልተገመተ ሁኔታ አምስተኛ ሆና አጠናቃለች፡፡
ከሦስት ዓመት ወዲህ የተከሰተችውና በዳይመንድ ሊግ በርቀቱ እየመራች ያለችው አበባ፣ የመጀመርያውንና የግማሽ ፍፃሜ ማጣርያዎችን
በብቃት በአንደኛነት ማሸነፏ ብዙዎች ድሉን ለእርሷ ሰጥተው ነበር፡፡ ቢያንስ ከሜዳሊያው ተርታ እንደማትርቅም ገምተው ነበር፡፡ መሐመድ
አማን በ800 ሜትር ያጋጠመውን ዓይነት ሽንፈት አስተናግዳለች፡፡ ከመነሻው መጨረሻ ላይ የነበረችው አበባ ወደ መሀል ስትገባ መደነቃቀፉ
የፈጠረባት ጫና በውጤቷ ላይ ተፅዕኖ ማሳደሩ አልቀረም፡፡ ከልምድ ማነስ፣ መውጣት በሚገባት ጊዜ ያለመውጣትና በሥነ ልቦና አለመዘጋጀት
ከሥልጠና ችግር የመጣ መሆኑ ለውጤቱ መጥፋት እንደምክንያት እየተቆጠረ ነው፡፡ ውድድሩን ቱርካዊቱ አልሲ ካኪር አልናቴኪን በ4 ደቂቃ
10፡23 ሰከንድ ስታሸንፍ፣ ሌላዋ የአገሯ ዜጋ ጋምዜ ቡሉት ሁለተኛ፣ ለባህሬን የሮጠችው ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ መርያም ዩሱፍ ጀማል
ደግሞ ሦስተኛ ሆናለች፡፡ ትናንትና ምሽት የወንዶች 5‚000 ሜትር ሩጫ የተካሄደ ሲሆን፣ ማተሚያ ቤት ቀድመን በመግባታችን ውጤቱን
አልያዝንም እንጂ ኢትዮጵያ በወጣቶቹ ደጀን ገብረ መስቀል፣ ሐጎስ ገብረ ሕይወትና የኔው አላምረው ተወክላለች፡፡ ሐምሌ 20 ቀን
የተጀመረው 30ኛው ኦሊምፒያድ ከ17 ቀናት በኋላ የሚያከትመው ዛሬ ከእኩለ ቀን በኋላ በሚደረገው የማራቶን ውድድር ይሆናል፡፡
በወንዶች ማራቶን የወርቅ ሜዳሊያ ካገኘች ሁለት
ኦሊምፒያዶች ያሳለፈችው ኢትዮጵያ የአበበ ቢቂላን፣ የማሞ ወልዴን፣ የገዛኸኝ አበራን ድል የሚያስቀጥልላት አትሌት ከዲኖ ስፍር፣
ከአየለ አብሽሮና ከጌቱ ፈለቀ መካከል ማን ይሆን? ኢትዮጵያ እስከ ትናንት ድረስ በጥሩነሽ ዲባባ ወርቅና ነሐስ፣ በቲኪ ገላና ወርቅ፣
በመሠረት ደፋር ወርቅ፣ በሶፍያ አሰፋና በታሪኩ በቀለ ነሐሶች 22ኛ ደረጃ ላይ ትገኝ ነበር፡፡
No comments:
Post a Comment