Thursday, July 28, 2016

የኦሊምፒክ ቅብብሎሽ ከሜልቦርን እስከ ለንደን


በደረጀ ጠገናው
            ከዓለም ሕዝብ በበለጠ ራሷ ለንደን የጓጓችለትና ፍንክንክ እያለችበት ስትጠብቀው የቆየችው የ2012 ለንደን ኦሊምፒክ ሊጀመር ስድስት ቀን ቀርቶታል፡፡ ሰባት ቢሊዮን ዶላር ወጪ እንደተደረገለት በሚነገርለት የለንደን ኦሊምፒክ ዝግጅት ከሚታደሙ የዓለም ስፖርት ቤተሰቦች መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ናት፡፡
የኢትዮጵያን በኦሊምፒክ ጌምስ ተሳትፎ አስመልክቶ የተፃፉ መዛግብት እንደሚያስረዱት፣ ስምንተኛው የኦሊምፒክ ጌምስ እ.ኤ.አ. 1924 በፓሪስ ሲካሔድ በአጋጣሚ ተገኝተው የነበሩት፣ ልዑል አልጋ ወራሽ ራስ ተፈሪ መኮንን አውሮፖን ይጐበኙ ስለነበር የወቅቱ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ (አይኦሲ) ፕሬዚዳንት ፒየር ዴ ኩበርቲን አልጋ ወራሹን በክብር እንግድነት በበዓሉ ላይ እንዲገኙ ይጋብዟቸዋል፡፡
አልጋ ወራሹም በተገኙበት የክብር እንግድነት በዓል ላይ በውድድሮቹ ድምቀት እጅግ ይማርካሉ፡፡ አስከትለውም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አባል አገር የምትሆንበትን ቅድመ ሁኔታ ከኩበርቲን ጋር ውይይት ያደርጋሉ፡፡ የፕሬዚዳንቱ ምኞትና ፍላጐት በመላው ዓለም ማስፋፋት ስለነበር የአልጋ ወራሹን ሐሳብ በደስታ መቀበላቸውንና ከዚያም አልጋ ወራሹ ወደ ኢትዮጵያ እንደተመለሱ አገሪቱ እ.ኤ.አ. በ1928 በሚካሔደው በ9ኛው የአምስተርዳም ኦሊምፒክ ጌምስ ላይ እንድትሳተፍ ጥያቄ ቢያቀርቡም ኩበርቲንን የተኩት ቤልጀማዊው ሄነሪ ኢትዮጵያ የአባልነት መስፈርቱን አታሟላም በማለት ጥያቄዎቿን ውድቅ ያደርጉባታል፡፡
መስፈርቶቹ ብሔራዊ የኦሊምፒክ ኮሚቴን ምርጫ ማካሔድ፣ ከዚያም ቢያንስ፣ ቢያንስ አምስት አገር አቀፍ ፌዴሬሽኖችን በመመስረት የዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን አባል መሆን የሚሉት ይጠቀሳሉ፡፡ አልጋ ወራሹ በወቅቱ የተጠየቁት ቅድመ ሁኔታ ለማሟላት ሲሉ የኢትዮጵያ ስፖርት ኮንፌዴሬሽንን በነጋሪት ጋዜጣ ጥቅምት 1941 ዓ.ም. እንዲቋቋም አድርገው የቦርድ አባላቱ ደግሞ በግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ እንዲሰየም ያደርጋሉ፡፡ ቀጥሎም በአገሪቱ በመስፋፋት ላይ ከነበሩት ስፖርቶች እግር ኳስ፣ አትሌቲክስ፣ ቦክስ፣ ብስክሌትና ቅርጫት ኳስ ፌዴሬሽኖች ተመስርተው የዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን አባል እንዲሆኑ ጥረቱ ይቀጥላል፡፡
ይህም ሆኖ ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ፌዴሬሽን አባል ለመሆን ፈተናው ቀላል እንዳልነበረ የሚያስረዳው መረጃው፣ በግሪክ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ድጋፍ ተደርጎለት አገሪቱ ኢትዮጵያ የራሷን ኦሊምፒክ ኮሚቴ እስክታቋቁም የኢትዮጵያ ስፖርት ኮንፌዴሬሽን የአይኦሲ አባል እንዲሆን ጥያቄ ቀርቦ ምንም እንኳ የተሟላ መስፈርት ባይሆንም በልዩ አስተያየት ኢትዮጵያ በ1948 ዓ.ም. በአባልነት መመዝገቧ እውን ሆነ፡፡
ኮንፌዴሬሽኑ የበጀት እጥረት የሙያተኛና የጽሕፈት ቤት ችግር የወቅቱ ሁለተኛ ፈተና የነበረ ቢሆንም፣ ነገር ግን እ.ኤ.አ. በ1956 እና በ1960 በተካሔዱት ኦሊምፒክ ጌሞች የመሳተፍ ዕድል ገጥሟታል፡፡ ከዚያም ሐምሌ 8 ቀን 1960 ዓ.ም. የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ተወካዮች በመሰብሰብ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መቋቋሚያና መተዳደሪያ ደንብ ተዘጋጀ፡፡ ሐምሌ 10 ቀን 1960 ዓ.ም. የኮንፌዴሬሽኑ ቦርድ የቀረበለትን በማሻሻል አፀደቀ፡፡
ሐምሌ 12 ቀን 1960 ዓ.ም. የብሔራዊ ፌዴሬሽኖች ተወካዮች ባደረጉት ስብሰባ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባላት ተመርጠው ሐምሌ 21 ቀን 1960 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ መተዳደርያ ደንብና የተመራጮች ዝርዝር ለአይኦሲ ተልኮ ተቀባይነትን አገኘ፡፡ የመጀመርያው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ፕሬዚዳንት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ ሲሆኑ ዋና ፀሐፊው ደግሞ አቶ ፍቅሩ ኪዳኔ እንደነበሩ መዛግብቱ ያስረዳል፡፡
ኢትዮጵያ ከሜልቦርን ኦሊምፒክ ጌምስ ጀምሮ እስከ ቤጂንግ ድረስ በተካሄዱት ኦሊምፒኮች ከ1976ቱ ሞንትሪያል፣ ከ1984ቱ ሎስ አንጀለስና ከ1988ቱ ሴኡል ኦሊምፒኮች በቀር በሁሉም ተወዳድራለች፡፡ በሦስቱ ኦሊምፒያዶች ያልተሳተፈችበት ምክንያትም  አገሪቱ በምትከተለው ርዕዮት ዓለም የተነሳ እንደነበርም መዛግብቱ ያስረዳሉ፡፡
የድል ቅብብሎሽ 
ሻምበል አበበ ቢቂላ እ.ኤ.አ. በ1960 በሮም በተደረገው ኦሊምፒክ ጌምስ በባዶ እግሩ ማራቶን ሮጦ ርቀቱን በ2 ሰዓት፣ 15 ደቂቃ 16 ሰኮንድ አጠናቆ ለጥቁር ሕዝቦች የመጀመሪያውን ድል አበሰረ፡፡ ከአራት ዓመት በኋላ ቶኪዮ ላይ አበበ አይበገሬነቱን ማራቶንን 2 ሰዓት 12 ደቂቃ ከ11 ሰከንድ አጠናቆ ለሁለተኛ ጊዜ ባለድልነቱን አረጋገጠ፡፡ የአትሌቱን አርአያ በመከተል ማሞ ወልዴ በሜክሲኮና ሙኒክ የወርቅ፣ብርና ነሐስ ተሸላሚ በመሆን የአበበን ጣፋጭ ድል አስከብሯል፡፡ የሁለቱን ጀግኖች ፈለግ የተከተለው “ማርሽቀያሪው” በሚል ቅፅል ስም የሚጠራው የአየር ኃይል ሻምበል ምሩፅ ይፍጠር በሙኒክ በ10 ሺሕ ነሐስ፣ በሞስኮ  በ10 ሺሕና 5 ሺሕ ሜትር ሁለት ወርቅ  በማስመዝገብ የድሉን ቅብብሎሽ አጠናከረው፡፡ መሐመድ ከድር በሞስኮ 10 ሺሕ ነሐስ፣ ሻምበል እሸቱ ቱራ በተመሳሳይ በሦስት ሺሕ ሜትር መሰናክል የነሐስ ሜዳሊያ ያስመዘገቡ የወቅቱ ጀግኖች ብቅ ያሉበትም ይጠቀሳል፡፡
ኮሎኔል ደራርቱ ቱሉ በባርሴሎናና ሲድኒ ኦሊምፒክ በ10ሺሕ ሜትር ወርቅና በአቴንስ ደግሞ የነሐስ ሜዳልያ በማስመዝገብ ለአፍሪካውያት ፋና ወጊ ሆና ዛሬም ድረስ ከሚወደሱት ትጠቀሳለች፡፡ እንዲሁም አዲስ አበበ በባርሴሎና ኦሊምፒክ በ10ሺሕ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ከማግኘቱ በተጨማሪ በአፍሪካና አውሮፓ በተደረጉ ታላላቅ ዓለም አቀፍ ውድድሮች በርካታ ድሎችን ተጐናፅፏል፡፡ ፊጣ ባይሳ በባርሴሎና ኦሊምፒክ በአምስት ሺሕ ሜትር የነሐስ ሜዳሊያ ያስመዘገበበት ላይዘነጋ ማለት ነው፡፡
ከ26 በላይ ክብረ ወሰኖችን በመሰባበርና አሁንም ድረስ እየሮጠ የሚገኘው  ኃይሌ ገብረ ሥላሴ በአትላንታና ሲድኒ ኦሊምፒክ ወርቅ፣ ፋጡማ ሮባ በማራቶን ወርቅ፣ አትሌት ጌጤ ዋሚ በ10 ሺሕ ሜትር ነሐስ፣ እንደገና በሲድኒ ኦሊምፒክ በ10ሺሕ ሜትር ብር፣ በአምስት ሺሕ ሜትር ደግሞ የነሐስ፣ ሜዳልያ ያስመዘገቡበት ትውልድ ላይ ደርሰናል፡፡
ሚሊዮን ወልዴ በሲዲኒ ኦሊምፒክ በአምስት ሺሕ ሜትር የወርቅ፣ እንዲሁም በማራቶን ገዛኸኝ አበራ የወርቅ፣ ተስፋዬ ቶላ ደግሞ የነሐስ አሰፋ መዝገቡ በ10ሺሕ ሜትር ነሐስ በማስመዝገብ ታሪክ የሚዘክራቸው ናቸው፡፡
የድሉ ቅብብሎሽ አልቆመም፡፡ ከሳምንት በኋላ በሚጀመረው ለንደን ኦሊምፒክ በ10ሺሕ ሜትር ከሚጠበቁት ጀግኖች አንዱ ነው፡፡ እንደ ኃይሌ ሁሉ እስከ አሁን ወደ 18 የሚጠጉ ክብረወሰኖችን ሰብሯል፡፡ በአቴንስ ኦሊምፒክ በ10ሺሕ ወርቅ፣ በአምስት ሺሕ ብር እንዲሁም በቤጂንግ አሊምፒክ በሁለቱም ርቀቶች የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት የሆነው  ቀነኒሳ በቀለ ነው፡፡  ፈረንጆቹ “ዘሲልቨር ማን” ሲሉ የሚጠሩት ሌላው አትሌት ስለሽ ስሕን ምንም እንኳ ለለንደን ኦሊምፒክ ባይሳካለትም በአቴንስ ኦሊምፒክ በ10ሺሕ ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤት ነው፡፡ እጅጋየሁ ዲባባ በተመሳሳይ የ10ሺሕ ሜትር የብር ሜዳሊያ ባለቤት ሆና የድሉ አድማቂዎችን ትቀላቀላለች፡፡
በርካታ የስፖርት ቤተሰቦች በ2012 ለንደን ኦሊምፒክ ላይ ከሚጠብቋቸው አትሌቶች ጥሩነሽ ዲባባና መሠረት ደፋር ግንባር ቀደም ናቸው፣ ሁለቱ፣ መሠረት በአቴንስ ኦሊምፒክ በአምስት ሺሕ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ስትሆን ጥሩነሸ ደግሞ የነሐስ ሜዳሊያ አስመዝግባለች፡፡ በቤጂንግ ኦሊምፒክ ደግሞ ጥሩነሽ ዲባባ በ10 እና 5 ሺሕ ሜትር የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት መሆን የቻለች ናት፡፡ መሠረት በበኩሏ በአምስት ሺሕ የነሐስ ሜዳሊያ ባለቤት ነበረች፡፡
የለንደን ኦሊምፒክ ዝግጅት
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ 33 አትሌቶችን ከመካከለኛው ርቀት እስከ ማራቶን እንዲሁም በሚኒማ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መስፈርት በውኃ ዋና አንድ ወንድና አንድ ሴት አትሌቶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 35 አትሌቶች ከ18 የልኡካን አባላት ጋር በለንደን ኦሊምፒክ እንደሚገኙ ይፋ አድርጓል፡፡
ኮሚቴው ባለፈው ሐሙስ ምሽት  በአዲስ አበባ ሒልተን ባደረገው የገቢ ማሰባሰቢያና የሽኝት ሥነ ሥርዓት ለለንደኑ ኦሊምፒክ ልኡክ ውጪና ተያያዥ ሥራዎች 46 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ አሰባስቧል፡፡ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ 14 ሚሊዮን ብር በአጭር የጽሑፍ መልእክት ከሚላኩ የሎተሪ እድሎች የተገኘ መሆኑም ተመልክቷል፡፡
የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን መሪ ኢንጂነር ግርማ ዘውዴ በ2012 ለንደን ኦሊምፒክ፣ አገሪቱ በአምስት የስፖርት ዓይነቶች ማለትም በአትሌቲክስ፣ በውኃ ዋና፣ በቦክስ፣ በሴቶች እግር ኳስና በቴኳንዶ ለመሳተፍ እቅድ እንደነበራት፣ ይሁንና ለተሳትፎ የሚያበቃው መስፈርት ሊሟላ ባለመቻሉ በአትሌቲክስና ውኃ ዋና ብቻ ለመሳተፍ ተገደናል ይላሉ፡፡
የአትሌቲክሱንና ውኃ ዋናውን ዝግጅት በተመለከተ ኃላፊው፣ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና ከስፖርት ኮሚሽን ጋር ጥምረት በመፍጠር ከስልጠና ጀምሮ አትሌቶች ሚኒማ ማሟላት ይችሉ ዘንድ አስፈላጊውን የፋይናንስ ድጋፍ መደረጉን ጭምር ተናግረዋል፡፡
በአቴንስና ቤጂንግ ኦሊምፒክ የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ቡድን የቡድን መሪ የነበሩትና የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ የሥራ አስኪያጅ ኮሚቴ አባል አቶ ገበያው ታከለ በበኩላቸው፣ የ2012 ለንደን ኦሊምፒክ በሚጀመርበት ወቅትና እስከ ፍፃሜው ይኖራል ተብሎ የሚገመተውን የአየር ሁኔታ አስመልክቶ ዝቅተኛው 13 ከፍተኛው 22 ዲግሪ ሴንቲግሬድ ሊሆን እንደሚችል፣ የእርጥበቱ መጠን ደግሞ 75 ዲግሪ ሴንቲ ግሬድ ድረስ እንደሚገመት ያስረዳሉ፡፡
ከዚህ አንፃር በአዲስ አበባና አካባቢዋ ዝግጅታቸውን አድርገው ወደ ለንደን ለሚሔዱት ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የለንደን አየር ተስማሚ ሊሆን እንደሚችል  ኃላፊው ይናገራሉ፡፡ ከውጤት አንፃርም ቢሆን እስከ አሁን ከተመዘገበው ውጤት የተሻለ እንደሚመዘገብ ጭምር ግምታቸውን ሰጥተዋል፡፡

No comments:

Post a Comment