23 Jul, 2016
 ሔኖክ ያሬድ's blog
‹‹ጥበበኛ በጥበብ እግር ይመላለሳል›› (ጠቢብ የሐውር በእግር ጥበብ) እንዲሉ፣ አባተ መኩሪያ ከግማሽ ምታመት በዘለለ በኢትዮጵያ ቴአትር ሕዋ ውስጥ በጥበብ ለጥበብ ኖሯል፡፡ ለቴአትር እስትንፋሱ ነበርም ይሉታል፡፡ በርሱ ጥበብ ያለፉት ሁሉ፡፡
በጥበብ የባተው አዘጋጅ፣ የውዝዋዜ አሠልጣኝ (ኬሪዮግራፈር)፣ ጸሐፌ ተውኔት፣ የፊልም አዘጋጅ የነበረው አባተ መኩሪያ በአገሪቱ የቴአትር ታሪክ ውስጥ ስማቸው በግዘፍ ከሚነሱትና አሻራቸውን ካሳረፉ በኩሮች አንዱ ነበር፡፡ በተለይ በተውኔት አዘጋጅነት ስመ ጥር ለመሆኑ ዘመን ተሻጋሪ ተውኔቶችን ወጥ እና ትርጉሞች በማዘጋጀቱ ይጠቀሳል፡፡
ከታዋቂ ሥራዎቹ መካከል ሀሁ በስድስት ወር (1966) አቡጊዳ ቀይሶ (1971)፣ መልእክተ ወዛደር (1971)፣ የመንታ እናት (1971)፣ መቅድም (1972)፣ ጋሞ (1973)፣ አሉላ አባነጋ (1979) ይጠቀሳሉ፡፡ በተለይ በ19ኛው ምታመት አሐዳዊት ኢትዮጵያን እውን ባደረጉት ዳግማዊ አፄ ቴዎድሮስ ላይ የተመሠረተው የጸሐፌ ተውኔት ጸጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹ቴዎድሮስ›› ነውን ከነበር ጋር ያስተሳሰረበት አዘገጃጀቱ፣ የንጉሠ ነገሥቱን ቴዎድሮስ ልዕልና ያንፀባረቀበት ነበር፡፡
ብዙዎቹ አባተ ያዘጋጃቸው ተውኔቶች በሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን የተደረሱ ሲሆኑ ረዣዥም ቃለ ተውኔት፣ ታሪክ ጠቃሽ ዘይቤዎችን ያዘሉ ናቸው፡፡ የአባተ ክሂል የተንፀባረቀውም እነዚያን ረዣዥም ቃለ ተውኔቶች (መነባነቦች) ተደራሲን በሚይዝ መልኩ እንዲመደረኩ በማድረጉ ነበር፡፡ እንደ አዘጋጅነቱም የድራማን ሥነ ጽሑፍ በምሁራዊ ዓይን አይቶ ማዳበሩን ተክኖታል፡፡
በዎርልድ ኢንሳይክሎፒዲያ ኦፍ ኮንቴምፖራሪ ቴአትር እንደተገለጸው፣ አባተ ተውኔት ተመልካቹን በግሩም ሁኔታ መቆጣጠር የሚያስችል ክሂል ነበረው፡፡ በጸጋዬ የተተረጐሙት የዊልያም ሼክስፒር ማክቤዝ፣ ኦቴሎና ሐምሌት በታዳሚው ትውስታ ውስጥ የቃለ ተውኔቱ (ግጥም) ውበት ብቻ ሳይሆን፣ ተውኔታዊ ክዋኔዎች እንዲታወሱ የሆነው በአባተ መኩሪያ አዘገጃጅ ስምረት መሆኑን ኢንሳይክሎፒዲያው አስነብቧል፡፡
ከመንግሥቱ ለማ ታዋቂ ሥራዎች አንዱ የሆነው ‹‹ያላቻ ጋብቻ›› የአባተ አዘጋጅነት እጅ አርፎበታል፡፡ አባተ ከሚታወቅባቸው የመድረክ ተውኔቶች ባሻገር በአደባባይ ላይ ባዘጋጃቸው (ከአዳራሽ ውጭ) ተውኔቶቹም ይወሳል፡፡ ‹‹ኤዲፐስ ንጉሥ›› ተውኔትን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ራስ መኰንን አዳራሽ ፊት ለፊት በሚገኘውና በዘልማድ ‹‹ኪሲንግ ፑል›› በሚባለው ወለል ላይ ያሳየው ይጠቀሳል፡፡ ሐቻምና በኢትዮጵያ የተውኔት ታሪክ ከቀዳሚዎቹ ተርታ የሚሰለፈው የቀኝ ጌታ ዮፍታሔ ንጉሤ ‹‹አፋጀሽኝ›› ዳግም የመድረክ ብርሃን ያየው በአባተ መኩሪያ ነበር፡፡
አባተ ከአዘጋጅነቱ ሌላ በጸሐፌ ተውኔትነቱም ይታወቃል፡፡ ራሱ ደርሶ ራሱ ያዘጋጀው ‹‹የሊስትሮ ኦፔራ›› (1982) በወቅታዊ ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ የተመሠረተ በሙዚቃ የታጀበ ሥራው ነበር፡፡ ዓለም አቀፍ ሽልማትም አግኝቶበታል፡፡
በዩኔስኮ አፍሪካዊ ተውኔትን በደብሊን አቤይ ቴአትር እንዲያዘጋጅ የተመረጠው አባተ፣ የጸጋዬ ገብረ መድኅንን “Oda Oak Oracle” (የዋርካው ሥር ንግርት) አዘጋጅቷል፡፡ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ከእንግሊዛዊው ዕውቅ የቴአትር አዘጋጅ ሰር ፒተር ሆል ጋር በኮንቬንት ጋርደን ኦቴሎን ለማዘጋጀት ዕድል አግኝቷል፡፡
መቀመጫውን በታንዛኒያ ያደረገውን የምሥራቅ አፍሪካ ቴአትር ኢንስቲትዩት በመሥራች አባልነትና በኃላፊነት ከመምራቱም ባሻገር፣ በአዲስ አበባ የመኩሪያ ቴአትር ስቱዲዮና መዝናኛ የተሰኘ ተቋምን መሥርቶ ‹‹ቴአትር ለልማት›› የሚባለውን የተውኔት አቀራረብ ፈለግ መሠረት በማድረግ ብዙ ትምህርት ሰጪ ተውኔቶችን በማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተመሥርተው በማዘጋጀት ለመድረክ አብቅቷል፡፡ በታሪካዊ መዝገበ ሰብ እንደተመለከተው፣ ለመድረክ ካበቃቸው ተውኔቶች መካከል ሕሊና፣ ጠለፋ፣ ጆሮ ዳባ፣ በሐምሌ ጨረቃ ጉዞ፣ ድንቅ ሴት ሲጠቀሱ ከዘጋቢ ፊልሞችም የፍትሕ ፍለጋ እና የመስከረም ጥቃት ይገኙበታል፡፡
መኩሪያ ስቱዲዮ በየክልሉና በአዲስ አበባ ከተማ ለሚገኙ አማተር ከያንያን የቴአትር፣ የሰርከስና የሙዚቃ ሥልጠና መስጠቱን፣ ከኢትዮጵያ ውጪም ወደ ተለያዩ አገሮች እየተጓዘ ትርኢት ማቅረቡም ይታወቃል፡፡
በየዓመቱ ከሚከበረው የዓድዋ ድል ጋር ተያይዞ አባተ መኩሪያ ከነጥበብ ጓዙ የሚነሳበት አጋጣሚ ከ30 ዓመት በፊት ተፈጥሯል፡፡ የካቲት 23 ቀን 1888 ዓ.ም. በዳግማዊ ምኒልክ ጠቅላይ አዝማችነት፣ በወራሪው የኢጣሊያ ሠራዊት ላይ ኢትዮጵያ የተቀዳጀችው ድል በየዓመቱ ሲዘከር በቴሌቪዥን መስኮት የሚታይ የቅድመ ጦርነት ዝግጅት የቪዲዮ ምሥል የአባተ መኩሪያ ትሩፋት ነው፡፡ አዲስ አበባ ከተማ የተመሠረተችበት 100ኛ ዓመት ኢዮቤልዩ በዓል ሲከበር ለበዓሉ ድምቀት ከተዘጋጁት አንዱ ንጉሠ ነገሥቱ ‹‹ምታ ነጋሪት ክተት ሠራዊት›› ብለው ለዘመቻ ሲነቃነቁ ባለፉበት በባልደራስ አካባቢ በሚገኘው የቀበና ወንዝ ነባር ድልድይ አጠገብ አዲስ የተሠራው ‹‹የዓድዋ ዘመቻ መታሰቢያ ድልድይ›› የተመረቀው የዚያን ዘመን የክተት ስሪት በሚያሳይ መልኩ አምሳያ የተፈጠረላቸው ንጉሠ ነገሥቱን፣ እቴጌይቱን፣ መኳንንቱን፣ የጦር አዝማቾችን፣ ዘማቾቹን፣ ሴቶች አገልግል ተሸክመው ሁሉም እየፎከሩ እየሸለሉ የሚያሳየውን ‹‹የራስ አባተ ጦር እለፍ ተብለሃል…›› ወዘተ እየተባለ በ400 ተሳታፊዎች የቀረበው ክዋኔ ለዘመን ተሻጋሪነት የበቃው በአባተ መኩሪያ ነበር፡፡ አባተ ዓድዋንና ድሉን የሚዘክር ላቅ ያለ ይዘት ያለውን የዓድዋ ፊልም ፕሮጀክትን ከአራት ዓመት በፊት ቢቀርጽም፣ በወቅቱም በ35 ሚሊዮን ብር በጀት ሊሠራ መታቀዱንና ፕሮጀክቱን ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በበላይ ጠባቂነት እንደያዙት ቢነገርም እስካሁን ድምፁ አልተሰማም፡፡
ትምህርትና ኃላፊነት
አባተ በትምህርት ዝግጅቱ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን በእንግሊዝኛና በንኡስ ትምህርት (ማይነር) ድራማን በማጥናት አግኝቷል፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በጀርመን ብሮድካስቲንግ ኢንስቲትዩት በፊልምና ሚዲያ ሲሠለጥን ከለንደን ኦፔራ ሴንተር የኦፔራ ትምህርት፣ በአየርላንድ አቤይ ቴአትርና በአሜሪካ ቴአትርና ሙዚቃ በምሥራቅ አውሮፓና በአፍሪካ አዘገጃጀትን አጥንቷል፡፡ የተለያዩ አገሮች ትምህርታዊ ጉዞም አድርጓል፡፡
በሥራ አገልግሎትም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት (የአሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር) የቴአትር ዳይሬክተር፣ እንዲሁም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ኪነ ጥበባት ወቴአትር (ባህል ማዕከል) ዳይሬክተር ሆኖ ሠርቷል፡፡
በ1950ዎቹ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ‹‹መዝናኛ በክዋኔ ጥበባት›› (Entertainment in Performing Arts) በሚል ርዕስ በየሳምንቱ ዓርብ ለአንድ ዓመት የዘለቀ ፕሮግራም ማዘጋጀቱን፣ ፕሮግራሙም የአዝማሪ ጨዋታ በኢትዮጵያ ሕዝብና በክዋኔ ጥበባት ውስጥ የነበራቸውን ሚና ይዳስስበት ነበር፡፡ የተለያዩ ብሔረሰቦች ባህልን፣ እምነትን፣ ደስታን፣ ሐዘን፣ ወዘተ በጥበብ አንፃር ይታይበት እንደነበር፣ ቤተ ክህነት ለጥበቡ ዕድገት ያደረገችውን አስተዋጽኦ ከታዋቂ የጥበብ ሰዎች ካበረከቱት ሥራ ጋር የሚቀርብበት እንደነበር ገጸ ታሪኩ ያስረዳል፡፡ ለምሳሌ ጸጋዬ ገብረ መድኅን ‹‹የከርሞ ሰው›› የሚለውን የጻፈውና ሙላቱ አስታጥቄ ለከርሞ ሰው ሙዚቃውን የሠራው በዚሁ የአባተ ፕሮግራም ነበር፡፡
አባተ ከብሔራዊ ቴአትር ሌላ በሀገር ፍቅር ቴአትር፣ በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ በአዘጋጅነት፣ በጸሐፌ ተውኔትና መራሔ ተውኔትነት እንዲሁም በኃላፊነት ጭምር አገልግሏል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ ነበር፡፡ ባለፈው ታኅሣሥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባህል ማዕከል ‹‹ዝክረ አባተ መኩሪያ›› ብሎ ባዘጋጀው መድረክ ላይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጥበባት ኮሌጅ ዲን አቶ ነቢዩ ባዬ እንደተናገረው፣ ‹‹አባተ የዩኒቨርሲቲ የቴአትር ትምህርት በትክክለኛው መሠረት ላይ እንዲገኝ የላቀ ሚና ተጫውቷል፡፡ በዩኒቨርሲቲው የኪነ ጥበብ የፈጠራ ማዕከል እንዲቋቋም አሻራውን አኑሯል፡፡ የተለያዩ የቴአትር ንድፈ ሐሳቦችን በማቅረብ ግንባር ቀደም አርቲስት ነው፡፡››
ከዓመታት በፊት የኢትዮጵያን የቴአትር ዕድገትና የተመልካቹን ሁኔታ በተመለከተ አባተ መኩሪያ በአንድ መድረክ የተናገረውን የፋንታሁን እንግዳ ‹‹ታሪካዊ መዝገበ ሰብ›› እንዲህ ገልጾታል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዝብ የራሱን ባህል አትኩሮ የሚያጣጥምና የሚወድ ነው፡፡ ቴአትር ቤቱ ይሞላል፡፡ ግን ከቴአትር አንፃር (ከድርሰቱ) ያየነው እንደሆነ ብዙ የሚተቹ ነገሮች አሉ፡፡ እንደ ቴአትር አዋቂ ተመልካች ቴአትሮቹን ብናያቸው ብዙ ግድፈቶች እናገኛለን፡፡ ተመልካቹ ለዚያ ሁሉ ደንታ የለውም፡፡ የራሱን ሕይወት ማየት ይወዳልና ይመጣል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ጥበቡ ሳይሆን ተመልካቹ ነው የሚፈታተነን፡፡ ደግሞ የኛን አገር ቴአትር እንዳያድግ የገደለው ቴአትር ቤቶች በመንግሥት እጅ መሆናቸው ነው፡፡ ቴአትር ቤቶች አንድ ዓይነት ሥራ ነው የሚሠሩት፡፡››
የአባተ የጥበብ ጉዞ አልጋ በአልጋ አልነበረም፡፡ ውጣ ውረዶችን አይቷል፡፡ ቀዳሚው ፈተና በዩኒቨርሲቲ ትምህርቱን ጐን ለጐን በኪነ ጥበብ ወቴአትር (ክሬቲቭ አርት ሴንተር) በሚሠራበት አጋጣሚ በነበረው የግጥም ጉባኤ ባለቅኔው ዮሐንስ አድማሱ ያቀረበው ‹‹ላም እሳት ወለደች በሬ ቀንድ አወጣ፣ በሥልጣን ሊቅ መሆን ይህም አለ ለካ›› ግጥም በዩኒቨርሲቲው ኃይለኛ ቁጣ በመቀስቀሱ ማዕከሉ ይዘጋል፡፡ አባተን ጨምሮ ሁሉም ባልደረቦች እንዲባረሩ መደረጉ አንዱ ነው፡፡
በየዐረፍተ ዘመኑ በሦስቱ ሥርዓተ መንግሥታት ፈተና አልተለየውም፡፡ ቴአትር ቤቶች መድረክም ነፍገውት ነበር፡፡ የሎሬት ጸጋዬ የተውኔቶች መድበል በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር በተመረቀበትና ቅንጫቢ ትዕይንቶች በቀረቡበት ጊዜ መድረክ እንደሚሰጠው ቢነገርም የውኃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል፡፡
ለዚህም ይመስላል በታኅሣሡ የብሔራዊ ባህል ማዕከል የአክብሮት መድረኩ ላይ አባተ ለተሰጠው ሽልማትና ለደረቡለት ካባ ምስጋናውን ያቀረበው፣ ‹‹እባካችሁ መድረክ ስጡኝ ልሥራበት፡፡ እኔ ሠርቼ አልጠገብኩም፤ ገና ብዙ መሥራት እፈልጋለሁ፤ ስለዚህ እባካችሁ መድረኩን ስጡኝ፤›› ብሎ በመማፀን ነበር፡፡ ሳይሆንለት አዲሱ ትውልድም ነባሩን ብሉዩን (ክላሲክ) የነጸጋዬ ገብረመድኅን ሥራዎችን በአባተ መኩሪያ አጋፋሪነት ሳያይ አመለጠ፡፡
ሰኞ ኅዳር 10 ቀን 1932 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አዋሬ ሠፈር ከአባቱ ከአቶ ስለሺ ማንደፍሮና ከእናቱ ከወ/ሮ ውብነሽ መኩሪያ የተወለደው አባተ መኩሪያ፣ የእናቱ አባት ስምን እንደ አባት የወሰደው አያቱ ‹‹እኔ ነኝ የማሳድገው›› ብለው በስድስት ወሩ ወስደው ስላሳደጉት ነው፡፡ በተወለደ በ76 ዓመቱ ሐምሌ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ያረፈው አባተ በማግሥቱ በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሥርዓተ ቀብሩ ተፈጽሟል፡፡ ከ42 ዓመት በፊት ከወ/ሮ ምሕረት አረጋ ጋር ጎጆ የቀለሰው አባተ ቴዎድሮስና ውቢት የተባሉ ሁለት ልጆቹን ሲያፈራ የልጅ ልጆችም አይቷል፡፡
በዐውደ ምሕረቱ ላይ የሕይወት ታሪኩን ያነበበው ከዕለታት ባንዱ ዕለት ‹‹ራሴን ፈልጌ እንዳገኝ የገራኝ፣ መንገዱን ያሳየኝ፣ የገሰፀኝ፣ ዛሬ ለደረስኩበት ደረጃ ያበቃኝና ያሳደገኝ የጥበብ አባቴ ነው፤›› ያለው ታዋቂው ተዋናይ ፍቃዱ ተክለማርያም ነበር፡፡
እንዲህም አነበበ፤ ሕፃኑ አባተም በአያቱ አባትነት ያድጋል፡፡ አያቱ አባትም ሆነውታልም፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ስማቸው መጠሪያው ሆነ፡፡ እነሆም በተግባር የናኘው የዛሬው ገናን ስም ‹‹አባተ መኩሪያ!›› እንዳባተ እንዳኮራ ዘመናትን ሊሸጋገር በቃ! የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቱን በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት (ኮከበ ጽባሕ) ሲከታተል፣ አቶ መኩሪያ ልጃቸው ነገረ ፈጅ እንዲሆንላቸው ቢፈልጉም አባተ ግን ‹‹በፊደል ነው የተለከፍኩት!›› እንዲል እሱ ያገዘፈው የ‹‹ሀሁ በስድስት ወር››ሩ ገጸ ባሕሪ፣ እሱውም ‹‹በጥበብ ነው የተለከፍኩት!›› ብሎ ጥበብን የሙጥኝ አለ፡፡ ተለክፎም ቀረ! መለከፉም ለመልካም ሆነ፡፡ ተከታታይ የጥበብ ትውልድ ፈጠረ፤ እሱውም በትውልዶች ውስጥ ኖረ፡፡ …ከዚያስ በሰባ ስድስት ዓመቱ… ተንቀሳቃሹ ቴአትር ቤት አረፈ!