በመለስ
ዓ.
ኢትዮጵያ በዓለምአቀፉ መድረኮች ቀና ብላ ከምትሄድባቸው በጣም ውስን ነገሮች አንዱ አትሌቲክስ ነው፡፡
ኢትዮጵያውያን ዘር፣ ሃይማኖት፣ ፖለቲካ፣ ቋንቋ፣ ወዘተ ሳይገድበን አንድ የምንሆንበት ወቅት የአትሌቶቻችን ውጤት ነው፡፡ በተለይም
በረዥምና መካከለኛ ርቀት ሩጫ የሚገኝ ድል ያስፈነድቃል፡፡ ሽንፈቱ ያመናል፡፡ ኦሊምፒክ የዓለም ስፖርተኞች ወንድማማችነታቸውን የሚያሳዩበት
መድረክ የስፖርቱ መርሕ ነው፡፡ ሽንፈቱን ከመላመድ ሕመም ይሻላል፡፡ ለዚህም ነው በየአራት ዓመቱ አንድ ጊዜ ብቅ የሚለውን ኦሊምፒክ
በታላቅ ጉጉት ይጠብቀናል፡፡ ትክክል፡፡ ይሁን እንጂ ለእኛ ሜዳሊያ ከማግኘትም በላይ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ኬንያውያን ለአትሌቲክስ
ትልቅ ትርጉም ነው ያላቸው፡፡ ከለንደን ኦሊምፒክ በትንሹ 20 ሜዳሊያ (10 ወርቅ፣ 6 ብር
እና 4 ነሐስ) ይጠብቃሉ፡፡ ለኬንያ ኦሊምፒክ ኮሚቴ አሁን አሳሳቢ የሆነው አትሌቶች
ካሸነፉ በኊላ ደስታቸውን ሲገልጹ ሀገራቸውን በሚገባ የሚያስተዋውቁ መሆን አለባቸው የሚለው ነው፡፡ በአትሌቲክስና አትሌቶቹ ኢትዮጵያዊ
ብቻ ቀናዒ ነው ብሎ ማሰብ ስህተት ነው፡፡ ኬንያውያንም የሚገርም ክብርና ፍቅር አላቸው፡፡
በቆጂ እና ኢቴን
አፍሪካ በኦሊምፒክ ለመጀመርያ ጊዜ የተሳተፈችው ከ104 ዓመት በፊት
ነበር፡፡ እ.ኤ.አ. 1904 አፍሪካ ለመጀመርያ ጊዜ የተወከለችው በደቡብ አፍሪካ ነበር፡፡ ለዚህም
ምክንያቱ ሌሎች አገሮች ቅኝ አገዛዝ ስር መኖራቸው ነው፡፡ አብዛኞቹ ሀገሮች በራሳቸው ባንዲራ መወዳደር የጀመሩት . 1960ዎቹ ነፃነታቸውን ካገኙ በኊላ ነው፡፡ ድህረ ነፃነት ሁሉም የአፍሪካ አገሮች በኦሊምፒክ ይሳተፉ እንጂ የሜዳሊያ ሰንጠረዥ በመግባት የሚታወቁት ኢትዮጵያ፣ኬንያ፣ናይጄሪያ፣ደቡብ አፍሪካ፣ግብፅና ጋና ናቸው፡፡ በዚህኛውም ኦሊምፒክ ሶማሊያና ደቡብ ሱዳንም (በኦፊሴላዊ ባይሆንም በአንድ የማራቶን ሯጭ በዓለም አቀፍ ኦሊምፒክ ኮሚቴ ባንዲራ ሥር) ቢሳተፉ ሜዳሊያ የሚጠበቀው ከእነዚሁ አገሮች ነው፡፡ በተለይም በመካከለኛና ረዥም ርቀት ዓለም ኬንያና ኢትዮጵያን በጉጉት ይጠብቃል፡፡
የቢቢሲ ሬዲዮ ከቀናት በፊት ታዋቂ የስፖርት ባለሙያዎችን ጋብዞ ሲነጋገርበት የነበረው ጉዳይ ከኢትዮጵያውያን እንዲሁም ኬንያውያን አትሌቶች ስኬት ጀርባ ያለው ምሥጢር ምንድነው? የሚለው ነው ´´ The Asian Age´´ የተሰኘ ድረ ገጽም ባስነበበው ጽሑፍ ለኢትዮጵያና ኬንያ አትሌቶች በኦሊምፒክ ሜዳሊያ ማሸነፍ ሳይሆን የሚከብዳቸው ከምርጦቹ ምርጥ ሆኖ አገራቸውን በመወከል በውድድሩ መሳተፍ ነው ብሏል፡፡ ለሁለቱ ሀገሮች አትሌቶች ውጤታማነት በዋና ምክንያትነት የቀረበው የሚኖሩበት አካባቢና አፈጣጠራቸው (geography and genetics) አብዛኞቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች ከአርሲ የኬንያ ደግሞ ከስምጥ ሸለቆ ኢቴን ነው፡፡ (ከናይሮቢ ደቡብ ትገኛለች) ተራራማ አካባቢ ነው፡፡ አትሌቶቹ የተገኙ ከባሕር ወለል በላይ ከ2000 ሜትር ከፍታ በላይ በመሆኑ ረዥም ርቀት ለመሮጥ የሚያስችላቸው ኦስክጂን ደማቸው ውስጥ እንዲኖር አስችሏቸዋል የሚል ትንተና የቢቢሲም ድረ ገጹ ነው፡፡ የእግራቸው ቅልጥም ረዥምና የሰውነታቸው ክብደት አነስተኛ መሆን፣ ከድህነት ለማምለጥና ዕውቅናን ለማግኘት ሩጫ አቋራጭ መሆኑን ተርከዋል፡፡ ሁለቱም በአገሮቹ እየዳበረ የመጣው የአሸናፊነት የሌላውን ዱካ የመከተል መንፈስ (motivation) አትሌቲክስን እንዲቆጣጠሩት አድርጓቸዋል ሲሉ ይደመድማሉ፡፡ ከዚህ መደምደሚያ የተነሳ ይመስላል እንግሊዛውያኑ ሞ ፋራህና ፓውላ ሪድ ክሊፍ (በ10ሺሕና ማራቶን) በለንደን ድል ያቀዳጀናል ያሉትን ልምምድ ኢቴን ውስጥ አድርገዋል፡፡ የኬንያ አትሌቶችም ናይሮቢና ኢቴን ጠንካራ ልምምድ እያደረጉ ናቸው፡፡ ጥሩ ይዘት ላይ ይገኛሉ፡፡ ለኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች አበበ ቢቂላ በሮም ኦሊምፒክ በማራቶን፣ ኪፕቶጌ ኪኖ በሜክሲኮ ኦሊምፒክ በ1,500 ሜትር ባያሸንፉ ኖሮ የዛሬዎቹ አትሌቶች ከየት ይመጡ ነበር ሲሉ ይጠይቃሉ?
44 ዓመት
ኬንያውያን የኢትዮጵያ አትሌቶችን የራሳቸው ያህል ያውቋቸዋል፡፡ በተለይም ታዋቂው ኃይሌ፣ ቀነኒሳ፣ መሠረት፣ ጥሩነሽ፣ ወዘተ፡፡ በኢትዮጵያውያን ካጋጠማቸው ሽንፈት መካካል በሲዲኒ ኦሊምፒክ ፓል ቴርጋት ከኃይሌ ጋር ተናንቆ ያጣው ወርቅ ይቆጠቁጣቸዋል፡፡ ኬንያውያን በኢትዮጵያ አትሌቶች የበላይነት የተነሳ ለ44 ዓመት በ10 ሺሕ ሜትር ወንዶች ወርቅ አሸንፈው አያውቁም፡፡ ዘንድሮ ይህን የሜዳሊያ ድርቅ እንሰብራለን እያሉ ነው፡፡ ዊልሰን ኪፕሮፕ የተባለውን አትሌት ለውጤት ይጠብቁታል፡፡ ለቀነኒሳ መድኃኒት ነው ይላሉ፡፡ በአምስት ሺሕ ከኢትዮጵያውያን ደጀን ገ/መስቀልን፣ ሐጎስ ገ/ሕይወት ከእንግሊዝ ሞ ፋራህ፣ ከአሜሪካ በርናርድ ላጋት ይፈራሉ፡፡ ኬንያውያን 3000ሜትር መሰናክል ወድድር የላቸውም፡፡ በኦሊምፒክ የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤት ናቸው፡፡ ለ44 ዓመት ወርቅ ከእነርሱ እጅ አልወጣም፡፡ ብዙ ጊዜ ውድድሩ በኬንያውያን አትሌቶች መሀከል ነው፡፡ በለንደንም ይህ ይደገማል ብለው ያምናሉ፡፡ ኢዝቅኤል ኪምቦይ የተባለው የሩጫው አቀጣጣይ ሰሞኑን በወሲብ ቅሌት ተከሶ ፍርድ ቤት ከመቅረቡ ውጭ ማለት ነው፡፡ ሦስቱም ተወዳዳሪዎቻቸው እስከ መጨረሻው ሜትር በቡድን በመሥራት የመጨረሻው 600 ርቀት ላይ የራሳቸውን እንዲሮጡ ይፈልጋሉ፡፡ በዚህ ረገድ የመሸነፍ ሥጋት ባይኖርባቸውም ጃፓን የሚሮጠውን ኢትዮጵያው ሮባ ጋሪ በጥንቃቄ ማየት ይፈልጋሉ፡፡ በአምስት ሺህ እና አስር ሺህ የምትወዳደረውን ቪቪያን ቼሪዩት በሁለት ወርቅ ይጠብቃሉ፡፡ መሠረት ደፋርና ጥሩነሽ ዲባባን በዋና ተፎካካሪነት ያያሉ፡፡ ዴቪድ ሩዲዣ በ800 ሜትር ድንቅ ብቃት ላይ ይገኛል፡፡ በሴቶችም ፓውላ ጃሊሞ እንደዚያው፡፡ ከኢትዮጵያ አማን መሐመድና ከሱዳን አቡበከር ካኪ፤ በሴቶች ፋንቱ ሜጌሶን በጠንካራ ተፎካካሪነት ይጠብቃሉ፡፡
በዓለም ካሉ 100 የማራቶን ምርጥ ራጮች ወይንም ፈጣን ሰዓቶች 81ዱ በኬንያውያን የተያዘ ነው፡፡ ከዚህ ቁጥር ሦስት ተወዳዳሪና አንድ ተጠባባቂ ማውጣት ፈተና ሆኖ ሰንብቷል፡፡ አቤል ኪሩዋ፣ አማኑኤል ሙታይ፣ ዊልሰን ኪፕሳንግ የተባሉትን የምርጦች ቁንጮ ሰይመዋል፡፡ በሴቶች ሜሪ ኪታኒና ኤድና ኪፕላጋትን በሜዳሊያ ሰንጠረዥ ይጠብቃሉ፡፡ ከወንዶቹ ይልቅ በሴቶቹ ይበልጥ ቢተማመኑም ከኢትዮጵያ አሁንም ጌቱ ፈለቀ፣ ቲኬ ገላና ለብርቱ ፉክክር ቢገምቱም በሁለቱም ጾታ ያልተጠበቀ አትሌት ብቅ ይላል ሲሉ ይጠብቃሉ፡፡ ለምሳሌ የቻይና፣ የጃፓንና የሞሮኮ አትሌቶች፡፡ ኬንያውያን ባለፈው ቤጂንግ ውድድር 14 ሜዳሊያ (6 ወርቅ፣ 4 ብር እና 4 ነሐስ ) አግኝተዋል፡፡ ዘንድሮ ለ20 ቆርጠዋል፡፡ ከዚህ ውስጥ 10 ወርቅ ነው፡፡
ማታ ነው ድሌ
የኬንያ መገናኛ ብዙኀን ስለራሳቸው አትሌቶች ሲናገሩ ሁሌም በንጽጽር የሚያስቀምጡት ኢትዮጵያውያንን ነው፡፡ ለኢትዮጵያውያን አትሌቶች ክብር አላቸው፡፡ የኬንያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ኃላፊ ኢሳ ኪፕላጋት ወደ ለንደን የምንሄደው በኦሊምፒክ መንፈስ ተወዳድሮ ለመመለስ ሳይሆን ሜዳሊያን ከእጃቸው ነጥቀን ለመምጣት ነው ሲሉ መደመጣቸው ሊገርም አይገባም፡፡ «ማታ ነው ድለ» መባል ተጀምሯል፡፡ አሊምፒኩ የሁለቱ አገሮች ብቻ መስሏል፡፡ ለኦሊምፒክ ቡድኑ አርቲስቶቻቸው ቀስቃሽ ዘፈን አውጥተዋል፡፡ እንደእኛው “ከፍ አለ በሲድኒ ኦሊምፒክ” እና “ አንበሳ ቀነኒሳ” ዓይነት መሆኑ ነው፡፡ የእኛ አርቲስቶችን ፈጠራ በጉጉት እንጠብቃለን፡፡
አትሌቶቹ ከውድድሩ በፊትና በኊላ የት፣ መቼ፣ እንዴት መግለጫ እንደሚሰጡ ትምህርት እየተሰጣቸው መሰንበታቸውን ጋዜጦቻቸው ዘግበዋል፡፡ መልካሙን ከጐረቤት ብንማር አይከፋም፡፡ ደለብ ያለ ገንዘብ ቃል ተገብቶላቸዋል፡፡ ኬንያውያን እንደዚሁ የተዘጋጁት ሜዳሊያ ለማሸነፍ ብቻ አይደለም፡፡ ስፖርቱ ትልቅ የአንድነት፣ የብሔራዊ ስሜት መፍጠርያ መሣርያ ነው ብለው ያምናሉ፡፡ አገሪቱም ከስፖርት ቱሪዝም ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ታገኝበታለች፡፡ እንደ ኬንያ ሁሉ በአራት ዓመት የምንሳተፍበት ኦሊምፒክ የአንድነትና የብሔራዊ ስሜት መንፈሳችንን የሚያቀጣጥል ነው፡፡ አትሌቶቻችን በድል የአገራችንን ባንዲራ ከፍ ሲያደርጉ ዘር፣ ሃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ወዘተ ሳይለየን በጣታችን ቆመን እንዘምራለን፡፡ ሰላም!!
No comments:
Post a Comment