Wednesday, May 18, 2016

ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ (1939 - 2008)


በሔኖክ ያሬድ

ግንቦት 10 ቀን 2008 ዓ.ም.
- 18 May, 2016 
ከስድስት አሠርታት በላይ በሚቆጠረው የኢትዮጵያ ኦሊምፒክ ታሪክ በአትሌቲክስ ተሳትፎዋ ኢትዮጵያ ካሸነፈቻቸው 45 ሜዳሊያዎች ውስጥ 28 የሚሆኑትን በማስመዝገብ አገሪቱን በውጤት ያደመቋት፣ ኢትዮጵያውያንን በድል ያስተቃቀፉ፣ ከሳተና ሯጮችና ከተወንጫፊ አትሌቶች ጀርባ የነበሩ ናቸው፡፡ የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሔራዊ አትሌቲክስ ቡድን ዋና አሠልጣኝ ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ፡፡ ከ92 ዓመታት በፊት በፈረንሣይዋ መዲና ፓሪስ በተካሄደው የኦሊምፒክ ጨዋታ፣ በክብር እንግድነት በተገኙት የኢትዮጵያ ንግሥተ ነገሥት መንግሥት አልጋ ወራሽ ተፈሪ መኰንንና የክብር ተከታዮቻቸው የኦሊምፒክ ተመልካችነት አሐዱ የተባለው የአገሪቱ ጉዞ ኦሊምፒክ፣ ከተወዳዳሪነት አልፎ በድል አድራጊነቱ አሐዱ ያለው በሮም ኦሊምፒክ ከ56 ዓመት በፊት በሜጀር ኦኒ ኒስካነን በሠለጠነው አበበ ቢቂላ ነበር፡፡ የአፍሪካ ሴት አትሌቶች በኦሊምፒኩ የድል ሰገነት መቼ ይሆን የሚታዩት? እያሉ ባሕር ማዶውያን በ1970ዎቹና 80ዎቹ መጀመሪያ መወትወት ሲጀምሩ፣ አለን! በማለት ከ24 ዓመታት በፊት በባርሴሎና ኦሊምፒክ በ10,000 ሜትር የወርቁን ሜዳሊያ ኢትዮጵያዊቷ ደራርቱ ቱሉ እንድታጠልቅ በሩን የከፈቱት ዶ/ር ወልደ መስቀል ኮስትሬ ነበሩ፡፡ የወንዶቹ አትሌቶች አኩሪ ውጤት እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያውያት የኦሊምፒክ የድል ቀንዲል እንዲለኮስ ግንባር ቀደም ተዋናይ የነበሩት ዶ/ር ወልደ መስቀል፣ በ69 ዓመታቸው ግንቦት 7 ቀን 2008 ዓ.ም. አርፈው ግንቦት 9 ቀን 2008 ዓ.ም. በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓተ ቀብራቸው ተፈጽሟል፡፡ በምሥሉ ላይ ዶ/ር ወልደ መስቀል እ.ኤ.አ. በ2006 በፈረንሣይ ሞናኮ ከዓለም አትሌቲክስ ማኅበራት ፌዴሬሽን ሽልማት በተበረከተላቸው ወቅት ነው፡፡


No comments:

Post a Comment