20 Apr, 2016
‹‹የሽምብራው ጥርጥር የዛፎቹ ፍሬ
የትም የትም ዞሬ ትዝ አለኝ ሀገሬ››
ዘመን ተሻጋሪ ከሆኑ የባህል ሙዚቃ ጨዋታዎች ከግንባር ቀደምቱ መካከል ይጠቀሳል፡፡ ‹‹ትዝ አለኝ ሀገሬ››፡፡ የማሲንቆው ጌታ ድምፃዊው ጌታመሳይ አበበን በዐቢይ ሥራው ሁሌ እንዲዘከርም አድርጎታል፡፡ በአገር ጥላ ውስጥ ከትውልድ ቦታው ርቆ የሄደም ይሁን፣ ባሕር ማዶ የተሻገረ ሁሉ ይቺን የጌታ መሳይ ዘፈንን ካንደበቱ አይለያትም፡፡ በተለይም ቀደምቱ፡፡ በአገሪቱ የሙዚቃ መሠረት ውስጥ ከሚቀነቀኑት ትውፊታዊ ዜማዎች አንዷ ስልት ‹‹ትዝታ›› በጌታመሳይ ውስጥም ቦታ አላት፡፡ ለርሱም መሠረቱ ናትና፡፡
‹‹ትዝታሽ ዘወትር ወደኔ እየመጣ
እፎይ የምልበት ሕይወቴ ጊዜ አጣ››
በዚህች ስንኝ ተመላልሶ ጋር ብቻ አልተቆራኘም፡፡ የሦስት ጉልቻን ምሥጢር፣ የሠናይ ጎጆን ይበልታን፣ የትዳር ትስስር ስምረትን እንዴትነት አመላክቶባታል፡፡ ጌታመሳይ፡፡ ‹‹የአካላዊ አንድነትና መንፈሳዊ ውሕደት፣ የአእምሮአዊ ቁርኝትና የስሜታዊ ብስለት›› መገለጫ በስኬት ሊታይበት የሚገባውን ትዳር በሰም ለበስ ዜማው ፈንጥቆበታል፡፡
‹‹የምትሠሪው ሥራ የሚገባ ነው ወይ?
መልክ ቢያምር ፀባይ ያጠፋ የለም ወይ!››
ይህችን መንቶ ግጥም የጥበብ ዜናዊው ተወልደ በየነ እንዳመሰጠራት፣ ትዳር በጋራ ትከሻ እኩል መያዝ ያለበት የኑሮ ሸክም ነው፡፡ አለዚያ መተሳሰብና መረዳዳት፣ መተማመንና መተዛዘን ከሌለ አደጋ አለው፡፡ በተለይም ዘላቂነቱ ላይ አንዱ ሲግል ሌላው ካላበረደ፣ ሌላው ሲንድ አንደኛው ካልካበ፣ በጋራ በፍቅርና በመተሳሰብ ካልኖረ በእልህና በግትርነት ሊዘልቅ እንደማይችል አስገንዝበውበታል፡፡
ፍቅረ ሀገርን በአርበኝነትና በጀግንነት ከሚያጎሉ የጌታ መሳይ ቅንቀናዎች ቀድሞ የሚጠቀሰው አርበኞችን የሚያጀግነው ዜማው ነው፡፡ በ1960ዎቹ መጨረሻ ጎረቤት አገር ሶማሊያ ምሥራቅ ኢትዮጵያን በወረረች ጊዜ ‹‹ክተት ሠራዊት ምታ ነጋሪት›› በተባለበት፣ ‹‹ተነሥ ታጠቅ ዝመት አብዮታዊት ኢትዮጵያ ተደፍራለች›› በተባለበት ጊዜ ከመደበኛው ሠራዊት ሌላ ከ300,000 በላይ ሚሊሺያ ሲከት፣ የጌታመሳይ አጃጋኙ ዜማ ሞገድ አሳብሮ ተደምጧል፡፡ ከሬዲዮ እስከ ቴሌቪዥን፣ ከመድረክ እስከ አደባባይ፡፡
ሆ ብዬ እመጣለሁ
ሆ ብዬ በድል
ጥንትም ያባቴ ነው
ጠላትን መግደል››
እንዲህም ዘፍኗል፡፡
‹‹ተው በለው ነግረናል
አሳር ይከተላል፤
እምቢ አላርፍ ካለ
በለኮሰው እሳት ራሱን ያጋያል፤
የጭቁን አብዮት በለውጥ ትግል ያሸንፋል፡፡››
- የማሲንቆው ጌታ - ጌታመሳይ አበበ ሲገለጥ
በ18 ዓመቱ፣ ከትውልድ መዲናው አሰላ አዲስ አበባ በ1953 ዓ.ም. የዘለቀው ኮበሌው ጌታመሳይ፣ ቀድሞ ከጥበብ አደባባይ ደጃፍ የዘለቀው ከተቋቋመ ስድስተኛ ዓመቱን ባስቆጠረው ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ቴአትር ቤት (ያሁኑ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር) ነበር፡፡ ለሦስት ወራት በተለማማጅነት ከቆየ በኋላ በድምፃዊነትና በመሰንቆ ተጫዋችነት ለመንፈቅ ሠርቷል፡፡ በይቀጥላልም በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ቤተ ኪነጥበባት ወቴአትር (ያሁኑ አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ባህል ማዕከል) ሲደራጅ ሙያውን በ1954 ዓ.ም. አጠናክሮ ቀጥሏል፡፡ በዩኒቨርሲቲው ባህልና ኪነ ጥበብን የሚደግፍ የቴአትር ቤት ለማቋቋም ጥረት አድርገው ያልተሳካላቸው ትውልደ ግብፃዊው አሜሪካዊ ሃሊም ኤልዳብ፣ የኢትዮጵያ ሙዚቃ ፋኩልቲ እስኪቋቋም ድረስ የሚያገለግሉና የጥንቱን ሙዚቃ የሚያውቁ የሀገር ባህል ሙዚቃ ጓድ ሲያቋቁሙ፣ አንዱ ተሳታፊ የነበረው ጌታመሳይ ነበረ፡፡ ክራር፣ ማሲንቆ፣ በገና፣ ዋሽንት፣ እምቢልታ፣ መለከት፣ ከበሮ፣ ቶም የተሰኙ ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች በያዘው ኦርኬስትራው የጌታመሳይ ድርሻ፣ ለዘለቄታው የተጠበበባት ‹‹ሊቅ›› ያሰኘችው መሰንቆ ናት፡፡
ከመጀመርያው ዳይሬክተር ሃሊም ኤልዳብ በኋላ የተተካው ዳይሬክተር አሜሪካዊው የሰላም ጓድ አባሉ ጆን ኮ ሲሆን፣ ሦስተኛው ዳይሬክተር ተስፋዬ ለማ (1959 እስከ 1968 ዓ.ም.) የኦርኬስትራው ፈርጥ ሆነው ዘለቀዋል፡፡ በዘመነ ተስፋዬ በ1960 ዓ.ም. የአሜሪካ ሰላም ጓድ አባል ሆኖ ለበጎ ፈቃድ አገልግሎት የመጣው የሃርቫርድ ምሩቁ ቻርልስ ሰተን ኦርኬስትራውን በአስተዳዳሪነት እንዲመራ መመደቡ አዲስ አቅጣጫን አስገኘ፡፡ ቻርለስ ሰተን በ1958 ዓ.ም. ኢትዮጵያ በደረሰ ጊዜ ቀልቡን የገዛው ባህላዊ ሙዚቃ ነበር፡፡ በሙዚቃው መመሰጥ ብቻ ሳይሆን መሰንቆውን ለመማርና ለመጫወት የቻለው በኦርኬስትራው አባል በጌታመሳይ አበበ መማሩ ነው፡፡
የጌታመሳይ ዱካን ተከትሎ ማሲንቆውን ያነገተው ሰተን፣ ለመጀመርያ ጊዜ በ1959 ዓ.ም. ወርኃ መጋቢት እንደ መምህሩ ማሲንቆውን ይዞና የኦርኬስትራው ጭፍራ ሆኖ በአማርኛ ማቀንቀን ያስጀመረው በአሰፋ አባተ ዜማ ነበር፡፡
‹‹ሸጊዬ ሸጊዬ ሸጊቱ ወጣቱ …
ጠጋ ብለሽ ተኚ ወደ ግድግዳው
ከልቤ ላይ ብትሞች የማነው ዕዳው?
ሆይ ናና ያገሬ ልጅ፣ የወንዜ ልጅ …››
ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ባገር ቤት ትርዒቱን በማቅረብ ከመወሰን ተላቆ፣ ባሕር ማዶ እንዲዘልቅ የማመቻቸቱን ዐቢይ ድርሻ በሚወስደው ቻርልስ ሰተን አማካይነት ጌታመሳይና ጓደኞቹ ሀገረ አሜሪካ ዘለቁ፡፡ በዩኒቨርሲቲው፣ በአዲስ አበባ ሆቴሎች፣ በአሜሪካ ኤምባሲ፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮና በብሥራተ ወንጌል ሬዲዮ፣ በቴሌቪዥንም ተወስኖ የነበረው ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ፣ በቻርልስ ሰተንና በአሜሪካ ሰላምጓድ ጥረት በዩናይትድ ስቴት ኦፍ አሜሪካ በመካከለኛው ምዕራብ ጥግ እስከ ምሥራቅ ‹‹ዘ ብሉ ናይል ግሩፕ›› (የዓባይ ልጆች) በሚል መጠሪያ በ20 ከተሞች ማንሃታንስን፣ ታውንሆልንና ዘ ኢድ ሱሊቫን ሾውን ጨምሮ ትርዒቱን አቅርቦ አድናቆትን አትርፏል፡፡
‹‹እኛም አለን ሙዚቃ
መንፈስ የሚያነቃ፤
ክራራችን፣ ማሲንቋችን …›› እያለ የባህል መሣሪያዎቹን ሲያስተዋውቅ የማሲንቆው ጌታ (ማስተር) ጌታመሳይ አበበ ነበረበት፡፡
የነጌታመሳይ ሥራዎች በ1962 እና 1965 ዓ.ም. ‹‹ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ›› በሚሉ በሁለት አልበሞች ተለቋል፡፡ የመጀመርያ ‹‹ዘ ብሉ ናይል ግሩፕ›› የሚል ንኡስ ርእስ ነበረው፡፡ የኦርኬስትራው ጉዞም ናሽናል ጂኦግራፊክ ባዘጋጀው ‹‹Ethiopia: The Hidden Empire (1970)›› ዘጋቢ ፊልም ውስጥ ተካትቷል፡፡
1968 ዓ.ም. ለኦርኬስትራ ኢትዮጵያ ገዳ’ም (የገድ ዓመት) አልነበረም፡፡ የደርግ ሥርዓት መመሥረቱን ተከትሎ ኦርኬስትራው ታገደ፡፡ በርካቶቹ ሙዚቀኞች ወደ ተለያዩ ቡድኖች አመሩ፡፡ አስቀድሞ ሀገር ፍቅር ቴአትርን የተቀላቀለው ጌታመሳይ ድምፃዊነቱንና ማሲቆኛነቱን ተያይዞ እሰከ ዘመነ ጡረታው ቀጥሎበታል፡፡
በኢትዮጵያ ሦስተኛ ሚሊኒየም ዋዜማ፣ የኦርኬስትራ ኢትዮጵያ በሪል ኦዲዮ ቴፕ ተቀርፆ የነበረው ነባር ሥራም ወደ ኦዲዮ ሲዲ በአንድሪው ሎረንስ አማካይነት ተገልብጦ፣ በቡዳ ሙዚክ ኢትዮፒክስ በኩል በአውሮፓና በአሜሪካ በ2000 ዓ.ም. መሠራጨቱን የነጌታመሳይ አበበ ሥራን ሕያው አድርጎታል፡፡
ከኦርኬስትራ ኢትዮጵያ የቀድሞ አባላት መካከል ከዓመታት መለያየት በኋላ አራቱ ዳግም በዋሽንግተን የተገናኙት በ1998 ዓ.ም. ነበር፡፡ በ1950ዎቹ መጨረሻና በ1960ዎቹ መጀመርያ የተጫወቷቸውን ዳግም ‹‹ዞሮ ግጥም›› በሚል ርእስ በናሆም ሪከርድስ አማካይነት ያወጡት ጌታመሳይ አበበ፣ ቻርልስ ሰተን፣ መላኩ ገላውና ተስፋዬ ለማ ናቸው፡፡ ከዋሽንግተን ሌላ ከስምንት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጥናት ተቋም ራስ መኰንን አዳራሽ በሚያዝያ 2000 ዓ.ም. መመረቁ ያኔ ‹‹ኦርኬስትራ ኢትዮጵያ እንደገና›› መሰኘቱ በሪፖርተርም መዘገቡ ይታወሳል፡፡
- ጌታመሳይና ሀገር ፍቅር
ከሦስት አሠርታት በፊት በተከሰተው ድርቅና ረሃብ ሳቢያ ‹‹We are the World››ን ጨምሮ ድጋፋቸውን ለሰጡ ሁሉ ምስጋና ለማቅረብ በ1979 ዓ.ም. በመላው ዓለም የዞረው፣ የሕዝብ ለሕዝብ ኢትዮጵያ የኪነ ጥበብ ቡድን ውስጥ ተሳታፊ የነበረው የጌታመሳይ አበበ ማራኪ እንቅስቃሴን ብዙዎች ያስታውሱታል፡፡ የአገሪቱ አንቱ የተባሉ የተለያዩ የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች የተሳተፉበትና ‹‹አደይ አበባ›› የሚል መጠርያ ባለው ትርዒት የጌታመሳይ አበበ ባህላዊ ሙዚቃ ሁነኛ ቦታ ነበረው፡፡
አንዱ ‹‹ኢዮሐ አበባዬ . . . መስከረም ጠባዬ›› የሚለውን በሚያስገመግም ድምፅ በአውሮፓና በአሜሪካ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባው ማጠቃለያ ዝግጅት በጉባኤ አዳራሽ
የተከታተሉት (የታደሙት) ሁሌም ያስታውሱታል፡፡ ‹‹ሰምና ወርቅ እስኪ አማርኛን እንወቅ›› ይሉ ነበር የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ የአማርኛና የግእዝ፣ የቅኔም መምህርት የነበሩት ፕሮፌሰር ዓለማየሁ ሞገስ፡፡ የጌታ መሳይ ዘፈኖች ቱባ አማርኛቸው ከሰምና ወርቅ ጎራ ውስጥ መግባታቸው አልቀረም፡፡ በአንዱ ሥራው ውስጥ፡-
‹‹እምቧይ ነሽ ወይ ሎሚ
ጠረጠሩሽና ሰማሁ ስትታሚ›› ብሎ ያቀነቀነው ትኩረት የሚስብ ነው፡፡ እምቧይና ሎሚ ለየቅል ናቸው፡፡ አንደኛው የጤና እክል የሚፈጥር፣ ሁለተኛው ፈውስ የሚሆን፡፡ አንቺ የቱነሽ ኧረ እየታማሽ ነው፤ ‹‹አደናግር መስተፃምር›› ሆነሻል የሚል ሴማ አለው፡፡
ጌታ መሳይ ካቀነቀናቸው የፍቅር ዜማዎች መካከል ግዘፍ የምትነሳው ቀልብን የምትገዛው ‹‹የኔ አያል›› ተጠቃሽ ናት፡፡ ከአገር ፍቅር ዝነኛ ተወዛዋዦችና ድምፃውያን ጋር የተመደረከችው፣ በቴሌቪዥን መስኮትም ሆነ በዩቲዩብ የተለቀቀችው የኔ አያል ቅንብራዊ ገጽታ ስምረት ሁሌም የሚወሳ ነው፡፡
‹‹የኔ አያል የኔ አያል
አያል የኔ አበባ
አበባሽ ለምለሜ
ሳላይሽ መክረሜ››ን በቅብብሎሽ ሀገር ፍቅሮች ሲጫወቱት፡ የውዝዋዜ ዓይነቱ ብዘኃነት በተለይ ማብቂያው ላይ ጌታመሳይ ከዘነበች ታደሰ (ጭራ ቀረሽ) ጋር ያሳየው ዳንኪራ ላየው ሁሌም የሚያወሳው ነው፡፡
ከአርባ ዓመታት በላይ በኪነ ጥበብ ቤት፣ በተለይም በባህላዊ ሙዚቃ ልዕልና የተጎናፀፈው ጌታመሳይ አበበ፣ የኢትዮጵያን ባህላዊ ሙዚቃ ከአጋሮቹ ጋር በዓለም ዙሪያ ለማስተዋወቅ ከአፍሪካ እስከ አሜሪካ፣ ከእስያ እስከ አውስትራሊያ፣ አውሮፓን ጨምሮ የተጋው ጌታመሳይ፣ ዕውቀትና ልምድን ለተተኪው ትውልድ ብቻ ሳይሆን በሀገረሰብ ሙዚቃ ላይ ጥናትና ምርምር ለሚያደርጉ ኢትዮጵያውያንና የውጭ የሙዚቃ ምሁራን ብሂልን ከባህል እያዛመደ አሳውቋል፡፡ አስገንዝቧል፡፡ አሜሪካዊውን የሰላም ጓድ አባል የሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ምሩቁን ቻርልስ ሰተን በአዲስ አበባ የሰጠው ሥልጠናና ያስቀሰመው ትምህርት በርሱ ብቻ አልተገደበም፡፡ በሃርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በመገኘት የኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃን ማጥናት መመርመር ለሚሹ ሁሉ ጨዋታውን ከነማብራሪያው መስጠቱን ገጸ ታሪኩ ያሳያል፡፡
ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ከዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያ ጋር በማቀናጀት ቀድሞ ከሚጠቀመው በተሻለ መንገድ ለመሥራት፣ ከተለያዩ የሁለቱም የጥበብ ጎራ ሙያተኞች ጋር በመቀናጀት፣ ሥራውን ለማቅረቡ አንዱ ማሳያ የኢትዮ ጃዝ ሙዚቃ ቀማሪው ሙላቱ አስታጥቄ በ1970ዎቹ መካተቻ፣ መሰንቆና በገናን ከዘመናዊ የሙዚቃ መሣሪያዎች ጋር በማቀናጀት የቀመረው ‹‹ንዋይ ማሕሌት›› ነው፡፡ ራሱ ሙላቱ በዛይሎን የሙዚቃ መሣሪያ እየተጫወተ፣ በመራሔ ሙዚቃነት (ኮንዳክተርነት) በመራው፣ ዕውቁ ድምፃዊ ቴዎድሮስ ታደሰ ባቀነቀነው ‹‹ጾመ ድጓ›› በተሰኘው ‹‹መዲና ዘለሰኛ›› ጨዋታ ውስጥ
‹‹ኧ-ኧ-ኧ- ምነው ወዳጄ ምነው . . .
ከወጥ ቤት ገብቼ ድንገት
ሥጋ ጠብሼ ለመብላት
ወድቄ ነበር ከሳት ላይ
ሥጋ ሥጋዬን ሳይ፡፡
ትንሽ ቤት ሠራሁ ዳግመኛ
ሁለት ሦስት ሰው የሚያስተኛ፤
አላስገባ አለች እሷው ጠባ
ሰው በሰው ላይ እየገባ፡፡›› ውስጥ የማሲንቆው ጌታ፣ ጌታመሳይ አበበ ማለፊያ ማሰንቆ ማለፊያ ቦታውን በማዕረግ ይዛ ታይታለች፡፡
- ጀንበሯ ስትጠልቅ
- የጌታመሳይ ጎጆ
ጌታመሳይ ሰኞ ኅዳር 28 ቀን 1935 ዓ.ም. የተወለደባት ልዩ ቦታ፣ ዲገሉና ጢጆ አራቢ ጊዮርጊስ አጥቢያ እንደሆነ፣ ሥርዓተ ቀብሩ በመንበረ ፀባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በተፈጸመበት ጊዜ ተገልጿል፡፡ የመሰንቆው ጌታ ጌታመሳይ፣ ባለትዳርና የ10 ልጆች (የአምስት ወንዶችና የአምስት ሴቶች) አባት እንዲሁም የ19 የልጅ ልጆች አያትም ነበረ፡፡
- ዓይን ገላጩ
‹‹በኢትዮጵያ ታላቅና ተወዳጅ ከነበሩ ሙዚቀኞች መሀል የአቶ ጌታመሳይ አበበን በሞት መለየት ሰምቼ በጣም አዝኛለሁ፡፡ በመልካም ሰውነቱና ከዚህም በተጨማሪ ከዛሬ 50 ዓመት በፊት፣ የመሰንቆ አስተማሪዬ ሆኖ ከማደነቀው ከኢትዮጵያ የባህል ሙዚቃ ጋር እንድተዋወቅ ዓይኔን ስለገለጠልኝ በጣም አከብረዋለሁ፡፡ ጌታመሳይ በጣም የምወደውና የማምነው ወዳጄ ነበር፡፡ ለቤተሰቡና በጠቅላላ፣ ጌታመሳይን በሙዚቃ ለሚያውቁትና ለሚያፈቅሩ ኢትዮጵያውያን በያሉበት የሐዘናቸው ተካፋይ መሆኔን እገልጻለሁ፡፡ ነፍሱ በሰላም ትረፍ፡፡›› አበቃ፡፡
‹‹ትዝ አለኝ
ዳገት ቁልቁለቱን
ስንወጣ - ስንወርድ
ወለል ካለው ሜዳ
ላሞች ስናግድ
ያሁሉ ቀረና
ቁምነገር መጣና
ትምህርት ቤት ገባን
ሀሁ ልናጠና
ፊደል ልጠና፡፡›› እያለ ዘመን ተሻጋሪውን ዜማ
‹‹የሽምብራው ጥርጥር የዛፎቹ ፍሬ
የትም የትም ዞሬ ትዝ አለኝ ሀገሬ››
ያቀነቀነው ጌታመሳይ አበበ ተከተተ፡፡ ሞትም ፊደልን አጥንቶ የመሰንቆውን ጌታ ከተተ፡፡
- ሔኖክ ያሬድ's blog
- 97 reads